Jul 30, 2015

እመጓ..!



እመጓን እንዳነበብኳት…!
ተስፋ በላይነህ
            
     አሜሪካ ሁሉ ነገር ትልቅ ነው፡፡ ትልቅ አዳራሽ፣ ትልቅ ኤርፖርት፣ ትልልቅ ድልድይ(ዮች?)፣ ሰፋፊ መንገድ፣ ትልልቅ መኪና(ኖ?)፣ ትልልቅ ሀምበርገር፣ በቃ ትልልቅ ነገር ያለባት ሀገር ናት፡፡ ምናልባትም ትልቅነትን በትውልዳቸው ከሚቀርጹባቸው መንገዶች አንዱ ይሄው ትልቅ ነገሮችን ማሳየት ማለማመዷና መስተዋወቅ ሊሆን ይችላል፡፡ አስቦ መስራት ካለ ምን ችግር አለ፤ ሁሉንም ነገር ማሥተማሪ፣ ሥነ ልቡናዊ ማንነት መገንቢያ አድርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ‹‹እመጓ›› ገጽ 16፡፡

የዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ መጽሐፍ ይሕንን ዓላማ አንግቦ የተጻፈ በመሆኑ ጭምር ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ ዋናውንና ተጨባጭ መረጃ-ማስረጃ የሚጠይቀውን የቅዱስ ጽዋ (holy grail) መገኛ ኢትዮጵያን ማድረጉ እንደ ሁለተኛ የመጽሐፉ ምሶሶ አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡
ትውልድን ታላቅ ነገር በማሳዬት፣ ታላቅ አገር መፍጠር ይቻላል፡፡ የሰውን ልብወለድ ራሳችን ላይ በመካብ አንድ ትውልድ ላይ አጥር ከመሥራት፤ የራሥን ታሪክ መዝኖ በጎና አዎንታዊ አስተሳሰብ የሚፈጥርን ትልቅ ሐሳብ ማቅረብ ከጉዳቱ ጥቅሙ የሚያመዝን ሆኖ ይታዬኛል፡፡ ሁልጊዜም ምዕራባዊያኑ ያላጠኑትን፣ ያልባረኩትን እውቀት እና ያልቀደሱትን መረጃ እንደ እውነት የማንሳለም ሰዎች፤ ይሕንን አይነት መጽሐፍ ማቅረቡ ላይ እንከን አለበት ብዬ ሙሉ በሙሉ አልኮንነውም፤ ሆኖም..

ሆኖም አንድ ትልቅ ፊኛ በአየር ተነፍቶ ወደ ሰማይ ሲለቀቅ፤ ያለው እብጠት እና ኩራት፤ ውስጡ የራሱ ማንነትና ልዕልናን የተጎናጸፈ መሥሎት፤ አየር ላይ እንደሚከንፍ አውራ ደሮ መሥሎ ሲያንዣብብ፤ ወዮ! ለዛ ፊኛ፤ ትንኝ የነከሰችው ‘ለት…! መርፌ የተጠጋችው ‘ለት!

እኛም እንዲሕ እንዳንሆን ስጋት አለብኝ! በባዶ ማንነት ላይ ትልቁን አየር ሞልተን ፊተኛ፣ አንደኛ ነን ስንል! ዋናውን መሰረት ልብ ውስጥ ሳንገነባ መብረር ትልቅ ጉዳት አለው፡፡ ትልቅ አገርን ለመመሥረት በልቡና የሚሞላ ትልቅ ጠጣር እውነት ያስፈልገናል፡፡ ጠጣር እውቀት፡፡ ማሕበረሰቡ እየታመመ ግለሰቦች ጤነኛ ነን ቢሉ ፋይዳው ፍደሳ ብቻ ይሆንብናልና! “በሰለጠነው በምዕራቡ ዓለም መጥፎው ግለሰቡ ሳይሆን ማሕበረሱ ነው” እመጓ ገጽ 93፡፡ሥለዚህ እመጓን ስናነብ ውስጣችንን በጠጣር እምነት ሞልተን፤ አውቀትንና እውነትን ለመገንባት ከፍተኛ ትግል እንደሚጠበቅብን እገነዘባለሁ፡፡
‹‹እመጓ›› ምናልባትም ከዴርቶጋዳ ቀጥሎ የወጣች አነጋጋሪ መጽሐፍ መባል አይበዛባትም! ጎጃምን መሠረት እያደረጉ የሚወጡ መሰል መጽሐፍት፤ መንዝን፣ በጌምድርን፣ ደቡብ ጎንደርን እና የሠሜኑን ክፍል በምሥጢራዊ ዋሻዎች ጥልቀትና ድምቀት፤ ኢትዮጵያ በጉያዋ የያዘቻቸውን ቅርሶች፣ ጸጐች፣ ረድኤትና በረከቶች እንድናሰላስል- ‹‹ዴርቶጋዳም›› ‹‹እምጓም›› ይተይባሉ! አያይዘንም የ‹‹እመጓ››ው ጸሐፊ ከዴርቶጋዳ መጽሐፍም ሆነ ጸሐፊ መማር ያለበት ብዙ ነገር እንዳለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በኔ በኩል ‹‹እመጓ›› የጸሐፊውን ሳይንሳዊ ሲሳዮች (በረከቶች) እንደ ማጣፈጫ አድርጋ ስላዘለች፤ ኢትዮጵያ ያሏትን ባሕላዊ፣ ጥንታዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች (እሴቶች) በቀላል አማርኛ እየጠቀሰ፤ ከኛ የነበረውን ወስደው ወደኛ ሸጡልን አይነት ዘገባዎች አካታ ይዛለች- ‹‹እመጓ››፡፡ ይሕንን ለመቅረፍ መፍትኄው ምንድን ነው??

መልሱ፡- በመጀመሪያ ሥለኛ ማንነታችን ያለን ዋጋ እና ክብር የመሠረት ድንጋይ ነው! ቀጥሎሥ..?
እመጓ በ204 ገጽ አጥር እጥር፣ ምጥን ክሽን ተደርጋ እንደተቁላላች ወጥ በአምሳሁለት ብር ሂሳብ ቀርባለች፡፡ በውስጧ የያዘችውን መልዕክት ስናስብ፡- ቅዱሱ ጽዋ እውነት በዚሕች ምድር አለ? የለም? ብሎ ለሚጠይቅ አንባቢ፤ በለበጣ የሚደመም እና ይሕንን ጉዳይ እንደፌዝ 
የሚወስድ የትውልድ ቁጥር ጥቂት አይሆንም!

አንድ ጥያቄ፡-
ይሕ ቅርስ በዚህች ምድር የለም ለማለት ምን ምክንያት አለን? ይህ ቅርስ በዚህ ምድር አለ ለሚለው ደግሞ የዓለማየሁ ሲሳይ በእመጓ ደረቱን ነፍቶ በቆላማዋ እመጓ ጉያ ውስጥ ተቀምጧል ይለናል፡፡
የዓማየሁ ሲሳይ፡-

የዓለማየሁ ሲሳይ ምናልባትም የሥነ-ምሕዳር ሙያዊ ብቀቱን እና ልምዱን ከጎበኛቸው የገዳም ሰዎች እና ቦታዎች ጋር ተዳምሮ ይሕን መጽሐፍ ለመጻፍ ረድቶታል፡፡ የዓለማየሁ ሲሳይ ማለት ደግሞ በ‹‹እመጓ›› መሪ ገጸባሕርዩን ይዞ የሚተርክልን ሰጋ አልባ ግለሰብ ነው፡፡ ሲሳይ አለማየሁን ፈጠረ ወይንስ አለማየሁ ሲሳይን…?

አሁንም በመጽሐፉ ውስጥ ቀላል የማይባሉ ቁምነገር አዘል ትርክቶች ቀርበዋል፡፡ ከቦሌ አየር ማረፊያ አንስቶ እስከ ዋሽንግተን፤ ከዚያም መልስ ደግሞ ወደ ገጠራማ የሰሜን ሸዋ ተራሮች፣ ጨጨሆንና በጌምድርን እንዲሁም ጎጃምን ያስቃኘናል፡፡እንደ አዋሽ ወንዝ ፈስፈው ባንደኛው ገጽ ላይ ጠፍተው የሚቀሩ፤  ደራሲው ፈጥሮ የገደላቸውን አንዳንድ ገጸ ባሕርያትም ሥናስብ፤ ታስቦበት ከሆነ እና ለታሪኩ ፍሰት የበቀሉ ቋጥኝ ገጸባሕርያት ከሆኑ ብንቀበልም፤ የሰው ነፍስ ማጥፋት ደግሞ ሥለሚያስጠይቅ ልብ ማለቱ ላይ እንበረታለን፡፡ (የፒስኮሩ አንድሪው ባረነስን የመሰሉ ገጸ ባሕርያትን ልብ ይሏል፤ አሊያም የመርዝ መከላከያ እና ኦክስጅን ቃል የተገባላቸው መነኩሴ…)

በተጨማሪም እመጓ ይሕንን ትውልድ እና አገራዊ ገጽታ ለመቃኘትም ትሞክራለች፡፡ ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ምእራባዊያንን የሙጥኝ ማለታችን ይጎዳናል እንጂ የሚጠቅመን ነገር የለም ትለናለች፡፡ (ሉሲን እንደ ብርቅዬ የሚያይ ሲሆን ደግሞ ሌላ ጥያቄ ያስነሳል)፡፡ በገጽ 164 “ብርቅዬ ሉሲን እንኳ አሜሪካ ድረስ የወሰድን፣ ጎብኝ ወደ ቅርስ የመጣል እንጂ ቅርስ ወደ ጎብኚ…” በማለት መላካችንን እንደ ድክመት ይገልጸዋል፡፡ ቅዱሱን ጽዋ እንደ ታላቅ በረከት እና ቅርስ የሚቆጥር ሰው “ሉሲ”ን እንደ ብርቅዬ መቁጠሩ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይዞት ከሚጓዘው ጭብጥ ጋርም የሚጣረስ ነው፡፡

በብራና ላይ ገጽ የተገኘውን ካርታም (በመጽሐፉ ገጽ መመልከት ይቻላል)፤ አራቱን አቅጣጫ ያስቀመጠ እና አምስት ክቦች የትክተት ነጥቡን (center) አቋርጠው የሚሄዱ አውታሮች (diameter) ልክ እንደ የተባበሩት መንግሥታት አርማ ጋር ይመሳሰላል፡፡(በመጽሐፉ ገጽ 174 መላምት ቀርቦበታል) ፡፡የዩናይትድ ኔሽኑ አርማ 33 ክፍሎችን የያዘ ክብ ሲሆን ይሔኛው ደግሞ ከ6 የተከፋፈሉ አምዶችን ይዟል፡፡ ይሕ ክፍፍል በጸሐፊው ዘንድ ታስቦበት እና የተባበሩት መንግስታት አርማን ልብ ብሎት ከሆነ ብዙ መመራመር የሚያስፈልገው ስራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጸሐፊው ሥለ ሚጥራዊ ቡድናት ዓላማ፣ ማንነትና መረጃ ቢኖረው መልካም እንደሚሆን ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም፡፡



ከዚህ ጋር ተያይዞም የሚነሳው ነገር በመጽሐፉ ሽፋን የተቀመጠችው የተጠላለፉ የ “ቪ” ፊደል መሳይ ምልክትን ነው፡፡ ምልክቶች በየአገልግሎት ስፍራቸው እና ቦታቸው የየራሳቸውን ትርጉም ሊሰጡ ቢችሉም፤ በኔ አስተሳሰብ የ“ቪ” ንብርብሮሽ የሚሰጠን ምልክት የፈሪሜሶኖችን አርማ ይሆናል፡፡ (ትሪያንግል ሆቴልን ድሬዳዋ ላይ ስመለከት ግራ ተጋብቻለሁ አርማውን ልብ ይበሉ)

ሆኖም እንደ ጸሐፊው እምነት የ “ቪ” ፊደል መጠላለፍ የቅዱስ ጽውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በተደጋጋሚ እጃቸው ላይ ያሳዩት ነበረውን ምልክት ልብ እንድንል ከማስቻሉም በላይ በምልክቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጥናት እና ምርምር ማድረግ እንዳለብን በስፋትና በጥልቀት እንረዳለን!

ወጣም ወረድም ከዚሕ በኋላ ኢትዮጵያ የዓለማችንን ምስጢራዊ ቅርሶች አሉኝ ከሚሉ አገሮች ጋር እንድትቀጥል ትሆናለች፡፡ ጽላተ ሙሴ፣ ግማደ መስቀል፣ ቅዱሱ ጽዋ… እንደዚህ ጽሑፍ ጸሐፊና በዚህ አስተያዬት ሰጪ አስተሳሰብ መሠረት መጽሐፉ በቅድሚያ ትልቅ አገር የመፍጠርን መፈክር ይዞ የተነሳ በሚለው ሐሳብ ላይ ከማተኮር ውጭ፤ ይሕ ቅርስ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የለም በሚለው ክርክር ላይ በዚህ ጽሁፍ ላይ ለማተኮር ፈቃዱን አይወስድም፡፡ ጊዜ ይፈልጋልና፡፡ የፊኛውን ታሪክ ግን እናስታውስ…!
መልካም ንባብ፤

ዶክተሩንም በሌላ ሥራ እንድምንገኛ እየተመኘን ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር የተለማመዱ ግለሰቦች መሠል ስራዎችን እንዲሰሩ፤ አገራቸውን እንዲያነቡ፣ እንዲያስነብቡ አገርንና ትውልድን ከእልቂት እንያድኑ በመማጸን፤ በትልቅ አገር እና ታላቅ ትውልድን የመፍጠር ዓላማ ላይ ቢሳተፉ፤ ከወሬ የዘለለ ተግባር እና እውቀት እንዲሁም እምነትን አንግበው ቢንቀሳቁ የበኩላቸውን ድርሻ ኃላፊነት እየተወጡ ነው ማለት ስለሚቻል፤ መጽሐፉን ያገኘኋትን ምክር ዘአል ሐብረ-ቃል በመጋበዝ እንሰነባበበት!

“ጨለማ ጸጥታ ነው፡፡ ጨለማ ሰላም ነው፡፡ ትኩረትህን የሚስብ ምንም የምታየው ውጫዊ ነገር የለም፡፡ የምታየው ነገር ቢኖር የውስጥ አንተነትክን ነው፡፡ በብርሃን ሌሎችን እናያለን በጨለማ ግን ራሳችንን እናያለን፡፡ ሰው ራሱን እንደማየትና እንደማወቅ ያለ ኃይል የለውም፡፡ ጨለማ ደግሞ ይህን ኃይል ያጎናጽፍሃል፡፡ ገጽ 194፡፡

በሐዲስ ኪዳን ወንጌል ጸጋዎች እና በተደጋጋሚ ሲነሳ የምናስተውለው “ብርሃን” እዚህ ላይ የተነጻጸረ አይመስለኝም፡፡ ቢሆን የዚህ ጽሑፍ ዓላማና ጭብጥ በዚህ ቃል በዜሮ ይባዛል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ራሱን ብቻ መመልከቱ እና ሌሎችን ያለማየት ኃይልን ሲጎናጸፍ፤ “እኔ ነኝ” ወደ ሚለው የውድቀት ቃል ተወርውሮ ወደ ጥልቁ እንዳይከንፍ የዚህ አስተሳየት ሰጪ የሁልግዜ ምክር ነው፤ የተጣለውን መላዕክ እንመልከት፤ የሚበረውን ፊኛ እናሰብን..!



No comments: