Showing posts with label ታሪክ. Show all posts
Showing posts with label ታሪክ. Show all posts

Jun 9, 2019

መራራ እውነት- በኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፍ ዳሰሳ

ራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፍ ቅኝት!!





"ታሪክ ጠላ ቤት ተቀምጦ በጥላቻ ስካር የሚደረስ ልቦለድ ሳይሆን በማስረጃ ላይ ተመስርቶ የሚፃፍ እውነታ ነው::" ገፅ 228:: 


አንድ የመፅሐፍ ወዳጄ ገዝቶ ላከልኝ:: እስክቀበለው ድረስ በጣም ጏጉቼ ስለነበር እጄ ሲገባ ደስ አለኝ:: አለሁበት ቦታ እንደተቀመጥኩ ጀመርኩት:: 100 ገፅ መሆኑን ያወቅሁት ስልኬ ሲጠራ የነበረኝን ቀጠሮ ሳስታውስ ነው:: ቁጭት ነው:: ሃቅ ነው:: የሩብ ክፍለዘመኗን ኢትዮጵያ በመረረ መንፈስ ይመላለስባታል:: የሰው እስትንፋስ እጅግ አስቸጋሪ ኃይል ነው:: እምቅ ጉልበት:: ደፍቶ ይጥላል:: የታጨቀ የዘመን ኩርፊያ:: ያውም የታሪክ ስቅለት የደረሰባትን አገር እዳ መሸከም ቀንበሩ እጅግ የከፋ ነው:: 


"ታሪክ የታመመ ጭንቅላትን ያክማል" የሚባለው የሌቭን አባባል በራሱ ባለታሪኮችን ጭንቅላት በክፉኛ ሳያሳምም አይቀርም:: ምክንያቱም በታሪክ ለመታመም መጀመርያ ሰው መሆንን ይጠይቃል:: ሰው መሆን ደግሞ ጭንቅላት ልብ እና ኅሊና ያለተቃርኖ በስሙሙነት የሚተዳደደሩበት "ሥጋለባሽ ፍጥር" መሆን ነው:: በኢትዮጵያ በሩብ ክፍለ ዘመን ታሪኳ ግን ሶስቱ ዓበይት ውቅሮች ከስጋ ለባሹ ጋር መጣመራቸውን መመስከር ያስቀስፋል:: በታሪክ ስጋ ለባሹ ብቻ በሚከበርባት አገር መፈጠር ህመም ነው!!


ይቺ የማትመቸኝ <<27 ዓመት>> የምትባልን ቃል ላለመደጋገም "ሩብ ክፍለ ዘመን" በሚል ዘይቤ ብወክላት የሚሻል ይመስለኛል::


የመፅሐፉ አዘጋጅ በሥነ ፅሑፍ ስልነቱ አቻ አይገኝለትም:: በየገፁ የተሞሉት የዘይቤያዊ ገለፃዎች ልክ ቁጭ ብሎ እንደሚተርክልህ አይነት ባለታሪክን ይመስላሉ:: ኃያል ነው:: ብእሩ አድምቶ እዛው ፈጭቶ ጋግሮ እንደሚመግብ መና አቅራቢ ነው::


መፅሐፉ ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት "ብርሃኔ" ነው ለሚሉት ለስርአቱ አሽከሮች ከሽፋን ገፁ ጀምሮ ሲታይ ገፊ መሆኑ አያጠያይቅም!! ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ አክሱምን አለማስቀመጡ የሆን ተብሎ ሊመስል ይችላል:: የሽፋን ገፁ መራር እውነት ብሎ አፄ ቴዎድሮስን የአበገዳውን ገፅ እና  ድንቅነሽን አጣምሯል:: 



እንደዚህ ፅሁፍ አስተያዬት ሰጭ እምነት መሰረት:: በኢትዮጵያ ታሪክ የተከሰቱ ተቃርኖዎችን በመፈተሽ  የፖለቲካ ንትርካችንን ማከም መቻል የምንጊዜም ታሪክ አዋቂያን አላማ ሊሆን ይገባዋል የሚል ፅኑ እድል ፈንታን ወስዷልና መስለ ስራዎችንም ይሁን ግለሰቦችን አጥብቆ ይሞግታል ይማፀናል ኃቀኝነታቸውን ፈትሾም ይወዳጃል::


መፅሐፉ በ416  ገፆች ተጠርዞ:: አራት አበይት ምእራፎችን ይዞ የኢትዮጵያ ታሪክ ላለፉት አርባ እና ሃምሳ አመታት የደረሰበትን እዥ "ነቀርሳ" ለማከም ይታትራል::  (ነቀርሳ ቫይረስ ነውና ለቫይረስ ህመም ህክምናው ቀላል እንደማይሆን እያሰብን የአካሚውን ተጋድሎ ብርትት እና ቁርጠኝነት ሳናደንቅ አናልፍም)


በምእራፍ አንድ የታሪክ አፃፃፍ ትምህርትን -የታሪክ ምንድርነትን -ማስረጃዎችን የታሪክ አፃፃፍ ጅምሮችን (በተለይምለታሪክ አፃፃፍ ያለን የዘመን ቅርበት) እንዲሁም ዋነኛ የችግሮቻችን ማጠንጠኛ አለት የሆኑትን "የኢትዮጵያ ታሪክ ፀሐፍት ተቃርኖ" በአንደኛው ምእራፍ ወስጥ ተተንትነው ቀርበዋል::


በገፅ 123 የቀረበው የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፍት ተቃርኖ ክፍል ውስጥ 

ሀ) የቤተ መንግሥት ታሪክ መዝጋቢዎች 


ለ)የማርክሲስት ሌኒኒስታዊ አመለካከት ታሪክ ጸሐፊዎች


ሐ) የዘውግ ታሪክ ጸሐፊዎች በሚል ካስቀመጠ በሁዋላ ለአሁኗ ኢትዮጵያ የችግር ሁሉ ምንጭ ሆኖ የቀረበውን "ዘውጌነት" በአስር ምደባዎች በማስቀመጥ እርቃናቸውን ሳያስቀር አደባባይ ላይ ይገልጣቸዋል:: 


የዘውጌ ታሪክ ፀሐፊዎችን ከኦሮሞ ዘውግ ታሪክ ጀምሮ ኦነግን እንደ ፅንሱ መስራች በመቁጠር መራር እውነት እንጋት ዘንድ ብርቱ ሰይፉን ይመዝዛል:: በዚህ ክፍል ውስጥ ትልቅ ጥናት ውይይት የሚያስፈልገውን የናዚዎች መሸሸግያ ማጣት እና ምሽጋቸውን ኢትዮጵያን የማድረጋቸው ትንተና የዚህን ፅሑፍ አስተያዬት ሰጭውን ቀልብ እና ልቡና የሳበቡት-  የመፅሀፉ 133ኛ ገፅ አንድ ሙሉ መፅሐፍ የሚወጣው እንደሆነም ሳይሸሽግ አያልፍም!!


ከኦሮሞ ዘውግ ታሪክ ፀሐፊዎች ተሻግሮ የትግራይ ዘውገኞችን የሚተነትነው በገፅ 135 ሲሆን የሰሜኗ ኢትዮጵያን ህውሃት መራሽ ኃይል ከደቡቡ ኢትዮጵያ ኦነግ መራሽ ሰይፍ ጥምረት የፀረ ኢትዮጵያዊነት ዘመቻ (በፀረ አማራነት ሽፋን) እና የአለም አቀፋዊውን ደባ መላመት አያይዞ ማቅረቡ አሁንም የዚህን ፅሑፍ አስተያዬት ሰጭ ቀልብ የሳቡት ወቅታዊ ጉዳዮች ናቸው!! 


በትግራይ ዘውጌዎች ርእስ ስር በተደጋጋሚ ሲጠቀስ የምናዬው ፖለቲከኛ/ፀሐፊ አስራት አብርሃም ይህ መፅሐፍ በሚፃፍበት ወቅት የነበረውን አመለካከት ደራሲው ቢፈትሽ መልካም መሆኑን እየገለፅን- በግለሰቦች አመለካከት የዘውግ መዋቅራችን መፈተሹ አልፎ አልፎ ክርክራችንን በውሃ ላይ ቆረቆር እንዳያስብሉብን መጠንቀቅ ሳያሻ አይቀርም:: ፕር ገብሩ ታረቀኝ በጉልህ ተማጋሽ ሆነው የቀረቡበትም ምእራፍ እንዳለ ልብ እንልለን::: 


ከሁለቱ ዘውጌዎች ሌላ  ወደ ሶስተኛው ዘውጌ ተረኛ "አማራ" ዘውግ የታሪክ ፀሐፊያን ያሸጋግረናል:: ፀሐፊው እንደአብዛኞቹ የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኞች "አማራ የለም" በሚል የፖለቲካ አፍ መፍቻ መወድስ አይታወቅም:: 


ለዚህም በቅርቡ በማህበራዊ ድረገፆች የተነበበቡት አጫጭር ፅሁፍ የግል ምልከታዎች "ውሃልክነት እና አማራ የኢትዮጵያ ፈጣሪ..." አባባሎች ፀሐፊውን ክፉኛ እንደነኩት ሳንጠቅስ ማለፍ አይቻልም:: (የዚህን ዝርዝር ምልከታ በሌላ ፅሁፍ ብንመለስበት የሚበጅ ይመስላል)


ቀጥሎም የሶማሊ ዘውገኞችን ከዳሰሰ በሁዋላ በዘመናችን የሚታዬውን የታሪክ ሽሚያም እስከ ቀጣዩ ምእራፍ ድረስ በበላይ ዘለቀ በአፄ ቴዎድርስ በእፄ ኃይለሥላሴ ላይ የሚነሳውን "የዘር" ጥያቄ ግምት ውስጥ በማስገባት ሚዛናዊውን <<መራር እውነት>> በተባው ቁጭት ስሜት ይሞግተናል::


ቀጣዩ ምእራፍ ገፅ 156 የሚጀምረው <<የደማቅ ታሪካችን ሰበዞች>> በሚል ርእስ ነው:: 


ከቅሪት አካል ሳይንሳዊ ግኝቶች "ድንቅነሽ" ጀምሮ ጥንታዊዋን ኢትዮጵያ በዓበይት የታሪክ ምእራፍ አምዶች እየከፋፈለ ፑንትን -ዳእማትን አክሱምን ዛግዌን ሰለሞናዊውን ያስቃኘናል:: ይህ መፅሐፍ ሰለሞናዊውን ስርአት በትእምርተ ጥቅስ ውስጥ ካላስገቡ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ መመደቡን  ልብ ብለን እያሰመርን ወደ ሶስቱ የኢትዮጵያዊነት አምዶች <<ዋቄፈና _ክርስትና እና እስልምና>> ሽግግር እንዘምታለን:: ገፅ 169-ገፅ 190::


በተቃርኖ የተሞላው ፖለቲካችን ክምችት የታሪክ አተያያችን እና ግልብ አዘጋገባችን እንደሆነ ይነገራል:: ለዚህም ተቃርኖ መፈጠር ለችግር መዳረጋችን ለመራር እውነት ፍለጋው ለተቃርኖው "ነቀርሳ" ታሪክን በጥልቀት መመርመር ፈውስ እንደሚሆን ታምኗል:: ጥያቄው እነኚህ ተመራማሪ ኃቀኛ ታሪክ አዋቂያን እንዴት ብለው ነው የፖለቲካውን ድር መበጣጠስ የሚችሉት? የፖለቲከኞችን አዙሪት ቀልበው ለሰከነ አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያስናዱት? የሚለው ይሆናል::


በኢትዮጵያ ታሪክ ፀሃፍያን እና በኢትዮጵያዊነት የረዥም አመታት ተንታኝ ግለሰቦች ዘንድ የሚጠቀሱትን "አይሁድ-ክርስትና-እስልምና" እምነት ትስስሮችን ወደ "ዋቄፈና-ክርስትና እና እስልምና" መስተጋብር የተገለፀበት መንገድ የፀሐፊው ልዩ ገፅታ ይመስለኛል::  እንደነ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያዊነት ገለፃ አይሁድ ክርስትናና እና እስልምና የፈጠሩት ውህደት የኢትዮጵያዊነትን መአዛ እንዳሰፈነ ሲገለፅ የኖረውን የታሪክ አተያይ የመምህር ታዬ ቦጋለ መፅሐፉ ግን ስለ ደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ የኦሮሞ ጎሳዎችን ቦረናን እና ጉጂን በድንቅዬ እሴታቸው በገዳ ስርአት ቀለም እያስዋበ ያቀርብልናል:: 


የገዳ ስርዓትን ከአቴንሱ የዴሞክራሲ መነሻነት ጋር በማነፃፀር አቅሙን ይፈትሽልናል:: የግሪኮቹ ዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ከገዳው ስርአት በእድሜም በፍትሃዊነትም በአተገባበርም ሆነ በትርጉም ከቦረኖቹ ጋር ሲመዘን <<በንፅፅር ሚዛን>> ቀልሎም ተገኝቷል:: በአጠቃላይ ይህንን የገዳ ስርአት "የዴሞክራሲ ውሃ ልክ" ሲልም በግልፅ በገፅ 191 በማስቀመጥ እስከ 212 ገፅ ተተንትኖ ቀርቦልናል:: 


ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊንትን ከገዳ ስርአት ውጭ ማሰብ እንደማይቻል ደጋግሞ በማስቀመጥ ይሞግተናል:: ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪቃ እውቅና እና ግልጋሎት ይቸረው ዘንድ   አብዝቶም ይመክራል!!


ፀሐፊው  የኢትዮጵያን ህብረ ቀለማዊ እይታን ሳይሸሽግ የሚመሰክር ነው:: ፅንፈኛ ዘውጌዎችን አጥብቆ ሲሟገት አሃዳዊ ስርአትን ከሚሹት ወገኖች ሊመደብ እንደማይችል "የፖለቲካውን ስፔክትረም" ቀለማት አጥንቶ የተዘጋጄ በመሆኑ ለሃሜት እንዳይዳረግ ሆኖ ራሱን የጦር ልብስ አልብሷል!!


ይህንንም አገላለፅ በፍቱንነት የሚመሰክርልን ኢትዮጵያን ከብሄረሰቦች እስርቤትነት የፖለቲካ ቅኝት ወደ የብሄረሰቦች ሙዝየምነት እና የብሔረሰቦች ሞዛይክነት እንዲሁም ባለ ብዙ ፀጋዎች ሀገርነት (ገፅ209) ስያሜ ማስቀመጡን ልብ ስንል ነው:: 


ሌላኛው ተቃርኖ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የነገስታትቻችንን ታሪክ ቅርፅ ይዘት በጥልቀት መለዬት ጉዳይ ነው:: አፄ ቴዎድሮስ በዘውጌ ታሪክ ፀሐፊያን ዘንድ በተለይም የዘውግ ፖለቲካ መዋቅራዊ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ በተጨማሪም እውነት እስኪመስል ድረስ የሚሰበኩት "ምኒልክ ተኮር ዘገባዎች" በዚህ መፅሐፍ ተመርመረው ቀርበዋል:: 


"አባት እሆንሀለሁ ልጅ ትሆነኛለህ:: ጠላት ዙርያችንን ከብቦናል:: አንድነታችንን እናጠናክር:: ሠራዊቴ ኃያል ስለሆነ ብትገጥመኝ ወገን ታጨራርሳለህ:: በሰላም ለእኔ አድረህ ገብር:: ራስህን በራስህ ታስተዳድራለህ:: በውስጥህ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም::" 

የሚለው አባባል ለፌዴራሊስቶቹ ጭንቅ የሚሆን ነው:: "ራስህን በራስ ታስተዳድራለህ" የሚለው ስንኝ ለዘመነኛ ፌዴራሊስት ነን ባዮች (ስሁታዊያን) ከማን አፍ የወጣ ቃል ነው ተብለው ቢጠየቁ ወደ ምኒሊክ የሚያተኩር ልእልናውን አልፈጠረባቸውም::  


በኢትዮጵያ ታሪክ ከመራሩ እውነት አንደኛው "የታላቁ ተቃርኖ" ምእራፍ መግቢያ የምኒሊክ ጉዳይ ነው:: ምኒሊክን እንደ አቅላጭ/ አሃዳዊ መሪ ሳይሆን እንደ ፌዴራሊስት መሪ እንዲሁም እንደ ጨቋኝ ሳይሆን እንደ ነፃ አውጭ መሪ መውሰድ የታዬ ቦጋለ ብእር ቋሚ ተማጋች ነው:: 


እንዲህ አይነቱን መራር እውነት መጋት ግድ ሳይል አይቀርም:: የመፅሐፉ አቅራቢም ኦሮሞን በገዳ ስርአት እሴቱ በኢትዮጵዊነት ማማ ላይ ቋሚ አምድ የማድረጉን ያክል አፄ ቴዎድሮስ እና አጤ ምኒልክን ጉልህ አሻራነት ለድርድር ሳያቀርብ የተለመድ ዝናሩን ያበረታል!! ፀሐፊው በዚህ ብርታቱ እውነትን ተናግሮ እመሸበት ማደርን ብሂል ሊተገብር ላይ ታች ሲልም ይስተዋላል:: 


ልጅ እያሱ -ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ እና ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በበጎነታቸው ሚዛን ላይ ሲቀመጡ የደርግ እና በተለይ የቀጣይ 1983ቱ ስርአት በዘመነ ፅልመት ስያሜነታቸው ተከትበው እናነባለን:: 


ይህ የአዲሱ ዘመን ታላቁ ተቃርኖአችን ነው:: ከ1966 እስከ አሁን በተልይም ከ1983 ወዲህ ኢትዮጵያ ነፃ የሆነችበት የብርሃን ዘመን ወይንስ እንደ ፀሐፊው አባባል ዘመነ ፅልመት?


በቀጣይ የምንዳስሰው ይሁን:: ምናልባትም የታሪክ መምህራን (ምሁራን) በዚህ ክፍል ላይ የሰላ ትኩረታቸውን ቢሰጡበት እና ኢትዮጵያችንን ከእንቅልፏ ከድንንዛዜ ከነቅርሳዋ ያክሟት ዘንድ ቅን ባለሙያዎችን እና ጋሻ ጃግሬ ባለሟሎች የምትሻበት የዘመን ምእራፍ ላይ እንገኛለን:: 


የዚህ ፅሑፍ ፀሐፊ ባለሙያ ሳይሆን የባለሙያዎች ባለሟል:: የኢትዮጵያዊነት ጋሻ ጃግሬነቱን እድል ፈንታን በመውሰድ አሁንም ከንባብ ከሃሳብ ከመሰል ተሳትፎነት ሌት ተቀን አይቦዝንም:: 


ስጋለባሽ ከሶስቱ መዋቅሮች ጋር ትሥሥር አለው ብሎ ያምናልና!! ለዚህም አይነት ፍጡር ታሪክ አኪሙ ነው:: አካሚዎችን አያሳጣን እያለ ለጊዜው ይሰናበታል!! 



May 20, 2018

የዶክተር አማረ ኃይሌ ፊዳ



ኃይሌ ፊዳን እንዳየሁት…
Portrait_of_HAILE_FIDA

በ60ዎቹ ትውልድ ውስጥ፤ የፖለቲካውን ቅመማ ሲያቀናብሩ ከነበሩ ተቀዳሚ ተዋንያን፤ ኃይሌ ፊዳ  ቀዳሚው ነው፡፡ ልጅ ሆኜ “ፊዲስት!” ሲባል እስማ ነበር፡፡ ምን አንደሆነ ስጠይቅ ተገቢውን መልስ ማግኜት አልቻልኩም፡፡
ከጊዜ በኋላ የኃይሌ ፊዳ ምስከርነትን ሳነብ እና ሥለ ግለሰቡ የሩቅ አሳቢነት ተክለ ስብእና በኣጫጭር ጽሑፎች ስመለከት፤ የዚያን ትውልድ ታሪክ ለማወቅ በብርቱ መፈለግ የነበረብኝ የዚህን ግለሰብ ማንነት ማወቅ ነበር፡፡ የአንዳርጋቸው አስግድን “ባጭር የተቀጨ…”ን እና አልፎ አልፎ የሚወጡ ጽሑፎችንም ለማዬት ሞክሬያለሁ፡፡

በመጠኑም ቢሆን የማነባቸው ጽሑፎች ኃይሌ ፊዳን የኦሮሞ ብሔረተኛ አንቃኝ አድርጎ የመሳል አዝማሚያ ይስተዋላል፡፡ “በእርግጥ ይሕ ሰው ብሔረተኛ ነበር ወይ?” የሚለው ጥያቄም የግለሰቡን ማንነት ለማወቅ ገፊ ምክንያት ከሆኑልኝ ዝርዝሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡
ዶ/ር አማረ ተግባሩ “ኃይሌ ፊዳ እና የግል ትዝታዬ” በሚል አርእስት የተለቀቀውን የመጽሐፍ ገጽ ሽፋን ስመለከት በዚህ ክረምት ከማነባቸው መጽሐፍት ውስጥ ዋናው እንደሚሆን እና ጀምሬውም በጥልቀት ማንበብ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡

የመጽሐፍ ሽፋኑን በማሕበራዊ ድረገጽ ተለቅቆ ስምለከት ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡ ሰዎችንም ከማዬት ባሻገር ቀልቤን የሳበው የፊት ገጽ ላይ በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የተቀመጠው መከረኛው የኦሮሚያ ግዛት ድምቀት ነበር፡፡

በግሌ ከነበረው የኃይሌ ፊዳን ከኦሮሞ ብሄረተኛነት አስተሳሰብ ጋር የማያያዙ ጉዳይ ምናልባትም መልስ ያገኛል በሚል መጽሐፉን ቶሎ በመግዛት ንባቤን ጀምርኩ፡፡ በእርግጥ መጽሐፉን አንዴ ከጀመሩት አለማቋረጥ የሚከብድ መሆኑን መጠቀስ ተገቢ ነው፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር አማረ ተግባሩ ከዚህ ስራ ውጭ “ያንዲት ምድር ልጆች” የተሰኘ ረዥም ድርሳን እንዳዘጋጁ በበይነ መረብ ውስጥ ያገኘሁት መረጃ ይመሰክራል፡፡

“ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” መጽሐፍ 236 ገጾችን ይዞ ከኃይሌ ፊዳ ማነው እስከ ለመሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ምን ይላሉ? የሚሉ አጠቃላይ 20 ንዑስ አርእስቶች አሳጥሮ በቀላል መልኩ የቀረበ ስራ ነው፡፡

“እውነት ኃይሌ ፊዳ ብሔረተኛ አስተሳሰብ የነበረው `ኦሮሞ ፈርስት` ልሳን አቀንቃኝ ምሁር ነበርን?” የሚለውን ጥያቄ ከጅምሩ የሚያፈርሱ ምልከታዎችን ማገኜት በመቻሌ እስከ ገጽ መጨረሻው ድረስ ይህንን መልስ ለማግኜት በጥረት ማንበቤን አልክድም፡፡ በቁቤ ጉዳይም የጠበበ ሳይሆን ሰፋ ያለ ምልክታ እንደነበረው (የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛ ቋንቋ ልሳንን መግለጽ ከቻለ መቀበል እንደሚችል በመግለጹ) መመልከት እንችላለን፡፡
ብሔረተኛ አቀንቃኝ አለመሆኑን በገጽ 7 ላይ ብሔረተኛነትና ጠባብ ብሔረተኝነት ሊያስከትል ከሚችለው መዘዝ ጋር አያይዞ የኤርትራ ጉዳይን ጨምሮ የአካባቢውን ቅኝት የተመለከተበት መንገድ ኃይሌ ፊዳን በይበልጥ እንዳውቀው እና እንድፈልገው ያደረገም መጽሐፍ ነበር፡፡

ኃይሌ ፊዳ ዓለም አቀፋዊ አመለካት የነበረው እና ኩሩ የሆነው ያገር ፍቅር ስሜት ከራስ የመተማመን መንፈስን የተላበስ ስብዕና ባለቤት እንደነበር ከመጽሐፉ ለመቃኔት ችያለሁ፡፡ ታድያ ለምንድን ነው በኢትዮጵያ ካርታ  ውስጥ የኦሮሚያን ግዛት አጽንኦት ውስጥ ማስገባት የተፈለገው? ታስቦበት ነው? አልገባምኝም!!

ይሕ በኃይሌ ፊዳ ስብእና ላይ ሌላ አቅጣጫን መቀየስ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለመጭው ትውልድም ሌላ የቤት ስራን የሚጭር ጉዳይ መሆኑን ሳልገልጽ ማለፍ አይቻለኝም፡፡ የሽፋን ገጹ በዚህ መልክ ለምን እንደቀረበም ትልቅ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም የኃይሌ ፊዳን ትውልድ ስፍራ ጠቅሶ ኃይሌ ፊዳን ወደ አለም አቀፋዊ አመለካከት ባለቤትነቱን ለማሳዬት ቢሆን አጋሮን እና ወለጋን ማቅለሙ ከበቂ በላይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ የትዝታ አተራረክ እና ጸሐፊው እያጣቀሰ የሚነግረንን ማስረጃዎች እውነታነት በጊዜው የነበሩ ግለሰቦች በተለያዬ ጊዜ ተገናኝተው ሲጠይቃቸው የእነርሱ ተጨማሪ ምስክርነት ጋር ስሙሙነት መፍጠሩን በማመሳከር ነው፡፡

የአንዳርጋቸው አሰግድ ባጭር የተቀጨ… የፕ/ር ሽብሩ ከጉሬዛ ማርያም እስከ  አዲስ አበባ እና መሰል መጽሐፍት በተደጋጋሚ የተጠቀሱ ናቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃም ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እስከ ካቶሊክ ቄስ፤ በጊዜው የነበሩ በቤተ ዝምድና እና ማሕበራዊ ሕይወት ግንኙነት ያላቸው በርካታ ገለሳቦች በስም እየተጠቀሱ የደራሲውን ማሰረጃ እንደ ማመሳከረያ እንዲረዱት ጠቅመውታል፡፡

ደራሲው ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ያልተወራረደ ጉዳይ እንዳላቸው መመልከት እንችላለን፡፡ የኮሎኔሉን ተክለ ስብእና በኃይሌ ፊዳ በኩል የሚያገኛቸውን ጥቆማዎች በመውሰድ፤ ኮሎኔሉ ጫማቸውን ሊፈቱላቸው ሲሽቀዳደሙ የነበሩ አንጋቾችን ጨምሮ በያ ትውልድ የነበረውን የፖለቲካ እና ማሕበራዊ ድባብ ለማስቃኜት የበኩሉን የተወጣ ስራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በየዝርዝር ሐሳቦችም የመኢሶንን መዳረሻ ሐሳብ አሁን ስገነዘበው ትክክል እንዳልነበረ በማለትም ሚዛናዊ ሊባል በሚል መልኩ ራሱን ከሕሊና እዳ እና ጠባሳ ሕመም ለመፈወስ የተጋ ስራ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ 

አሁንም ብዙ እንደሚቀረን ግን አልዘነጋውም!

መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ አዕምሮዬ ጋር የተዳመረው አስተሳሰብ ቢኖር ኢትዮጵያ እንዲህ በፖለቲካ ምስቅልቅል ውስጥ እና ማንነት ቀውስ ውስጥ ከገባችባቸው ቀዳሚ ምክንያቶች ውስጥ ኃይሌ ፊዳን የመሰሉ ግለሰቦችን በየወቅቱ መግደላችን ነው ወደሚለው ድምዳሜ እንድደርስ ተጨማሪ ግብኣት ሆኖልኛል፡፡

አሁንም ቢሆን መስል ግለሰቦችን በማወቅ እና በማሳወቅ ደረጃ የሚሳተፉ ግልሰቦችን እንዲያበረታልን በመጸለይ፤ አሁንም ቢሆን ተወራርዶ ያልተቋጨው የያ ትውልድ የፖለቲካ ግብግብ ለአሁኗ እና ለመጭዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ አምድ ሊሆን የሚገባው በመሆኑ ዶ/ር አማረን እያመሰገንን በዚህ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን መርምሮ ወደ መፍትኄ ሐሳብ መድረስ የሁላችንም የቤት ስራ እንደሚሆን ሁልጊዜም በማሳሰብ ዶከተሩን አጅ እየነሳሁ አጭር ምልክታዬን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡

ከመጽሐፉ ምን ጎደልብሀ ብትሉኝ ምናልባት በየገጹ ተራርቀው የሚታዩቱን አራት ነጠቦች ማጠጋጋት ቢቻል፡፡ አራት ነጠቦች ሲበዙ አጠር መጠን ያሉ ሐሳቦች ቀርበው ተደራሲውን ያለማሰላቸት እና ሐሳቡን ያለመስረቅ እድል ፈንታን ይቸሩታል፡፡

(ተስፋ በላይነህ ግንቦት 2010 ዓ.ም)


Aug 29, 2017

Habtamu Alebachew 4th book_ Talaku_Tekarno


የቄሳር መንፈስ “በታላቁ ተቃርኖ” መጽሐፍ፡፡

ሀብታሙ አለባቸው ዛሬም ብዕሩን እና ብራናውን አጣምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቅኝት ለመቃኘት ሞክሯል፡፡  ቅኝት በመቃኘት ይታዘዛል፡፡ ጥሩ ቃኚ ጥሩ ዜማን እንደሚያወጣ እሙን ነው፡፡ ሀብታሙ በቅኝቱ ጥሩ ዜማን አውጥቶ ይሆን አይሆን እንደ አዳማጮቹ የሚወሰን ይሆናል፡፡ በበኩሌ ያልተደፈረውን የቤተመንግስት ጓዳ፣ ያልተደፈረውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እና ያልተለመደውን የኢህአፓ ዘመን ድብብቆሽ ባለፉት ስራዎቹ ለመቃኘት መሞከሩን ወድጄለታለሁ፤ የነበሩኝን አስተያዬቶችም በወቅቱ የሰጠኋቸው አጭር ጽሑፎች በቂ ይመስሉኛል፡፡

ዛሬ በወፍ በረር መቃረም የፈለግኩት “ታላቁ ተቃርኖ” የተሰኘውን ስራውን ነው፡፡ በእርግጥ ይሕንን መጽሐፍ ማኄስም ሆነ ጥናታዊ ዳሰሳ ለማድረግ አቅሉም አቅሙም ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሆኖም እንደ አንባቢ እና ባገር ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ/ለመጠየቅ/ እንዲሁም የግል አስተያዬትን ከመስጠት የተፈጥሮ መብትና/ግዴታ ከመሆን አንጻር ስለመጽሐፉ ጥቅል ሐሳብ የተሰማኝን ለመተው ነው፡፡

በበኩሌ የምስማማበት ጉዳይ (ከሌሎች ጋር አለመስማማት እንዳለ ሆኖ) የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ችግር ከአንድ ነጠላ መንግስት እና “ሬዥም” ጋር ማያያዙ የውድቀታችን መነሻ ነጥብ ነው፡፡

በዚህም አግባብ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያ ታሪክ ማጠንጠኛ “የትክተት ነጥብ” ሆነው ሲወሰዱ፤ ልንወጣው ወደማንችልበት እና ሸክማችንን የሚያበዙ ጋሬጣዎችን ይሰበሰባሉ፡፡ ሌላኛው አስከፊ ችግር ጋሬጣዎች መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ጋሬጣውን የምናስወግድበት እሾኩ ላይ ይሆናል፡፡

ሀብታሙ አለባቸው የዚህ ምሳሌ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡ በመጽሐፉ ሽፋን የመሃል ኢትዮጵያን እና የሰሜን ጫፍ ድንበርን እንደ መነሻ በማድረግ “ታላቁ ተቃርኖ”ን በማመልከት፤ “አጼ ምኒልክ ሠርተውት ያለፉት ነገር በትክክል ምንድን ነው?” ሲል አጼ ሚኒልክን ምስል አስቀምጦ እናየዋለን፡፡ በእርሱ አተያይ እና ጥልቅ ምርምር የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የተገለጸው ወይንም የተጠቀለለው በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስጥ እና ከዚህ ወዲህ ነው ማለት ነው፡፡

ይህን መሰል የምሁራን ቅኝት (ቅዠት ላለማለት)፤ ከ1960ዎቹ የምዕራባዊያን እና የምስራቁ ዓለም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውዥንብር በፈጠራቸው አስተሳሰቦች(የያ ትውልድ አባላት)  ኢትዮጵያን ቀርጸው (የፈጠሯት እስኪመስል ድረስ) የዘመናችንን ትኩሳት እና የወደፊት እጣፈንታችን በየመቶ አመት ታሪክ ብሂል ውስጥ ይቀብረናል፡፡ ይሕ በራሱ የታላቁ ተቃርኖ አንኳር መነሻ ነው፡፡ (የኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ክርክር ሐሳብ በእነ ዮሐንስ አድማሱ፣ እሸቱ ጮሌ፤ ፈቃደ አዘዘ እና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ተችተው የተነሱበትን ዘመን ያስታውሷል)

የፖለቲካ ድንበር እና የአገርን ማስተዳደር ቅርጽ መልኩን ቀይሮ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በተስፋፋበት ዘመን ላይ ቆመን፤ መፍትኄም ይሁን የጥናታችንን ዛቢያ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ሆነን ስናንዣብብ “የታላቁ ተቃርኖ” መነሻም መድረሻም እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

“የኤርትራ” ችግር እና “የደቡብ ቅራኔ” በምኒልክ መጀመሩን እንደ ፖለቲካዊ ትንታኔ አድርጎ መነሳት የሃብታሙ አለባቸው እና የመሰሎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ውድቀት መሆኑ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ (ግል እይታዬ) ነው፡፡

የዳዕማት ሥልጣኔ አንድምታው ምንድን ነው? የአሁኑ ትውልድ ምን ያሕል ያውቀዋል? የአክሱምን ሥልጣኔ ማን አቆመው?  ማን መራው? ማን ማን ገበረ? የትኛው ሕዝብ በየትኛው ህዝብ ትስስሩን ፈጠረ? በምን መንገድ ከየት ወደዬት? ሕዝብ በምን ተለያዬ?  በምን ተሳሰረ? ፤

የዛጉዌ ሥልጣኔ ከየት የት ይደርስ ነበር? የውጭው ዓለም በወቅቱ በምን መልኩ ይረዱት ነበር? በዚህ ወቅት የደቡቡ ይዞታ በምን መልኩ ይተሳሰር ይተዳደር ነበር?

የመካከለኛው ዘመን የይኩኖ አምላክ መንግሥት ከደቡቡ ጋር የነበረው ትስስር? የሸዋ ነገሥታት እና ቀሪው ማሕበረሰብ የነበራቸው ገጽ፤ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ሶማሌ ድንበር ድረስ ሄደው የገነቡት ልማት፣ ጥፋት፣ የትዳርም ይሁን የማስገበር/የመገበር ታሪካችን፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እስከ ቀይ ባሕር እና ህንድ ውቅያኖስ ወይንም የአፍሪካ ቀንድ ጫፍ መታዬት፤ የልብነ ድንግል ንጉሳዊ ስም አጠራር በራሱ የሚሰጠው ትርጓሜ፤ የምስራቁ ዘመቻ ወደ ሰሜን ያመጣው ለውጥ፤  ለምላሹም የተሰጠው አጸፋ (አሉታዊም አዎንታዊም የአገር ግንባታ ሂደት..)

የእነሰርጸድንግል ታሪክ፤ የጎንደር ነገሥታት ከደቡቡ በተለይም ከኦሮሞው ሕዝብ ጋር የነበራቸው ትስስር፤ የየጁ መሳፍንት በጎንደር ዘመን የነበራቸው ሚና፣ ኦሮምኛ በጎንደር የነበረው ቦታ፤ ባሕረነጋሽ/ኤርትራ የነበረችበት ሁኔታ(ይዞታ)፤

የአጼ ቴዎድሮስ አነሳስ፣ ዘመኑ የጠየቀው መስፋፋት ምክንያት፤ ለምን አጼ ቴዎድሮስ?፤ በዘመኑ የነበረው የግዛት አወሳሰን እንዴት ይገለጽ ነበር?፤ ነው ወይንስ “አቢሲኒያ”ን ቀርጸን ማነብነብ ይቀልለናል? …

(እዚህ ላይ ትልቅ የሚዘነጋ ሐሳብ ይታየኛል፤ ይሄውም የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ከታቢ እና ምጡቅ ግለሰብ አለቃ ዘነብ የኦሮምኛን ቋንቋ ማጥናታቸው፤ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ ለመተርጎም ማሰባቸው፤ አስበውም መተግበራቸው በምን መልኩ የሚታይ ሐሳብ ነው?)

በአጼ ዮሐንስ ዘመን መባቻ ላይ የተደረገው የባዕዳን ወረራ እና ተጽዕኖ፤ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ለምን?  የባሕረ ነጋሽስ ይዞታ፤ የሂወት ውል፤ የምዕራባዊያን ቅኝ ግዛት ዘመቻ፤ የፖለቲካ አስተሳብ ዘመቻ፤ የመንግሥታት ትብብር ሐሳብ፤ የዘመናዊነት ትርጓሜ፤ … ወዘተ

እንዲህ እንዲህ እያልን ጥናታዊ ምርምር፤ የታሪክ ጥናት የሚጠይቀውን መነጽር እየተጠቀመን “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ሐሳብ እያላወስን፤ የኢትዮጵያን ችግር ነቅሰን እናውጣ ቢባል አዕምሮየንም ሆነ ስሜቴን የሚገዛ ጭብጥ የማገኝ ይመስለኛል፡፡

ዋናው ሀብታሙ አለባቸውን የምሞግትበት ነጥብም ይሄው ነው፤ ከእዘኒህ ጭብጦች ውስጥ ነበር የአጼ ምኒልክን ቦታ ፈልቅቀን በማውጣት ወዳለንበት ደረጃ ደርሰን ተቃርኖንም ይሁን የግጭት መንስኤዎችን አልያም ስኬቶችን ልንገልጽ የምንገደደው፡፡ ከአንድ ትልቅ ሰፌድ ውስጥ አንዱን ሰንደዶ አውጥቶ የሰፌዱን ሕልውና አድርጎ መውሰድ በሰፌዱ እና በሌሎች ሰንደዶዎች ላይ የሚሰራ ደባ ሆኖ መታሰቡ አይቀሬ ነው!

ኤርትራ ከምኒልክ በፊት የኢትዮጵያ ግዛት የሆነችበት እና ያልሆነችበት ጊዜ በታሪክ ተፈትሾ ሲጠና፤ የደቡቡን ይዞታ እና ትስስር ቅድመ ታሪክ ጥናት ሳናደርግ፤ ምኒልክን መነሻም መድረሻም ማድረጉ ትልቅ የታሪክ ሸፍጥ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ምኒልክ ሳይፈጠሩ ኤርትራ የነበረች እና ለበርካታ ነገስታት የድልም የውድቀትም የስኬትም የክሽትም ማጠንጠኛ ሆኖ የዘለቀች በመሆኗ፤ “ኤርትራ” “ኤርትራ” የምንለው የምዕራባዊያኑ እርኩስ መንፈስ ወርሶን ለመግባቢያነት የምንጠቀምበት የቦታ ስም ብቻ ሳይሆን ለውድቀታችን የተበተብነው የቄሳሩ መንፈስ አዚም /አዙሪት/  ነው፡፡ ደቡቡንም በመቶ አመት ውስጥ የተፈጠረ መልክዓምድራዊ ይዞታ እስኪመስል ድረስ፤  ስለ ሺሕ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት እያወራን ቦታና የሕብረተሰብን ፍልሰት ሳናጤን፤ የጥንቱን ስያሜ በዘመነኛ “ሰካራም” ስያሜ እየሰጠን፤ በአሁኑ ትርጉምና ዘመን አመጣሽ መቀመርያ መመዘን፤ የውድቀታችን መነሻ እና የታላቁ ታቃርኖ ክስተት መደምደሚያው/መፈጸሚያው/ ነው፡፡

ሀብታሙ አለባቸው በመጽሐፉ በርካታ አገር ውስጥ እና የባዕዳንን ሰም እየጠቀሰ፤ የሐሳብ ክርክሩን ለማጠናከር ሲሞክር እናስተውላለን፡፡ የምሑራኑን ሐሳብም እየጠቀሰ ለ“ታላቁ ተቃርኖ” መፍትኄ ‹‹ፋይዳ የሌለው›› እና ‹‹ያለው›› እያለ ሲገልጽ እናስተውላለን፤ በተለይም ከአገር ውስጥ ገብረሕይወት ባይከዳኝን እና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ማስተዋላችን አልቀረም፡፡

በበኩሌ ፕ/ር መስፍን መልደማርያምን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ባሕል እና ፖለቲካ ትንታኔ አረዳድ ላይ በአንድ እና በሁለት መጽሐፎቻቸው ዙሪያ ላይ ብቻ በማተኮር አጠቃላይ ሐሳባቸውን ሲተችም ይሁን መፍትኄ የለውም ብሎ መነሳቱ በሰፊው ጸሐፊውን ያስገመግመዋል፡፡ “አዳፍኔ” ይሕንን አላስቀመጠም ብሎ ወደ ፍርጃ መውረድ ጸሐፊው የተልዕኮ ማስፈጸሚያ አንደበት መያዙን ያጎላበታል፡፡ (አንባቢ ሆይ በሀንታሙ አለባቸው መጽሐፍ ውስጥ ከበርካታ ምሁራን ሐሳቦች በመጡ መደምደሚያዎችን ስናጤን፤ “መስፍን ወልደማርያም በዘመናቸው ያልጠቀሱት ሐሳብ (መፍትኄ) ይሄ ነው” ብሎ የሚያሳየኝ ሰው ካል ለመቀጣት ዝግጁ ነኝ!- ፕሮፌሰሩ ከጻፏቸው መጽሐፍት ውስጥ እንደዋቢ የጠቀሳቸው ከሶስት አለመብለጡን ያጤኗል!)

መጽሐፉ የበርካታ ምሁራንን ሐሳቦች በቁንጽልም ቢሆን መያዙ ምሁራኑ ተሰባስበው እንዲመካከሩበት እና እንዲወያዩበት የኢትዮጵያን ትልቁን ቁልፍ ችግር ለመያዝም እና የተዘጋብንን ደንቃራ አስተሳብ ለመክፈት፤ ብሎም ቁልፉን ለእያንዳንዱ ዜጋ ሰጥቶ ወደ ብርሃናማው “የታሪክ አቅጣጫ”  እንደንዘልቅ ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ጸሐፊው ለመማርም ይሁን ለመታረም ዝግጁነቱን ሲያሳይ እና በአካለ መንፈስ ሲገኝ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

መጽሐፉን በተደጋጋሚ እየተመለስኩ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምርምራዌ ሂደትን ለመከተል የታሰብ ከመሆኑ አንጻር አሁንም ልዩ ትኩረት እና አንጽንዖት ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ እንደ መቋጫ ሁለት ነጥብ ብቻ ላንሳ፡፡ አንደኛ የኔ የአስተሳሰብ አድማስ ልኬት በእጅጉ የተወሰነ መሆኑን ወይንም በሌላኛው ጎን የጸሐፊው ሐሳብ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ፖለቲካ ዙሪያ አዲስ አስተሳሰብን ይዞ ስለመጣ ለመረዳት አዳግቶኛል፡፡ በበኩሌ ጸሐፊው (ለእኔ) ይሕንን የፈጠረበት ምክንያት  ምንድን ነው ብዬ ሳብብ አንዳንድ ነጥቦችን ማስቀመጥ ይኖርብኛል፡፡ በተቻለኝ መጠን በማሳጠር በሦስት ነጥቦች ብቻ ላጠቃልል፡፡

  1. የኢትዮጵያን ችግር ከአጼ ምኒልክን ጋር አቆራኝቶ መነሳቱ እና የመፍትኄ ሐሳቡንም እዚያው ዙሪያ በማድረጉ
  2. በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የባዕዳንን ተልዕኮ እና ጫና ራሱን የቻለ ሰፊ ግምት የመያዙን ያክል ጸሐፊው ጥናቱን በዚያ ላይም ባለማድረጉ
  3. አሁንም በምሁራን እይታ ይቀርቡ የነበሩ ቃላትንን ለምሳሌ፤ ብሔር፣ አገር፣ ሐገረ መንግስት፣ ስልጣኔ፣ ባሕል፣ መንግስት ሬዥም…. ወዘተ መሰል ቃላትን አጠቃቀማቸውን ከነልዩነታቸው ለማስረዳት ቢሞክርም በተለያዩ ገጾች ላይ ግን ራሱ ሲዳክርባቸው መመልከታችን አልቀረም፡፡

ሶስቱን ነጥቦች በመያዝ ሌላ አንድ ረዥም ትንተና የሚያስፈልገው ጽሑፍ ይዞ ብቅ ማለት ይቻላል፡፡ ለጊዜው ይብቃን፡፡

ታላቁ ተቃርኖ በባዕዳን አስተሳብ የተቃኘ የምሁር እይታ መሆኑን መካድ አልችልም፡፡ የገብረህይወት ባይከዳኝን ሐሳቦች ላይ አተኩሮ ሚዛኑን እሱ ላይ መድፋቱን ሲገልጽ እናየዋለን፡፡ የሌሎችንን ባዕዳን አስተሳሰቦች/ጥናታዊ እይታ/ ከውስጣዊ ታሪካችን ጋር እያነጻጸሩ ለመግባቢያነት መቀመጡ ላይ ውስጤን ሲኮረኩረው በተደጋጋሚ ተይዣለሁ፡፡

የበርካታ ምሑራንን ሐሳቦች ጥናታዊ ስራ እና የምርምር ውጤቶችን ደርድሮ በጫት የታገዘ ጽሑፍ እንዳይሆን  ጸሎቴን አድርሼ፤ በመጽሐፉ ዙሪያ የወጡ አስተያየቶችን ለማንበብም ሆነ ለመሳተፍ ዝግጁነቴን ጀምሬያለሁ፡፡ መጽሐፉ አሁንም በተደጋጋሚ ሊመረመር እና ሊታይ ሚገባው መሆኑን ግን የሚክድ አንደበት የለኝም፡፡

  Article:- by Tesfa Belayneh. 

Jun 27, 2017

ሚስጥረ-ኢትዮጵያ -1


ሚስጥረ-ኢትዮጵያ!

http://abbaymedia.com/tewodros-kassahun-weni-weni-%e1%8b%88%e1%8a%92-%e1%8b%88%e1%8a%92-new-ethiopian-music/

ሰሞኑን “ወኒ ወኒ” የሚል ቅማንትኛ ሙዚቃ በምስለ ድምጽ /ክሊፕ/ ተሰርቶ አየሁ፡፡ “ቋንቋችሁ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል” በሚል አንደኛ ምክንያት ከማንነት ጥያቄያችሁ ጋር ለተነሳው ጥያቄ ተገቢ መልስ ለመስተት ተቸግሮ ለቆዬው አካል አንድ መረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ሊያስደስተኝ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” የምንል ግለሰቦች ፍትሃዊ ልንሆን ምንችለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ቋንቋዎች እውቅና ሊሰጣቸው፤ ሊያድጉ፤ አገልግልግሎት ላይ ሊውሉ፤ በሥነ-ጽሑፍ እነ በኪነ-ጥበብ  ደረጃም ከፍ ያለ እምርታን እንዲያሳዩ በጋራ ስንተጋ ነው፡፡

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለይም ጎንደር ተወልዶ እንደማደግ ይህ ጉዳይ ያገባኛል/ያሳስበኛል/፡፡ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች ወይንም የብሐረተኛ ጽንፍ አራማጆች በእጅጉ ከሚወቀሱበት ነገር አንዱ፤ ልዩነትን የሚያስተናግዱበት መንገድ ዝግ መሆኑ ነው፡፡ ዝግ ባይሆንም እና ትንሽ የመግቢያ ጭላንጭል ቢያስተርፉልን እንኳ የጥላቻ እና የቂም ፖለቲካ ውስጥ ሆነው ስለሚዘጉብን የመግባባት መጠኑን ያቀጭጨዋል፡፡ በዚህም ምክንያት “ኢትዮጵያ” ክፉኛ ታምማለች፡፡ የታመመ አንድነት አስተጋቢዎችም መሰል ችግሮችን ሲያስተናገድ ይስተዋላሉ፡፡ ከለመዱት ቋንቋ ውጭ ሌላ ቋቋ ሲነገር እና ማንነቱን ለማቆም የሚተጋ አካል ሲያዩ አንድነታችን ተናጋ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይሕም አንዱ የሕማማችን መንስኤ መሆኑን መካድ የለብንም!

ይህን ሁሉ ያስባለኝ ጉዳይ የቅማንትኛ ሙዚቃ መውጣቱን ተከትሎ፤ ከኢትዮዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ጋር አጣምሬ የምለው ነገር ስላለኝ ነው፡፡ “ጎንደሬ ነኝ” የሚል ግለሰብ ቅማንት ሊሆን ይችላል፣ ወልቃይቴ ሊሆን ይችላል፤ አርማጭሆ፤ ሰሜን፤ ጋይንቴ፣ በለሴ፣ ወገሬ፤ ቋሬ፣ እብናት ወዘተ…. የሚገርመው ትግሬም ሆኖ ጎንደሬ ሊሆን ይችላል፡፡ የወላይታም ሰው ጎንደሬ ይሆናል፤ ከአሩሲም መጥቶ ጎንደሬነትን ለመቀበል የሚያግደው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ ይህ አውነት ነው፡፡ ሆኖ አይተነዋልና!!

አሁን የተነሳው የዘውግ ፖለቲካ ይህን ልዩነት ማስተናገድ አይቻለውም፡፡ ጎንደር ተወልዶ ጎንደሬነትን እያቀነቀነ የተለያየ ሕብረ ጎሳዊ ማንነቶችን ተዋህዶ “ጎንደሬ ነኝ” “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ለማለት ማንም አያግደውም፡፡  በጎንደር በደሴ በአዋሳ፣ በአምቦ፣ በድሬድዋ፣ በሐረር፣ በጅማ፣ በደብረማርቆስ፣ በይርጋለም፣ በጨንቻ፣ ወዘተ ክፍሎች ያደገ ግለሰብ ይሕ ሁኔታ የበለጠ የሚሰማው እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ያደግንበት ማሕበራዊ ሥነ-ልቡናም ይህንን የመለያዬት አባዜ አያስተጋባም፡፡ “ብዙ ነን ግን አንድ፤ አንድ ነን ግን ብዙ!”

ሆኖም አሁን ባለው የብሔር-ተኮር  ፖለቲካ፤ አንድ ግለሰብ ወይ “ትግሬ” ነው፣ ወይም “አማራ” ነው፣ ወይ “ኦሮሞ” ነው አልያም ደግሞ ሕውሃት በከፋፈለችው የማንት ወሽመጥ ውስጥ ሆኖ “አንድ” ብቻ ነው፡፡ ብዝሀነት የለም፡፡ ብዝሃት በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚስተናግድ ስርዓት  ትክክለኛው የዴሞክራሲ ስያሜን ይቀዳጃል፡፡

ከብዙው የሆነን ግለሰብ አንድ ማንነት ብቻ ስትሰጠው ጎኔን ይልሃል፤ ሚስቴን ይልሃል፤ እናቴን ወይም ቅም አያቴን ወይም አበልጄን፣ መምሬን… እያለ ይጠይቅሃል፤ ለየትኛውም መወገን አይቻለውም፡፡ አንድ ሆኖ ለሁሉም ነው፤ ሁሉንም ሆኖ ግን አንድ ነው! ይሕ የገሃድ ምስጢር ነው፡፡

በቤተ ክርስትያን ትምሕርት “ሚስጥረ ሥላሴ” የሚባለው ክፍል እጅግ ረቂቅ ነው፡፡ ለመረዳት የስጋን እና የመንፈስን ቁርኝት ፤ በበሰለ ምጡቅ ሕሊና እና ከፍ ባለ ሥነልቡናዊ ደረጃ ልንረዳው ይገባናል፡፡ እንዲያም ሆኖ በቸርነቱ እና በመልካም ፈቃዱ ካልታገዝን መገኛችን መናወዝ ባሕር ውስጥ ይሆናል!

ምስጥረ ሥላሴን ለሊቃውንቶቹ እንስጥና “ሚስጥረ ኢትዮጵያን” ለመረዳት ፈቃድ እንስጥ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በዚህ ርዕስ ላይ የራሱን ትንተና ለመስጠት ጊዘውን እና አቅሙን ሰጥቷል፡፡ በተቻለ መጠን ወደፊት የበኩሉን ለመወጣት መሰል ጽሑፎችን እየመረመረ በማስረጃ ለማስቀመጥ ይታትራል፡፡ የሁላችን ኃላፊነት ቢሆን ኢትዮጵያ ከሕመሟ ታገግማለች፤ በሒደት እየተሸላት ጤናማ እና የበለጸገጭ አገር ማቆም ይቻላናል፡፡ ይሕንነ የሚዲርጉ ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ አምላክ ያበርታቸው፤ ያጠንክራቸው!

ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ በሞርጋን ስቴትዩኒቨርሲቲ  የፖለቲካ መምህር ሲሆኑ፤  ስለ ሰው ልጅ ስብዕና በቀላል ምሳሌ  ሲያስረዱ የብራዚሉን ፓውሎ ፌሬሬን ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ፓውሎ ፌሬሬ አባባል የሰው ልጅ ሥነ-ልቡና እያደገ ከመጣ እንደ አንድ ሰው መተያየት እንደሚጀምር ይገልጻሉ፡፡ የመለያየት እና የመነጣጠል ጸባይ መንደርተኛ ጠባብ ሥነልቡና መሆኑን ሳይንሱን አጣቅሰው ይነግሩናል፡፡ ማንነት እንደሽኩርት ነው የላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ይላላጣል፤ ብዙ ማንነቶች በአንድ ግለሰብ ውስጥ እየተላጡ ሉታዩ ይችላሉ፡፡  የመለያዬት ማንነት ሊገለጥ የሚችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ከፍ ያለ የሥነልቡና ደረጃን /ስብዕናን/ የያዘ ግለሰብ “ኢትዮጵያዊነት” አጠቃላይ መገለጫ ሆኖት፤ ኢትዮጵያዊነት የሥነ-ልቡና ከፍታ የሚያመጣው ማንነት እንደሆነም ያሳያሉ፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ከፍ እያለም ወደ አህጉር እና ወደ አንድ የሰው ልጅ ማንነት ተስሎ መገለጽ ይጀምራል፡፡ ከአባባሉ እንደምንረዳው እንደሽንኩርት ልጣጭ (ነጠላዋን ማንነት ሳንደፈጥጥ) ትልቁን ማንነት ማሳየት ማቆም ከፍ ያለ ጥበብ እና የከፍታ ሥነልቡና ላይ መሆንን ይጥይቃል!!

የወቅቱ ብሔር ተኮር ፖለቲካ አራማጆች በብሔር የተቦዳደንበት ዋናው ምክንያት ብሔር ተኮር አጀንዳ ዋና የማንነት አቅም እና አቋም እስከሆነ  ድረስ፤ ይህ አቅም ፈርጥሞ ሌሎችን ማጠቃት እና መዋጥ ሲጀምር ዝም ብሎ መበላት የተበይውን ሕዘብ ስቃይ ማባባስ ወንጀል ነው ይላሉ፡፡ በብሔር የተቧደነን የፖለቲካ ስርዓት ከብሔር ውጭ በሆነ ክበብ /ማንነት/ መታገል ሞኝነት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ያሳደገንን ማሕበረሰብ ለእሳት ማገዶ አሳልፎ መስጠትም ህሊናን የሚያጠለሽ ኃጥያትም ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ አበሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያዊነት ላይ ያንዣበበው ፈተና ነው!! ለዚህ ምላሽ ሐብታሙአያሌው በሚገባ መልስ የሰጠበትን ንግግር ማድመጥ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያም ጅፉን በክፉ መመለስ የሚያስከትለው ክፋትን ሲሆን፤ ጠላት የመረጠውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ እንደ ግብ መውሰድ የጠላት መሳሪያ መሆኑን በአጽንዖት ይመሰክራል፡፡ ለትልቅ ክብር መሰዋትን የድል አክሊል ያወርሳል!!

በኢትዮዮያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ካንዣበቡት የታሪክ ገጠመኞች ውስጥ የጥልያንን የዓምስት ዓመት ክፉ ጊዜ የነበረ አይመስለኝም! ሌሎችን በራሳችን ችግር ያመጣነቸው ራሳችን ልንፈታቸው የሚገቡን ገጠመኞች እንደሆኑም አምናለሁ፡፡ አሁን የደረሰብን ፈተና ከጥልያን የተቀዳ የመከራ ደመና ስለሆነ፤ ችግሩን ከጥልያን ዓላማ ጋር እያስተባበርን ማከም ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ጽሑፍ የመረጥኩት ከመግቢየ ላይ የጠቀስኩትን የቅማንትኛ ሙዚቃ ጥልያን በ1928ቱ ወረራ ወቅት ከተከሰተው አንድ ገጠመኝ ጋር በማዛመድ ይሆናል፡፡ ይህን የታክ ገጠመኝ የምናገኘው “ጎንደሬ በጋሻው” በሚለው የገሪማ ታፈረ መጽሐፍ በገጽ 29 ይሆናል፡፡

    “አንድ ቀን የፋሬ ፖሌቲች ኮማንዳ ቶሪ ባሊ ፔሮ የከርከርን የበጋ አገርን የጋባን፤ የጭልጋን ቅማንቶች እንዲሰበሰቡ በማለት በየአገሩ የጥሪ  ደብዳቤ ላከ፤ የጥሪው ደብዳቤ ከተናኘ በኋላ ታላላቅ የሆኑትን የቅማንት ባላባቶች በተለይ ከቢሮው አግብቶ ከዚህ በየሚቀጥለው የፖለቲካ መርዝ ሕይወታቸውንና ክብራቸውን ይመርዛቸው ጀመር፡፡ የሚለውም ሬሙስና ሬሙሉስ የተባሉትን ወንድማማቾች አጥብታ ያሳደገቻቸው ተኩላ ናት፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የተኩላይቱን ጡት ጠብተው ከአደጉ በኋላ በዓለም ውስጥ ካሉት ከተሞች ከፍ ከፍ ብላ የምትታየውን የሮማን ከተማ መሠረቱ በሮማ ውስጥ የተፈጠሩትም ኃያላን በጦረኝነታቸው ዓለምን ሲያስገብሩት ይኖራሉ፡፡

የናንተም አባት አይነርን በከርከሃ በረሃ አጥብታ ያሳደገችው ሰስ ናት ይባላል፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ታሪክ በመካከላችን ስለተፈጠረ ፤ የናንተም ሰስ እንድትከበርና፤ የሰስ ምልክት ያለበት ዓላማ እንዲሰጣችሁ መንግስት ሥለአዘዘ ዓላማውን ተቀብላችሁ መንግሥት ያደረገላችሁን መልካም አርኣያ እየወሰዳችሁ ለሕዝቡ እንድታሳዩት፤ ብሎ ከአንድ ትልቅ የዋርካዛፍ ስር ሰስ ቁማ የተሣለበት ትልልቅ ሰሌዳ አውጥቶ አሳያቸው፡፡

   እንግዲህ በዚህ የጥልያን መርዝ ፖለቲካ ምላሽ ሁለት ሰዎችን እናገኛለን፡፡ የመጀመርያው  ቀኛዝማች ጣሹ ሲሆኑ በተቃራኒው የደጃዝማች ቢተዋ ልጅ ፊታውራሪ ዓለማየሁን ይሆናል፡፡

   የመጀመርያው ግለሰብ ይህንን የመርዝ ፖለቲካ በመረዳታቸው “ሕዝቤን ልጠይቅ” ብለው ሄደው ሕዝቡን እንዳማከሩት እና የዚህ አይነት ታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያለያይ መሆኑን አምነው፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ስር እንተዳደር ነበር፤ አሁን ደግሞ በጣልያን ባንዴራ ሆነን እንተዳደራለን እንጂ ሌላ ታሪክ አንቀበልም በማለት ዋናውን የመርዝ ፖለቲካ አጥፍተው መልሰዋል፡፡ ቀጣዩ የጭልጋው ባላባት ልጅ ፊታውራሪ ዓለማየሁ ግን ይህን ፖለቲካ ተቀብለው ምስሉን ተቀብለው በረዥም እንጨት ከቤታቸው በር ተሰቀለ፤ በጭልጋ አውራጃ የሚገኘው የቅማንት ሕዝብም 15 ቀን ሙሉ ሲዘፍን እንደቆዬ እና “አባታችን አይነር ነው አጥብታ ያሳደገችንም ሰስ ናት” እያሉ ታሪኳን በማስጠናት ይዘዋት ይዞሩ ነበር፤ ሰስ እንዳይገደልም የሚል አዋጅ እስከማስወጣት እንደሰቡም ይጠቁማሉ፡፡

እንግዲህ ይህ ሰዓት ጠላት እና ወዳጅ አርበኛው እና ባንዳው የሚለይበት ጊዜ በመሆኑ በየትኛውም ጎሳ ያለ ግለሰብ እንደግለሰቡ ልዕልና እንጂ እንደጎሳው ጥቅል ሐሳብ ሊወከል የማይችል ውሳኔን እንዲደሚየስተላልፉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ አርበኛነትም ይሁን ባንዳነት የግለሰብ ውሳኔ እንጂ የጎሳ መጠርያ ሊሆኑ አይቻላቸውም፡፡ ይሕ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን እያሰመሟት ከሚገኙት አንዱ ነው፡፡

የቅማንት ሕዝብን የማንነት ጥያቄ ግራዝማች ካሰኝ አለማየሁ በእግቸራው ከጎንደር አዲስ አበባ እየተመላለሱ እንደጀመሩት ወዳጆቼ ነግረውኛል፡፡ የማንነት ጥያቄው ላይ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊጋራው እና የራሱም ጥያቄ እደሆነ አስቦ መረዳት ያስፈልገዋል፡፡ (እንዲህ ስል ይሕ ሰው ቅማንት ነው እንዴ የሚሉ እንደማይጠፉ አልጠራጠርም)፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ቅርስ፤ ባሕል፤ ቋንቋ እና መገለጫ ሁሉ የኔ ነው! ልጠብቀው፣ ጥብቅና ልቆምለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ችግር የሚሆንበት ብዬ የማምነው ጠያቂው አካል በሌሎች ሕዝቦች ላይ የተበዳይነት ስሜትን አዝሎ ለጥላቻ እና ለቂም ፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኖ ብቅ ሲል ብቻ ሲሆን፤ በተጨማሪም በዳይ የሚባለው አካልም ራሱን ነጻ ለማውጣት ችግሩን ለመፍታት ከመቅረብ ይልቅ የአፋኝነት፣ የጡንቻ እና የመለያዬት ፖለቲካን ሲያራምድ ችግሩ ተባብሶ የጠላት ዓላማ እንዲሳካ ማድረጉን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

 ይሕንን ከጥልያን ያየነው ሲሆን ከታሪክ ያለመማር ችግራችን ታሪክን እየደገምን ወደኋላ ቁልቁል እንድንንሸራተት ምክንያት እንዳይሆን የበኩላችንን መወጣት ይኖብናል!!

የማጥቃለያውን ጭብጥ የማደርገው በመግቢያው የተጠቀሰውን ሙዚቃ በማስታወስ ይሆናል፡፡ ሙዚቃው ጥሩ ኢትዮያዊ ይዘት ያለው፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ነው፡፡ ችግሩ የሚሆነው የተዘፈነለት ዓላማ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ወጣት ተሰብስቦ የሚዘፍነው በወንድሙ በእናቱ በአያቱ በአበልጁ በጎረቤቱ ላይ የመለያትን መንፈስ ወርሶ በቂም እና በበቀል ፖለቲካ ተመርዞ ነው? ወይንስ ወንድማማችነትን፤ አብሮነትን እና አንድነትን በሚያጠነክር መልኩ? ጥያቄው ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ ይህን የማይመልስ እንቅስቃሴ ግን ትልቅ ችግርን እንደሚያስከተልማጤን አለብን፡፡

ኢትዮጵያዊ ቅርስ የሆውን አንድ አካል “ቅማትንኛን” ለማስተዋወቅ ለመጠበቅ፤ ለሕብረት በአንድነት መንፈስ የተቃኘ…ዜም እን እንቅስቃሴ ሁሉ ሊደገፍ ይገባዋል!! ይሕ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል! ብዙዎች ስንሆን አንድ፤ አንድ ስንሆን ብዙ ነን! አገራችንም አንድ ስሟም ስንጠራው የማይሰለቸው…

ኢ.ት.ዮ.ጵ..ያ ነው!!     

ተስፋ በላይነህ ሰኔ 2009 ዓ.ም

Jun 16, 2015

አውሮራ እና የቄሳር እንባ!



ተስፋ በላይነህ

Habtamu Alebachew_AWRORA-YEKESAR INBA

አንድ ጸሐፊ ልክ እንደ ውቅያኖስ ውስጥ እንደሚዋኝ ፍጡር፤ ሰፊ ነጻነትን ይዞ በውቅያኖስ ውስጥ እንደሚኖሩ ኅልቆ መሳፍርት ፍጥረታ ብዛት፤ እንደ ፈጠራቸው ገጸባሕርያት አስመስሎ ማቅረብን የመሰለ አስደሳች ነገር የለም፡፡
በእኔ አመለካከት በአሁኑ ሰዓት በነጻነት የሚጽፍ ሰው አለ ብዬ ማመን እየከደበኝ መጥቷል፡፡ ጸሐፊ ነጻነቱን ሲቀማ ምን ሊሆን እንደሚችልም ስናስብ፤ በአንዲት የደረቀች ኩሬ ውስጥ ግባና ዋኝ እንደመባል የተፈረደበት ጸሐፊ ምንኛ ያሳዝናል፡፡-ልግመት ይሉሃል ይሄ ነው!
አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጸሐፊ የቤተ-መንግስትን ውሎ በነጻ ሕሊናው አስቦ ለመጻፍ የሞከረ በብዛት አይገኝም፡፡ ይሕ የሚያሳዬው ደራሲያን ምን ያክል በጠበበች ኩሬ ውስጥ ለመዋኘት መገደዳቸውን ነው፡፡ የኩሬን እና የውቅያኖስን ንጽጽር ለማቅረብ የዳዳሁት ሀብታሙ አለባቸው ምን ያክል በውቅያኖስ ውስጥ ለመዋኘት መመኘቱን ከዚያም አልፎ መዋኘት መሞከሩን ለማሳዬት ነው፡፡
በ‹‹አውሮራ››ም ሆነ በ‹‹ቄሳር እንባ›› የምናስተውለው እና የምናደንቀውም ሀብታሙ አለባቸው በሶስት አይደፈሬ የአፍሪቃ መሪዎች ቤተ-መንግስት ውስጥ ዘልቆ በመግባት፤ በእነዚህ መሪዎች ሆድ እና ልብ ውስጥ ምን እንደሚብላላ ለመጻፍ ያሳየው ሙከራውን ነው፡፡
‹‹አውሮራ›› ላይ የአስመራውን ርዕሰ ብሔር ኢሳያስ አፈወርቂን እና የአዲስ አበባውን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን ቤተ መንገስት መኝታ ቤታቸው ድረስ በሃሳብ ተወርውሮ ሕሊና ጓዳቸው ሥር ምን እንደሚነጋገሩ ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡
‹‹አውሮራ›› የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጦርነት ውሎ ከመዘገቡም ባሻገር የኢሳያስ አፍወርቄ መንግስት ለጦርነት ምን ያክል ጥማት እንደነበረው ለማሳዬት እንደተጻፈም መገንዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹ፍልይቲ›› የአስመራዋ ፍልቅልቅ ውብ ገጸ ባሕርይን የተላበቸች ሴት፤ ከሸዌው ተወላጅ ‹‹አስራደ›› ጋር የምታደርገውን የፍቅር ክስተት ከነፍለጋ መስዋዕቱ ድረስ ለማሳዬት ተሞክሯል፡፡ ከዛም በተጨማሪ ባድመ ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያትነቷ እንዴት ሊሆን እንደቻለ በጥያቄ ያልፈዋል፡፡ ሃይላይን የመሳሰሉ ግለሰቦች ደግሞ ከአስመራ የተገኙ ጦርነትን የሚቃወሙ እና መስዋዕትነትን የከፈሉ ገጸ-ባሕርያት ናቸው፡፡ የባድመ ጦርነት መምስዔነት በእርግጥ ጥሩ እና ግልጽ ጥያቄ ሆኖ ሳለ፤ የዚህ አስተያየት ጽሑፍ ጸሐፊ ግን ያለተዋጠለት ጉዳይ ቢኖር የአውሮራ ጸሐፊ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ሙሉ በሙሉ በኤርትራዊያን ርዕሰ ብሔር ቡድኖች ላይ በማሸከም፤ ይባስ ብሎም የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር በልማት ጽንሰ ሐሳባቸው ራዕይ ላይ ከአልጋ ቀስቅሶ እርባና የለሹን ጦርነት ውስጥ እንደገቡ ለማመላከት መጻፉን ነው፡፡
የ‹‹አውሮራ›› ደራሲ ከቤተ-መንግሥት አካባቢ የማይጠፋ አሊያም ቤተ-መንግሥት ውስጥ ያለን ትዕይንት የሚያቃብለው ሰው እንዳለ ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ ይሕም በገጽ 166 ላይ እንደምናነበው ጠ/ሚ/ር መለስ ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የቲ.ሳሙኤልሰን አስራ ሰባተኛ ቅጽ የኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መማሪያ መጽሐፍ እያነበቡ ነበር፤ ይሕም ጥናት ከአገራችን አርሶ አደር ጋር ለማዋሃድ እየሞከሩ የነበረበት ወቅት ሲሆን፤ ከዚህ የልማት አስተሳሰብ ራዕይ ተጠምደው በነበረበት ወቅት አንዳች አይነት ብሔራዊ  የስልክ ድምጽ ይጮኻል፤ አደጋ ስጋት እንደማዕበል መጥቶም ቀይ ፊታቸውን አደፈረሰው፡፡ ገጽ167፡፡
ይሕ የቤተ-መንግሥት የጥሪ ጩኸት ተራና መደበኛ አልነበረም፤ ለአገሪቱ ቀውሶች የአስቸኳይ ጊዜ የደኅንነት መረጃ ማቅረቢያ መሳሪያ ነበር፡፡ የሚሰራውም በጣት አሻራ ሲሆን የደርግ መንግስት ከሰሜን ኮርያ መሐንዲሶች አስመጥቶ ያስገጠመው ነው…፡፡ ይሕን አይነት መረጃ በጽሑፉ ውስጥ ማንበባችን ጸሐፊው በነጻነት ቤተ-መንግሥትን ለመቃኘት የተሠጠውን እድል(ነጻነት) እንመለከታለን፡፡
‹‹አውሮራ›› በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ተቀምጣ የተከለለውን የእሾሕ ፖለቲካዊ አጥር አፈር አድርጋ የማዋሃድ አቅም አላት? አንባቢ መጽሐፏን አንብቦ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡ በኔ በኩል ወገናዊነት የታየበት የአጻጻፍ መልክ በመያዙ፤ የተፈጠረውን የሕዝቦች መራራቅ ስፋት አጥብቦ ከአንድ የሥነ-ሑፍ ሰው እንደሚጠበቀው እምቅ የጥበብን ኃይል በመንተራስ ይሕንን የታሪክ ስብራት ይጠግናል ብዬ አላምንም፡፡ አውሮራ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሕብረት ድምጽ ብቻ ነውና!
“..ሲጀመር ደፋር አትበሉኝና ይሕንን መጽሐፍ በጭብጥና ይዘቱ ስመዝነው ከኦሮማይ በኋላ የተፈጠረ ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ..” ተብሎ ከአንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ዲፕሎማት ከሰጡት አስተያየት የተቀነጨበ ነው ሲባል፤ ‹‹ኦሮማይ›› ምን ያክል በአዞዎች መንጋጋ ውስጥ ሥጋ ትለቅም የነበረችን ወፍ እንደነበረች እና ፤ ከጉማሬዎች ትከሻ ላይ ተጠልላ ትጓዝ ከነበረች ወፍ ጋር ለማወዳደር መሞከሩን በቀላሉ እናያለን፡፡
‹‹ኦሮማይ››ን እና ‹‹አውሮራ››ን ማነጻጸር ለምን እንደተፈለገ አልገባኝም፡፡ ‹‹ኦሮማይ›› በደርግ አባላትም ይሁን በሻብዕያ አባላት አልተወደደችም፡፡ መስዋዕትነቷንም እናውቃለን፡፡ ‹‹አውሮራ›› በ‹‹ኦሮማይ›› ስር ለመዳኘት መሞከሩ አግባብ ያልሆነ የንጽጽር ሚዛን ይመስለኛል፡፡
ለ‹‹አውሮራ›› ጸሐፊ የምጠይቀው ቀላል ጥያቄ ቢኖር የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በጠ/ሚኒስትር መለስ ውስጥ በድንገት የተፈጠረ፤ የኤርትራው ርዕሰ ብሔር የጦርነት አባዜ ውጤት ብቻ ነው? የሚል ይሆናል፡፡ የትግራይ ርዕሰ መስተዳደር አባላት ከመለስ ዜናዊ ጋር ያላግባባቸው ምሥጢር ምንድን ነበር? ‹‹አውሮራ›› ይሕንን መመለስ ብትችል ኖሮ ከ‹‹ኦሮማይ›› ቀጥሎ የተጻፈች የዘመናችን ድንቅ ጽሑፍ በሚል፤ መጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ ለታሪክ አስቀምጣት ነበር፡፡ በአጭሩ ‹‹አውሮራ›› የወገናዊነት ድምጽ ጩኸት መሆኗን ራሷ የአውሮራ ፍቺ ይነግረናል፡፡
በመጽገፉ እንደተገለጸው ‹‹አውሮራ›› የኢትዮጵያ ሰራዊት ሕብረት ድምጽ ጩኸት ነው፡፡ ይሕ ደግሞ የሁለቱን ሕዝቦች መራራቅ ስፍር ያሰፋዋል እንጂ ለማጥበብም ጭራሽ የሚፈልግ አይመስልም፡፡
‹‹የቄሳር እንባ››፡፡
ልክ እንደ ‹‹አውሮራ›› ነጻነት፤ ደራሲው አሁንም እነኚህን አምባገነን መሪዎችን ልብ መቃኘት በሞመከሩ ለዬት ያለ ፈር ቀዳጅ ስራ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ልብ ውስጥ ገብቶ፤ አንድ ደራሲ ያሻውን ሲጽፍ መመልከት በ‹‹ሆሊውድ›› እንደምንመለከተው ‹‹ኃይት ሐውስ›› ውስጥ ያለውን የቤተ-መንግሥት ትዕይንት ለማስቃኘት እንደሚሞክሩ ‹‹ፊልሞች››፤ ሀብታሙ አለባቸውም በአራት ኪሎው ቤተ-መንግሥት ውስጥ የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ባለቤት፣ ልጆች፣ እና አጠቃላይ ውሎ መዘገብ መቻሉ መጽሐፉን ይዘን እንድንቀጥል የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል፡፡ መንጌ ከባለቤቱ ጋር እንዴት እንደተገናኙ የገለጸበት መንገድም በሕሊናችን ሩቅ እንድንጓዝ አስችሎታል፡፡
የ‹‹ቄሳር እንባ›› ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ የተጻፈ ምላሽ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ትግላችን››ን አንብቦ የተናደደ ሰው ሊጽፈው የሚችለው፤ በልብ ወለድ አጻጻፍ መልክ የተጻፈ፤ ከ1966 አብዮት ወዲህ የተከሰተውን የትውልድ መላሸቅ፤ የሕብረተሰብ ዝግመት እና የአገር ውድቀት- በ”ልግመተ ኢትዮጵያ” ስያሜነት የተተየበ ጽሑፍ ነው- ‹‹የቄሳር እንባ››፡፡
የዚህ አስተያየት ሰጪ ግለሰብ በቄሳር እንባ የቀረበችው ኢትዮጵያ ከደርግ መገርሰስ ማግስት እስከ አሁን ፍንትው ብላ የምትታይ መሆኗን ለመናገር ይደፍራል፡፡ መጽሐፉን የሚያነብ አመዛዛኝ ሕሊና ያለው ማንኛውም ግለሰብ በደርግ ዘመን እየተንጸባረቁ የነበሩ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ክስተቶች አሁንስ የሉምን? እያለ እንደሚያሰምርባቸውም ያለ ጥርጣሬ መገመት እንችላለን፡፡
ለደርግ ባለስልጣን የቤተክርስትያን ቀሳውስት ወጥተው መረብ ማቅረባቸው፡፡
ስደት፡፡
ሕዝብ ለመንግስት ድጋፍ  አሰጣጥ፡፡
ብሔርተኝነት..፡፡
የማሕበረሰብ የታሪክ የባሕል ልሽቀት፤አድር ባይነት…፡፡
የሚድያው ቁጥጥር እና ፕሮፖጋንዳ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለገዥዎች ያለው አመለካከት፡፡
መንግሥት የሚገጠመውን የየዕለት ጉዳይ ከላይ ወደታች እና ከውጭ ወደ ውስጥ መመልከት፡፡
የወሲብ ንግድ፡፡.. እና መሰል የደርግ መንግስት መገለጫዎች አሁን በምኖርባት አገሬ ውስጥ ፈልጎ ማጣት አይቻልም፡፡ ሥለዚህ ሀብታሙ አለባቸው በደርግ መንግስት የነበረውን ስርዓት ሲቃኝ- አሁን ያለበትን ሥርዓት እየዳሰሰ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለማሳዬት ሞክሯል፡፡
አሁንም ወገናዊነት የተንጸባረቀበት ጽሑፍ የመምሰል ክስተትን ለመገንዘብ የሚያስችል ሃሳብ ለማስተዋል እንሞክር፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገጸ-ባሕርይ ከሆኑት አንዱ በላይነህ ደሴ፤ በቤተ-መንግሥት ውስጥ ተቀምጦ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ስብዕና እያስተዋለ፤ በልቡ ይቃወም የነበረ የውባንቺ የእህት ልጅ ነው፡፡ ለመንግሥቱ ኃይለማርያም በጻፈው ደብዳቤ ላይም መንግሥቱን በቀጥታ ለመግለጽ በሚሞክርበት ጊዜ- ሀብታሙ አለባቸው በቀረጸው የመንግስቱ ልብ ውስጥ ግን “በላይነህን ሻዕቢያ እና ወያኔ ላከብኝ” በሚል አስተሳሰብ መገለጹ ትልቅ ጥያዌ የሚያስነሳ ነው፡፡ ገጽ 361-364፡፡መጽሐፉ ውስጥ የደራሲውን አስተሳሰብ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም አስተሳሰብ ጋር ለይቶ ማቅረብ ስላልተቻለ ከታሪካዊ ገጽታ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ደራሲው የፈጠረውን ገጸባሕርይ እንደ ልቡ መሳል የማይከለከል ቢሆንም፤ ልክ ስብሓት ገብረ እግዚአብሄር ተስፋዬ ገብረ ኣብን የገለጸበትን መንገድ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በእንዳለ ጌታ ማዕቀብ መጽሐፍ ላይ ስብሃት ስለ ተስፋዬ ገብረኣብ ሲጠየቅ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡.. የምታውቀውንና የማታውቀውን አውነት በብዛት ይነግርህና መጨረሻ ላይ የሚነግርህ ውሸት መሆኑን ሳታውቅ ትቅበለዋለህ..፡፡(ቃል በቃል ላይቀመጥ ይችላል፡፡) ስለዚህ እንደዚህ አይነት ጸሐፊዎችን መከላከል የምንችለው የስብሓት ገ/ብረ እግዚእብሔርን ምክር መያዝን ሳንዘነጋ ነው፡፡
ሀብታሙ አለባቸው በገጽ 392 “የትምህርት ምሁራን `ትውልድ ሥርዓተ ትምህርቱን ይመስላል` ይላሉ” ብሎ ሲገልጽ የትኛውን ትውልድ እየተመለከተ መሆኑን ማሰብና መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከሞላ ጎደል ‹‹የቄሳር እንባ›› እንደ ገጹ ብዛት ምንችክ ያላለ ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊውንም ለወደፊት ብዙ እንድንጠብቅበት የሚረዳው ይሆናል፡፡ ሆኖም ከአጼ ቴዎድሮሥ እስከ ኃይለ ስላሴ የነበሩ መሪዎች(ገዥዎች) ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ ማንባታቸውን ሲገልጽልን “ጥቁሩ ቄሳር” የተባለው መንግሥቱ ያነባውን እንባ “ቄሳራዊ” ማድረግ በእጅጉ ያጠያይቃል፡፡ ሲጀመር መንግሥቱ ለቄሳር የሚቀርብ አይደለም፡፡ መንግሥቱን ቄሳር ካልን ደግሞ የሌሎች መሪዎቻችንንም እንባ ቄሳራዊ ስያሜ ልናሰጥ ነውና፡፡
ቢያንስ በገጽ 402 የተገለጸው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የግል ስብዕና ለአንዲት አገር የሚቅም በጎ ገጽታ ይኖረዋል፡፡ ምዕራባዊያንን የገለጹበት መንገድ፣ ገንዘብ አለመፈለጋቸውንም በበጎ እይታ መመልከት ሥንችል “በመሪነታቸው ገንዘብ ይቅርና አገሪቱ የራሳቸው ናት” ተብሎ መገለጹንም ሳንተዛዘብ መተላለፋችን አልቀርም፡፡
እንደነ ዶ/ር ኃየሉ አርዓያ እና የሐረሩ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እንዲሁም ሻዕቢያም፣ወያኔም እና ደርግም ያልተቀበሏቸውን ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ አንዳንድ ግለቦች ኢትዮጵያ በምጥ ጊዜ የደረሱላት ሰዎች መሆናቸውንም መገንዘብ እንችላለን፡፡  
በአጠቃላይ ደራሲው በመንግሥቱ ኃይለማርያም ልብ ውስጥ ገብቶ የሚስቡትንና የነበራቸውን የአስተሳሰብ ልኬት መግለጽ ሲሞክር በታሪክም ሆነ በአንድ ግለሰብ ሕልውና ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ሳንረዳ ማለፍ የለብንም፡፡
መንግሥቱ ሃይለማርያም በጥቁርነታቸው የሚያፍሩ መሪ ነበሩ ወይ? ይሕም በገጽ 112 በአንድ አፍሪቃዊ መሪ ስም መጠራታቸው ቆሽታቸው ማረሩን እናነለን፡፡ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ጨካኝነት እና በቀል ከእድገት፣ ከቆዳ ቀለም መገለል፣ ከከንፈር መስፋት ጋር ማነጻሩ ትልቁን የነጻ አጻጻፍ ሥልት ወደ ታች የሚያርደው ይመስለኛል፡፡ ለአንድ አፍሪቃዊ መሪ አምባገነንነት የውጭ ኃይል ተጽዕኖ ሰፊውን ድረሻ የሚወስድ ይመስለኛልና፡፡
አንድ አጭር ጽሑፍ እንግለጽና እንሰነባበት “መንግስቱ በደም ኦሮሞና አማራ ቅይጥ ናቸው፡፡ በሥነ-ልቡናና በኢትዮጵያ ማንነት ጥያቄ ላይ ግን ቅልጥ ያሉ አማራ ናቸው፡፡” ገጽ 111፡፡ ከዚህ ጽሑፍ የመጽሐፉ ሃሳብ ምን ሊመስል እንደሚችል መረዳት እንችላለን፡፡ ኦሮሞ ሆነው በአንዲት ኢትዮጵያዊነት ስሜት የማያምኑ እንደሌሉ ተደርጎ ሳይታሰብ አሊያም ታስቦ ተጽፏል፡፡ የሀብታሙ አለባቸውን ቀበሌኛ  ቃላት ለምሳሌ መሸርገጊያ፣ አበባ ቆሎ፣ ፎቴ፣ ሙርጥ  ወዘተን ስናስብ ከመንደረኛ አስተሳሰብ ጋር እንዳይላተሙ በመመኘት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ከጠበበ ብሔርተኝነት ጸዳ ሰሜት፣ ሰፊ እና ነጻ አዕምሮ፣ ከተሻለ የእውቀት አስተሳሰብ ጋር የሚፈይዳት ይመስለኛል፡፡ ከልግመቷም የሚፈውሳት ይህ ነውና! አድር ባይነት በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ በላይነህ ደሴ የተመለከታት ልግመት ኢትዮጵያን ስናስብ-   ጥያቀው አንድ ነው፡፡
የኛ የቤት ስራ ልግመት ኢትዮጵያን ለማዳን አምባገነን መሪዎችን በመቃወም፤ስደትን እንደ አማራጭ በመውሰድ የሚፈታ ነው? የቄሳር እንባ አልመለሰውም…፡፡ ቸር ኢትዮጵያ!