ጥያቄ ለሕይወት ተፈራ፡፡
ተስፋ በላይነህ
Tower In The Sky. Amharic Translation |
የያ ትውልድ አባላት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የራሳቸውን አሻራ ጥለው
ያለፉ፤ በአዎንታዊም በአሉታዊም ጎኑ ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡ ሆኖም አንድ ትውልድ የሚያልፍ እና ለቀጣይ ትውልድ አሻራውን ሲያሳትም፤
ከትውለድ የሚጠበቀውን ኃላፊነት በመገንዘብ ለቀጣይ ትውልድ ቢያንስ አንድ ሸክም አቅልሎ ማለፍን እንደ ግዴታ መታየት እንዳለበት
የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለው ትውልድም ያለፈውን ትውልድ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፡፡
1. `አብዮት` በረዥሙ
የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ምን አይነት ድርሻ ነበረው?
2. ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ
አገሮች በእርግጥ በፊውዳሊዝም፣ በኢምፔሪያሊዝም፣ በካፒታሊዝም መዳፍ ስር ነበረች?
3. ለለውጥስ የግድ የእነ
ቼጉቬራ፣ ሆ ቺሚኒም ሆነ መሰል ቀንደኛ የሶሻሊዝም ተከታዮች ብቻ አርአያ አድርገን መከተል ነበረብን?
4. እናንተ በ60ዎቹ የነበራችሁ
ወጣቶች ከባሕል ማፈንገጥ ጋር ተይይዞ ለውጡ ንጉሱን የማውገዝ ብቻ ነበር? ኢትዮጵያን ለማዳን ነበር ወይ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ችግር
ተረድታችሁ ጥንታዊነቷን ተገንዝባችሁ የሚያስፈልጋት ለውጥ ከታሪካዊነቷ፣ ከቅርሶቿ እና ከጥበቦቿ አንጻር መሻሻል ነበረብን ብላችሁ
ማሰብ ነበረባችሁ ወይንስ ማርክስ ኤንግልስን እና ሌኒንን እንደ ሶስትዮሽ አማልክት አደርጋችሁ መቀበላችሁ ትክክል ነበር?
Where was Ethiopia When you were drunk by those western songs and eastern
philosophies?
5. በዚያን ጊዜ ከዚህ
አስተሳሰብ ውጭ ምን አይነት አማራጭ አልነበረም የሚል መልስ ሲሰጥ እንሰማለን፡፡ ሆኖም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለአንድ አማራጭ ብቻ
እንዲኖር ተደርጎ የተፈጠረ ፍጡር ባለመሆኑ፤ ወደዳችሁም ጠላችሁም ዘመኑ ሆን ብሎ ባመጣው “የሳሻሊዝም ካፒታሊዝም” ጣጣ ውስጥ ገብታችሁ
ምሁራን እንዲጠፉ፣ ታሪክ እንዲበረዝ፣ ባሕል እንዲመረዝ አምባገነን መንግስት እንዲመሰረት ተደርጎ በተጠነሰሰው ሴራ ውስጥ ታጭቃችሁ
መስዋዕት የሆናችሁ ያክል አይሰማችሁም!?
6. ተሳስተናል ይቅርታ የምትሉበት አንደበትስ እንዴት ለትውልድ ጥላችሁ ለማለፍ
አልታገላችሁም! ኢህአፖም ሆነ ሌሎች በጊዜው ከአንድ ማሕጸን የወጡ ፓርቲዎች የተነካከሱበት ምክንያት ለኢትዮጵያ ጥሎት ያለፈውን
ጠባሳ ግምት ውሰጥ በማስገባት ለግል ማንተቻሁ ብቻ አሊያም ለፓርቲያችሁ ሕልውና ሳይሆን ለኢትዮጵያ ልዕልና ስትሉ ምን አደረጋችሁ!
ምን እያደረጋችሁ ነው! ጊዜ እያለፈ ነው፡፡ ጥቁር ጸጉር እየነጻ ነው፡፡ ጎፈር ደ ምድረበዳማነት እየተቀየረ ነው…፡፡
7. በእርግጥ ሕይወት በመጽሐፍሽ
ማጠቃለያ እንዳስቀመጥሽው “የነጻነትን ዋጋ ተረዳሁት፣ ተምኔታዊ ዓለም
ለመፍጠር ከመፍጨርጨር ይልቅ፣ የግል ኀላፊነት፣ የግል ሉአላዊነት፣ ሐቀኝነት፣ አብዝቶ የተሻለ መሆኑን ተገነዘብኩ” በሚል
ዓረፍተ ነገር መለቋጨት ብትሞክሪም- አሁንም ፍትኃዊ ሥርዓት ለማስፈን የግለሰቦች ትብብር፣ ትስስር፣ ስብጥር አስፈላጊ አይደለም
ብለሽ ታምኛለሽ-? ያን ጊዜ ሶሻሊዝም በሚል ቋንቋ መደብ አልባ ስርዓት ለመፍጠር ሁሉም እኩል መዳረሻ እንዲኖረው በሚል አስተሳሰብ፤
ፍትህን በማቀንቀን የሰውን ልጅ በአንድ ቅርጫት አድርጎ የሚገዛን የማሕበረሰብ “የሰማይ ላይ ማማ” ሥርዓት ለማዬት ስትታገሉ እንዳልነበር፤
አሁንስ በተቃራኒው በግለሰባዊነት ስርዓት ብቻ ያተኮረ ማንነት በራሱ አገርን ይገነባል ወይ ትያለሽ-? በእርግጥ ግለሰቦች ኃላፊነት
ሲሰማቸው፣ የግል ሉዓላዊነት ሲገባቸው እና ሐቀኝነትን ሲከተሉ በራሱ የሚያሳድረው አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዳለው አይካድም፡፡ ለዚህም
መትጋት ኣያስፈልግም እያልኩ አይደለም፡፡ ሆኖም ግለሰቦች ከዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ በማሕበራዊው ዑደት ውስጥ መሳተፍን ያክል
መተጋገዝ፣ መተባበርን አንኳር ነጥብ መዘለሉ የሚያጠያይቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
በመዝጊያሽ ላይ ከጀግናሽ ከጌታቸው ማሩ የተማርኩት ብለሽ ያስቀመሺው
ሐሳብ ማለትም “ለሰው ሕይወት ክብር መስጠትን፣ መቻቻልንና፣ ግጭቶችን
በሠላማዊ መንገድ መፍታትን ነው” የሚለው መዳረሻሽ ሲፈተሸ አንድ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ጌታቸው በሕቡዕ እንዲደራጅ ማን አስተማረው፤
ጅዶም ሆነ ሌሎች ሥልጠናዎችን ለመውሰድ ሰላማዊ መንገድን ለመፍታት የሚያገለግል መሣሪያ ነበር ወይ-? ሽጉጥንስ መግዛት ችግሮችን
በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያገለግል አማራጭ እንኳ ሊሆን የሚችል መፍትሄ ነበረን?
እኔ እንደሚመሰልኝ በሚድያው “ማኒውፑሌት” የመደረጋችሁን ትልቅ ነጥብ
የዘነጋችሁት ይመስለኛል! እኔ “ያ ትውልድ”ን ለመንቀፍ ከትውልዶች ሁሉ ለማሳነስ እና በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሽግግር ድልድይን
የሰበራችሁ እናንተ ናችሁና መወቀስ አለባችሁ እያልኩ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ ይዛው ከመጣችው የታሪክ ቅብብሎሽ- መሻሻል የሚገባውን አሻሽላችሁ
-መቅረት የሚገባውን አስቀርታችሁ- መጨመር የሚገባውን ጨምራችሁ- ከትውልድ የሚጠበቀውን ተፈጥሮአዊ ኃላፊነት ማስተላለፍ ሲቻል፤
በጀግንነትም ሆነ በአርበኝነት ታሪክ ኢትዮጵያ ለማንም ተምሳሌት አገር መሆን ስትችል፤ አርዓያ ማድረግ የምንችላቸው የኛ ጀግኖች
ከታሪክ መዝዘን መሆን ስንችላቸው፤ ማክበር ሲገባን፤ ቼ ጉቬራ አርበኛችሁ መሆኑ፤ ሆቺ ሚኒ መንገዳችሁ መሆኑን ስንመለከት፤ ያኔ
ሚዲያው ያስተጋበው የነበረውን ተምኔታዊ መፍጨርጨር እንደ ብቸኛ አማራጭ መውሰዳችሁ፤ የታሪክ ስህተት መሆኑን ተገንዝባችሁ፤ የማያልቀውን
ተተኪ ትውልድ ላይ ይቅርታም ሆነ የማስተማር አርዓያነት ለማስተላለፍ አለመትጋታችሁ ትልቁን ነጥብ ይዞ የሚገኝ ሃሳብ ነው፡፡
በሚድያ መሰለባችሁን ለማጠየቅየትም መሄድ ሳይጠበቅብን በአንቺው መጽሐፍ
ገጽ 102 ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ አንባቢን ላለማሰልቸት በአጭሩ ላስቀምጠው፡፡ በ1967 ዩኒቨርሲቲ ተመልሳችሁ ያያችሁት አንድ
ፊልም ነበረ፡፡የፍሬሊሞ ፊልም፡፡
“እጅግ ከመነሸጤ የተነሳ፣ ጩሂ-ጩሂ አለኝ፡፡ ፊልሙ ሲያበቃ፣ ተመልካቹ በደስታ ሰከረ፡፡ አንዳንዶቹ ይሮጡ፣ ወንበርም
ይወረውሩ ጀመር፡፡ ሌሎቹም ከአዳራሹ ለመውጣት ተጋፉ፤ ተተረማመሱ፡፡ እኔና ጉዋደኞቼ ጥለው እንዳይረጋግጡን ፈርተን ነበር፡፡ እንደምንም
በሰላም ወጣን፡፡ ቀደም ሲል ኦክቶበር የተባለውን ስለሌኒንና ስለጥቅምቱ
አብዮት የተቀረጸውን ድምጽ-የለሽ ፊልም አይተናል፡፡ ከፍሬሊሞ ጋር ሲወዳደር በቅስቀሳ ኃይሉ ከጫፉም አይደርስ፡፡
ብቻ፣ ጫካ አዕምሮን የሚያሸፍት አንዳች ነገር አለው፡፡ ገጽ102፡፡
ከዚሕ ክስተት መረዳት የምንችለው ነገር ግልጽ ነው፡፡ ‹‹ሚዲያው››
ምን ያክል እንደተቆጣጠራችሁ እና ሆን ተብሎ በሚነዛ የአዕምሮ ብክለት ጋዝ መመረዛችሁ፤ አነበብን ከምትሏቸው መጽሐፍት ጋር ተዳምረው
ያ ትውልድ ‹‹የአንድ ሴራ ውጥን›› መተግበርያ፣ ሙከራ ሆኖ ሰማዕት ሆኖ ያለፈ ትውልድ መሆኑን ልንረዳ እንችላለን-መረዳትነ የሚገባንም
ይመስለኛል፡፡ ይሕንን ሐሳብ እግዚአብሔር ይስጠውና ገስጥ ተጫኔ በ‹‹ነበር›› መጽሐፉ አስረግጦ ጽፎልናል፡፡ “…እርስ በርስ ተነካከስን፣
ተበላላን እኛ በምናደርገው አራዊታዉ ትንቅንቅ መውጭ ሆነው የሚያዩን ይሳለቁብን ነበር… ፡፡ ነበር…ነበር፡፡” /ዓረፍተ ነገሩ ከራሴ
ነው፡፡/ “ነበር” ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በ60ዎቹ ትውለድ
ዙሪያ መረቅ የመሰለን መጽሐፍ አላገኘሁም፡፡ አዳም ረታ እጁን ያስልጥለት!
ማጠቃለያዬ አጭር ነው፡፡ “ያ ትውልድ ይቅርታ” መባባልን ሳያሳየን
ከትውልድ መስመር ውጭ እንዳይወጣ አደራ፡፡ ስለ ማሕበረሰባዊ ፍትሕ የሚጨነቅ ትውልድ ሳንገነባ አሸነፍን ልትሉ እንደማትችሉ ሳታገነዘቡ፤
በአንድ ሴራ ውጥን ሙከራ ውስጥ ገብተን ወደ ተሳሳተ መንገድ የገባን አገር ላይ አንድ ክፍተት የፈጠርን ትውልዶች ነን ሳትሉ፤ ዘላለማዊነትን
እንደ መገለጫ በመቅረጽ አሁንም ከበላይነት ስሜት እና እኛ ብቻ እናውቃለን ከሚለው የሰው ልጅ ድኩማን ሓሳብ ተላቅቃችሁ፤ ያኔ የነበረውን ቆራጥነታችሁን.. አገር ወዳድነታችሁን... ትኩስ ኃይላችሁን
ለትውልድ ማስቀመጥ መቻል የአሸናፊነት መገለጫው ነው፡፡ የትውልድ አደራውም ጭምር፡፡ አደራ ሲል ይማጸናል ይሕ ትውልድ!
ውዷ ሕይወት ሆይ! መጽሐፉን መጻፍሽ አንድ ትልቅ እርምጃ እና ብቁ
አርዓያነት ነው፡፡ በግሩም ቃላት ተርጉሞ ያቀረበልንን ጌታነህ አንተነህንም
በሚገባ እናመሰግነዋለን፡፡ የአዲሥ አበባ ዩኒቨርሱቲ ሕትመት ክፍልንም እንዲሁ፡፡ እኛ ሰዎች እናልፋለን! የማያልፍ ትውልድ እና ኢትዮጵያን እናስብ- መልዕክቴ ነው፡፡ ለመማማር
እና ለመመከር እንዲሁም ለመኮርኮም ጭንቅላቴ ክፍት ነው፡፡
ታናሽ ወንድምሽ “ምናሴ”!
No comments:
Post a Comment