አሌክስ አብርሃምን በእናት ፍቅር ሐገር
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
ይገርመኛል፤ እንዲህ አይነት ጸሐፊ ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ ለዚህም ነው
የምስጋና ብዕሬን የሠደርኩት፡፡ ሥለ ልጁ የግል ማንነት፣ መልክ፣
ጥይምና፣ ዕድሜ አሊያም አጠቃላይ ገጸ ሰብ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ሆን ብሎ የተደረገ መሆኑን ስናስብም ነው የሚደንቀን፡፡ ስሙን
“አሌክስ አብርሃም” ብሎ በመሰየም፤ ዓለም በፈጠረው ዘመን አመጣሽ የልቡና ማስተንፈሻ ሽንቁር (ፌስቡክ) በየዕለቱ የሚለጥፋቸው
ሕብረ ቀለማማ፣ ዜማ ሙሉ ሐተታ ግርም ድንቅ ይሉኛል፡፡
አርት እና አርቲስት በሚል ርዕስ ይዘት ፈላስፋው ዘርዓ ሌሊሳ፤ “አርት
ከምንም በላይ ቀድሞ ሊታይ እና ሊተረጎም የሚገባ ሲሆን አርቲስቱ ግን ከገጠጠ እና ቀድሞ የሚሸለም ከሆነ ውርደት መሆኑን” ገልጾ
ነበር፡፡ በአፍሮ ጋዳ ድርሰቱ!!
አሌክስ አብርሃ የብዕር ስሙ ሲሆን ግለሰቡን የምናውቀው እና ገጸ ሰቡን
በሕሊናችን የምንስለው በየዕለቱ ለእውነት ሲታገል፤ ለተፈጥሮአዊ ሕልውና ዘብ ቆሞ ዘራፍ ሲል ነው፡፡
‹‹ዘራፍ›› አንዳንድ ጊዜ ይጨንቃል፡፡ ሰውን በምኒሽር ገሎ ዘራፍ ይጨንቃል፤
ይሕኛው ብላቴና ግን በውብ ቃላት አቀማመጥ እና አመክኔያዊ ውብ ሓሳቦቹ አንባቢን እጅ ወደ ላይ ያስብላሉ፡፡ በፍቅር ማሸነፍ፤ በጥበብ
ማሸነፍ፤ ተሸንፎም ማሸነፍ የድሎች ሁሉ ድል ነውና!
ያበዛዋል፤ ሁልጊዜ ነቀፋ ነው የምትሉ ካላችሁ ደግሞ መልሱ ቀላል ነው፡፡
በአሁን ሰዓት ሊነቀፉ የሚገባቸው እኩይ ተግባራት በነገጉበት ዓለም ውስጥ ዝም ብለን የምንመለከት ከሆንን የዚህ እኩይ ተግባር ደጋፊዎች
ነን ማለት ነው፡፡ ለእኩይ ተግባራት ተቃውሞ ማሰማትን መንቀፍ የለብንም! እኩይ ተግባር ሲለመድ ባህርያችን መሆኑ ስለማይቀር ነው
ዓለም አኩይ ተግባራትን በይፋ እየነዛች ያለቸው!
“ዶክተር አሸብር…” ከ20ሺሕ ኮቢ በላይ መሸጧ፤ እንዲሁም ከዚህ በላይ
እንደምትሄድ ስናስብ፤ ከዚህ በተጨማሪም “እናት ፍቅር ሐገር” የግጥም ስብስብ ይዘት ስንመለከት ከዚህ የበለጠ እንደምናይ አንጠራጠርም፡፡
አገር ተቃጠለች….
ነጻነት አጠጠ
የጃጀ ስረዓት…
ሕዝብ ላይ አረጠ
መድፍ ተተኮሰ
ታንክ ብረት አገሳ፣
ሰላም ኮበለለ
ብጥብጥ ተነሳ…
ዝምታ አከተመ
አብዮት ተነዛ….
ሂድ ወደዛ!!
በሚል ስንኝ የተቋጠረው ‹‹ንጭንጭ ያደርገኛል›› የግጥም ዘለላ የትውልዴን እንቅልፍ(ለሽ ማለት በቆረጣ ያስቃኜናል፡፡)
33ኛው ግጥም “ገጣሚው ወዳጄ”
ዛሬ ከፊታችን
ዘላልም የሚያህል ባሕር ተዘርግቶ፣
ፍጥረት እህህ
ሲል የሚያሻግር ጠፍቶ፣
ትዝታው መጣብኝ
ገጣሚ ወዳጄ፣
ላልገጠመ
ነፍሱ ግጥም እያበጀ
በሚል አንጓ ግጥም የነፍስ ትሩፋት፣ የመንፈስ እርጋታ እና መገጣጠም መሆኑን
ያስረዳናል፡፡
ወረድ ካለው አንጓ ላይም
እናልህ ወዳጄ
እንደዚህ እንዳንተ እርሙን ለሚበሉ፣
ያለ የነበረን
“ምን ነበር” ለሚሉ፣
ምን አለ
መሰለህ…
የለት እንጀራህን
ማድቀቂያ ማግኛ፣
“ስም” ይሉት
ጥርስ አለ ሰላሳ ሦስተኛ…
ሲል ሃሳቡን ይገልጻል፡፡
“የኔ ፎቶ
ሞቷል!”
…
እኛ ነን
እያልን የምንፎክርበት፣
ስንት የሞተ
ትላንት ስንት ያለፈ ውበት፣
በየግድገዳችን
ክብር ሆኖ ነግሷል፣
ጊዜ ደራሽ
ወንዙ ትላንት ላየ ጥሎን የትና የት ደርሷ!
እና ይሄ ምስል እና ይሄ “ፎቶ”
ልክ እንደብርሃኑ በለጭ ብሎ ጠፍቷል፣
ዛሬ እኔን አይደለም ትላንትናም
ሞቷል!!
የሰው ልጅ ልቦና መልክ ለፈለገ
እኔ አሁንን መሳይ
እኔ ማልት ነገ!!
“እኔ የምኖርበት
ኮንዶሚኒየም ፊት…”፣ “አራተኛው ሰማይ”፣ “ዘፀዓት”፣” ባሕር ነን”፣
በሚገርም ቀለል ባለ አርዕሰት ውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኝባቸው ጀልባዎች ናቸው፡፡ ጀልባዋ አቅም አንሷት የውቅያኖሱ ወጀብ
እንዳይከድናት ጸሐፊው እንደ ሕይወት አድን ሆኖም ከጀርባችን አለ፡፡ እንደ አብዛኛው ጸሐፊ ጥሎን አይሄድም፡፡
“ግጥም ለሚገጥሙ…”
ግጥም የሚገጥሙ…፣
በፅንፍ የለሽ
ምናብ
በህዋ ነጻነት
አውነትን ይቃዡ
አውነትን
ያልሙ…
.
.
.
ጎዳና ይትለሙ.
.
.
ነብይ ከማጀብ
“ከነብይ” ይቅደሙ…
ወደ ጥበብ
ማዕድ ደፍረው ከቀረቡ፣
ሕልማቸውን
ጥለው እንቅልፍ አያንብቡ…
ወጣም ወረደም ይሕንን ልጅ አንብቡት፣ ምን ለማድረግ እና ለማለት እንደፈለገም
በሥጋ ብቻ አትመልከቱት፡፡ ሥጋ ለባሽ ፍጡር ነውና፤ መንፈሱ አርነት ታወጣው ዘንድ አጋር ሁኑት፡፡ ሆኖም በመንፈሱ አርነት የወጣ
መች የሥጋ ችንካር ያስቀረዋል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ኢንተርኔት›› ለማግኘት የሚችለው ሕዝብ እና ‹‹ኢንተርኔት››ም
አግኝቶ ፌስ ቡክ የሚጠቀመው ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ (ኢህአዴግ እንኳ በፌስቡክ 23 ሺህ ለይኮች ሲኖሩት አሌክ አብርሃም
በእጥፍ ይበልጠዋል፤ … ) 98 በመቶ የሚያሕለውን ሕዝብ ለመድረስ ፌስ ቡክ የውቅያኖስ ጭልፋ ነው፡፡ ሥለዚህ ይሕንን ልጅ “እንዴት
ውቅያኖስ እናድርገው” በሚለው ላይ ብንመክር የተሻለ ይመስላል፡፡ እሱን እና መሰል ወጣት ጸሐፊያንን፣ ዘመን በሥጋ ምች በተመታበት
አሁን፣ አበቅቴ በንዋይ መርዝ በተነደፈበት አሁን፣ ወገን በስሜት ልነዳ በሚልበት ፈረሰኛ ጉዞ -አሁን፣ እሱን አና መሰል ጸሐፊያንን
እንዴት እናሳድጋቸው? እንዴት ብርሃናቸው ከውቅያኖሱ አውድማ ላይ ተላትሞ ውብ ሕብረ ቀለምን ይስጥ? ነው ጥያቄያችን መሆን ያለበት፡፡
ለሽሽሽሽ ማለት ማንን ጠቀመ?
No comments:
Post a Comment