Apr 27, 2014

“የካሳ ትንሳዔ” በጥሩየ ልብስ



“የካሳ ትንሣዔ” በጥሩየ ልብስ
የጥሩ ሰው ልብስ???
*****
ከዚህ ልብስ መሐል- ስጋ ከሌለበት
አጥንት ካልቆመበት-ታሪክ ካልጻፈበት
የሚታየኝ መንፈስ- ጥሩ ሰው አለበት፡፡

 ካሳ አባ ታጠቅ ተዋቡን ሲሸኛት
በግሸን ተራራ እንደ ግማድ ቀብሯት
ሲመለስ በዚያን ወቅት ባዶነት ተሰምቶት፤
ከራሱ ከጥላው ከመኳንንት አልፎ
ከዛፉ ከምድሩ ደርሶ ተኮራርፎ
 በሰሜን በደቡብ ሲዘምትበት ቀፎ
 ባይተዋር እዳይሆን የሰው ሰው አሰኘው!
ወጣነት ባንዴ ሰው መሆን ኣማረው፡፡

ጥሩነሽን አይቶ በውበት ቁንጅና
ያባቷንም ግዞት፣ የጥሩየን እድሜ ከቶ ሳጠና
አገባት በዚያ ቀን ጥሩነሽ "ውቢቷን"
ሊያደርስ አንድነቱን ሊረሳም ተዋቡን፡፡
*****
ዑል ዓለማየሁ ካብራክ ቢገኝለት
ሩቅ ነበር ቴዲ መች ቅርቡን አየበት?
ናፒር ሲታይ ማዶ
ከሰሜን  ተዋዶ በካሳ ማግዶ
በጎጃም ተሰዶ
ሰተት ብሎ ገባ ናፒር እንግሊዙ በግብር ተላምዶ!!

ወሩ ሁዳዴ ነው- ሰሙነ ህማማት
ትንሣዔ መስሎታል በባሩድ  ሰው መሞት…

መቅደላ አሽካካች፣ እንግሊዝን ይዛ
ሲወረስ ጨፈረች ቀረች እንደዋዛ፡፡
ፈጠኑ ጌቶቹ የድርሻውን ያዙ
እጣ ተጣጣሉ፣ በቀሚስ በዘዱ ወርቁንም አበዙ

ብራናው ይከመር፣ ሽሩባውም ወዙ
ይሂድ ወደ ቤቱ ሸኙት ዕዳ ግዙ፡፡
******
ዕዳውን የገዛው ካፒቴን ስፒዲ
ባሻ ፈለቀ ነው አበሻው እንግዲ….
ጥሩየን ልዑሉን ወርቁን ይዘውታል
ለንግስት ሊያሳዩ "የጸሐይ መውጫዋን"
ጥሩየ አማጠች ዳዊቷን ሰደረች
ሞቷን አሳጠረች በዳዊት መዝሙራት ቀብሯን አሳረገች…
ባህር ሳትሻር -አገሯ ላይ ቀረች!!
 በበፍታ ቀሚስዋ ታሪክዋን ከተበች፡፡
.
.
ልዑሉም በዛበት የሙትነት መንፈስ
ደስታ የት ይገኛል በደት ሆድ ሲብስ..?
******
አሁን፡-

የጥሩየ ልብሷ ይታየኛል ፤ ባዶ መስሎ ውስጡ
የጥበቡ ማማር አወይ ጉድ ለምስጡ
ምስጥ እንደው ይበላል ስጋን ያፈራርሳል
ምስጢር መች ቀላል ነው በማንስ ይፈታል?
ያልተፈታ ምሥጢር ያለልተቀቁወዋጨ ፊደል
ያልተሳካ ታሪክ ያልተሳለ ምስል

በጥሩዬ ቀሚስ በጥሩዬ ሐብል፡፡
******
ካሳ ለምን ሞተ፣ ጥሩየስ ምን አለች?
ስደት አልቀናትም ሞቷን በዝታ ሻተች፡፡
ለምን ተቀበረ ገብርየ በወኔው ?
ታንጉት እንዴት ብላ ምስጢሯን ታካፍለው...
የነጭ እባብ ልክፍት አገሬን ሲያስታመው?

ባዶ አይታይም ዜሮም ወሰን የለው
በጨርቁ ገመድ ውስጥ መንፈስ ታሪክ አለው!!
ባዶ ነው አትበሉኝ አልቦ ታሪክ አገር
በዮሐንስ አንገት ይታየኛል ትንቢት የኑዛዜ ቀመር፡፡
መልሰህ ትከለው የኢትዮጵያን አንገት
ራዕዩ ታላቅ ይሻገራል ጉንደት…
ባዶ ነው አትበሉኝ የዚህ ጥበብ ግጥም
በባደዶ ነው አትበሉኝ የጥሩ ቀሚስ የጥሩየ ሕመም፡፡
-
ለመርዛማው እባብ ይዣለሁ ቀጥቃጩን መድህን የአለም
ካልሞቱ ካልሄዱ ካልተሰው ባለም ያ ትንሳሣኤ የለም!
***
"የካሳ ትንሣዔ" ይዘከር በዓለም...
                             ቀሚሱን እዩት  ውስጡ ማንም የለም!
Tsefa B. MiYAZiYA 6- On Tewodros's death Ann.


No comments: