Jun 10, 2014

‹‹መወማ››

‹‹መወማ››

ምን ያያል ጎፈሬህ ምን ያያሉ አይኖችህ
ምን ያያል እንቅልፍህ ምን ያልማልስ ሌትህ
ያብቀቴው ቅበላ የመዓልቶች መንጎድ
ያፍቅሮተ ንዋይ የቁልቁለት መንገድ??
ለውጥ አልባ ፍርቅርቅ፤የጉልቻው ልውጥ
ጨው አልባ አልጫ፤ ያልበሰለ ‹‹ቀይ›› ወጥ
መንግስታት መታኮስ ዛሬን ለመለጠጥ…!
የስልጣን ግብግብ የነፍጥ ሹም ማበጥ
 የባንዳ ማሽካካት የድንጋይ ቅርስ ማግጠጥ…??
መወማ….
ምን ያስባል ነገህ፤ ምን ይመኛል ሞትህ
ምን ይላል ኑዛዜህ፤ ምን ይላል ትንሳኤህ?
ጎፈሬህን ቀባኝ
ዝናርህን ስጠኝ
ብዕርህ ይጠበኝ ሕልምህን አውሰኝ!
ትንፋሽህን ልያዝ ልታገል ከዘመን- ልዋደቅ ከዐለም
ጭቆናን ልታገል- ፍትህን ልፋረድ- ለነጻነት ልቁም
የሰላም ዝናሬ መንፈሴም ትቃትት ብዕሬም ትለምልም
ለሰው ክበር ልሙት -በመንግስታት ልቅለል-ከድሎቴ ልጹም!
ከችጋር ልፋታ- ድንቁርና ይክዳኝ
ክሽፈት ይሻር በኔ- ታሪክ ይፋረደኝ!!
ከንቱ አዋጅ ናቸው -አትሻም አውቃለሁ ሙገሳ ውዳሴ
አልችል ብሎ ይዞኝ ጨንቆት ነው መንፈሴ…!
መወማ
ጎፈሬህን ቀባኝ
ዝናርህን ስጠኝ
ብዕርህ ይርጠበኝ- ሕልምህን አውሰኝ!!
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››

No comments: