Jun 9, 2019

መራራ እውነት- በኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፍ ዳሰሳ

ራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፍ ቅኝት!!





"ታሪክ ጠላ ቤት ተቀምጦ በጥላቻ ስካር የሚደረስ ልቦለድ ሳይሆን በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የሚፃፍ እውነታ ነው::" ገፅ 228:: 


አንድ የመፅሐፍ ወዳጄ ገዝቶ ላከልኝ:: እስክቀበለው ድረስ በጣም ጏጉቼ ስለነበር እጄ ሲገባ ደስ አለኝ:: አለሁበት ቦታ እንደተቀመጥኩ ጀመርኩት:: 100 ገፅ መሆኑን ያወቅሁት ስልኬ ሲጠራ የነበረኝን ቀጠሮ ሳስታውስ ነው:: ቁጭት ነው:: ሃቅ ነው:: የሩብ ክፍለዘመኗን ኢትዮጵያ በመረረ መንፈስ ይመላለስባታል:: የሰው እስትንፋስ እጅግ አስቸጋሪ ኃይል ነው:: እምቅ ጉልበት:: ደፍቶ ይጥላል:: የታጨቀ የዘመን ኩርፊያ:: ያውም የታሪክ ስቅለት የደረሰባትን አገር እዳ መሸከም ቀንበሩ እጅግ የከፋ ነው:: 


"ታሪክ የታመመ ጭንቅላትን ያክማል" የሚባለው የሌቭን አባባል በራሱ ባለታሪኮችን ጭንቅላት በክፉኛ ሳያሳምም አይቀርም:: ምክንያቱም በታሪክ ለመታመም መጀመርያ ሰው መሆንን ይጠይቃል:: ሰው መሆን ደግሞ ጭንቅላት ልብ እና ኅሊና ያለተቃርኖ በስሙሙነት የሚተዳደደሩበት "ሥጋለባሽ ፍጥር" መሆን ነው:: በኢትዮጵያ በሩብ ክፍለ ዘመን ታሪኳ ግን ሶስቱ ዓበይት ውቅሮች ከስጋ ለባሹ ጋር መጣመራቸውን መመስከር ያስቀስፋል:: በታሪክ ስጋ ለባሹ ብቻ በሚከበርባት አገር መፈጠር ህመም ነው!!


ይቺ የማትመቸኝ <<27 ዓመት>> የምትባልን ቃል ላለመደጋገም "ሩብ ክፍለ ዘመን" በሚል ዘይቤ ብወክላት የሚሻል ይመስለኛል::


የመፅሐፉ አዘጋጅ በሥነ ፅሑፍ ስልነቱ አቻ አይገኝለትም:: በየገፁ የተሞሉት የዘይቤያዊ ገለፃዎች ልክ ቁጭ ብሎ እንደሚተርክልህ አይነት ባለታሪክን ይመስላሉ:: ኃያል ነው:: ብእሩ አድምቶ እዛው ፈጭቶ ጋግሮ እንደሚመግብ መና አቅራቢ ነው::


መፅሐፉ ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት "ብርሃኔ" ነው ለሚሉት ለስርአቱ አሽከሮች ከሽፋን ገፁ ጀምሮ ሲታይ ገፊ መሆኑ አያጠያይቅም!! ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ አክሱምን አለማስቀመጡ የሆን ተብሎ ሊመስል ይችላል:: የሽፋን ገፁ መራር እውነት ብሎ አፄ ቴዎድሮስን የአበገዳውን ገፅ እና  ድንቅነሽን አጣምሯል:: 



እንደዚህ ፅሁፍ አስተያዬት ሰጭ እምነት መሰረት:: በኢትዮጵያ ታሪክ የተከሰቱ ተቃርኖዎችን በመፈተሽ  የፖለቲካ ንትርካችንን ማከም መቻል የምንጊዜም ታሪክ አዋቂያን አላማ ሊሆን ይገባዋል የሚል ፅኑ እድል ፈንታን ወስዷልና መስለ ስራዎችንም ይሁን ግለሰቦችን አጥብቆ ይሞግታል ይማፀናል ኃቀኝነታቸውን ፈትሾም ይወዳጃል::


መፅሐፉ በ416  ገፆች ተጠርዞ:: አራት አበይት ምእራፎችን ይዞ የኢትዮጵያ ታሪክ ላለፉት አርባ እና ሃምሳ አመታት የደረሰበትን እዥ "ነቀርሳ" ለማከም ይታትራል::  (ነቀርሳ ቫይረስ ነውና ለቫይረስ ህመም ህክምናው ቀላል እንደማይሆን እያሰብን የአካሚውን ተጋድሎ ብርትት እና ቁርጠኝነት ሳናደንቅ አናልፍም)


በምእራፍ አንድ የታሪክ አፃፃፍ ትምህርትን -የታሪክ ምንድርነትን -ማስረጃዎችን የታሪክ አፃፃፍ ጅምሮችን (በተለይምለታሪክ አፃፃፍ ያለን የዘመን ቅርበት) እንዲሁም ዋነኛ የችግሮቻችን ማጠንጠኛ አለት የሆኑትን "የኢትዮጵያ ታሪክ ፀሐፍት ተቃርኖ" በአንደኛው ምእራፍ ወስጥ ተተንትነው ቀርበዋል::


በገፅ 123 የቀረበው የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፍት ተቃርኖ ክፍል ውስጥ 

ሀ) የቤተ መንግሥት ታሪክ መዝጋቢዎች 


ለ)የማርክሲስት ሌኒኒስታዊ አመለካከት ታሪክ ጸሐፊዎች


ሐ) የዘውግ ታሪክ ጸሐፊዎች በሚል ካስቀመጠ በሁዋላ ለአሁኗ ኢትዮጵያ የችግር ሁሉ ምንጭ ሆኖ የቀረበውን "ዘውጌነት" በአስር ምደባዎች በማስቀመጥ እርቃናቸውን ሳያስቀር አደባባይ ላይ ይገልጣቸዋል:: 


የዘውጌ ታሪክ ፀሐፊዎችን ከኦሮሞ ዘውግ ታሪክ ጀምሮ ኦነግን እንደ ፅንሱ መስራች በመቁጠር መራር እውነት እንጋት ዘንድ ብርቱ ሰይፉን ይመዝዛል:: በዚህ ክፍል ውስጥ ትልቅ ጥናት ውይይት የሚያስፈልገውን የናዚዎች መሸሸግያ ማጣት እና ምሽጋቸውን ኢትዮጵያን የማድረጋቸው ትንተና የዚህን ፅሑፍ አስተያዬት ሰጭውን ቀልብ እና ልቡና የሳበቡት-  የመፅሀፉ 133ኛ ገፅ አንድ ሙሉ መፅሐፍ የሚወጣው እንደሆነም ሳይሸሽግ አያልፍም!!


ከኦሮሞ ዘውግ ታሪክ ፀሐፊዎች ተሻግሮ የትግራይ ዘውገኞችን የሚተነትነው በገፅ 135 ሲሆን የሰሜኗ ኢትዮጵያን ህውሃት መራሽ ኃይል ከደቡቡ ኢትዮጵያ ኦነግ መራሽ ሰይፍ ጥምረት የፀረ ኢትዮጵያዊነት ዘመቻ (በፀረ አማራነት ሽፋን) እና የአለም አቀፋዊውን ደባ መላመት አያይዞ ማቅረቡ አሁንም የዚህን ፅሑፍ አስተያዬት ሰጭ ቀልብ የሳቡት ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው!! 


በትግራይ ዘውጌዎች ርእስ ስር በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የምናዬው ፖለቲከኛ/ፀሐፊ አስራት አብርሃም ይህ መፅሐፍ በሚፃፍበት ወቅት የነበረውን አመለካከት ደራሲው ቢፈትሽ መልካም መሆኑን እየገለፅን- በግለሰቦች አመለካከት የዘውግ መዋቅራችን መፈተሹ አልፎ አልፎ ክርክራችንን በውሃ ላይ ቆረቆር እንዳያስብሉብን መጠንቀቅ ሳያሻ አይቀርም:: ፕር ገብሩ ታረቀኝ በጉልህ ተማጋሽ ሆነው የቀረቡበትም ምእራፍ እንዳለ ልብ እንልለን::: 


ከሁለቱ ዘውጌዎች ሌላ  ወደ ሶስተኛው ዘውጌ ተረኛ "አማራ" ዘውግ የታሪክ ፀሐፊያን ያሸጋግረናል:: ፀሐፊው እንደአብዛኞቹ የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኞች "አማራ የለም" በሚል የፖለቲካ አፍ መፍቻ መወድስ አይታወቅም:: 


ለዚህም በቅርቡ በማህበራዊ ድረገፆች የተነበበቡት አጫጭር ፅሁፍ የግል ምልከታዎች "ውሃልክነት እና አማራ የኢትዮጵያ ፈጣሪ..." አባባሎች ፀሐፊውን ክፉኛ እንደነኩት ሳንጠቅስ ማለፍ አይቻልም:: (የዚህን ዝርዝር ምልከታ በሌላ ፅሁፍ ብንመለስበት የሚበጅ ይመስላል)


ቀጥሎም የሶማሊ ዘውገኞችን ከዳሰሰ በሁዋላ በዘመናችን የሚታዬውን የታሪክ ሽሚያም እስከ ቀጣዩ ምእራፍ ድረስ በበላይ ዘለቀ በአፄ ቴዎድርስ በእፄ ኃይለሥላሴ ላይ የሚነሳውን "የዘር" ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት ሚዛናዊውን <<መራር እውነት>> በተባው ቁጭት ስሜት ይሞግተናል::


ቀጣዩ ምእራፍ ገፅ 156 የሚጀምረው <<የደማቅ ታሪካችን ሰበዞች>> በሚል ርእስ ነው:: 


ከቅሪት አካል ሳይንሳዊ ግኝቶች "ድንቅነሽ" ጀምሮ ጥንታዊዋን ኢትዮጵያ በዓበይት የታሪክ ምእራፍ አምዶች እየከፋፈለ ፑንትን -ዳእማትን አክሱምን ዛግዌን ሰለሞናዊውን ያስቃኘናል:: ይህ መፅሐፍ ሰለሞናዊውን ስርአት በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ካላስገቡ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ መመደቡን  ልብ ብለን እያሰመርን ወደ ሶስቱ የኢትዮጵያዊነት አምዶች <<ዋቄፈና _ክርስትና እና እስልምና>> ሽግግር እንዘምታለን:: ገፅ 169-ገፅ 190::


በተቃርኖ የተሞላው ፖለቲካችን ክምችት የታሪክ አተያያችን እና ግልብ አዘጋገባችን እንደሆነ ይነገራል:: ለዚህም ተቃርኖ መፈጠር ለችግር መዳረጋችን ለመራር እውነት ፍለጋው ለተቃርኖው "ነቀርሳ" ታሪክን በጥልቀት መመርመር ፈውስ እንደሚሆን ታምኗል:: ጥያቄው እነኚህ ተመራማሪ ኃቀኛ ታሪክ አዋቂያን እንዴት ብለው ነው የፖለቲካውን ድር መበጣጠስ የሚችሉት? የፖለቲከኞችን አዙሪት ቀልበው ለሰከነ አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያስናዱት? የሚለው ይሆናል::


በኢትዮጵያ ታሪክ ፀሃፍያን እና በኢትዮጵያዊነት የረዥም አመታት ተንታኝ ግለሰቦች ዘንድ የሚጠቀሱትን "አይሁድ-ክርስትና-እስልምና" እምነት ትስስሮችን ወደ "ዋቄፈና-ክርስትና እና እስልምና" መስተጋብር የተገለፀበት መንገድ የፀሐፊው ልዩ ገፅታ ይመስለኛል::  እንደነ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያዊነት ገለፃ አይሁድ ክርስትናና እና እስልምና የፈጠሩት ውህደት የኢትዮጵያዊነትን መአዛ እንዳሰፈነ ሲገለፅ የኖረውን የታሪክ አተያይ የመምህር ታዬ ቦጋለ መፅሐፉ ግን ስለ ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ የኦሮሞ ጎሳዎችን ቦረናን እና ጉጂን በድንቅዬ እሴታቸው በገዳ ስርአት ቀለም እያስዋበ ያቀርብልናል:: 


የገዳ ስርዓትን ከአቴንሱ የዴሞክራሲ መነሻነት ጋር በማነፃፀር አቅሙን ይፈትሽልናል:: የግሪኮቹ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ከገዳው ስርአት በእድሜም በፍትሃዊነትም በአተገባበርም ሆነ በትርጉም ከቦረኖቹ ጋር ሲመዘን <<በንፅፅር ሚዛን>> ቀልሎም ተገኝቷል:: በአጠቃላይ ይህንን የገዳ ስርአት "የዴሞክራሲ ውሃ ልክ" ሲልም በግልፅ በገፅ 191 በማስቀመጥ እስከ 212 ገፅ ተተንትኖ ቀርቦልናል:: 


ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊንትን ከገዳ ስርአት ውጭ ማሰብ እንደማይቻል ደጋግሞ በማስቀመጥ ይሞግተናል:: ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪቃ እውቅና እና ግልጋሎት ይቸረው ዘንድ   አብዝቶም ይመክራል!!


ፀሐፊው  የኢትዮጵያን ህብረ ቀለማዊ እይታን ሳይሸሽግ የሚመሰክር ነው:: ፅንፈኛ ዘውጌዎችን አጥብቆ ሲሟገት አሃዳዊ ስርአትን ከሚሹት ወገኖች ሊመደብ እንደማይችል "የፖለቲካውን ስፔክትረም" ቀለማት አጥንቶ የተዘጋጄ በመሆኑ ለሃሜት እንዳይዳረግ ሆኖ ራሱን የጦር ልብስ አልብሷል!!


ይህንንም አገላለፅ በፍቱንነት የሚመሰክርልን ኢትዮጵያን ከብሄረሰቦች እስርቤትነት የፖለቲካ ቅኝት ወደ የብሄረሰቦች ሙዝየምነት እና የብሔረሰቦች ሞዛይክነት እንዲሁም ባለ ብዙ ፀጋዎች ሀገርነት (ገፅ209) ስያሜ ማስቀመጡን ልብ ስንል ነው:: 


ሌላኛው ተቃርኖ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የነገስታትቻችንን ታሪክ ቅርፅ ይዘት በጥልቀት መለዬት ጉዳይ ነው:: አፄ ቴዎድሮስ በዘውጌ ታሪክ ፀሐፊያን ዘንድ በተለይም የዘውግ ፖለቲካ መዋቅራዊ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ በተጨማሪም እውነት እስኪመስል ድረስ የሚሰበኩት "ምኒልክ ተኮር ዘገባዎች" በዚህ መፅሐፍ ተመርመረው ቀርበዋል:: 


"አባት እሆንሀለሁ ልጅ ትሆነኛለህ:: ጠላት ዙርያችንን ከብቦናል:: አንድነታችንን እናጠናክር:: ሠራዊቴ ኃያል ስለሆነ ብትገጥመኝ ወገን ታጨራርሳለህ:: በሰላም ለእኔ አድረህ ገብር:: ራስህን በራስህ ታስተዳድራለህ:: በውስጥህ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም::" 

የሚለው አባባል ለፌዴራሊስቶቹ ጭንቅ የሚሆን ነው:: "ራስህን በራስ ታስተዳድራለህ" የሚለው ስንኝ ለዘመነኛ ፌዴራሊስት ነን ባዮች (ስሁታዊያን) ከማን አፍ የወጣ ቃል ነው ተብለው ቢጠየቁ ወደ ምኒሊክ የሚያተኩር ልእልናውን አልፈጠረባቸውም::  


በኢትዮጵያ ታሪክ ከመራሩ እውነት አንደኛው "የታላቁ ተቃርኖ" ምእራፍ መግቢያ የምኒሊክ ጉዳይ ነው:: ምኒሊክን እንደ አቅላጭ/ አሃዳዊ መሪ ሳይሆን እንደ ፌዴራሊስት መሪ እንዲሁም እንደ ጨቋኝ ሳይሆን እንደ ነፃ አውጭ መሪ መውሰድ የታዬ ቦጋለ ብእር ቋሚ ተማጋች ነው:: 


እንዲህ አይነቱን መራር እውነት መጋት ግድ ሳይል አይቀርም:: የመፅሐፉ አቅራቢም ኦሮሞን በገዳ ስርአት እሴቱ በኢትዮጵዊነት ማማ ላይ ቋሚ አምድ የማድረጉን ያክል አፄ ቴዎድሮስ እና አጤ ምኒልክን ጉልህ አሻራነት ለድርድር ሳያቀርብ የተለመድ ዝናሩን ያበረታል!! ፀሐፊው በዚህ ብርታቱ እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደርን ብሂል ሊተገብር ላይ ታች ሲልም ይስተዋላል:: 


ልጅ እያሱ -ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ እና ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በበጎነታቸው ሚዛን ላይ ሲቀመጡ የደርግ እና በተለይ የቀጣይ 1983ቱ ስርአት በዘመነ ፅልመት ስያሜነታቸው ተከትበው እናነባለን:: 


ይህ የአዲሱ ዘመን ታላቁ ተቃርኖአችን ነው:: ከ1966 እስከ አሁን በተልይም ከ1983 ወዲህ ኢትዮጵያ ነፃ የሆነችበት የብርሃን ዘመን ወይንስ እንደ ፀሐፊው አባባል ዘመነ ፅልመት?


በቀጣይ የምንዳስሰው ይሁን:: ምናልባትም የታሪክ መምህራን (ምሁራን) በዚህ ክፍል ላይ የሰላ ትኩረታቸውን ቢሰጡበት እና ኢትዮጵያችንን ከእንቅልፏ ከድንንዛዜ ከነቅርሳዋ ያክሟት ዘንድ ቅን ባለሙያዎችን እና ጋሻ ጃግሬ ባለሟሎች የምትሻበት የዘመን ምእራፍ ላይ እንገኛለን:: 


የዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ ባለሙያ ሳይሆን የባለሙያዎች ባለሟል:: የኢትዮጵያዊነት ጋሻ ጃግሬነቱን እድል ፈንታን በመውሰድ አሁንም ከንባብ ከሃሳብ ከመሰል ተሳትፎነት ሌት ተቀን አይቦዝንም:: 


ስጋለባሽ ከሶስቱ መዋቅሮች ጋር ትሥሥር አለው ብሎ ያምናልና!! ለዚህም አይነት ፍጡር ታሪክ አኪሙ ነው:: አካሚዎችን አያሳጣን እያለ ለጊዜው ይሰናበታል!! 



No comments: