May 11, 2015

ዙቤይዳን እንዳነበብኳት…..እንዳ-ነበ-ነቧት!



ዙቤይዳን እንዳነበብኳት…..እንዳ-ነበ-ነቧት!

‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››

Alex Abreham-ZUBEYDA



“አሌክስ አብርሃም” አሁን አሁን የፌስቡክ ድረገጽ ስያሜ እስኪመስለን ድርስ በኢንተርኔት መስኮቶች ላይ እየታዬ መጥቷል፡፡ በዚሁ ዘመን አመሽ መተያያ /Facebook/ ዘይቤ የምናውቀው ይሕ ሰው፤ ይሕንን ዘመን አመጣሽ የጉርብትና ዘዴ በመጠቀም፤ ከአምደኛነት እስከ መጽሐፍ እስከማሳተም ደርሶ፤ ይሄው አሁን ሶስተኛ ሥራውን አቀረበልን- ዙቤይዳ፡፡
በ”አምልኮተ ቀን” ‹‹‹‹‹ቅዳሜ›››› ግንቦት አንድ ቀን 2007 ዓመተ ምሕረት አሁንም በተለመደው የፌስቡክ ገጽ ዜናው ሲሰራጭ፤ አዲስ ነገር ናፋቂው ተከታይ ትውልድ፤ ይሕችን መጽሐፍ ለመግዛት እሽድምድም ሲያሳይ እንደነበር፤ በግሌ እንኳ ተደውሎ “ገዛሃት?” ያላሉኝ “ጥቂቶች” ነበሩ!
እኔም “የሃበሻ ጀብዱን” እና “የቄሳር እንባን” መሰል መጽሐፍት ወደ ጎን አስቀምጬ- በቀነ ቅዳሜ ዙቤይዳን “ለመቃም” ተቀጣጠርን፡፡(የዋልንበት ቦታ ሁሉ ያለን እየመሰላቸው ስንቶች በዋልንበት ፈረጁን…ገጽ10)
አይናለም መጽሐፍት መደብር በጥሩ ዋጋ ሥላቀረበልን እና የሊትማኑ አንዋርን እያመሰገንኩ፤ አሌክስን ለመቃኘት ተሰየምኩ፡፡
ታድያ ብቻ መሆን ስለሚከብድ ሌሎች ወዳጆቼ አብረውኝ “ዛፍ ላይ” ወጡ፡፡
ከመካከላችን አንደኛው ለአሌክስ አብርሃም ልዩ ጥላቻ ሥለነበረው፤ እርሱን ይዞ ማንበብ ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም ልዩነቶች መኖራቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ማመሳከሪያችን ይሄው ክስተት ነበር፡፡ የድጋፍ ጥላቻ እና መውደድ ግን የትም እንደማያደርስ እንተማመን! "ድንቡጮ ለምን ለምን ሞተ!!!!!!" ሃሃ..፡፡ አዲሱ መፈክሬ ነው!
ልጁ(ጥላቻው) ሲያነበው አቃቂር እየለቃቀመ እና ሥሕተት የተባሉ ነገሮችን በሙሉ ከመጽሐፉ ዋጋ በላይ አግዝፎ ማሳየት ነበር፡፡ የፊደላት ግድፈቶችን ሳይቀር እየለቀመ፤ በ”ማይክሮስኮብ” ሲመለከት እንደነበር ማስተዋል ጀመርኩ፡፡( የገጽ30ዋ ‹‹የቁርጥ ገን›› አይነት ነቁጦችን ለመለቃቀም የሚያነብ ነበር የሚመስለው- የብሩክታዊት ጌታሁን “ማንም ፍጹም የለም” አልበም ገዝቶ ያመጣው እኮ እርሱ ነበር!?
 ጥሩነቱ አሌክስ ከ3 እና ከአራት ፊደላት በልጦ በግድፈት አልተገኘም (ለኔ የሚያስመሰግን ነው)፤አቤት ጥላቻ የሚባለው ግን- የማያደርገው የለ! መውደድም ግን `ንደዛው ነው!!
በዚህ አይነት የክርክር መድረክ ሆኖ ከማንበብ ብቻ ሆኖ ማንበብ ስለመረጥኩና፤ እያንዳንዳችንም ተውሰን ከማንበብ ይልቅ ገዝተን ማንበብን ስለምመርጥ ገዝተህ አንብብ አልኩት ወዳጄን፤(የወዳጄ ጠላት እንዴት ወደጄ ሆነ?)
“ኧረ ባክህ! 60 ብርማ ገዝቼ አላነብም” ሲል የ80 ብር ጫት በእጁ ይዞ እንደነበር ሳልናገር በአይኔ እያመላከትኩ መለስኩለት፡፡
ሲጀመር በምርጫ ሰዓት ይሕንን ይጽፋል…??? አዎ ይሄ ጫት ፍላጎቴ ነው፡፡” አሌክስ አብርሃም ደግሞ በፌስ ቡክም ሆነ በሌላ መድረክ የጻፋቸውን ብጥስጣሽ ሃሳቦችን በዚህ ዋጋ አይደለም በነጻ እንኳ  ቢሰጠኝ ላልቀበለው እችላለሁ! ገንዘብ ለመሰብሰብ እየሞከረ ነው፡፡” ሲል እና ተርዚናው ላይ ሲጎሰጉስ አንድ ሆኑ፡፡
“ለምን?” አልኩት ሲቅም ባሕርይ በየደቂቃው ስለሚለዋወጥ አሁን ላይ የማውራት ሙድ ላይ ነበር፡፡ በኋላ እኮ ሊዘጋጋን ነው - ትንሽዬ መስታውት በእጁ ይዞ መልኩን ሊመለከት!!!
“የተለየ ነገር አልጻፈማ!” ሲል መለሰልኝ፡፡
“ከዶክተር አሸብር የተለዬ ምን ጻፈ?” ቀጸለ፡፡
“ሳታነብ? ሁሉንም ጽሑፎች ሐሳባቸውን ሳትረዳ እና ምን ለማለት እንደተፈለገ ሳትገነዘብ አስቀድሞ መፍረዱ ትክክል አይደለም!” መለስኩለት፡፡
“ይሄውልህ አንተ ዝም ብለህ የአሌክስ አብርሃም አፍቃሪ ነህ! ቢራውን፣ ጫቱን፣ አደንዛዥ እጾችን ስለሚያወግዝልህ ትወደዋለህ እንጂ በሥነ-ጽሑፉ ምንም አይነት እርምጃ አላሳየኝም፡፡”(ጥላቻውን ፊቱ ላይ ስመለከት ምክንያቱን ለመመልከት እያቃተኝ)
“ሥነ-ጽሑፍ ዓላማው ምንድን ነው? ማሳቅ? መሳረርን በይፋ እና በአደባባይ አውጥቶ መሳለቅ ነው?” እኔ አልገባኝም ስል ጠየቅሁት!
“እስኪ ዙቤይዳን ለማንበብ እንሞክር” ብሎ መጽሐፉን ከእጄ ተቀብሎ ‹‹ዙቤይዳን›› መፈለግ ጀመረ፡፡
ከ22ቱ አርዐስት ውስጥ ‹‹ዙቤይዳ›› የሚል አንድ ርዕስ ፈልጎ ሲያጣ፤ ሌላ ነገር ሊያወራ ሲል- “አንዲት መርፌ ስንቱን ቀዳዳ ትስፋው” የሚለውን ርዕስ እንዲመለከት ጠቆምኩት፡፡
ልጁ ወደ ጥልቁ በዝምታው ሃይቅ እየዋኘ ነው፡፡
-*******-
የመጽሐፉን የፊት ገጽ ሽፋን በመመልከት ብዙ ነገር መጻፍ፣ መናገር እና መረዳት ይቻላል፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ እና ስናነብ ግን ከመጽሐፉ ሽፋን ጋር እንደማይገናኝ ለመናገር ሞከሮ ነበር፡፡ በዓሉ ግርማን በዚህ አደንቀዋለሁ ሲል የተለመደ አመክንዮዩን ለመዘርዘርም ሞከሮ-ከዝምታው ሃይቅ ዋና በፊት፡፡
እኔም “በዓሉ ግርማ በራሱ የግሉን ማንነት፣ የጊዜውን ሁኔታ ተመልክቶ ኦሮማይን ሲጽፍ በፊት ገጽ ሽፋኑ ምንም ነገር መናገር አልፈለገም፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ስንገባ ግን ሁሉን ነገር ዘከዘከው፡፡ በየቦታው ተሰራጭቶ የነበረው መጽሐፍ ሁሉ እንዲመለስ ተደረገ፤ ያኔ ማንበብ ያልመረጡት ሰዎች በሙሉ ማንበብ ጀመሩ፤ እንደውም ቅጂው በውድ ዋጋ እስከ መሸጥ ደረሰ፡፡ በዓሉም የመጥፋቱ ሞት ምክንያት ሆነ፡፡ አሁን ያለን ሰው እንደ ትላንት ሁን ማለት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡
አሌክስ አብርሃም ደግሞ የራሱ ስብዕና የአዲሱ ትውልድ አስተሳሰብ እና ማንነት፤ ከትላንትናው ትውልድ የተማረ ሆኖ የፊት ገጹ ላይ ግልጽ ነገር ተናገረ፤ ውስጥ ስትገባ ግን ሌላ ነው፡፡(ለኔ ግን በሰፊው ይታየኛል!)፡፡
ሥለዚህ ሁሉንም ሰው እንደ ሁሉ ማድረግን ትተን፣ ጸሐፊንም በሕዝብ ፍላጎት፣ አስተሳሰብ እና መዳፍ ስር ለማስገባት የምንሞክረውን ኃጥያት አውግዤ፣ ሌላም ሌላም ተያያዥ ምክንያቶችን ጨማምሬ ወደ ውቧ ‹‹ዙቤይዳ›› አመራሁ- እንዴት እንደወደድኳት!
የመጽሐፉ ርዕስ ‹‹ዙቤይዳ›› የተሰኘው “አንዲት መርፌ ስንቱን ቀዳዳ ትስፋው?” በሚል ርዕስ ስር በቀረበች አንዲት ገጸ ባሕርይ በመነሳት ነው፡፡
ጸሐፊው ምን ለማለት እንደፈለገ እና መርፌን፣ ቁምጣን፣ ኢፍትሃዊነትን፣ መለያየትን፣ ወጣቶችን እና ስደትን አያይዘን የሚሰጠንን ድምር ውጤን በመገንዘብ፤ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት እንችላለን፡፡ ሳናነብ መጥላት፣ ሳንገዘብ ለፍረድ መቸኮል ከጥላቻ ጋር ተደምሮ ወደ ዜሮ ያወርደናል፡፡ ወደየትም አያንቀሳቅሰንም- ወደ ዝምታ ሃይቅ እንጂ!! አንብበን እንረዳ፣ ተረድተን ለመነጋገር እንሞክር፡፡ እሱ ጫቱን ቀጠለ፡፡ በአንዲት የጫት እንጨት ጥርሶቹን እያነቀሰ፡፡ እኔም ዙቤይዳየን ቀጠልኩ፡፡
*****
በኔ አመለካከት አሌክስ አብርሃም የአዲሱን ትውልድ ማሕበረሰብ ቅኝት፣ በቀላል አማርኛ እንዲሁም በአንዳንድ አስገራሚ ተምሳሌታዊ ገላጭ ሃሳቦ እያዋዛ የሚስተምረን፣ ጉዳችንን በአደባባይ አውጥቶ፣ ውሸት፣ ኢ-ምክንያታዊነት ፍቅረ ንዋይ ምን ያክል እንደገዘፉብን የሚሳየን፤ በዚህ ትውልድ የራሱን አሻራ ጥሎ የሚያልፍ አንድ ገጸ ባሕርይ ነው፡፡ “አሌክስ አብርሃም” ግለሰብ አይመስለኝም- ገጸ ባሕርይ ነው…፡፡
ጽሑፎቹን በነጻ በፌስቡክም ሆነ በሌላ ገጽ አስነብቦን ይሆናል፤ ገንዘብንም ሆነ ታዋቂነትን ሳይሳሳ ጽሑፎችን ሌት ተቀን መጽውቶናል፡፡ ያውም መጽዋች ራሱ በተመጽዋች ክንድ ተንተርሶ መክበር በሚፈልግበት በአሁኑ ጸያፍ ገብያ ላይ…!
ሥለዚህ እነዚህን ጽሑፎች በአንድ ላይ አጠራቅሞ ለገበያ ማውጣቱ፤ እርሱን ለማበረታታት የሚለውን ዝቅተኛውን ምክንያት ትተን “ማንኛውም ነገር መፍ አለበት” የሚለውን የአዳም ረታን ብኂል ተከትለን፤ ይሕንን ዘመን ሊያስቃኙን የሚችሉትን ሃሳቦቹን ለታሪክ ማስቀመጡ በራሱ ጉዳቱ አይታዬኝም!
አዳም ረታ ከአጫጭር የጽሑፍ ስራዎቹ ጀምሮ “መረቅ”ን ሲሸልመን፤ እንዲሁም በሺዎች ገጽ የሚቆጠር መጽሐፍ እየጻኩ ነው ሲለን-(የሰንብት ቀለማት)፤ እኔ ነገ አሌክስ አብርሃም ምን እንደሚያስነብበን በማሳብ ልቤ በሐሴት ትሞላለች፡፡ ነገ የአዋቂ ጸሐፊ፣ ማሕበረሰቡን ተመልክቶ ወደ እውነተኛው ጎዳና ለመግራት የሚጥሩ ግለሰቦች እየደበዘዙ እና እየተረገጡ በሚሄዱበት አቅጣጫ ውስጥ ሆኜ አሁን አሌክስ አብርሃምን ማመስገን፣ መንከባከብ እንዳለብኝ ይሰማኛል!
3ኛው መጽሐፉ ዙቤይዳ፤ ቁጥር ሁለት ዶክተር አሸብር ብንላት ያው ነው፤ በውስጧም ከ90 በመቶ በላይ ሥለ ሴቶች ታወራለች፡፡ ሙሉ ገጸባሕርይውን የያዘውም አብርሃም (አብቹ) ነው፡፡ ሥለዚህ “አገር ሰው ነው” የሚለውን አስተሳሰብ  ሲቃወም ለነበረ ጸሐፊ(በግጥም መድብሉም ውስጥ አለ)፤ “አገር ሴት ነች”  “አገር ሰው” ነው፡፡ እያለን እንደሆነ ለመረዳት ዙቤይዳን ማንበብ ቀላል ይመስለኛል፡፡
አፍራህ፣ ዙቤየዳ፣ ዮርዲ፣ ሙና፣ ሄዋን፣…. አገሮቻችን ናቸው፡፡ ሰው አፈር መሆኑንም ግን ሳንዘነጋ!
`ሽንፈተ እና ስንፈተ`
`የአሳዛኙ የድንቡጮ ታሪክ`
`የሰይጣን ሥራ`
`የጸሎት ኃይል…` እና መሰል ስራዎቹ ማሕበረሰባችንን ከጊዜው ጋር አላትሞ፤ በምክንያታዊ መነጽር ለማመልከት የሚጥር ሥራ እንደሆነ መረዳት ችያለሁ፡፡ “ዶክተር አሸብርን” በቁጥር ሁለት ቢደግመውም የሚታዬኝ የነገ ማንነቱ ነውና- “አያያዙን አይቶ…፣ የሚያጠግብ እንጎቻ…” እንዲሉ፡፡
ፖለቲካውንም ተረድቶ ይሕንን አይነት አጻጻፍ እየተከተለ መሆኑን ለመረዳት አንድ አንቀጽ ውስጥ ያገኘሁትን ሃሳብ ላስቀምጥ፡፡ (አዕምሮ ያለውን ሁሉን ነገር ለመገንዘብ የሚያዳግተው አይመስለኝም፡፡)
“ሕይወት አገር ቢሆን…. ፍቅረኛ፣ ሥራ፣ ዕውቀት፣ መዝናናት፣ሐዘን፣ደስታ፣ ቤተሰብ ብሔር ብሄረሰቦች ናቸው፡፡” ገጽ123፡፡ “ድንቡጮ ለምን ለምን ሞተ!?!...” “39ኛው ዕቅድ”…፣ እና መሰል ጽሑፎችንም ከልብ ያስታውሏል!
ከዚህ በላይ ሌሎች ሃሳቦችን በሥነ ሒሳዊ ይዘት ተከትሎ ለመተቸት የሚችል ሰው ካለ ሃሳቡን ያቅርብልን፡፡ ሙልጌታ ሉሌ የበዓሉ ግርማን ጽሑፍ ሲተቸው እንዴት መተቸት እንዳለበት ሳያስተምረን አልቀረምና፡፡
እኔም መዝጊያየን በአንድ አንቀጽ በር ላይ ላሳይ…
ገነት ሆቴል ስደርስ ወደ አፍሪካ ኅብረት ታጠፍኩ፡፡ ጸጥ ባለው መንገድ ግራና ቀኝ በተሰለፉበት የዘንባባ ዛፎች መሐል እየተጓዝኩ ረዥሙ የአፍሪካ ሕብረት ሕንጻ ከፊቴ ተጋረጠ፡፡ አፍሪካዊ  ነኝ፣ እኔ አፍሪካ ነኝ፤ በአረንጓዴ ምድር የፍቅር ችግር አድርቆኝ ውስጤ ምድረበዳ የሆነ የአፍሪካ ልጅ ነኝ፤
አፍሪካ፣ አፍሪካ፣ አፍሪካ-
“ስደት” የሚል ቃል አእምሮዬ ውስጥ ፈነዳ! አዲስ አበባ የኔ አይደለችም፡፡
አንዲት መርፌ ስንቱን ቀዳዳ ትስፋው?

ገዝታችሁ አንብቡ፡፡ መልካም ንባብ!
.
.
.
ዙቤይዳ…!




No comments: