Jun 20, 2016

የዓለማየሁ ገላጋይ ሃተታ



የዓለማየሁ ገላጋይ ሃተታ
ተስፋ በላይነህ
ዓለማየሁ ገላጋይን በአዲስ አድማስ ግንቦት 27 2008 ዓ.ም ቅጽ 16 ቁጥር 855 ዕትም ላይ አስደናቂውን ዝናር አሳይቷል፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ደራሲያን መካከል የመሸነጋገል፣ የመሞጋገስ እና በትውውቅ ብቻ ሥራን ሳይሆን ስምን የማግነን ልክፍት ተላቅቆ በአንደበቱ ርትዕን ሲሻም ታይቷል፡፡ ያነሳው ነጥብም በግሌ ለዘወትር ሳናሠው የነበረውን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፤ ይሕም የጥበብ ሰዎች በጥበብ አልቦ ሰዎች ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ!!
የዚህ ሐሳብ ደረት በውቀቱ ስዩም ነበር፤ ዝናሮቼን ይዤ በተደጋጋሚ ብተኩስም የእያሪኮው አይነት የሕዝብ እውቂያ እና ሙገሳ ሊያሳልፋቸው አልፈቀደላቸውም፡፡ ከግጥም መድብሉ ውስጥ “ጤዛዊነት” የምትለዋ ትንኝ ስንኝ ስንቱን ትውልድ መፈወሻው እንደማይተወቅ ወረረርሽ እንደምትፈጅ በተደጋጋሚ ሰንዝሬ ነበር፡፡ በአገራችን (በዓለምም ሊሆን ይችላል) ስም ከሥራ በላይ መሆኑን ልብ ይሏል!! የምርጫ ጉዳይ ሆነና የመረጥነውን ይዘን እንጓዛለን፤ ይሕ ነው የዓለም ጉዙ! ምርጫ ይሉናል ነገር ግን ሌሎች በመረጡት እንጂ ግለሰቦች ራሳቸው በመረጡት ጎዳና ሲጓዙ የሚታዩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ካሉም እነርሡ በልዕልና ጎዳና ላይ ናቸው!! በነጻነት!!
ዓለማየሁ ገላጋይ ይሕንን ጽሑፍ ሲጽፍ በምን መንፈስ ሆኖ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ አይነት የአስተሳሰብ ከፍታ ላይ ቆሞ ደፍሮ መውጣት ቃላል የማይባል ወኔ ይጠይቃልና!! ዓለማየሁ የልብ ጸሐፊ ነው፡፡ መጣጥፎቹን በየሳምንቱ እያነበበ ልቡ ያልተገመሸረ አንባቢ ጥቂት አይደለም፡፡ መጣጥፎቹን ካላነበበ ሰው በቀር፡፡ (መገማሸር ምን ማለት እንደሆነ ዳኛቸው ወርቁን መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም)፡፡ አዲስ አድማስ ላይ ራሱን በራሱ አርታዒ አደርጎ ሊጽፍ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሲጽፍም ለአንድ የኪነ-ጥበብ ጋዜጣ እያለ በሰፊው የአዕምሮ እልፍኙ ውስጥ እንደሚዋኝ እጆቹና እግሮቹ ግን በገመድ ታስረው ፤ ‹‹ከዚህ ወጀብ›› አትለፍ አይነት መፈክር ተጽፎበት የጆርጅ ኦርዌሉን 1984 ገጸ ባሕርይ ያስተዋውሰኛል፡፡
“የዝንቡት ሃተታ” ወደር የማይገኝለት ሐሳብ ይዟል፡፡ ሶሥት ነጥቦችን ላንሳ
1.      ያልተለመደውን የመተቻቸት በወዳጀነት እና በስም ቀዳሚነት የነበረውን የመወዳደስ ክፉ ባሕል መስበሩ (አቻ የማይገኝለት ቀዳሚ)
2.     በጽሑፉ ውስጥ ጥበብ የጎደለውን (ዝንጉነት) የጠቢቡን ምክር ለጥበበኞች አጥበቆ ማሳወቁ፡፡
3.     የአንባቢያንን ወገብ የፈተሸ ፤ አንድን ደራሲ ስናደንቅ የደራሲውን ስራዎች ከ “ሀ” እስከ “ፖ” ድረስ መፈተሸ እና አጠቃላይ ግብኣት እና ተረፈ ምርታቸውን መፈተሸ ያስቻለ በመሆኑ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ብዕሬን እንዳሾር ምክንያት ከመሆናቸውም በላይ ትላንትም፣ ዛሬም ነገም የብዕሬ መፈክር ሆነው በቋሚነት ሊያገለግሉ የሚችሉ መለዮዎቼ ናቸው፡፡
አንድ አገር በፖለቲካው አለመረጋጋት ስትታመስ፣ ቀዳሚ የሆነው የሰው ልጅ ስብዕና ስሪት፤ የትውልድ ወይንም የማሕበረስብ ሥሪት ተጠንቶ ካልተሞረደ፣ ካልተገሰጸ፣ ካልተመከረ በሰብዓዊነት ቅብ ካልተቀባ ችግር አለ! አደጋውም ቀላል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡
ይሕንን ከሚመሩ መጠቁማን ውስጥ የሃማኖት መሪዎች፣ የአገር አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊያን ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በስብከት አቅጣጫቸው አገርንና ማሕበረሰብን መምራት የተሳናቸው ይመስለኛል፡፡ ከሕዝብ መሰላቸት አሊያም ከቅብዓ መንፈስ ቅዱስ ጉድለት፡፡ ይሕንን ለየመንፈሳችን ሰጥተን ታዝበነው ብናልፍ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ የአገር አስተዳዳሪዎቻችንንም ጉድለት ለበርካታ ዘመናት የምናውቀው የተላመድነው ሐቅ ይመስልን ዘንድ ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ ይሕንን ለትግል እና ለነጻነት ኀሠሳ ጋሻዣግሬ ማንነታችን ለሆነው እኛነታችን ሰጥተን እንለፍ (ሥርቆት ከተያዙ ነው ወንጀል አይነት የአደባባይ ምክር ከምን ጊዜውም በላይ በአቤታዊነቱ ሲጠቀስ የሚኖር መሆኑን ሳንጠቅስ ማለፍ ሁለንተናችን ይከስሰናል)
ሶስተኛው ግንባር ቀደም ኣካል ያልናቸው ጸሐፊያንን ነው፡፡ ይሕንን በሰፊው ብንመለከት የሚያዋጣ ይመስለኛል፡፡ ከዓለማየሁ መጣጥፍ ሳንወጣ በሐሳብ ለመግባባት እንዲያመቸን!!
የጸሐፊያን ተጽዕኖ!
የጸሐፊያን ተጽዕኖ ስንል የሥነጽፍ ተጽኖ ተብሎ ሊተረጎም እንደሚቻል ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የትኘው ጸሐፊ ትኛው አናባቢ ተገናኝቶ ነው ተጽዕኖ ማሳረፍ የተቻለው? የሚለውን ይዘት ሊደግፍልን ይችላልና፡፡ “አሌክስ አብርሀም” የተባለው ዝነኛው ‹‹ፌስቡከር›› በተደጋጋሚ የመገናኛ አውታሮቻችን ስለ መጠጥ የሚስተላልፉትን ሐሳብ በሙሉ ሲያወግዝ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የቢራ ፋብሪካዎችን በመጠየፍ እና በመገሰጽ አቻ አልተገኘለትም፡፡ እኔ በበኩሌ ውሸት ሲደጋገም ውነት ይመስላል በሚባለው ዘመነኛ ብሔል (“ፕሮፖጋንዳ” ይሉታል ስሙን ሲያሽሞነሙኑት) በዚህ ዘይቤ ቢራን በተደጋጋሚ ማሳየት፣ ማስተዋወቅ፣ እና ማለማመድ መጨረሻው ቢራ የመሠረታዊ ፍላጎቶቻችን ዝርዝር /ሜኑ/ ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ሙከራ /ዘመቻ/ ነው፡፡ በዚህም ተቃርኖ “አሌክስ አብርሃም” ይሕን በመቃወም በተደጋጋሚ መጻፉን አልጠላሁለትም፡፡ አልፎ አልፎም የአጻጻፍ ምቱ (ሪትሙ) ፍቅር የጎደለው እልክ እና አስገዳጅ ማድረጉን የሚከራረኩበት ሰዎችንም አስተናግጃለሁ፡፡ ሆኖም ተጽኖዕውን ለማስቀረት የበኩሉን እየታገለ ያለ የነጻነት አርበኛ ብዬ ሾሜዋለሁ!! የቢራ አስተዋዋቂዎች ጸሐፊያን ነቸው እኔ ሊያስብል ጥያቄ ከአንባቢ ሊጫር ይችላል፡፡ ወደ ጽሑፍ ተጽዕኖው ጉዳይ ተመለስ አትሉኝም?
ከቢራ ፋብሪካዎች በበለጠ መልኩ አንድ ግለሰብ መጠጥን ሲያሽነሙን እና ሲያወድስ ከዚያም አልፎ ሕዝቡ ሲያጨበጭብ እያዩ ዝም ማለት የቆጡን አውርድ በላ የብብቷን ጣለች ያገሬ ብሂልን ያስተውሳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ያገሬ ብኂል ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ለገጠመኞቻችን ምሳሌ እያቀረቡ የሐሳብን መሠረት በኮንክሪት “ጭቃ” ማያያዝ! ኧረ ለመሆኑ የኛ ትውልድ ብኂል የሚፈጥረው መቼ ነው…? ማለቴ ካለፈው ትውልድ ኣባባል እና ብኂል ከመውሰድ የራሱን ቅርስ በቋሚነት የሚገነባው…? ያለፈው ትውልድ ኮንክሪት ጭቃን ሲየወርስ የእኛ በውሃ ላይ ኩበት የመሠለውን ማያያዣ ለማውረስም አልታደልንም!!
ወደ መጠጡ ተጽኖ እና ተጋድሎ ልመለስ፡፡ በአንድ ወቅት ባለቅኔው ፈላስፋ ገጣሚ በውቀቱ ስዩም ከ‹‹እልም ዣት›› ያገኘውን ስንኝ ቋጠሮ በዘመነኛው ብኂል ፌስቡክ ግድግዳው ላይ “ዝገኑ” ሲለን፤ መጠጥን ለማስተዋወቅ አንድ ቢራ ፋብሪካ ማስተዋወቂያ ከሚሠራለት ኃይል በላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንሚችል አለመገንዘብ (ዝም ማለት ብለው ይቀልለኛል) ምን ሊሆን እንደሚችል ስገምት መስል አጣለሁ፡፡ ማለትም የቢራ ፋብሪካዎችን የሚገዳደር ግለሰብ፤ ሌላኛው ታዋቂ ግለሰብ መጠጥን በእውነት ማማ ላይ አጉኖ ሲያወድሳት እየተመለከቱ ዝምታን መምረጥ፤ ጸሐፊዎቻችን ከሥራ በላይ ስምን እንደሚስቀድሙ የሚለውን ሐሳቤን ያጠናክርልኛል፡፡ ሁለት ነገር፡- አንደኛው የጽሑፍ ተጽዕኖን እና ሌላኛው የጸሐፊያንን ዝምታ፡፡ በአንድ ወቅት ቦብ ማርሊን ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ ጉዳይ በውቀቱ ስዩም እና አሌክስ አብርሃም እሰጣ ገባ ውስጥ እንደገቡ አእታውሳለሁ፡፡ ጉዳዩ ለተከታዮች ግልጽ ቢሆንም በመጠጥ ጉዳይ ላይ ዝምታው ግን የርዕሴን ሐተታ የሚያጠናክርልኝ ማሳያ ምስክር ነው፡፡
የመጠጥን ጎጂነት ሲመሰክር፤ መጠጥን ከሚያስተዋውቁ ግለሰቦች እና ተቋማት ጋርም ሳይቀር ሲላተም የነበረ ግለሰብ፤ አንድ ታዋቂ ግለሰብ መጠጥን እንዲያ ሲያወድስ እና ሲያሞካሽ የተመለከትነውን ጸሐፊ ዝም ብሎ ማለፍ በግሌ ጥያቄን አጭሮብኛል፡፡ ዝምታ ከሚጠቅመው ጊዜ ይልቅ ባይበልጥ እንኳ እኩል /የማይተናነስ/ ጉዳት እንዳለው ልብ እንበል፡፡ በአንድ ዝምታ ውስጥ ሺሕ ቅቡልነቶች፣ ሺሕ ስምምነቶች፣ ሺሕ ስንፍናዎች፣ ሺሕ እያዩ አላየሁምን ግዴለሽት እና ተከታታይ ጣጣዎች ይስተናፈዳሉና!
ዓለማየሁ ገላጋይ ከዚሕ ስንፍና መላቀቁን በ”ዝንቡት ሃተታ” ላይ ማሳየቱን እመሰክራለሁ፡፡ መመስገን ያለበት እና ሊለመድ የሚገባ ጉዳይም ነው!
በበኩሌ ጸሐፊያን ያዩትን፣ የሠሙትን እንዲሁም ያለሙትን ይጽፉ ዘንድ ከማንም በላይ ነጻታቸውን በብዕራቸው ያወጁ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት እገሌ ለምን እንዲህ ጻፈ እገሊት ስለምን እንዲህ ብላ መልዕክትቷን አስተላለፈች የሚለው ጥያቄ ሲከተል ምክንያታዊ ፋይዳዎችን ዘርዝረን በማስቀመጥ መዋዬት እንጂ፤ “ሥነ-ጽሑፍ ለማሕበረሰብ” ወይስ “ሥነ-ጽሑፍ ለሥነ-ጽሑፍ” ወደሚለው የዶሮና የእንቁላል የልጆች ጥያዌና መልስ አዙሪት ውሰጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ አንድ ጸሐፊ በማሕበረሱ ውስጥ የተመለከተውን አጠቃላይ ሥሜት (ሕመም፣ ደስታ፣ ስኬት፣ ውድቀት፣ ሥሕተት፣ ተምሳሌት.. ወዘተ) በትረካ መልክ ማሰቀመጡ ጸሐፊውን የማሕበረሰቡ ደጋፊ፣ ተቃዋሚ አሊያም ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው ብሎ መፍረድ ሙሉ በሙሉ ትክክል ወን ብዬ አላምነም፡፡
እንዳለ ጌታ ከበደም ሆኑ ቀደምት ጉምቱ ጸሐፊያን ፤ ከነ ሎሬት እስከ ወንድምዬ አሊ፣ በዓሉ፣ ስብሐት፣ ዳኛቸው ወዘተ ሥለ ‹‹ዝምቡነት›› ጽፈዋልና “‹‹ዝምቡነትን›› አቀነቀኑ” የሚለው ሐሰባ ሾላ በድፍን የሚታለፍ አይደለም፡፡ ማሕበረሰቡ, ውስጥ የተከሠተ ድርጊት፣ ሊከሰት አሊያም ሳይከሰተም ሐሳቡብ በትረካ መልክ ማስቀመጣቸው ወንጀል ነው ካልን በመጽሐፍ ቅድሱ ውስጥ የተጻፉትን ምሳሌዎች የምንቃወም ሊሆን ነው፡፡ ጸሐፊያን ዩትን  መጻፋቸው ስላዩት ነገር ደጋፊነታቸውን መመስከራቸው ላይሆን እንደሚችል የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለምና፡፡ ሥለዚህ በሐሳቡ ዙሪያ የተስማማን ስንሆን ነው ወደ ቀጣዩ “ውስጠ ወይራ” ርዕስ ልንገባ የምንችለው፡፡ የጽሑፎች ተጽዕኖ ግቡን መቷል አልመታም ለሚለው የመዝጊያ ጥያዌ “ከመታማ ዓመታትን አስቆጠረ” ወደሚለው የግል ድምዳሚዬ በመድረስ ሐሳቤን ልቋጭ፡፡ የጠፋው ተጽዕኖዎችን ሊያከስም የሚችል የሐሳብ ሚሳዜል እንጂ፡፡ ሚሳኤል ሲሰራ ሚሳኤል የሚያከስም ጥበብ አብሮ ብቅ ይላል፡፡ በጽሑፎቻችን እና በጸሐፊዎቻችን ላይ ግን እምብዛም አልተለመደም!  
እንደዚህ ያሉ ጽሑፎች ሲበራከቱ ሐሳቦች እና አሳቢዎች ይበራከታሉ፡፡ በድጋፍ ብቻ የምንጯጯህ ከሆነ ግን ዝንቡነት ለስጋ ብቻ አይደለም፡፡ ለመንፈስም ደዌ ነው፡፡ ግለሰብን ለማንቋሸሽ ሳይሆን የግለሰቡን ሐሳብ ላይ አተኩረን ሐሳብ ላይ ተወያተን ሐሳብ ደውር በሽመናው ላይ እንዲመላለስ በማድረግ በተመረጠልን መንገድ ብቻ ሳይሆን በመረጥነው ጎዳና የማቅናትን ልዕልን እንድንላበስ እና ጸዐዳ ሸማ እንድንጎናጸፍ ፈጣሪ ይርዳን!!
  

No comments: