ተስፋ በላይነህ
Habtamu Alebachew_AWRORA-YEKESAR INBA |
አንድ ጸሐፊ ልክ እንደ ውቅያኖስ
ውስጥ እንደሚዋኝ ፍጡር፤ ሰፊ ነጻነትን ይዞ በውቅያኖስ ውስጥ እንደሚኖሩ ኅልቆ መሳፍርት ፍጥረታ ብዛት፤ እንደ ፈጠራቸው ገጸባሕርያት
አስመስሎ ማቅረብን የመሰለ አስደሳች ነገር የለም፡፡
በእኔ አመለካከት በአሁኑ ሰዓት
በነጻነት የሚጽፍ ሰው አለ ብዬ ማመን እየከደበኝ መጥቷል፡፡ ጸሐፊ ነጻነቱን ሲቀማ ምን ሊሆን እንደሚችልም ስናስብ፤ በአንዲት የደረቀች
ኩሬ ውስጥ ግባና ዋኝ እንደመባል የተፈረደበት ጸሐፊ ምንኛ ያሳዝናል፡፡-ልግመት ይሉሃል ይሄ ነው!
አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ
ጸሐፊ የቤተ-መንግስትን ውሎ በነጻ ሕሊናው አስቦ ለመጻፍ የሞከረ በብዛት አይገኝም፡፡ ይሕ የሚያሳዬው ደራሲያን ምን ያክል በጠበበች
ኩሬ ውስጥ ለመዋኘት መገደዳቸውን ነው፡፡ የኩሬን እና የውቅያኖስን ንጽጽር ለማቅረብ የዳዳሁት ሀብታሙ አለባቸው ምን ያክል በውቅያኖስ
ውስጥ ለመዋኘት መመኘቱን ከዚያም አልፎ መዋኘት መሞከሩን ለማሳዬት ነው፡፡
በ‹‹አውሮራ››ም ሆነ በ‹‹ቄሳር እንባ›› የምናስተውለው እና የምናደንቀውም ሀብታሙ አለባቸው በሶስት አይደፈሬ የአፍሪቃ መሪዎች ቤተ-መንግስት
ውስጥ ዘልቆ በመግባት፤ በእነዚህ መሪዎች ሆድ እና ልብ ውስጥ ምን እንደሚብላላ ለመጻፍ ያሳየው ሙከራውን ነው፡፡
‹‹አውሮራ›› ላይ የአስመራውን ርዕሰ ብሔር ኢሳያስ አፈወርቂን እና
የአዲስ አበባውን ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን ቤተ መንገስት መኝታ ቤታቸው ድረስ በሃሳብ ተወርውሮ ሕሊና ጓዳቸው ሥር ምን እንደሚነጋገሩ
ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡
‹‹አውሮራ›› የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጦርነት ውሎ ከመዘገቡም ባሻገር
የኢሳያስ አፍወርቄ መንግስት ለጦርነት ምን ያክል ጥማት እንደነበረው ለማሳዬት እንደተጻፈም መገንዘብ ይቻላል፡፡ ‹‹ፍልይቲ›› የአስመራዋ
ፍልቅልቅ ውብ ገጸ ባሕርይን የተላበቸች ሴት፤ ከሸዌው ተወላጅ ‹‹አስራደ›› ጋር የምታደርገውን የፍቅር ክስተት ከነፍለጋ መስዋዕቱ
ድረስ ለማሳዬት ተሞክሯል፡፡ ከዛም በተጨማሪ ባድመ ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያትነቷ እንዴት ሊሆን እንደቻለ በጥያቄ ያልፈዋል፡፡
ሃይላይን የመሳሰሉ ግለሰቦች ደግሞ ከአስመራ የተገኙ ጦርነትን የሚቃወሙ እና መስዋዕትነትን የከፈሉ ገጸ-ባሕርያት ናቸው፡፡ የባድመ
ጦርነት መምስዔነት በእርግጥ ጥሩ እና ግልጽ ጥያቄ ሆኖ ሳለ፤ የዚህ አስተያየት ጽሑፍ ጸሐፊ ግን ያለተዋጠለት ጉዳይ ቢኖር የአውሮራ
ጸሐፊ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ሙሉ በሙሉ በኤርትራዊያን ርዕሰ ብሔር ቡድኖች ላይ በማሸከም፤ ይባስ ብሎም የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር
በልማት ጽንሰ ሐሳባቸው ራዕይ ላይ ከአልጋ ቀስቅሶ እርባና የለሹን ጦርነት ውስጥ እንደገቡ ለማመላከት መጻፉን ነው፡፡
የ‹‹አውሮራ›› ደራሲ ከቤተ-መንግሥት
አካባቢ የማይጠፋ አሊያም ቤተ-መንግሥት ውስጥ ያለን ትዕይንት የሚያቃብለው ሰው እንዳለ ያለ ጥርጥር መናገር ይቻላል፡፡ ይሕም በገጽ
166 ላይ እንደምናነበው ጠ/ሚ/ር መለስ ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የቲ.ሳሙኤልሰን አስራ ሰባተኛ ቅጽ የኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መማሪያ መጽሐፍ
እያነበቡ ነበር፤ ይሕም ጥናት ከአገራችን አርሶ አደር ጋር ለማዋሃድ እየሞከሩ የነበረበት ወቅት ሲሆን፤ ከዚህ የልማት አስተሳሰብ
ራዕይ ተጠምደው በነበረበት ወቅት አንዳች አይነት ብሔራዊ የስልክ
ድምጽ ይጮኻል፤ አደጋ ስጋት እንደማዕበል መጥቶም ቀይ ፊታቸውን አደፈረሰው፡፡ ገጽ167፡፡
ይሕ የቤተ-መንግሥት የጥሪ ጩኸት
ተራና መደበኛ አልነበረም፤ ለአገሪቱ ቀውሶች የአስቸኳይ ጊዜ የደኅንነት መረጃ ማቅረቢያ መሳሪያ ነበር፡፡ የሚሰራውም በጣት አሻራ
ሲሆን የደርግ መንግስት ከሰሜን ኮርያ መሐንዲሶች አስመጥቶ ያስገጠመው ነው…፡፡ ይሕን አይነት መረጃ በጽሑፉ ውስጥ ማንበባችን ጸሐፊው
በነጻነት ቤተ-መንግሥትን ለመቃኘት የተሠጠውን እድል(ነጻነት) እንመለከታለን፡፡
‹‹አውሮራ›› በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ተቀምጣ
የተከለለውን የእሾሕ ፖለቲካዊ አጥር አፈር አድርጋ የማዋሃድ አቅም አላት? አንባቢ መጽሐፏን አንብቦ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡ በኔ
በኩል ወገናዊነት የታየበት የአጻጻፍ መልክ በመያዙ፤ የተፈጠረውን የሕዝቦች መራራቅ ስፋት አጥብቦ ከአንድ የሥነ-ሑፍ ሰው እንደሚጠበቀው
እምቅ የጥበብን ኃይል በመንተራስ ይሕንን የታሪክ ስብራት ይጠግናል ብዬ አላምንም፡፡ አውሮራ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሕብረት ድምጽ ብቻ
ነውና!
“..ሲጀመር ደፋር አትበሉኝና ይሕንን መጽሐፍ በጭብጥና ይዘቱ ስመዝነው ከኦሮማይ በኋላ የተፈጠረ
ድንቅ የጥበብ ሥራ ነው ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ..” ተብሎ ከአንድ ስማቸው
እንዳይጠቀስ ያልፈለጉ ዲፕሎማት ከሰጡት አስተያየት የተቀነጨበ ነው ሲባል፤ ‹‹ኦሮማይ›› ምን ያክል በአዞዎች መንጋጋ ውስጥ ሥጋ ትለቅም የነበረችን ወፍ እንደነበረች እና ፤ ከጉማሬዎች ትከሻ
ላይ ተጠልላ ትጓዝ ከነበረች ወፍ ጋር ለማወዳደር መሞከሩን በቀላሉ እናያለን፡፡
‹‹ኦሮማይ››ን እና ‹‹አውሮራ››ን ማነጻጸር ለምን እንደተፈለገ አልገባኝም፡፡ ‹‹ኦሮማይ›› በደርግ አባላትም ይሁን በሻብዕያ አባላት አልተወደደችም፡፡ መስዋዕትነቷንም እናውቃለን፡፡ ‹‹አውሮራ›› በ‹‹ኦሮማይ›› ስር ለመዳኘት መሞከሩ አግባብ ያልሆነ የንጽጽር ሚዛን ይመስለኛል፡፡
ለ‹‹አውሮራ›› ጸሐፊ የምጠይቀው ቀላል ጥያቄ ቢኖር የኢትዮ-ኤርትራ
ጦርነት በጠ/ሚኒስትር መለስ ውስጥ በድንገት የተፈጠረ፤ የኤርትራው ርዕሰ ብሔር የጦርነት አባዜ ውጤት ብቻ ነው? የሚል ይሆናል፡፡
የትግራይ ርዕሰ መስተዳደር አባላት ከመለስ ዜናዊ ጋር ያላግባባቸው ምሥጢር ምንድን ነበር? ‹‹አውሮራ›› ይሕንን መመለስ ብትችል ኖሮ ከ‹‹ኦሮማይ››
ቀጥሎ የተጻፈች የዘመናችን ድንቅ ጽሑፍ በሚል፤ መጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ ለታሪክ አስቀምጣት ነበር፡፡ በአጭሩ ‹‹አውሮራ›› የወገናዊነት ድምጽ ጩኸት መሆኗን ራሷ የአውሮራ ፍቺ
ይነግረናል፡፡
በመጽገፉ እንደተገለጸው ‹‹አውሮራ›› የኢትዮጵያ ሰራዊት ሕብረት ድምጽ ጩኸት ነው፡፡ ይሕ
ደግሞ የሁለቱን ሕዝቦች መራራቅ ስፍር ያሰፋዋል እንጂ ለማጥበብም ጭራሽ የሚፈልግ አይመስልም፡፡
‹‹የቄሳር እንባ››፡፡
ልክ እንደ ‹‹አውሮራ›› ነጻነት፤
ደራሲው አሁንም እነኚህን አምባገነን መሪዎችን ልብ መቃኘት በሞመከሩ ለዬት ያለ ፈር ቀዳጅ ስራ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በመንግሥቱ
ኃይለ ማርያም ልብ ውስጥ ገብቶ፤ አንድ ደራሲ ያሻውን ሲጽፍ መመልከት በ‹‹ሆሊውድ›› እንደምንመለከተው ‹‹ኃይት ሐውስ›› ውስጥ
ያለውን የቤተ-መንግሥት ትዕይንት ለማስቃኘት እንደሚሞክሩ ‹‹ፊልሞች››፤ ሀብታሙ አለባቸውም በአራት ኪሎው ቤተ-መንግሥት ውስጥ
የመንግስቱ ኃ/ማርያምን ባለቤት፣ ልጆች፣ እና አጠቃላይ ውሎ መዘገብ መቻሉ መጽሐፉን ይዘን እንድንቀጥል የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል፡፡
መንጌ ከባለቤቱ ጋር እንዴት እንደተገናኙ የገለጸበት መንገድም በሕሊናችን ሩቅ እንድንጓዝ አስችሎታል፡፡
የ‹‹ቄሳር እንባ›› ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› መጽሐፍ የተጻፈ ምላሽ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ትግላችን››ን አንብቦ የተናደደ ሰው ሊጽፈው የሚችለው፤ በልብ ወለድ
አጻጻፍ መልክ የተጻፈ፤ ከ1966 አብዮት ወዲህ የተከሰተውን የትውልድ መላሸቅ፤ የሕብረተሰብ ዝግመት እና የአገር ውድቀት- በ”ልግመተ ኢትዮጵያ” ስያሜነት የተተየበ ጽሑፍ ነው- ‹‹የቄሳር እንባ››፡፡
የዚህ አስተያየት ሰጪ ግለሰብ
በቄሳር እንባ የቀረበችው ኢትዮጵያ ከደርግ መገርሰስ ማግስት እስከ አሁን ፍንትው ብላ የምትታይ መሆኗን ለመናገር ይደፍራል፡፡ መጽሐፉን
የሚያነብ አመዛዛኝ ሕሊና ያለው ማንኛውም ግለሰብ በደርግ ዘመን እየተንጸባረቁ የነበሩ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ክስተቶች አሁንስ
የሉምን? እያለ እንደሚያሰምርባቸውም ያለ ጥርጣሬ መገመት እንችላለን፡፡
ለደርግ ባለስልጣን የቤተክርስትያን ቀሳውስት ወጥተው መረብ ማቅረባቸው፡፡
ስደት፡፡
ሕዝብ ለመንግስት ድጋፍ አሰጣጥ፡፡
ብሔርተኝነት..፡፡
የማሕበረሰብ የታሪክ የባሕል ልሽቀት፤አድር ባይነት…፡፡
የሚድያው ቁጥጥር እና ፕሮፖጋንዳ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለገዥዎች ያለው አመለካከት፡፡
መንግሥት የሚገጠመውን የየዕለት ጉዳይ ከላይ ወደታች እና ከውጭ ወደ ውስጥ መመልከት፡፡
የወሲብ ንግድ፡፡.. እና መሰል የደርግ መንግስት
መገለጫዎች አሁን በምኖርባት አገሬ ውስጥ ፈልጎ ማጣት አይቻልም፡፡ ሥለዚህ ሀብታሙ አለባቸው በደርግ መንግስት የነበረውን ስርዓት
ሲቃኝ- አሁን ያለበትን ሥርዓት እየዳሰሰ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለማሳዬት ሞክሯል፡፡
አሁንም ወገናዊነት የተንጸባረቀበት
ጽሑፍ የመምሰል ክስተትን ለመገንዘብ የሚያስችል ሃሳብ ለማስተዋል እንሞክር፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገጸ-ባሕርይ ከሆኑት አንዱ በላይነህ
ደሴ፤ በቤተ-መንግሥት ውስጥ ተቀምጦ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ስብዕና እያስተዋለ፤ በልቡ ይቃወም የነበረ የውባንቺ የእህት ልጅ
ነው፡፡ ለመንግሥቱ ኃይለማርያም በጻፈው ደብዳቤ ላይም መንግሥቱን በቀጥታ ለመግለጽ በሚሞክርበት ጊዜ- ሀብታሙ አለባቸው በቀረጸው
የመንግስቱ ልብ ውስጥ ግን “በላይነህን ሻዕቢያ እና ወያኔ ላከብኝ”
በሚል አስተሳሰብ መገለጹ ትልቅ ጥያዌ የሚያስነሳ ነው፡፡ ገጽ 361-364፡፡መጽሐፉ ውስጥ የደራሲውን አስተሳሰብ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም
አስተሳሰብ ጋር ለይቶ ማቅረብ ስላልተቻለ ከታሪካዊ ገጽታ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ደራሲው የፈጠረውን ገጸባሕርይ እንደ ልቡ
መሳል የማይከለከል ቢሆንም፤ ልክ ስብሓት ገብረ እግዚአብሄር ተስፋዬ ገብረ ኣብን የገለጸበትን መንገድ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በእንዳለ
ጌታ ማዕቀብ መጽሐፍ ላይ ስብሃት ስለ ተስፋዬ ገብረኣብ ሲጠየቅ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡.. የምታውቀውንና የማታውቀውን አውነት በብዛት
ይነግርህና መጨረሻ ላይ የሚነግርህ ውሸት መሆኑን ሳታውቅ ትቅበለዋለህ..፡፡(ቃል በቃል ላይቀመጥ ይችላል፡፡) ስለዚህ እንደዚህ
አይነት ጸሐፊዎችን መከላከል የምንችለው የስብሓት ገ/ብረ እግዚእብሔርን ምክር መያዝን ሳንዘነጋ ነው፡፡
ሀብታሙ አለባቸው በገጽ
392 “የትምህርት ምሁራን `ትውልድ ሥርዓተ ትምህርቱን ይመስላል` ይላሉ” ብሎ ሲገልጽ የትኛውን ትውልድ እየተመለከተ መሆኑን ማሰብና
መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከሞላ ጎደል ‹‹የቄሳር እንባ›› እንደ ገጹ ብዛት ምንችክ ያላለ ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊውንም ለወደፊት
ብዙ እንድንጠብቅበት የሚረዳው ይሆናል፡፡ ሆኖም ከአጼ ቴዎድሮሥ እስከ ኃይለ ስላሴ የነበሩ መሪዎች(ገዥዎች) ሁለት ጊዜ እና ከዚያ
በላይ ማንባታቸውን ሲገልጽልን “ጥቁሩ ቄሳር” የተባለው መንግሥቱ ያነባውን እንባ “ቄሳራዊ” ማድረግ በእጅጉ ያጠያይቃል፡፡ ሲጀመር
መንግሥቱ ለቄሳር የሚቀርብ አይደለም፡፡ መንግሥቱን ቄሳር ካልን ደግሞ የሌሎች መሪዎቻችንንም እንባ ቄሳራዊ ስያሜ ልናሰጥ ነውና፡፡
ቢያንስ በገጽ 402 የተገለጸው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የግል ስብዕና
ለአንዲት አገር የሚቅም በጎ ገጽታ ይኖረዋል፡፡ ምዕራባዊያንን የገለጹበት መንገድ፣ ገንዘብ አለመፈለጋቸውንም በበጎ እይታ መመልከት
ሥንችል “በመሪነታቸው ገንዘብ ይቅርና አገሪቱ የራሳቸው ናት” ተብሎ መገለጹንም ሳንተዛዘብ
መተላለፋችን አልቀርም፡፡
እንደነ ዶ/ር ኃየሉ አርዓያ
እና የሐረሩ ሀገረ ስብከት ጳጳስ እንዲሁም ሻዕቢያም፣ወያኔም እና ደርግም ያልተቀበሏቸውን ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ጨምሮ አንዳንድ
ግለቦች ኢትዮጵያ በምጥ ጊዜ የደረሱላት ሰዎች መሆናቸውንም መገንዘብ እንችላለን፡፡
በአጠቃላይ ደራሲው በመንግሥቱ
ኃይለማርያም ልብ ውስጥ ገብቶ የሚስቡትንና የነበራቸውን የአስተሳሰብ ልኬት መግለጽ ሲሞክር በታሪክም ሆነ በአንድ ግለሰብ ሕልውና
ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ሳንረዳ ማለፍ የለብንም፡፡
መንግሥቱ ሃይለማርያም በጥቁርነታቸው
የሚያፍሩ መሪ ነበሩ ወይ? ይሕም በገጽ 112 በአንድ አፍሪቃዊ መሪ ስም መጠራታቸው ቆሽታቸው ማረሩን እናነባለን፡፡ የመንግሥቱ ኃይለማርያም ጨካኝነት እና በቀል ከእድገት፣
ከቆዳ ቀለም መገለል፣ ከከንፈር መስፋት ጋር ማነጻሩ ትልቁን የነጻ አጻጻፍ ሥልት ወደ ታች የሚያርደው ይመስለኛል፡፡ ለአንድ አፍሪቃዊ
መሪ አምባገነንነት የውጭ ኃይል ተጽዕኖ ሰፊውን ድረሻ የሚወስድ ይመስለኛልና፡፡
አንድ አጭር ጽሑፍ እንግለጽና
እንሰነባበት “መንግስቱ በደም ኦሮሞና አማራ ቅይጥ ናቸው፡፡ በሥነ-ልቡናና በኢትዮጵያ ማንነት ጥያቄ ላይ ግን ቅልጥ ያሉ አማራ
ናቸው፡፡” ገጽ 111፡፡ ከዚህ ጽሑፍ የመጽሐፉ ሃሳብ ምን ሊመስል እንደሚችል መረዳት እንችላለን፡፡ ኦሮሞ ሆነው በአንዲት ኢትዮጵያዊነት
ስሜት የማያምኑ እንደሌሉ ተደርጎ ሳይታሰብ አሊያም ታስቦ ተጽፏል፡፡ የሀብታሙ አለባቸውን ቀበሌኛ ቃላት ለምሳሌ መሸርገጊያ፣
አበባ ቆሎ፣ ፎቴ፣ ሙርጥ ወዘተን ስናስብ ከመንደረኛ አስተሳሰብ
ጋር እንዳይላተሙ በመመኘት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ከጠበበ ብሔርተኝነት ጸዳ ሰሜት፣ ሰፊ እና ነጻ አዕምሮ፣ ከተሻለ የእውቀት አስተሳሰብ
ጋር የሚፈይዳት ይመስለኛል፡፡ ከልግመቷም የሚፈውሳት ይህ ነውና! አድር ባይነት በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ በላይነህ ደሴ የተመለከታት
ልግመት ኢትዮጵያን ስናስብ- ጥያቀው አንድ ነው፡፡
የኛ የቤት ስራ ልግመት ኢትዮጵያን
ለማዳን አምባገነን መሪዎችን በመቃወም፤ስደትን እንደ አማራጭ በመውሰድ የሚፈታ ነው? የቄሳር እንባ አልመለሰውም…፡፡ ቸር ኢትዮጵያ!
No comments:
Post a Comment