Feb 26, 2021

በዕውቀት መገበያዬት!

የመፅሐፍ ዳሠሳ::


የመፅሐፉ ርእስ:- <<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት>>


ፀሐፊ:- ደሳለኝ ከበደ (Eng: MSc, MBA-IB]


የመፅሐፉ ገፅ ብዛት:- 234



በአንድ ሙያ ዘርፍ ልምድን እውቀትን እና ጥልቅ

ግንዛቤን ያካበቱ ግለሰቦች ስለሙያው መፅሐፍ 

ሲፅፉ ተሽቀዳድሞ የማንበብ ልማድ አለኝ:: 


ደሥታዬም ወሰን አይኖረውም:: ምክንያቱም ብዙ አመታትን ተምሬ ገንዘብ ከፍዬ የምማረውን 

ትምህርት በምወደው ሥነ ፅሑፍ ዘርፍ ንባብ [መፅሐፍመልክ ተከሽኖ ሲገኝ የደሥታዬ ዓቢይ ምክንያት ነው:: 


ይህንን የምለው የካቲት ወር 2013 . ለንባብ የበቃውን የኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ 

<<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንትአስተዳደር እና ግብይት>> በሚል ርእስ የታተመውን 

የሙያ ነክ የንግድ ምክረ ሐሳብን የያዘ 

መፅሐፍ ለገብያ ሲወጣ ነው::


አንድ መፅሐፍ በተለምዶ በተደጋጋሚ የምናውቀውን ድርጊት 

ሥሕተት መሆኑን አርሞ ትክክለኛውን ትርጓሜ እና

አቅጣጫ ሲያስቀምጥልን በረከቱ ሁለንተናዊ ነው:: 


ይህንንም የምናዬው በመፅሐፉ  ጅማሬ ላይ እንዲህ በሚል ይነበባል:: 


[...] አንዳንዶች ግንባታን እና የሪል እስቴት ልማትን አንድ አድርገው ሲገልጹ ይስተዋላል:: ይህ ግን ስሕተት ነው::  ገፅ 3


[...] የሪል እስቴት ልማት ሥራ የሂሳብ እና ገንዘብ ነክ ባለሙያዎችን  

የሕግ ባለሙያዎችን  የፕሮጄክት ትግበራ ባለሙያዎችን  

የግንባታ ሥራ መሪዎችን  የተለያዩ የዲዛይን ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን  

የሕንጻ አስተዳደርሥራ አዋቂዎችን  

የሽያጭ እና 

ገበያ ጥናት ሥራ የሚሠሩ ሙያተኞችን የመሣሰሉትን ያካትታል:: ገፅ 3


እንግዲህ መፅሐፉ በዚህ አይነት ቅኝት  

ሥሕተትን እየነቀሰ በማውጣት 

የባለሙያ ሐተታዎችን እና 

ዝርዝር ትንታኔዎችን 

ቀለል ባለ አማርኛ ያቀርብልናል:: 


በሃገራችን ረዥም ታሪክ  የሚታወቁትን ቁሳዊ ቅርሶችንም በመጥቀስ 

የሪል እስቴት ታሪክ አመጣጥን ትርጓሜን 

በመግለፅ እንዲሁም ሌሎችን 

ዝርዝር ሐሳቦች ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማስተሳሰር ይሞክራል:: 


የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ሰፊ 

የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከመሆኑ ጎን ለጎን 

ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎችን 

እና ባለድርሻ አካላትን እንዲሁም 

ለኪሳራ የሚያጋልጡ ተጓዳኝ የጎንዮሽ 

ተፅእኖዎችን የሚያስተናግድ ሆኖ በመገኜቱ በሚጠበቀው ልክ 

ስኬታማ አለመሆኑን እንገነዘባለን:: 


ይህም በቁጥር ሲገለፅ ለምሳሌ 

1481 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች 

በሪል እስቴት ፕሮጄክት ውስጥ የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልፆ

 3.4% ማለትም 50ዎቹ ብቻ እየተሰሩ ፤ 

60ዎቹ ደግሞ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ መግባታቸውን ይገልፃል:: 


የውጭ ባለሃብቶችን የሚያሳትፍ ዘርፍ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ  

እስካሁን 6% የሚሆኑ የውጭ ባለሀብቶች የተመዘገቡበት ነው:: 

ገፅ 164


ከዚህ ጋር ተያይዞ ለውጭ ባለሃብቶች አገራችን ያስቀመጠችው የገንዘብ መጠን እና የመሬት ስፋት ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይ 

እጅግ ዝቅተኛ መሆኑም ተቀምጧል:: 

ገፅ 180


መፅሐፉ አጠቃላይ የሪል እስቴት ዘርፍን ከታችኛው መዘጋጃ ቤታዊ አገልግልቶች ችግር (ገፅ 165) ጀምሮ እስከ ላይኛው ዝርዝር የመንግሥት ተቋማት ጋር በማዛመድ የዘርፉ ተግዳሮቶችን 

በግልፅ ቋንቋ ዘርዝሮ አስቀምጧል:: 


በሪል እስቴት ዘርፍ ለመሰማራት 

አስፈላጊ የሙያ ትንተናዎችን 

የሚያካትተው መፅሐፉ በዚህ ንግድ ዘርፍ ሊሰማሩ የሚያስቡ ግለሰቦች 

(በጋራ ቢሆን ይመክራል - ገፅ 203) የመግቢያ በሩን በተደላደለ የእውቀት መርህ ስር እንዲዋቀር የሚረዳ ፈር ቀዳጅ ሥራ ፍኖተ ካርታ ሆኖ የሚያገለግል ነው::


በአገራችን እንደዚህ አይነት የንግድም ይሁን የትኛውም ዘርፎች 

ውስብስብ የሆኑ የአስተዳደር ሂደቶችን የሚጠይቁ ከሆኑ ከስኬታማነታቸው 

ይልቅ በጅምር ሲቀሩ ለከፋ ኪሳራ 

እና ለግለሰባዊ ለአካባቢያዊ 

ምስቅልቅሎች 

ስንዳረግ በተደጋጋሚ የምናስተውለው ሐቅ ሆኗል:: 


ፕሮጄክት አፈፃፀም ላይ የሚስተዋለው 

ክሽፈታችን የትኛውንም የሙያ ዘርፍ 

በቂ ልምድ ክትትል እና ሙያተኞችን 

የማያሳትፍ የስራ ቅንጅት አለመኖሩን 

የሪል እስቴት መፅሐፍ በሚገባ ያሳየናል:: 


የመሬት አቅርቦቱ  የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ  

መንግስት ከግለሰቦች ጋር በጋራ ቢሰራ በሚል የተቀመጡት ምክረ ሀሳቦች 

ፀሐፊው በሙያው ያካበተውን 

የቆዬ የስራ ልምድ ታሳቢ የሚያደርግ ጥቆማዎች አሉት:: ገፅ 190/191


<< አብዛኞቹ የሪል እስቴት ፕሮጄክት አልሚዎች የግንባታ ሥራ 

የሚያከናውኑት እንደ ሪል እስቴት 

አልሚ ባለሀብት ተመዝግበው  

የሪል እስቴት ንግድ ፈቃድ ኖሯቸው 

ሳይሆን የሕንጻው ግንባታ ፈቃድ ብቻ 

አውጥተው ግንባታ የሚያከናውኑ በመሆናቸው ነው::


አብዛኞቹ  የሪል እስቴት አልሚዎች ወደ ሪል እስቴት ሥራ ምዝገባ የሚገቡት  

የመጠቀሚያ ፈቃድ አውጥተው 

ለማከራዬት ወይም ለመሸጥ 

በሚያስቡበት ወቅት ነው>> 

ገፅ 163 ::


ይህ አካሄድ ለጥናት ምቹ አለመሆኑን እና ዘርፉን በሙያዊ እይታ የተለያዬ ተጨማሪ 

ችግሮችን ማስተናገዱን ይጠቅሳል:: 


በአጠቃላይ መፅሐፉን በዘርፉ ሊሰማሩ ላሰቡ ድርጅቶች "አጤሪራ" ቋሚ ማስታወሻም ተይዞለት የሚነበብ ነው:: 


የእውቀት እና ክህሎት ልምምድን 

በቅድሚያ ታሳቢ በማድረግ 

የንግድ ባህላችንን ጥናታዊ 

ሂደትን የሚያበረታታ 

ወቅቱን የጠበቀ በብዙዎች 

የአገራችን ክፍል

ለውይይት ቀርቦ እገዛውን በተጨባጭ ሊያረጋግጥ የሚገባው ነው:: 


የመፅሐፉ አላማ የሪል እስቴት ዘርፍ በነዋሪው ሊገዙ የሚችሉ  (Afordalbe houses) 

እንዲበራከቱ የሚጥር 

በመሆኑ ምናልባትም ፀሐፊው 

በተካነበት ሥልት ለቀጣይ ተያያዥ 

ሥልጠናዎችን

ለመስጠት የተዘጋጄበት ትጋት በድጋሚ የሚያስመሰግነው ነው:: 





በፕሪፋብ (ተገጣጣሚ የቤት አይነቶች

ላይ የደረሰውን የተጣደፈ ውድቀት እና 

በተለይ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የሚታወቀውን 

የእክሰስ ሪል እስቴት ድርጅት 

አጠቃላይ ሂደት በምሳሌነት 

በማስቀመጥ የፕሮጄክት 

አፈፃፀሙን ውስጣዊ እና ውጫዊ 

ዝርዝር ሂደቱን ከመፅሐፉ በግሌ 

ጠብቄ ያጣሁት ክፍል ቢሆንም 


ለንባብ ምቹ ሆኖ ቀለል ባለ አማርኛ 

መቀመጡ ብቻ ሳይሆን 

በዝግታ የተሰናዳ የቃላት ህፀፆች ከሞላ ጎደል የማይታዩበት 

(የሚያስፈሎገውን ገፅ 39) አይነት 

የተልባ ፍንጣሪ ጥቃቅን ስህተቶች 

ከማውጣት ውጭ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን 

የሚያበረታታ አርዐያ ሊሆን 

የሚገባው እንደ 'ማንዋል'  ሆኖ የሚያገለግል ሥራ ነው:: 


በየቢሮአችን መፅሐፍ መደርደርያ ልናጣው የማይገባ አገልጋይ መፅሐፍ::  <<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት>>


ተስፋ በላይነህ 

የካቲት 2013 - ኢትዮጵያ!


No comments: