Apr 28, 2014

ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!

ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!
ተስፋ በላይነህ
አንዳንድ ጊዜ /ሁልጊዜም ሊሆን ይችላል/ ታዋቂ ጸሐፊ መሆን ዕዳው በታዋቂነት ልክ ሲከፋ ይታያል፡፡ አያያዙን እና አጻጻፉን የተረዱትን ጸሐፊ ሁሉም ወገኖች አበጥረው የዩታል፤ አንደኛው ወገን እንደ ሚሳኤል ሲፈሩት ሌላኛው ወገን ደግሞ ለአብዮታቸው ፋና ነው፡፡
የዩክሬን የቀለም አብዮት ሳይቀሰቀስ ስለ ቀለም አብዮት የሚናገሩ ታዋቂ ጸሐፊያን ከቅርብ ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰውን የአረብ አብዮት በመጥቀሳቸው ወደ ዘብጥያ የወረዱትን ልንዘነጋቸው ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ አሁን አሁን የምሰማው ዜና ደግሞ እነኚህ ጸሐፊያን ጋዜጠኛ ሆነው ሳለ የጋዜጠኛነትን ሙያ በማያሟላ መልኩ እየተጠቀሙበት፣ ከሽብርተኛ ቡድናት ጋር ተለጥፈው እየነገዱ መሆኑን ተደርሶበት “ፍትህ” እንዳገኙ ሲነገረን ነገን ማሰብ የሌለበት ክህደት ነው፡፡
አብዮት /ሪቮሊዩሽን/ እምቢተኛነት፣ ዓመጽ የሚለውን ትርጉም የሚደመድም ቃል ነው፡፡ ዓብዮት እና አብዮት በእጅጉ የሚለያዩ ሐሳቦች መሆናቸውን ከአማርኛ ፊደላት አጠቃቀም ደንብ ባሻገር የሚፈጥሩትን የቃላት ትርጉም ልዩነት ሊጤን ይገባዋል፡፡ አበየ- እምቢ አለ፡፡ መታበይ- ከሚለው ስርወ ቃል ጋር የሚያስተሳስረው ፍቺ ቢኖረውም ቅሉ፤ ልክ እንደ ‹‹ነጩ ፈረስ›› ታሪክ የሚየዛምደው ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡
የነጭ ፈረሱ ታሪክ ከየት መጣ ብትሉኝም በምናባችሁ አንድ የሚያምር የደለበ ነጭ ፈረስ ተመልክታችሁ ባማረ እና በተሽቆጠቆጠ ሰረገላ ተውቦ ወደ ሰርግ ሲወስዳቸሁ አስተውላችሁ ተመለሱ፡፡
አሁንም እንደገና ልጓም አልባ የምናብ ፈረሳችሁን አስፈንጥራችሁ ያንን ነጭ ድልብ ፈረስ ተመልክታችሁ ጦር እና ጋሻ ያነገበ ወታደር በጥሩር እና ሰይፍ ተሞሽሮ ወደ ጦርን ሲጋልበው አስተውሉ፡፡ አንድ ፈረስ ለሰርግም ለጦርነትም ሲያገሰግስ ተገንዘቡ፡፡
አብዮትም እንደዛው ነው፡፡ ከአብዮት ይልቅ ትንሳኤን እናፍቃለሁ፡፡ እርግጥ አብዮት ወደ ለውጥ ይወስዳል፤ ወደ እልቂትም፡፡ ወደ ሞት ይወስዳል፤ ወደ ትንሳዔም፡፡ ጋንዲም አብዮተኛ ነው፣ ስታሊንም አብዮተኛ ነው፣ ደርግም አብዮተኛ ነው፣ ኢሕአፓም አብዮተኛ ናት፤ ሔዋንም አብዮተኛ ናት ማርያምም አብዮተኛ ናት፤ ዲያቢሎስ አብዮተኛ ነው፤ ክርስቶስም አብዮተኛ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ አብዮተኛነታችን በማን ላይ፣ በምን ላይ እና ወደ ምን እንደሚወስደን አስቀድሞ አቅጣጫውን ማስመር እና መንገዱን ማሳመር ነው፡፡ ክርስቶስ ታዋቂነቱ በድፍን እየሩሳሌም ተሰምቶ ነበር፡፤ ከዚያም አልፎ ወደ ሌሎች ቦታዎች ተሰራጭቷል፡፡ ያውም ጡመራም ሆነ ማሕበራዊ ድረ-ገጽ፣ ማስ ሚዲያ /ምሕዋረ ዜና/ ባልነበረበት 0ኛ ዘመን፡፡ ለሞት ያበቃው የታዋቂነቱ መጠን ጭምርም እንደነበር ልብ እንበል፡፡ ሆኖም ሰይፍ ሲመዙበት ሰይፍን ከለከለ እንጂ አላስተባበረም፤ ጥፊን ሲቀበል ተደገመ እንጂ አልተገዳደረም፡፡ መንገዱን፣ አቅጣጫውን፣ መዳረሻውን እና ውጤቱን በአይኑ ይመለከተው ነበር፡፡  አብዮቱን/ዓብዮቱነትንም “የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው…” በማለትም ፈጸመው፤ እንጂ 60ዎችን ለጥይት እራት አስደርጎ ፍትሕን አላዛባም፡፡ ለዚህ ነው ስኬታማ አብዮት ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው፡፡ የትላንትናው የደርግ አብዮት እንኳ ‹‹ግንቦት ሃ.ያ. ደርግ የወደቀበት›› ተብሎ በመሰየም ብሔራዊ በዓል በመሆን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እጅግ የሚወዱት ቃል እንደነበር እና ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በጣም የተጸየፉት ቃል እንደሆነ ሲናዘዙ በብዕራቸው ያስቀመጡበት ሐቅ አሁን ግልጽ ይሆንልናል፡፡
ታዋቂ አይደለሁም፡፡ ታዋቂ መሆንንም በመሻት አልጽፍም፡፡ ከዚህ በፊት ልክ እንደ አሁኑ ታዋቂ ሳልሆን በአንድ ስሙን መግለጽ በማልፈልገው ‹‹ጋዜጣ›› ስለ አብዮት ጽፌ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ምን አይነት አብዮት ያስፈልጋታል? የሚል አንድምታን የያዘ ሲሆን ከብዙ ዝርዝር በኋላ አንዳንድ ወቅታዊ ክስተቶችን በማስታወስ ምሳሌ አቅርቤ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ታክሲ ለመጠበቅ የምንይዘውን ሰልፍ ምንም አይነት ረብሻ  እና የትራፊክም ሆነ የጊዜን መሸራረፍ ሳንፈጥር በተሰለፍንበት አሰላለፍ ወደ ፊት በእርምጃ ብንሄድ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከእንቅልፉ ሲነቃ በህግ ህሊናው ያሳትምበት ነበር፡፡ /ሕሊና መች አለው እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ!!/
የስጋ ውድነት እንዲህ በአፍሪካ በቀንድ ከብት 1ኛ ከምትባል አገር ሲጫወትብን ስጋ ገዝቶ አለመብላት የሚለውን አብዮት ብንጠቀም ለጥቂት ጊዜያት ከመጮህ የማያቋርጠውን ወስፋታችን ታግሰን ለዘላቂው እኛነታችን እና ክብራችን፣ሃይላችን እንዲሁም ጥያቄዎቻችን ምላሽ መስጠት የምንችልበት ዘዴ መሆኑን ለመግለጽ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ታዋቂ ስላልሆንኩ አዋቂው መንግስትም ሆን አዋቂው ህዝብ አላወቀብኝም፡፤ “ተመስገን!” ብታወቅ እና ቢታወቅብኝ ኖሮ አሁን ደግሜ ባልጻፍኩትም ነበር፡፡ ብታወቅ ኖሮማ አሁን የት እንደምገኝ እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ከተለያዩ ቦታዎች ያሉ አዋቂዎቼ/ እኔን በግል ዝምድና እና ወዳጅነት የሚያውቁም/ ሰዎች “እባክህ የምትጽፈውን ነገር አቁም!” የሚል ግልጽ ኢ-ህገመንግስታዊ ምክራቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ትንሳኤ ናፋቂ መሆኔን የተረዱት በየቀኑ የምጽፈውን ጽሑፍ ካነበቡ እና ከተረዱ በኋላ ነው-ዝምታቸውን ለግሰው ዛሬስ ምን ጻፍክ በማለት የሚጠይቁኝ፡፡ መጻፍ እንዲህ ቀላል ነገር እንዳለሆነ ደግሞ ቢረዱት የተሸለ ነበር፡፡
በህገ-መንግስቴ አንቀጽ 29 መሰረት ተጠቃሚ መሆኔን ካለመረዳታቸውም ባሻገር ከፈጣሪ የተቸረኝ ምዕራፍ እና ቁጥር/አንቀጽ/ ሊጠቀስ የማያስፈልገው ጸጋ መሆኑን ልብ አላሉትም፡፡ ልብ የት አለና!? “ልብማ ቢኖራት..?” እንዳለችው ውሻ ተገላቢጦሽ እንደይተረክብን ‹‹ልብ እንላለን!››፡፡ ልብማ ቢኖረን የሚለው ለኔ ለጸሐፊው ነው? ወይንስ ለተናጋሪዎቹ? ልብ ቢኖራቸውማ ይህንን አይናገሩኝም ብዬ ነው ማሰብ እና ማሳሰብ ያለብኝ፡፡ እነርሱም በመጻፌ ልብ የለውም እያሉ ተርተውብኛል፡፡ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ… አልታበይም!!
የተገላቢጦሽ ምድር ውስጥ እንዳለን ግን ልብ ይሏል!! 
የዩክሬን የቀለም አብዮት ወደኛ “አብዮተተስፋ” ምድራችን ሲነዘነዝብን ሰነባብተናል፡፡ ራሺያና ዩክሬን ከሚነዛነዙት በላይ ወደኛ ምድር በቀለም አብዮት የሚነዛነዙት አይለዋል፡፡ ታብየዋል፡፡ በቅድሚያ የዩክሬኑን የቀለም አብዮት ለመዘገብ የበቃው መንግስት? ወይንስ የቀለም አብዮት ናፋቂ ወገን?  ይህንን ለመመለስ ደግሞ የኢትዮጵያ አብዮት የተቀለበሰው በደርግ እና በኢሕአፓ ንዝንዝ ሆኖ ማን የመጀመሪያዋን የጥይት ድምጽ አሰማ ወደሚለው 40 ዓመት ያልተፈታ ጥያቄ ይከተናል፡፡ መንግስትም ሆነ ሌላኛው አንጃ የቀለም አብዮት ብሎ መነዝነዙ ለእኛ “ቱርካዊያኖች” የሚያመላክተው መንግስት የቀለም አብዮትን አጥብቆ እንደሚፈራ እና እንደሚጠባበቅ ሲሆን ሌላኛው “ኢሕአፓ” ደግሞ አብዮት እንደናፈቀ የሚያሳብቅ የልጅነት ጨዋታ ይመስላል፡፡ የልጅነት ጨዋታ ደግሞ አጀማመሩ እንዲያ እንዳልተሽሞነሞነ ሲቆይ ግን አቅጣጫው እና አጨራረሱ እቃቃ ፍርስርስ ዳቦው ቁርስርስ እይነት ‹‹ወግ›› ‹‹ልማድ›› ቢቻል አመል እና ሱስ ብለው ያስደስተኛል፡፡
ኢትዮጵያ አብዮት ያስፈልጋታል? ኢትዮጵያ አብዮት በዓብዮት ያስፈልጋታል፡፡ ነገርግን ከምንጊዜውም በአለም ታይቶ የማይታወቅ አብዮት ከማስፈለጉም በሻገር የሚደርሰውን የእቃቃ ፍርስርስ ልማድ በከፍተኛ ሁኔታ ከማጦዙም በላይ ዳግመኛ የማትመለስበት መደናበር ውስጥ እንደምትዘፈቅ ለመገመት ነብይ በድንግል ማሕጸን ውስጥ ገብቶ ተጸንሶ ተወልዶ እስኪነግረን መጠበቅ የለብንም፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዮት እየሸተተን ከሆነ አብዮቱ የሚያስከትለውን መፈራረስ አስቀድመን ልናሸተው ይገባናል፡፡ ይህን ስል ‹‹ፈሪ›› የሚሉኝ አዋቂዎቼ ብቻ ሳይሆኑ አብዮትን በከፍተኛ ደረጃ እያሸተቱ የሚገኙ ወገኖቼም ጭምር ናቸው፡፡ ሲጀመር አብዮት ያስፈልገኛል ብሎ የሚያስበው ህዝብ በእጅጉን ከማያስበው አንሶ በመገኘቱ፣ የአብዮትን ፋይዳ፣ አስፈላጊነት፣ አካኄድ፣ መንገድ እና መዳረሻ የማይረዳው ሕዝብ የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ አያበቃም አብዮት ያስፈልጋል  ብለው ከሚሟገቱት ወገኖቼ ውስጥም ባልታወቅ እና በታወቅ ምክንያት አብዮቱን ለግል ጥቅም ማዋላቸውን እንደሚጎዳኙት ልብ ልንል ይገባናል፡፡ አብዮት ማስፈለጉን በየማያውቁት ወገኖች መበራከት፣ እያወቁትም ለዝርፊያ፣ለእልቂት፣ “እኔ በነበርኩበት ዘመን ሰላም ነበር አሁን ግን አብዮት አብዮት ብላችሁ በጠበጣችሁን” እስከማለት  የሚሞክሩትን በመቁጠር ከዛም ባሻገር “ከመንግስት” ጎን ሆነውም ቤንዚን እና ክብሪት በነጻ የሚያድሉትን ወገኖች አጥብቀን ልንገነዘባቸው የሚገቡን ናቸው፡፡ በሶስቱ መሪ ምክንያች ኢትዮጵያ አብዮት ሊዘገይባት፣ ሊብላላላት እና ሊመከርባት እንደሚገባ እንረዳለን፡፡ አሁንም አብዮት ናፋቂዎች ሁለቱ ወገኖች በተለይ አንደኛው ይህንን ድምዳሜ እንደ ካድሬነት አሊያም ፈሪነት አድርጎ ሲፈርጀው ገላጋይ የለውም፡፡ ትዕግስት ፍርሃት አይደለም! ክፉን በመልካም መመለስ ፍርሃት አይደለም… ወ.ዘ.ተ!
እስካሁን የተከሰቱት አብዮቶች እና አብዮተኞች ዋነኛ መገለጫቸው መነሻ /መካሪያቸው/ እና መዳረሻ/ ግባቸው/ ተለክቶ ነው፡፡ የኄዋን አብዮተኛነት ከዲያቢሎስ ምክር የተገኘ ነው፡፡ የዲያቢሎስ አብዮተኛነት ከእኔነት መታበይ የመጣ የክፉ የአብዮተኛነት አነሳስ ነው፡፡ የጋንዲ አብዮተኛነት የነ ማኦ፣ የነ ቼጉቬራ ፣የስታሊን የመንግሰቱ ኃ/ማርያም አብዮት እና አብዮተኛነት እዲሁም መሰል አብዮቶች በጥቂቱም እንኳ መነሻ ቢኖራቸውም መዳረሻቸው ግን ታሪክ ፍርዱን አስቀምጦ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ ከሳጥናኤል እስከ ዩክሬን የቀለም አብዮት ድረስ የተደረደሩት አብዮቶች እና ብቅ ጥልም ያሉት አብዮተኞች በጥቅሉ ሌላ አብዮት እንድናፍቅ አሊያም በክፉ ዳርቻ አብዮትን እንድንጠላ ያደረጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሃል በዘመናት መካከል የተደረገው አብዮተኝነት በትንሳኤ ተቀይሮ ግቡን ያሳካው እርሱ መሲህ ሆነው ክርስቶስ እሱን ብቻ ነው!!
ውድ ሙስሊም እህትና ወንድሞቼ እየደረጉት ያለውን ሳምታዊ ሶላት ጠገግ አብዮት አጀማመሩን ብናስታውሰውም/በጭጋግ ብንመለከተውም-ችግራችንም ሆኖ ስለማንጠይቅ…./ አጨራረሱን አልደረስንበትም፤ ሆኖም ከሚዘከርለት ውስጥ አንዱ እየሆነ መሄዱን ለመመስከር እንደምንታደል ፈጣሪ ይርዳን፡፡ ምናልባት ስብከት ባይሆንብኝ እና በቀናነት ቢታይልኝ ትንሳኤ የምትለዋን ቃል በፍልስፍና ደረጃ እንኳ ለመጤን ብትሞከር በእጅጉ ስኬታማ የምንሆንበት ብርሃን የሚበራ ይመስለኛል፡፡ ከእኔ ሃሳብ በቀር በሚል ማነቆ አልገዳደርም፡፡ ለእኔ ግን “በእኔ በቀር ወደ እርሱ የሚመጣ የለም፣ እኔ መንገድ እውነት ትንሳኤም ነኝ” ሚለው መፈክሬ መነሻዬ እና መዳረሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአብዮት በፊት ትንሳኤ አጥብቆ ያስፈልጋታል!! የትንሳኤው ጉዞ ክፉን በክፉ አትመልሱ፣ ግራ ጉንጭህን የመታህን ቀኝህን ደግሞ ስጠው አና መሰል አንቀጾችን የያዘ ሲሆን መዳረሻውም የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!! የሚል ነው፡፡ ግቡም ትንሳኤ/ እንደገና መወለድ፣መታደስ ዘር ፍሬ ሆኖ ማፍራት-ማበብ ነው፡፡ ከዓመት በላይ ታሽጎ የኖረ የስንዴ ዘር እንደምን ተዘርቶ ሊበቅል ቻለ? የትንሳዔ ምስጢር የገባው ብቻ የሚመልሰው ነው፡፡ ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!  
ዓመታትን ቆይቶ ለዘርነት የሚበቃው ስንዴ የተመረጠው ከንጹህ ዘር ተለይቶ እንክርዳድ እንዳይኖረው ተበጥሮ ነው፡፡ ተበጥሮም በጥንቃቄ ተይዞ ነው፡፡ ነቀዝ እንዳያፈራ ተጠብቆ ነው፡፡ እንክርዳድ እና ነቀዝ ለመጪው ዘር/ትውልድ/ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው፡፡ እንክርዳዱ ቂም ነው፡፡ ጥላቻ ነው፡፡ ጎሰኝነት፣ እብሪት፣ ጠባብነት እና መሰል እርግማኖች ናቸው፡፡ ነቀዙ ደግሞ ያው የውጭ ሃይላት ናቸው፡፡ አብዮት ለእነርሱ መርዛማ እጅ ዋነኛ የጅብ መስኮት ነው፡፡ ጅብ በቀደደው የሚገቡት ውሾች ደግሞ ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ እንክርዳድ እና ከነቀዝ የጸዳ ስንዴ/ አብዮት/ ወደ ትንሳዔነት ለመሸጋገር የበቃ ይሆናል፡፡ የሚከተለውም ንጹህ ዘር የሚያብብ የሚያምር አዝመራ ነው፡፡ ትንሳዔ አለው፡፡ ለዚህ ነው ከአብዮት በፊት ትንሳዔን ከአብዮት በኋላም ትንሳዔን የምንሰብከው፡፡ ከአብዮት በፊት ትንሳዔ- ለኢትዮጵያ!! 












                      

No comments: