የኢትዮጵያዊያንን አዲስ ትውልድ ማንነት ያየንበት ትዕይንት!
በተስፋ በላይነህ
“No I don’t want to talk about my relationship has
affected my country, either way I will still continue to see bolt” ቤቲ
የኢትዮጵያ አዲስ ትውልድ ከጣልያን 5 ዓመት ወረራ በኋላ በተደረገው የትምህርት
መስፋፋት ጋር የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ በተለይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት መከፈት ተማሪው የለውጥ አብዮት እንዲስፋፋ በር
ከፋች ነበር፡፡
በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አመለካከት ከ1950 ዎቹና 60 ዎቹ ትውልድ የነበረው ትኩስ አገራዊ ስሜት ሊደገም አልተቻለም፡፡
በአገራዊ ማንነት፤ ባህል እና እውቀትን በማጣመር ለአገራቸው ቅድሚያ በመስጠት ታግለዋል፡፡ ይህ ትውልድ በእርስ በርስ የፖለቲካ
ቆሻሻ ጨዋታ በጫካ አልቋል፤ በጠበንጃ ተደፍቷል፤ ከአገር ተሰዷል፤ ወኔውን ወደ እትብቱ ቀብሮታል፡፡ የትውልድ ሽግግር ሲካሄድ መሃል
ላይ አያያዥ ሊሆን የቻለ አንድ ትውልድ ባለመኖሩ ከ70 ዎቹ እና ሰማንዎቹ ትውልድ የተፈጠረው በተጭበረበረ ኢትዮጵያዊነት ይመስለኛል፡፡
ምንም አይነት የተሳካለት ትውልድ አልተፈጠረም ማለት ሳይኾን በይበልጥ በተፈጠረው የአለም ወደ አንድ መንደርነት መተሳሰር ሌላው
ትልቅ ገጽታ መታየቱን በማሰብ ነው፡፡
የዚህኛውን ትውልድ ማንነት ትንተና ለመስጠት በጣም እንቸገር ይሆናል፡፡ ሆኖም
አጠቃላይ መግለጫ ለመስጠት ያክል ይህ ትውልድ ከዛኛው ትውልድ ያለው ንቃተ ህሊና የተሻለ ነው፡፡ የዚህኛው ትውልድ ከዛኛው ትውልድ
በበለጠ የአለሙን ስርዓት ተቆራኝቶታል፡፡ /በስፋት ተሻሽሎ የተሰራጨው የመረጃ ዘመን በራሱ ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ሳንዘነጋ፡፡/
በዛ ዘመን የነበረው ትውልድ አንባቢ ነው፤ ወደ ዘመናዊው የአለም አዲስ ስርዓት በቅርብ ስላልተሳሰረ ባህሉንና እምነቱን እንዲሁም
ማንነቱን አልተወም፡፡ ለቤተሰቡ መታዘዝ፤ ወገኑን ማገልገል፤ አገሩን ማስቀደም በደሙ ውስጥ የነበረ ትውልድ ነው፡፡ አዚህ ላይ አገርን ማስቀደም የሚለው ነጥብ እንዲሰመርበት፡፡
ዘመናዊነት የንቃተ ሕሊና ለውጥ፤ የአስተሳሰብ እድገት ከሆነ ልንቀበለው እንገደዳለን፡፡
ነገር ግን የንቃተ ህሊና መሻሻል ራስ ወደዳድነት፤ ብልጠት፤ ተንኮልን መቀበል እንዲሁም ማንነትን መርሳት፤ ባህልን መግደል ከሆነ
ግን በእጅጉን ያስተዛዝባል፡፡ እነዚህ ለውጦች ደግሞ ከዛኛው ትውልድ ይልቅ በዚህኛው ትውልድ በይበልጥ ይንጸባረቃሉ፡፡ ይህኛው ትውልድ
በሰባዎቹ የተወለደ ነው፡፡ ትውልድ ይተካካል፤ ትውልድ ይለዋወጣል…
የዚህን ትውልድ ማንነት ለመገንዘብ በየዩኒቨረሲቲዎቻችን አና ትምህርት ቤቶቻችን
ላይ ማየት በቂ ነው፡፡ የስነ-ጥበቡንም እድገት መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡ ንቁ የኾነ ዜጋ ነበረን ነገር ግን ይህ ንቃተ ህሊና
በፍጥነት እየተሸሻለ ቢሄድም በከፍተኛ ለውጥ እየተፈጠረ የሚገኘው ትውልድ ግን ባህሉን የዘነጋ፤ ማንነቱ የተጭበረበረበት፤ ራስ ወዳድነት
የራስ ፍላጎትና አስተሳሰብ ከማንም ቀድሞ የታየበት በዚህ ትውልድ እና በዚህ ባለንበት የአለም ስርዓት ነው፡፡ ሳይንሳዊ ግለሰባዊነት
በአለማችን ላይ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ሳይንሳዊ ግለሰባዊነት የሚባለው አንድ ሰው ከማንኛውም ውጫዊ ነገር ራሱን ማስቀደም፤ ለራስ
ጥቅም ብቻ የፈለገውን የመሰለውን ማድረግ ነው፡፡
ይህ አይነት ግለሰባዊነት ለቤተሰብ፤ ለወገን ወይንም ለባህልና ለሃይማኖት
እንዲሁም ለአገር የሚከፈሉ መስዋዕቶች የሚመጡት ከራስ ጥቅምና ፍላጎት በኋላ ይሆናል፡፡ ይህ የአዲሱ ዓለም ስርዓት ነው፡፡ ኢትዮጵያም
ከዚህ ዓለም ስርዓት ውስጥ ከኾነች ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ኾኗል፡፡ በተለይ ከ66ቱ አብዮት አና ከ83ቱ የመንግሰት ለውጥ የጥንቷን
ኢትዮጵያ ማግኘት ‹‹ከጸጉር ምላስ እንደመፈለግ›› እየተቆጠረ ነው፡፡ ከ1980ዎቹ ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አለሙ ስርዓት ተቀላቅለናል፡፡
ከ‹‹ኬጂ›› ትውልድ እስከ የከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎቻችን ከኢትዮጵያ ስልጣኔ ይልቅ የምዕራባዊውን የእለት ተለት እንቅስቃሴ
ይከታተላል፡፡
በዚህ ትውልድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተንኮታኩተዋል፡፡ የምዕራባዊያኑንም
ሆነ የሩቅ ምስራቁን ባህል ወይንም ስልጣኔ ተገድደን ተሸክመናል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ወይንም የአንድ አገር ዜጋ ለሄደበት አገር
እንደ ተወካይ/ አምባሳደር/ ነው፡፡ አገሩ በብሔራዊ ደረጃ ወከለችውም አልወከለችውም በራሱ በተፈጥሮው የተወከለ ነው፡፡ የያዘው
የማለፊያ መታወቂያ /ፓስፖርት/ ህጋዊ ከለላ የሚያስገኝለት፤ ለክፉም ለመልካምም ይዞት የወከለው ማንነቱ መገለጫ ነው፡፡ በድሮው
ስርዓት ለነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ /ምንመ እንኳ ኢትዮጵያኖች ስደት ጀመሩት ከ66ቱ አብዮት ወዲህ ቢኾንም/ በየትኛውም ቦታ የሚገኝ
ኢትዮጵያዊ ከራሱ በማስቀደም ኢትዮጵያን ያስብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አገሩ ብቻ ሳትኾን እናቱ ነበረች፣ እህቱ፣ ሚስቱ፣ ልብሱ፣ ማንነቱም
ጭምር! ምክንያቱም ሌላ የሚያውቃት አገር አልነበረችውም፡፡ አገሩ በደሙና በአጥንቱ ተሰብካለች፡፡ ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ ኢትዮጵያኖች
በሄዱበት አገር ኾነው የአገራቸውን ስም እና ጥቅም ለማስጠበቅ ይተጋሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚያውቁት አገር አልነበረምና! ዘመን
ዘመንን ሲተካ፤ የአለሙ ትስስር ሲጨምር ‹‹ዘመናዊነት›› ሲስፋፋ፤ ንቃተ ህሊና ሲጨምር ሰው ‹‹ግለሰባዊነቱ›› እያየለ ስለሚሄድ
አገሩን መጥላት ባይችልም አገሩን ከራሱ ጥቅም ማስቀደሙ ግን ይከስማል፡፡ “መጀመሪያ መቀመጫዬን” አለች ጦጢት እንዲሉ መጀመሪያ
የራስን ጥቅም ማስቀደም ‹‹ግዴታ›› የምንኾንበት ስርዓት ሰለጠነ፡፡ ለራሴ ጥቅም እና ፍላጎት ስል ብቻ አገር፣ ቤተሰብ፣ ባህል
ምንም ጫና አያሳድሩም፡፡ መጀመሪያ ‹‹እኔ›› ይቀድማል፡፡ አሁን ባለንበት ስርዓት ‹‹እኔ›› የምትባለዋ ግዛት ከማንም በላይ ‹‹መሪ›› ከማንም በላይ ‹‹አዋቂ›› ከምንም በላይ ተጠቃሚ እንድትኾንልን ተደርገን እየተቀረጽን ነው፡፡ ለእኔነት ብሎ አገሩን የሚሸጥ
‹‹ባንዳ›› ይባላል፡፡ ባንዳነት ምን ያክል የሚያሳፋር ተግባር መኾኑን ለመገንዘብ ታሪክ ማወቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ
ሰዓት ሰንቶቻችን ‹‹እኔነታችንን›› ከባህል፣ ከቤሰተብ፣ ከሃይማኖት አስበልጠን አየሸጥን ነው? በአገር ውስጥም ኾነ በባዕድ አገር
ኾነን ስንቶቻችን ለአገር ክብር ‹‹እኛነታችንን›› አስከትለናል? የራስ ጥቅም፣ ፍላጎት ወይንም አስተሳሰብ ምን ያህል ከአገር በልጦብናል?
በዚህ አለም ስርዓት ለሌሎች መኖር የሚባለው ትምህርት የሞኝ ተረት ከኾነ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የራስ ማንነት ከሌሎች በላይ ረዝሞ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ፣ ለአካባቢ ስርዓት ሲገዛ
አሊያም ለእነዚህ ምክንያቶችም ጭምር መኖር አላማን ሲያራምድ ሰብዓዊነት
ትርጓሜ ይኖረዋል፡፡ ክብር ያሰጣል፣ ኩራት ይኾናል፣ ገንዘብ ርስት ኾኖ የሚያገለግልበት ጊዜም ይመጣል፡፡ ገንዘብ ከራስ በላይ፤
ከአገር በላይ ራስ ጥቅም ከሁሉም በላይ ኾኖ ሲገኝ ግን ወደ ሳይንሳዊ ግለሰባዊነት እንሸጋገራለን፡፡
ሌሎችን ሳይጎዱ መኖር አንድ አማራጭ ነው፡፡ የራስ ፍልስፍና አብዛኛውን ማህበረሰብ
የሚያስከፋ ከኾነ፤ ቤተሰብን የሚያሳዝን፤ ባህልንና እምነትን የሚያናጋ ሲኾን ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ በአሁኑ ሰዓት
የሚገኘው ትውልድ ወደድንም ተገደድንም በዚህ አይነት በ‹‹እኔነት ስልጣኔ›› ተጽዕኖ ስር ተደቁሰናል፡፡ አውቀነውም ይኹን ሳናውቅ
በህልማችን እና በእውናችን እኔነትን ማስቀደም የኑሮ መርህ ነው፡፡ ሁሉም ‹‹እኔ›› ‹‹እኔ›› ይላል! የቻለው ሌሎችን አድቅቆ
እኔነቱን ያፋፋል፡፡ እኔ ብቻ ልብላ እኔ ብቻ ልኑር ነው ስርዓቱ… ይህ ዓይነቱ የአስተሳሰብ ቀንበር በላያችን ላይ ተጠምዷል፡፡
ይህ ኹሉ ሐተታ የሚያመራን በዚህ ወር የሰማነው የ‹‹ቢግ ብራዘር አፍሪካ››
የትዕይንተ መስኮት የቀጥታ ዝግጅት ወሬ ነው፡፡ ብዙዎቻችን በስሜት ተነጋግረንበታል፡፡ በስሜት ፍርድ ወስነንበታል፡፡ ከተደረገው
ስራ አንጻር ስሜታዊ ባንኾን ይገርመኝ ነበር፡፡ ወደድንም ጠላንም ደግሞ ምንም ያክል በአለሙ ስርዓት እየደበዘዝን ብንሄድም ያቺ
ማንነታችን አትለቀንም፡፡ ‹‹ያቺ ጭዋነት›› ‹‹ያቺ ኩራት›› ‹‹ያቺው ባህል›› ‹‹ያቺ ኢትዮጵያዊነት!›› አትተወንም፡፡ ልትለቅ
ብትሞክርም ከነጭራሹ አልተወገደችም፡፡ ልትተወንም ብትዳዳም ሙሉ በሙሉ ‹‹አልቦ ኢትዮጵያዊነት›› አልተደነገገም፡፡ ከኢትዮጵያዊነት
ለመላቀቅ ገና ይቀረናል፡፡ ወደ ‹‹ኢ-ኢትዮጵዊነት›› የምናደርገው ጉዞ በሁለት አኃዝ እያሻቀበ ነው፡፡ ኾኖም ግን ኢትዮጵያዊነት
ፈጽሞ አልጠፋም፡፡
ቤቲ ግን በጣም ጠንካራ ፍጡር ነች! ቤቲ ግን ደግሞ በጣም ደካማ ሰው ነች!
ይህን ስል በፈራጅ ወንበር ላይ ተቀምጬ ፍርድ እንዳልሰጥ እየሰጋሁ ነው፡፡ በሰው እንደ መፍረድ የሚያስኮንን ኩነኔ የለም፡፡ እኔ
ማን ነኝና? ደግሞም በቤቲ ላይ የድንጋይ መዓት የማዘንብስ፤ የመወገርን ትዕዛዝ የምፎክርስ እኔ ማነኝ? የመቅደላዊት ማርያምን ታሪክ
ያስታውሷል! ይህም ጽሑፍ ስለቤቲ ፍርድ ብይን መዘገብ ሳይኾን ልናስታውስ የሚገባው ነገር ከቤቲ ጀርባ የመሸጉትን ሚስጥራዊ ማህበራት
ሴራ ለማስገንዘብ ነው፡፡ የቤቲ ግለሰባዊ ማንነት፣ የቤቲ ግለሰባዊ አስተሳሰብ እንዲሁም ግለሰባዊ ነጻነት እንደተጠበቀ ኾኖ አገራችን
ወደ ምን አቅጣጫ እና ወደ የትኛው አለማዊ ስርዓት እየተመራች እንዳለች አመላካች መግባቢያ ሃሳብ ለማስተላለፍ ነው፡፡ ነገር ግን
ይህን አይነት ድርጊት ለመፈጸም ትልቅ ‹‹ጥንካሬ›› ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ የግል አቋምን ይጠይቃል! እንዲህ አይነቱን ድርጊት
ለመፈጸም ሽምጥጥ አድርገን ከእኛነት ውጭ ያሉትን አካላት የምንክድ ሲኾን ነው፡፡ ኾኖም ግን
ይህ አይነት ውሳኔ የተንጸባረቀው ለበጎ ተግባር በሚውል ድርጊት አልነበረም!
ኦ ቤቲ ግን እንዴት? ግን ለምን? አንድ ስህተት ሊኾን ይችላል! 4 ጊዜ ሽምጠጣ ግን …. ያውም ከ28 ቀናት ላላለፈ ቆይታ…!?
ይህች ልጅ
‹‹በተወዳደረችበት›› መድረክ በዝግጅቱ ዋና መርህ መፈክር መሰረት ‹‹ራሷን ኾና›› ተገኝታለች፡፡ ጨዋታው ዋነኛ መስፈርት ራስን
ኾኖ መቅረብ ነውና! የራስን ማንነት ይዞ መኖርን እና ይህ ማንነታችን በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትን ሲያገኝ ‹‹ለውድድሩ ብቁ›› እንሆናለን፡፡
በሶስት ወር ቆይታ ውስጥ ከውጨኛው ዓለም መስተጋብር ተገልለን በአንድ ቤት ውስጥ ታጉሮ መቆየት፡፡ በየጊዜው በሚደረገው ህዝብ ምርጫ
‹‹ኢቪክሽን›› ውስጥ በመግባት /ተገልሎ በመቆየት/ ወደዚህ ክፍል የተለዩ ‹‹ተወዳዳሪዎች›› ‹‹ከውድድሩ›› ውጭ የመኾን ድርሻቸው
ከፍተኛ ነው፡፡ የዕለት ተዕለት መዝገብም አለ ‹‹ዲያሪ››፡፡ የዚህም መዝገብ ንግግር ‹‹ለውድድሩ›› ስንቅ ኾኖ ከማገልገልገሉም
ባሻገር የማንነት መገለጫ መድረክም ኾኖ ያገለግላል፡፡ በየቀኑ የሚደረገው የግለሰቦች ትርዒት በቀጥታ ‹‹ሃያ አራት ሰባት››
24/7 ይተላለፋል፡፡ እያንዳንዱ ‹‹ሀውስሜት›› በዚህ አካሄድ ይወዳደራል፡፡ ብቸኛ ተመራጭ ኾኖ የቀረ ‹‹ተወዳዳሪ›› ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይሰጠዋል፡፡ /ከ5ሚለዮን ብር በላይ/
የዚህ ዝግጅት ሃሳብ
ከጆርጅ ኦርዌል 1984 ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ ነው፡፡
big brother is watching you /ወንድም ጋሼ እየተመለከተህ ነው!/ ብለን እንተርጉመው፡፡/ግደይ ገብረ ኪዳን በግሉ
ጡመራ እንዳቀረበልን/፡፡
ይህ መጽሐፍ እ.ኤ.አ 1949 ዓ.ም የተጻፈ ነው፡፡ በተምሳሌታዊ አጻጻፍ የቀረበው ይህ መጽሐፍ ዊኒስተን ስሚዝ በተባለ ዋና ገጸ-ባሕርይ
አማካኝነት ቢግ ብራዘር በሚባል ምናባዊ መሪ ይተዳደራል፡፡ war is peace, freedom is slavery, ignorane
is strength በሚሉ ሶስት መፈክሮች ይመራል፡፡ ዊንስተን ስሚዝ የታላቁን መሪ መፈክር በመያዝ ተግቶ ሚሰራ ታማኝ ባለሟል ነው፡፡
ሁሉም ነገር ግን ከመሪው ከ‹‹ቢግ ብራዘር›› እይታ ውጭ መኾን አይቻለውም፡፡ ቢግ ብራዘር የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የራሱን
ሃይል ያስፋፋል፡፡ ‹‹ቢግ ብራዘር›› በየቦታው ነው! ‹‹ቢግ ብራዘር›› የሁሉም ነገር ምንጭ ነው፡፡ ህዝብ በ‹‹ቢግ ብራዘር››
ርዮተ ዓለም ውስጥ በግድ እና ያለምንም ምርጫ በበላይነት ሲጨቆን ይኖራል፡፡ ቋንቋ እና መገናኛ ብዙኃንን እንደዋነኛ መሳሪያ በመጠቀም
በተጋገነነ ስብከት/propaganda/ አእምሮአቸውን ይቆጣጠረዋል፡፡ ህዝቡ ምንም አይነት መረጃ መያዝ አይቻለውም፡፡ እንደ ፎቶግራፍ፣
ጽሑፍ፣ ዘመናዊ መረጃን የሚመዘግቡ መሳሪዎች አይፈቀድላቸውም፡፡ ያለፈ ታሪክ የለም! ‹‹ቢግ ብራዘር›› ያለፈውን ታሪክ በራሱ መዝገብ
ይመዘግባል፡፡ ይህን ኹሉ የሚመራው እና የሚመዘግበው ዊኒስተን ሰሚዝ ነው፡፡ ዊኒስተን ስሚዝ ግን ይህንን ስርዓት አጥብቆ አይደግፈውም፡፡
ከፍተኛ ጥላቻ አለበት!
መጽሐፉ በአለም ዘንድ በብዛት ተነብቧል፡፡ የ‹‹ኮሚውኒዝምን›› እና ቅኝ
ግዛትን አካሄድ ለማሳየት የተሞከረ ሃሳብ አለው፡፡ ከዚም በላይ መንግስታት ህዝብን እንዴት እንደሚገዙ በጉልህ ያስተምረናል፡፡
ይህንን መጽሐፍ መሰረት በማድረግ በሆላንድ ወደ ምትሃተ መስኮት ዝግጅት
መተላለፍ ተጀመረ፡፡ አዘጋጆቹ ይህንን ዝግጅት በመላው ዓለም ማስተላለፍ ጀመሩ፡፡ ቢግ ብራዘር አፍሪካም የአህጉራችንን ውክልና በመያዝ
ከተለያዩ አገራት የምርጫ መስፈርቱን የሚያሟሉ ‹‹ተወዳዳሪዎችን›› ይዞ ያቀርባል፡፡ የመጽሐፉን እና የስርጭቱን ዝግጅት መረጃ ለየግላችን
በመተው ወደ ዋናው የግሌ ሃሳብ አመራለሁ፡፡
አለምን አየመሯት የሚገኙ ጥቂት ቡድናት እንዳሉ ልንገነዘብ የሚያስፈልግበት
ጊዜ ነው፡፡ የምናየው አለም ስርዓት በተወሰኑ ሰዎች ውጥን ሴራ እና አላማ ይተዳደራል፡፡ የሰውን ልጅ ከተፈጥሮአዊ ማንነቱ እና
ለተፈጠረበት አላማው እንዳይኖር የሚያደርጉ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ውስጥ የካበተ ገንዘብ ያካብታሉ፡፡ ዋና ዋና የአገራት መንግስታትን
ተቆጣጥረዋል፡፡ ታዋቂ የለውጥ ሰዎችን መጠቀሚያ ያደርጋሉ፡፡ በመገናኛ አውታር፣ በታላላቅ አለም አቀፋዊ ድርጅቶች በየሙዚቃው በሌሎችም
ትዕይንቶች ውስጥ እጃቸው አለ፡፡ መሪያቸው ግን ዲያቢሎስ ነው! ጦርነት፣ በሽታ፣ የምጣኔ ሐብት ቀውስ ሁሉም በእጃቸው ነው፡፡ ዘመናዊ
መሳሪዎችን፣ የስልጣኔ መገለጫዎችን ያመርታሉ፡፡ አሳማኝ በሚመስሉ ምክንያቶች በየጊዜው ይቀርቡልናል፡፡ የአለምን ሐብት ግን በጥቂቶች
እጅ ነው፡፡ ዋናው ዓላማቸው ሰውን ከተፈጥሮአዊ ማንነቱ እና ሥጦታው በማራቅ ወደ ጥልቁ መወርወር ነው፡፡ አለም አንድ እንድትኾን
ይፈለጋል፡፡ መሪው የሚፈልገውን ለማድረግ የሚቸግረው ነገር የለም፡፡ በተለይ ስሜታዊ የተፈጥሮ ባሕርያትን በመጠቀም፤ ገንዘብን እንደ
ትልቅ መሰረታዊ ዓላማ በማድረግ፤ መንፈሳዊነትን በማቀጨጭ፤ ባህልን፣ እምነትን እንዲሁም አገራዊ መገለጫን በማጥፋት ሴራቸውን ሴራሉ፤
ስራቸውን ያሰራሉ፡፡ /ስለ ሚስጥራዊ ቡድናት ማንነት፣ አመሰራረት እንዲሁም ዓላማ ማወቅ ከፈለጉ የተክሉ አስኳሉን እና የግደይ ገብረኪዳንን
‹‹ህልም አጨናጋፊዎቹ›› መጽሐፍ እንዲሁም ጡመራ ቢከታተሉ በበለጠ
ይረዳሉ፡፡/
እንግዲህ ያለነው በዚህ የአለም ስርዓት በመኾኑ፤ ከዚህ ዓለም ስርዓት ተጽዕኖ
ለመላቀቅ ቀላል አይደለም፡፡ አስበነውም ኾነ ሳናስብ በዚህ ወጥመድ ስር ኾነን እንገኛለን፡፡ ባሕል፣ ሃይማኖት አና አገራዊ ስሜት
ለዚህ አለም ስርዓት ተፈላጊ አይደሉም፡፡ አገርን ማስቀደም አይፈለግም፡፡ ከማንም በላይ የራስ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ይደመጣሉ፡፡
በአገራችንም ይህንን አይነት ማንነት በዚህ ትውልድ እየታዘብነው ነው፡፡ አገር
ተረካቢ የሚባለው ትውልድ፤ የአገሪቱን የተማረ ሃይል የሚባለው ‹‹ከተሜ››፤ ከ8 በመቶ በላይ የኾነውን ህዝብ ይለውጣል የተባለው
ሃይል ‹‹በራስ ወዳድነት›› አስተሳሰብ ከዛም አልፎ በባዕድ አመለካከት ሲወረር እጅግ የሚያሳስብ ነገር ነው፡፡
በቤቲ ብዙ ልንማር ይገባል! በአሁኑ ሰዓት ስንት አይነት ቤቲ መሰል ስብዕና
የተላበሱ ሰዎች ተፈጥረዋል? ከዚህስ በኋላ ስንቶች ይፈጥራሉ? በባዕድ አስተሳሰብ ብቻ የተቀረጸ ትውልድ ይዞ ኢትዮጵያዊነትን ማሰብ
መቀለድ ነው፡፡ ቤቲ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊነትን ወክላ ‹‹በውድድሩ›› አልቀረበችም፡፡ ኾኖም ግን ከእያንዳንዳችን ስብዕና ውስጥ
የአገር ህልውና ቢታሰብበት እንደማይጎዳ ልንግባባ እንችላለን፡፡ የባህል፣የቤሰተብን እንዲሁም የሃይማኖት እሴቶቻችን ባይጠፉ ይመከራል፡፡
ሰው እንስሳ አይደለም! እነዚህ ምስጢራዊ ቡድናት እንስሳ እንድንኾን ይፈልጋሉ፡፡ በቤቲ ተግባር በበለጠ ልንማር የሚገባን ከዚህ
አይነቱ የአለም ስርዓት እንድላቅ እና ለአገር ለወገን እንዲሁም ለቤተሰብ ዋጋ በማሰጠት ራሳችንን እንድናስከብር ነው፡፡ ይህ ካልኾነ
ግን ከዚህም በላይ ጉድ ማየታችን አይቀርም፡፡ እድሉን ስላላገኙ ነው እንጂ ከቤቲ በላይ አነጋጋሪ ነገር የሚፈጽም ትውልድ እንደ
“አሸን ፈልቷል”፡፡ መንግስት ትልቅ ሃላፊነቱን ውሰዶ ሊሰራ ይገባል፡፡ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶቻችን እና የስነ-ጥበብ ስራዎቻችን
በተለየ መልኩ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ብዙ ወጣት እያጣን ነው! አንድ ትውልድም እየጠፋ ነው!
ቤቲ ከ‹‹ውድድሩ›› ተሰናብታለች፡፡ በነበራት ቆይታ የአቅሟን እንደሞከረች፣
አሸናፊም እንደኾነች ታስባለች፡፡ ይህንን ያክል በመቆየቷም በራሷም እንደምትኮራ ገልጻለች፡፡ በፈጸመችው ድርጊት የአገሯ ሰዎች በጣም
እንደተበሳጩ እና የሷ አመለካከት ምን እንደኾነ ስትጠየቅ “no I don’t want to talk about my
relationship has affected my country, either way I will still continue to see
bolt” /“የኔና የቦልት ግንኙነት አገሬን ምን ያክል እንደጎዳ ማውራት አልፈልግም ከቦልት ጋር ያለኝን ግንኙነት ግን እቀጥላለሁ”/
ነበር ያለቸው፡፡ /ትርጉም የራሴ ነው/፡፡ ከውድድሩ ከተሰናበተች
በኋላ ቦልት ከሌላኛዋ ‹‹ተወዳዳሪ›› ጋር ሲዳራ ታይቷል፡፡
ሚስጥራዊ ቡድናት በተለያዩ ምልክቶች ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል የፒራሚድ ቅርጽ፣
በጸሐይ፣ ባለ አምስት ኮከብ፣ ባለ አንድ አይን ምስል በአብዛኛው ይወከላሉ፡፡ የ‹‹ቢግ ብራዘር›› አፍሪካን አርማ ብንመለከተውም
የአንድ አይን ምልክት ነው፡፡
አንድ ትውልድ በዚህ ሰርዓት ቀንበር ሳይወድ በግዱ ተይዟል፡፡ ልንታደገው ይገባል፡፡
ይህ ካልኾነ ከቅኝ ግዛቱ የከፋ ባርነት በዚህች አገር ይንሰራፋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይጠፋል… እማማ ኢትዮጵያ ማን ይኾን የሚያነሳሽ?
ቸሩ
ቸር ያቆዬን!
No comments:
Post a Comment