Jul 29, 2014

ቁልቢ



ቁልቢ


ከአራቱም መዓዘናት የሚመጡ ሰዎችን የምታስተናግደው ቁልቢ  ለድሬዳዋመ ሆነ ለሐረር ቅርብ ስትሆን፤ በዓመት ውስጥ በተለይ ታህሳስ እና ሐምሌ ወር ላይ ከፍተኛ የሆነ ምዕመንን ታስተናግዳለች፡፡
የቁልቢ ገብርኤል ሲባል ሁላችንም እንሰማለን፡፡ ታሪኩን በአጭሩ ለመጥቀስ ስንሞክር፡-
 በዮዲት ዘመን ከአክሱም ጽዮን ጽላተ ሙሴ ጋር በደባልነት ይኖር የነበረውን የቅዱስ ገብርኤልን ጽላት እና ንዋዬ ቅዱሳቱን ይዘው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ጉዙ ቀጥለው፤ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በዝዋይ ሀይቅ ውስጥ ደብረ ጽዮን ማርያም ተብላ ከምትጠራ ደሴት እንደተቀመጡ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
በዚያን ጊዜ የ5 ዓመት ንጉስ እንደነበር የሚነገረው አንደሳ ውዱም፤ ዮዲት ከ40 ዓመታት በኋላ ከዙፋን ስትወርድ በሸዋ ተሸሽጎ የነበረው አንበሳ ውዱም ተመልሶ አክሱም ላይ ነገሰ፡፡
በዚህም ጊዜ በዮዲት የተቃጠለውን የአክሱም ጽዮን ቤተክርስትያን አሳድሶ ጽላቱን ሲያኖር የቅዱስ ገብርኤል ጽላት (ታቦት) እንዳልተመለሰ ተነገረው፡፡
ይሕም ለምን ሆነ ሲባል ካህናቱ ከሁሉም ንዋዬ ቅዱሳት እና ታቦተ ጽዮን(ጽላተ ሙሴን) ጨምረው ለመውሰድ ሲሞክሩ የቅዱስ ገብርኤል ታቦት ግን ለመነሳት ‹‹እምቢ አለ››፡፡
ንጉሱም አዘኑ፡፡ በዚህ ወቅት ኤርትራ ውስጥ ከሚገኝ አባ አጽቀ ሌዊ የተባሉ ባህታዊ መጥተው ታቦቱን እንዲያመጡት ፈቃድ ጠየቁ፡፡
በማህተም የተደገፈ የይለፍ ደብዳቤ እና ስንቅ ይዘው ዝዋይ ደብረ ጽዮን ማርያም ደረሱ፡፡ /እንግዲህ ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመት በላይ ኤርትራ፣ ደቡቡ የኢትዮያ ክፍል ይገናኙ እንደነበር ማሰብም ያስደስታል/
እቦታው ደርሰው ታቦቱንም ይዘው ሲወጡ አንድ ሰው ከፊት ቆሞ “ወዴት ትሄዳለህ?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ወደ ሰሜን እንደሆነ መለሱላቸው፡፡ ወደ ሰሜን መሄድ እንደሌለበት እና ወደ ምስራቅ መሄድ እንዳለበት ይነገራቸዋል፡፡
የንጉስ ትዕዛዝ እንደሆነና ወደ ምስራቅ መሄድ እንደማይችሉ ነገር ግን ወደ ሰሜን መሄድ እንዳለባቸው ተናገሩ፡፡ በዚህ ክርክር መሃል ተናጋሪው ሰው ወደ ብርሃን ተለወጠ፤ ተናጋሪውም የጽላቱ ባለቤት ገብርኤል መሆኑ ተነገራቸው፡፡ ተከተለኝ በሚል ትዕዛዝ ጉዟውን ቀጠሉ…፡፡
አባ አፅቀ ሌዊም በመልዐኩ ቅዱስ ገብርኤል ተመሪነት ወደ ተቀደስ ተራራ ታህሳስ 19 ቀን ሀረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደደረሱ ተዓምሩ ላይ ተጠቅሷል፡
ባህታዊውም ቃልኪዳኑን ከመልዐኩ ተቀብለው በጾም በጸሎት ከኖሩ በኋላ ታሪኩን በድንጋይ ላይ ጽፈው በማኖር፤ ስውር ሆኖ እንዲኖር በማድረግ  ህልፈተ ሕይታቸውን ተቀበሉ፡፡
ከዚህም በኋላ ለብዙ ዓመታት ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምስራቅ 150 ኪ.ሜ በቡልጋ አምባ በአጋዥጌ ካህናተ ሰማይ ቤተክርስትያን ውስጥ በደባልነት ይኖር ነበር፡፡
አጼ ምኒልክ በ1882 ሀረርን ሲጠቀልሉ ራስ መኮንን ከሾሙ በኋላ፤ ራስ መኮንን ሀረርን መናገሻ ቢያደርጉም ቁልቢንም በነበራት የቅዝቃዜ አየር ጠባይ እንደ ሁለተኛ ከተማቸው እንደመረጡ ይነገራል፡፡
ራስ መኮንንም ይሕንን ቦታ ከባህታዊያን ጋር በመነጋገር የነበረውን ታሪክ በመረዳት ታቦቱ መጥቶ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ቦታውንም መጠነኛ መጠለያ በማዘጋጀት ካስቀመጡ በኋላ ስዕለት እንደተሳሉም የሚነገር ሲሆን፤ አካባቢን ሰላም ካደረክልኝ ህንጻ እንደሚያሰሩ ተሳሉ፤ …ይሕም ሆነ፡፡
አድዋ ሲዘምቱ እዚህ ቤተ-ክርስትያን ጸልየው፣ ቆርበው እና ተስለው እንደሄዱም ይነገራል፡፡ በብዛት እንደ አሁኑ ሰው የማይጎበኘው የበነረበት ወቅት እንዳለ ቢታወቅም፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ በ1954 ዓ.ምህረት የህንጻው መሰረት ድንጋይ አኖረው፤ በ1957 ዓ.ምህረት ታኅሣሥ 19 ቀን ተመረቀ፡፡/ በ423 ሺህ ብር እነደሆነም ተጠቅሷል/፡፡.. አጠቃላይ ታሪኩን ለማግኘት መዛግብትን ማጋላበጥ እንሚያስፈልግ እየጠቀስኩ መ/ር ኃይለ መስቀል ፋንታሁን ያዘጋጀውን ባለ 40 ገጽ ጥራዝ ለዚህ ጽሑፍ ዋቢ አድርጌ የተጠቀምኩ መሆኑንም በማጣቀስ ለአዘጋጁ ላቅ ያለ ምስጋዬን አቀርባለሁ፡፡

በቁልቢ ገብርኤል ምን እንታዘባለን…?
ህንጻ ቤተክርስትያኑ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር መተዳደሪያ ደንቡንም አብሮ መመልከት ይቻላል፡፡ ከክርስትና ትምህርት መስፋፋት ጥቅም ባሻገር ሌሎች እሴቶችን ይዞ እንደተመሰረተም መመልከት ይቻላል፡፡
በመኪና ፓርክ በኩል ከፍተኛ የሆነ ምስቅልቅል/ ብዛት ስላለበት/ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የሆነ አሰራር እንደሚያስፈልግ ለመገንዘብ ይቻላል/
አካባቢውን ማደራጀት፣ ከተማዋን ማሳደግ እና በተለይ ከከተማዋ ወደ ደብሩ የሚወስደውን መንገድ ‹‹በአስፓልት›› አሊያም ‹‹በኮልብ ስቶን›› ማልበስ ግድ የሚባልበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ይሕም ደብሩ ከሚየገኘው የስዕለት ገቢ እና በየጊዜው የሚሄደውን ምዕመን ለዚህ አገልግሎት የሚል የገንዘብ ማሰባሰብ መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ማሳካት የሚቻል ሲሆን፤ መንግስትም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡
ከከተማዋ እስከ ደብሩ ያለው ስፍራ የረብሻ እና የምስቅልቅል ሂደት እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ቤተክርስትያናችን የንግድ መገበያያ መንገድ አድርጎ መውሰድ እና ይሕንንም ስርዓት ማስቀጠል የክርስቶስን ጅራፍ መቀበል ነው፡፡ ‹‹የሞንታርቦች›› እና የረብሻ ድምጽ የአርምሞ እና የጸጥታ እንዲሁም የመረጋጋት መንፈስን አይፈጥርም፡፡ / ደብሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ስንገባ ግን የተሻለ መረጋጋት እና ጸሎት ለማድረስ ሚያስችል ድባብ ነበረው፡፡
የስርቆት ነገር አያድርስ ነው፡፡ የቦታውን ኃያልነት እና ቅዱስነት በከፍተኛ ሁኔታ ያሳጣዋል፡፡ ለስርቆት ብቻ የሚመጡ አረመኔዎች እንዳሉም ይነገራል፡፡ / ስራውን አምላክ ካላገዘን ቀላል ነገር አይደለም/ ፖሊሶች ጳጳሱን ከሚጠብቁበት ጥንካሬ አንጻር ለምዕመኑም በተመጣጣኝ ሁኔታ ሊያስቡበትት ይገባል፡፡
መብላት፣ መጠጣት፣ መስከር ከኃይማኖት ስርዓት አንጻር የማይዛመዱ ናቸው፡፡ ቤተክርትያን በየሓይማኖት ስርዓቶች ይሕንን አይነት ነገር በማስተዋል በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠበቀው በላይ እየተስፋፋ በመሄዱ ማውገዝ አለባት፡፡ ነጋዴው ይሕንን ነገር ባይፈልግም ቦታው ላይ አልኮል መጠጦችን እና ከሐይማኖት ስርዓት ውጭ የሆነውን ነገር ሁሉ መቆጣጠር መቻል አለብን፡፡  የቢራ ፋብሪካ ማስታወቂያዎች “እንኳን ለቁልቢ ገብርኤል በዓል አደረስዎ” ብለው ሰፋፊ መጋረጃዎችቸን ሰቅለው ተመልክተናል፡፡ ….እኛንም ጋርደውብናል፡፡
ሐይማኖታችንን መጠበቅ ያለብን እኛ ነን፡፡ ይሕን ነገር ልንቃወም ይገባል፡፡ እርግጥ  ደብሩ ቅጥር ግቢ በተቃረብን ቁጥር እና ቅጥር ግቢው ውስጥ ይህ አይነት ችግር አለ ባንልም…አነስተኛዋን የቁልቢ ከተማ መቆጣጠር እና በተለይ በዓሉን በምናከብርበት ጊዜ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ ተጠብቆ በረከቱን ተካፍለን ብንመለስ አማራጭ የማይቀርብለት መንገድ ነው፡፡
ይሕ ሁሉ ህዝብ ምን ይሳላል…?
መቼስ ስዕለት በልብ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚነገር የሕይት ፍላጎት ነው፡፡ ጣልቃ አንገባም፡፡ ሁሉም ሰው ግን ለራሱ ብቻ ስዕለቱን ተናግሮ፤ ከሚመለስ በሕብረት ብንጸልይ እና በአገራችን ስርዓት ያለበትን፣ እውቀት የሚስፋፋበትን መረዳዳት የሚስተዋልበትን የማስተዋልና እና የጥበብን ስብዕና እንዲያላብሰን ብንመኝ ሊሻል እንደሚችል በግሌ ሃሳቤን እሰነዝራለሁ፡፡  ሰላም ያገናኘን!! ታኅሳስ 19/ 2006 ሀረር

No comments: