May 13, 2014

‹‹ሪሞት ኮንትሮሉ›› የት ገባ? የአያቶቻችን ኑዛዜ!

‹‹ሪሞት ኮንትሮሉ›› የት ገባ? የአያቶቻችን ኑዛዜ!
በእውነተኛ ገጠመኝ የተመረኮዘ የፈጠራ ስራ
----ክፍል አንድ----
በቴሌቪዥናችን ውስጥ ከሚገኘው የሳተላይት ጣቢያዎች ውስጥ በአንደኛው እገኛለሁ፡፡ በእጄ የርቀት መቆጣጠሪያ /ሪሞት ኮንትሮል/ ይዣለሁ፡፡ ሲያሻኝ ወደላይ ሲያሻኝ ወደታች እያደረኩ ከጣቢያዎቹ ባንደኛው አጽንኦቴን እየሰጠሁ እገረማለሁ፡፡ ቢያንስ 1000 የሚደርሱ ጣቢያዎች አሉ፡፡  የአረቡ፣የሩቅ ምስራቁ፣ የምዕራባዊያኑ እንዲሁም የጥቁሩ አህጉር መገለጫዎች ሞልተዋል፡፡ በብዛት የሚደጋገሙም አሉ፡፡ ነጻ መስመር /Free channel/ እንደመሆኑ  በብዛት የሚታየው  የአረቡ አለም ገጽ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ስንቶቻችን አረብኛ እንደተላመድን መገመት የሚከብድ አይደለም፡፡  ሳሙናው፣ ቸኮሌቱ፣ የቂጣ ቃተኛው/ፒዛ/ ለስላሳ መጠጡ ወዘተ ይደጋገማሉ፡፡ ይሄን እያየን ነው ረሃብ የጠፋው ብዬ እገምታለሁ፡፡
ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ጣቢያ ማግኘትም ይቻላል፡፡ የአረቡ የሕልም ዓለም ከሰለቸኝ ጊዜ ጀምሮ፣ የሩቅ ምስራቁ ሩቅነት ከደከመኝ ጊዜ አንስቶ፣ የምዕራባዊያኑ ውሸት ከመረረኝ ወቅት ጀምሮ ወደ አገርኛ ጣቢያዎች ብቻ እንድለጠፍ አድርጎኛል፡፡ አልፎ አልፎም ወደ ሌሎቹ አገራት ለአለም ወሬ መዳረሴ አይቀርም፡፡
ከአንድ ሺህ ጣቢያዎች ውስጥ በአገርኛ ቋንቋ የሚቀርቡት ጣቢያዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ኢቲቪ 1፣ ኢቲቪ 2፣ ኢቲቪ 3 /ኦሮ-ቲቪ/፣ ኢሳት፣ ኢቢኤስ፣ ኢአርቲቪ፣ ኤልሻዳይ፣ ሶማሊያ ቲቪ ለእኛነታችን የቀረቡን እና በጣቢያነት ተመዝግበው የቀረቡልን ናቸው፡፡ የኢቲቪ 1፣2፣3 ቁጥሮች በአንድ ሲጠቃለሉ፣ ኢቢእስ እና ኢሳት ሶስቱም የእኛነታችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ በቤታችን ውስጥ የሶስቱ ጣቢያዎች ድብልቅ ትዕይንት በብዛት በየቀኑ ይስተዋላል፡፡  
በኢሳት እና በኢቲቪ መካከል ትልቅ የሆነ ጽንፍ ይታያል፡፡ ‹‹ሪሞት ኮንትሮሌን›› ዝቅ ሳደርገው ኢሳት ላይ እጫን እና ማየት ስከፍት አፈወርቅ የሚባል አቅራቢ በአንድ ትንፋሽ የሚንተገተግ ሐሳብን ስሰማ በተመስጦ እደመማለሁ፡፡ ሰውየው ምን ሆኖ እንደሆነ የምንረዳው በእሱ አስተሳሰብ ጫማ ውስጥ ስንሆን እና ኢትዮጵያ ውስጥ የመተንፈሻ ቀዳዳ ለተለጎመባቸው ዜጎች በአጠቃላይ ተወክሎ የሚናገር ይመስለኛል፡፡ የአንገቱ ጅማቶች ይወጣጠራሉ… ከፊት ለፊቱ የሚነበብብ ነገር እንደሌለው ሁልጊዜ የምንመለከተው አሳምነን እንረዳዋለን፡፡ ከውስጡ ግን የቆመው በብሶት አትሮንስ  ሁልጊዜም መጽሐፍ እንደተገለጠ ነው፡፡ በጥልቅ ስሜት ሳያቋርጥ በአንድ ትንፋሽ ይቀጥላል፡፡ በቤታችን የፖለቲካ ወሬ ሰይጣን የቄስን ድግምት እነደሚፈራው የሚፈሩት እና የሚያንገፈግፋቸው ቤተኞች አይወዱትም፣ በተቃራኒው ደግሞ ከ40 ዓመት በላይ ፖለቲካን ‹‹በታፈነ ጩኸት›› ሲገልጹት ለነበሩ ደግሞ ለሚያሳክክ ቁስል ፈዋሽ ቀኝ እጅ ነው፡፡ እኔ ታዲያ የምደመመው በሶስቱም ነው፡፡ በአገሬ፡፡ ይኸኛው የታፈነ ጩኸቱ እና ያበጠው ቆስሉን እንደ ፈውስ ሲጠቀምበት፤ አብሮ ያለው ተመልካች ደግሞ የሚያነበንበው ሰው ጩኸቱ አደንዝዞታል፣ የልብ ቁስል ሆኖበታል፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ራሱ ጣቢያው ይገርመኛል፡፡ ሪሞት ኮንትሮሉ እኔ እጅ ስላለ ራሴን ከማስደሰት ይልቅ አብረውኝ ካሉት ሰዎች ፍላጎት አንጻር ወደ ላይ ወደ ታች ማድረግ ይጠበቅብኛል፡፡ ለኔ አታስቡ፡፡ ከየትኛውም አይደለሁም፡፡ ምባልባትም ኤልሻዳይ የሚባለውን ጣቢያ ስከፍት ማናቸውም  የተመልካች ቡድናት ስለማይደግፉት ተከፍቶ አያውቅም፡፡ እስኪ ይታያችሁ እንዲያ ካለ ከማያቋርጥ ጩኸት እና ሌላኛው የደስታ ፈንጠዚያ ጣቢያ የእግዚአብሔር ቃል አይመከርምን ብዬ አፌን አውጥቼ ጠይቄ ባላውቅም  ለራሴ ግን በየጊዜው እጠይቃለሁ፡፡ ብቻየን ስሆን እመለከተዋለሁ እልና ለምን እንደምረሳው ግን አሁንም ድረስ አልተገለጠልኝም፡፡/ በነገራችን ላይ ኤልሻዳይ ማለት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ስብከት፣ መዝሙራት እና ተዓምራት የሚቀርቡበት ጣቢያ ነው/

ኢቲቪን የሚፈልጉት ሰው ለሰው ጀመረ፣ ቤቶች አለ፣ ሜሪቾ፣ የልጆች ጊዜ፣ ጥያቄና መልስ፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ፣ ለወጣቶች እና መሰል ዝግጅቶችን ለመከታተል ነው፡፡
የአፈወርቅ አግደውን የማያቋርጥ ሀሳብ እና የተመስጦ ዝርዝር ሂደት ትትን ሌሎች ተመልካቾችን ለማስደሰት ወደ ኢቲቪ እንሸጋገራለን፡፡ ኢቲቪ ነው ወይንስ ኢቴቪ? እርግጠኛ አይደለሁም፡፡‹‹የሪሞት ኮንትሮሉን›› የላይና ታች አቅጣጫ ምልክቶች በመነካካት ‹‹ኦኬ›› የሚለውን ስጫን ኢቴቪን እናገኛለን፡፡ የለበሱት ቀሚስ ቀሚስ ተብሎ የሚጠራ አለመሆኑን የሚነግሩን አያታችን ናቸው፡፡ እግዞ ወይ ዘመን እብደት እንደዚህ ይፋ ሆነ እግዞ ጨርቅ ጥሎ መሄድ እብደት ሲሆን እዚህ ቤት ውስጥ ግን ስልጣኔ ነው እያሉ ደግሞ ከወደ ጥግ የሚያማርሩ አሉ፡፡ በእርሳቸው አስተሳሰብ እና ልቡና ውስጥ ሆኜ ስመለከተው ሞትን የሚያስመኝ ነው፡፡ መቀመጫን ማንቀጥቀጥ፣ጭንን መክፈት መዝጋት፣ እምብርትን ማሳየት እና ማሻሸት በኢቲቬ በነጻ እና ያለሀፍረት/ነውር የቀረበ ትዕይንት ነው፡፡  ይታያችሁ ይህኛው የሚቀረበው በአገርኛው ጣቢያ ነው፡፡ ታዲያ ልጆች ያንን የማያቋርጥ የፖለቲካ ኑዛዜ ከመስማት ጭን ላይ አፍጥጦ መዋል አይበጅም ትላላችሁ? የኢቲቪ ጣቢያ ባለቤቶችማ ዘመኑን በደንብ አጢነውታል፡፡ ተመልካችም የሚያገኙት ለዚህ ነው፡፡ ከጭን ማንቀጥቀጥ ትዕይንት ሌላ ደግሞ አረንጓዴ ማሳ ላይ ከፍ ብሎ ቆሞ ያመረተውን እህል ትርፋማነት የሚመሰክር ሰውየ ይመጣል፤ ልማታዊ ጋዜጠኛው በሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ የተሰሩ መንገዶችን እያሳየ ያስደምመናል፡፡ በዚህኛው ጣቢያ ያለው የማያቋርጥ ሰላም ነው፡፡ የውስጥ ጭንቀት የለም፡፡ የጉሮሮ ጅማቶች የሚገተሩት በሰላም በደስታ የሚዘፍነው አዝማሪው ብቻ ላይ ነው፡፡ ታዲያ የኔ መደመም እናንተንስ አያስደምማችሁም? ያኛው በነጻነት እጦት ጅማቱ ሲገታተር ይኸኛው በሰላም እና በልማት ብዛት እያዜመ ጅማቱ ሲገታተር እንመለከታለን፡፡ እንደመማለን፡፡ ግራ እንጋባለን፡፡ አንድ መሆናችንን ለመዘንጋት እስኪፈታተነን ድረስ ግራ እንጋባለን፡፡
መሃል ላይ ያሉ ዘመን ተረካቢ ወጣቶች ደግሞ የኮሪያን ፋሽን፣ ተመረጡ መልከመልካም ፊት እና አልባሳትን ለመመልከት እኔን ይማጸናሉ፡፡ MTV Friend zone , Mtv cribs, PIMP my ride, world hit እኮ አለፈን እያሉ ቁም ስቅሌን ያሳዩኛል፡፡ በአሁን ዘመን ሪሞት ያዥ ከመሆን የሚከብድ ስራ ያለ አይመስለኝም፡፡ ኢቢኤስ ደግሞ አጥብቃ የምትከታተል ልጅ ትመጣለች፡፡ “ዛሬ እኮ ጆሲ በቤቱ ውስጥ ሾ አለ!” “ሰይፉ ሾ እንዳያልፈን”፣ “አዳዲስ ሙዚቃዎች የሚቀርቡበት ሰዓት ነው” እየተባባልን ስንመጻጸን እናመሻለን፡፡ ይኸኛው የኣዳዲስ ሙዚቀኛች መቅረቢያ ትዕይንትማ አያሳየችሁ፡፡ አገሩ ኹ ሉ ዘፋኝ ሆነ እንዴ የሚያስብል ነው፡፡ ጠጉራቸው አያሌ ቀለማትን ያሰባጠረ ገጽታን ተላብሶ ከውስጥ ሱሪ ባልዘለለ ድንክየ ቀሚሳት ተሸላልመው እንደ ዋሻ ጅራት ጅራታቸውን ሲቆሉብን ስንመለከት ሁላችንም በአንድ ጊዜ ከአያታችን ብሰን እንገኛለን፡፡ አሁን አሁንማ አያቴ የለመደችው ይመስለኛል፡፡ ሲከፈት ዝም ማለት ጀምራለች፡፡ /እየተመለከተች አለመሆኑን ከዕለታት በአንዱ ተረድቻለሁ/

ሰሞኑን ቴሌቪዥናችን አልተከፈተም፡፡ ምክንየቱም አያታችን ሞታለች፡፡ ይህንን ጉድ ከሚያሳየኝ ምነው ሞቴን አረዘምከው ብላ በትጋት ስትጸልይ በጆሮየ አይቻለሁ፤ በአይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ ሰሞኑን ሪሞት ኮንትሮል አልያዝኩም፡፡ ስትገነዝ ግን ሁሉንም ቆሜ ስከታተል ነበር፡፡
አገሬ ውስጥ እንዲህ የተቸገርነው ሪሞት ኮንትሮሉ በአንድ ሰው እጅ  ብቻ ስለተያዘ መሆኑን የተረዳሁት የሐዘን ድንኳን ውስጥ ሆኘ ነው፡፡ የሐዘን ድንኳን ውስጥ ብቻውን የተቀመጠ፣ ከእድርተኛው ጋር የተቀመጠ፣ በተወሰነ መልኩ ቡድን ቡድን ሰርቶ ካርታ የሚጫወት ሰዎች ተቀምጠዋል፡፡ ሁሉም የራስ የራስ ማንነቱን እፈለገ ከፈለገው እና ይጠቅመኛል ካለው ‹‹ጣቢያ›› ጋ ሄዶ ይቀላቀላል፡፡ ሀዘን ላይ ብንሆንም የሚሳኝ ግን ደስታ እና ጨዋታ ነበር፡፡ እኔም መቸስ ታሪከኛ ነኝ ከአያቴ አድሮ አደጎች ጎን ተቀምጬ ጣላይንን እያሰብን እንጨዋወታለን፡፡ “አየህ ልጄ ያኔ ጥልያን ስትገባ እሚትህ /አያትህ ለማለት/ እሚታህ የ12 ዓመት ጨቅላ ነበረች፡፡ ከአባቷ ጋር ሆና አብራ ዱር ለዱር ስትንገላታ፣ ስንቅ ስታቀብል መልዕክት ስታስተላልፍ ነው ላይ ታች የባዘነችው” ሲሉኝ የእኔ ሪሞት ኮንትሮል ለመቀያር ላይ ታች የምባዝነው ትውስ ይለኛል፡፡ አሁን በነጻነት እንዲህ ሪሞት ለመቀያየር ያበቃን የእንሱ ላይ ታች መባዘን መሆኑን ለማስረዳት ይጥራሉ፡፡ ሆኖም በነጻነት ሪሞት ኮንትሮሉን እየቀያየርን የምናየው ነገር እንዳላግባባን እና እንዳልጠቀመን አሊያም ማንነታችንን እንዳላሳየን ሰዎቹ ባይነግሩኝም ይህን አይነት መልዕክት እያስተላለፉ እንደሆነ ልቡናየ ይሰማዋል፡፡
ቀናት አለፉ ግብዓተ መሬት ተፈፀመ፡፡ ሰለስት፣ ሰባት ቀን፣ ሰላሳ፣ አርባም አለፈ፡፡ የእድርተኛው ትበብር፣ የማጽናናት ድርሻ ከህይወት ውስጥ በዋጋ የማይተመን ስጦታ እነደነበር አስተውያለሁ፡፡ ሙስሊሙ፣ ጴንጤው፣ ኦርቶዶክሱ፣ ካድሬው፣ ተቃዋሚው፣ የኔብጤው፣ የእድሩ ለፋፊ፣ በየዘር ማንነቱ ሁሉም ሲሰባሰብ የምናየው በዚህ ቦታ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት መገለጫውም ይህ ነው፡፡

ከቀናት በኋላም ሪሞት ኮንትሮሉን ፍለጋ ተያያዝን፡፡ ሪሞት ኮንትሮሉ ከጠፋ ሳምንት አለፎታል፡፡ እነዴፍላጎታችን እንዳንቀያይረው ወደ ሪሲቨሩ ተጠግተን ቁጢጥ ብለን መቀመጥ ስላለብን ትተነዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በአያታችን ሞት ባገኘነው አብሮነት ስሜት አብረን እንጨዋወታለን፣ አብረን እንሳሳቃለን፣ ህጻናቱ ከአባታችን እግር ስር ሆነው ተቀምጠው ወሬ ያዳምጣሉ፡፡ የሰሞኑን አንድነት ስሜታችን መደመምን ፈጥሮብኛል፡፡ ደስታንም አክሎልኛል፡፡ ምስጥሩ ግን አልተገለጠልኝም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ሪሞቱን ያየሁት ካ,ከማን እጅ እንደነበር ግራ በተጋባ ስሜት ራሴን ጠየኩት፡፡ በደስታ ውስጥ ሆነን ወደ ጥልቅ ማንነታችን ገብተን የምንፈትሸው ነገር መልስ ያስገኝልናል፡፡ ዛሬ ነው የአያታችን ጀግንነት፣ መስዋዕትነት እና ብልሃት የተገለጠልኝ፡፡ የናቅናቸውን ያህል አከበሩን፣ የተራራቅነውን ያህል አቀራረቡን፣ የጠፋነውን ያህል ሰበሰቡን፡፡ ሪሞት ኮንትሮሎ አብሮ ተገንዟል፡፡ ኑዛዜ እና ጸሎቷ ይህ ነበር፡፡  

No comments: