የሕማማት መፅሐፍ አጭር የግል ምልከታ::
(ተስፋ በላይነህ)
ዲያቆን ኄኖክ "ሕማማት" የተሰኜውን ድንቅ የፍልስፍና መፅሐፍ ሲፅፍ የተሰማኝ ጉዳይ ቢኖር :- አምላክ በየትኛውም ዘመን ቢሆን ቃሉን ሊገልፁልን የሚችሉ ደቀመዝሙራትን በየትኛውም ጊዜ እንደሚዘክረን ማስመስከርያ ነው::
በበኩሌ የተሰጠኝን አዕምሮ እጠራጠረዋለሁ:: እያንዳንዷን የእግዚአብሔር ቃል በጥያቄ እና ዝርዝር ሀቲቱን አውቅ ዘንድ በምርምር ስሌት አነባለሁ:: አንኳኳለሁ ፅድቁን እሻለሁ:: ነገር ግን በስጋዊ አዕምሮዬ ጠይቄ በስጋዊው አዕምሮዬ መልሱን እንዳልመልስ ስለምፈራ የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ እማፀናለሁ:: ነገር ግን ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቅርበት የትየለሌ ክንዶችን የራቅሁኝ ርኩስ ሰው ነኝ:: በፆም በፀሎት:: በስአታት ምልጃ እና ንሥሃ እንዲሁም ለቅዱስ ቁርባን ያልበቃሁ ጭንጋፍ ስለሆንኩ የእግዚአብሔርን ቃል ራሴው ጠይቄ ራሴው እንዳልመልስ ራሴው ስለሚጠይቀኝ:: ራሴን አላምነውም::
በዚህ ማንነቴ ውስጥ ሆኜም ቢሆን የማይጥለኝ ጌታ ፥ በዚህ ድኩማንነቴ ውስጥም ሆኜም የማይተወኝ አምላክ ፥ አልፎ አልፎ ትጉሃን ሰባኪዎችን ፀሀፊ ዲያቆን ካህናትን ይሰጠኛል:: የማይተወኝ አምላክ በሄድኩበት ሁሉ ተአምር ድንቅ የማዳን ስራውን ሸሽጎብኝ አያውቅም:: የምሸሸገው እኔው ብሆንም ቅሉ:: ያቺን የቃዬል ድንጉጥ አይነት መሸሸግ::
በሚያዝያ 2011 አ.ም የሁዳዴ ፆም ለንባብ የፈቀድሁት መፅሐፍ "ሕማማት" የተሰኜውን ነው:: መፅሐፉን ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ለሕትመት እንደበቃ አንድ ወዳጄ ገዝቶት ለማንበብ ሞክሬው <<ከብዶኝ>> የተውሁት ነበር::
መንፈሳዊ መፅሐፍትን የመረዳት ዝንባሌ የራሱ የሆነ ወቅት ፥ የራሱ የሆነ ኃይል ፥ ጊዜና ቦታ ይፈልጋል:: አንድ አማኝ የመንፈሳዊ መፅሃፍትን የመረዳት አቅሙን እና ዝንባሌውን ፈቃድ ፥ ቁርኝቱን በመመልከት ብቻ ራሱን ሊመዝን ይገባዋል:: የዛሬ 15 አመት አንድ የመፅሃፍ ቅዱስ ቃል አንብቤ ምንም አይነት ትርጉምም ይሁን ፍቺ ላገኝ የምችልበት ሁኔታ ላይ አልነበርሁም::
አይደለም አንድ ምእራፍ አንድ ገፅ እንኳ አነብንቤ (አንብቤ ላለማለት) ስዘጋው የምረዳው አንዳች ነገር አልነበረም:: ልቤ ምን ያክል ደንዳና እና ለቃሉ ያን ያክል "ዝግ ዓለት" እንደነበረ ማሰብ አያዳግትም::
በጊዜው እንዲህ ነበር:: የጌታ ፈቃድ ሆኖ መፅሐፍ ቅዱስን በማንበብ ቢያንስ ለጠያቂ አዕምሮ ባለቤትነት መሰጠትን መታደል ትልቅ እድለኝነት ነው:: ደንዳና ልብን እንደመስበር የሚሰጥ እድል ፈንታ ቀላል የሚባል በረከትም አይደለም::
"እነሆ በድጅቆሜ አንኳኳከለሁ..." የሚለው ጌታ የማንኳኳቱን ድምፅ ችላ ያልነው ስንቶቻችን ነን?
የተሰበረ ልብ ፥ የተሰነጣጠቀ ልብ ልክ እንደ "ሰፍነግ" መልሶ ቆምጣጣ እና መራራ ፥ መርዛማ ምድራዊ ክህደቶችን ፥ ጥላቻ ስንፍናዎችን እንዳይሞላም የዘወትር ጥንቃቄን የሚጠይቅ ዓቢይ ጉዳይ ነው::
ልባቸው ተሰብሮ ፥ ለተጠሙ የሚያዝኑ የነበሩ ባልታወቀ የህይወት መስመር ሳቢያ እጅግ ጨካኞች ፥ እጅግ ዘማዎች ፥ እጅግ ክፉዎች ሲሆኑ ታይተዋልና ትልቅ ጥንቃቄን የሚጠይቅ የህይወት መዳረሻ ይህ መስመር ነው:: የተሰበረን ልብ መጠገኛ ወጌሻውን የመምረጥ ጉዳይ!!
በተሰነጣጠቀ ልብ ውስጥ ስጋዊ እና መንፈሳዊ ኃይላት እየተፈራረቁ መሻማታቸው አይቀርም:: የህይወት ግቡ ልብን መስበር:: የተሰበረውን ልብ በብርሃን ጫጩት አስፈልፍሎ ለብቁ ንስር ወፍ እንዲበቃ ማስቻል ነው::
አልፎ አልፎ ወቅቱ በፈቀደ መጠን የእግዚአብሔር ድጋፍ ያልተለያቸው የሃይማኖት መንፈሳዊ መሪዎች ብቅ ይላሉ:: በእርግጥ በየትኛውም ዘመን በየትኛውም ክፍለ አለም እነዚህ ስዎች አሉ:: ጉዳዩ የኛ አይን እነዚህን ሰዎች ፈልጎ የማግኜት የምርጫ እድል ፈንታን መውሰድ ትልቁ ድርሻችን ሊሆን ከተገባው ነው::
እንደኔ አይነት በጥያቄ አዕምሮ ለተሞሉ ጭንጋፎች ገለባነታችንን የሚነግሩን መንፈሳዊ መምህራን በየቦታው አሉ::
እያንዳንዷን የእምነት ነክ ታሪክ ፥ ክስተቶች እና ቅዱሳት መፃፍት ላይ የተከሰቱ ድርጊቶችን በጥልቅ ትንታኔ ፥ በድብቅ ውብ ምስጢራት ፍቺ ፥ ትርጓሜ እና ተያያዥነትን አመሳክሮ የሚመግብ ፥ ልብን ሰብሮ ብርሃናዊ ወበቅን በስንጥቁ ልሙላ የሚል ፀሐፊ ምንኛ ማለፊያ ምንኛ ባይለጠጋስ ነው?
በዚህ አገላለፅ ዲያቆን ኄኖክ ኃይሌ የክርስቶስን የሕማም ጉዞ እያንዳንዷን ክንዋኔ ምስጢር እና ፍቺ ከብሉይ ፥ ከቅዱሳን ድርሳናት እና ከአበው ትውፊታት ጋር እያዋዛ ለደንዳና ልብ ሊሆን ዘንድ የተመረጠን "ማሽያ" የታመመ "ወለምታ ልብን" ይፈውሳል::
በክርስቶስ ሕማም ወቅት የተደረጉ ታላላቅ ንግርቶችን ጥቃቅን ኩነቶችን እና ምሳሌዎችን ከመዳናችን ምስጢር ጋር እያጣበቀ ቤዛችንን በጉልህ ያቀርብልናል::
"እኔስ ትል ነኝ" የሚለውን የዳዊት መዝሙር ክርስቶን በስቅለቱ ወቅት "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?" ኦሎሄኦሎሄ ላማ ሰበቅታኒ የሚለውን ቃሉን ይዞ ፥ የልበ አምላክ የዳዊት 21ኛ መዝሙር ጋር አቆራኝቶ ፥ ለስጋ አዕምሮ የሚደንቀውን የሰው ልጅ የድኅነት ድንቅ ተአምር በ"ቪዝዋላይዥሽን" አብርቶ ያቀርብልናል::
ክርስቶስ ትል ሆኖ ፥ በአሳ የተመሰለውን ዲያቢሎስን በመስቀሉ መቃጥን ላይ ወጥመዱን አነጣጥሮ ፥ ክርስቶስ ነፍሱን ከስጋው ሊለይ ሲል ፥ ሊጨልፍ የተጠጋውን አሳ (ዲያቢሎስ) ፥ "ትል አገኜሁ" "የሰው ስጋ በላሁ" ሲል በወጥመድ መቃጥን ውስጥ የተጠመደውን ዲያቢሎስ አያያዝ ፥ ለእስር መዳረግ ተንትኖ ያቀርብልናል:: ይህ ለአዕምሮ የሚከብድን ዘመን አይሽሬ ትዕይንት ዲያቆን ኄኖክ ኃይሌ በቀላል አማርኛ ሳያንዛዛ እንደ ህፃን ወተት ይግተናል::
ከዚህ በላይ ዋጋ ከዚህ በላይ ድኅነት ከዚህ በላይ ድንቅ ምስጢር ከዚህስ በላይ አቀራረብ ከወዴት ይገኛል? ስንል አፋችንን ፥ ጭንቅላታችንን ፥ አደብ የለሽ አንደበታችንንም ልንይዝ እንገደዳለን::
ብቻ ልባችን ከዘመነኛ የክህደት ትምህርት የኑፋቄ ግኖስጣዊያን ረብ የለሽ ፍልስፍና ስር ወድቀን ፥ ሰባራ ልባችንን ክፉኛ መርዘን ፥ የዲያቢሎስ ፈረስ እንዳንሆን ወደ ፈትና እንዳንጣል ዘንድ "የሕማማቱን" ስእል ትርጉም እና ምስጢር በህይወት ዘመናችን ኹሉ እንከትበው ዘንድ ዲያቆን ኄኖክ "እነሆ!" ብሎናል::
ልብ የሕይወት መውጫ ነውና አጥብቀን እንጠብቀው ዘንድም ተነግሮናልና ፥ መውጫ መግቢያውን በጥንቃቄ እናሰምር ዘንድ የነፃ ፈቃድ አምላክ እድል ፈንታውን ችሮናልና:: ከሕማማቱ:: ከሞቱ:: ከትንሣኤው:: ከትንሣኤ በኋላ ያሉት ዕለታትንም ፥ ማዕዶት ፥ ቶማስ ፥ አልዓዛር ፥ አዳም ፥ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት አንስት ፥ ዳግማዊ ትንሣኤ:: እስከ ምፅዓት እለተሞታችን ድረስ ልንይዘው የሚገባን ትምሕርት መሆኑን የዚህ ኅፂር ፅሁፍ ፀሐፊ ምስክርነቱን ይሰጣል::
"ለልብ ጠበቃ ይሆኑልን ዘንድ የሚመላለሱ ጙቤኛዎችን(ጠባቂዎችን) አምላክ አይንሳን" እያልን:: የአገልግሎት ዘመናቸውንም ያብዛልን:: በቤቱም አያርቃቸው:: ድንቅ ተአምራትህን ያሳዩን ዘንድ የኛንምልብ ስበር የእነርሱንም ፀጋ አብዛላቸው ...:: ይሁን:: አሜን! እያልን:: እንማፀናለን::
(መፅሃፉን ተርኮ በዩቱብ ላቀረበው እዮብ ዮናስ ምስጋና ይግባው!!)
ወስብሃት ለእግዚአብሔር::
No comments:
Post a Comment