Feb 22, 2013

ግጥሞች







የክርስቶስ ቀለም
ባዶ ነው ይሉታል
የሞላውን ክፍል
የኛ ነው ይሉታል
የአለሙን ቁስል…
          ጥቁር  ቢጫ ነጭ ነው
       ክርስቶስ ሲሰቀል?
እያሉ ሲያሟሹ
ሙሾ ሲያሞካሹ
ያልገባቸው ሞቱ ክርክር ሲያበጁ
በደም ሳለላቸው ደሙን እንዲዋጁ!
ለሠዓሊ ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ 




የታከተኝ እረኛ
ክልክል ባይኾን መኖር
ህግ ባኖር ለአገር
መቀመጥ መራመድ በመሬት ስበት ስር
የትራፊክ መብራት ባይሰራ ባይበራ
መኪኖች ሲፋጩ ሲጋጩ በተራ
አገር ኹሉ ቢጨስ
በፉጨት ቢታመስ
ቢታራ ቢሸና መንገዱ ቢገማስ;
ህግ ባይኖር ባገር
ስበት ባይኖር በ፣ግር
የመሬት ምስቅልቅል
የፀሀይ መሽከርከር
ክልክል ባይኖር ቀመር
ህግ ባይኖር በምድር
አንተን ስከለክል አንተን ስቆጣጠር…
ለክልክል ነው ግብረ መልስ በዕውቀቱ ስዩም ስብስብ ግጥሞች ገጽ 99 2001 ዓ.ም




አበባ-ቢራቢሮና-ሰው

ስንቴ ተመኘች ልቤ አበባ መኾንን
ስንት ጊዜ ከጀልለች ነፍሴ- መምሰል ቢራቢሮን
መሬት ተተክዬ ስመስል አበባን
ያሻው እንዲስመኝ ሁሉም እንዲያርፍብኝ
የከዳኝን እንኳ እንዳልከተለው
እንዳልደክም ብሎ ስሬን አረዘመው…
ቢራቢሮም ሆኜ ስበር ስስም ሁሌ
በስንቱ ተረገምኩ
በስንቱ ተለከፍኩ መብረር መባተሌ…
ሰው አርጎ ፈጥሮኛል
ሲያሻኝ እንደመብረር
ሲያሻኝ እርፍ እንድል
ሰው አርጎ ፈጥሮኃል
ተመስገን አሜን በል!
ለ‹‹ሐተታ ቢራቢሮ›› ግብረ መልስ በዕውቀቱ ስዩም ስብስብ ግጥሞች ገጽ88 2001ዓ.ም




አጤ ቴዎድሮስ ለ ጠጋዬ
ምንና ተማረ ቅኔውም ያማረ
ከየትኛው መንደር ፊደል የቆጠረ
ቃሉ የተዋበ
ለነፍስ የቀረበ
ማህሌት የቆመ ውዳሴው የተጋ ወረብ የወረበ
ከየት ነው የቀዳው ጥበብ ተጠበበ፡፡
በዛን ጊዜ  ቁስል በዛች  ህመም ሰዓት
ተስፋ ባጣ ምድ-ረበዳ
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት;
ብለህ ያቀረብከው ለዛች ክፉ ሰዓት
የት ብለህ  የት ቆመህ የት ሆነህ አየሃት
የልቤን ፍቅር በስተቀር የማውሰስሽም ውል የለኝ
የኮሶ ሻጭ ልጅ ድሓ ነኝ
ደሞም ያላንቺ የለ ዳኛ
ድሌም የተስፋው ጎህ ባይሆን ከሞት ጋር ትግል ነውና፡፡
ብለህ የቀመስከው በዛች ክፉ ሰዓት
የት ብለህ የት ቆመህ የት ሆነህ ሰማሃት;
ህምሜን ታመህ እንጂ ቁስሌን ቆስለህ እንጂ ያስታመምካት!
ልማዴ ሆኖ ኮሶ መራር ሃሞት ብጋትም
ያኔም ጠጣሁ እንጂ የጥይቱን ቅመም
አልመሸም ጠጋዬ አይዞህ አልረፈደም፡፡
አንቃው ትውልድህን በብራና ቀለም
አይዞህ ጠጋዬ ስራህ ሕያው ነው አይጠፋም
            አንፃው ወገንህን በጥበብ ዘላለም፡፡
አልመሸም ኢትዮጵያ አይዞሽ አልረፈደም
ታሪክሽ ህያው ነው ቢነገር ለዛሬም
ልጆችሽ ይነሱ ባንድነት ከአለም፡፡
አልመሸም ጠጋዬ አይዞህ አልረፈደም
ይህን ትውልድ አንቃው ይህን ወገን አጥባው
ይህን ሰማይ ያጽዳው ይህን ጭጋግ ያጥራው፡፡
ቀለምህ ህሩይ ነው- ምጥቀትህ ጠሊቅ ነው!
ይህን ትውልድ አንቃው ይህን ሰማይ ያጥራው፡፡

እንግዲህ የአንዱን ሰው ህመም፣ ሰቆቃ፣ ደስታና ሃሴት መታመም መሰቅየት መደሰት የሚቻለው ያንዱ ሞት ለሌላው ሞት ያንዱ ሰቆቃ ላንዱ ስቃይ ደስታው ሲሰማው አንድ አላማና መንፈስ ሲኖራቸው ነው፡፡ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የአጼ ቴዎድሮስን የመጨረሻ ሰዓት የዘገበው በወቅቱ ኖሮ ሳይሆን የአጼውን ሞት ሞቶት ነው፡፡ የአቡነ ጴጥሮስን  ሰቆቃ የዘገበው ስቃያቸው ተሰምቶት በአንድ ስሜት ሆኖ ነው፡፡ እኛም ለዚህች አገር የተሰውትን፣ የተጋደሉትን የታፈሉለትን አላማ ካልተቀበልነው ስሜቱ ካልተሰማን ፈጽሞ ሊገባን አይችልም፡፡ የዚህች አገር ህመም የዚህች አገር ስቃይ ክሽፈት የሁላችን ነው፡፡




እርሜን ብጽፍ ዛሬ
ምንድን ነው መርበትበት
ለምንስ መወትወት
አርፈህ ቁጭ አትል-ልጻፍ ብሎ መዝመት?
የምን በዕር ማጦር
የምን ሃሳብ ማሾር?
አርፈህ ዝም አትልም-አጉል ከመሞንጨር?
በሌሊት ተነስተህ
ወረቀት ፈልገህ
ብራና ደጉሰህ
ብዕር አለሳልሰህ
ግጥም ለመሞንጨር
ፅሑፍ ለማዥጎርጎር
እንደው ‹‹ሸም›› የልህም…
የምን ታሪክ ማሰብ
የምን መዝሙር ማንበብ
ቅኔ መዝረፍ ማቅረብ
እንደው እርም አትልም
ነውርስ አታውቅም
ከከበቶቹ መሃል ጠባቂው ወንድሜ
ልግጠም ብትል ኣንዴ ላንብብ ብትል ቆሜ
እረኛ ወግ እንጅ መች ቁምነገር ሰሚ?
ፍየሎች ፈረሶች በጎቹ ተኝተው
የምን ግጥም ማነበብ የምን መፎከር ነው?
እርሜን ብጽፍ ዛሬ
አምጨ ሰብስቤ ለቃቅሜ ጥሬ
ከብቶቹ ዘመቱ
ፈረሶች ሸፈቱ
ፍዬሎችም ሞቱ
በጎቹ ታገቱ…
እርሜን ብጽፍ ዛሬ
ከረኝነት ውሎ ስራም ተባርሬ
ቀረሁ ተበግሬ…!
ሌላ ከብት ልፈልግ ፈሌጌ ላደልብ
ሌላ በበግ ላሳድግ ፈረስም ላጠግብ
ሌላ ፍየል ቅጠል ልላ ወንዝ ልገድብ…!
እርሜን ብጽፍ ዛሬ
እንዳይለምደኝ ግጥም እንዳይለምደኝ ወሬ
ከረኝነት አለም ከጥበቃው ፍቅሬ
ተባረርኩ ከመንደር ላልመለስ ዞሬ
እርሜን ብጽፍ ዛሬ…



ከውበት ፍካት ጥፋት
ምን ጠይቀህ ነበር በህይወትህ ዘመን
ምን ጀምረህ ነበር ባ’ራቱ ማዕዘን
በነዚያ ጊዜያት አስደሳች የበጋ በጸዳው ሰማይህ
በመከራው ጉዞ በክረምት ልፋትህ…?
ምን ፈልጋ መታች የልብህ መሻት
ምን  ተግታ ሰረጻት በነፍስ መ-ቃተት…
በህልምህ በ’ውንህ የወደፊት ምኞት
በነዚያ ቀን መዓልት
ባማሩ ባበቡ በጨቅላነት ወራት
ጉልበትህ ሮጦ
አእምሮህ ተገልጦ
ለመልስ ሲንከራተት
ምን አገኘህ ዛሬ ምን ፈለህስ ትናንት?
የጠበክ’ው ቀመር ምን ሰጠህ ስሌቱ
የበተንከው ሃሳብ ምን ሆነ ልኬቱ…?
ጥበብንስ ሽተህ መንፈስህን ክደህ
ከጥልቁ ውቅያኖስ ካ’ውድማው ሸምተህ
ወንዙን ተከትለህ ከሐይቁ ተኝተህ
ምን አተረፍክ ያኔ… ምን ጨበጥክ ዋ!ኝተህ…
ምድር እንደው ግዙፍ ህይወት እንደው ወረት
ጠፈር እንደው ሰፊ ፍቅር ቢሆን ዘበት
ህይወት ያለ ለከት-ፍቅር ያለ ጽናት
ጉዞ ያለመድረስ እውቀት ያለ እውነት…
ምን ጠንክረህ ታገል’ክ በጉብዝናህ ወራት
ምን አድነህ ገደልክ በዝናህ ኩንትራት (ዝና ኩንትራት ነው)
ምንስ ፈትለህ ቋጨህ በጊዜ ሰዓታት
ጥቋቁር ጸጉሮችህ ሲተቡ በሽበት
ነጫጮቹ ጥርሶች ጠቆሩ ከቅጽበት
የፈካው ፊትሽም ሲደበዝዝ ድንገት
ዋላ መሳይ ጡቶች ሲጠጉ ወደ’ንብርት
የታገለው ጡንቻ የገደለው አጥንት
የሟሸሸው ቆዳ ሲጎብጥ ያ! ሰውነት…
በጊዜ ተዋረድ በዘመን ትሩፋት
ምን እያየሽ መጣሽ በጸዳልሽ ፍካት
ምን ተምረሽ ቆዬሽ በውበትሽ ጥፋት
ምን አትርፈህ አለፍክ በተጓዝከው ት-ላንት?
ተጣፈ በትናንት
የሚንከራተቱ ከዋክብት፡፡



ላኦ ቢረ*ን ሰም-
ኦላ ረቢ ብለህ ገጠምክ ተባለ አሉ
ከጫንቃዬ ውረድ በቃኝ አልክም አሉ
ይስማህ አሜን ብለህ ጠንክረህ በቃሉ
ሸምተህ አትርፈህ እድሜህን በሙሉ..
ሁሉን ያዬህ መስሎህ ዝነኛ መባሉ..
               ያ’ንስታይ ተወካይ
የጲላጦስ ወገብ-የሌጊዮን ደዋይ
  የማሳሳት ቀመር-የሐሰት ተጋዳይ                
የተጣለው ኮከብ-የክደት ተከታይ
በምን እንወቅህ-የጥበብ ወላዋይ?
ለምነሽ ለምነሽ ስትኖሪ ስታታ
ሲጠፋሽ መንገዱ ስታጪ ገላጋይ
ወይ ያዙኝ ልቀቁኝ ሳይገድሉ ነኝ ገዳይ…
እሱ ንደው ከሃሊ ሁሉን ታጋሽ ከላይ
ምንም አያልቅበት
ምኑም አይጎድልበት
አንተ ብን አባይ*
 ይከብራል ይነግሳል በምድር በሰማይ..!
ድንቄም አባራሪ -10 አባራሪ
ሁሉን እይዛለሁ-ሁሉን አውቃለሁ ባይ
ተመለስ! ተመለስ! አንዱን ይዘህ አሳይ፡-
ህዝቤም ስታዳምጥ ሰሙን ከወርቅ ለይ!
እጅግ በጣም የተሳሉ ልኂቃን እየመጡብን ነው፡፡ የማርያም መቀነት ይላሉ- ፍጡርን በፈጣሪ ያመሳስላሉ…ኦላ ረቢ ረቡኒ(መምህርን) ይሰናበታሉ፤ ቃሉን ደግሞ ይጠቅሳሉ ሃይሉን ግን ይክዳሉ! እባካችሁ አንዱን ያዙና እንለያችሁ በመሐል ቤት አላዋቂ አበዛችሁ…
*ላኦ ቢረ- ኦላ ረቢ
                                          *አባይ (ወንዙና ሚዛኑ) - አባይ ወንዝ፤ አባይ ሚዛን፡፡

የክሽፈቶች ክሽፈት
ክሽፈት…
ገንዘብ ሲኾን ጌታ
ጌታ ሲኾን ገዥ
ገዥም ሲኾን ጨቋኝ
ክሽፈት…
ትዳር ሲሆን ግዞት
ግዞት ሲኾን ምሬት
ምሬት ሲሄድ ስርቆት
ክሽፈት…
ጎሳ ሲሆን ዋና
የሰው ልጅ ፈተና
ጠባብ ሲሆን ሃሳብ
ሃሳብ ሲኾን ሰበብ
የሰው ዘር ሲጠና
ትውልድ ሲያጣ መና
ህይወት ሲያጣ ቃና
በችጋር በስቃይ መሬት ስትኾን ኦና
ፍቅር ሲቀር መና…
ክሽፈት…!
አንዱ ሲንፈላሰስ
በሊሞዚን ዝና
በካዲላክ ወገን በፖርሹ ሲዝናና
ሌላው በባዶግሩ ለከርሱ ሲናና
ልዩነት ሲሰፋ-በህዝብ ሃብት-በወንጀል ሲነግስ በሙስና
የክሽፈቶች ዋና…!

ክሽፈት ማለት ግዞት
በመንፈስ ልቦና በህሊና መሞት፡፡
መታሰር በደዌ መተብተብ በጠኔ
እጅ እግር ተይዞ ማጣት ትግል -ወኔ፡፡
ክሽፈት መዋዠቅ ነው መንደርደር ቁልቁለት
እንዳይመለሱት ልጓም አትቶ መቅረት…
አለመማር ክሽፈት ከኖርንባት ትላንት
እድገት አለየማት ታሪክ ሲሆን ተረት
                  -ተረት ሲሆን ቅዠት፡፡
ክሽፈት ክሽፈት ክሽፈት…
በቀደመው ግዛት ሲታጣ ነጻነት
በጎሳ በድንበር ሲበዛ ጦርነት
ያያቶችህ አለት ሲናጋ መሰረት
ያባቶችህ መንገድ ሲደገም ስህተት
        የነገ ማንነት ራዕይህ ሲሞት
የማክሸፊያው ቁልፉ ጠፍቶብን መዋትት፡፡
የክሽፈቶች ክሽፈት፡-
                           ትላንት-ዛሬ-ነገ መንደርደረ ቁልቁለት
                         ነገ-ትላንት-ዛሬ መሸከም ያን ዳገት!




የስኬቶች ስኬት
በታሪክ በወኔ አልበገር ማለት
ለክብር ለኩራት መሞት ለነጻነት..
ካገዛዝ ጭቆና ለስልጣን መታገት
ሰው በህግ ሰው ለህግ ስርዓት መገዛት፡፡
ዜጋ በነፃነት በልቦና መዝመት
በስራ በኑሮ ተሻሻሎ ማየት
ችጋር ከምድረ-ገፅ እስኪጠፋ መትጋት
በሰላም በፍቅር መገዛት ለእውነት፡፡ 



ጊዜ ቁስል ፈዋሽ
እንዳትፈራው ያን ሞት
እንዳትፈራ ልደት
እንዳትፈራ መውደድ
እንዳትፈራ መንገድ፡፡
የጀመርከው ክምር
የጠበቅከው ፍቅር
ቢደረመስ ቢያጥር
ባይገኝ ባያምር
ሁሉም ባይጀመር
ሁሉም ባይሰመር
ሁሉም ባይቀመር
የመውደድ ወሰኑ
የጊዜ መጠኑ
የኑሮ ውጥኑ
ላይለካ ላሳር
ላይታሰር በክር
ላይሟላ ባጭር
ነገን አታብሳስል
ትናንትን ላትፈትል
ዛሬን ሳታቃልል
ጊዜን አትታገል፡፡
ጊዜ ህመም አዳሽ
ጊዜ ቁስል ፈዋሽ
የታመመው ልብህ-
የቆሰለው ስጋህ
ጠባሳ ቢሆንም ትዝታው ቢከብድም
ጊዜ የጣለውን
ጊዜ ያመጣውን
ማንም አያነሳው ማንም አይወስደውም፡፡
ጊዜ  ህመም አዳሽ
ጊዜ ህመም ፈዋሽ…




የሕይወት መንጃ ፈቃድ
ሕይወት መኪና ናት
ሾፌሩ ነዋሪው
ነዋሪው ዘዋሪው
‹‹ስፖኪዎ›› ትናንት
የኋላን ሚያይባት
ፊት-ለፊት እያዬ አስተውሎ መንዳት
ሲፈልግ ሲያዘገይ ሲያሻው የሚያበራት
መሪውን ጨብጦ ሕይወት መኪናው ናት!



ምንኛ ታደለች
እንዴት ታድለናል
በመፈጠራችን ባ’ርአያው ባምሳሉ
ምንም እንኳ ባይቀርብ ባናየው ባ’ካሉ
የዚህ ኹሉ ዓለም ጀማሪ ፈጣሪ
የዚህ ሁሉ ፍጡር አለቃ ቀማሪ
አምሳሉ ማድረጉ የፍጥረት ዘካሪ
ሰውን አሰልጥኖ ማድረጉ መካሪ
ምንኛ ታደለች ቁንጅናዋም መሪ
ባ’ርአያ ባምሳያ መኾን ከፈጣሪ
ምንኛ መታደል ምንኛ መመረጥ
ባምላክ አምሳል ኾኖ ባርያ ኾኖ መሮጥ…!
ለይስማዕከ ወርቁ የቀንድ ዓውጣ ኑሮ ገጽ //ግብረመልስ



ናፍቆት ሲመሰገን
ስትናፍቅ አንድ ሰው
ሲታይህ ልዩ ሰው
ልብህ ደስ ይበለው
ናፍቆት ሲደጋግመው
ፍቅር ትዝ ሲለው
ወስጥህ ደስ ይበለው!
በልብህ ያለው ሰው
ከጎንህ ርቆ ተሻግሮ ‘ሚኖረው
ትዝ ሲለህ ላፍታ
የናፈቀህ ለታ
እንዳይከፋህ ጎበዝ
እንዳትዋኝ ባ’ሳብ ወንዝ
ትዝታ እንዳያስርህ ናፍቆት እንዳይገልህ
ፍቅር ናፍቆት ካለው
ናፍቆት ዋጋ ያለው የፍቅር እውነት ነው
የናፈቀህ ኹሉ የኖሮህ ትርጉም ነው
የናፈቀህ ፍቅር የህይወት ጣዕም ነው…!



ጀግና ጠፍቶ ባገር
ጀግና ጠፋና ባገር
አምድ ቀረና ማገር
አንድ የሚያደርግ ኣገር
ታሪክ ኾኖ ችግር
ህዝብ ወጣ ከመንድር
ተሰደደ ካገር…
‹‹ባርሳ›› ኾነ ታሪክ
ላንድነት ሚተርክ
ህፃን ኾነ አዛውንት
ሲቀርብ ለውይይት
‹‹አርሴ›› ኾነ ትውፊት…
በምን ይወዳጅ ያገሩ ሕዝብ
በምን ተወያይቶ በምን ይቀራረብ
አንዱ ታሪክ አልባ ሌላው ባለታሪክ
ጠፋ የጋራ ወግ ለኹላችን መድረክ
‹‹ማንቼ ›› ኾነ ስራ ‹‹ቼልሲ ›› ሲኾን ታሪክ
ጀግና ጠፍቶ ግል
ታሪክ ጠፍቶ የወል
ጥበብ ጠፍቶ ባገር
ህዝቤ ተሰደደ ሄደ ወጥቶ ካገር…

No comments: