Jul 4, 2015

“እሪያዎች” እነማን ናቸው-? ‹‹የአመጻ መንገድ›› በተክሉ አስኳሉ




 
Teklu_Askualu_YEAMETSA MENGED

“የማሕበረሰብ ባሕል በአለባበስ እና በአመጋገብ ብቻ አይታጠርም” የሚለን ተክሉ አስኳሉ፤ ቋንቋን፣ አስተሳሰብን፣ አኗኗር ዘይቤን፣ ሥነ ምግባር ደንቦችን፣ እምነት ወዘተ ትልቁን የማሕበራዊ እሴት የሚገነቡና በከፍተኛ ደረጃ ሕልውናውን የሚሸከሙ ናቸው- የአመጻ መንገድ ገጽ 33፡፡
የአንድ አገር ምጣኔ ሐብታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ምጣኔ ሃብት አጠቃቀም ከባሕል ጋር ይገናኛል በሚል ፈር ቀዳጅ ሀሳብ (ገጽ 33) ተክሉ አስኳሉ በአመጻ መንገድ መጽሐፉ ውስጥ ለአገራችን ብሎም ለዐለም ሠለጠነ ለሚባለው የማሕበረሰብ አስተሳሰብ፤ ሰይጣናዊ ብልጠትን በተጎናጸፉ ግለሰቦች ጋሻጃግሬነት ወደ ተፈለገ አንድ አቅጣጫ(እነርሱ ወደፈለጉት) እንድንመራ በመደረጉ፤ አሁን ያለው ዐለም አቀፋዊ የሰው ልጆች እጣ ፈንታ ይህንን እንዲመስል ሆኗል ይለናል፡፡
የማሕበረሰቡ ልቡሰ ጥላ፣ አሊያም የአስተሳሰብ ልኬቱ የአንድን አገር ሕልውና ድባብ ከመፍጠሩም ባሻገር፤ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ስጋና ነፍስ ከእንስሳነት አንሶም ይሁን በእኩል ደረጃ መታየቱ በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
የአንድን ማሕበረሰብ አስተሳሰብ ስሪት በባዕዳን ፍርፋሪዎች ለጉሞ፤ የማሕበረሰቡን ሕልውና በሚፈታተን መልኩ ልጓሙ እንደተፈለገ የሚዘወር ሲሆን ደግሞ የባሰ አሰቃቂ ድርት ከመሆኑም ባሻገር፤ ጥቂቶች ነጻነታቸውን ለማወጅ የእውቀት መርህን በመከተል፤ እውቀትም እውነትን ሲመዝ፤ እውነትም አርነትን ሲያስከትል፤ የእያንዳንዳችን ማንነት ፍንትው ብሎ መታዬት ይጀምራል፡፡ እንዲህ እያደረግን ግን አይደለም፡፡
እርስዎ እየተነዱት ያለው በየትኛው የማሕበረሰብ አስተሳሰብ ስሪት ነው? ታዋቂና አዋቂ በተባሉ ዝነኛ ግለሰቦች ዘንድ የተመከረና የተዘከረ ሁሉ (ሲግመንድ ፍሮይድ -ቁንጮ) እውነትን ይዟል ብለን ካሰብንና፤ በእነዚህ ዝነኛ ጸሐፊያንም ሆነ ደስኳሪያን አሊያም የጥናት ተመራማሪዎች፤ ማሕበረሰቡን ለመምራት የሚያስችላቸውን ብቃት ከየት አገኙት? መመሪያቸውስ ከኛ ማሕበረሰብ ቋንቋ፣ ሥነ-ምግባራዊ ደንቦች፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካም ሆነ የዕለት ተዕለት አኗኗር ዘይቤያችን ጋር ይስማማሉ ወይ? ይጣመራሉ ወይ? እኛን ለዘለዓለም የሚያስጨንቀን ሽንቁር ሁሉ በእነዚህ “ሰባኪያን” ዘንዳ አጽንዖት ተሰጥቶባቸው ለፈውስ የሚሆን መላምት እንደ መድኃኒት ቀምመው ይሰጡናል? ወይንስ መድኃኒቱ ፈዋሽነቱ ቀርቶ አስካሪ መጠጥ  ነው? ገዳይ መርዝ ነው ? ሲል ይሞግታል ተክሉ አስኳሉ በአመጻ መንገድ መጽሐፉ፡፡
የአመጻ መንገድ እስካሁን ካየኋቸው መጽሐፍት ለዬት የሚያደርገው ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ  እስካሁን የምናውቃቸው የሥነልቡናም ሆነ የአስተሳሰብ ድምቀት ሰጭ መጽሐት አጻጻፋቸው አንድን ግለሰብ (ማሕበረሰብ) ወደ ተፈለገ አቅጣጫ ማስፎነን ሲሆን፤ መጽሐፍቶቹ የያዙትን ጭብጥ ለውሰው ለማዋጥ የሚጠቀሙት ዘይቤ የሰው ልጅ ሁልጊዜም ሲመኝ የሚኖረውን ነጻነትን እንጎናጽፍሃለን በማለት ማለቂያ ወደሌለው ጥልቅ መስመር በመወርወር፤ ከዚህ ምላሽ ያ የተወረወረ ግለሰብ መያዥያ መጨበጫ ሲያጣ “ይሄው ሃይማኖትህ”፣ “ይሄው ፍልስፍናህ” “ይሄው ለእንክርትቱ ልቡናህ -መዳረሻ” ብለው የሚያቀርቡት መፍትኄ እኛን ወደ ነጻነት ሳይሆን ወደ ባርነት የሚከቱት ጆንያ ወጥመዶች ናቸው፡፡ ለእነዚሕም የሞሆን ማሕበረሰባችንን ተገን ያደረገ ምላሽት ትንታኔ ሲቀርብ እምብዛም አላጋጠመኝም፡፡
ተክሉ አስኳሉም በአመጻ መንገድ መጽሐፉ ወደዚሕኛው መንገድ ብቻ “ሂድ!” ከሚለው የተለመደ የሥነልቦና ጠቢባን ልምድ ወጣ በማለት፤ አሁን ያገዘፍናቸው፣ እንደ ታላቅ ፈር ቀዳጅ የእውቀትና የሥልጣኔ መምህራችን አድርገን የምንወስዳቸውን እንደነ ሲግመን ፍሮይድ ያሉ ግለሰቦች ስራዎችን በማመዛዘን፤ ይዘው የተነሱትን ጭብጥ፣ መካከል ላይ ያለውን ጥልቅ ውርዋሮሽ እና መዳረሻ እንድንፈትሽ፤ የእውቀት መስመር ዝነኞች፣ አሊያም ምዕራባዊያን በመሆናቸው ብቻ በሚዘውሩት ጉዞ ላይ ሆኖ መወዛወዝ እና መመላለስ ሳይሆን፤ ጸሐፊው ወደ የት እየሄድን ነው? ሲል በመጠየቅ በተለይ አሁን ያላደጉ አገራት ከሚባሉት ተርታ የምትሰለፈውን አፍሪቃንና የኛዋን ባተሌ አገር “እባክሽ ተመከሪ!” ሲል ያስነብበናል፡፡ ከዚህ በላይ የአዋቂ ድርሻ ምን ሊሆን ይችላል? ታዋቂዎች ስራቸው ማስተጋባትና ሰውን ወደ ጥልቁ ባሕር መወርወር ሲሆን አዋቂዎች ግን “ተመለሱ” “ጠይቁ” “መርመሩ” ይሉናል!
አሜሪካ ከ1950ዎቹ ወዲህ የማሕበረሰብ ንቅዘት እንደ ክፉ ቫይረስ ሲያሳማት፣ በማሕበረሰብ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን እንደ ፍቅር፣ ባሕል፣ ቤተሰብ፣ ሃይማኖት እና መሠል እሴቶችን በመሸርሸር፤ የሰውን ልጅ የኩነኔ ተገዥ እና ተከታይ ብሎም ተሟጋች በማድረግ፤ ከፈጣሪ ጋር ያለውን የትላንት፣ የዛሬና ዋናው መዳረሻው ወደ ሆነው ሕያውነቱ ላይ የማለያየት ተግባር እየከናወነች እንደሆነ እባካችን ልብ እንበል ይለናል ተክሉ አስኳሉ- በአርዕስቱም እንዲገልጽ (የአመጻ መንገድ)! ተክሉ አስኳሉ ከግደይ ገብረኪዳን ጋር ሌሎች ትርጉም ስራዎችም አሉት!
ታዲያ ይሕን ማን ይሰማል?

አሌክስ አብርሃም የሚባል አንድ የማሕበረሰብ ሚዲያ ጸሐፊ፤ ትውልዱን ለሽ! በሚል ረዥም እድሜ እንቅልፋ ላይ እንዳለ አድርጎ መውሰዱ፤ ጥቂት ቀስቃሾች ቢበራቱ ይህንን ድንዛዜ አይመክቱት ይሆን ብለን መጠየቃችን አይቀርም?
ቁምነገሩ እነዚህ ቀስቃሽ ግለሰቦች አብረው እንዳይደነዝዙ መበርታቱ ላይ እንጂ፤ ጥቂቶች መላውን እንደሚያደነዝዙት ሁሉ፤ ጥቂቶች መላውን ብርሃን ማልበስ ይችላሉ፡፡ ቁምነገሩ በጸሐይ ቃጠሎ ወቅት ራስን በቀዝቀዛ እርጥበት አቀዝቅዞ መገኘትና፣ ጸሐይ በጸለመችበት ጊዜ በርቶ መገኘት ነው፡፡ ጥቂቶች ራሳቸው ጸሐይ መሆንን ሳይሆን የሚመኙት፤ ከጸሐይ የተዋሰውን ብርሃን ለድቅድቅ ጭለማው እንደሚሰጡ ከዋክብት አሊያም ጨረቃ መሆን ነው፡፡ ሕያዋን ናቸው፡፡ ጤዛነትን አይመለከቱም፡፡
የጥቂት አጥፊዎች ልዩነትም እዚህ ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ ጥቂቶች አጥፊዎች መልካቸው እንደ ጸሐይ እንዲያበራ መትጋት፤ ፤ሌሎችንም እናንት አማልክት ናችሁ እንደ ጸሐይ ታበራላችሁ፤ እውቀታችሁም ሁሉ መልክ ይኖረዋል ሕያው ትሆናላችሁ የሚል የመጀመሪያውን መፈንቅለ አለቃ ከዲያቢሎስ ትምሕርት ማስተጋባት ነው፡፡ እኛም ታናናሾቹ ከጥቂት አጥፊዎች መከለል እና መንቃት የግል ድርሻ የሕይወት ተጋድሎአችን ይሆናል፡፡ ወደ የት እየሄድን ነው? ማን ነው እየማረን ያለው? በእውን በምጣኔ ሐብት አደጋችሁ ሲሉን የምድርና የሰማዩ (የሰማዩ ብቻ አላልኩም) ስኬት ተጠናቀቀ ማለት ነው? የሰው ልጅ ምድርን ሲቀላቀል፣ በምድር ላይ በተሰጡ ግዑዝና መንፈሳዊ ተፈጥሮዎች እንዳይገዛ፣ እንዳይታለል፣ የመኖርን ምስጢር በየደረጃው እየተመለከተ የኀልዮትን ሕግ እየመረመረ ወደ ተሻለ ውበት፣ ቅድስና እና ጤዛዊ ሕይወቱን (የምድሩንም) አልፎ ዘላለማዊ ርስትን ለመውረስ ይታገላል እንጂ፤ ጤዛነትን ዛሬን ዘላለማዊ አድርጎ ተመክቶ ሰማይ በቃኝ በሚል አስተምሕሮ ከግዙፉ የኑሮ ምስጢር ጋር ሊናናቅ አይገባውም፡፡ ፕሮፉሰት መስፍን ወልደ ማርያም ለታሪክ መክሸፍ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ዛሬን መለጠጥ፣ ዘላለማዊ ማድረግ ነው የሚሉንን ልብ እንበል!
አሁን ኢትዮጵያ ከነበረችበት የምድር ሥልጣኔዎች ወደኋላ ቀርታ፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ ማንም ማለፍ የሚገባውን ሁሉ አልፋ፤ ጊዜና ቦታ በሚፈቀድላት  ዛሬ ላይ ሆና የቤተሰብ ብርቱ ትስስር፣ የማንነት ብርቱ ልዕልና፣ የድንበር ግዙፍ ነጻነት እንዲሁም የፈጣሪ ኃያል መከታ ጋር ያላትን ተፈጥሮአዊ መስመር ለመስበር ታች ላይ በሚሉ አካላት መዳፍ ስር ወድቃለች፡፡
ትምሕርት ቤቶችን ስንገነባ የአስተሳሰብ ሕልውናችን በምዕራባዊያን የአስተሳሰብ ልኬት ተመዝነን፣ ይሕንን ብቻ ተቀበሉ፤ በሚል አስተምሕሮት ከመቼውም በላይ ሰርተን፣ጸልየንና ደክመን የማናገኛቸውን እሴቶች እየተነጠቅን ነው፡፡ ጸሐፊዎቻችን በዝተዋል፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን በዝተዋል- ኋላ መቅረታችንን አላበሰሩልንም፡፡ የቀደመ ሥልጣኔችንን አልመለሱልንም… ወደየት ነው የምንዘምተው?

“የሳይኮሎጂ አባት” የሚባለውን ሲግመንድ ፍሮይድ ስነቶቻችን ስራዎቹን ጠልቀን፣ መርምረን፣ ፈትሸን ከኛ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕልና ሌላው ቀርቶ ዐለም ዓቀፋዊ ምስል ከሆነው አንድ የሰው ልጅ ነባራዊ ሕልውና ጋር አካተን ምን ያክል መዝነን ፍርዱን ይዘነዋል?
ታዋቂ አርቲስቶች እንደነ ስብሃት ለዐብ ነጋ፣ በእቀቱ ስዪምም ሆነ ሌሎች በሲግመንድ ፍሮይድ አስተምሕሮት ፍስሃን ተመርኩዘው ስንቶቻችንን ነጻ አወጡን? ስንቶቻችንን የኃዘን ዳባ አለበሱን- ዳባ ሌላውን እንዳንሰማ የሚያደርግ መሆኑነ  ልብ ይሏል! ሥለዚህ እስኪ እነዚህ ታዋቂ የስነልኑና ጠበብት የሚባሉትን እንፈትሻቸው ይለናል ተክሉ አስኳሉ፡፡
ሥለ ነገረ ወሲብ፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የግለሰብ አስተሳሰብ፣ ሕልም፣ የቤተሰብ ተፈጥሮአዊ ትስስር፣ አዕምሮ፣ መንፈስ እነዚህ የሰው ልጅ የመቆመበት ማንነት ሕልውናው የተገነባበት መታወቂያዎቹ ናቸው፡፡ አሸዋ ና ጠጠር የጎደለው ኮንክሪት ወይም ውሃ ያነሰው ኮንክሪት ብሎም ስሚንቶ ያጠረው ኮንክሪት የገነባው ሕንጻ መሰነጣጠቁ፤ መዝቀጡና መፈራረሱ አይቀርም፡፡ ማሕበረሰብ ሕንጻ ነው፡፡ (በሕንጻ ምሕንድስና ትምህርት ኮንክሪት ማለት የውሃ፣ የአሸዋ፣ የስመኒንቶና የጠጠር ድብልቅ ነው)፡፡ ሕንጻቻችንም ሳይቀር እየፈራረሱብን ነው፡፡ የማሕበረሰብ መፈራረስ ምንኛ ያስከፋል?
ማሕበረሰባችንን ማን ነው እየገነባው ያለው? መሠረቱስ ምንድን ነው? ሕንጻው ሲቆም ምን ይመስላል? መሰል ጥያቄዎችንና እይታዎችን የማሕበረሰብ አጥኚዎች ስራዎችንና እኛ ላይ ሲወድቅ ምን እንደሚያስከትል ተክሉ አስኳሉ በአመጻ መንገድ ተይቦልናል፡፡
የሴቶች መብት በወሊድ፣ በስርዓተ ጾታ፣ ከተፈጥሮዊ ጋር በሚደረግ ግብግብ አሁን የዓለማችን አውታሮች ጥብቅናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የሴቶች እኩልነት ሲባል ሴትን ልጅ ራቁት ማስቀረት ነውን? ሴት ልጅ ከወንድ እኩል ናት አይነት አመለካከት ሴትን ከሰውነቷ (ሰው መሆኗ) ጋር አነጣጥሎ ሴትን ለማሕበረሰብ መጠበቂያ ማድረግ ሲገባ ማሕበረሰብ በሴት እንዲወድቅ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁመናል፡፡ አሁን ያለውን የሴቶች እኩልነት ጥበቅና ስንመለከት ልንረዳ የምንችለው ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ሴት ልጅ ርህራሄን፣ ፍቅርን ዘዴን፣ እንክብካቤን መያዟ በራሱ ትልቅ ጸጋ ነበር፡፡ እኩል እናደርጋለን የሚለው ዐለምም እንኳን እኩል ሊያደርግ፤ በፋሽን የሚሰራቸው ልብሶችና ትላልቅ ቆጥ ጫማዎች አስፈጋሪውን ፈተና ለመጋፈጥ እኩልነታቸውን አላመሳከሩም፡፡ አሁንም አሌክስ አብርሃም ሚስቴን አከሻፏት በአጭር ልብ ወለድ ውብ ጽሑፍ ላይ ዘርዝሮ አስቀምጦልናል፡፡ ተክሉ አስኳሉ ደግሞ በጥናቶችና በአጥኚዎች ላይ ተመርኩዞ!
የፌሚኒዝም፣ የስርዓተ ጾታ፣ “ጀንደር” ውርጃና ግብረሰዶም አሁን እንዲህ ደረታቸን ነፍተው፤ ሕግጋቱ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ጥብቅናው ሀሉ እነርሱ ሲሆኑ፤ ይሕ ሁደትም “አደጉ” በተባሉ አገራት ላይ ከየት ተጀምሮ እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ፤ የእነርሱን የቤት ሤራ (የቤት ሥራ አላልኩም) ጨርሰው ወደኛ እንዴት እየገቡ እንደሆነ መመመልከትና መገንዘብ ለመቻል የተክሉ አስኳሉ የአመጻ መንገድ እንዲያነቡ እመክራለሁ!
ፌሚኒዝም፣ ሄትሮሴክሹዋል፣ቅቡልነት፣ ወሲባዊ ፍንገጣ፣ የብልት ንቅለት፣ ግብራውናን፣ የሃቭሎክ ኤልስ ዕይታዎች፣የአልፈርድ ኪንሰይ አደጋዎች፣ የወሲብ ተአቅቦት እና ወዘተ በተለምዶ የማናውቃቸውን በአዳዲስ ቃላት እየዘራ በማሕበረሰብ ምህንድስና ጠበብት እየተሰራጩ ያለውን ጸረ ሰው መርዞችን ለማምከን ይጥራል መጽሐፉ፡፡  
የተክሉ አስኳሉን የአመጻ መንገድ መጽሐፍ በየአርዕስቱና በየገጹ እየጠቀስኩ ለመተቸት ሌላ መጽሐፍ የሚወጣውና ለገንዘብ ችርቻሮም ቢሆን እንኳ የሚያዋጣ ስራ ይመስለኛል፡ የአሁን ዘመን መጽሐፍት በፎንት አኳሃናቸው (style) ዘ ር ዘ ር ተደርገው፣ በአንድ ገጽ ከ15-20 እና 25 መስመሮችን ተመልተው፣ ገጽንና ብዛትን አሊያም ግልብ ሐሳብን ይዘው፣ ወደ ገበያ ሲወጡ፤ ተክሉ አስኳሉ ሶስትና አራት መጽሐፍ መሆን የሚገባውን መጽሐፍ በባለ 40 መስመር ጥቅጥቅ ያለ ጽሑፍ፤ ማሕበረሰባችንን ወዳልተፈለገ አዙሪት የሚያሰክሩ ያላቸውን መመሪያዎች እየፈተሸ “እንንቃ፣ እንመለሰ!” ተመለሱ ይለናል!  

“ተመለሱ! አትመለሱም!” የሚል ድምጽ በክርስቶስ ፊልም ውስጥ የምሰማው አንድ እረኛ አለ! እረኛው ያሳዝነኛል፡፡ “ተመለሱ!” እያለ የሚጮኸው በሰባት አጋንነንት-ሌግዮን ጭፍሮች የተለከፉ እሪያዎችን ነው! አስቡት!! ከእንስሳም እሪያ-! ከመናፍስትም ሌግዮን! እሪያዎቹ አልሰሙትም!--------
ማሕበረሰባችን ከአሳማነት (ከእሪያነት) ይመልሰን ዘንድ- መላሽ እረኛም እንሆን ዘንድ- ፈጣሪ ጸጋውን ያብዛልን፡፡ እስኪ የተክሉ አስኳሉን የአመጻ መንገድ ፈትሹ! የእረኛው ዳዊት ድምጽ ከመታየቱም ባሻር ራሳችንንም ሆነ ማሕበረሰብን ለመጠበቅ ዘቦች ያደርገን ይሆናል- እኔን እንደተሰማኝ!! የመጽፍ ቅዱሱን ጥቅስ መዝዤ ልጨርስ- የአመጻ መንገድን እንድታነቡ በማሳሰብ!
አጋንንቱም ታወጣንስ እነደሆንህ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት፣ ሂዱ አላቸው፡፡ እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎች ሄዱና ገቡ፤ እነሆም እሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባህር እየተጣደፉ ሮጡ  በውሃውም ውስጥ ሞቱ፡፡ ማቴ 8፡31-32
እሪያዎች እነማን ናቸው?

No comments: