“ማንዴላ”
ነጻነት ነው የወጣኸው?
ነጻነት ነው የወጣችው?
ለነጻነት ነው ለነጻነታችሁ?
ለግል ማንነትህ ወይስ ላ’ገራችሁ…?
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ…?!
`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ? የውነት ነጻ ሰው ነህ?`
ነጻም ነኝ ካልክ ማን አሳዶ ማን መለሰህ?
ማንስ አስሮ ማን አስፈታህ? ማን አቁስሎ ማን ጠገነህ?
‹‹ኖቤል›› ማን ሸለመህ? ነጻነት ማን ነሳህ?
`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ…
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ?`
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ?
`ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ?`
*****
ነጻ ነኝ ካልክ በማን በሬ ነው
የማን ሰርዶ የሚጋጠው?
ማንስ ጫንቃ ላይ ነው ነጫጭ ውሻ የታሰረው?
እኮ እንዴት?
እድሜን አስረጅቶ ደረስኩልህ ማለት¡
ነጻነትን ነፍጎ ‹‹ኖቤል›› ሸላሚነት
እኮ እንዴት….?
ይልቅስ ልንገርህ ተረት ነው ነጻነት
ደሮን ሲደልሏት በመጫኛ ጣሏት!
አርዝመው ቢያስሯት የፈቷት መሰላት..
ለዚህም ሁሉ ነጻነትን ነፍጎ ለነጻነት ታጋይ ‹‹የኖቤል›› ሽልማት
ማታለል ይመስላል ምጸት እና ኩሸት…!
ስድስት ወራት በከለለህ
ባገሬ አፈር ልጠይቅህ
እውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ…?
ያገርህ ላይ ጥቁሮች ዛሬን ይጠግባሉ?
ባገራቸው መሬት እነርሱ ያርሳሉ?
ወይስ የነጭን ዘር ቃርሚያ ይለቅማሉ?
“ስድስት ወራት በከለለህ
በመንደርህ በኩልፌ አፈር ልጠይቅህ
አውነት ነው ማንዴላ የውነት ነጻ ሰው ነህ….?”
በኤፍሬም
ስዩም ተሰማ
‹‹ሙዚ-ቃል››
የግጥም ሸክላ
No comments:
Post a Comment