Showing posts with label ግጥሞች. Show all posts
Showing posts with label ግጥሞች. Show all posts

Apr 27, 2015

አሌክስ አብርሃምን `በእናት ፍቅር ሐገር`...



አሌክስ አብርሃምን በእናት ፍቅር ሐገር
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››


ይገርመኛል፤ እንዲህ አይነት ጸሐፊ ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ ለዚህም ነው የምስጋና ብዕሬን የሠደርኩት፡፡ ሥለ ልጁ  የግል ማንነት፣ መልክ፣ ጥይምና፣ ዕድሜ አሊያም አጠቃላይ ገጸ ሰብ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ሆን ብሎ የተደረገ መሆኑን ስናስብም ነው የሚደንቀን፡፡ ስሙን “አሌክስ አብርሃም” ብሎ በመሰየም፤ ዓለም በፈጠረው ዘመን አመጣሽ የልቡና ማስተንፈሻ ሽንቁር (ፌስቡክ) በየዕለቱ የሚለጥፋቸው ሕብረ ቀለማማ፣ ዜማ ሙሉ ሐተታ ግርም ድንቅ ይሉኛል፡፡
አርት እና አርቲስት በሚል ርዕስ ይዘት ፈላስፋው ዘርዓ ሌሊሳ፤ “አርት ከምንም በላይ ቀድሞ ሊታይ እና ሊተረጎም የሚገባ ሲሆን አርቲስቱ ግን ከገጠጠ እና ቀድሞ የሚሸለም ከሆነ ውርደት መሆኑን” ገልጾ ነበር፡፡ በአፍሮ ጋዳ ድርሰቱ!!
አሌክስ አብርሃ የብዕር ስሙ ሲሆን ግለሰቡን የምናውቀው እና ገጸ ሰቡን በሕሊናችን የምንስለው በየዕለቱ ለእውነት ሲታገል፤ ለተፈጥሮአዊ ሕልውና ዘብ ቆሞ ዘራፍ ሲል ነው፡፡
‹‹ዘራፍ›› አንዳንድ ጊዜ ይጨንቃል፡፡ ሰውን በምኒሽር ገሎ ዘራፍ ይጨንቃል፤ ይሕኛው ብላቴና ግን በውብ ቃላት አቀማመጥ እና አመክኔያዊ ውብ ሓሳቦቹ አንባቢን እጅ ወደ ላይ ያስብላሉ፡፡ በፍቅር ማሸነፍ፤ በጥበብ ማሸነፍ፤ ተሸንፎም ማሸነፍ የድሎች ሁሉ ድል ነውና!
ያበዛዋል፤ ሁልጊዜ ነቀፋ ነው የምትሉ ካላችሁ ደግሞ መልሱ ቀላል ነው፡፡ በአሁን ሰዓት ሊነቀፉ የሚገባቸው እኩይ ተግባራት በነገጉበት ዓለም ውስጥ ዝም ብለን የምንመለከት ከሆንን የዚህ እኩይ ተግባር ደጋፊዎች ነን ማለት ነው፡፡ ለእኩይ ተግባራት ተቃውሞ ማሰማትን መንቀፍ የለብንም! እኩይ ተግባር ሲለመድ ባህርያችን መሆኑ ስለማይቀር ነው ዓለም አኩይ ተግባራትን በይፋ እየነዛች ያለቸው!
“ዶክተር አሸብር…” ከ20ሺሕ ኮቢ በላይ መሸጧ፤ እንዲሁም ከዚህ በላይ እንደምትሄድ ስናስብ፤ ከዚህ በተጨማሪም “እናት ፍቅር ሐገር” የግጥም ስብስብ ይዘት ስንመለከት ከዚህ የበለጠ እንደምናይ አንጠራጠርም፡፡
አገር ተቃጠለች…. ነጻነት አጠጠ
የጃጀ ስረዓት… ሕዝብ ላይ አረጠ
መድፍ ተተኮሰ ታንክ ብረት አገሳ፣
ሰላም ኮበለለ ብጥብጥ ተነሳ…
ዝምታ አከተመ አብዮት ተነዛ….
ሂድ ወደዛ!!
በሚል ስንኝ የተቋጠረው ‹‹ንጭንጭ ያደርገኛል›› የግጥም ዘለላ የትውልዴን እንቅልፍ(ለሽ ማለት በቆረጣ ያስቃኜናል፡፡)
33ኛው ግጥም “ገጣሚው ወዳጄ”
ዛሬ ከፊታችን ዘላልም የሚያህል ባሕር ተዘርግቶ፣
ፍጥረት እህህ ሲል የሚያሻግር ጠፍቶ፣
ትዝታው መጣብኝ ገጣሚ ወዳጄ፣
ላልገጠመ ነፍሱ ግጥም እያበጀ
በሚል አንጓ ግጥም የነፍስ ትሩፋት፣ የመንፈስ እርጋታ እና መገጣጠም መሆኑን ያስረዳናል፡፡
ወረድ ካለው አንጓ ላይም
እናልህ ወዳጄ እንደዚህ እንዳንተ እርሙን ለሚበሉ፣
ያለ የነበረን “ምን ነበር” ለሚሉ፣
ምን አለ መሰለህ…
የለት እንጀራህን ማድቀቂያ ማግኛ፣
“ስም” ይሉት ጥርስ አለ ሰላሳ ሦስተኛ…
ሲል ሃሳቡን ይገልጻል፡፡
“የኔ ፎቶ ሞቷል!”
እኛ ነን እያልን የምንፎክርበት፣
ስንት የሞተ ትላንት ስንት ያለፈ ውበት፣
በየግድገዳችን ክብር ሆኖ ነግሷል፣
ጊዜ ደራሽ ወንዙ ትላንት ላየ ጥሎን የትና የት ደርሷ!
እና ይሄ ምስል እና ይሄ “ፎቶ”
ልክ እንደብርሃኑ በለጭ ብሎ ጠፍቷል፣
ዛሬ እኔን አይደለም ትላንትናም ሞቷል!!
የሰው ልጅ ልቦና መልክ ለፈለገ
እኔ አሁንን መሳይ
እኔ ማልት ነገ!!
“እኔ የምኖርበት ኮንዶሚኒየም ፊት…”፣ “አራተኛው ሰማይ”፣ “ዘፀዓት”፣” ባሕር ነን”፣  በሚገርም ቀለል ባለ አርዕሰት ውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኝባቸው ጀልባዎች ናቸው፡፡ ጀልባዋ አቅም አንሷት የውቅያኖሱ ወጀብ እንዳይከድናት ጸሐፊው እንደ ሕይወት አድን ሆኖም ከጀርባችን አለ፡፡ እንደ አብዛኛው ጸሐፊ ጥሎን አይሄድም፡፡
“ግጥም ለሚገጥሙ…”
ግጥም የሚገጥሙ…፣
በፅንፍ የለሽ ምናብ
በህዋ ነጻነት አውነትን ይቃዡ
አውነትን ያልሙ…
.
.
.
ጎዳና ይትለሙ.
.
.
ነብይ ከማጀብ “ከነብይ” ይቅደሙ…
ወደ ጥበብ ማዕድ ደፍረው ከቀረቡ፣
ሕልማቸውን ጥለው እንቅልፍ አያንብቡ…
ወጣም ወረደም ይሕንን ልጅ አንብቡት፣ ምን ለማድረግ እና ለማለት እንደፈለገም በሥጋ ብቻ አትመልከቱት፡፡ ሥጋ ለባሽ ፍጡር ነውና፤ መንፈሱ አርነት ታወጣው ዘንድ አጋር ሁኑት፡፡ ሆኖም በመንፈሱ አርነት የወጣ መች የሥጋ ችንካር ያስቀረዋል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ኢንተርኔት›› ለማግኘት የሚችለው ሕዝብ እና ‹‹ኢንተርኔት››ም አግኝቶ ፌስ ቡክ የሚጠቀመው ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ (ኢህአዴግ እንኳ በፌስቡክ 23 ሺህ ለይኮች ሲኖሩት አሌክ አብርሃም በእጥፍ ይበልጠዋል፤ … ) 98 በመቶ የሚያሕለውን ሕዝብ ለመድረስ ፌስ ቡክ የውቅያኖስ ጭልፋ ነው፡፡ ሥለዚህ ይሕንን ልጅ “እንዴት ውቅያኖስ እናድርገው” በሚለው ላይ ብንመክር የተሻለ ይመስላል፡፡ እሱን እና መሰል ወጣት ጸሐፊያንን፣ ዘመን በሥጋ ምች በተመታበት አሁን፣ አበቅቴ በንዋይ መርዝ በተነደፈበት አሁን፣ ወገን በስሜት ልነዳ በሚልበት ፈረሰኛ ጉዞ -አሁን፣ እሱን አና መሰል ጸሐፊያንን እንዴት እናሳድጋቸው? እንዴት ብርሃናቸው ከውቅያኖሱ አውድማ ላይ ተላትሞ ውብ ሕብረ ቀለምን ይስጥ? ነው ጥያቄያችን መሆን ያለበት፡፡
ለሽሽሽሽ ማለት ማንን ጠቀመ?

Dec 20, 2014

የጋሻው አዳልን እና የወንዴ ማክ ሙዚቃ ንጽጽር


https://www.youtube.com/watch?v=iDCl56JhjFIhttps://www.youtube.com/watch?v=iDCl56JhjFI
አንቺ ልጅ ምን ይበቃ….!
ሸግዬ ምን ይብቃ..
እንደ ልብ አይገኝ ከሰው ቤት ያለው ዕቃ
አንቺየ ምን ይብቃ?
እህ…እህ
የሁሉ አይን ሮጦ አሄሄ ሲሆን ከርሷ ላይ
እህ.. እህ ኧረ እንዴት አስቻላት አሄሄ እቺ ዘበናይ
እህ ህ አምሳ ሎሚ ለአንድ አሄሄ ከተባለ ሸክም
ሰማሽ ሆይ ታይታ መወደዷ አሄሄ ምነው ለሷ አይከብድም
ታይታ ወደደዷ ምነው ለሷ አይከብድም አንቺየ ምን ይብቃ!
ኮለል በይ አካሌ ኮለል በይ አካሌ
ተጓዡን ይመርጣል አሄሄ መንገደኛ አመሌ
ጎርደድ በይ ጎርደድ በይ በደጁ
አለፍ በይ አለፍ በይ አለፍ በይ በደጁ
ኮለል በይ ኮለል በይ ኮለል በይ በደጁ
እንደ አባይ ምንጭ ውሃ አካሌ አሄሄ እንዲያ እንደወራጁ
*******
አንቺየ ምን ይብቃኝ
አንቺ ልጅ ምን ይብቃ
ኧረ አንቺ ልጅ ምን ይብቃ
ሸግዬ ምን ይብቃኝ
እንደልብ አይገኝ ከሰው ቤት ያለ ዕቃ
አንቺዬ ምን ይብቃ!
እንደልብ አይገኝ ከሰው ቤት ያለ ዕቃ
አንቺዬ ምን ይብቃ!
እህህ.. የሠው ናት የሰው ናት አሄሄ የሰው ናት ይላሉ
እህህ በሰው መወደዷን አሄሄ ላይከላከሉ
እህህ እንደማልወስናት አሄሄ እያወቀው ሆዴ
አሄሄ ለሰው የማትራራ እህህ ሺሕ ገዳይ መውደዴ
ለሰው የማትራራ ሺሕ ገዳይ መውደዴ…አንችዬ ምን ይብቃ!
ኮለል በይ አካሌ ኮለል በይ አካሌ
ተጓዡን ይመርጣል አሄሄ መንገደኛ አመሌ
ተጓዡን ይመርጣል አሄሄ መንገደኛ አመሌ
ጎርደድ በይ ጎርደድ በይ በደጁ
አለፍ በይ አለፍ በይ አለፍ በይ በደጁ
እንደ አባይ ምንጭ ውሃ አካሌ (አሄሄ) እንዲያ እንደወራጁ

አንቺየ ምን ይብቃ….
ሸግዬ ምን ይብቃ
ኧረ አንቺ ልጅ ምን ይብቃ
ሸግዬ ምን ይብቃ
እንደልብ አይገኝ ከሰው ቤትያለ ዕቃ
አንችየ ምን ይብቃ
እህህ ሄዳችሁ ንገሯት አሄሄ ጥሯትና ትምጣ
እህህ ቆስሎ አካሌ እያየች አሄሄ እንዲህ ካፏ ይውጣ
አሄሄ ትቅለበለባለች እህህ እሷ ጭምት ሆና
አሄሄ ላንድም አልተገኘች ያቺ ልጅ ባስር ተለምና
 ላንድም አልተገኘች  ባስር ተለምና አንቺየ ምን ይብቃ
ላንድም አልተገኘች  ባስር ተለምና አንቺየ ምን ይብቃ?
ብርቱ ናት ብርቱና የሚሏት ለምን ነው?
ብርቱ ናት ብርቱና የሚሏት ለምን ነው?
ካንዱ ስፍር መርጋት ልቧ እየ(ጠፋ) ነው
ሽህ ገዳይ ስትመጣ የልምዷን ደርድራ
ያንችው ነው ብላችሁ አሄሄ (አሃሃ) አስጥሉኝ አደራ
 ኮለል በይ አካሌ ኮለል በይ አካሌ
ተጋዡን ይመርጣል መንገደኛ አመሌ
ጎርደድ በይ ጎርደድ በይ በደጁ
አለፍ በይ አለፍ በይ አለፍ በይ በደጁ
ኮለል በይ ኮለል በይ ኮለል በይ በደጁ

እንደ አባይ ምንጭ ውሃ አካሌ አሄሄ እንዲያ እንደወራጁ
https://www.youtube.com/watch?v=und1rETET-8

Jul 31, 2014

“ማንዴላ” በኤፍሬም ስዩም ተሰማ



“ማንዴላ”


ነጻነት ነው የወጣኸው?
ነጻነት ነው የወጣችው?
ለነጻነት ነው ለነጻነታችሁ?
ለግል ማንነትህ ወይስ ላ’ገራችሁ…?
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ…?!

`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ? የውነት ነጻ ሰው ነህ?`

ነጻም ነኝ ካልክ ማን አሳዶ ማን መለሰህ?
ማንስ አስሮ ማን አስፈታህ? ማን አቁስሎ  ማን ጠገነህ?
‹‹ኖቤል›› ማን ሸለመህ? ነጻነት ማን ነሳህ?

`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ…
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ?`
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ?

`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ?`
*****
ነጻ ነኝ ካልክ በማን በሬ ነው
የማን ሰርዶ የሚጋጠው?
ማንስ ጫንቃ ላይ ነው ነጫጭ ውሻ የታሰረው?
እኮ እንዴት?
እድሜን አስረጅቶ ደረስኩልህ ማለት¡
ነጻነትን ነፍጎ ‹‹ኖቤል›› ሸላሚነት
እኮ እንዴት….?

ይልቅስ ልንገርህ ተረት ነው ነጻነት
ደሮን ሲደልሏት በመጫኛ ጣሏት!
አርዝመው ቢያስሯት የፈቷት መሰላት..
ለዚህም ሁሉ ነጻነትን ነፍጎ ለነጻነት ታጋይ ‹‹የኖቤል›› ሽልማት
ማታለል ይመስላል ምጸት እና ኩሸት…!

ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ…?
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ?
“ስድስት ወራት በከለለህ
በመንደርህ በኩልፌ አፈር ልጠይቅህ
አውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ….?”
በኤፍሬም ስዩም ተሰማ
‹‹ሙዚ-ቃል›› የግጥም ሸክላ

Jun 11, 2014

‹‹የምድር እምብርት!››

‹‹የምድር እምብርት!››
                                                         ‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››


ከመደብ ተኝተህ ከሚጎረብጠው
ውስጥህ ጣራ ያየ ህዋውን ሲስለው
ክንድህን ኣጣጥፈህ፣ እጆችህ ገብተዋል ራስ ቅልን ይዘው
ጉልበትህም ታጥፎ እግሮችህ ተሳስረው፤
አይኖችህ ያያሉ የሳር ጣራን አልፈው…!

ተመልከት ህዋውን፣ የጣራውን ስፋት
ያዘለውን ምስጢር የከዋክብት ብዛት
ፈጣሪን ስታስብ ከዚህ ግዝፈት ኬላ
ምንድን ነው ይሕ ዐለም የስፋቱ መላ….?
ተመለስ ከሰማይ ከዋክብትን ይዘህ
ፈጣሪን ስታስብ ረቂቅ ነው ብለህ
የውስጥህን ጣራ ልብህን ፈልገህ...!!
ማዕዘኑን ለካው
ከክንድ እሰከ ጉልበት፤ ከጉልበት ጉልበትህ
ከጉልበት እስከ ክንድ፤ ከክንድ እስከ ክንድህ!
አራት ማዕዘናት የሰው ልጅ ቅርጽ ያለው
መሀሉን ተመልከት ሆድ ገመድ የያዘው
የሁሉ መዓዘን የምድር እምብርት ነው!!!

የዚህን ‹‹ልብ ቃል››፤ ወደ ሰው ፈልገው
ወደ ወስጥህ ስታይ፤ ጥልቅ ነው ፍጻሜው!!
ጥልቅ ነህ ለዐለም ውድ ነህ ለምድር
ጢለቅ ነሽ ለህዋው ማይፈታ ምስጢር
ተመልከች ህዋውን ተመልከት ውስጥህን

የምድር መሰረቱ ያዢው መንገድሽን
የምድር መሰረቱ ያዘው እምብርትህን….!

‹‹የምድር ጣር አውሪዎች››

‹‹የምድር ጣር አውሪዎች››
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››

እንኳን ወዳጅህን ጠላትክን መርቀው
ነበረ ትዛዙ ፈጣሪ የሰጠው..
የሰው ልጅ በክፉ በዓመጽ ተያዘ
አውሬ ሆኖ ታየ በደም ፈነጠዘ
ከአቤል ጀምሮ ቃየል የባረከው
ከምድር ጫፍ እስከ ጫፍ ደሙን ከልብ አ’ረገው::
ሰው ፈጣሪ ሲሆን ህግን መስመር ሲስት
ቅጣቱ ይበልጣል ከሲኦልም በፊት….!
እዩት የሰው ልጅን፤ በፍርዱ ወንበር ላይ
ሲኦልን ሲቀምም የላይ ታቹን ሳያይ
ወንድሙን ሲቀላው ቃየል መጀመሪያ
ዐለም ታውካለች ፍርድን ሰስታለች- ትወግጣለች ጓያ
ሽባነት ደርሷታል የፍርድም አባያ…
ይጮሃል ድሐው ሕዝብ በነጻነት ጩኸት
ይጮኻሉ ህዝቦች- ሰሚ አላገኙም- በፍትህ ጥም እጦት
በቃየል መስዋዕት፤ በቁም ቂም ቂል ምኞት
ይጮኻ ሉ ህዝቦች- ይጮኻሉ- ድሖች በነጻነት አጦት

ሰክረዋል ቃየሎች፣ ይጮኻሉ ድሖች ይጮኻሉ ህዝቦች በፍትህ ጥም እጦት….!!!

Jun 10, 2014

‹‹መወማ››

‹‹መወማ››

ምን ያያል ጎፈሬህ ምን ያያሉ አይኖችህ
ምን ያያል እንቅልፍህ ምን ያልማልስ ሌትህ
ያብቀቴው ቅበላ የመዓልቶች መንጎድ
ያፍቅሮተ ንዋይ የቁልቁለት መንገድ??
ለውጥ አልባ ፍርቅርቅ፤የጉልቻው ልውጥ
ጨው አልባ አልጫ፤ ያልበሰለ ‹‹ቀይ›› ወጥ
መንግስታት መታኮስ ዛሬን ለመለጠጥ…!
የስልጣን ግብግብ የነፍጥ ሹም ማበጥ
 የባንዳ ማሽካካት የድንጋይ ቅርስ ማግጠጥ…??
መወማ….
ምን ያስባል ነገህ፤ ምን ይመኛል ሞትህ
ምን ይላል ኑዛዜህ፤ ምን ይላል ትንሳኤህ?
ጎፈሬህን ቀባኝ
ዝናርህን ስጠኝ
ብዕርህ ይጠበኝ ሕልምህን አውሰኝ!
ትንፋሽህን ልያዝ ልታገል ከዘመን- ልዋደቅ ከዐለም
ጭቆናን ልታገል- ፍትህን ልፋረድ- ለነጻነት ልቁም
የሰላም ዝናሬ መንፈሴም ትቃትት ብዕሬም ትለምልም
ለሰው ክበር ልሙት -በመንግስታት ልቅለል-ከድሎቴ ልጹም!
ከችጋር ልፋታ- ድንቁርና ይክዳኝ
ክሽፈት ይሻር በኔ- ታሪክ ይፋረደኝ!!
ከንቱ አዋጅ ናቸው -አትሻም አውቃለሁ ሙገሳ ውዳሴ
አልችል ብሎ ይዞኝ ጨንቆት ነው መንፈሴ…!
መወማ
ጎፈሬህን ቀባኝ
ዝናርህን ስጠኝ
ብዕርህ ይርጠበኝ- ሕልምህን አውሰኝ!!
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››

May 17, 2014

‹‹‹ማፈር እና ማፍራት›››


‹‹‹ማፈር እና ማፍራት›››

ለምን አልሸፈኑም ያፍሪካ መንግስታት ነውራቸውን ላለም
ለምን አልሸፈቱም ያፍሪቃ ወራዙት ሸክማቸውን ባለም?
አዳም እና ሄዋን ባፈሩበት መቅጸበት ሸፍነውት የለም!?
ለምን አልሸፈኑም?- ለምን አላፈሩም?- ለምን አልሸፈቱም
የዘር ፍሬያቸውን- ፍሬያልባ ቅጠሉን….ለምን አላፈሩም!??
ለምን ‹‹አላፈሩም›› ሰዎች ነውራቸውን በጋርዮሽ ስልጣን
አዳምና ሄዋን ከገነት ተባረው እያሉ ወደቅን..??
ያን ጊዜ ሰቀቀን- አሁንም ሰቀቀን- እያልን ወደ--ቅን!!
ለምን ‹‹አላፈሩም!!›› አዳም እና ሄዋን
የሕይወት ጥም ጠገን???
ለምን አላፈሩም!!??
አሁንም ሮሮ አሁንም ሰቀቀን በብርሃን ዘመን!!!???

May 12, 2014

‹‹ዝናቡም አካፍቷል!›› ቀስተደመናው የታል?

‹‹ዝናቡም አካፍቷል!›› ቀስተደመናው የታል?

ህጻን ሳለሁ ገና- ልጅ
ዝናብ ማለት ለኔ- ጠጅ!
የግዜር ፌሽታ አምሃ ውጋጅ
በደስታ ብዛት ከብጫነት-ወደ ነጭነት ተውላጠ ጽዳጅ!!
በዛ ጽዳጅ ቀን ታጥቤ
ጽዱ ልቤን አራጥቤ
እኔና’ንቺ በጭቃ ውስጥ ስንታጠብ
ድነን ነበር ካ’ለም መቅሰፍት-ከምድር ጠብ!
የበረዶው ጥል ክብ ልማድ-ራሴን እየኮረኮመኝ
ከተፈጥሮ አጣመረኝ…
ካጉራ ዘለል ካጉል ትነት ልጓም ያዘኝ!
ኢትዮያዊ ነኝ!!
በዛን ወቅት ሰንደቅ አላማውን ስንመለከተው
አያይዞን ለልባችን ተስፋ ሰጠው…
ከአጽናፍ አጽናፍ ወንዝ አሻጋሪ  ቃል የሠጠው
በደመናው ቀስቱን ዝርግቶ የኢትዮጵያ መቀነት የተዘረጋው
ለልብ ውስጥ የታተመው አንድነት-ሶስት ቀለም- አረንጓዴ- ቢጫ ቀይ ነው!!
አሁን ታዲያ በዝናብ ውስጥ የሚታየው
በብረት ታስሮ የታሰረው ይህ ሰንደቅ አላማ ነው??
ሰባት ነው ይሉናል የቀስተደመና ስብጥሩ
ይሉናል!! ከሰባትም በላይ ናቸው በተናጠል ሲቆጠሩ!!
ለእንያንዳንዱም አገር ሰጡት በክፍፍል መዋቅሩ፡፡
ሳቅንባቸው ባይገባቸው  የብዙው ባንድ መጣመሩ
ሳይገባቸው በሶስት ገመድ የአንድነት ሃይል ስሩ--ምስጢሩ!!
አሁን፡-
በዝናብ ውስጥ ቀስተ ደመናው የለም
የተዋበው ህያው አርማ በዝናቡ አይታይም
‹‹ጨርቁ›› ይታየኛል በዝናቡ መጽዳት ናፍቆት
አጎንብሶ በዶፍ ሲወርድ የጉድፍ ቋት…
ነው ወይንስ በዘመን ሰንኮፍ እድገቴ ሸፍኖት??
አልገባኝም!!
ቀስተደመናው ርቋል በክፍልፍል ተሸንሽኗል
በሳይንሱ መዳፍ ታሽቶ ከተፈጥሮ ተቆራርጧል
ልጅነት ተረስቷል፣ አገር ተሸጧል  ‹‹ዝናቡም አካፍቷል!››
ቀስተ ደመናው ግን የታል…?
ተስፋ በላይነህ

**ይህ ግጥም  በግንቦት 20 1983ተጸነሰ-  ግንቦት 20 2003-ተወለደ

Apr 27, 2014

“የካሳ ትንሳዔ” በጥሩየ ልብስ



“የካሳ ትንሣዔ” በጥሩየ ልብስ
የጥሩ ሰው ልብስ???
*****
ከዚህ ልብስ መሐል- ስጋ ከሌለበት
አጥንት ካልቆመበት-ታሪክ ካልጻፈበት
የሚታየኝ መንፈስ- ጥሩ ሰው አለበት፡፡

 ካሳ አባ ታጠቅ ተዋቡን ሲሸኛት
በግሸን ተራራ እንደ ግማድ ቀብሯት
ሲመለስ በዚያን ወቅት ባዶነት ተሰምቶት፤
ከራሱ ከጥላው ከመኳንንት አልፎ
ከዛፉ ከምድሩ ደርሶ ተኮራርፎ
 በሰሜን በደቡብ ሲዘምትበት ቀፎ
 ባይተዋር እዳይሆን የሰው ሰው አሰኘው!
ወጣነት ባንዴ ሰው መሆን ኣማረው፡፡

ጥሩነሽን አይቶ በውበት ቁንጅና
ያባቷንም ግዞት፣ የጥሩየን እድሜ ከቶ ሳጠና
አገባት በዚያ ቀን ጥሩነሽ "ውቢቷን"
ሊያደርስ አንድነቱን ሊረሳም ተዋቡን፡፡
*****
ዑል ዓለማየሁ ካብራክ ቢገኝለት
ሩቅ ነበር ቴዲ መች ቅርቡን አየበት?
ናፒር ሲታይ ማዶ
ከሰሜን  ተዋዶ በካሳ ማግዶ
በጎጃም ተሰዶ
ሰተት ብሎ ገባ ናፒር እንግሊዙ በግብር ተላምዶ!!

ወሩ ሁዳዴ ነው- ሰሙነ ህማማት
ትንሣዔ መስሎታል በባሩድ  ሰው መሞት…

መቅደላ አሽካካች፣ እንግሊዝን ይዛ
ሲወረስ ጨፈረች ቀረች እንደዋዛ፡፡
ፈጠኑ ጌቶቹ የድርሻውን ያዙ
እጣ ተጣጣሉ፣ በቀሚስ በዘዱ ወርቁንም አበዙ

ብራናው ይከመር፣ ሽሩባውም ወዙ
ይሂድ ወደ ቤቱ ሸኙት ዕዳ ግዙ፡፡
******
ዕዳውን የገዛው ካፒቴን ስፒዲ
ባሻ ፈለቀ ነው አበሻው እንግዲ….
ጥሩየን ልዑሉን ወርቁን ይዘውታል
ለንግስት ሊያሳዩ "የጸሐይ መውጫዋን"
ጥሩየ አማጠች ዳዊቷን ሰደረች
ሞቷን አሳጠረች በዳዊት መዝሙራት ቀብሯን አሳረገች…
ባህር ሳትሻር -አገሯ ላይ ቀረች!!
 በበፍታ ቀሚስዋ ታሪክዋን ከተበች፡፡
.
.
ልዑሉም በዛበት የሙትነት መንፈስ
ደስታ የት ይገኛል በደት ሆድ ሲብስ..?
******
አሁን፡-

የጥሩየ ልብሷ ይታየኛል ፤ ባዶ መስሎ ውስጡ
የጥበቡ ማማር አወይ ጉድ ለምስጡ
ምስጥ እንደው ይበላል ስጋን ያፈራርሳል
ምስጢር መች ቀላል ነው በማንስ ይፈታል?
ያልተፈታ ምሥጢር ያለልተቀቁወዋጨ ፊደል
ያልተሳካ ታሪክ ያልተሳለ ምስል

በጥሩዬ ቀሚስ በጥሩዬ ሐብል፡፡
******
ካሳ ለምን ሞተ፣ ጥሩየስ ምን አለች?
ስደት አልቀናትም ሞቷን በዝታ ሻተች፡፡
ለምን ተቀበረ ገብርየ በወኔው ?
ታንጉት እንዴት ብላ ምስጢሯን ታካፍለው...
የነጭ እባብ ልክፍት አገሬን ሲያስታመው?

ባዶ አይታይም ዜሮም ወሰን የለው
በጨርቁ ገመድ ውስጥ መንፈስ ታሪክ አለው!!
ባዶ ነው አትበሉኝ አልቦ ታሪክ አገር
በዮሐንስ አንገት ይታየኛል ትንቢት የኑዛዜ ቀመር፡፡
መልሰህ ትከለው የኢትዮጵያን አንገት
ራዕዩ ታላቅ ይሻገራል ጉንደት…
ባዶ ነው አትበሉኝ የዚህ ጥበብ ግጥም
በባደዶ ነው አትበሉኝ የጥሩ ቀሚስ የጥሩየ ሕመም፡፡
-
ለመርዛማው እባብ ይዣለሁ ቀጥቃጩን መድህን የአለም
ካልሞቱ ካልሄዱ ካልተሰው ባለም ያ ትንሳሣኤ የለም!
***
"የካሳ ትንሣዔ" ይዘከር በዓለም...
                             ቀሚሱን እዩት  ውስጡ ማንም የለም!
Tsefa B. MiYAZiYA 6- On Tewodros's death Ann.