Jul 11, 2013

የይስማዕከ - "ክቡር ድንጋይ"ን እንዳነበቡኩት

“ውሻ መሪ”…ውሻ ትውልድን ይፈለፍላል…!
የፖለቲካ ትግል በአሉባልታና በመንደር ወሬ? የይስማዕከ “ክቡር ድንጋይ” ወደ ምን ሊያመራን ነው? የንጋት ኮከብስ ማን ነው?
ተስፋ በላይነህ
A DOG IS CHANGED IN TO MAN?

  የስነ ጥበብ ሰው በስነጥበብ ሥራው ሲቃዥ፤ደራሲ ተደራሲንን ጭፍግግ አድርጎ ሲይዝ፤ታዳሚ ከጥበብ ትዕይንት የድርሻውን “እውነት” “ጥበብ” እና መፍትሄ ሳይሰንቅ ከተመለሰ ወዮለት ለዛ የጥበብ ሰው!
  በደብዛዛ ልቡና፣ባልጠራ ብዕር፣ በማይተጋ መንፈስ የተተየበ የሥነ ጽሁፍ ሥራ ያስነውራል፡፡ በተለይ “ጊዜ እና እውቀት” ፈስሶበት ተብሎ ተደራሲን በጥበብ ጥም ደዌ ሲሰቅዝ ማየት የአስርት ዓመታት የኋላ ታሪካችን  አሳባቂ ነው፡፡ የአንድ አገር የሰነ-ጥበብ ሙያ ሲዋዥቅ፣ባለሙዎቹ ነጻነት ሲያጡ፣ ጥበበኞቹ በንዋይ ሲደለሉ፣ በፍርሃት ቆፈን ሲርበተበቱ፣ በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሲደቆሱ፣ ስነ-ጥበቡ “ፕሮፓጋንዳ” ሲነዛበት፣ በአሉባልታ የመንደር ውሬ ሲልመሰመስ ማየት የአንድ አገርን መዋዠቅ ቀጥተኛ አመላካች ነው! ወደ ዚህ ሃሳብ ያስገባኝ የስማዕከ ወርቁ “ክቡር ድንጋይ” የሁነቶች ልቦለድ /የሃሳቦች ልቦለድ/ ሥራ ነው፡፡ 
2013 BOOK BY THE `AUTHOR`
   
  ብላቴናው ቀላል አይደለም፡፡ 7 ሥራዎቹን በማይታመነው የእድሜው ቁጥር ጉድ አስብሏል፡፡ ኾኖም ግን ዘመኑ ትውልድን በለጋነት እየቀሰፈ፤የሰብዓዊነትን ሕልውና እያኮላሸ፤የሰውነትን ድርሻ ጥልቅ ሀይል እየቀበረ እያሽካካ ነው እንጂ ክርስቶስ በ12 ዓመቱ ስንት የአይሁድ ሊቆችን አስደምሟል? በሀገራችን የነገሱት ነገስታት በሥንት አመታቸው ታሪክ መዝገብ ውስጥ ተከትበዋል? ልጅ ተፈሪ በ13 ዓመቱ ከአባቱ ባገኘው ሥልጣን ወደ ዘውድነት የሚያመራውን ካባ ተከናንቧል፡፡ ነጋድረስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በምኒልክ ዘመን…ለገሰ ዜናዊስ “ወገኑን”አርነት ሊያበስር በ19 ዓመቱ አልተሽቀዳደም? ኧረ ስንቱ…! የሌሎችን ግለ-ታሪክ ለታሪክ መዘርዘር ለየግላችን እንተወው፡፡
      ነገር ግን በአንድ አገር ውስጥ ትኩስ “ወጣት” እያለን ሲኮላሽ ማየት ውርደት ነው፡፡ይህ ብላቴና ከተኮላሸ ትውልድ ውስጥ ገንኖ ቢወጣ ያስመሰግነዋል፡፡ መግነኑ ግን በንኖ እንዳይቀስፈው ወዮለት!
