ሚስጥረ-ኢትዮጵያ!
http://abbaymedia.com/tewodros-kassahun-weni-weni-%e1%8b%88%e1%8a%92-%e1%8b%88%e1%8a%92-new-ethiopian-music/
ሰሞኑን “ወኒ ወኒ” የሚል ቅማንትኛ ሙዚቃ በምስለ ድምጽ
/ክሊፕ/ ተሰርቶ አየሁ፡፡ “ቋንቋችሁ ከምድረ ገጽ ጠፍቷል” በሚል አንደኛ
ምክንያት ከማንነት ጥያቄያችሁ ጋር ለተነሳው ጥያቄ ተገቢ መልስ ለመስተት ተቸግሮ ለቆዬው አካል አንድ መረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል
ነው፡፡ ለዚህም እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ሊያስደስተኝ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” የምንል ግለሰቦች ፍትሃዊ ልንሆን
ምንችለው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ቋንቋዎች እውቅና ሊሰጣቸው፤ ሊያድጉ፤ አገልግልግሎት ላይ ሊውሉ፤ በሥነ-ጽሑፍ እነ
በኪነ-ጥበብ ደረጃም ከፍ ያለ እምርታን እንዲያሳዩ በጋራ ስንተጋ
ነው፡፡
እንደ አንድ
ኢትዮጵያዊ ዜጋ በተለይም ጎንደር ተወልዶ እንደማደግ ይህ ጉዳይ ያገባኛል/ያሳስበኛል/፡፡ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች ወይንም የብሐረተኛ
ጽንፍ አራማጆች በእጅጉ ከሚወቀሱበት ነገር አንዱ፤ ልዩነትን የሚያስተናግዱበት መንገድ ዝግ መሆኑ ነው፡፡ ዝግ ባይሆንም እና ትንሽ
የመግቢያ ጭላንጭል ቢያስተርፉልን እንኳ የጥላቻ እና የቂም ፖለቲካ ውስጥ ሆነው ስለሚዘጉብን የመግባባት መጠኑን ያቀጭጨዋል፡፡ በዚህም
ምክንያት “ኢትዮጵያ” ክፉኛ ታምማለች፡፡ የታመመ አንድነት አስተጋቢዎችም መሰል ችግሮችን ሲያስተናገድ ይስተዋላሉ፡፡ ከለመዱት ቋንቋ
ውጭ ሌላ ቋቋ ሲነገር እና ማንነቱን ለማቆም የሚተጋ አካል ሲያዩ አንድነታችን ተናጋ ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይሕም አንዱ የሕማማችን መንስኤ
መሆኑን መካድ የለብንም!
ይህን ሁሉ
ያስባለኝ ጉዳይ የቅማንትኛ ሙዚቃ መውጣቱን ተከትሎ፤ ከኢትዮዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ጋር አጣምሬ የምለው ነገር ስላለኝ ነው፡፡ “ጎንደሬ
ነኝ” የሚል ግለሰብ ቅማንት ሊሆን ይችላል፣ ወልቃይቴ ሊሆን ይችላል፤ አርማጭሆ፤ ሰሜን፤ ጋይንቴ፣ በለሴ፣ ወገሬ፤ ቋሬ፣ እብናት
ወዘተ…. የሚገርመው ትግሬም ሆኖ ጎንደሬ ሊሆን ይችላል፡፡ የወላይታም ሰው ጎንደሬ ይሆናል፤ ከአሩሲም መጥቶ ጎንደሬነትን ለመቀበል
የሚያግደው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ ይህ አውነት ነው፡፡ ሆኖ አይተነዋልና!!
አሁን የተነሳው
የዘውግ ፖለቲካ ይህን ልዩነት ማስተናገድ አይቻለውም፡፡ ጎንደር ተወልዶ ጎንደሬነትን እያቀነቀነ የተለያየ ሕብረ ጎሳዊ ማንነቶችን
ተዋህዶ “ጎንደሬ ነኝ” “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ለማለት ማንም አያግደውም፡፡
በጎንደር በደሴ በአዋሳ፣ በአምቦ፣ በድሬድዋ፣ በሐረር፣ በጅማ፣ በደብረማርቆስ፣ በይርጋለም፣ በጨንቻ፣ ወዘተ ክፍሎች
ያደገ ግለሰብ ይሕ ሁኔታ የበለጠ የሚሰማው እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ያደግንበት ማሕበራዊ ሥነ-ልቡናም ይህንን የመለያዬት አባዜ
አያስተጋባም፡፡ “ብዙ ነን ግን አንድ፤ አንድ ነን ግን ብዙ!”
ሆኖም አሁን
ባለው የብሔር-ተኮር ፖለቲካ፤ አንድ ግለሰብ ወይ “ትግሬ” ነው፣
ወይም “አማራ” ነው፣ ወይ “ኦሮሞ” ነው አልያም ደግሞ ሕውሃት በከፋፈለችው የማንት ወሽመጥ ውስጥ ሆኖ “አንድ” ብቻ ነው፡፡ ብዝሀነት
የለም፡፡ ብዝሃት በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የሚስተናግድ ስርዓት
ትክክለኛው የዴሞክራሲ ስያሜን ይቀዳጃል፡፡
ከብዙው የሆነን
ግለሰብ አንድ ማንነት ብቻ ስትሰጠው ጎኔን ይልሃል፤ ሚስቴን ይልሃል፤ እናቴን ወይም ቅም አያቴን ወይም አበልጄን፣ መምሬን… እያለ
ይጠይቅሃል፤ ለየትኛውም መወገን አይቻለውም፡፡ አንድ ሆኖ ለሁሉም ነው፤ ሁሉንም ሆኖ ግን አንድ ነው! ይሕ የገሃድ ምስጢር ነው፡፡
በቤተ ክርስትያን
ትምሕርት “ሚስጥረ ሥላሴ” የሚባለው ክፍል እጅግ ረቂቅ ነው፡፡ ለመረዳት የስጋን እና የመንፈስን ቁርኝት ፤ በበሰለ ምጡቅ ሕሊና
እና ከፍ ባለ ሥነልቡናዊ ደረጃ ልንረዳው ይገባናል፡፡ እንዲያም ሆኖ በቸርነቱ እና በመልካም ፈቃዱ ካልታገዝን መገኛችን መናወዝ
ባሕር ውስጥ ይሆናል!
ምስጥረ ሥላሴን
ለሊቃውንቶቹ እንስጥና “ሚስጥረ ኢትዮጵያን” ለመረዳት ፈቃድ እንስጥ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በዚህ ርዕስ ላይ የራሱን ትንተና ለመስጠት
ጊዘውን እና አቅሙን ሰጥቷል፡፡ በተቻለ መጠን ወደፊት የበኩሉን ለመወጣት መሰል ጽሑፎችን እየመረመረ በማስረጃ ለማስቀመጥ ይታትራል፡፡
የሁላችን ኃላፊነት ቢሆን ኢትዮጵያ ከሕመሟ ታገግማለች፤ በሒደት እየተሸላት ጤናማ እና የበለጸገጭ አገር ማቆም ይቻላናል፡፡ ይሕንነ
የሚዲርጉ ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ አምላክ ያበርታቸው፤ ያጠንክራቸው!
ፕሮፌሰር
ጌታቸው መታፈሪያ በሞርጋን ስቴትዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር ሲሆኑ፤ ስለ ሰው ልጅ ስብዕና በቀላል ምሳሌ ሲያስረዱ የብራዚሉን ፓውሎ ፌሬሬን ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ፓውሎ ፌሬሬ አባባል
የሰው ልጅ ሥነ-ልቡና እያደገ ከመጣ እንደ አንድ ሰው መተያየት እንደሚጀምር ይገልጻሉ፡፡ የመለያየት እና የመነጣጠል ጸባይ መንደርተኛ
ጠባብ ሥነልቡና መሆኑን ሳይንሱን አጣቅሰው ይነግሩናል፡፡ ማንነት እንደሽኩርት ነው የላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ይላላጣል፤ ብዙ ማንነቶች
በአንድ ግለሰብ ውስጥ እየተላጡ ሉታዩ ይችላሉ፡፡ የመለያዬት ማንነት
ሊገለጥ የሚችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡ ከፍ ያለ የሥነልቡና ደረጃን /ስብዕናን/ የያዘ ግለሰብ “ኢትዮጵያዊነት” አጠቃላይ መገለጫ
ሆኖት፤ ኢትዮጵያዊነት የሥነ-ልቡና ከፍታ የሚያመጣው ማንነት እንደሆነም ያሳያሉ፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ከፍ እያለም ወደ አህጉር እና
ወደ አንድ የሰው ልጅ ማንነት ተስሎ መገለጽ ይጀምራል፡፡ ከአባባሉ እንደምንረዳው እንደሽንኩርት ልጣጭ (ነጠላዋን ማንነት ሳንደፈጥጥ)
ትልቁን ማንነት ማሳየት ማቆም ከፍ ያለ ጥበብ እና የከፍታ ሥነልቡና ላይ መሆንን ይጥይቃል!!
የወቅቱ ብሔር
ተኮር ፖለቲካ አራማጆች በብሔር የተቦዳደንበት ዋናው ምክንያት ብሔር ተኮር አጀንዳ ዋና የማንነት አቅም እና አቋም እስከሆነ ድረስ፤ ይህ አቅም ፈርጥሞ ሌሎችን ማጠቃት እና መዋጥ ሲጀምር ዝም ብሎ መበላት
የተበይውን ሕዘብ ስቃይ ማባባስ ወንጀል ነው ይላሉ፡፡ በብሔር የተቧደነን የፖለቲካ ስርዓት ከብሔር ውጭ በሆነ ክበብ /ማንነት/
መታገል ሞኝነት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ያሳደገንን ማሕበረሰብ ለእሳት ማገዶ አሳልፎ መስጠትም ህሊናን የሚያጠለሽ ኃጥያትም ነው ሲሉ
ይደመጣሉ፡፡ ይህ አበሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያዊነት ላይ ያንዣበበው ፈተና ነው!! ለዚህ ምላሽ ሐብታሙአያሌው በሚገባ መልስ የሰጠበትን
ንግግር ማድመጥ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያም ጅፉን በክፉ መመለስ የሚያስከትለው ክፋትን ሲሆን፤ ጠላት የመረጠውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ
ዓላማ እንደ ግብ መውሰድ የጠላት መሳሪያ መሆኑን በአጽንዖት ይመሰክራል፡፡ ለትልቅ ክብር መሰዋትን የድል አክሊል ያወርሳል!!
በኢትዮዮያ
እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ካንዣበቡት የታሪክ ገጠመኞች ውስጥ የጥልያንን የዓምስት ዓመት ክፉ ጊዜ የነበረ አይመስለኝም! ሌሎችን
በራሳችን ችግር ያመጣነቸው ራሳችን ልንፈታቸው የሚገቡን ገጠመኞች እንደሆኑም አምናለሁ፡፡ አሁን የደረሰብን ፈተና ከጥልያን የተቀዳ
የመከራ ደመና ስለሆነ፤ ችግሩን ከጥልያን ዓላማ ጋር እያስተባበርን ማከም ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ጽሑፍ የመረጥኩት ከመግቢየ
ላይ የጠቀስኩትን የቅማንትኛ ሙዚቃ ጥልያን በ1928ቱ ወረራ ወቅት ከተከሰተው አንድ ገጠመኝ ጋር በማዛመድ ይሆናል፡፡ ይህን የታክ
ገጠመኝ የምናገኘው “ጎንደሬ በጋሻው” በሚለው የገሪማ ታፈረ መጽሐፍ በገጽ 29 ይሆናል፡፡
“አንድ
ቀን የፋሬ ፖሌቲች ኮማንዳ ቶሪ ባሊ ፔሮ የከርከርን የበጋ አገርን የጋባን፤ የጭልጋን ቅማንቶች እንዲሰበሰቡ በማለት በየአገሩ የጥሪ ደብዳቤ ላከ፤ የጥሪው ደብዳቤ ከተናኘ በኋላ ታላላቅ የሆኑትን የቅማንት ባላባቶች
በተለይ ከቢሮው አግብቶ ከዚህ በየሚቀጥለው የፖለቲካ መርዝ ሕይወታቸውንና ክብራቸውን ይመርዛቸው ጀመር፡፡ የሚለውም ሬሙስና ሬሙሉስ
የተባሉትን ወንድማማቾች አጥብታ ያሳደገቻቸው ተኩላ ናት፡፡ እነዚህ ታላላቅ ሰዎች የተኩላይቱን ጡት ጠብተው ከአደጉ በኋላ በዓለም
ውስጥ ካሉት ከተሞች ከፍ ከፍ ብላ የምትታየውን የሮማን ከተማ መሠረቱ በሮማ ውስጥ የተፈጠሩትም ኃያላን በጦረኝነታቸው ዓለምን ሲያስገብሩት
ይኖራሉ፡፡
የናንተም አባት አይነርን በከርከሃ በረሃ አጥብታ ያሳደገችው
ሰስ ናት ይባላል፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ታሪክ በመካከላችን ስለተፈጠረ ፤ የናንተም ሰስ እንድትከበርና፤ የሰስ ምልክት ያለበት ዓላማ
እንዲሰጣችሁ መንግስት ሥለአዘዘ ዓላማውን ተቀብላችሁ መንግሥት ያደረገላችሁን መልካም አርኣያ እየወሰዳችሁ ለሕዝቡ እንድታሳዩት፤
ብሎ ከአንድ ትልቅ የዋርካዛፍ ስር ሰስ ቁማ የተሣለበት ትልልቅ ሰሌዳ አውጥቶ አሳያቸው፡፡
እንግዲህ በዚህ የጥልያን መርዝ ፖለቲካ ምላሽ ሁለት ሰዎችን
እናገኛለን፡፡ የመጀመርያው ቀኛዝማች ጣሹ ሲሆኑ በተቃራኒው የደጃዝማች
ቢተዋ ልጅ ፊታውራሪ ዓለማየሁን ይሆናል፡፡
የመጀመርያው ግለሰብ ይህንን የመርዝ ፖለቲካ በመረዳታቸው “ሕዝቤን ልጠይቅ”
ብለው ሄደው ሕዝቡን እንዳማከሩት እና የዚህ አይነት ታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያለያይ መሆኑን አምነው፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ
ሰንደቅ ዓላማ ስር እንተዳደር ነበር፤ አሁን ደግሞ በጣልያን ባንዴራ ሆነን እንተዳደራለን እንጂ ሌላ ታሪክ አንቀበልም በማለት ዋናውን
የመርዝ ፖለቲካ አጥፍተው መልሰዋል፡፡ ቀጣዩ የጭልጋው ባላባት ልጅ ፊታውራሪ ዓለማየሁ ግን ይህን ፖለቲካ ተቀብለው ምስሉን ተቀብለው
በረዥም እንጨት ከቤታቸው በር ተሰቀለ፤ በጭልጋ አውራጃ የሚገኘው የቅማንት ሕዝብም 15 ቀን ሙሉ ሲዘፍን እንደቆዬ እና “አባታችን
አይነር ነው አጥብታ ያሳደገችንም ሰስ ናት” እያሉ ታሪኳን በማስጠናት ይዘዋት ይዞሩ ነበር፤ ሰስ እንዳይገደልም የሚል አዋጅ እስከማስወጣት
እንደሰቡም ይጠቁማሉ፡፡
እንግዲህ
ይህ ሰዓት ጠላት እና ወዳጅ አርበኛው እና ባንዳው የሚለይበት ጊዜ በመሆኑ በየትኛውም ጎሳ ያለ ግለሰብ እንደግለሰቡ ልዕልና እንጂ
እንደጎሳው ጥቅል ሐሳብ ሊወከል የማይችል ውሳኔን እንዲደሚየስተላልፉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ አርበኛነትም ይሁን ባንዳነት የግለሰብ
ውሳኔ እንጂ የጎሳ መጠርያ ሊሆኑ አይቻላቸውም፡፡ ይሕ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን እያሰመሟት ከሚገኙት አንዱ ነው፡፡
የቅማንት
ሕዝብን የማንነት ጥያቄ ግራዝማች ካሰኝ አለማየሁ በእግቸራው ከጎንደር አዲስ አበባ እየተመላለሱ እንደጀመሩት ወዳጆቼ ነግረውኛል፡፡
የማንነት ጥያቄው ላይ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊጋራው እና የራሱም ጥያቄ እደሆነ አስቦ መረዳት ያስፈልገዋል፡፡ (እንዲህ ስል ይሕ ሰው
ቅማንት ነው እንዴ የሚሉ እንደማይጠፉ አልጠራጠርም)፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ቅርስ፤ ባሕል፤ ቋንቋ እና መገለጫ ሁሉ
የኔ ነው! ልጠብቀው፣ ጥብቅና ልቆምለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ችግር የሚሆንበት ብዬ የማምነው ጠያቂው አካል በሌሎች
ሕዝቦች ላይ የተበዳይነት ስሜትን አዝሎ ለጥላቻ እና ለቂም ፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኖ ብቅ ሲል ብቻ ሲሆን፤ በተጨማሪም በዳይ የሚባለው
አካልም ራሱን ነጻ ለማውጣት ችግሩን ለመፍታት ከመቅረብ ይልቅ የአፋኝነት፣ የጡንቻ እና የመለያዬት ፖለቲካን ሲያራምድ ችግሩ ተባብሶ
የጠላት ዓላማ እንዲሳካ ማድረጉን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ይሕንን ከጥልያን ያየነው ሲሆን ከታሪክ ያለመማር ችግራችን ታሪክን እየደገምን
ወደኋላ ቁልቁል እንድንንሸራተት ምክንያት እንዳይሆን የበኩላችንን መወጣት ይኖብናል!!
የማጥቃለያውን
ጭብጥ የማደርገው በመግቢያው የተጠቀሰውን ሙዚቃ በማስታወስ ይሆናል፡፡ ሙዚቃው ጥሩ ኢትዮያዊ ይዘት ያለው፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ነው፡፡
ችግሩ የሚሆነው የተዘፈነለት ዓላማ ላይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ወጣት ተሰብስቦ የሚዘፍነው በወንድሙ በእናቱ በአያቱ በአበልጁ በጎረቤቱ
ላይ የመለያትን መንፈስ ወርሶ በቂም እና በበቀል ፖለቲካ ተመርዞ ነው? ወይንስ ወንድማማችነትን፤ አብሮነትን እና አንድነትን በሚያጠነክር
መልኩ? ጥያቄው ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ ይህን የማይመልስ እንቅስቃሴ ግን ትልቅ ችግርን እንደሚያስከተልማጤን አለብን፡፡
ኢትዮጵያዊ
ቅርስ የሆውን አንድ አካል “ቅማትንኛን” ለማስተዋወቅ ለመጠበቅ፤ ለሕብረት በአንድነት መንፈስ የተቃኘ…ዜም እን እንቅስቃሴ ሁሉ
ሊደገፍ ይገባዋል!! ይሕ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል! ብዙዎች ስንሆን አንድ፤ አንድ ስንሆን ብዙ ነን! አገራችንም አንድ ስሟም ስንጠራው
የማይሰለቸው…
ኢ.ት.ዮ.ጵ..ያ
ነው!!
ተስፋ በላይነህ
ሰኔ 2009 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment