በ60ዎቹ
ትውልድ ውስጥ፤ የፖለቲካውን ቅመማ ሲያቀናብሩ ከነበሩ ተቀዳሚ ተዋንያን፤ ኃይሌ ፊዳ ቀዳሚው ነው፡፡ ልጅ ሆኜ “ፊዲስት!”
ሲባል እስማ ነበር፡፡ ምን አንደሆነ ስጠይቅ ተገቢውን መልስ ማግኜት አልቻልኩም፡፡
ከጊዜ
በኋላ የኃይሌ ፊዳ ምስከርነትን ሳነብ እና ሥለ ግለሰቡ የሩቅ አሳቢነት ተክለ ስብእና በኣጫጭር ጽሑፎች ስመለከት፤ የዚያን ትውልድ
ታሪክ ለማወቅ በብርቱ መፈለግ የነበረብኝ የዚህን ግለሰብ ማንነት ማወቅ ነበር፡፡ የአንዳርጋቸው አስግድን “ባጭር የተቀጨ…”ን እና አልፎ አልፎ የሚወጡ ጽሑፎችንም ለማዬት
ሞክሬያለሁ፡፡
በመጠኑም
ቢሆን የማነባቸው ጽሑፎች ኃይሌ ፊዳን የኦሮሞ ብሔረተኛ አንቃኝ አድርጎ የመሳል አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ “በእርግጥ ይሕ ሰው ብሔረተኛ
ነበር ወይ?” የሚለው ጥያቄም የግለሰቡን ማንነት ለማወቅ ገፊ ምክንያት ከሆኑልኝ ዝርዝሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡
ዶ/ር
አማረ ተግባሩ “ኃይሌ ፊዳ እና የግል ትዝታዬ” በሚል አርእስት የተለቀቀውን የመጽሐፍ ገጽ ሽፋን ስመለከት በዚህ ክረምት ከማነባቸው
መጽሐፍት ውስጥ ዋናው እንደሚሆን እና ጀምሬውም በጥልቀት ማንበብ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡
የመጽሐፍ
ሽፋኑን በማሕበራዊ ድረገጽ ተለቅቆ ስምለከት ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡ ሰዎችንም ከማዬት ባሻገር ቀልቤን የሳበው የፊት ገጽ ላይ
በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የተቀመጠው መከረኛው የኦሮሚያ ግዛት ድምቀት ነበር፡፡
በግሌ
ከነበረው የኃይሌ ፊዳን ከኦሮሞ ብሄረተኛነት አስተሳሰብ ጋር የማያያዙ ጉዳይ ምናልባትም መልስ ያገኛል በሚል መጽሐፉን ቶሎ በመግዛት
ንባቤን ጀምርኩ፡፡ በእርግጥ መጽሐፉን አንዴ ከጀመሩት አለማቋረጥ የሚከብድ መሆኑን መጠቀስ ተገቢ ነው፡፡
የመጽሐፉ
ደራሲ ዶክተር አማረ ተግባሩ ከዚህ ስራ ውጭ “ያንዲት ምድር ልጆች”
የተሰኘ ረዥም ድርሳን እንዳዘጋጁ በበይነ መረብ ውስጥ ያገኘሁት መረጃ ይመሰክራል፡፡
“ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” መጽሐፍ 236 ገጾችን ይዞ ከኃይሌ
ፊዳ ማነው እስከ ለመሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ምን ይላሉ?
የሚሉ አጠቃላይ 20 ንዑስ አርእስቶች አሳጥሮ በቀላል መልኩ የቀረበ ስራ ነው፡፡
“እውነት
ኃይሌ ፊዳ ብሔረተኛ አስተሳሰብ የነበረው `ኦሮሞ ፈርስት` ልሳን አቀንቃኝ ምሁር ነበርን?” የሚለውን ጥያቄ ከጅምሩ የሚያፈርሱ
ምልከታዎችን ማገኜት በመቻሌ እስከ ገጽ መጨረሻው ድረስ ይህንን መልስ ለማግኜት በጥረት ማንበቤን አልክድም፡፡ በቁቤ ጉዳይም የጠበበ
ሳይሆን ሰፋ ያለ ምልክታ እንደነበረው (የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛ ቋንቋ ልሳንን መግለጽ ከቻለ መቀበል እንደሚችል በመግለጹ) መመልከት
እንችላለን፡፡
ብሔረተኛ
አቀንቃኝ አለመሆኑን በገጽ 7 ላይ ብሔረተኛነትና ጠባብ ብሔረተኝነት ሊያስከትል ከሚችለው መዘዝ ጋር አያይዞ የኤርትራ ጉዳይን ጨምሮ የአካባቢውን ቅኝት የተመለከተበት መንገድ ኃይሌ ፊዳን በይበልጥ እንዳውቀው እና እንድፈልገው
ያደረገም መጽሐፍ ነበር፡፡
ኃይሌ ፊዳ ዓለም አቀፋዊ አመለካት
የነበረው እና ኩሩ የሆነው ያገር ፍቅር ስሜት ከራስ የመተማመን መንፈስን የተላበስ ስብዕና ባለቤት እንደነበር ከመጽሐፉ ለመቃኔት
ችያለሁ፡፡ ታድያ ለምንድን ነው በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የኦሮሚያን
ግዛት አጽንኦት ውስጥ ማስገባት የተፈለገው? ታስቦበት ነው? አልገባምኝም!!
ይሕ በኃይሌ ፊዳ ስብእና ላይ
ሌላ አቅጣጫን መቀየስ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለመጭው ትውልድም ሌላ የቤት ስራን የሚጭር ጉዳይ መሆኑን ሳልገልጽ ማለፍ አይቻለኝም፡፡
የሽፋን ገጹ በዚህ መልክ ለምን እንደቀረበም ትልቅ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም የኃይሌ ፊዳን ትውልድ ስፍራ
ጠቅሶ ኃይሌ ፊዳን ወደ አለም አቀፋዊ አመለካከት ባለቤትነቱን ለማሳዬት ቢሆን አጋሮን እና ወለጋን ማቅለሙ ከበቂ በላይ ነው ብዬ
አስባለሁ፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ የትዝታ አተራረክ
እና ጸሐፊው እያጣቀሰ የሚነግረንን ማስረጃዎች እውነታነት በጊዜው የነበሩ ግለሰቦች በተለያዬ ጊዜ ተገናኝተው ሲጠይቃቸው የእነርሱ
ተጨማሪ ምስክርነት ጋር ስሙሙነት መፍጠሩን በማመሳከር ነው፡፡
የአንዳርጋቸው አሰግድ ባጭር የተቀጨ… የፕ/ር ሽብሩ ከጉሬዛ ማርያም እስከ አዲስ አበባ እና መሰል
መጽሐፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እስከ ካቶሊክ ቄስ፤ በጊዜው የነበሩ በቤተ ዝምድና
እና ማሕበራዊ ሕይወት ግንኙነት ያላቸው በርካታ ገለሳቦች በስም እየተጠቀሱ የደራሲውን ማሰረጃ እንደ ማመሳከረያ እንዲረዱት ጠቅመውታል፡፡
ደራሲው ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም
ጋር ያልተወራረደ ጉዳይ እንዳላቸው መመልከት እንችላለን፡፡ የኮሎኔሉን ተክለ ስብእና በኃይሌ ፊዳ በኩል የሚያገኛቸውን ጥቆማዎች
በመውሰድ፤ ኮሎኔሉ ጫማቸውን ሊፈቱላቸው ሲሽቀዳደሙ የነበሩ አንጋቾችን ጨምሮ በያ ትውልድ የነበረውን የፖለቲካ እና ማሕበራዊ ድባብ
ለማስቃኜት የበኩሉን የተወጣ ስራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በየዝርዝር ሐሳቦችም የመኢሶንን
መዳረሻ ሐሳብ አሁን ስገነዘበው ትክክል እንዳልነበረ በማለትም ሚዛናዊ ሊባል በሚል መልኩ ራሱን ከሕሊና እዳ እና ጠባሳ ሕመም ለመፈወስ
የተጋ ስራ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
አሁንም ብዙ እንደሚቀረን ግን አልዘነጋውም!
መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ አዕምሮዬ
ጋር የተዳመረው አስተሳሰብ ቢኖር ኢትዮጵያ እንዲህ በፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ እና ማንነት ቀውስ ውስጥ ከገባችባቸው ቀዳሚ ምክንያቶች
ውስጥ ኃይሌ ፊዳን የመሰሉ ግለሰቦችን በየወቅቱ መግደላችን ነው ወደሚለው ድምዳሜ እንድደርስ ተጨማሪ ግብኣት ሆኖልኛል፡፡
አሁንም ቢሆን መስል ግለሰቦችን
በማወቅ እና በማሳወቅ ደረጃ የሚሳተፉ ግልሰቦችን እንዲያበረታልን በመጸለይ፤ አሁንም ቢሆን ተወራርዶ ያልተቋጨው የያ ትውልድ የፖለቲካ
ግብግብ ለአሁኗ እና ለመጭዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ አምድ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ ዶ/ር አማረን እያመሰገንን በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉ
መጽሐፍትን መርምሮ ወደ መፍትኄ ሐሳብ መድረስ የሁላችንም የቤት ስራ እንደሚሆን ሁልጊዜም በማሳሰብ ዶከተሩን አጅ እየነሳሁ አጭር
ምልክታዬን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡
ከመጽሐፉ ምን ጎደልብሀ ብትሉኝ
ምናልባት በየገጹ ተራርቀው የሚታዩቱን አራት ነጠቦች ማጠጋጋት ቢቻል፡፡ አራት ነጠቦች ሲበዙ አጠር መጠን ያሉ ሐሳቦች ቀርበው ተደራሲውን
ያለማሰላቸት እና ሐሳቡን ያለመስረቅ እድል ፈንታን ይቸሩታል፡፡
(ተስፋ በላይነህ ግንቦት
2010 ዓ.ም)
No comments:
Post a Comment