“ክቡር ድንጋ”ን እንዳነበቡኩት
በአስማት ቃላት፣ በጥቁር ውሻ እና በድንጋይ የተከበበ ሽፋን የደራሲውን ስም ይዞ ይታያል፡፡ /በአንድ የሆሊውድ ፊልም አባት ወደ ውሻነት ሲቀየር ያየሑት ፊልም ትዝ አለኝ፡፡/ ሽፋኑ በአንድነት ተሾመ ቢሰራም “ዲዛይኑ” የራሱ የደራሲው ነው፡፡ ደራሲው በዘመነኛው የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ለዚህች አገር ትልቅ ስም አለው፡፡ ይህ መኾኑም ያለንበትን ደረጃ ማሳየት የሚችል መረጃ ነው! /ያለንበት በቂ ነው አይደለም የሚለው ጥያዌ እንዳለ ሆኖ/
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 2005 ዓ.ም በግዕዝ ተጽፏል፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ቁጥር አጻጻፍ ተነስቶ የታዘብነው ውዝግብ ነበር፡፡ 2005 በግዕዝ ሲሳፍ እንዴት ነው? የመ.ይትባረክ ገሰሰን መጽሐፍት ማገላበጥ ግድ ይለናል፡፡ ለ”ክቡር ድንጋይ” መጽሐፍ ዶ/ር አድማሡ መሸሻ እና ገዛኸኝ ጸጋው ሀተታ እና ፍተታ ሰጥተዋል፡፡ ለፍተታው መልካም ንባብ! መባሉ መጀመሪያ መቅረብ የነበረበት አስተያየት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የቀረበልን መጽሐፉን አንብበን ከጨረስን በኋላ ነው፡፡
የምናምነው የምንጠራጠረውን ነው፡፡ የምትል አንዲት መጽሐፍ የሚወጣላት ዐረፍተ ነገር በገጽ5 እናነባለን፡፡ ለራሴ ብዙ ጥያቄዎችን በመስጠት አሰላሰልኩ፡፡ በህይወታችን ማንን እናምናለን? ማንን እንጠራለን? ጥርጣሬ ያለበት እምነት ዋጋ ቢስ ነው! የምንጠራጠረውን ካመንን እምነታችን ከንቱ ነው! እምነት የሰናፍጭ ታክል ብትደቅም ምልዕነቷ ግን ዝግ ነው! የቅንጣት ጠብታ ታክል ጥርጣሬ በውስጧ አታስተናግድም፡፡ የዚህ ብላቴና እምነት ግን በትልቅ ጥርጣሬ እንደተሳካች ናት፡፡ ትልቅ ጥያቄ ምልክት በገጽ 5!
የዚህ አባባል ንድፍ በገጽ 6 ላይ ቀርቧል፡፡ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን የአስማት ቃላት በሞመከር ለሚመጣው ችግር ደራሲው ተጠያቂ አይደለም፡፡ ይለናል! አቤቱ… እኛን በማጠራጠር ሊያሳምን የሚሞክር ሙከራ ነው ለማለት ዳዳሁ፡፡ የዚህ “አስማት ቃል”   ማሳሰቢያ በገጽ 169 ተደግሟል፡፡ የአስማት ቃሉን ግን ከገጽ 144 በቀር  በመጸሐፍ ውስጥ አይገኝም፡፡ ምናልባት ከመጽሐፉ ሽፋን ላይ የተጻፈውን ከሆነ? ነገር ግን ልጁ የዋዛ አይደለም… ሁለተኛ መጽሐፌን ሰረቁኝ ብሎ አስወርቷል… “ሥራዎቹ የበዓሉ ግርማ ናቸው”ን ዱብዳ ዜና …. ሌሎች ሌሎች…አሁንም በዚህ መጽሐፍ ለተደራሲያን ምክንያታዊ አክብሮት እና በስልታዊ ተዘዋዋሪ አጽንዖት እንዲታሰር ያስገድደናል…. በካፒታሊዝም ብልጠት የተነደፈ ጸሐፊ ይህ ነው ትርፉ!
ከዚህ መጽሐፍ ተምሬአለሁ፡፡ ብዙም ተማርሬያለሁ! ልብወለድ ነው? ወይስ ታሪካዊ መጽሐፍ?  መጣጥፍ? እያልኩ አነበው ጀመር፡፡ የስነ-ጥበብ ጥማቴን ለመወጣት ጊዜዬን ሰጠው… በአንድ መጽሔት የወጡ ሃሳቦች ተደገዋል… ልጁ የፖለቲካ ምሬቱን በልቦለድ ስም ይለጥፋል፡፡ አይተ ስብአት ነጋ ገጸ-ባህሪ ተሰጥቷቸው እናያለን /ገፅ 64/፡፡ ይሄ ልጅ የሰውን የፖለቲካ ጥማት በየመንደሩ የሚወራውን አሉባልታ ስብስብ ለታሪክ ምስክር እንዲሆን እየሞከረ ይኾን? ጠ/ሚኒስትሩ ከህመማቸው  ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው የዜና እወጃ ከዚያም የቀብር ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የነበረውን ጊዜ ሊያስታውሰን ይሞክራል… ክረምቱን ተገን በማድረግ የሙት አመቱን ሊያሳስበን ይሆን? እያልኩ በግድ ማንበቤን ቀጠልኩ…
በአስማት ወደ ውሻነት የተቀየረው መሪ ገጸ-ባህሪ እና ሩጫው ከደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ መሀል ኢትዮጵያ ወደ ቤተ መንግስት ይነጉዳል… በየቦታው የሚሰማውን አሉባልታ ወይንም ምሬት ከዚያም አልፎ በሀገራችን የሚታየውን የገሀድ ገፅታ ሊያሳየን ደፍሯል፡፡ ከአይሱዚ መኪኖች ፍጥነት እስከ የሴቶች መደፈር… ከሥጋ ቆራጭ አስፈሪነት እስከ ትውልድ በጫት በሲጋራና በአልኮል መነደፍ…የገዢው ቡድን (ፓርቲ) ስርዓት…..አድርባይ የ”ፓርቲው” አባላትን ያስቃኘናል፡፡ አንዳንዴም የሚነግረን ተምሳሌታዊ መረጃ ጸሐፊው ይህንንም አውቃለሁ እያለ ይመስላል፡፡
የብልግናን (ጸያፍ ቃል) በመጠቀም ድርሰቴን በመብረቅ በማጀብ አነጋጋሪነቱን ለማወጅ “ግልጽ ነኝ!” ያክል ድፍረት ነው የተሰማኝ… በገፅ 30 ላይ የተጻፈው አባባል የመጽሐፉን ይዘት በሁለት አሀዝ እንዲዋዥቅ አድርጎብኛል፡፡ እንዲሁም ከእንስሳ ጋር የሚደረግን ግንኙነት ያቀረበበት አባባል ወይም ስነ-ጥበባዊ መልዕክት እንዲሁም መፍትሄ በቂ ምላሽ አላስገኘልኝም፡፡
 ጸሐፊው የጥንቷን ኢትዮጵያ አጥብቆ ይመኛታል፡፡ የነበረንን ታላቅነት በአፈ-ታሪካዊ ሀተታ እያዋዛ ሊያስታውሰን ይዳዳል፡፡ የካፒተሊስትን አሰቃቂ ሸክም ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ለኔ ግን ራሱ ከካፒታሊስት የባሰ ጨካኝ ርዕዮተ ኣለም አራማጅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ካፒታሊዝም “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው!” አይነት የሰግብግብነት ኑፋቄ እንዳለው ሊያስተምረን ይዳዳውና ይህች አገር የምታድገው ህቡዕ ቃል (በአስማት እያለ በሚጠራው) መተት እንደሆነ ሊያሳየን ሲሞክር አይኑን አያሽም፡፡
 በገጽ 7 “የእውነቱን የማይኖር የእውነቱን የማስቅ፣ የእውነቱን የማያለቅስ ትውልድ ይህንን አስቸጋሪ ሀቅ እንዲያይ አይገደድም” ከሚል አባባል ጀምሮ ዘመኑን የሚቃኙ በርካታ ሀተታዎችን በማስቀመጡ  መልካም ሆኖ ሳል  በጸሐፊው ፍላጎት ይህ ትውልድ ወደ አስማታዊው “ጥበብ” እንዲመለስ አስማተኛ ትውልድ እንዲፈጠር ይሽቀዳደማል፡፡
ስለውሻ፣ ስለ ሰው ባሕርያት፣ የእንስሳን እና ያውን ወሲባዊ ግንኙነት፣የሰውን ሳይንሳዊ ትንታኔ፣ ስለአመጋገብ እና ታሪክ ከጎግል የቀዳው መረጃ መሆኑን ጠርጥሬለሁ፡፡ የ“ዣንቶዣራ” ዓይነት አፃፃፍ አሳይቶናል፡፡ በዣንቶዣራ ውስጥ ስለ ፍሪሜስን፣ቴምፕላርስ፣ አሉሚናቲ ታሪካዊ አመጣጣቸው እና ምልክቶቻቸውን የጎግል ፍብርኮች ነበሩ፡፡ ሰውየው ዓለሙን ሁሉ ልብ-ወለድ አድርጎ፤ምትሃታዊ ትውልድ ፈጥሮ ፈሪ ጸሐፊያንን አበራክቶ አዋቂነቱን በልቦለድ መድረክ ማቅረብ መፈለጉ ምን ነካው አስብሎኛል? እባክህ ተገለጥልኝ!
ቻይናዊያን ስለ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አመለካከት አሳይቶናል፡፡ በገጽ 33 ያ ቻይናዊ የኢትዮጵያኖችን የስራ ጥላቻ ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ስራ ወዳድ ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ተብለን ስንጠየቅ ምላሹ ሊቀርብልን ይገባ ነበር፡፡ ገበሬው አመቱን ሙሉ አስቦ፣ ዝናብ ጠብቆ፣ ክረምቷን አርሶ፣ አርሞ፣ ጸሉቶ የሚያገኛትን እህል ላልዘራው እና ላላረሰው ወስዶ ሲገብር ምን ያህል ተስፋው አይታጨድ? ምን ያህል በስራው አይለግም? ዛሬ ልደታ፣  ነገ አቦ ከዛም ስም እየጠራ ስራን ማቅለሉ ታይቶን ይሆን? አሁንም ሴቷ መራዛማ አመድ ተነስንሶባት፣ ቀኑን ሙሉ ከአህያ ሳትተናነስ ስትሸከም ውላ ክብሯን እያጣች የምታገኘውን ገቢ ለአንድ ቀን ምሳ አጠራጣሪ እየሆነባት “ያለችበት አግባብ” እያለ እንዴት በስራ አትለግም? ፈረሱ ተላልጦ  ተሸክሞ፤ መሪውን እና ጋሪውን እየጎተተ  እየታየ ያለው  የማን ህዝብ ነው?  /በገጽ 50 የተገለጸውን ተምሳሌታዊ አቀራረብ አድንቄዋለሁ/
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እለተ ዕረፍታቸው ከታወጀበት ቀን አንስቶ እስከ ቀብራቸው የነበረው ጊዜ ስንት ቀን ነበር? በገጽ 3 ሀተታ ላይ “ይስማዕከ በተፈጥሮ በተለገሰው ክህሎት ሲፈልግ አንዱን ሴኮንድ የዘላለምን ያህል ያረዝመዋል፤ሲያሻው ዘመንን ጠቅልሎ በአንዲት ሰኮንድ ውሥጥ ይከተዋል” በማለት አምልኮታዊ ስብዕናን ያለብሰው አሰትያዬት ሰጪ… ነሐሴ 2004 ግን ለኢትዮጵያ ዝንት አለም አልነበረችምን? በዚህ መጽሐፍ ላይ ግን በሩጫ ታልፋለች! ደራሲው ወደ ገጽ 191 ለመድረስ ነካ ነካ አድርጎ አልፏታል፡፡ ነካ ነካ ያደረጋት እንደው ፖለቲካዊ ለዛ ለማሳደር እንጂ ሌላው አልመስልህ አለኝ..!
ከዚህ መጽሀፍ ምን እንረዳ? የኋላን ታሪክ አንድንማርበት፣ ኢትዮጵያ በመሪዎቿ እንደዋዠቀች፣ ጥቂቶች የሚያወሩባት የሚመራመሩባት ሀገር እንዳለችን፣ የተደበቀ ጥበብ እንዳለ፣ ከህይወት መማር እንዳለብን የሚጠቁሙ አንቀጾች አሉት፡፡ በገጽ 41  የተጠቀሰቸውን አባባል  እንዳለ   ላቅርባት፡፡
“ህይወት እንደ ካርቱን ፊልም ቀለም ዘቅም በሰጣቸው ስዕሎች ተንቀሳቃሽነት ጀብድ የሚፊጸምባት የህልም አለም አይደለችም፡፡ ለመሄድ የራስን ቋንጃ፣ ለመዞር የራስህ ጋንጃ፣ ለመወሰን የራስን ፍርጃ፣ ለመንዳት የራስን አቅም፣ ፍሬን ለመያዝ የራስን ቅልጥም ትጠይቃለች” ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን ካልክ ለምን ሙሉ በሙሉ አድናቆትህን ችረህ አትዘጋም እዳትሉኝ፡፡ ልጁ እኮ የ“ዴርቶጋዳ” ጸሓፊ ነው! ሰው እየደገ ሲመጣ፤ እየተሻሻለ ይሄዳል፣ የበለጠ ይጠነክራል የበለጠ ያይላል እንጂ…. ይደበዝዛል?  መጽሐፍ በሽያጭ ብዛት ፣በገጽ ብዛት ብቻ አይደነቅም፡፡ ምን ተማርኩ? ምን አሳየኝ? ምን የማላውቀውን አስተማረኝ? ምን ለወጠኝ? ምን አንዳስብ አደረገኝ? ምን ጭብጥ አገኘሁበት ተብሎ ይመዘናል…! በቅዠት ብቻ ተለውሶ የሚወራጭ ከኾነ በእኔ እምነት መጽሐፍ ነው ብዬ መጥራት ያዳግተኛል፡፡ ዝና ሊገኝ ይችላል፤ ስምም ሊስፋፋ ይችላል፤ ገንዘብም ሊከማች ይችላል ነገር ግን ሰውን  ወደ ተሻለ ስብዕና መቀየር ካልተቻለ የጥበብ ትልቁን ትርጉም ያመክነዋል፡፡
በክቡር ድንጋይ ውስጥ አስማተኛ እንድንኾን…ሀገራችን “የንጋት ኮከብን” መተት እንድትከተል ጸሐፊው ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ የባዕዳን ርዕዮተአለም ፍልስፍናዎችን ማለትም ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ታላቅ ክቡር ተብሎ በተገጸው ቃል አማካኝነት አስማታዊ ሃይልን ይዘን እንድናድግ ይወተውተናል፡፡ ለመኾኑ የንጋት ኮከብ ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የንጋት ኮከብ ተብሎ የተሰየመው የዳዊት ዘር ስር እየሱስ ክርስቶስ ነው! /ራዕይ 21/ ኾኖም ዲያቢሎስንም በንጋት አጥቢያ ኮከብ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡/ኢሳ 14/ ፡፡ በዚህ ደራሲ አገላለጽ የንጋት ኮከብ ማን እንደኾነ የግላችንን መላምት ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ከሰውነት ተርታ ወደ ውሻነት ከዚያም ወደ ዘንዶነት እንዲሁም ወደ ፈለግነው ፍጥረት እንድንለወጥ የሚያደርገን የአስማት “ጥበብ” ከዲያቢሎስ እንጂ ከክርስቶስ እንደማይኾን እንተማመናለን፡፡ በአስማት ሃይል ምጣኔ ሃብት ይደግ፤ ሀገርም ትልማ ቢባል ከካፒታሊስቶቹ ፍልስፍና በምን ተለዬ? “የክቡር ድንጋይ” ደራሲ ግን ለዚህች ሀገር ከካፒታሊስቶቹ በተለዬ በአስማታዊ ጥበብ ሊገዛት ይፍጨረጨራል… የባሰ አታምጣ! የህንጻ ጥበብ አስማት ከተባለ የሰለሞን ጥበብ ከምን ሊመደብ ይችላል? በዲያቢሎስ ተመርቶ መኖር እና ዲያቢሎስን መርቶ ገዝቶ መኖር አንድ አይደሉም፡፡ /ሰለሞን አጋንንትን ገዝቷል/
ውሻው ወደ ቤተ-መንግስት ይሮጣል… ጉዞው  ቤተ-መንግስት ላይ አይፈጸምም፡፡ የውሻው ሩጫ ወደ ባለቤቱና ወደልጆቹ ይቀለበሳል፡፡ በአስማታዊ ሃይልም ከውሻነት ወደ ዘንዶነት ይለወጣል… “በንጋት ኮከቡም” መሪነት ወደ “ሰውነት” ይቀየራል፡፡ ባለቤቱን እና የቀድሞ ጓደኛውን በምሕረት ይሸኛቸዋል… “ለባዶ ሰው በቀል ትርጉም የለውምና… ያለውን ሀተታ በሙሉ ለአንባቢያን በመተው
ልጆቹንና መጽሐፍቱን ይዞ ይሄዳል… መጽሐፍት እና ልጆች ትልቅ ሐብት ናቸው፡፡ እውነት ነው፡፡ የመጽሐፍቱ ይዘት ግን ሊመረመር ይገባል… አጥፊም አልሚም መጽሐፍት አሉና!

ሰው ወደ ውሻነት እየተቀየረ ነው….ሰው ወደ አውሬነት እየተለወጠ ነው… ይህ ደግሞ የኾነው “በመሪዎቻችን” ውሻነት ነው…! ጸሐፊያን መሪዎቻችን ናቸው! “ውሻ መሪ እና ውሻ ትውልድ ቀስ በቀስ ይታያሉ…! ይስማዕከ ከውሻነት ወደ ሰውነት እንድንቀየር አጥብቆ ወትውቶናል፡፡ ሰው ከኾን በኋላ ግን ምን አይነት ሰው እንደምንኾን የወሰደው አማራጭ የሚያስተዛዝብ ነው…. መጽሐፉን ያንበንቡት እና የግልዎን ድምዳሜ ይያዙ፡፡   

No comments: