Showing posts with label African Writers. Show all posts
Showing posts with label African Writers. Show all posts

Jun 20, 2016

የዓለማየሁ ገላጋይ ሃተታ



የዓለማየሁ ገላጋይ ሃተታ
ተስፋ በላይነህ
ዓለማየሁ ገላጋይን በአዲስ አድማስ ግንቦት 27 2008 ዓ.ም ቅጽ 16 ቁጥር 855 ዕትም ላይ አስደናቂውን ዝናር አሳይቷል፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ደራሲያን መካከል የመሸነጋገል፣ የመሞጋገስ እና በትውውቅ ብቻ ሥራን ሳይሆን ስምን የማግነን ልክፍት ተላቅቆ በአንደበቱ ርትዕን ሲሻም ታይቷል፡፡ ያነሳው ነጥብም በግሌ ለዘወትር ሳናሠው የነበረውን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፤ ይሕም የጥበብ ሰዎች በጥበብ አልቦ ሰዎች ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ!!
የዚህ ሐሳብ ደረት በውቀቱ ስዩም ነበር፤ ዝናሮቼን ይዤ በተደጋጋሚ ብተኩስም የእያሪኮው አይነት የሕዝብ እውቂያ እና ሙገሳ ሊያሳልፋቸው አልፈቀደላቸውም፡፡ ከግጥም መድብሉ ውስጥ “ጤዛዊነት” የምትለዋ ትንኝ ስንኝ ስንቱን ትውልድ መፈወሻው እንደማይተወቅ ወረረርሽ እንደምትፈጅ በተደጋጋሚ ሰንዝሬ ነበር፡፡ በአገራችን (በዓለምም ሊሆን ይችላል) ስም ከሥራ በላይ መሆኑን ልብ ይሏል!! የምርጫ ጉዳይ ሆነና የመረጥነውን ይዘን እንጓዛለን፤ ይሕ ነው የዓለም ጉዙ! ምርጫ ይሉናል ነገር ግን ሌሎች በመረጡት እንጂ ግለሰቦች ራሳቸው በመረጡት ጎዳና ሲጓዙ የሚታዩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ካሉም እነርሡ በልዕልና ጎዳና ላይ ናቸው!! በነጻነት!!
ዓለማየሁ ገላጋይ ይሕንን ጽሑፍ ሲጽፍ በምን መንፈስ ሆኖ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ አይነት የአስተሳሰብ ከፍታ ላይ ቆሞ ደፍሮ መውጣት ቃላል የማይባል ወኔ ይጠይቃልና!! ዓለማየሁ የልብ ጸሐፊ ነው፡፡ መጣጥፎቹን በየሳምንቱ እያነበበ ልቡ ያልተገመሸረ አንባቢ ጥቂት አይደለም፡፡ መጣጥፎቹን ካላነበበ ሰው በቀር፡፡ (መገማሸር ምን ማለት እንደሆነ ዳኛቸው ወርቁን መጠየቅ ሳይሻል አይቀርም)፡፡ አዲስ አድማስ ላይ ራሱን በራሱ አርታዒ አደርጎ ሊጽፍ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሲጽፍም ለአንድ የኪነ-ጥበብ ጋዜጣ እያለ በሰፊው የአዕምሮ እልፍኙ ውስጥ እንደሚዋኝ እጆቹና እግሮቹ ግን በገመድ ታስረው ፤ ‹‹ከዚህ ወጀብ›› አትለፍ አይነት መፈክር ተጽፎበት የጆርጅ ኦርዌሉን 1984 ገጸ ባሕርይ ያስተዋውሰኛል፡፡
“የዝንቡት ሃተታ” ወደር የማይገኝለት ሐሳብ ይዟል፡፡ ሶሥት ነጥቦችን ላንሳ
1.      ያልተለመደውን የመተቻቸት በወዳጀነት እና በስም ቀዳሚነት የነበረውን የመወዳደስ ክፉ ባሕል መስበሩ (አቻ የማይገኝለት ቀዳሚ)
2.     በጽሑፉ ውስጥ ጥበብ የጎደለውን (ዝንጉነት) የጠቢቡን ምክር ለጥበበኞች አጥበቆ ማሳወቁ፡፡
3.     የአንባቢያንን ወገብ የፈተሸ ፤ አንድን ደራሲ ስናደንቅ የደራሲውን ስራዎች ከ “ሀ” እስከ “ፖ” ድረስ መፈተሸ እና አጠቃላይ ግብኣት እና ተረፈ ምርታቸውን መፈተሸ ያስቻለ በመሆኑ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ብዕሬን እንዳሾር ምክንያት ከመሆናቸውም በላይ ትላንትም፣ ዛሬም ነገም የብዕሬ መፈክር ሆነው በቋሚነት ሊያገለግሉ የሚችሉ መለዮዎቼ ናቸው፡፡
አንድ አገር በፖለቲካው አለመረጋጋት ስትታመስ፣ ቀዳሚ የሆነው የሰው ልጅ ስብዕና ስሪት፤ የትውልድ ወይንም የማሕበረስብ ሥሪት ተጠንቶ ካልተሞረደ፣ ካልተገሰጸ፣ ካልተመከረ በሰብዓዊነት ቅብ ካልተቀባ ችግር አለ! አደጋውም ቀላል ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡
ይሕንን ከሚመሩ መጠቁማን ውስጥ የሃማኖት መሪዎች፣ የአገር አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊያን ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በስብከት አቅጣጫቸው አገርንና ማሕበረሰብን መምራት የተሳናቸው ይመስለኛል፡፡ ከሕዝብ መሰላቸት አሊያም ከቅብዓ መንፈስ ቅዱስ ጉድለት፡፡ ይሕንን ለየመንፈሳችን ሰጥተን ታዝበነው ብናልፍ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ የአገር አስተዳዳሪዎቻችንንም ጉድለት ለበርካታ ዘመናት የምናውቀው የተላመድነው ሐቅ ይመስልን ዘንድ ከፊት ለፊታችን አለ፡፡ ይሕንን ለትግል እና ለነጻነት ኀሠሳ ጋሻዣግሬ ማንነታችን ለሆነው እኛነታችን ሰጥተን እንለፍ (ሥርቆት ከተያዙ ነው ወንጀል አይነት የአደባባይ ምክር ከምን ጊዜውም በላይ በአቤታዊነቱ ሲጠቀስ የሚኖር መሆኑን ሳንጠቅስ ማለፍ ሁለንተናችን ይከስሰናል)
ሶስተኛው ግንባር ቀደም ኣካል ያልናቸው ጸሐፊያንን ነው፡፡ ይሕንን በሰፊው ብንመለከት የሚያዋጣ ይመስለኛል፡፡ ከዓለማየሁ መጣጥፍ ሳንወጣ በሐሳብ ለመግባባት እንዲያመቸን!!
የጸሐፊያን ተጽዕኖ!
የጸሐፊያን ተጽዕኖ ስንል የሥነጽፍ ተጽኖ ተብሎ ሊተረጎም እንደሚቻል ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የትኘው ጸሐፊ ትኛው አናባቢ ተገናኝቶ ነው ተጽዕኖ ማሳረፍ የተቻለው? የሚለውን ይዘት ሊደግፍልን ይችላልና፡፡ “አሌክስ አብርሀም” የተባለው ዝነኛው ‹‹ፌስቡከር›› በተደጋጋሚ የመገናኛ አውታሮቻችን ስለ መጠጥ የሚስተላልፉትን ሐሳብ በሙሉ ሲያወግዝ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የቢራ ፋብሪካዎችን በመጠየፍ እና በመገሰጽ አቻ አልተገኘለትም፡፡ እኔ በበኩሌ ውሸት ሲደጋገም ውነት ይመስላል በሚባለው ዘመነኛ ብሔል (“ፕሮፖጋንዳ” ይሉታል ስሙን ሲያሽሞነሙኑት) በዚህ ዘይቤ ቢራን በተደጋጋሚ ማሳየት፣ ማስተዋወቅ፣ እና ማለማመድ መጨረሻው ቢራ የመሠረታዊ ፍላጎቶቻችን ዝርዝር /ሜኑ/ ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ሙከራ /ዘመቻ/ ነው፡፡ በዚህም ተቃርኖ “አሌክስ አብርሃም” ይሕን በመቃወም በተደጋጋሚ መጻፉን አልጠላሁለትም፡፡ አልፎ አልፎም የአጻጻፍ ምቱ (ሪትሙ) ፍቅር የጎደለው እልክ እና አስገዳጅ ማድረጉን የሚከራረኩበት ሰዎችንም አስተናግጃለሁ፡፡ ሆኖም ተጽኖዕውን ለማስቀረት የበኩሉን እየታገለ ያለ የነጻነት አርበኛ ብዬ ሾሜዋለሁ!! የቢራ አስተዋዋቂዎች ጸሐፊያን ነቸው እኔ ሊያስብል ጥያቄ ከአንባቢ ሊጫር ይችላል፡፡ ወደ ጽሑፍ ተጽዕኖው ጉዳይ ተመለስ አትሉኝም?
ከቢራ ፋብሪካዎች በበለጠ መልኩ አንድ ግለሰብ መጠጥን ሲያሽነሙን እና ሲያወድስ ከዚያም አልፎ ሕዝቡ ሲያጨበጭብ እያዩ ዝም ማለት የቆጡን አውርድ በላ የብብቷን ጣለች ያገሬ ብሂልን ያስተውሳል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ያገሬ ብኂል ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ለገጠመኞቻችን ምሳሌ እያቀረቡ የሐሳብን መሠረት በኮንክሪት “ጭቃ” ማያያዝ! ኧረ ለመሆኑ የኛ ትውልድ ብኂል የሚፈጥረው መቼ ነው…? ማለቴ ካለፈው ትውልድ ኣባባል እና ብኂል ከመውሰድ የራሱን ቅርስ በቋሚነት የሚገነባው…? ያለፈው ትውልድ ኮንክሪት ጭቃን ሲየወርስ የእኛ በውሃ ላይ ኩበት የመሠለውን ማያያዣ ለማውረስም አልታደልንም!!
ወደ መጠጡ ተጽኖ እና ተጋድሎ ልመለስ፡፡ በአንድ ወቅት ባለቅኔው ፈላስፋ ገጣሚ በውቀቱ ስዩም ከ‹‹እልም ዣት›› ያገኘውን ስንኝ ቋጠሮ በዘመነኛው ብኂል ፌስቡክ ግድግዳው ላይ “ዝገኑ” ሲለን፤ መጠጥን ለማስተዋወቅ አንድ ቢራ ፋብሪካ ማስተዋወቂያ ከሚሠራለት ኃይል በላይ ተጽዕኖ ማሳደር እንሚችል አለመገንዘብ (ዝም ማለት ብለው ይቀልለኛል) ምን ሊሆን እንደሚችል ስገምት መስል አጣለሁ፡፡ ማለትም የቢራ ፋብሪካዎችን የሚገዳደር ግለሰብ፤ ሌላኛው ታዋቂ ግለሰብ መጠጥን በእውነት ማማ ላይ አጉኖ ሲያወድሳት እየተመለከቱ ዝምታን መምረጥ፤ ጸሐፊዎቻችን ከሥራ በላይ ስምን እንደሚስቀድሙ የሚለውን ሐሳቤን ያጠናክርልኛል፡፡ ሁለት ነገር፡- አንደኛው የጽሑፍ ተጽዕኖን እና ሌላኛው የጸሐፊያንን ዝምታ፡፡ በአንድ ወቅት ቦብ ማርሊን ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ ጉዳይ በውቀቱ ስዩም እና አሌክስ አብርሃም እሰጣ ገባ ውስጥ እንደገቡ አእታውሳለሁ፡፡ ጉዳዩ ለተከታዮች ግልጽ ቢሆንም በመጠጥ ጉዳይ ላይ ዝምታው ግን የርዕሴን ሐተታ የሚያጠናክርልኝ ማሳያ ምስክር ነው፡፡
የመጠጥን ጎጂነት ሲመሰክር፤ መጠጥን ከሚያስተዋውቁ ግለሰቦች እና ተቋማት ጋርም ሳይቀር ሲላተም የነበረ ግለሰብ፤ አንድ ታዋቂ ግለሰብ መጠጥን እንዲያ ሲያወድስ እና ሲያሞካሽ የተመለከትነውን ጸሐፊ ዝም ብሎ ማለፍ በግሌ ጥያቄን አጭሮብኛል፡፡ ዝምታ ከሚጠቅመው ጊዜ ይልቅ ባይበልጥ እንኳ እኩል /የማይተናነስ/ ጉዳት እንዳለው ልብ እንበል፡፡ በአንድ ዝምታ ውስጥ ሺሕ ቅቡልነቶች፣ ሺሕ ስምምነቶች፣ ሺሕ ስንፍናዎች፣ ሺሕ እያዩ አላየሁምን ግዴለሽት እና ተከታታይ ጣጣዎች ይስተናፈዳሉና!
ዓለማየሁ ገላጋይ ከዚሕ ስንፍና መላቀቁን በ”ዝንቡት ሃተታ” ላይ ማሳየቱን እመሰክራለሁ፡፡ መመስገን ያለበት እና ሊለመድ የሚገባ ጉዳይም ነው!
በበኩሌ ጸሐፊያን ያዩትን፣ የሠሙትን እንዲሁም ያለሙትን ይጽፉ ዘንድ ከማንም በላይ ነጻታቸውን በብዕራቸው ያወጁ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት እገሌ ለምን እንዲህ ጻፈ እገሊት ስለምን እንዲህ ብላ መልዕክትቷን አስተላለፈች የሚለው ጥያቄ ሲከተል ምክንያታዊ ፋይዳዎችን ዘርዝረን በማስቀመጥ መዋዬት እንጂ፤ “ሥነ-ጽሑፍ ለማሕበረሰብ” ወይስ “ሥነ-ጽሑፍ ለሥነ-ጽሑፍ” ወደሚለው የዶሮና የእንቁላል የልጆች ጥያዌና መልስ አዙሪት ውሰጥ መግባት ያለብን አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ አንድ ጸሐፊ በማሕበረሱ ውስጥ የተመለከተውን አጠቃላይ ሥሜት (ሕመም፣ ደስታ፣ ስኬት፣ ውድቀት፣ ሥሕተት፣ ተምሳሌት.. ወዘተ) በትረካ መልክ ማሰቀመጡ ጸሐፊውን የማሕበረሰቡ ደጋፊ፣ ተቃዋሚ አሊያም ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው ብሎ መፍረድ ሙሉ በሙሉ ትክክል ወን ብዬ አላምነም፡፡
እንዳለ ጌታ ከበደም ሆኑ ቀደምት ጉምቱ ጸሐፊያን ፤ ከነ ሎሬት እስከ ወንድምዬ አሊ፣ በዓሉ፣ ስብሐት፣ ዳኛቸው ወዘተ ሥለ ‹‹ዝምቡነት›› ጽፈዋልና “‹‹ዝምቡነትን›› አቀነቀኑ” የሚለው ሐሰባ ሾላ በድፍን የሚታለፍ አይደለም፡፡ ማሕበረሰቡ, ውስጥ የተከሠተ ድርጊት፣ ሊከሰት አሊያም ሳይከሰተም ሐሳቡብ በትረካ መልክ ማስቀመጣቸው ወንጀል ነው ካልን በመጽሐፍ ቅድሱ ውስጥ የተጻፉትን ምሳሌዎች የምንቃወም ሊሆን ነው፡፡ ጸሐፊያን ዩትን  መጻፋቸው ስላዩት ነገር ደጋፊነታቸውን መመስከራቸው ላይሆን እንደሚችል የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለምና፡፡ ሥለዚህ በሐሳቡ ዙሪያ የተስማማን ስንሆን ነው ወደ ቀጣዩ “ውስጠ ወይራ” ርዕስ ልንገባ የምንችለው፡፡ የጽሑፎች ተጽዕኖ ግቡን መቷል አልመታም ለሚለው የመዝጊያ ጥያዌ “ከመታማ ዓመታትን አስቆጠረ” ወደሚለው የግል ድምዳሚዬ በመድረስ ሐሳቤን ልቋጭ፡፡ የጠፋው ተጽዕኖዎችን ሊያከስም የሚችል የሐሳብ ሚሳዜል እንጂ፡፡ ሚሳኤል ሲሰራ ሚሳኤል የሚያከስም ጥበብ አብሮ ብቅ ይላል፡፡ በጽሑፎቻችን እና በጸሐፊዎቻችን ላይ ግን እምብዛም አልተለመደም!  
እንደዚህ ያሉ ጽሑፎች ሲበራከቱ ሐሳቦች እና አሳቢዎች ይበራከታሉ፡፡ በድጋፍ ብቻ የምንጯጯህ ከሆነ ግን ዝንቡነት ለስጋ ብቻ አይደለም፡፡ ለመንፈስም ደዌ ነው፡፡ ግለሰብን ለማንቋሸሽ ሳይሆን የግለሰቡን ሐሳብ ላይ አተኩረን ሐሳብ ላይ ተወያተን ሐሳብ ደውር በሽመናው ላይ እንዲመላለስ በማድረግ በተመረጠልን መንገድ ብቻ ሳይሆን በመረጥነው ጎዳና የማቅናትን ልዕልን እንድንላበስ እና ጸዐዳ ሸማ እንድንጎናጸፍ ፈጣሪ ይርዳን!!
  

Sep 1, 2015

የተስፋ ክትባት! በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፡፡



የተስፋ ክትባት! በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፡፡
ተስፋ በላይነህ    



‹‹የተስፋ ክትባት›› የባለ አስራ ሰባት ገጽ መግቢያ አዘል፤ ነሐሴን 2007ዓ.ም  ሳንጨርስ 2008 ዓ.ም ስር የተመዘገበች የባለ 100 ገጽ የግጥም መድብል ነች፡፡ በ45 ብር፡፡
በድሉ ዋቅጅራ(ዶ/ር) አምስት ስራዎችን እንዳቀረበልን ከመጽሐፏ የሽፋን ጀርባ ላይ ማዬት እንችላለን፡፡ በተማሩበት የትምሕርት ዘርፍ፣ ባስታመረው ሕብረተሰብ ሕመም እና ደስታ ማዕድ ሥር ሆኖ፤ ማሕበረሰብን መከርከም፣ መንገድ መምራት እንዲሁም የልቡን ሕመም መጋራት፣ አልፎም መጻፍን የመሰለ ክብር ያለ አይመስለኝም! አለ ብዬም መሟገት የሚያስችል አቅም አይኖረኝም፡፡ በርታልን ዶ/ር ከማለት ውጭ!!
የጥልቅ ምናብ ባለቤት
‹‹የተስፋ ክትባት›› በመግቢያዋ ሥለ ግጥም መባል የሚገባቸውን፤ አንኳር ነጥቦች አንግባ፤ 43 ግጥሞችን ተሸክማለች፡፡ በመግቢያው እንደተገለጸልን ሃያሲ እንደ ገጣሚው የጥቅል ምናብ ባለቤት መሆን ይጠበቅበታል በሚል እውነታ፤ ይሕችን የግጥም መድበል ለማሄስ ራሴን ጠየክሁት፡፡ የጥልቅ ምናብ ባለቤት ነኝን? ሥል፡፡
የጥልቅ ምናብ ባለቤት መሆኔን ለመረዳት፤ ጥልቅ ምናብ ያላቸውን ገጣሚዎች ስራ ፈልጎ ማግኘት እናም አንብቦ መረዳት በራሱ አመሳካሪ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሥለዚህ የተስፋ ክትባትን ከገጽ 23-100 ማንበብና መረዳት፤ ከዚያም የጥልቅ ምናብ ባለቤት እኔ ወይንስ ገጣሚው በሚል ኃልዮት ለማንበብ ፈቀድክሁ፡፡
የውበት ፍጽምና መታደል፣ ለምናባዊ ፍጽምና መቅረብ ከዛም ቃላትን፣ እየገጣጠሙ፣ ምሳሌዎችን፣ ዘይኔዎችን፣ ፈሊጦችን..   ቋንቋ የፈቀደለትን በሙሉ በመጠቀም፤ የምናቡን ስዕል ለአናባቢው ለማሳየት መሞከር ከዚያም በስተመጨረሻ ምናባዊ ምስሉ ገሀዳዊ ህልውና እስኪያገኝ ድረስ የሚደከንበት ስራ ነው- ግጥም!...ገጽ 22፡፡
እዚህ ላይ መስማማት ያለብን ነገር ቢኖር፤ የገጣሚው የጥልቅ ምናብ ባለቤትነት፤ የአንባቢውንም ምናባዊ ጥልቀት መፈተሹ እና ትስስራቸው የተደጋገፈ መሆኑን ማወቅ ነው፡፡ ገጣሚው ጥልቅ ምናብ ባለቤት ከሆነ፤ አንባቢው (በስፋት ሃያሲው) ምናቡን ሊያሰፋለት መቻሉንና መደጋገፋቸው ትልቅ ኃይል መሆኑን በማሳሰብ ወደ ግጥሞቹ እናዝግም፡፡ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ምናቢ ጥልቀት ኃይል ግን ከገጣሚው እንደሚጠበቅ ሳንስማማ አናልፍም
ግጥሞቹ ለኑሮ ጓደኛ፣ ለማሕበረሰብ ድንቁርና፣ ለሴት ልጅ ስሜት፣ ለቤተሰብ፣ ለአገር እንዲሁም ለፖለቲካ ምልከታ ውለው፤ አጋጣሚዎችን ተገን አድርገው የተጻፉ ይመስላሉ፡፡ እያንዳንዱ ግጥሞች በመቼት እና በቦታም ተሰድረዋል፡፡
በግሌ የግጥም ምናባዊ ጥልቀት ወደ ተጨባጭ የወግ፣ የሥርዓት እና ተፈጥሮአዊ ይዘት ውስጥ ሆነው የምኖረውን ሕይወት ባልተመለከትኩበት ማዕዘን እና ስሜት የተጻፈ ሲሆን ቀልቤን ይስበዋል፡፡ ምናቤን ያጎነዋል፡፡ ነፍሴን ያሾራታል፡፡ ጥልቀቴን እንደ ጅረት ውሃ ድምቀት እያስዋበ ትስፍህት ዜማ ሊያሰማኝ ይጋባል፡፡
ሆኖም ወደ ምናባዊ ጥልቀት ውስጥ መግባት ቀላል ጉዞ አይደለምና፡፡ ምንባዊ ጥልቀት ዝም ብሎ ተነስቶ የደርሶ መልስ “ትኬት” ቆርጦ እንደመጓዝ አይነት ጉዞ አይደለም፡፡ ወደ ጥልቁ ለመጓዝ ስናስብ የጉዞውን ርቀት፣ ስፍር በተለይም መመለሻ ባቡሩን ማሰብም የሚጠበቀው ከአንባቢ ነው፡፡ አንባቢ ልክ እንደ ተሳፋሪ ነው፡፡ መሪውን የያዘው ገጣሚው (ጸሐፊው) ከሆነ፤ ተሳፋሪ በፈለገበት መንገድ መጓዝ እይችልም፡፡ የመንገዱ አቅጣጫ የሚወሰነው በባለመሪው መዳፍ ስር ነውና! ጥንቃቄው የትየለሌ ነው፡፡ ሆኖም ተሳፋሪው ዋና መቻል አለበት፡፡ መዋኘት ከመቻልም ባሻገር የቅድመ ደህንነት ትጥቁን ማሟላት አለበት፡፡  ወደ ጥልቁ ተጉዘው መመለስ አቅቷቸው አቅጣጫቸው ጠፍቶባቸው ሲመላለሱ የምናያቸው፤ ጥልቁን የሕይወት ውቅያኖስ መሻር አቅትቸው ሲዋልሉ የቀሩት ጥቂቶች አይደሉምና!!
በበኩሌ ግጥሞቹ አነስተኛ ገላጭ ስዕሎች ቢታከሉበት የትየለሌ ምናባዊ አድማሳችንን ከማስፋታቸውም ባሻገር፤ ውበት ፈላጊ አንባቢን የልቡን ስፋት፣ የነፍሱን ጥማት ያበዙለታል ብዬ እገምታለሁ፡፡(“ኗሪ አልባ ጎጆዎች”  ልቤ ላይ የቀረኝ ውበት)
ገጣሚው ለእድር እና ለአድባር መጨነቁ፤ በዚህ ስራው ብቻ አይደለም አየምናውቀው፡፡ በቀደምት ስራቹም ሆነ በየመጽት መጣጥፎቹ ‹‹አገር ማለት ሰው ነው›› አይነት ፈሊጥ አራማጅ በመሆኑ፤ እዚህ ስራ ላይም ተደጋግሞ መመልከት እንችላለን፡፡ ‹‹ለየቅል አደርን››ን ዋቢ ማድረግ እንችላለን፡፡
እንደ ጥንት መርከበኛ፣ የጊዜ መስፈሪያ አሸዋ፣
አለ ስንለው ተንሸራቶ፣ ፍቅራችን እንሰተሰዋ፤
ልብህ እያወቀ፣ ሹክ ሳትለኝ፣
ልቤ እያወቀ ፣ ሳላጫውትህ፤
እኔም ከአድባር መገለሌ፣
አንተም ከእድሬ መውጣትህ፡፡
አይቆጭህም?!
አሁንም ገጣሚው በየዕለት የሚያጋጥመንን ታሪክ ቀረሽ ምልከታዎች በግጥሙ ክታብ ይጣባናል፡፡ ‹‹ዮሀንስን ናፍቆት›› በምድረበዳ አጥማቂውን ሲያስናፍቀን፤ በምደረ ባዳ ደግሞ
አይገራ ትውልድ፣ አንድ ዮሀንስ ወዶ፤
ከተማው ጭር አለ፣ ምድረ ዳ ወርዶ፡፡ ሲል ከአድማሱ ይሰርቅልናል፡፡
ከአገዛዞቻችን ጋር ግብ ግብ የሚገጥምበት የግጥም ስንኞችን ጥቂት አይደሉም፡፡
‹‹ምስጋና›› ገጽ 76
ገዥያችን ተመስገን!!
እንደፍርሃታችን፣
ኮርቻ ጭነህ ያላጋለብከን፤
እንደሆዳምነታችን፣
ስብእናችንን ገፈህ፣ ከከብት ጋጣ ያላኖርከን፤
እንደተገዥነታችን፣ የጸሎት ቤታችንን ንደህ፣ መመለኪያህን ያላቆምክ፤
እንደአለመጠየቃችን፤
እንበላነት ዘንድ ፈቅደህ፣ አፋችንን ያለጎምክ፤
ተመስገን!!
(ምን ቀረው ባይ ነኝ- የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ድምጽ ምን ሆነና-??)
‹‹ኑ ሀውልት እንስራ››
‹‹አንድም በድንቁርና አንድም በእሳት››
‹‹የበደሌን ሀውልት››
‹‹ስም አወጣህልኝ አሉ….›› እና የመሳሰሉትን መጠቆም እንችላለን፡፡ በተለይ ደግሞ የኢህዴግን ፌዴራሊዝም በጣት ተቆጣሪ ስንኞች፤ እንደ አጭር ቁምጣ ልብስ ሲጠቅማቸው እናያለን፡፡
‹‹ለኢህአዴግ››
ጨለማዬን ልትገፍ፣ የለኮስከው ሻማ፣
ተስፋ መድረሻዬን፣ በወንዜ ካጠረው፣
ነጻ ተፈጥሮዬን፣ ቋንቋዬ ካሰረው፣
ልንጓዝ ወደፊት፣ የጠረከው መንገድ
ጉዞ ሳንጀምር፣ ጠቦ ካጫረሰን፣
ተራመድን ስንል፣ ኋላ ከመለሰን፣
ጎዳናው እጅግ ጠቦ፣ ጨለማው ከሰፋ
ወይ መንገድክን ቀይር፣ ወይ ሻማህን አጥፋ፡፡ ገጽ46

 ‹‹ተስፋሽን ፈራሁት›› ግሩም እይታ የታየበት፤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የወደፊት ፈንታችንን የሚያሳይ ምናባዊ እይታ ነው፡፡
    እንዲህ እንዲህ እያለ ረጃጅም ግጥሞችን ይዞ ይዘልቃል፡፡ አንባቢ በትኩረት አይቶ እንዲጋብዝልኝ በመቃኘት እኔም ጽሑፌን ልግታ፡፡
ገጣሚው ከ2003ዓ.ም እስከ 2005 ዓ.ም ወጡ የግጥም መድብሎችን በመቃኘት የግል ጥናት ማድረጉን ነግሮናል፡፡ ከሰባ አምስት በመቶ በላይ የሚሆኑትም “ከመጥፎ ግጥም የሚመደቡ” ሲል ደምድሟል፡፡ ‹‹የተስፋ ክትባት›› ለአዲሱ የጥናት ስራ ራሷን አጋልጣ ብቅ ብላለች፡፡ ከመጥፎው ከጥሩው ናት-? አንባቢና ሃያሲ ይክረምባት፡፡
ዶ/ር በድሉ የአማርኛ ፊደላት ይቀነሱ ከሚለው የምሁራን ወገን ይመስለኛል፤ ይሕንንም በስነጽሑፍ/ሥነጽሑፍ ቃል እና መሰል ቃላት(አለም/ዓለም…) ውስጥ ፈልገን ማግኘት እንችላለን፡፡ ሥነ- ማለት ‹‹ጥናት›› ወይም ‹‹ውበት›› ማለት ሲሆን ስነ ሲሆን ግን ‹‹ጥርስ›› ማለት እንደሆነ የግዕዝ ልሒቃን ሲነግሩን እንመለከታለን፡፡ በዚህም ጉዳይ ትልቅ ውይይት እና መፍትኄ እንደሚያስፈልገው የሁላችንም ፍልጎት እና ምኞት ነው፡፡
የመጨረሻው ረዥም ግጥም ተደጋጋሚ ገጾችን ከመያዙ በቀር፤ እንዲሁም የግጥሞቹ ቁጥር ማነስም በቀር ያስተዋልሁት ደቂቃን ሕጸጾች አልነበሩም፡፡ ለተደራሲው መልካም ንባብ! ለደራሲውም ሌላ ማለፍያ ሥራ፤ ከጥልቀት ምናባዊ እይታ ጋር!!
ቸር፡፡

Aug 6, 2015

ሌሳ ሠው በምሕረት

ሌሳ ሠው በምሕረት
                                                                                                                                       ተስፋ በላይነህ
LELA_SAW-DR_MEHRET
ይመስለኛል በመጽሐፍ ያለን ባሕል በመጠኑም ቢሆን ከእንቅልፉ እየነቃ ያለበት አቅጣጫ ላይ ነን፡፡ ምንም እንኳን የሕትመት ቁጥር፣ የአንባቢ ብዛት እና አጠቃላይ አለም አቀፋዊ ንጽጽራችን ያሽቆለቆለ ቢሆንም፤ ከእንቅልፍ መንቃት በራሡ አንድ እርምጃ ነውና፤ ረዥሙን ርምጃ በማሰብ በርብርብ ካልተንቀሳቀስን አሁንም ቆመን ማንቀላፋታችን አይቀርም፡፡ ተያይዞ መቅረብ ያለበት ነገር ቢኖር የንባብ ባሕሉን ለፖለቲካ ጥቅም ማሳኪያ እና ገቢ ምንጭ-ተኮር(ሸቀጥ) አዝማሚያችን እየሰፋ ከሄድን ደግሞ ሌላ ኣዙሪት ውስጥ እንደምንገባ በመገንዘብ የሁላችንም ኃላፊነት ሰፊ ነው፡፡
‹‹ሌላ ሠው›› የተሠኘውን የዶክተር ምሕረት መጽሐፍ ስመለከት፤ “ይሕ ሁሉ ብዛት ምን ሊኖረው ይችላል?” ከሚል ጥያቄ አንብቦ የመጨረስ ፍላጎቴ መነሻ ነበር፡፡ big books are evil የሚባለውን እና ሸክሙን ለተሸካሚው እዘኑለት አይነት አባባል በውስጤም ነበር፡፡ አሁን አሁን አጫጭር ልብወለዶች እና ወጎች ረዥም ጊዜ ሰጥተን አንድ መጽሐፍ ላይ የትዕግስትን ኃይል፣ ስሜትን የመግዛት ጥበብ እና የማስተዋል አቅማችንን ለሚፈትኑት፤ አንባቢም ጥቂት ነገር የመያዝ እንዲሁም ባንዴ አስቂኝ እና አስገራሚ ይዘት ያላቸውን ጭብጦች ለማካለል ሲል፤ የገበያው ሁኔታም ተደምሮለት በወግ እና በአጫጭር ልቦለዶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደረገው ይመስለኛል፡፡
በበኩሌ በእነዚህ ቅርበ ዓመታት ውስጥ ካነብኳቸው አጫጭር ልቦለዶችና ታሪኮች እንዲሁም የወግ ይዘት ካላቸው መጽሐፍት የአሌክስ አብርሃም በላቀ ይዘትና ጭብጥ አስደምሞኛል፤ በአጫጭር ታሪኮች የሥነ-ጽሑፍ ደርዝ ውስጥ የራሱን አሻራ እያኖረ ያለ ነው! ሥለዚህ ያጫጭር ልቦለዶችን የጎንዮሽ ጉዳት ስንመለከት መሠል ስራዎችን እያጥላላን አይደለም! የራሳቸው ድርሻ አላቸውና! ሥለዚህ ማንም በመክሊቱ እና በተገለጠለት ጸጋ ሆኖ ያሻውን እንዲጽፍ የፈቃድ ድርሻውን እንዲወስድ ተፈጥሮአዊ መብቱን እየሠጠነው፤ ይሕንን የገበያ ሁኔታ፣ የዘመን አባዜ እና መርህ ተላቆ ደግሞ “ረዥም ልብወለድ ያዋጣኛል”፣ “ምርጫየም ነው” ብሎ የሚጽፈውንም ከማመስገን አልፎ ልናበረታታና ትኩረት ልንሠጠውም ይገባል! ለዚህ ነው ‹‹ሌላ ሠው››ን በአትኩሮት እንዳነበብና ያለኝን አስተያዬት ለመሥጠት የተነሳሁት!
መጽሐፉ!
መጽሐፉ ባለ 451 ገጽ፤ ስድሰት አበይት ክፍሎች (የመዳረሻው መነሻ፣ድልድይ፣ሰዎቹ፣ሌሎቹ ሰዎቹ፣ ሌላ ሰው፣እና ማሳረጊያ)፤ በ49 ንዑስ ክፍሎች ተከፋፍሎ፤ አንድ ከአሜሪካን አገር በመጣ የአዕምሮ ሕክምና ጠበብት (ስፔሻሊሥት) አባቱ በተወለት “ውርስ” አማካኝነት አደራውን ለመወጣት የሚከፍለውን ምድራዊ መስዋዕትነትት ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡ ውርስ ሁልጊዜ ሃብት እና ርስት ላይሆን ይችላል፡፡ ያ’ባት የ’ናት አደራ ትልቅ ውርስ ነው፡፡ ውርስ ተቀባይ ትውልድ ደግሞ ድልድይ ነው፡፡ ድልድዩ ድንጋይ፣ አርማታ እና ስሚንቶ ብቻ ሳይሆን በዋጋ የማይተመነው የሰው ልጅ ነው፡፡ መጽሐፉ በአጠቃላይ ሥለ ሰው ጀምሮ በሰው ላይ የሚያልቅ፣ በግልጽ ልማት እና እድገት ተብሎ ዘወትር ከምንሰማው ሐሳብ ተላቅቆ የሰውን ልጅ እናክብር ሲል የሚሟገት የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን በመፈተሸ ደረቱን ሰጥቶ የሚሟገት ነው!
ገጽ 439 እንዲህ ይነበባል፡
“….አስበው እስኪ… አባትህም ያሉት እኮ… ህንጻና መንገዱን ሳይሆን… ሰዎችን ይመስለኛል… ሀገር ሰው ነው…. ሰው ሰው ሲሆን ሀገር ሀገር ይሆናል….” 
መጽሐፉ መንግስት ከሚከተለው የልማታዊነት አስተሳሰብ የተለየ ዜናን ይዞ ነው ከአራት መቶ ገጽ በላይ የሚያስከንፈን፡፡ ሁሉም ገጽ፣ ሁሉም ሐሳብ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ክብር ጋር ያላትመናል፤ የሰውን ክቡር እቃ ጭንቅላት ላይ የሚሠራን ልማት እንደ ስኬት ቆጥሮ በማማው ላይ ነጋሪቱን ይጎስማል- በለሆሳስም ያንኳኳል!
መጽሐፉ እያንዳንዷን ድርጊት ተራ በተራ ስለሚዘግብ አንዳንዴ ትዕግስት ያስጨርሳል፣ “ይሕም መጻፍ ነበረበት?” የምንላቸው ብዙ ቦታዎች አሉበት፣ በእርግጥ ጸሐፊው ያለውን የሥነልቦና እና የአዕምሮ ሕክምና ሙያ ተጠቅሞ የሥነጽሑፍ ጸጋውም በሁለት ሰይፍ እንደተሳለ ብዕር ባለቤት ቢሆን ከዚህ የበለጠ ሥራ ሊወጣው እንደሚችል አስባለሁ! በየንዑስ መዳረሻ ገጾች ላይ አዕምሮን ያዝ የሚያደረጉ አጠቃለይ ሰብዓዊ ምክሮች ን ደግሞ ስናስብ ለመጽሐፉ ውበት እና ምሶሶ የሆኑት የማንክዳቸው መሰረቶች ናቸው!
አንድን ማሕበረሰብ ለመገንባት የማሕበረሰብ ጠበብት በዋነኝነት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው እንደሚያገለግሉት ሁሉ፤ በዚሕ መጽሐፍም የምናዬው አንድ ማዕከልን በማቋቋም የታመመውን ሕብረተሰብ ለመፈወስ የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ሆኖም ታማሚን ማከም ብቻ ሳይሆን ጤነኛውም እንዳይታመም በሚለው ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ዋናው የስራ ድርሻም ያለው እዚህ ላይ መሆኑን ተረድቶ አንድ አዕምሮ ገንቢ እና አስተማሪ የሆነ ማዕከል እንደሚያስፈልግ የዚህ ጽሑፍ አስተያዬት ጸሐፊ ጥብቅ ምክሩ ነው፡፡ በመጽሐፉ ትምሕርት ቤቶች እንዴት መገንባት እንዳለባቸው፣ አካባቢያችን እንዴት መጠናከር እንዳለበት እና ባለድርሻ አካላት በተለይ መንግሥት ኃላፊነቱን አስታክኮ ሙያዊ ድርሻው ላይ ከፍተኛ ጫና በብዛት ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ የሱስ፣ በጾታዊ ጥቃት፣ ባለፈ ታሪክ ሽንቁሮች ተለክፈው የአእምሮአቸው ሚዛን የተዛባባቸው ግለሰቦችን ለማከም የተቋቋመው ማዕከል የራሱን ድርሻ የመወጣት ኃይል ቢኖረውም፤ የዚህች አገር ችግር ከስር መሰረቱ አጥንቶ ማሕበረሰባዊ ድውይን ለማከም ያለመ የጤና ባለሙያን እንመለከታለን -ዶ/ር ሌላሠው፡፡
የማሕበረሰብ ጠበብቱ ለማሕበረሰብ ምሕንድስና መሪና ቀንደኞች አድርገው ሲጠቅሷቸው የምንመለከታቸው እነ ሲግመንድ ፍሩይድን እና መሠል ደቀመዛሙርትን ሥለሆነ፤ ከኛ የበቀሉ፣ የኛን ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖት እንዲሁም ቤተሰባዊ መዋዕቅር የተላበሱ ጠቢባን እንደሚያስፈልጉን ለማንም የሚካድ አይደለምና! እንደውም ‹‹የአመጻ መንገድ›› የተሠኘው የተክሉ አስኳሉ መጽሐፍ የሲግመንድ ፍሩይድን እያንዳንዱን መላምት እየነቀሰ ከኛ ባሕል፣ ሃይማኖት እና ማሕበረሰባዊ ድባብ ጋር እያጣመረ ውድቅ ሲያደርገው በማንበባችን፤ በመጽሐፉ በገጽ 97 እና በሌሎችም የሲግመንድ ፍሩይድ ሥራ የሆኑትን የህልም አተረጓጎም (ዘ ኢንተርፕሪቴሽን ኦፍ ድሪም) እና ኦዲፐስ ኮምፕሌክስ… አፈታሪኮችን እንደምሳሌ እየጠቀሰ ማቅረቡ በዋናነት፤ ስለ መወላወል የተፈጥሮ ባሕርይ ወይንም በምስራቁ አለም “ዪን እና ያንግ” ፍልስፍና በገጽ 251፣ እንዲሁም ስለ ጾታ ቅራኔ “ፌሚኒስት” አስተሳሰብ ውይይቶች ትልቅ ሙግትን እና የመወያያ መድረክን የሚሹ ናቸው!  ሆኖም በገጽ 100 ላይ የጠጠቀቀሰው ንግግር ከጸሐፊውም ሆነ ከሙያው ሙያተኞች ማሕበረሰባችን ብዙ እንደሚጠበቅ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ቀጣይ ሥራ እንዳለውም እንረዳለን፡፡ ገጽ 100 አራተኛ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል!
“ከዛ በተጨማሪ ደግሞ መጻፍና ምናልባትም ሚድያ ውሰጥ ገብቶ የሰውንሥነልቦናዊ ንቃት መኮርኮርና ማሳደግ ይመስለኛል ዋና የትረኩረት አቅጣጫዬ እኔ እንደማማነው ያበሻ ነፍስና ሥነልቦና ለረዥም ዘመናት ከምናስበው በላይ የቆሠለና መከራ የተሸከመ ነው፡፡ ያለፈውን አርባና አምሳ ዓመት እንኳን ብታስበው ይዘገንንሃል፡፡ ያ ሁሉ ያልታከመ ሕመም ያልተከፈለ የሥነልቦና ዕዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገሩ ያንድ ቀን ሥራ አይደለም በርግጥ፡፡”
ጥያቄ፡- ባጠቃላይ ሱሰኛ ሆኖ የሚወለድ ሰው ባይኖርም ሱሰኛ ለመሆን የበለጠ የተጋለጠ ማንነት ይዘን ልንወለድ ግን እንችላለን---
አስደማሚ ቅንጥብጣብ ሐሳቦች
…እና አንዳንዴ የድብቅነት ባሕላችንን ከምን ጋር ይመሳሰልብኛል መሰለሽ? … አስቢው ከደጅ የሚታዩትን በረንዳችንንና አጥራችንን እንዴት እንደምናሳምር፡፡ ደግሞ የበለጠ የሚጠቅሙንን የምንጠቀምባቸውን ኩሽዎቻችንንና የሽንት ቤቶቻችን… አስቢያቸው- ገጽ 71
…ስኪዞፍሬን… የቃሉ ትርጉም የተከፋፈለ አዕምሮ እንደማለት ነው… ይህም ሕመሙ የውጭውን ነባራዊ እውነታ እና በውስጣችን የሚገኘውን የሐሳብ ዓለም አጣጥሞና አስማምቶ ለመኖር አለመቻልን ስለሚፈጥር ነው፡፡ ያልሆኑ ነገሮችን ማመንና የሆኑትን መካድ… ያልተፈጠሩ ነገሮችን ማየትና መስማትን… በዚህም የውስጥ መረበሽ የተነሳ የንግግር፣ የባሕርይና የስሜት መዛባቶችም ይፈጠራሉ፡፡ ገጽ 93፡፡/ይሕ የእብደት ምሳሌ ነው- አገራችን ሰንቱ እንዳበደ ማሰቡ በቻ በቂ ነው፡፡ የሚነገረን ሌላ፣ የምናዬው ሌላ፣ የምናምነው ሌላ የሆንነው ሌላ… ይሕም ራሳችንን በሚገባ እንድንመለከት ያስገነዝበናል!/
“…ማንን ትከሳለህ ሌላሠው? ሆስፒታሉን….ሐኪሞቹን… ነርሲቹን…ዘበኞቹን….የጽዳት ሠራተኛዋን….ጤና ጥበቃን….ማንን? የተለከፈ ሀገር ውስጥ እኮ ነው የምንኖረው፡፡ ደግና ሰው አክባሪ ባሕል እየተባለ ቢለፈፍም እውነቱ ግን ኅሊና የሌለው ጨካኝና ለሰው ዋጋ ደንታ የማይሠጠው ሰው ነው የሚበዛው፡፡ ማንን ትከሳለህ?.... ገጽ 163
“…ግን ምን ይደረግ ሕያዋኑ ቲሸሹን(ሲሸሹን) ጊዜ ተሙታን(ከ) ተጠግተን እንኖራለን… ገጽ 183 (ቅንፍ የኔ)፡፡
“…ፍቅር ስለ ሌላው እንጂ ስለ ራስ ማሰብ አይደለም፡፡ ራስን ስሌላሰው ደስታ ስለ መስጠት እንጂ ሌላውን ሰው በግድ የራስ ማድረግ ሊሆን አይችልም፡፡ ፍቅር ሲታመም ሁሉም ነገር ይታመማል… ስብእናም… አስተሳሰብም… ስሜትም….የራስም…የሌላው ሰውም፡፡ የታመመ ፍቅር ከሁሉ የተወሳሰበ የነፍስ ደዌ ነውና ማዳኑም የዛኑ ያክል ይከብዳል፡፡ ገጽ 268
የአንድዮሽ ፍቅር… ገጽ 304
ጥቃቅን ሕጸጾች
አልፎ አልፎ እንደጠዋት ሰማይ ከዋክብት የሚታዩት የፊደል ግድፈቶች፣ እንግሊዝኛን ባማርኛ ቀጥታ መጻፍ፣ ያላግባብ የገቡ የሚመስሉ ሐረጎች(ስምንት ሰዓት ሊሆን ምንም አልቀረውም ነበር- አይነት…)፤ የፊደላት እና የቃላት አገባብ ወጥነት መዛባት ለምሳሌ ሥነልቦና-ስነልቦና፣ ዘበኛ ጥበቃ…፤እንደ አረም በቅለው የተቀጠፉ ገጸ ባሕርያት(ታካሚዎች ለምሳሌ እነ ኑረዲን፣ ሕሊና፣ የንጹሕ ልጆች ቶሎ ማደግ፣ የምስጢር ቶሎ የሕጻን (የልጅ) ገጸ ባሕርይ መልበስ፤ አልፎ አልፎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ አንድን ባሕርይ ለገጸ ባሕርይ ማልበስ(ጥቁር ቤልት ለሳንቾ የተሠጠው ማስረሻ ለማጠቃት እንደሆነ፣ ሌላሠው ከሠራተኛው ልጆች ጋር ደብተር እንደሚያይላቸው ሲነገረን፣ የአዕምሮ ሙያ ሕክምና ባለሙያ ያገባት ሚስት አስቀድማ ለአሉባልታ እና ለወሬ የማትበገር ስብዕና አለመላበስ ባመዛኙ ቅር ያሰኙን ትረካዎች ናቸው….)
አጠቃላይ ጭብጥ!
በአጠቃላይ መጽሐፉ ከ “ቆሼ እስከ ቦሌ”፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኑሮ ልዩነት፣ በተለይ በሡስ እየተሰቃዬ ያለውን ወጣት ትውልድና ኢትዮጵያን በዜና ለሚያውቋት የልማት ጆሮዎች አንድ ትልቅ የአይን እማኝ ከሆነ ዘጋቢ የተገኘ ምስል ነው ‹‹ሌላ ሰው›› መጽሐፍ፡፡
አጨራረስ
ማሳረጊያው እንደ ተለመደው ብዙኃኑ ኪነጥበብ ስራዎቻችን እንትናን ከንትና ተፋቅረዋልና ማጋባት፣ እንትና ታማለችና ትሙት፣ አሊያም ትዳን… አይነት ሳይሆን መሆን ያለበትን ሁሉ እስኪሆን ሁሉንም ለጊዜ መስጠት ትልቅ ጸጋና በረከት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የደብረ ሊባኖስንም መልእከ ምድር ለማስቃኘት የሞከረበት መንገድ ውብና ማራኪ ነው! የኛ “ግራንድ ካንየን”
Debrelibanos_Cann..

በተረፈ የመጽሐፉ ውይይት መድረክ ተዘጋጅቶለት ደራሲውም በአካል ተገኝቶ ሰፊ ልምዱንና ጊዜውን እንደሚያካፍለን ተስፋ በማድረግ፡-
ፍቅር በልመና ማስፈራራት በማጭበርበር በአንዱ ሰው ጠንካራ ስሜትና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ፍቅር በሁለት ሰዎች በጎ ፈቃድ ብቻ የሚፈጠር የሁለትሽ መንገድ ነው፡፡ በሚለው ሐሳብ ተመራርቀን
ሁሉም ነገር ገብቶኛል ሀገር ሰው ነው… ቤት ፍቅር ነው….ምቾት ለሌላ ሰው መኖር ነው… በሚለው ነጥብ ተስማምተን
ቤትን ከሚያፈርስ፣ ፍቅርን ከሚፈትን፣ ሰውን ከሚቀብር  ሌላ ሰው ይሠውረን!! ተማጽነን
ቸር እንመኛለን…!


Jul 30, 2015

እመጓ..!



እመጓን እንዳነበብኳት…!
ተስፋ በላይነህ
            
     አሜሪካ ሁሉ ነገር ትልቅ ነው፡፡ ትልቅ አዳራሽ፣ ትልቅ ኤርፖርት፣ ትልልቅ ድልድይ(ዮች?)፣ ሰፋፊ መንገድ፣ ትልልቅ መኪና(ኖ?)፣ ትልልቅ ሀምበርገር፣ በቃ ትልልቅ ነገር ያለባት ሀገር ናት፡፡ ምናልባትም ትልቅነትን በትውልዳቸው ከሚቀርጹባቸው መንገዶች አንዱ ይሄው ትልቅ ነገሮችን ማሳየት ማለማመዷና መስተዋወቅ ሊሆን ይችላል፡፡ አስቦ መስራት ካለ ምን ችግር አለ፤ ሁሉንም ነገር ማሥተማሪ፣ ሥነ ልቡናዊ ማንነት መገንቢያ አድርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ‹‹እመጓ›› ገጽ 16፡፡

የዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ መጽሐፍ ይሕንን ዓላማ አንግቦ የተጻፈ በመሆኑ ጭምር ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ ዋናውንና ተጨባጭ መረጃ-ማስረጃ የሚጠይቀውን የቅዱስ ጽዋ (holy grail) መገኛ ኢትዮጵያን ማድረጉ እንደ ሁለተኛ የመጽሐፉ ምሶሶ አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡
ትውልድን ታላቅ ነገር በማሳዬት፣ ታላቅ አገር መፍጠር ይቻላል፡፡ የሰውን ልብወለድ ራሳችን ላይ በመካብ አንድ ትውልድ ላይ አጥር ከመሥራት፤ የራሥን ታሪክ መዝኖ በጎና አዎንታዊ አስተሳሰብ የሚፈጥርን ትልቅ ሐሳብ ማቅረብ ከጉዳቱ ጥቅሙ የሚያመዝን ሆኖ ይታዬኛል፡፡ ሁልጊዜም ምዕራባዊያኑ ያላጠኑትን፣ ያልባረኩትን እውቀት እና ያልቀደሱትን መረጃ እንደ እውነት የማንሳለም ሰዎች፤ ይሕንን አይነት መጽሐፍ ማቅረቡ ላይ እንከን አለበት ብዬ ሙሉ በሙሉ አልኮንነውም፤ ሆኖም..

ሆኖም አንድ ትልቅ ፊኛ በአየር ተነፍቶ ወደ ሰማይ ሲለቀቅ፤ ያለው እብጠት እና ኩራት፤ ውስጡ የራሱ ማንነትና ልዕልናን የተጎናጸፈ መሥሎት፤ አየር ላይ እንደሚከንፍ አውራ ደሮ መሥሎ ሲያንዣብብ፤ ወዮ! ለዛ ፊኛ፤ ትንኝ የነከሰችው ‘ለት…! መርፌ የተጠጋችው ‘ለት!

እኛም እንዲሕ እንዳንሆን ስጋት አለብኝ! በባዶ ማንነት ላይ ትልቁን አየር ሞልተን ፊተኛ፣ አንደኛ ነን ስንል! ዋናውን መሰረት ልብ ውስጥ ሳንገነባ መብረር ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ትልቅ አገርን ለመመሥረት በልቡና የሚሞላ ትልቅ ጠጣር እውነት ያስፈልገናል፡፡ ጠጣር እውቀት፡፡ ማሕበረሰቡ እየታመመ ግለሰቦች ጤነኛ ነን ቢሉ ፋይዳው ፍደሳ ብቻ ይሆንብናልና! “በሰለጠነው በምዕራቡ ዓለም መጥፎው ግለሰቡ ሳይሆን ማሕበረሱ ነው” እመጓ ገጽ 93፡፡ሥለዚህ እመጓን ስናነብ ውስጣችንን በጠጣር እምነት ሞልተን፤ አውቀትንና እውነትን ለመገንባት ከፍተኛ ትግል እንደሚጠበቅብን እገነዘባለሁ፡፡
‹‹እመጓ›› ምናልባትም ከዴርቶጋዳ ቀጥሎ የወጣች አነጋጋሪ መጽሐፍ መባል አይበዛባትም! ጎጃምን መሠረት እያደረጉ የሚወጡ መሰል መጽሐፍት፤ መንዝን፣ በጌምድርን፣ ደቡብ ጎንደርን እና የሠሜኑን ክፍል በምሥጢራዊ ዋሻዎች ጥልቀትና ድምቀት፤ ኢትዮጵያ በጉያዋ የያዘቻቸውን ቅርሶች፣ ጸጐች፣ ረድኤትና በረከቶች እንድናሰላስል- ‹‹ዴርቶጋዳም›› ‹‹እምጓም›› ይተይባሉ! አያይዘንም የ‹‹እመጓ››ው ጸሐፊ ከዴርቶጋዳ መጽሐፍም ሆነ ጸሐፊ መማር ያለበት ብዙ ነገር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በኔ በኩል ‹‹እመጓ›› የጸሐፊውን ሳይንሳዊ ሲሳዮች (በረከቶች) እንደ ማጣፈጫ አድርጋ ስላዘለች፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ባሕላዊ፣ ጥንታዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች (እሴቶች) በቀላል አማርኛ እየጠቀሰ፤ ከኛ የነበረውን ወስደው ወደኛ ሸጡልን አይነት ዘገባዎች አካታ ይዛለች- ‹‹እመጓ››፡፡ ይሕንን ለመቅረፍ መፍትኄው ምንድን ነው??

መልሱ፡- በመጀመሪያ ሥለኛ ማንነታችን ያለን ዋጋ እና ክብር የመሠረት ድንጋይ ነው! ቀጥሎሥ..?
እመጓ በ204 ገጽ አጥር እጥር፣ ምጥን ክሽን ተደርጋ እንደተቁላላች ወጥ በአምሳሁለት ብር ሂሳብ ቀርባለች፡፡ በውስጧ የያዘችውን መልዕክት ስናስብ፡- ቅዱሱ ጽዋ እውነት በዚሕች ምድር አለ? የለም? ብሎ ለሚጠይቅ አንባቢ፤ በለበጣ የሚደመም እና ይሕንን ጉዳይ እንደፌዝ 
የሚወስድ የትውልድ ቁጥር ጥቂት አይሆንም!

አንድ ጥያቄ፡-
ይሕ ቅርስ በዚህች ምድር የለም ለማለት ምን ምክንያት አለን? ይህ ቅርስ በዚህ ምድር አለ ለሚለው ደግሞ የዓለማየሁ ሲሳይ በእመጓ ደረቱን ነፍቶ በቆላማዋ እመጓ ጉያ ውስጥ ተቀምጧል ይለናል፡፡
የዓማየሁ ሲሳይ፡-

የዓለማየሁ ሲሳይ ምናልባትም የሥነ-ምሕዳር ሙያዊ ብቀቱን እና ልምዱን ከጎበኛቸው የገዳም ሰዎች እና ቦታዎች ጋር ተዳምሮ ይሕን መጽሐፍ ለመጻፍ ረድቶታል፡፡ የዓለማየሁ ሲሳይ ማለት ደግሞ በ‹‹እመጓ›› መሪ ገጸባሕርዩን ይዞ የሚተርክልን ሰጋ አልባ ግለሰብ ነው፡፡ ሲሳይ አለማየሁን ፈጠረ ወይንስ አለማየሁ ሲሳይን…?

አሁንም በመጽሐፉ ውስጥ ቀላል የማይባሉ ቁምነገር አዘል ትርክቶች ቀርበዋል፡፡ ከቦሌ አየር ማረፊያ አንስቶ እስከ ዋሽንግተን፤ ከዚያም መልስ ደግሞ ወደ ገጠራማ የሰሜን ሸዋ ተራሮች፣ ጨጨሆንና በጌምድርን እንዲሁም ጎጃምን ያስቃኘናል፡፡እንደ አዋሽ ወንዝ ፈስፈው ባንደኛው ገጽ ላይ ጠፍተው የሚቀሩ፤  ደራሲው ፈጥሮ የገደላቸውን አንዳንድ ገጸ ባሕርያትም ሥናስብ፤ ታስቦበት ከሆነ እና ለታሪኩ ፍሰት የበቀሉ ቋጥኝ ገጸባሕርያት ከሆኑ ብንቀበልም፤ የሰው ነፍስ ማጥፋት ደግሞ ሥለሚያስጠይቅ ልብ ማለቱ ላይ እንበረታለን፡፡ (የፒስኮሩ አንድሪው ባረነስን የመሰሉ ገጸ ባሕርያትን ልብ ይሏል፤ አሊያም የመርዝ መከላከያ እና ኦክስጅን ቃል የተገባላቸው መነኩሴ…)

በተጨማሪም እመጓ ይሕንን ትውልድ እና አገራዊ ገጽታ ለመቃኘትም ትሞክራለች፡፡ ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ምእራባዊያንን የሙጥኝ ማለታችን ይጎዳናል እንጂ የሚጠቅመን ነገር የለም ትለናለች፡፡ (ሉሲን እንደ ብርቅዬ የሚያይ ሲሆን ደግሞ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል)፡፡ በገጽ 164 “ብርቅዬ ሉሲን እንኳ አሜሪካ ድረስ የወሰድን፣ ጎብኝ ወደ ቅርስ የመጣል እንጂ ቅርስ ወደ ጎብኚ…” በማለት መላካችንን እንደ ድክመት ይገልጸዋል፡፡ ቅዱሱን ጽዋ እንደ ታላቅ በረከት እና ቅርስ የሚቆጥር ሰው “ሉሲ”ን እንደ ብርቅዬ መቁጠሩ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይዞት ከሚጓዘው ጭብጥ ጋርም የሚጣረስ ነው፡፡

በብራና ላይ ገጽ የተገኘውን ካርታም (በመጽሐፉ ገጽ መመልከት ይቻላል)፤ አራቱን አቅጣጫ ያስቀመጠ እና አምስት ክቦች የትክተት ነጥቡን (center) አቋርጠው የሚሄዱ አውታሮች (diameter) ልክ እንደ የተባበሩት መንግሥታት አርማ ጋር ይመሳሰላል፡፡(በመጽሐፉ ገጽ 174 መላምት ቀርቦበታል) ፡፡የዩናይትድ ኔሽኑ አርማ 33 ክፍሎችን የያዘ ክብ ሲሆን ይሔኛው ደግሞ ከ6 የተከፋፈሉ አምዶችን ይዟል፡፡ ይሕ ክፍፍል በጸሐፊው ዘንድ ታስቦበት እና የተባበሩት መንግስታት አርማን ልብ ብሎት ከሆነ ብዙ መመራመር የሚያስፈልገው ስራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጸሐፊው ሥለ ሚጥራዊ ቡድናት ዓላማ፣ ማንነትና መረጃ ቢኖረው መልካም እንደሚሆን ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም፡፡



ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚነሳው ነገር በመጽሐፉ ሽፋን የተቀመጠችው የተጠላለፉ የ “ቪ” ፊደል መሳይ ምልክትን ነው፡፡ ምልክቶች በየአገልግሎት ስፍራቸው እና ቦታቸው የየራሳቸውን ትርጉም ሊሰጡ ቢችሉም፤ በኔ አስተሳሰብ የ“ቪ” ንብርብሮሽ የሚሰጠን ምልክት የፈሪሜሶኖችን አርማ ይሆናል፡፡ (ትሪያንግል ሆቴልን ድሬዳዋ ላይ ስመለከት ግራ ተጋብቻለሁ አርማውን ልብ ይበሉ)

ሆኖም እንደ ጸሐፊው እምነት የ “ቪ” ፊደል መጠላለፍ የቅዱስ ጽውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በተደጋጋሚ እጃቸው ላይ ያሳዩት ነበረውን ምልክት ልብ እንድንል ከማስቻሉም በላይ በምልክቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጥናት እና ምርምር ማድረግ እንዳለብን በስፋትና በጥልቀት እንረዳለን!

ወጣም ወረድም ከዚሕ በኋላ ኢትዮጵያ የዓለማችንን ምስጢራዊ ቅርሶች አሉኝ ከሚሉ አገሮች ጋር እንድትቀጥል ትሆናለች፡፡ ጽላተ ሙሴ፣ ግማደ መስቀል፣ ቅዱሱ ጽዋ… እንደዚህ ጽሑፍ ጸሐፊና በዚህ አስተያዬት ሰጪ አስተሳሰብ መሠረት መጽሐፉ በቅድሚያ ትልቅ አገር የመፍጠርን መፈክር ይዞ የተነሳ በሚለው ሐሳብ ላይ ከማተኮር ውጭ፤ ይሕ ቅርስ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የለም በሚለው ክርክር ላይ በዚህ ጽሁፍ ላይ ለማተኮር ፈቃዱን አይወስድም፡፡ ጊዜ ይፈልጋልና፡፡ የፊኛውን ታሪክ ግን እናስታውስ…!
መልካም ንባብ፤

ዶክተሩንም በሌላ ሥራ እንድምንገኛ እየተመኘን ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር የተለማመዱ ግለሰቦች መሠል ስራዎችን እንዲሰሩ፤ አገራቸውን እንዲያነቡ፣ እንዲያስነብቡ አገርንና ትውልድን ከእልቂት እንያድኑ በመማጸን፤ በትልቅ አገር እና ታላቅ ትውልድን የመፍጠር ዓላማ ላይ ቢሳተፉ፤ ከወሬ የዘለለ ተግባር እና እውቀት እንዲሁም እምነትን አንግበው ቢንቀሳቁ የበኩላቸውን ድርሻ ኃላፊነት እየተወጡ ነው ማለት ስለሚቻል፤ መጽሐፉን ያገኘኋትን ምክር ዘአል ሐብረ-ቃል በመጋበዝ እንሰነባበበት!

“ጨለማ ጸጥታ ነው፡፡ ጨለማ ሰላም ነው፡፡ ትኩረትህን የሚስብ ምንም የምታየው ውጫዊ ነገር የለም፡፡ የምታየው ነገር ቢኖር የውስጥ አንተነትክን ነው፡፡ በብርሃን ሌሎችን እናያለን በጨለማ ግን ራሳችንን እናያለን፡፡ ሰው ራሱን እንደማየትና እንደማወቅ ያለ ኃይል የለውም፡፡ ጨለማ ደግሞ ይህን ኃይል ያጎናጽፍሃል፡፡ ገጽ 194፡፡

በሐዲስ ኪዳን ወንጌል ጸጋዎች እና በተደጋጋሚ ሲነሳ የምናስተውለው “ብርሃን” እዚህ ላይ የተነጻጸረ አይመስለኝም፡፡ ቢሆን የዚህ ጽሑፍ ዓላማና ጭብጥ በዚህ ቃል በዜሮ ይባዛል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ራሱን ብቻ መመልከቱ እና ሌሎችን ያለማየት ኃይልን ሲጎናጸፍ፤ “እኔ ነኝ” ወደ ሚለው የውድቀት ቃል ተወርውሮ ወደ ጥልቁ እንዳይከንፍ የዚህ አስተሳየት ሰጪ የሁልግዜ ምክር ነው፤ የተጣለውን መላዕክ እንመልከት፤ የሚበረውን ፊኛ እናሰብን..!