May 12, 2014

‹‹ዝናቡም አካፍቷል!›› ቀስተደመናው የታል?

‹‹ዝናቡም አካፍቷል!›› ቀስተደመናው የታል?

ህጻን ሳለሁ ገና- ልጅ
ዝናብ ማለት ለኔ- ጠጅ!
የግዜር ፌሽታ አምሃ ውጋጅ
በደስታ ብዛት ከብጫነት-ወደ ነጭነት ተውላጠ ጽዳጅ!!
በዛ ጽዳጅ ቀን ታጥቤ
ጽዱ ልቤን አራጥቤ
እኔና’ንቺ በጭቃ ውስጥ ስንታጠብ
ድነን ነበር ካ’ለም መቅሰፍት-ከምድር ጠብ!
የበረዶው ጥል ክብ ልማድ-ራሴን እየኮረኮመኝ
ከተፈጥሮ አጣመረኝ…
ካጉራ ዘለል ካጉል ትነት ልጓም ያዘኝ!
ኢትዮያዊ ነኝ!!
በዛን ወቅት ሰንደቅ አላማውን ስንመለከተው
አያይዞን ለልባችን ተስፋ ሰጠው…
ከአጽናፍ አጽናፍ ወንዝ አሻጋሪ  ቃል የሠጠው
በደመናው ቀስቱን ዝርግቶ የኢትዮጵያ መቀነት የተዘረጋው
ለልብ ውስጥ የታተመው አንድነት-ሶስት ቀለም- አረንጓዴ- ቢጫ ቀይ ነው!!
አሁን ታዲያ በዝናብ ውስጥ የሚታየው
በብረት ታስሮ የታሰረው ይህ ሰንደቅ አላማ ነው??
ሰባት ነው ይሉናል የቀስተደመና ስብጥሩ
ይሉናል!! ከሰባትም በላይ ናቸው በተናጠል ሲቆጠሩ!!
ለእንያንዳንዱም አገር ሰጡት በክፍፍል መዋቅሩ፡፡
ሳቅንባቸው ባይገባቸው  የብዙው ባንድ መጣመሩ
ሳይገባቸው በሶስት ገመድ የአንድነት ሃይል ስሩ--ምስጢሩ!!
አሁን፡-
በዝናብ ውስጥ ቀስተ ደመናው የለም
የተዋበው ህያው አርማ በዝናቡ አይታይም
‹‹ጨርቁ›› ይታየኛል በዝናቡ መጽዳት ናፍቆት
አጎንብሶ በዶፍ ሲወርድ የጉድፍ ቋት…
ነው ወይንስ በዘመን ሰንኮፍ እድገቴ ሸፍኖት??
አልገባኝም!!
ቀስተደመናው ርቋል በክፍልፍል ተሸንሽኗል
በሳይንሱ መዳፍ ታሽቶ ከተፈጥሮ ተቆራርጧል
ልጅነት ተረስቷል፣ አገር ተሸጧል  ‹‹ዝናቡም አካፍቷል!››
ቀስተ ደመናው ግን የታል…?
ተስፋ በላይነህ

**ይህ ግጥም  በግንቦት 20 1983ተጸነሰ-  ግንቦት 20 2003-ተወለደ

No comments: