May 19, 2015

“ቆይታ ከታሪክ ጋር”



በፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ጎጆ፡፡


                                                                                                               ተስፋ በላይነህ



       ወደ ቤታቸው ስገባ የሲ.ኤን.ኤን የቴሌቪዥን ስርጭት ድምጽ እየተሰማ ነበር፡፡ የገብረ ክርስቶስ ደስታን ስዕሎች፣ በርካታ መጽሐፍችን ለመመልከት ቤቱን በመቃኘት ገባሁ፡፡…
አጭር ናቸው፡፡ ትከሻቸው የታገሉለትን የጭቆናና እና የአገዛዛ ታሪክ የተሸከሙበት ይመስል፤ ቀና የማለትን የነጻነት ቀን የሚናፍቅ ይመስላል፡፡
ቀኝ እጃቸው ላይ ጠቆር ያለ ጠባሳ ይታየኛል፡፡ አጠገባቸው የተለያዩ የመድኃኒት እቃዎች ተደርድረዋል፡፡ ቀይ ምንጣፉን ላለማበላሸት የጫማ ማውለቅ ጥያቄ ሳቀርብ ኤልሳቤጥ ችግር እንደሌለበት ነግራኝ ወደ ወንበር አመራሁ፡፡
መሃል ላይ አንዲት ጠረጴዛ ለያይታን ወደ ውይይታችን ቀጠልን፡፡
ከዚህ በፊት ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ በዚሕ ቤት ተገኝቶ ያሳለፈውን ልምዱን ሰጥቶናል፡፡ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ እግዚአብሔር ይስጠውና ያካፈለንን ልምድ በመውሰድ የእሳቸውን መጽሐፍት አንብቤ መሄድ እንዳለብኝ ከማወቅም ባሻገር፤ ባሕርያቸውንም እንዳጠናም መንገድ ሰጥቶኛል፡፡ "ወደ አንድ ጸሐፊ ቤት ሲሄዱ መጽፉን ይዘው መሄድዎ አይርሱ" የሚለው አባባል የሚያስማማን ይመስለኛል፡፡ (የክደት ቁልቁለትን ግን አላበብኩላቸውም)

ፕሮፌሰር መስፍን ግን ቁጡ ናቸው?

በ1920ዎቹ  የተወለዱ መሆናቸውን በማሰብ የዚሕ ዘመን ሰዎች ባሕርይ መገለጫ ከሆኑት ነገር አንዱ የአባትነት ቁም ነገራዊ ግሳጼ ለቁጡነታቸው መንስኤ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ በዚህም የእሳቸውን ሙሉ ባህርይ ቁጡ እና ተሳዳቢ አድርጌ መቀበል ግን ያዳግተኛል፡፡

እንደኔ አረዳድ የሚቆጡት አንድ ሰው ያለ መሠረታዊ ሓሳብ፣ ያለሳይንሳዊ ማስረጃ እና ያለ እውቀት “አዋቂነቱን” ለማስረዳት በሚሞክርበት ወቅት ነው፡፡ ያለ እውቀት መሠረትነት ለመግባባት መሞከር እና አዋቂ መስሎ መገኘት ከቁጣም በላይ ከግሳጼም በላይ ሌላ ነገር እንደሚያስፈልገው ቀዳሚ ተሟጋች ነኝ፡፡(ይሕ ሐሳብ ከቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ ጋር እንዳይነጻጸር) ሥለዚህ እኔም ያለ እውቀት እና ያለ ተጨባብ መረጃ አሊያም ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ወሬ ከአፌ ላለማውጣት በማሰብ፤ የማላውቀውን ነገርም ለመጠየቅ እና ጥቆማ ለማግኘት ነበር አካሄዴ፡፡

ስሜን አስተዋወቋቸው፡፡

ከዚህ በፊት ተገናኝተን እንደምናውቅ፣ አድናቂያቸው መሆኔን እና ሥለ ስብዕናቸው ውደሳ ማቅረብ እንደሌለብኝ አስቀድሜ የወሰንኩት ነገር ሥለነበር ቀጥታ ወደ ጥያቄዬ ቀጠልኩ፡፡

አመጣጤ አንድ ታሪክን መሰረት ያደረገ ጽሑፍ እንደጀመርኩ እና ምናልባትም ከፍተኛ ምርምር የሚጠይቅ እንዲሁም በርካታ መጽሐፍትን ማገላበጥ እንዳለበኝ ሥለተሰማኝ፤ ከፕ/ር ላጵሶ ጌድሌቦ፤ ከፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ከፕ/ር እፍሬም ይስሃቅ እና ሌሎችም በተጨማሪ እሳቸው ጋር በተለያዩ ሐሳቦች ላይ ለመወያዬት ነበር፡፡

መጽሐፌ ያተኮረው በዋናነት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን የ2000 ዓመት ታሪክ በየ33 ዓመቱ እየዘገቡ ማስቀመጥ ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ክፍለ ዘመን ውስጥ ያሉትን 33፣66 እና 99 ዓመተምሕረቶች በመከፋፈል የተከሰቱትን የታሪክ ገጠመኞች በአጭር በአጭር ከየመጽሐፍቱ እያሰባሰቡ በማስቀመጥ ነው፡፡

“ለምን ሠላሳ ሶስትንን መረጥክ?” አሉኝ፡፡
ከዚህ በፊት ከአንድ ወዳጄ ጋር ይሕንን ጉዳይ አንስተን ተወያይተንበት ሥለነበር- የተዘጋጀሁበት ጥያቄ ነበር፡፡ 33 ቁጥርን ለምን መረጥን ስንል፡-
1.     ክርስቶስ በ33 ዓመቱ ምድራዊ ተልዕኮውን እንደጨረሰ፤
2.    አንድን ነገር ከሶስት መከፋፈል(ሶስትዮሽ-ትሪያንግል) ያለውን ሂሳባዊ ቀመር
3.    100 ዓመትን ከሁለት ብንከፋፍል አንዳንድ የታሪክ ገጠመኞች እንዳያልፉን በመግለጽ
4.    33 ቁጥር በባዕዳን ሴረኛ ኃይሎች ከፍተኛ ትርጉም እና ቦታ ያለው በመሆኑ ሲሆን
የእኔ ጥያቄም ለምን 33ን መረጡ በሚለው ላይ በማተኮር ጥቄውን አንባቢ እንዲመልሰው በመተው እየተጻፈ ያለ መጽሐፍ እንደሆነ እንደተወያየንበት እና ለፕሮፌሰርም ይሕንን አስረድቼ፤ ሆኖም ከዚህ ደመነፍሳዊ ምልከታዬ ባሻገር ሰፊ እውቀት ቢጨመርበት በታሪካችን ልዩ ምልከታን ልናገኝበት እንደምንችል አስረዳሁ፡፡ ታሪካችንንም ለመዘገብ በ2000 ዓመታት ውስጥ ያሉ 20 ክፍላተ ዘመናትን ከሶስት ብንከፋፍላቸው 60 አበይት የታሪክ ክፍልፋዮች ሥለሚኖሩን፤ ታሪኩን ባዕድ ላደረገው ትውልድም ቀለል ባለ መልኩ ማስቀመጥ የሚችል መሆኑን ጨመርኩ፡፡

“አጀማመርህ የእውቀት መሠረትነት የለውም፡፡ የደመነፍስ ነው፡፡ እውቀትን ይዘሕ ብትነሳ 33ን አትመርጥም፡፡” አሉኝ፡፡ “ሥለዚህ አነሳስሕ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው፤ እንደ ራዕይ አይነት ወይም የጥንቆላ አሊያም የመገለጥ አካሄድ እንጂ የእውቀት መሰረትነት የለውም፡፡” ሲሉ ሃሳባቸውን ገለጹ፡፡

ይቀጥላል....፡፡

ሆኖም በግሌ መድረስ የነበረብኝ የእውቀት ደረጃ በስፋት እንደሚኖር በመተማመን ከታሪካችን እንጂ ከቁጥሩ ችግር እንደሌለብኝ ተናግሬ ወደ ጥያቄዬ ቀጠልኩ፡፡(የሆነ ጊዜ እንደዚህ አይነት ክፍልፋይ ቁጥር ወስደው ጥናት እንደሞከሩ (ሌካ ሰው እንደሞከረ አጫወቱኝ))
ጥያቄዎቼ፡-

1.     በ34 ዓ.ምሕረት ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ወቅት ኢትዮጵያ ምን ትመስል ነበር? አካባቢያዊ ሁኔታው የሕዝቦች ስብጥር እና አኗኗር ምን ይመስል ነበር? በዚህ ዙሪያስ የተጻፉ መጽሐፍትን እነማን ናቸው?   
“በጣም የሚከብድ ነገር ነው፡፡” ቀጠሉ ፕ/ር፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ዝርዝር ነገር ማግኘት ከባድ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፊያን ሥለ ሮማ ታሪክ አወዳደቅ ሲጽፉ፣ በአንድ ክፍለ ዘመን ውስጥ የተመረጠች 30ና 40 ዓመታት ላይ በማተኮር የጥናት ጽሑፍ ሲያቀርቡ፣ አሁንም ሃሳቡ ሁሉ ሲያልቅባቸው ሥለ ጫማ እንኳ ሳይቀር ሲጽፉ እኛ አገር ላይ እንዲዚህ አይነት ነገር ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡” ምናልባትም የሰርግው ሐብለ ሥላሴ…”
2.    ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ ወደምንሰማው ወደ ኢዛና እና ሲዛና ታሪክ መሸጋገር፤ የፍሪምናጦስ ታሪክ እና የክርስትና መስፋፋት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? በሰላም እና በስብከት የተካሄደ ነበር ወይ?
3.     የአጼ ካሌብ ዘመን፤ አጼዎች “መናኔ መንግስት” በመባል የሥልጣን ጊዜያቸውን ወደ ገዳም መሄድ ማቆማቸው፤ በታሪክ ላይ ያለው ተጽዕኖ፡፡ ሥልጣንን በዚህ መልኩ መገደብ እና ሌላው ማስተላለፉ የሚመሰገን በጎ ጎን ቢኖረውም በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጥረው ተጽዕኖ? ተተኪ ተመራጩ መሪ ለሥልጣን የሚደረገው ሽኩቻ(አለመረጋጋት) የሚፈጥረው ተፅዕኖ?
4.    የአክሱም ነገስታት ወደ ሸዋ የሚሄዱበት መንገድ እና በሸዋስ ተሸሽገው የነበሩ እና የቀጠለው ትውልድ ዘር ሃረግ በኋላ ላይ የሸዋ ስርወ መንግስት የተመሰረተው በትክክለኛው የአክሱም ስርወ መንግስት ተከታይ ትውልድ ነው? በቂ ማስረጃችን ምንድን ነው?
እነዚህ ጥያቄዎች በአንድ አጠቃላይ ምላሽ ተሰጥተዋል፡፡

“ነገስታት በባሕርያቸው እዛው የሚቀመጡ እና በጣም የሚዘዋወሩ ሲሆኑ ይታያል፡፡ መንፈሳዊ ነገስታት፣ ተዘዋዋሪ ነገስታት እና ሁለቱንም ሊያጠቃልሉ የሚችሉ ነገስታት አሉን፡፡ ጻድቁ ዮሐንስን ብንወስድ የራሳቸውን ሰሌን እንኳ እየሰሩ መንፈሳዊነታቸውን አጥብቀው የሚይዙ ንጉሥ ነበሩ፤ አምደጽዮንን ብንወስድ ደግሞ በሰፊው ይዘዋወር ነበር፡፡ ዘርዓ ያዕቆብ ደግሞ ሁለቱን አይነት ሲሆን ይታያል፡፡ ሆኖም ነገስታት የማይዘዋወሩ እና ባሉበት ብቻ ረግተው በሚቀመጡበትበ ጊዜ አገር “ሽሪንክ” የማድረግ እና የመጥበብ ሁኔታ ያጋጥማታል፡፡ ሲዘዋወሩ ደግሞ በዛው ልክ ይሰፋል፡፡
ሆኖም ሥለ የሸዋው ስርወመንግስት የአክሱሙ ስርወ መንግስት ተከታይ የትውልድ ሃረግ አለው የለውም በሚለው ላይ ተጨባጭ የሆነ የታሪክ ማስረጃ የለንም፡፡ እኔስ የት አውቄው ብለህ ነው…”
5.    እሺ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የአቡነ ተክለሃይማኖት ከዛጉዌ ስርወ መንግስት ወደ ሸዋው መዘዋወር እና የሲሶ ውል በታሪካችን ላይ ያለው ተጽዕኖ በምን መልኩ ሊታይ ይችላል? ሕዝቡን ገባር የማድረግ ክስተት የሚባለው ጥያቄ በምን መልኩ ሊታይ ይችላል?
ገባር ማለት ምን ማለት ነው? ፕ/ር ጠይቁኝ፡፡
ገባር ማለት ለመንግስት የሚገብር፡፡ ገበሬ አሊያም ግብር የሚከፍል፡፡ በሚል ለመመለስ ሞከርኩ፡፡
ቀጠሉ እሳቸው፡፡
“ገባር ሲባል ጭሰኛ እና ሌላ ስያሜ እንዳይሰጠው መጠንቀቅ መቻል አለብን፤ ትክክለኛውን ትርጓሜ ሳታውቅ ለመተንተን መሞከር አትችልም፡፡ ገባር ማለት ግብር የሚከፍል ነው፡፡ በማንኛውም ዓለም በየትኛውም ዘመን ሕዝብ ለመንግስት ሲገብር ኖሯል፡፡ አሁንም ይገብራል፡፡ ገባር ሆነ ማለት ያ ሰው መሬት አለው ማለት እንደሆነ እንዳንዘነጋ፡፡ ሆኖም በዛን ወቅት የነበረውን የመሬት ሁኔታ ላጥና ብትል እድሜሕን ሁሉ ልትፈጅ ትችላለህ፡፡ ትልቁ የታሪክ ክፍል የመሬት ጥያቄ ነውና፡፡ ሥለዚህ አሁን በተሰጠን አረዳድ ብቻ ተነስተን የቆየውን ታሪክ ለመተንተን መሞከር አይቻልም፡፡ ሲሶ ውል(ሲሶ ለአራሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ ለአወዳሽ..) ይሕንን ለማጥናት ሕዝብ፣ መሬት እና መንግስት የሚለውን ዝርዝር ሓሳብ ላይ ማተኮር አለብን፡፡ ባላባት ምንድን ነው? በጎጃም ባላባት ነኝ ሲልህ ከአንድ አባት የተወለደ በትግራይም ባላባት ሲባል እና በሸዋ የተለያዩ ስያሜዎች ነበሩት፡፡ ሕዝቡ አልተበዘበዘም? ያ ግልጽ ነው! ያኔ የነበረው የሶስቱ ስብስብ “ሃገረ መንግስትስ” ምን ይመስል ነበር? ሆኖም በዚሕ ሃሳብ ውስጥ ተረት የሚመስል ነገር አለው…፡፡ ዝርዝር ሃሳቡ ሰፊ ስለሚሆን እንተወው…፡፡
ትንሽ ደከም የማለት ስሜት እንዳልሰጣቸው በመስጋት እና ሃሳባችንም ሰፊ እንዳየሆን በመፈለግ ወደ ቀጣይ ጥያቄዬ መቀጠል ነበረብኝ፡፡
6.    በ13ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ አሰፋፈር በየት ነበር?
“ኢንትሮዳክሽን ቱ ኢትዮጵያን ጂኦግራፊ” ላይ ማየት ትችላለህ- የጠቀስኩት ይመስለኛል፡፡…. ያው መጽሐፍትን ስትፈትሽ ስያሜ    ነው”
7.    ሥለ ዘርዓ ያዕቆብ ታሪክ፣ ሥለ  አህመድ ግራኝ እና አጠቃላይ ሥለ 14ኛው፣ 15ኛውና 16ኛው ክ/ዘመን ታሪክ መጠየቅ ትቼ ወደ 17ኛው ክዘ/መን ስለ ፖርቹጋሎች እና የጀዝዊቶችን ተጽኖ ላይ ማተኮር ፈለግሁ፡፡ ሥለ ጀዝዊቶች ምን ያስባሉ?
“ምን ማለት ነው?” አሉኝ፡፡
እነዚህ ራሳቸውን እየሱሳዊያን ብለው በመጥራት የሚታወቁት ጀዝዊቶች በታሪካችን ትልቅ ስፍራ ይዘው ይገኛሉ፡፡ እነዚሕን ሰዎች በምን መልኩ ያዩዋቸዋል፡፡ የነበራቸውንስ ተጽዕኖ በምን መልኩ ልናዬው እንችላለን?
አሁን ማቀላቀል ጀመርክ፡፡ ፖርቹጋሎችን ነው የምትለው?

አይ ጀዝዊቶች፡፡ ማለትም በ1540 እ.ኤ.አ የተቋቋው የእየሱሳዊየን ማሕበር የፕረስተር ጆን ሃገርን ለማዬት በሚል … ለምሳሌ እንደ ፖኤዝ ሜንዴዝ ያሉ ግለሰቦች…
ፖኤዝን ነው የምትለው?
አዎ፡፡
“ምን እነርሱ ምን እንደሚፈልጉ ይታወቃል፡፡ የጻፈውን መጽሐፍም መመልከት ይቻላል፡፡ የሃይማኖት ሰው ነው ልንል አንችልም፡፡ መጽሐፉ ሥለ ወርቅ ነው የሚያወራው፡፡ ሥለ ሃብት … ሥልጣኔን በማስመልከት ሱስንዮስን “በማታለል” ስራቸውን ለመስራት ሞክረዋል….
ከዚህ በለጠ ዝርዝር ሃሳብ መጠየቅ አልፈለግሁም፡፡ ከበቂ በላይ ሃሳብ ያቀረቡልኝ መስሎኛል፡፡

8.    የጀምስ ብሩስ እና የራስ ሚካኤል ግንኙነት፤ ለዘመነ መሳፍንት መጀመር የሚኖራቸው ተጽዕኖ ምን ይመስላል?

“እኔ እንጃ! ምን አውቄ! ሁለቱን በአንድ ዘመን ስታገኛቸው ለጠየከኝ ጥያቄ አንተ ያገኘኀውን እና የታየሕን ተናገር፡፡…
አይ የሆነ ጽሑፍ ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ “ኢትዮጵያን ፕሪንስስ ዘ ኢራ ኦፍ ዘመነ መሳፍንት” የሚል፡፡ ጸሐፊው ስማቸው ጠፋብኝ፡፡ አልኳቸው፡፡
“ማን ናቸው?” አሉ፡፡
ህምምም… ሞርቢች…? የሆኑ ትልቅ ሰውዬ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር…፡፡ ብዬ ስማቸውን ለማስታወስ ዝም አልኩ፡፡ ርዕሱን ስደግምላቸው አስታወሱት፡፡ ስማቸውን ግን ማስታወስ አልቻልንም፡፡ ሆኖም አይሁድ መሆናቸውን እና በመጽሐፋቸውም እንደ ተግባባባን ወደ ሌላኛው ሃሳብ ቀጠልኩ፡፡  (ጸሐፊው ፕ/ር ሞርዲቻይ አቢር ናቸው)
9.    ዘመነ መሳፍንትን አልፈን ወደ አጼ ዮሐንስ ዘመን ስንገባ ከእንግሊዞች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እና በታሪክ የተከሰቱትን ገጠመኞች አነሳን፡፡ ጥያቄዬም አጼ ዮሀንስ በምጽዋ ወደብ ላይ የተካሄደው የእንግሊዝ ጫና እና በተለይም በሰሐጢ ጦርነት ወቅት አጼ ዮሐንስ ያሳዩት ቸለልተኝነት፤ እንደውም ባሕሩ ዘውዴ በመጽሐፉ ጠይቆት ማለፉን በመጠቆም ጥያቄዬን አቀረብኩ፡፡
“ባሕሩ ዘውዴ ምን ላይ ነው የጻፈው?” ጠየቁኝ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 ….
“እዛ ላይ እንደተጠቀሰው አላስተዋልኩም ነበር፡፡ ሆኖም በዚህ ላይ አንድ ጽሑፍ እየጻፍኩ ነበር፡፡”
ሥለዚህ ጽሑፉን መጠበቅ ይሻላል በሚል እና የእንግሊዝ ተጽዕኖ ላይ በመስማማት ወደ ቀጣይ ጥያቄዬ አለፍኩ፡፡
10.  አጼ ምኒሊክ 10 ዓመታት ጎንደር ከአጼ ቴዎድሮስ በምን ሁኔታ ነበሩ? ቆይታቸው ምን ይመስል ነበር? በዚህ ዙሪያ የተጻፈ መጽሐፍ አለ?
“ይሄንን እኮ መሰለኝ እስካሁን ያወራነው፡፡ የተጠናከረ መረጃ አታገኝም፡፡ ሬከርድድ የሆነ የታሪክ መረጃ ማግኘት ይከብዳል፡፡ በተለይ በአሁን ሰዓት ስንት መጽሐፍት በኪሎ በሚሸጡበት ሰዓት፣ ታሪክን ልናገኝበት የምንችለው መሳሪያ ድንጋይ ላይ እየሆነ ነው፡፡” (ይሕንን ሲናገሩ ውስጤ በጣም እያዘነ ነበር.. ታሪክ ማንበቤን፣ መጠየቄን ጥያቄ ውስጥ አስገባሁት…)

ቀጠሉ… በል ቶሎ ቶሎ ብልን እንጨርስ አሉኝ፡፡ ቁርስ ሳይበሉ ነው እንዲህ ያስለፈለፍኳቸው፡፡ ሰሞኑንን ጥርሳቸውን አሟቸውም ሥለነበር በጣም ማድከም እንደሌለብኝ እና ለሰጡኝ ጊዜም በውስጤ እያመሰገንኩ ወደ ማጠቃለያ ጥያቄዬ አመራሁ፡፡
11.    ብዙ ጥያቄዎች እንደነበሩኝ እና ሁኔታው በበቂ ሁኔታ ስላልተመቸኝም ማጠቃለያ ሃሳቤን በቀላሉ ለማቅረብ አልቻልኩም፡፡ የኔ ዋና መነሻ ሃሳብ በታሪካችን ውስጥ የባዕዳን ሴራዎችን (ተጽዕኖዎችን) ፈትሾ በማውጣት፣ ሕዝቡም ላይ የሚታየውን የእውቀት ማነስ የአስተሳሰብ እና የባሕል ሁኔታዎች፣ የመሪዎች የሥልጣን ጥም፤ ምን ያክል አገራችንን እንደጎዳ በማመላከት በተለይም እኛ እንዲህ የምንነካከስበት እና የተለያየንበት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የባዕዳን ተጽዕኖ ላይ በማተኮር፤ ወደ መፍትሄ ሐሳቦች ለመምጣት ነበር፡፡
-በ1833 የሳሕለ ሥላሴ እና የእንግሊዞች ውል፤ በ1866 የእንግሊዝ እና የአጼ ዮሐንስ ግንኙነት፣ በ1899 የአጼ ምኒልክ እና የሶስት መንግስታት ውል፤ በ1933 የእንግሊዝ ሞግዚትነት፣ በ1966 የተነሳው አብዮት እና በ1999 የተካሄደው 33ኛው የቡድን ሰባት(G-7) አባል አገራት ስብሰባ ከጠ/ሚስትር ዜናዊ ጋር…፡፡ እነዚህ ሁሉ የተፈጸሙት በየ33 ዓመታት መሆኑ፤ የኋላ ታሪክን በጥልቀት ያጠና ነገን መቆጣጠር የሚያስችል ነጻነት ስለሚያገኝ አሁንን እናሻሽል፤ አሁንን እንለወጥ  ነገን በምን እንገንባ የሚል ሃሳብ ነበር የያዝኩት፡፡

የባዕዳንን ተጽዕኖ በጋራ ማጥናት ለአንድነታችን ከመጥቀሙም ባሻገር የተተበተበብንን የታሪክ እንቆቅልሽ ለመፍታትም ያስችለናል የሚል ሐሳብ ነው ያለኝ፡፡ በቀላሉ የራስ አሉላ አባ ነጋ ሐውልት በዶጋሊ መፍረሱን እና አሁን የጣልያን ሐውልት እንዳለ ለማመላከት ሞከርኩ፤ በ20ኛው ክ/ዘመንም የተካሄደውን የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ተጽዕኖ፤ ኢትዮጵያ ከፋሽት ወረራ በኋላ ያገኘችው እና ያጣቸው የታሪክ ሂደት ምን ይመስላል?(ቃኘው) አሁንስ እንዴት እንመለከተዋለን? ለወደፊስም? የሚል ነበር፡፡

ምስራቅ አፍሪካ እንዲህ በምዕራባዊያን ተጽኖ እንዲህ ሲከፋፈል እና ወዳልተፈለገ መንገድ ውስጥ ከምንገባ ውሕደት ሊያስገኝ የሚያስችል ዓላማ ብናስብ እንዴት ማሳካት እንደምንችል፤ በሚለው ላይ በሰፊው ለመወያየት ነበር ፍላጎቴ፡፡(በዚሁ ቀን ማታ “ኢትዮጵያ እና አሜሪካ” የሚል ጽሑፍ መልቀቃቸው አስደሰተኝ)
12.  በአጠቃላይ ሥለ አሉላ አባ ነጋ ታላቅነት፣ በደርግ ጊዜ በዶጋሌ የተሰራን ሐውልት ለማዬት እንደሄዱ እና አንድ የደርግ ባለስልጣን በዶጋሌ የነበረውን የመስቀል ቅርጽ ሐውልት ሄዶ እንዳፈረሰው፤ እሳቸውም እንደተቆጡት፤ ሐውልት ማፍረስ እንደማይጠቅም፤ በዓለም ታሪክም ተሸናፊዎች በአሸናፊዎች ሜዳ ላይ ታሪክ እንዳልሰሩ እና ይሕ ትልቅ የታሪክ ክስተት እንደሆነ በማስረዳት እንደተለያዩ አጫወቱኝ፡፡ ከማሞ ውድነህ አሉላ አባ ነጋ መጽሐፍም አንድ ነገር ለማዬት ስጠይቃቸው ሌላኛዋ “ክፍል” ሄደው መጽሐፉን አመጡት፡፡ ትንሽ ተነጋግረን ወደ ስንብቱ ቀጠልን… (ቀኑን በሙሉ “ሳደርቃቸው” ብቆይ ፍላጎቴ ነበር፡፡)

“ዶጋሊ ላይ የነበረው የመስቀል ቅርጽ ሐውልት  በጣልያንኛ “ኤል ከዱቱ” የሚል ጽሑፍ ነበረው፡፡ ትርጉሙም ለወደቁት ማለት ነው፡፡ የሽንፈት ታሪክ በአሸናፊው ሜዳ ላይ ሲቀመጥ ሌላ ራሱን የቻለ ታረሪክ ነው፡፡ ምዕራባዊያን ይሕንን አረመኔያዊ ጭካኔ ነው ሲሉት እነርሱ ግን ስንቱን ዓለም ሲጨፈጭፉ አረመኔ አይባሉም፡፡”…አሉ፡፡
13.  እኔም ለመሰነባበቻ አንድ ወዳጄ በፌስ ቡክ አማራ በሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንዳነሳና በዚህ ጉዳይ የእርስዎን ምላሽ እንደሚጠብቅ ጠይኳቸው፡፡

እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ነገር አልመልስም፡፡ አንዴ ተናግሬዋለሁ፡፡ ሃሳቡን ለማግኘት መጽሐፉን ማንበብ ይቻላል፡፡ ያልገባው ካለም ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ አሉ፡፡

እኔም መጽሐፉ ላይ ይለውን ሐሳብ ለመመልከት መጽሐፉ እንዳላቸው ጠየቋቸው፡፡ አሁንም ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ይዘው መጡ፡፡ ሰጡኝ፡፡ ከጻፏቸው መጽሐፍ ሙሉውን ያላነበብኩት ይሕንን እንደሆነ ተናግሬ እንዲያውሱኝ ጠየኳቸው፡፡ ብቸኛ ኮፒ እንደሆነ በመንገር እንደማይሆን መለሱኝ፡፡
በስልኬ ፎቶ ለማንሳት ገጽ ስገልጥ “ስለ አማራ ጎሳ መሆን አለመሆን” የሚሳየውን ገጽ ራሳቸው  ፈልገው ሰጡኝ፡፡ እኔም የስልኬን ካሜራ ወደ ሳቸው በማዞር ፎቶ አነሳኋቸው፡፡ ማስፈቀድ ነበረብኝ? የተሳሰትኩ መሰለኝ፡፡ ሆኖም ታሪክን በስልከ ከመያዝ የበለጠ ምን ምንም አስደሳች ነገር የለም!
Professor_Mesfin_Woldemariyam_May_2015

ወደ በሩ አመራን፡፡ በሩን ከፈቱልኝ፡፡
ጤና ይስጥልኝ!
ጤና ይስጥልኝ! ተሰነባበትን..፡፡
---
የመጀመሪያውን ደረጃ ጨርሼ ከግቢው ውጭ ወዳለው አስፓልት ስራመድ በመስኮት
“ተስፋ” የሚል ድምጽ ሰማሁ!
ዞር አልኩ፡፡
እስክርቢቶየን ይዘው በመስኮት ለማቃበል ቆመዋል፡፡
እሺታዬን ነግሬ ወረወሩልኝ፡፡
ተቀበልኩ፡፡
እጄን ለሰላምታ አነሳሁ
እጃቸውን አነሱ!
ፊት ለፊት አንዲት እናት ጃንጥላ ይዛ ወደ ታች ትወርድ ነበር፤ በመስኮት ፕሮፌሰሩን እየተመለከተች የአድናቆት እና የሃዘኔታ ፊት ሰጠችኝ፡፡ የኔም ፊት እንደዛው ነበር…፡፡
 *****
ከመጣሁበት መንገድ ይልቅ የምሄድበት ሩቅ መስሎ ታዬኝ!!
ግንቦት 2007፡፡

No comments: