Showing posts with label Books. Show all posts
Showing posts with label Books. Show all posts

Feb 26, 2021

በዕውቀት መገበያዬት!

የመፅሐፍ ዳሠሳ::


የመፅሐፉ ርእስ:- <<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት>>


ፀሐፊ:- ደሳለኝ ከበደ (Eng: MSc, MBA-IB]


የመፅሐፉ ገፅ ብዛት:- 234



በአንድ ሙያ ዘርፍ ልምድን እውቀትን እና ጥልቅ

ግንዛቤን ያካበቱ ግለሰቦች ስለሙያው መፅሐፍ 

ሲፅፉ ተሽቀዳድሞ የማንበብ ልማድ አለኝ:: 


ደሥታዬም ወሰን አይኖረውም:: ምክንያቱም ብዙ አመታትን ተምሬ ገንዘብ ከፍዬ የምማረውን 

ትምህርት በምወደው ሥነ ፅሑፍ ዘርፍ ንባብ [መፅሐፍመልክ ተከሽኖ ሲገኝ የደሥታዬ ዓቢይ ምክንያት ነው:: 


ይህንን የምለው የካቲት ወር 2013 . ለንባብ የበቃውን የኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ 

<<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንትአስተዳደር እና ግብይት>> በሚል ርእስ የታተመውን 

የሙያ ነክ የንግድ ምክረ ሐሳብን የያዘ 

መፅሐፍ ለገብያ ሲወጣ ነው::


አንድ መፅሐፍ በተለምዶ በተደጋጋሚ የምናውቀውን ድርጊት 

ሥሕተት መሆኑን አርሞ ትክክለኛውን ትርጓሜ እና

አቅጣጫ ሲያስቀምጥልን በረከቱ ሁለንተናዊ ነው:: 


ይህንንም የምናዬው በመፅሐፉ  ጅማሬ ላይ እንዲህ በሚል ይነበባል:: 


[...] አንዳንዶች ግንባታን እና የሪል እስቴት ልማትን አንድ አድርገው ሲገልጹ ይስተዋላል:: ይህ ግን ስሕተት ነው::  ገፅ 3


[...] የሪል እስቴት ልማት ሥራ የሂሳብ እና ገንዘብ ነክ ባለሙያዎችን  

የሕግ ባለሙያዎችን  የፕሮጄክት ትግበራ ባለሙያዎችን  

የግንባታ ሥራ መሪዎችን  የተለያዩ የዲዛይን ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን  

የሕንጻ አስተዳደርሥራ አዋቂዎችን  

የሽያጭ እና 

ገበያ ጥናት ሥራ የሚሠሩ ሙያተኞችን የመሣሰሉትን ያካትታል:: ገፅ 3


እንግዲህ መፅሐፉ በዚህ አይነት ቅኝት  

ሥሕተትን እየነቀሰ በማውጣት 

የባለሙያ ሐተታዎችን እና 

ዝርዝር ትንታኔዎችን 

ቀለል ባለ አማርኛ ያቀርብልናል:: 


በሃገራችን ረዥም ታሪክ  የሚታወቁትን ቁሳዊ ቅርሶችንም በመጥቀስ 

የሪል እስቴት ታሪክ አመጣጥን ትርጓሜን 

በመግለፅ እንዲሁም ሌሎችን 

ዝርዝር ሐሳቦች ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማስተሳሰር ይሞክራል:: 


የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ሰፊ 

የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከመሆኑ ጎን ለጎን 

ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎችን 

እና ባለድርሻ አካላትን እንዲሁም 

ለኪሳራ የሚያጋልጡ ተጓዳኝ የጎንዮሽ 

ተፅእኖዎችን የሚያስተናግድ ሆኖ በመገኜቱ በሚጠበቀው ልክ 

ስኬታማ አለመሆኑን እንገነዘባለን:: 


ይህም በቁጥር ሲገለፅ ለምሳሌ 

1481 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች 

በሪል እስቴት ፕሮጄክት ውስጥ የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልፆ

 3.4% ማለትም 50ዎቹ ብቻ እየተሰሩ ፤ 

60ዎቹ ደግሞ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ መግባታቸውን ይገልፃል:: 


የውጭ ባለሃብቶችን የሚያሳትፍ ዘርፍ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ  

እስካሁን 6% የሚሆኑ የውጭ ባለሀብቶች የተመዘገቡበት ነው:: 

ገፅ 164


ከዚህ ጋር ተያይዞ ለውጭ ባለሃብቶች አገራችን ያስቀመጠችው የገንዘብ መጠን እና የመሬት ስፋት ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይ 

እጅግ ዝቅተኛ መሆኑም ተቀምጧል:: 

ገፅ 180


መፅሐፉ አጠቃላይ የሪል እስቴት ዘርፍን ከታችኛው መዘጋጃ ቤታዊ አገልግልቶች ችግር (ገፅ 165) ጀምሮ እስከ ላይኛው ዝርዝር የመንግሥት ተቋማት ጋር በማዛመድ የዘርፉ ተግዳሮቶችን 

በግልፅ ቋንቋ ዘርዝሮ አስቀምጧል:: 


በሪል እስቴት ዘርፍ ለመሰማራት 

አስፈላጊ የሙያ ትንተናዎችን 

የሚያካትተው መፅሐፉ በዚህ ንግድ ዘርፍ ሊሰማሩ የሚያስቡ ግለሰቦች 

(በጋራ ቢሆን ይመክራል - ገፅ 203) የመግቢያ በሩን በተደላደለ የእውቀት መርህ ስር እንዲዋቀር የሚረዳ ፈር ቀዳጅ ሥራ ፍኖተ ካርታ ሆኖ የሚያገለግል ነው::


በአገራችን እንደዚህ አይነት የንግድም ይሁን የትኛውም ዘርፎች 

ውስብስብ የሆኑ የአስተዳደር ሂደቶችን የሚጠይቁ ከሆኑ ከስኬታማነታቸው 

ይልቅ በጅምር ሲቀሩ ለከፋ ኪሳራ 

እና ለግለሰባዊ ለአካባቢያዊ 

ምስቅልቅሎች 

ስንዳረግ በተደጋጋሚ የምናስተውለው ሐቅ ሆኗል:: 


ፕሮጄክት አፈፃፀም ላይ የሚስተዋለው 

ክሽፈታችን የትኛውንም የሙያ ዘርፍ 

በቂ ልምድ ክትትል እና ሙያተኞችን 

የማያሳትፍ የስራ ቅንጅት አለመኖሩን 

የሪል እስቴት መፅሐፍ በሚገባ ያሳየናል:: 


የመሬት አቅርቦቱ  የቀረጥ ነፃ ማበረታቻ  

መንግስት ከግለሰቦች ጋር በጋራ ቢሰራ በሚል የተቀመጡት ምክረ ሀሳቦች 

ፀሐፊው በሙያው ያካበተውን 

የቆዬ የስራ ልምድ ታሳቢ የሚያደርግ ጥቆማዎች አሉት:: ገፅ 190/191


<< አብዛኞቹ የሪል እስቴት ፕሮጄክት አልሚዎች የግንባታ ሥራ 

የሚያከናውኑት እንደ ሪል እስቴት 

አልሚ ባለሀብት ተመዝግበው  

የሪል እስቴት ንግድ ፈቃድ ኖሯቸው 

ሳይሆን የሕንጻው ግንባታ ፈቃድ ብቻ 

አውጥተው ግንባታ የሚያከናውኑ በመሆናቸው ነው::


አብዛኞቹ  የሪል እስቴት አልሚዎች ወደ ሪል እስቴት ሥራ ምዝገባ የሚገቡት  

የመጠቀሚያ ፈቃድ አውጥተው 

ለማከራዬት ወይም ለመሸጥ 

በሚያስቡበት ወቅት ነው>> 

ገፅ 163 ::


ይህ አካሄድ ለጥናት ምቹ አለመሆኑን እና ዘርፉን በሙያዊ እይታ የተለያዬ ተጨማሪ 

ችግሮችን ማስተናገዱን ይጠቅሳል:: 


በአጠቃላይ መፅሐፉን በዘርፉ ሊሰማሩ ላሰቡ ድርጅቶች "አጤሪራ" ቋሚ ማስታወሻም ተይዞለት የሚነበብ ነው:: 


የእውቀት እና ክህሎት ልምምድን 

በቅድሚያ ታሳቢ በማድረግ 

የንግድ ባህላችንን ጥናታዊ 

ሂደትን የሚያበረታታ 

ወቅቱን የጠበቀ በብዙዎች 

የአገራችን ክፍል

ለውይይት ቀርቦ እገዛውን በተጨባጭ ሊያረጋግጥ የሚገባው ነው:: 


የመፅሐፉ አላማ የሪል እስቴት ዘርፍ በነዋሪው ሊገዙ የሚችሉ  (Afordalbe houses) 

እንዲበራከቱ የሚጥር 

በመሆኑ ምናልባትም ፀሐፊው 

በተካነበት ሥልት ለቀጣይ ተያያዥ 

ሥልጠናዎችን

ለመስጠት የተዘጋጄበት ትጋት በድጋሚ የሚያስመሰግነው ነው:: 





በፕሪፋብ (ተገጣጣሚ የቤት አይነቶች

ላይ የደረሰውን የተጣደፈ ውድቀት እና 

በተለይ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የሚታወቀውን 

የእክሰስ ሪል እስቴት ድርጅት 

አጠቃላይ ሂደት በምሳሌነት 

በማስቀመጥ የፕሮጄክት 

አፈፃፀሙን ውስጣዊ እና ውጫዊ 

ዝርዝር ሂደቱን ከመፅሐፉ በግሌ 

ጠብቄ ያጣሁት ክፍል ቢሆንም 


ለንባብ ምቹ ሆኖ ቀለል ባለ አማርኛ 

መቀመጡ ብቻ ሳይሆን 

በዝግታ የተሰናዳ የቃላት ህፀፆች ከሞላ ጎደል የማይታዩበት 

(የሚያስፈሎገውን ገፅ 39) አይነት 

የተልባ ፍንጣሪ ጥቃቅን ስህተቶች 

ከማውጣት ውጭ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን 

የሚያበረታታ አርዐያ ሊሆን 

የሚገባው እንደ 'ማንዋል'  ሆኖ የሚያገለግል ሥራ ነው:: 


በየቢሮአችን መፅሐፍ መደርደርያ ልናጣው የማይገባ አገልጋይ መፅሐፍ::  <<ሪስ እስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ግብይት>>


ተስፋ በላይነህ 

የካቲት 2013 - ኢትዮጵያ!


May 20, 2018

የዶክተር አማረ ኃይሌ ፊዳ



ኃይሌ ፊዳን እንዳየሁት…
Portrait_of_HAILE_FIDA

በ60ዎቹ ትውልድ ውስጥ፤ የፖለቲካውን ቅመማ ሲያቀናብሩ ከነበሩ ተቀዳሚ ተዋንያን፤ ኃይሌ ፊዳ  ቀዳሚው ነው፡፡ ልጅ ሆኜ “ፊዲስት!” ሲባል እስማ ነበር፡፡ ምን አንደሆነ ስጠይቅ ተገቢውን መልስ ማግኜት አልቻልኩም፡፡
ከጊዜ በኋላ የኃይሌ ፊዳ ምስከርነትን ሳነብ እና ሥለ ግለሰቡ የሩቅ አሳቢነት ተክለ ስብእና በኣጫጭር ጽሑፎች ስመለከት፤ የዚያን ትውልድ ታሪክ ለማወቅ በብርቱ መፈለግ የነበረብኝ የዚህን ግለሰብ ማንነት ማወቅ ነበር፡፡ የአንዳርጋቸው አስግድን “ባጭር የተቀጨ…”ን እና አልፎ አልፎ የሚወጡ ጽሑፎችንም ለማዬት ሞክሬያለሁ፡፡

በመጠኑም ቢሆን የማነባቸው ጽሑፎች ኃይሌ ፊዳን የኦሮሞ ብሔረተኛ አንቃኝ አድርጎ የመሳል አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ “በእርግጥ ይሕ ሰው ብሔረተኛ ነበር ወይ?” የሚለው ጥያቄም የግለሰቡን ማንነት ለማወቅ ገፊ ምክንያት ከሆኑልኝ ዝርዝሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡
ዶ/ር አማረ ተግባሩ “ኃይሌ ፊዳ እና የግል ትዝታዬ” በሚል አርእስት የተለቀቀውን የመጽሐፍ ገጽ ሽፋን ስመለከት በዚህ ክረምት ከማነባቸው መጽሐፍት ውስጥ ዋናው እንደሚሆን እና ጀምሬውም በጥልቀት ማንበብ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

የመጽሐፍ ሽፋኑን በማሕበራዊ ድረገጽ ተለቅቆ ስምለከት ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡ ሰዎችንም ከማዬት ባሻገር ቀልቤን የሳበው የፊት ገጽ ላይ በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የተቀመጠው መከረኛው የኦሮሚያ ግዛት ድምቀት ነበር፡፡

በግሌ ከነበረው የኃይሌ ፊዳን ከኦሮሞ ብሄረተኛነት አስተሳሰብ ጋር የማያያዙ ጉዳይ ምናልባትም መልስ ያገኛል በሚል መጽሐፉን ቶሎ በመግዛት ንባቤን ጀምርኩ፡፡ በእርግጥ መጽሐፉን አንዴ ከጀመሩት አለማቋረጥ የሚከብድ መሆኑን መጠቀስ ተገቢ ነው፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር አማረ ተግባሩ ከዚህ ስራ ውጭ “ያንዲት ምድር ልጆች” የተሰኘ ረዥም ድርሳን እንዳዘጋጁ በበይነ መረብ ውስጥ ያገኘሁት መረጃ ይመሰክራል፡፡

“ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” መጽሐፍ 236 ገጾችን ይዞ ከኃይሌ ፊዳ ማነው እስከ ለመሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ምን ይላሉ? የሚሉ አጠቃላይ 20 ንዑስ አርእስቶች አሳጥሮ በቀላል መልኩ የቀረበ ስራ ነው፡፡

“እውነት ኃይሌ ፊዳ ብሔረተኛ አስተሳሰብ የነበረው `ኦሮሞ ፈርስት` ልሳን አቀንቃኝ ምሁር ነበርን?” የሚለውን ጥያቄ ከጅምሩ የሚያፈርሱ ምልከታዎችን ማገኜት በመቻሌ እስከ ገጽ መጨረሻው ድረስ ይህንን መልስ ለማግኜት በጥረት ማንበቤን አልክድም፡፡ በቁቤ ጉዳይም የጠበበ ሳይሆን ሰፋ ያለ ምልክታ እንደነበረው (የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛ ቋንቋ ልሳንን መግለጽ ከቻለ መቀበል እንደሚችል በመግለጹ) መመልከት እንችላለን፡፡
ብሔረተኛ አቀንቃኝ አለመሆኑን በገጽ 7 ላይ ብሔረተኛነትና ጠባብ ብሔረተኝነት ሊያስከትል ከሚችለው መዘዝ ጋር አያይዞ የኤርትራ ጉዳይን ጨምሮ የአካባቢውን ቅኝት የተመለከተበት መንገድ ኃይሌ ፊዳን በይበልጥ እንዳውቀው እና እንድፈልገው ያደረገም መጽሐፍ ነበር፡፡

ኃይሌ ፊዳ ዓለም አቀፋዊ አመለካት የነበረው እና ኩሩ የሆነው ያገር ፍቅር ስሜት ከራስ የመተማመን መንፈስን የተላበስ ስብዕና ባለቤት እንደነበር ከመጽሐፉ ለመቃኔት ችያለሁ፡፡ ታድያ ለምንድን ነው በኢትዮጵያ ካርታ  ውስጥ የኦሮሚያን ግዛት አጽንኦት ውስጥ ማስገባት የተፈለገው? ታስቦበት ነው? አልገባምኝም!!

ይሕ በኃይሌ ፊዳ ስብእና ላይ ሌላ አቅጣጫን መቀየስ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለመጭው ትውልድም ሌላ የቤት ስራን የሚጭር ጉዳይ መሆኑን ሳልገልጽ ማለፍ አይቻለኝም፡፡ የሽፋን ገጹ በዚህ መልክ ለምን እንደቀረበም ትልቅ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም የኃይሌ ፊዳን ትውልድ ስፍራ ጠቅሶ ኃይሌ ፊዳን ወደ አለም አቀፋዊ አመለካከት ባለቤትነቱን ለማሳዬት ቢሆን አጋሮን እና ወለጋን ማቅለሙ ከበቂ በላይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ የትዝታ አተራረክ እና ጸሐፊው እያጣቀሰ የሚነግረንን ማስረጃዎች እውነታነት በጊዜው የነበሩ ግለሰቦች በተለያዬ ጊዜ ተገናኝተው ሲጠይቃቸው የእነርሱ ተጨማሪ ምስክርነት ጋር ስሙሙነት መፍጠሩን በማመሳከር ነው፡፡

የአንዳርጋቸው አሰግድ ባጭር የተቀጨ… የፕ/ር ሽብሩ ከጉሬዛ ማርያም እስከ  አዲስ አበባ እና መሰል መጽሐፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እስከ ካቶሊክ ቄስ፤ በጊዜው የነበሩ በቤተ ዝምድና እና ማሕበራዊ ሕይወት ግንኙነት ያላቸው በርካታ ገለሳቦች በስም እየተጠቀሱ የደራሲውን ማሰረጃ እንደ ማመሳከረያ እንዲረዱት ጠቅመውታል፡፡

ደራሲው ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ያልተወራረደ ጉዳይ እንዳላቸው መመልከት እንችላለን፡፡ የኮሎኔሉን ተክለ ስብእና በኃይሌ ፊዳ በኩል የሚያገኛቸውን ጥቆማዎች በመውሰድ፤ ኮሎኔሉ ጫማቸውን ሊፈቱላቸው ሲሽቀዳደሙ የነበሩ አንጋቾችን ጨምሮ በያ ትውልድ የነበረውን የፖለቲካ እና ማሕበራዊ ድባብ ለማስቃኜት የበኩሉን የተወጣ ስራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በየዝርዝር ሐሳቦችም የመኢሶንን መዳረሻ ሐሳብ አሁን ስገነዘበው ትክክል እንዳልነበረ በማለትም ሚዛናዊ ሊባል በሚል መልኩ ራሱን ከሕሊና እዳ እና ጠባሳ ሕመም ለመፈወስ የተጋ ስራ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ 

አሁንም ብዙ እንደሚቀረን ግን አልዘነጋውም!

መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ አዕምሮዬ ጋር የተዳመረው አስተሳሰብ ቢኖር ኢትዮጵያ እንዲህ በፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ እና ማንነት ቀውስ ውስጥ ከገባችባቸው ቀዳሚ ምክንያቶች ውስጥ ኃይሌ ፊዳን የመሰሉ ግለሰቦችን በየወቅቱ መግደላችን ነው ወደሚለው ድምዳሜ እንድደርስ ተጨማሪ ግብኣት ሆኖልኛል፡፡

አሁንም ቢሆን መስል ግለሰቦችን በማወቅ እና በማሳወቅ ደረጃ የሚሳተፉ ግልሰቦችን እንዲያበረታልን በመጸለይ፤ አሁንም ቢሆን ተወራርዶ ያልተቋጨው የያ ትውልድ የፖለቲካ ግብግብ ለአሁኗ እና ለመጭዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ አምድ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ ዶ/ር አማረን እያመሰገንን በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን መርምሮ ወደ መፍትኄ ሐሳብ መድረስ የሁላችንም የቤት ስራ እንደሚሆን ሁልጊዜም በማሳሰብ ዶከተሩን አጅ እየነሳሁ አጭር ምልክታዬን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡

ከመጽሐፉ ምን ጎደልብሀ ብትሉኝ ምናልባት በየገጹ ተራርቀው የሚታዩቱን አራት ነጠቦች ማጠጋጋት ቢቻል፡፡ አራት ነጠቦች ሲበዙ አጠር መጠን ያሉ ሐሳቦች ቀርበው ተደራሲውን ያለማሰላቸት እና ሐሳቡን ያለመስረቅ እድል ፈንታን ይቸሩታል፡፡

(ተስፋ በላይነህ ግንቦት 2010 ዓ.ም)