ሌሳ ሠው በምሕረት
ተስፋ በላይነህ
LELA_SAW-DR_MEHRET |
ይመስለኛል በመጽሐፍ ያለን ባሕል በመጠኑም ቢሆን ከእንቅልፉ እየነቃ ያለበት አቅጣጫ ላይ ነን፡፡ ምንም እንኳን የሕትመት ቁጥር፣ የአንባቢ ብዛት እና አጠቃላይ አለም አቀፋዊ ንጽጽራችን ያሽቆለቆለ ቢሆንም፤ ከእንቅልፍ መንቃት በራሡ አንድ እርምጃ ነውና፤ ረዥሙን ርምጃ በማሰብ በርብርብ ካልተንቀሳቀስን አሁንም ቆመን ማንቀላፋታችን አይቀርም፡፡ ተያይዞ መቅረብ ያለበት ነገር ቢኖር የንባብ ባሕሉን ለፖለቲካ ጥቅም ማሳኪያ እና ገቢ ምንጭ-ተኮር(ሸቀጥ) አዝማሚያችን እየሰፋ ከሄድን ደግሞ ሌላ ኣዙሪት ውስጥ እንደምንገባ በመገንዘብ የሁላችንም ኃላፊነት ሰፊ ነው፡፡
‹‹ሌላ ሠው›› የተሠኘውን የዶክተር ምሕረት መጽሐፍ ስመለከት፤ “ይሕ ሁሉ ብዛት ምን ሊኖረው ይችላል?” ከሚል ጥያቄ አንብቦ የመጨረስ ፍላጎቴ መነሻ ነበር፡፡ big books are evil የሚባለውን እና ሸክሙን ለተሸካሚው እዘኑለት አይነት አባባል በውስጤም ነበር፡፡ አሁን አሁን አጫጭር ልብወለዶች እና ወጎች ረዥም ጊዜ ሰጥተን አንድ መጽሐፍ ላይ የትዕግስትን ኃይል፣ ስሜትን የመግዛት ጥበብ እና የማስተዋል አቅማችንን ለሚፈትኑት፤ አንባቢም ጥቂት ነገር የመያዝ እንዲሁም ባንዴ አስቂኝ እና አስገራሚ ይዘት ያላቸውን ጭብጦች ለማካለል ሲል፤ የገበያው ሁኔታም ተደምሮለት በወግ እና በአጫጭር ልቦለዶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደረገው ይመስለኛል፡፡
በበኩሌ በእነዚህ ቅርበ ዓመታት ውስጥ ካነብኳቸው አጫጭር ልቦለዶችና ታሪኮች እንዲሁም የወግ ይዘት ካላቸው መጽሐፍት የአሌክስ አብርሃም በላቀ ይዘትና ጭብጥ አስደምሞኛል፤ በአጫጭር ታሪኮች የሥነ-ጽሑፍ ደርዝ ውስጥ የራሱን አሻራ እያኖረ ያለ ነው! ሥለዚህ ያጫጭር ልቦለዶችን የጎንዮሽ ጉዳት ስንመለከት መሠል ስራዎችን እያጥላላን አይደለም! የራሳቸው ድርሻ አላቸውና! ሥለዚህ ማንም በመክሊቱ እና በተገለጠለት ጸጋ ሆኖ ያሻውን እንዲጽፍ የፈቃድ ድርሻውን እንዲወስድ ተፈጥሮአዊ መብቱን እየሠጠነው፤ ይሕንን የገበያ ሁኔታ፣ የዘመን አባዜ እና መርህ ተላቆ ደግሞ “ረዥም ልብወለድ ያዋጣኛል”፣ “ምርጫየም ነው” ብሎ የሚጽፈውንም ከማመስገን አልፎ ልናበረታታና ትኩረት ልንሠጠውም ይገባል! ለዚህ ነው ‹‹ሌላ ሠው››ን በአትኩሮት እንዳነበብና ያለኝን አስተያዬት ለመሥጠት የተነሳሁት!
መጽሐፉ!
መጽሐፉ ባለ 451 ገጽ፤ ስድሰት አበይት ክፍሎች (የመዳረሻው መነሻ፣ድልድይ፣ሰዎቹ፣ሌሎቹ ሰዎቹ፣ ሌላ ሰው፣እና ማሳረጊያ)፤ በ49 ንዑስ ክፍሎች ተከፋፍሎ፤ አንድ ከአሜሪካን አገር በመጣ የአዕምሮ ሕክምና ጠበብት (ስፔሻሊሥት) አባቱ በተወለት “ውርስ” አማካኝነት አደራውን ለመወጣት የሚከፍለውን ምድራዊ መስዋዕትነትት ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡ ውርስ ሁልጊዜ ሃብት እና ርስት ላይሆን ይችላል፡፡ ያ’ባት የ’ናት አደራ ትልቅ ውርስ ነው፡፡ ውርስ ተቀባይ ትውልድ ደግሞ ድልድይ ነው፡፡ ድልድዩ ድንጋይ፣ አርማታ እና ስሚንቶ ብቻ ሳይሆን በዋጋ የማይተመነው የሰው ልጅ ነው፡፡ መጽሐፉ በአጠቃላይ ሥለ ሰው ጀምሮ በሰው ላይ የሚያልቅ፣ በግልጽ ልማት እና እድገት ተብሎ ዘወትር ከምንሰማው ሐሳብ ተላቅቆ የሰውን ልጅ እናክብር ሲል የሚሟገት የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን በመፈተሸ ደረቱን ሰጥቶ የሚሟገት ነው!
ገጽ 439 እንዲህ ይነበባል፡
“….አስበው እስኪ… አባትህም ያሉት እኮ… ህንጻና መንገዱን ሳይሆን… ሰዎችን ይመስለኛል… ሀገር ሰው ነው…. ሰው ሰው ሲሆን ሀገር ሀገር ይሆናል….”
መጽሐፉ መንግስት ከሚከተለው የልማታዊነት አስተሳሰብ የተለየ ዜናን ይዞ ነው ከአራት መቶ ገጽ በላይ የሚያስከንፈን፡፡ ሁሉም ገጽ፣ ሁሉም ሐሳብ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ክብር ጋር ያላትመናል፤ የሰውን ክቡር እቃ ጭንቅላት ላይ የሚሠራን ልማት እንደ ስኬት ቆጥሮ በማማው ላይ ነጋሪቱን ይጎስማል- በለሆሳስም ያንኳኳል!
መጽሐፉ እያንዳንዷን ድርጊት ተራ በተራ ስለሚዘግብ አንዳንዴ ትዕግስት ያስጨርሳል፣ “ይሕም መጻፍ ነበረበት?” የምንላቸው ብዙ ቦታዎች አሉበት፣ በእርግጥ ጸሐፊው ያለውን የሥነልቦና እና የአዕምሮ ሕክምና ሙያ ተጠቅሞ የሥነጽሑፍ ጸጋውም በሁለት ሰይፍ እንደተሳለ ብዕር ባለቤት ቢሆን ከዚህ የበለጠ ሥራ ሊወጣው እንደሚችል አስባለሁ! በየንዑስ መዳረሻ ገጾች ላይ አዕምሮን ያዝ የሚያደረጉ አጠቃለይ ሰብዓዊ ምክሮች ን ደግሞ ስናስብ ለመጽሐፉ ውበት እና ምሶሶ የሆኑት የማንክዳቸው መሰረቶች ናቸው!
አንድን ማሕበረሰብ ለመገንባት የማሕበረሰብ ጠበብት በዋነኝነት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው እንደሚያገለግሉት ሁሉ፤ በዚሕ መጽሐፍም የምናዬው አንድ ማዕከልን በማቋቋም የታመመውን ሕብረተሰብ ለመፈወስ የሚደረግ ትግል ነው፡፡ ሆኖም ታማሚን ማከም ብቻ ሳይሆን ጤነኛውም እንዳይታመም በሚለው ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ዋናው የስራ ድርሻም ያለው እዚህ ላይ መሆኑን ተረድቶ አንድ አዕምሮ ገንቢ እና አስተማሪ የሆነ ማዕከል እንደሚያስፈልግ የዚህ ጽሑፍ አስተያዬት ጸሐፊ ጥብቅ ምክሩ ነው፡፡ በመጽሐፉ ትምሕርት ቤቶች እንዴት መገንባት እንዳለባቸው፣ አካባቢያችን እንዴት መጠናከር እንዳለበት እና ባለድርሻ አካላት በተለይ መንግሥት ኃላፊነቱን አስታክኮ ሙያዊ ድርሻው ላይ ከፍተኛ ጫና በብዛት ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡ የሱስ፣ በጾታዊ ጥቃት፣ ባለፈ ታሪክ ሽንቁሮች ተለክፈው የአእምሮአቸው ሚዛን የተዛባባቸው ግለሰቦችን ለማከም የተቋቋመው ማዕከል የራሱን ድርሻ የመወጣት ኃይል ቢኖረውም፤ የዚህች አገር ችግር ከስር መሰረቱ አጥንቶ ማሕበረሰባዊ ድውይን ለማከም ያለመ የጤና ባለሙያን እንመለከታለን -ዶ/ር ሌላሠው፡፡
የማሕበረሰብ ጠበብቱ ለማሕበረሰብ ምሕንድስና መሪና ቀንደኞች አድርገው ሲጠቅሷቸው የምንመለከታቸው እነ ሲግመንድ ፍሩይድን እና መሠል ደቀመዛሙርትን ሥለሆነ፤ ከኛ የበቀሉ፣ የኛን ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖት እንዲሁም ቤተሰባዊ መዋዕቅር የተላበሱ ጠቢባን እንደሚያስፈልጉን ለማንም የሚካድ አይደለምና! እንደውም ‹‹የአመጻ መንገድ›› የተሠኘው የተክሉ አስኳሉ መጽሐፍ የሲግመንድ ፍሩይድን እያንዳንዱን መላምት እየነቀሰ ከኛ ባሕል፣ ሃይማኖት እና ማሕበረሰባዊ ድባብ ጋር እያጣመረ ውድቅ ሲያደርገው በማንበባችን፤ በመጽሐፉ በገጽ 97 እና በሌሎችም የሲግመንድ ፍሩይድ ሥራ የሆኑትን የህልም አተረጓጎም (ዘ ኢንተርፕሪቴሽን ኦፍ ድሪም) እና ኦዲፐስ ኮምፕሌክስ… አፈታሪኮችን እንደምሳሌ እየጠቀሰ ማቅረቡ በዋናነት፤ ስለ መወላወል የተፈጥሮ ባሕርይ ወይንም በምስራቁ አለም “ዪን እና ያንግ” ፍልስፍና በገጽ 251፣ እንዲሁም ስለ ጾታ ቅራኔ “ፌሚኒስት” አስተሳሰብ ውይይቶች ትልቅ ሙግትን እና የመወያያ መድረክን የሚሹ ናቸው! ሆኖም በገጽ 100 ላይ የጠጠቀቀሰው ንግግር ከጸሐፊውም ሆነ ከሙያው ሙያተኞች ማሕበረሰባችን ብዙ እንደሚጠበቅ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ቀጣይ ሥራ እንዳለውም እንረዳለን፡፡ ገጽ 100 አራተኛ አንቀጽ እንዲህ ይነበባል!
“ከዛ በተጨማሪ ደግሞ መጻፍና ምናልባትም ሚድያ ውሰጥ ገብቶ የሰውንሥነልቦናዊ ንቃት መኮርኮርና ማሳደግ ይመስለኛል ዋና የትረኩረት አቅጣጫዬ እኔ እንደማማነው ያበሻ ነፍስና ሥነልቦና ለረዥም ዘመናት ከምናስበው በላይ የቆሠለና መከራ የተሸከመ ነው፡፡ ያለፈውን አርባና አምሳ ዓመት እንኳን ብታስበው ይዘገንንሃል፡፡ ያ ሁሉ ያልታከመ ሕመም ያልተከፈለ የሥነልቦና ዕዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገሩ ያንድ ቀን ሥራ አይደለም በርግጥ፡፡”
ጥያቄ፡- ባጠቃላይ ሱሰኛ ሆኖ የሚወለድ ሰው ባይኖርም ሱሰኛ ለመሆን የበለጠ የተጋለጠ ማንነት ይዘን ልንወለድ ግን እንችላለን---
አስደማሚ ቅንጥብጣብ ሐሳቦች
…እና አንዳንዴ የድብቅነት ባሕላችንን ከምን ጋር ይመሳሰልብኛል መሰለሽ? … አስቢው ከደጅ የሚታዩትን በረንዳችንንና አጥራችንን እንዴት እንደምናሳምር፡፡ ደግሞ የበለጠ የሚጠቅሙንን የምንጠቀምባቸውን ኩሽዎቻችንንና የሽንት ቤቶቻችን… አስቢያቸው- ገጽ 71
…ስኪዞፍሬን… የቃሉ ትርጉም የተከፋፈለ አዕምሮ እንደማለት ነው… ይህም ሕመሙ የውጭውን ነባራዊ እውነታ እና በውስጣችን የሚገኘውን የሐሳብ ዓለም አጣጥሞና አስማምቶ ለመኖር አለመቻልን ስለሚፈጥር ነው፡፡ ያልሆኑ ነገሮችን ማመንና የሆኑትን መካድ… ያልተፈጠሩ ነገሮችን ማየትና መስማትን… በዚህም የውስጥ መረበሽ የተነሳ የንግግር፣ የባሕርይና የስሜት መዛባቶችም ይፈጠራሉ፡፡ ገጽ 93፡፡/ይሕ የእብደት ምሳሌ ነው- አገራችን ሰንቱ እንዳበደ ማሰቡ በቻ በቂ ነው፡፡ የሚነገረን ሌላ፣ የምናዬው ሌላ፣ የምናምነው ሌላ የሆንነው ሌላ… ይሕም ራሳችንን በሚገባ እንድንመለከት ያስገነዝበናል!/
“…ማንን ትከሳለህ ሌላሠው? ሆስፒታሉን….ሐኪሞቹን… ነርሲቹን…ዘበኞቹን….የጽዳት ሠራተኛዋን….ጤና ጥበቃን….ማንን? የተለከፈ ሀገር ውስጥ እኮ ነው የምንኖረው፡፡ ደግና ሰው አክባሪ ባሕል እየተባለ ቢለፈፍም እውነቱ ግን ኅሊና የሌለው ጨካኝና ለሰው ዋጋ ደንታ የማይሠጠው ሰው ነው የሚበዛው፡፡ ማንን ትከሳለህ?.... ገጽ 163
“…ግን ምን ይደረግ ሕያዋኑ ቲሸሹን(ሲሸሹን) ጊዜ ተሙታን(ከ) ተጠግተን እንኖራለን… ገጽ 183 (ቅንፍ የኔ)፡፡
“…ፍቅር ስለ ሌላው እንጂ ስለ ራስ ማሰብ አይደለም፡፡ ራስን ስሌላሰው ደስታ ስለ መስጠት እንጂ ሌላውን ሰው በግድ የራስ ማድረግ ሊሆን አይችልም፡፡ ፍቅር ሲታመም ሁሉም ነገር ይታመማል… ስብእናም… አስተሳሰብም… ስሜትም….የራስም…የሌላው ሰውም፡፡ የታመመ ፍቅር ከሁሉ የተወሳሰበ የነፍስ ደዌ ነውና ማዳኑም የዛኑ ያክል ይከብዳል፡፡ ገጽ 268
የአንድዮሽ ፍቅር… ገጽ 304
ጥቃቅን ሕጸጾች
አልፎ አልፎ እንደጠዋት ሰማይ ከዋክብት የሚታዩት የፊደል ግድፈቶች፣ እንግሊዝኛን ባማርኛ ቀጥታ መጻፍ፣ ያላግባብ የገቡ የሚመስሉ ሐረጎች(ስምንት ሰዓት ሊሆን ምንም አልቀረውም ነበር- አይነት…)፤ የፊደላት እና የቃላት አገባብ ወጥነት መዛባት ለምሳሌ ሥነልቦና-ስነልቦና፣ ዘበኛ ጥበቃ…፤እንደ አረም በቅለው የተቀጠፉ ገጸ ባሕርያት(ታካሚዎች ለምሳሌ እነ ኑረዲን፣ ሕሊና፣ የንጹሕ ልጆች ቶሎ ማደግ፣ የምስጢር ቶሎ የሕጻን (የልጅ) ገጸ ባሕርይ መልበስ፤ አልፎ አልፎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ አንድን ባሕርይ ለገጸ ባሕርይ ማልበስ(ጥቁር ቤልት ለሳንቾ የተሠጠው ማስረሻ ለማጠቃት እንደሆነ፣ ሌላሠው ከሠራተኛው ልጆች ጋር ደብተር እንደሚያይላቸው ሲነገረን፣ የአዕምሮ ሙያ ሕክምና ባለሙያ ያገባት ሚስት አስቀድማ ለአሉባልታ እና ለወሬ የማትበገር ስብዕና አለመላበስ ባመዛኙ ቅር ያሰኙን ትረካዎች ናቸው….)
አጠቃላይ ጭብጥ!
በአጠቃላይ መጽሐፉ ከ “ቆሼ እስከ ቦሌ”፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኑሮ ልዩነት፣ በተለይ በሡስ እየተሰቃዬ ያለውን ወጣት ትውልድና ኢትዮጵያን በዜና ለሚያውቋት የልማት ጆሮዎች አንድ ትልቅ የአይን እማኝ ከሆነ ዘጋቢ የተገኘ ምስል ነው ‹‹ሌላ ሰው›› መጽሐፍ፡፡
አጨራረስ
ማሳረጊያው እንደ ተለመደው ብዙኃኑ ኪነጥበብ ስራዎቻችን እንትናን ከንትና ተፋቅረዋልና ማጋባት፣ እንትና ታማለችና ትሙት፣ አሊያም ትዳን… አይነት ሳይሆን መሆን ያለበትን ሁሉ እስኪሆን ሁሉንም ለጊዜ መስጠት ትልቅ ጸጋና በረከት እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የደብረ ሊባኖስንም መልእከ ምድር ለማስቃኘት የሞከረበት መንገድ ውብና ማራኪ ነው! የኛ “ግራንድ ካንየን”
Debrelibanos_Cann.. |
በተረፈ የመጽሐፉ ውይይት መድረክ ተዘጋጅቶለት ደራሲውም በአካል ተገኝቶ ሰፊ ልምዱንና ጊዜውን እንደሚያካፍለን ተስፋ በማድረግ፡-
ፍቅር በልመና ማስፈራራት በማጭበርበር በአንዱ ሰው ጠንካራ ስሜትና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ፍቅር በሁለት ሰዎች በጎ ፈቃድ ብቻ የሚፈጠር የሁለትሽ መንገድ ነው፡፡ በሚለው ሐሳብ ተመራርቀን
ሁሉም ነገር ገብቶኛል ሀገር ሰው ነው… ቤት ፍቅር ነው….ምቾት ለሌላ ሰው መኖር ነው… በሚለው ነጥብ ተስማምተን
ቤትን ከሚያፈርስ፣ ፍቅርን ከሚፈትን፣ ሰውን ከሚቀብር ሌላ ሰው ይሠውረን!! ተማጽነን
ቸር እንመኛለን…!
No comments:
Post a Comment