አበበ ተካን ስንመለከት ምን ተሰማን? የፖለቲካ አስረኞችን ስንሰማ?
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
እንደ ኢትትዮጵያ ያለ አሳዛኝ አገር አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ እርግጥ ነው አገር የተባሉት ሁሉ ችግርን እንደተሸከሙ እናያለን፡፡ ፍልስጤምን አሻግረን እናያለን፡፡ የአገር ስያሜ ባይኖር በምን ስም ይሰቃዩ ነበር? የሰው ልጅ በአገር ጥላ ስር ሲጠለለል ከዝናብ፣ ከዶፉ- ከሐሩር ከእሳቱ- ከረሃብ፣ ስደቱ- ከጦርነት፣ እልቂቱ ሊከለል እና ሊጠበቅ እንጂ በአገር ስም ሲዋረድ እና ፤ ሐሞቱም ሲፈስ ደሙ ሲፈስ የሚታይበት ምክንያት ምንድን ነው?
ለመሆኑ አገር ማለት ምንድን ነው? አገር ለሰው ልጅ ሥለምን የእልቂት እና የስደት- እንዲሁም የምድር ጣር መገለጫ መንስዔያት ሊሆን ቻለ? ለምን ? አገር የመሬት የህዝብ እና የመንግስት ስብጥር/ሕብረት መገለጫ ሆኖ ሳለ መሬት እና ህዝብ የት ሄደው ነው መንግስት በብቸኝነት አገርን የሚመራው? እስከመቼስ እንዲህ ይኖራል? ለጠያቂዎች ያልሆነ መሬት እና ጠያቂ የሌለበት ህዝብ ሲገዙ መኖርን ማን ፈቀደው? /ሲገዙ- ጠበቅ ይበል!/
ሰሞኑን ታሰሩ የተባሉ ግለሰቦችን በየማህበራዊ ገጾች እና በመገናኛ ብዙሃን ስንሰማ ቆይተናል፡፡ ነገም ማን ታስሮ እንደሚጠብቀን አናውቅም..! ታሰሩ የሚባሉትንም ግለሰቦች የታሰሩበትን ምክንያትም አናውቅም…! ምን እንደሚሻለንም አናውቅም፡፡ አመት አመትን ሲሸጋገር ይዘን የምንሻገረው ነጻነትን፣ ፍትህን እና አንድነትን ወይንም ሰላምን አይደለም፡፡ አሊያም ከማንኛውም አይነት አገራዊ ክስተቶች መራቅ የግድ ሊሆንብ ነው ማለት ነው!
አበበ ተካን ስንመለከት ምን ተሰማን-? የኑሮው ውጣወረዱ፣ የግል ስብዕናው ወይንም ፍልስፍናው፣ በቀልድ እያዋዛ የሚያቀርበው ማንነቱ ምን ተሰማን? እኔ ግን አገር አልባ ማንነታችን… ማንነት አልባ ስብዕናችን… አገር አልባ ተስፋችን… ስቃይ እና ናፍቆት ከሁሉም በበለጠ ይህች አገር እንዲህ እየሆነች ማዬት ህመም ነው… ኢትዮጵያዊነቱን ተነፍጎ ከአገር አገር መንቀሳቀስ እንዳይችል ተደርጎ ከእስር በማይሻል ሕይወት የሚኖር ሰው አገሩ መምጣት ያልቻለበት ምክንያት የግል ጣጣው ነው ወይንስ የአገር ጣጣ?
ማን ነው እንዲህ እንድንሆን የፈረደብን? አገር ውስጥ ያለነው ስለ አገር ሙሉነት ስሜት እንዳይሰማን- ሙሉ በሙሉ እንዳንሰማ- እንዳንሳተፍ- ታሪክ ባሕል እና ፖለቲካን እንድንሸሽ እያደረገን ያለው ማን ነው…?
ህሊናን በብልኮ እንድንጋርድ፣ ዛሬን ለጥጠን እንድንኖር፣ ነገን ሳናስተውል ኑሮን እየገፋን እንድንኖር ያደረገን ማን ነው? መብላት መጠጣት ማውራት መተኛት የሕይወት ምስጢር አድርጎ አቡክቶ የሰራን ማን ነው? ምንድን ነው? ለምንድንስ ነው?
አገሬ ኢትዮያን እንዲህ እንድትሆን ያደረጋት ማን ነው? ወደየት እናዘግማለን? የት ነን? ምንድን ነን?
No comments:
Post a Comment