Jul 1, 2015

‹‹አዳፍኔ›› የመክሸፍ ወላጅ አባት፡- የማይከሽፈው የፕሮፌሰር መስፍን መክሸፍ!




ተስፋ በላይነህ
 
Prof_Mesfin_`Adafnie`_Book-2015
ሀ-አገር
ማን ነው ከእናቴ ጣፋጭ ጡት የነጠለኝ? ማን ነው ከምወዳት ውዷ ባለቤቴ ጣፋጭ ከንፈር የለየኝ? ማንስ ነው ከተኛውበት ረዥሙ የዘመን እድሜዬ የቀሰቀሰኝ…?
እርግጥ ነው ከእናቴ ጡት መነጠል፣ ከባለቤቴ ከንፈር መለየት እና ከዘመን እንቅልፌ መንቃት ነበረብኝ፡፡ የእናት ጡት- መርዝ ሲያመነጭ- እናት በርሃብ፣ በድርቅና በስደት ጡቷ ሲደርቅ- ሚስትስ አገር እየተወረረች፣ ባዕዳን እየሠለጠኑ- ሕዝብን እያሰየጠኑ- በሴራና በተንኮል ታሪክን እያሰናከሉ- እንቅልፍስ ቅዠት ሲሆን፤ ሕልሙ ሁሉ ወደ ትንሣኤ አልባ ዝምታ ሲቀየር- ረዥሙ እንቅልፍ ወደ ሞትነት ሲቀየር- የሰው ልጅ ድንጋይ ሲሆን- ከድንጋይ ጋር ሲተያይ (አዳፍኔ ገጽ 21)፤ ያኔ የእና ጡት፣ የሚስት ከንፈር፣ እና እንቅልፍ ምንድር ናቸው? አገር እናት ናትና! አገር ሚስት ናትና! አገር እንቅልፍ (ሠላም) ናትና! “መስፉን” ቀሰቀሰኝ!
ለ-የሰው ልጅ ከሸፈ ወይንስ ኢትዮጵያ ከሸፈች?
እንደኔ አመለካከት የሰው ልጅ የከሸፈው ትእቢት፣ አለመታዘዝ በዲያቢሎስ አማካሪነት ጥምረት የተገኘላቸው ዕለት በአዳምና በሔዋን ነው፡፡ የሰው ልጅ በየትኛው ዘመኑ ነው ፍትኃዊ፣ ዘላቂና ሠላማዊ ሥልጣኔን ለዘመናት ያቆዬው? መክሸፍ ትላንትም ነበር-ዛሬም አለ- መቆምያም የለውም፡፡ የሰው ልጅ በክፉ መንፈስ ጥሪት ተነፍቶ ነፍሱ በምድር እስካለች ድረስ መክሸፉን አያቆምም! መክሸፍ የምንጊዜም የሰው ልጅ ወዳጅ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍንን “ትላንት አልከሸፍንም?” ብዬ እንዳልጠይቃቸው እሳቸው ያዩት የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከ1933 ጀምሮ እየከሸፈ የመጣ ነው፡፡ አባቶቻችን ክብርና ኩራት ነበራቸው፤ ነገር ግን የመሻሻልንና የሥልጣኔን ጎዳና ስላላቀለሉልን መክሸፍ በክብርና በኩራት ማኅደር ውስጥም ነበር፡፡ የአክሱምን ሐውልት የጠረበ ትውልድ፤ የላሊበላን መቅደስ የወቀረ ትውልድ፤ ፋሲለደስን የገነባ ትውልድ በጢስ ቤትና በጎጆ ሳር የመኖር ምስጢር የመክሸፍ ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የከሸፉት መክሸፍን የምድር ጠላት ማድረጋቸው ሳይሆን፤ መክሸፍ የሰው ልጅ እጣ ፈንታ መሆኑን አለመረዳታቸው ነው፡፡ የሰው ልጅ ከክፉ መንፈስ ጥሪት ሳይነጣጠል፤ የሰው ልጅ ጠበንጃን፣ አመጽንና አራዊነትን ከምድረገጽ ሳያጠፋ መክሸፍን ማስቀረት ይቻላል ብሎ ማመን በራሱ መክሸፍ ይመስለኛል፡፡ የሰው ልጅ መቼም ቢሆን በምድር ሲኖር መክሸፍን ከጉያው ሊነጥል አይቻለውም፡፡ ምናልባት ጥቂቶች የነጻነት፣ የአርነት፣ የሠላምና የጽድቅ መንገድን ተከትለው በራሳቸው ላይ ያለውን የመክሸፍ እጣ ፈንታ ሊሰብሩ ይችላሉ፡፡ ይህ የሰው ልጅ እድል ፈንታው ነው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀውም ይሕንን ማድረግ እንጂ፤ አራዊቶች መሳሪያ በሚያነግቡባት ዓለም፣ ክፉ መንፈስ መሪ ተብየዎቹን ከመጋለብ ሳይቧዝን፤ የብሪታንያ ተንኮል ሳይሰበር፤ የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ከልብና ከመንፈሱ ሳያላቀቅ መክሸፍን ማስቆም የዐለምን ኃጥያት በደም እንደመሸከም፤ የክርስቶስን መስዋዕትነት እንደ መወከል ነው፡፡ የሰው ልጅ የምድር እጣፈንታው ይሄ ነው! መክሸፍ!!
ሐ- መክሸፍ ወይንስ መሸነፍ?

የጽድቅ መንገድ መምሕር እና ፈር ቀዳጅ ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ መክሸፍን ሊያቆም፤ የሰውን ልጅ እብሪት ሊደመስስ፣ የክፉ መንፈስ ልጆችን ከዲያቢሎስ አባታቸው ሊነጥል 33 ዓመት በምድር ሲቆይ፤ የመክሸፉ አለቃ ሰይጣን አራዊትነቱን ያሳየው በመግደል ነበር፡፡ ስቅላት፡፡ መግደል የክሽፈት አለንጋ ነው፡፡ ክርስቶስን በመስቀሉ ላይ ማዬት የመክሸፍ፣ የመሸነፍ ወይንስ የድል ምልክት ነው? ፕሮፌሰሩ ይህን አያጡትም፡፡
ዲያቢሎስም እስከ አሁን ድረስ መክሸፍን ያገዘፈው መግድልን እንደ “አልፋ ኦሜጋ” መርሁ ሥለተጠቀመበት ነው፡፡ ትንሣኤ የመክሸፍ ጌታ ነው፡፡ መክሸፍ የሚደነግጠው በትንሣኤ ነው፡፡ ክርስቶስም መክሸፍን ያሸነፈው በትንሣኤው ነበር፡፡ አዳፍኔ ሲወጣ ትንሳኤ ይገባል፤ ትንሣኤ ሲወጣ አዳፍኔ ይገባል!!
አሁንም ዲያቢሎስ በምድር እስካልተወገደ ድረስ፤ እስራቱን እስካልጨረሰ ድረስ፤ የሰዎችን ልብ ወደ ክፉ አሳብ መዘወሩ እስካልተገደበበት ድረስ፤ በስንዴው መካከል የተደባለቀው እንክርዳድ እስካልተቃጠለ ድረስ፤ የሰው ልጅ መክሸፍ አብሮት የሚኖር ካባው ነው፡፡ (ካባ፡ አዳፍኔ ገጽ 42) የተሸነፉትም (አዳፍኔ ገጽ 48) ስደትን የሙጥኝ ብለዋል- ምን ያድርጉ እዚሁ ሁነው ይለቁ? መሰደድ ከክርስቶስ ጀምሮ የነበረ የሰው ልጅ እጣ ፈንታው ነው፡፡ ወጀቡን ለማሳለፍ የሚሰደዱ አሉ- በርግጥ ሰው የተሰሰደ ዕለት እንደሞተ ይቆጠራል!
መ-የመክሸፍ ዓለቃ እና የመክሸፍ ሰለባ? 
ፕሮፌሰር መስፍን የመክሸፍን መንስዔነት ከአጼ ዮሐንስ ጋራ ለማዛመድ ሲጥሩ ለመመልከት (አጀማመራቸው ከገጽ 8-15) ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ ባልሳሳት እሳቸው የመክሸፍ መነሻችን ይሔ ነው እያሉ አለመሆኑን በመገመት ነው፡፡ እያሉንም ይሆናል፡፡ ሆኖም የመክሸፍ ምሳሌ ተደርጎ መቆጠሩ ላይ አልከራከርም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ የመክሸፍ መንስዔ ከየት ይጀምራል? ብሎ መጠየቅና መሰረቱን ማወቅ ከተገቢነቱ አልፎ ስለ መክሸፍ ትልቅ ጽንሰ ሀሳብ መያዝ ላይ እንድንደርስ ይረዳናል፡፡ እኔ እንደምለው የመክሸፍ መንስኤ የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር የተለያዬ ዕለት የተከሰተ ነው፡፡ ሔዋን የመክሸፍ መሰረት ስትሆንና የክፉ መንፈስ ምክር መክሸፍን ሊያመጣ እንደሚችል መገንዘብ ላይ አተኩራለሁ፤ ለዚህም መክሸፍ በዐለም ሕዝቦች ላይ የተጣለ ካባ ነው፡፡ እንጂ ፕሮፌሰር እንደሚሉት መክሸፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሕርይ ብቻ ሆኖ መሰጠቱ ላይ ብቻ አልዳክርም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እየዳከሩ ያሉት መክሸፍን ከኢትዮጵያ ገዥዎች እና ሕዝቦች ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ “በኢትዮጵያ ውሸት አይሞትም” ይላሉ፡፡ አዳፍኔ ገጽ 21፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ፤ ውሸት የሞተው በየትኛዋ የምድር ክፍለ ሐገር ነው? ከውሸት ውጭ ወደ ሥልጣን የታደመው ማን ነው? ከፍ ያለው ሥልጣኔን የማን ነው? መክሸፍ የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ነው! በትንሣኤ ካልገደብነው በቀር!
ፕሮፌሰር መስፍን የመናናቅንና የጎሳ መበዳደልን በየትኛውም ክፍለ ዘመንና ቦታ እንደነበረ ለማሳዬት ሞክረዋል፡፡ በጊዜ ቆይታም በደቡብ አፍሪካና በአሜሪካ ከነበረው የቀለም በደል ነገሮች ተቀይረው ማንዴላንና ኦባማን እንደ  ምሳሌ በአዳፍኔ ገጽ 24 ማቅረባቸው በጣም የሚያስቅና በሌላው ዓለም ቢያንስ የመክሸፍ መሻሻል አለ ብሎ ለመጥቀስ ከሞመከር ተለይቶ አይታየኝም፡፡ በገጽ 25 ላይ  የብሪታንያን እጅ ለማንሳት ተሞክሯል፤ የእንግልጣርን የእጅ አዙር ተጽኖ ከማንሳት የኦባማንና የማንዴላን ምሳሌነት አለመጥቀስ በጣም ይቀል ነበር፡፡ በአጭሩ አቦይ ስብሓት ነጋ ኢህአዴግ አማራና ኦርቶዶክስ ያልሆነ መሪ በኢትዮጵያ ላይ አስቀምጧል ከሚለው የስኬት ነጋሪት ጋር ለይቼ አላየውም! ይሕ ሐሳብ ዝርዝር ካስፈለገው ለብቻው ነጥለን መነጋገር እንችላለን! የገባው ግን በግልጽ ሊገባው ይችላል፡፡
ለኢትዮጵያ መክሸፍ ኃላፊነት አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቡም እንደሆነ ጠቅሰዋል (አዳፍኔ፡ ገጽ33) ፡፡ ሌላኛው የመክሸፍ ኃላፊነትም ሴራና ተንኮል እንዲሁም የምዕራባዊያን ሐይሎች ጉልበትና ገንዘብ መሆናቸውንም ገልጸዋል (አዳፍኔ፡ ገጽ 43)፡፡ በዚህ አባባል ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን የኔ የሁልጊዜ ነጥቤ ተንኮልንና ሴራን፣ ጌታና ባርነትን ከሰው ልጅ የምድር እጣ ፈንታ ውስጥ ነጥሎ ማውጣት እንዴት ይቻላል? የሚለው ነው! የሰው ልጅ በመክሸፍ ሲዳክር የሚኖር ፍጡር መሆኑን መዘንጋት ለብንም!
ፕ/ር መስፍን ሁልጊዜም በሚጠቅሻቸው በባንዳነት፣ በታክ ምሁራን እና በገዥዎች ዱላ ከዝምተኛው ሕዝብ ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያም ሆነ በምድር ላይ የመክሸፍ ምክንያቶች መሆናቸውን አልክድም፡፡ የእነዚህ ሁሉ መነሻው ግን ሳይጠቀስ መክሸፍን በሕዝብ ማሳበብ- ገነትን ምድር ላይ በሕዝቦች ተጋድሎ ለመትከል መጣር ይመስለኛል፡፡
ግሪክ የዐለም ሥልጣኔ መስራች ከሚባሉት ውስጥ ስትጠቀስ እንሰማለን- አሁን ግሪክ ምን ላይ ነች? ግብጽ የጥንታዊነት መገለጫና የሰውልጅ ምጡቅ ሥልጣኔዎች መከሰቻ ሆኖ እያለ አሁን ምን ላይ ነች? ቱርክ የታለች? ኢትዮጵያም በክፉኛ ከእነዚህ ተርታ ተነጥላ የማትታይ አገር ነች!
ፕሮፌሰሩ ተገለጠላቸው ብዬ የማላምነው ነገር ቢኖር አንድ ሕዝብ ፍትኃዊ ሥርዓትን፣ ሠላምና ብልጽናን፣ እንዲሁም ሥልጣኔን ለማስቀጠል ምን ማድረግ አለበት የሚለው ጥያቄ ላይ፤ መክሸፉን ብቻ ለማጉላት መጣራቸው ነው፡፡ ላለመክሸፍ ትምሕርት፣ ሕገ-ኅልዮትም ሆነ ከመሣሪያ ውጭ ሆኖ ማሰብን እንደ መፍትኄ ማቅረቡ ላይ እየለፉ (እየመከሩን) መሆኑን ብገነዘብም፤ አሁንም የኔ ሐሳብ ከሰው ልጅ ሴራና ተንኮልን እንዲሁም ሕገ አራዊትነትን እንዴት ማጥፋት ይቻላል ከሚለው ላይ ነው፡፡ ሕዝብ ለክፉ አገዛዝ እሺ ብሎ መገዛት የሌለበት በምን መልኩ ነው? በኔ እድሜ ያየሁትን ለማስታወስ እንኳ ራሳቸው ፕ/ር መስፍን ይነዱት የነበረውን የ97 ምርጫን ማስታወስ ከበቂም በላይ ነው፡፡ ሕዝቡ ከመሳሪያና ከሕገ አራዊትነት ወጥቶ (ማንም ሳይነግረው) በነቂስ ሠላማዊ ተቃውሞን አሰምቶ ገዥ መደብን በምርጫ ሲየሸንፍ፤ የት ላይ ነው መክሸፉ? እኔ አለውልህ ያለው መሪ ሲነጣጠል፤ እነርሱንም ለማዳን አይሆንም ብሎ የወጣውን ወጣት በጥይት ግንባር ግንባሩን ሲለው፤ በየአደባባዩ መንታ ጣቱን ቀስሮ ሰማይ ሰማዩን የተመለከተውን ወጣት ምኑ ላይ መክሸፉ!? የቱ ላይ የሕዝብ መክሸፍ! የከሸፉትን መሪዎች! የከሸፈውስ መሳሪያን እንደቀጥተኛ ኃይሉ የተጠቀመው ክፍል! ሕዝብ አይከሽፍም! በሰው ልጅ ያለው የመክሸፍ የምድር እጣ ፈንታ ግን እስካልተወገደ ድረስ ጥቂቶቹ የመክሸፍ ጌቶች አገርን ያከሽፋሉ እንጂ ሕዝብማ አድርግ የተባለውን እያደረገ ነው!
ሌላ ምሳሌ ለመጥቀስ የ66ቱን አብዮት ማንሳት ይቻላል፡፡ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ለማንም የሚታወቅ ሆኖ፤ ተማርኩ ያለው ወጣትም ለለውጡ ተሳትፎ አድርጎ፤ መሳሪያ አንጋች ደርግ ሥልጠኑን ሲይዝ- “እምቢ!” ብሎ የተቃመው ምን ደረሰበት! ደረቱን እጅ አልባ አስመስሎ በመጫኛ ታስሮ የጥይት ዝናብ የተቀበለው ማን ነው! ይሕ ሕዝብ እንዴት ከሸፈ ይባላል!!!? ይሕ ሕዝብ ምን ያድርግ!? ይሕንን ሕዝብ አድርግ ነው የምትሉት! መሳሪያ ካነገበ ጋር ማን ይታገላል!? ዞን ዘጠኝ እና መሰል እርስዎ የሚውቋቸውን ግለሰቦች አገዛዝን በመቃወማቸው አሁን የት ይገኛሉ! ምን እየደረሰባቸው ነው?
መሳሪያን ከሰው ልጅ እጅና አዕምሮ ማስwገድ ሳይቻል መክሸፍን እንዴት መግታት ይቻላል? የፕሮፌሰር ምኞት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ እውቀትን፣ ብርሃንን፣ ሠላምን፣ ብልጽግናን፣ ሥልጣኔን በምድር ላይ ማዬት ሰፍኖ ነው! ይሕ የማንም ፍላጎት ነው- ክፉ መንፈስ በሰው ልጅ እስካልተገደበ ድረስ- ጥቂቶቹ ብክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን መምራት እስካላቆሙ ድረስ፤ ምዕራባዊየን ሴራና ተንኮል እስካልተሰበረ ድረስ ‹‹የአመጻ መንገድ›› እስካልተጠና ድረስ (ተክሉ አስኳሉ)፤ መክሸፍ ትላንት እንደነበረው፣ አሁንም እንደምናዬው መክሸፍ፣ መከሻሸፍ የሰው ልጅ እጣ ፈንታ ሆኖ ይቀጥላል!
የማይከሽው የፕሮፌሰር መክሸፍ አሁንም ይቀጥላል! ጥያቄው የሰው ልጅ መክሸፍ ምክንያት መሆን ተባባሪ ነኝ ወይስ ተጻራሪ? የሚለው ነው፡፡ ይሕች ምድር ለተጻራሪዎች አይደለችም! ለኢትዮጵያም ሆነ ለሰው ልጅ የመክሸፍ ምክንያት ተጠያቂው ሕዝብ ሳይሆን፤ በጥቂት ክሽፎች ውስጥ የተቀበረው የአራዊትነት፣ የጠበንጃ፣ የተንኮልና ሴራ መርዝ ነው! የዚሁሉ የመክሸፍ ዓለቃም ዲያቢሎስ ነው-“አዳፍኔ”!! የእርስዎ አብዮተኛም ሔዋን የመክሸፍ ሰለባ ናት!  
 መክሸፍን ከሰው ልቡና አውጥቶ፤ የክፉ መንፈስ ሴራን ከሰው አዕምሮ ደምስሶ፤ ተንኮልና መሳሪያን ከሰው እጅ ነጥቆ፤ ሰላም፣ ፍትህ፣ ሥልጣኔና ብልጽግናን ከዚህች ምድር ማስፈን ከተቻለ- ቀንደኛ ፊትአውራሪዎ ነኝ፡፡ እርስዎ ይላሉ “በጠበንጃ የጠየቀ መልሱ በጠበንጃ ነውና..” (አዳፍኔ ገጽ 51) እኔ ግን እላለሁ በሰላምም የጠየቀ ቁርሱ ጠበንጃ ራቱ ስቅላት ነው!   
የሰው ልጅ መክሸፍ እንደሚቀጥል ሁሉ፤ የሰው ልጅ መክሸፍ ተምሳሌት ኢትዮጵያ እንደመሆኗ ሁሉ፤ የክሽፈት ተጻራሪ ነኝ! ለመክሸፍ አባት ለአዳፍኔ ተቃማዊ ነኝ- ሰውም ኢትዮጵያዊ ነኝና! የሔዋንም የዲያቢሎስም ሰለባ ላለመሆን-እታገላለሁና! ትንሳኤ ናፋቂ!
ልጅዎ!


No comments: