May 12, 2014

በአውሎ ነፋስ ውስጥ ያለች የፍቅር ብርሃን


በአውሎ ነፋስ ውስጥ ያለች የፍቅር ብርሃን
ተስፋ በላይነህ
በኒውዮርክ የህንጻ ጫካ ውስጥ በስልጣኔ ጥማት ሲሰቃይ የነበረው ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን፤ በድምቀት ከተማ ውስጥ መንደሩ የጨለመበት፤ አገሩ የጸለመችበት ምክንያት ምንድን ነው? ፈራን ፍቅርን ፈራን በሚል የተየበው ቅኔ  ለአስርት አመታት በመቃተት እንዴት አብሮ ተቀበረ?

ወደ እግዚአብሔር የቀረብሽበት መጠን እና ወደ እግዚአብሔር የቀረብኩበት ዘመን ፍቅራችንን እንደሚወስነው በተደጋጋሚ ነግሬሻለሁ፡፡ ወደ እግዚአብሔር የቀረብኩበት ዘመን/መጠን ወደ አንቺ እንደሚያቀርበኝ እና ከአንቺ ጋር የሚያኖረኝን ዘመን እንደሚወስነውም ጭር፡፡ ነግሬሻለሁ፡፡ ነገርግ ግን አልገባሽም! ነገር ግን አልገባኝም! ወደ እግዚአብሔር የሚያርበኝ ዘመን የእኔ እና ያንቺን የመኖር ዘመን እንሚወክለው፤ ያንቺ ወደ እግዚአብሔር የቀረብሽበት መጠን የእኔ እና ያንቺን የአብሮነት ርቀት እንደሚለካው አይተን ለምን እንደሆነ አልገባንም፡፡

በልቤ ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለሽ እና መኖርም እንደሌለበት ነግሬሻለሁ፡፡ አንቺም ፍቅር ልብን መስጠት እንዳልሆነ የነገርሽን ቃልሽ እንዳልቀና አድርጎኝ ፍቅር አይቀናም የሚለውን ጥልቅ የፍቅር ትርጓሜ እንድረዳ መሳሪያ ሆኖኛል፡፡ ከንቱነት በፍቅር ዝቅጠት መጠን ይለካል፡፡ የመላዕክትን ልሳን፤ ራስን አሳልፎ እስከመስጠት የሚያደርስ መስዋዕትነት፤ ተራሮችን ማፍለስ ድረስ እስከ ሚችል እምነት ብንለገስ ፍቅር ግን ከሌለን የከንቱነታችን ሚዛን ይደፋል፡፡ ከንቱነት ሚዛኑን ደፍቶብናል፡፡ ከእግዚአብሔር ስንርቅ በዛው ልክ ከአብሮነታችን እንርቃለን፡፡ አናፈቅርም፤ ልብ እስከሚፈውስ ድረስ የሚያስተፈህስ ልሳን በጆሮዋ እያንቆረቆርን ፍቅር ግን ስለሌለን ከንቱነታችን ደፍቶብናል፡፡ የአለም ሴቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ጠፍተው እኔ ብቻ ወንድ ሆኘ አብሬያቸው ተጉዤ ምድር በወንዶች ተሞልታ እንኳ አንቺ ከኔ በቀር ሌላ ወንድ እንደማትቀርቢ በእኔ እንደምትቆርቢ እያመንኩሽ ፍቅር ግን ስለተለየን የከንቱነችን ሚዛን በወንዶች ቁጥር እና ባንቺ ብቻሽን ሚዛን ታች ተቀምጦ ከንቱነታችን በወንዶች ቁጥር ልክ ተለካ፡፡ ከንቱነታችን ዘቀጠ፡፡ መዘነ፡፡ ፍቅር ተማጸነ፡፡

ፍቅር ተማጸነ፡፡‹‹ በፍጹም ልብህ በፍጹም አሳብህ በፍጹም ነፍስህ ፈጣሪህን ውደድ›› የሚለው የትዕዛዛት ሁሉ ድምዳሜ፤ ‹‹ፍቅር የትዕዛዛት ሁሉ ፍፃሜ›› የሚለው ቃል በልብ ማህተማችን ሆኖ አልተቀረጸም፡፡ ፍቅር በልብ ማተባችን ሆኖ አልታሰረም፡፡ 

ወደ ፍቅር የቀረብሽበት መጠን እና ወደ ፍቅር የቀረብኩበት ዘመን ፍቅራችንን እንደሚወስነው ተፈጥሮአችን/ፈጣሪያችን በነፋሱ/ በእስትንፋሱ ሹክ ያለብን አሁን እየገባን ነው፡፡ ያልተግባባነው ከፍቅር የራቅነው መጠን ስለረዘመ ነው፡፡
አሁን ተፈጽሟል፡፡ ፍቅራችን በዘመን አያረጅም፣ አይሳሳም፣ አይበጠስም፡፡ በናፍቆት አይሸበርም፤ በተራሮች ሳንካ፣ በወቅቶች መፈራረቅ፤ በሰዓታት አለመተያት አይዘናነፍም፡፡ በነፋሳት ጩኸት አይታወክም፡፡ በአለማት ጭንቀት አይረባበሽም!!

ኢትዮጵያን እንዲህ ያራቆታት ምን ይመስላቹኋል? ታጣቂ፣ታጋይ፣መስዋዕት ልጆች እያሏት እንዲህ ምን አራቆታት? እንዲህ ተናጋሪ፣ ተቆርቋሪ፣ ተራማጅ ጅግኖች እያሏት፣ እንዲህ በዱር በገደል፣ 17 ዓመታት ሲታገሉላት የነበሩ አርበኞች እያሏት እንዴት እንዲህ ተመሰቃቀለች? የሺ ዓመታት የህይወት ተሞክሮ/ታሪክ/ ባለቤት ሆና እያለ፤ የተሰበጣጠረ ህብረ ቀለም ውህደት እያሏት ምነው እንዲህ ልትነካከስ አሸረገደች? ፍቅር ማጣት!

 ፍቅር ማጣት የብኩንነት ሚዛን ውጤት ነው፡፡ ፍቅር ማጣት የከንቱነት ሚዛን ጠለል ነው፡፡ የጠርዛጠርዝ ክንፎች ወደ ከፍታው ለመብረር መሃል ላይ የሚያያይዛቸው ውህደት ካልፈጠሩ መብረር እንደማይችሉ አልተረዳንም፡፡ ለመብረር እንንደፈደፋለን- ክንፏን እንደተመታች ምስኪን ወፍ ስንከላወስ ችግሩ አልተገለጠልንም፡፡ አልገባንም፡፡ ክንፏ እንደተመሰበረች ምስኪን ወፍ ማዘኗ አይደለም የኢትዮጵያ ሰንኩልነት፤ ልጆቿን በክንፏ አለመሰብሰቧ፤ ተኩላው፣ሽለምጥማጡ፣ እባቡ፣ ጅቡ ከእነዚህ የተረፈውም ጥንብ አንሳው በልጆቿ ላይ መዝመቱ ነው- ስቃይዋ!!
በተሰበረ ክንፍ- ልጆቿ ከእቅፏ ተከልክላ የሰማይ ውቅንያኖስ ደጆች ተከፍተው ሲወደርዱባት፣ የመብረቅ ብልጭታው ሲያሸብራት፣ ወቅቶች ተፈራርቀውባት፣ በውሃ ጥም በርሃብ ጥል ጠኔ ቀንበር ተሸክማ የተቀመጠቸው ምስኪን ወፍ በፍቅር እጦት የምትሰቃየው ይህች አገር አንድ ናቸው… ፈራን… ፈራን…ፍቅረን ፈራን!!

ፍቅር የበራላቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙሃኑ በጋን ውስጥ በርተዋል፤ ገሚሶቹ በነፋስ እንደሻማ ሆነዋል፤ አንዳንዶቹ በጠብ መንጃ ውስጥ ባሩድ እሳት ሆነው ተቀምጠዋል፤ በዝናብ ውስጥ በመጠጥ ስኒ ውስጥ ዋኝተዋል፤ ሰክረዋል፡፡ በጎጆ ውስጥ ላሉት ነፍሳት እራት መብያ የሆኑት አንሰውብን ጨለማ የመሆናችን ኀሰሳ በርቶልናል!!
በጋን ውስጥ ያሉት መብራቶች ጋኑ እጅግ ገዘፈባቸው፣ በነፋስ ውስጥ ያሉ ሻማዎች ነፋሱ ወደ አውሎነት ከፋ፡፡ በዝናብ ውስጥ ያሉ የእሳት ራቶች የመብረቁን ሀይል አልቻሉትም፡፡

ጋኖቹ ሲበዙ፣ አውሎ ነፋሱ ሲሰለጥን፣ መብረቁን ስንለማመድ የሚፈጠረው ምንድን ነው? ትላንትና አንዲት ሴት በአንድ ወንድ በጩቤ ተበሳስታ ተጥላ ስትገኝ ቢላዋውን ማህጸኗ ውስጥ ተሰንቅሮ እንዲቀር ያደረገበት ጭካኔ ከምንነት የመነጨ ነው፡፡ በመብረቅ ካልታጀበ በስተቀር፡፡ በአውሎ ነፋስ ውስጥ እንዳለች ጭላንጭል የፍቅር መብራት እንደሆንን ነው!  ፍቅርን ፈርተናል!!
ተስፋ በላይነህ፡፡

No comments: