‹‹ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሆሆታ››
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነሀ›››››››
60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን
በማከበር ላይ የሚገኘው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ ሰኔ 28 2006 ዓ.ም ደማቅ ክብረ በዓል ለማክበር ተፍ ተፍ እያለ እንደሚገኝ ወደ
ዩኒቨርሲቲው አካባቢ ጎራ ማለት በቂ ነው፡፡ ኧረ በጠባቧ ጎንደር ከተማ መሆን በራሱ ይበቃል…፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ ስለ ዩኒቨርሲቲዎቻችን
መረን የለቀቀ ወጪን ያስረዳበት ጽሑፍ ሁልጊዜ ትውስ ይለኛል፡፡ ሰፋ ያለውን ሐሳብ ከራሱ ከጸሐፊው ቀንጨብ አድርገን እንውሰድ..
‹‹ራስ ብሩ ወልደ ገብርኤል አንድ የቅብጠት ስራ እንዳከናወኑ ታሪክ ይዘክራል፡፡ ራስ ብሩ
ቤታቸውን/ አሁን ኤግዚብሺን ማዕከል የሆነውን/ ለባንክ አስይዘው በመበደር የሰፋ-የተንተሰራፋ ድግስ ደገሱ፡፡ ድግሱ ላይ የአዲስ
አበባ ህዝብ በነቂስ እንዲገኝ አዝዘው አበሉት፤ አጠጡት፡፡ ድግሱ ቅጥ ያጣ ነበርና ጠጁ በገንዳ ተለቀቀ፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ
እንደከብት አፉን ገንዳው ላይ ለግቶ ጠጁን መጠጠ፡፡ ቅጥ አልባው ድግስ ቅጥ አልባ ስካር የለቀቀበት ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪ፤
በየሜዳው ተፈንችሮ የጅብ ሲሳይ ሆነ አሉ፡፡
የያኔው መከላከያ ሚኒስትር ራስ ብሩ ማን፣ ምን ሹክ ብሏቸው ይሄን እንዳደረጉ ግልጽ አይደለም፡፡
ምናልባት በማብላትና በመብላት ላይ ከተመሰረተው የጌታና የሎሌ ግንኙነት አንዳች ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት አስበው ይሆናል፡፡
‹‹የጮማዬ ጌታ!›› የሚል፤ ሞቱን ከሞታቸው ለማስቀደም መሽቀዳደሙ እሙን ነው፡፡ በሚል ይተነትንልናል ጸሐፊው፡፡››
ምናልባትም ምን ማለት እንደፈለግሁ
ይሕ ጸሐፊ በምሳሌ እና የምሑራንን ትንታኔ እያጣቀሰ የገለጸበት ጽሑፍ በመሆኑ ሙሉ ሐሳቡን መዋስ ግድ ሳይለኝ አይቀርም፡፡ ፋክት፡ ቁጥር 38 መጋቢት 2006 እትምን ማንበብ ትችላላችሁ፡፡
ይህ ጽሑፍ በሰፊው፤ የአገራችንን
ነባራዊ- ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ መዋቅር- የሚገልጽ ከመሆኑም ባሻገር በጠጣር አማርኛ በግልጽ እየተፈጸመ ያለውን የታይታ፣ የሆይታ፣
የመብላት እና የመበላላት ፖለቲካ የሚገልጽም ነው፡፡
ጸሐፊው ዓለማየሁ ገላጋይ በጽሑፉ
ወረድ ብሎ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ዋና ከተማዎችን ማጋጌጥ፣ የተንዛዙ በዓሎችን ማክበር፣ ዓይን የሚስቡ ‹‹ሃውልቶችን››
ለስም ማስጠሪያ ማቆም የብዙ አፍሪቃ መንግስታት ተቀዳሚ ተግባራት የሆኑ ይመስላሉ፡፡›› ብሎ ከምጣኔ ሐብት ባለሙያው የአቶ ገብርኤል ዳንኤልን ጥናት ያጣቅሳል፡፡
ጎንደር የኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት
60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሲያከብር ‹‹የተንዛዛ›› በዓል ነው ብለን ልንፈርጀው እንደማንችል የሚያግባቡን ሐሳቦች በርከት ይሉ
ይሆናል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት
የምስረታ በዓሉን ሲያከብር በቅድሚያ መታወስ ያለበት ጉዳይ ሶስቱም መንግስታት አሻራቸውን ያሳረፉ መሆናቸውን ነው፡፡ ሲሶ ሲሶውን
ይከፋፈላሉ፡፡ 60 ሲካለፈል ለ 3 ይሆናል 20፡፡ ማለትም ንጉሱ 20 ዓመት፣ ደርግ 17 ዓመት አህአዴግ 23 ዓመት…
ወደ ታሪካዊ ትንታኔው ሳንገባ
በታላቁ ክብር እና ስጦታ ‹‹በአሁን ላይ›› እናተኩር እና
በተጨባጭ የሚታየውን፣ የሚሰማውን ብንጽፍ የሚያዋጣን ይመስለኛል፡፡
ጎንደር የኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመቱን
ሲያከብር ‹‹ሪፈራል ሆስፒታልንም›› አብሮ ሊያስመርቅ በመሆኑ ሰሞኑን ከወደ ‹‹ሪፈራል ሆስፒታሉ›› አካባቢ ማለፍ ብዙ የሚያሳየን
ጉዳይ ይኖራል፡፡ ስራው በአፋጣኝ እየተከናወነ መሆኑን ማዬት ይቻላል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሕብረተሰቡ
ምን ሰራ? ብለን ብንጠይቅ “ምንም አልሰራም!” ብለን ሙሉ በሙሉ ጽንፈኛ እና ጨለምተኛ አስተሳሰብ መያዝ ያለብንም አይመስለኝም፡፡
በጎ በጎውንም ማጠያየቅ፣ ማፈላለግ
መፈተሸ እና ገባ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ለስመ ‹‹ሪፈራልነት›› መብቃቱ በራሱ በግልጽ የሚታይ ሲሆን፤ ሌሎች ማሕበረሰባዊ
ግልጋሎቶችን ለማየት ወደ የኒቨርሲቲው መረጃ ማዕከል ድረ ገጽ እና መሰል መገለጫዎች ጎራ ማለት በቂ ይመስለኛል፡፡ ፋና ሬዲዮ እና
ኢቲቪም ለዚህ እንደማይቦዝኑ ሁላችንም አንክደውም፡፡
ግለሰብም ሆነ ተቋም፣ ባለስልጣንም
ይሁን ስርዓት አሊያም የመንግስት መዋቅር ለትችት ሲቀርብ እየተሸሻለ እንዲሄድ ስለሚጠቅመው በቀና አስተሳሰብ እንደምንመለከተው አልጠራጠርም፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚታዩ ችግሮችን በማቅረብ የተሻሻለ ተቋም ሆኖ እንዲገኝ ለመንደር ብቻም ሳይሆን በአገር እና በአህጉር ደረጃ
ተጽዕኖ ማሳደር እንዲችል በማሰብ የተሰማንን፣ የሰማነውን፣ ያየነውን እንጽፋለን፡፡
ይሕ 60ኛ ዓመት በዓል ‹‹የተንዛዛ›› ነው ሊባል የሚችልበት ሁኔታ
ሊኖር እንደሚችል አንዳንድ ምክንያቶችን እናቅርብ፡፡ የተጋነነ ወጪ ለማይገባው እና ርባና ለሌለው ጉዳይ ‹‹ረብጣ›› ብር ሲመነዝር
ስንመለከት ክብረ በዓሉን ክፉኛ ያሳድፈዋል፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በይበልጥ አተኩሮ ሊሰራባቸው የሚገባቸው ቦታዎች እንደሚኖሩ
በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ ሰራተኞችን ማነጋገር በቂ ነው፡፡ ምናልባትም 90 በመቶ የሚሆኑት መምሕራን ተቋሙን ይወዱታል? ይደግፉታል?
በአስተዳደራዊ የስራ ዘርፉስ ደስተኛ ናቸው? ብለን መጠየቅ መሰረታዊም የሰብአዊነት ጥያቄ ነው፡፡
መንግስት ምናልባትም አውቆት ይሁን ሳያውቀው ልማቱን ቁሳዊ ብቻ አድርጎ
መፈረጁ በብዙ ሁኔታ በአገራችን ላይ ተጽዕኖ እንዳሳረፈ ማንም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አይን፣ ጆሮ በተለይ ልብ እና ሕሊና ያለው
ዜጋ የሚመሰከረው ነው፡፡ ሁላችንም ላይ ቁጭት አንዳለ ግልጽም ግልብም ነው!!
በተለይ ማሕበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ቁርኝት እና የዕለት ዕለት ግንኙነት
ያለው ሆስፒታሉ ለዚህ ጽሑፍ ዋና ርዕሰ ጉዳይ መሆን እንዳለበትም ሁላችንንም ያስማማናል፡፡
የየኒቨርሲቲዎች የበላይ ‹‹ሹማምንት›› በተንጣለለ የአውሮፓ ስሪት
የቤት ውስጥ እቃዎች መሞላት፣ በሚልየን ደረጃ በሚገመት ወጭ የሚገነቡ ቤቶች እና የቤት ዕቃዎች በተለይ አልጋ እና ወንበርን ስናስብ፤
በሕጻን ላይ ሕጻን ተደራርቦ እየተኙ የሚገኙትን የሕጻናት ሕክምና ቦታን ሲያስቡ እንዴት እንቅልፍ ይወስዳቸዋል?? ብለን እንድንጠይቅ
እንገደዳለን፡፡
“የተጋነነ ወጪ አለ!” ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄስ “ለገጽታ ግንባታ
ነው” /በዘመኑ ቋንቋ “ኢሜጅ”/ ተብሎ ሲመለስ ምን አይነት ስርዓት በላያችን ላይ እንደተተበተበብን ስናስተውል፤ ሰብኣዊነታችን
በእጅጉ ይጎዳል፡፡ “የውጭ እንግዶችን የምንቀበልበት ነው” ይሕንን ሲያዩ ያለንን ‹‹ኢሜጅ›› ለመቀየር ነው ተብሎ የሚነገረው በምን
አይነት የሰብአዊነት ቋንቋ ቢነገር እና ቢተረጎም ነው የምንግባባው?
በሽተኞች በመኝታ እጦት ሕይወታቸው እያለፈ፤ የተንጣለለ ቤት ውስጥ
መኖር የሚፈጥረው ገጽታ በምን መልኩ ታይቶ ነው ‹‹ኢሜጅን›› የሚቀይረው…? ምናችንስ ‹‹የሕዝብ አገልጋይ›› ሊያስብለን ይችላል?
ምናልባትም ይሕ አስተሳሰብ እስከላይኛው የመንግስት ስርዓት የሚቀባበል
ስለሚሆን ለልብ እንተወው፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት በዓሉን ሲያቀርብ ከፍተኛ ውጪውን የሚያወጣው
ለምግብ ነው ተብሎ ሲነገረን ከራስ ብሩ ጠጅ ግብዣ ጋር ምን
ያለያየዋል??
የመምህራንን ችግሮችን በቅጡ ሳይመልስ፣ የሕብረተሰቡን ልብ ምት በግለጽ
ሳይፈታ፣ ለበዓል ተብሎ የሚወጣ ረብጣ ብር ለምግብ ማዋል፤ ተቋሙን ‹‹ትምህርት ቤት ነው›› ተብሎ ሊያስጠራው ይችላልን?
7000 ሺህ ሰው ድረስ መያዝ የሚችል አዳራሽ መገንባት የሚያስፈልግበት
ሰዓት አሁን ነውን? በሽተኛ ሕጻናት አይታወሱንምን? ‹‹ፋውንቴን› ማስገንባት ጊዜውስ አሁን ነውን? በሆስፒታሉ ታዛ ላይ ወዳድቀው
የሚታዩት ሕመምተኞች ህንጻውን እያዩት ሊፈወሱበት ዘንድ የሚሰራ ይሆንን?
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከፍተኛ የስራ ድርሻውን የሚወስዱት መምሕራን ከአስተዳደሩ
ጋር በእኩል አይን ይታያሉ? ከጥበቃ ሰራተኛ አንስቶ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በፌደራል
መዋቅር የሚመደቡት መምህራንን እንዴት ነው የምንንከባከባቸው፣ ክብርስ አለን? ቦታስ አለን? ዋጋ እንሰጣቸዋለን? ኢትዮጵያዊነት
አንድነትስ በመምህራኖች ላይ ይስተዋላል? የዲፓርትመንት ተጠሪዎችስ ፍትሃዊ ስራ እየሰራችሁ ነው? ጥያቄው ለሁላችን ነው!!
የበላይ ሹማምንቶችስ ለዩኒቨርሲቲው ዋልታ ሆነው የሚያገለግሉ መምህራንን
እንዴት ነው የምትጎበኟቸው? ሁሉም መምህራን ቢሮ አሏቸው… ?? የሚኖሩበትን ቤት እና ኑሮ ሁኔታ አስባችሁት ታውቃላችሁ? ለጥናት
እና ምርምር ዝግጅት የሚሄዱበትን አጥር ቢሮክራሲስ አስተውላችሁት ታውቃላችሁ… ከ15 ሺህ ብር ለማይፈጅ የውጭ ስልጠና አሊያም ዩኒቨርሲቲውን
ወክለው ጥናት ለማቅረብ የሚፈልጉ መምህራን ተከልክለው ስንቶቻችሁ ለ ‹‹ቫኬሽን›› አውሮፓን እና አማሪካን ስትመላለሱባት ምንም
አይሰማችሁም?? ብዙ ነገር መዘርዘር በተቻለ…. ጊዜና ቦታ ለመቆጠብ፤ አሉባልታን ለመቀነስ ስለምንገደድ ነው እንጂ!!!
እነ ‹‹ጃሉድ››፣ በዓሉን ሊያደምቁት እንደሚመጡ ታዋቂው ስፖንሰራችን
እንደረዳም ሰምተናል… ለእነዛ ሁሉ ዘፋኞች የሚወጣውን ወጭ በየሜዳው ወድቀው የሚታዩትን ሕመምተኞች አስበንበት ቢሆን ስንት የሲኦል
ደጆች በተዘጉ?? ስንት የገነት በሮችስ ተከፍተው በቆዩን??
---ያው ልማታችን ቁሳዊ መሆኑ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚሰላ እድገት አለመሆኑ
የሚያመጣው ተጽዕኖ በገሃድ የምናይበት ነው…!!
አሁን እየተገነባ ያለው ሪፈራል ሆስፒታል፣ ለበዓሉ ድምቀት ማለቅ እንዳለበት
ተፍ ተፍ ሲባል፣ የውስጡን ዋነኛ የህክምና መገልገያ እቃዎች፣ አልጋ፣ የሰው ኃይል እና መሰል መሰረታዊ ግብአቶች የት አስቀምጠናቸው
ነው ለሰኔ 28 “ተጠናቀቀ” ብለን የምንዘግበው?? ‹‹የሆይታ›› ልማት እና አድገት ሁልጊዜም ለእንደነዚህ አይነት ክፍተቶች የተጋለጠ
ነው!!!
ሪፈራል ሆስፒታሉን ቢያንስ 5 ሚልዮን ህዝብን ለማገልገል ታስቦ ሲገነባ
የአገሬ አርሶ አደር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚሆንበት እየታወቀ ምን ያክል ምቹ ሆኖ ተገንብቶለታል????
ገመዱን ‹‹አይጥ በላው›‹› ተበሎ “ሲቲ ስካን” መነሳት ያለበት “ሲቲ
ስካናችንስ” የት ደረሰ?? ኧረ ስንቱ ተነግሮ ያልቃል????
በአጠቃላይ ‹‹ሆይታ›› ‹‹ብላ እንብላ›› በአገራችን በሰፊው የተሰራጩ
የስብዕና ማንነቶች ከሆኑ ዓመታት እየነጎዱ ነው…! ማን በቃችሁ ብሎ እንደሚያቆመንም ግራ ገብቶናል፡፡
- “ኧረ ምናረግነ??”
ብለን ስንጠይቅ “ፈርዶብነ” አለ የደባርቁ ስካውት…!! እውነትም ‹‹ፈርዶብነ›› እንጂ!!
በውድ ቪላ ቤት ውስጥ በውድ መኪና መፍነሽነሽ ለአገሬ ሕዝብ፣ ለእምዬ
እናታችን፣ ለሚጢጢ፣ ለአርሶ አደሩ የሚፈይደው አንዳችም ጠብታ አይኖርም…! ግዴለም እናንተ መኪናውን ንዱት… በውድ- ከላባ በተሰራ
የእንግሊዝ ትራስ ተንተርሳችሁ ‹‹ለ!ሽ›› በሉ፣ በውብ ጣልያን-ሰራሽ አልጋ ላይም ተኙ…. መኪናችሁንም ‹‹በራሳችሁ ወጭ በራሳችሁ
ውሃ እጠቡት…›› ውድ ውሰኪም እየተራጫችሁ ጠጡበት… የሕዝብ እንባ ጎርፍ ሆኖ ሁሉንም እንደሚያጥለቀልቀው ልብ እንዳላላችሁ በግልጽ
እየተመለከትን ነው….!! ምናልባትም ይሕ ጽሑፍ በተናጠል ለተቋም አሊያም ለግለሰብ ብቻ ታልሞ የተጻፈ እንዳልሆነ ልትረዱልኝ እንደሚገባ
አሳስባለሁ!!
የሰው ልጅ ሁሉም እኩል ነው…!! ድሃ -ባለጠጋ፣ ከተሜ -ገጠሬ፣ የተማረም
-ያልተማረም፣ ቀይ -ጥቁር፣ አጭር- ረዥም፣ ቀጭን- ወፍራም፣ ዘር -ቀለም ሳይለይ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው…! የሆይታን ልማት
እና እድገት ገታ አድርገን ለአንዲት ነፍስ ላዘለች ስጋ ሰብዐዊ ፍጡር ግድ ይበለን….!!! ካረጀው እኛነታችን ይልቅ በየዕለቱ ለሚወለዱት
ነፍሳት ግድ ይበለን…!! ከ60 ዓመታት በላይ 60 ሰከንድ ዋጋ አላት… አንድ ፍጡር ዋጋው ህልቆ መሳፍርት ነው!!!!
መልካም ‹‹ሞተ-ልደት›› ጎንደር ዩኒቨርሲቲ!!!!
ማስታወሻነቱ፡- ከልብ ላገለገሉ፣ የማሕበረሰቡን ቁስል ታምመው፣ ህመምተኞችን
ፈውሰው፣ አገርን ላስጠሩ የሩቅም የቅርብም የዩኒቨርሲቲው አባላት ይሁንልኝ!!!
No comments:
Post a Comment