Jul 1, 2014

ነገረ ጫት

ነገረ ጫት
ከወደ እንግሊዝ የተሰማ ዜማ….የጸረጫት ዘመቻ/ Anti Khat campaign.
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ››››››››

ይሕ ርዕስ ...ሰፊ… በመሆኑ ‹‹ሰፋ›› ያለ ትንታኔ ለመስጠት አልሞክርም፡፡ ምናልባትም በሂደት የሚሞከር ካልሆነ በስተቀር፡፡ ጫት የምጣኔ ሓብታችን ዋልታ ነው፡፡
‹‹የኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና
የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና›› የሚለው የት/ቤት ደወል ጥሪያችን… ሻሂ እና ዳቦ እየጠጣን እየበላን የምንሰማው ዜና አሁን አሁን 
የኮኖሚ ዋልታ በኛ በኛ
 የጫት  ቀናችን ነው በኛ በኛ
ድንዛዜ እና ምርቃና በኛ  በኛ…
 ከሰዓት ሐራራ በኛ በኛ
ልማት ነው ህልማችን በኛ በኛ….!! ተብሎ ዜማውን እንደያዘ ቢቀርብልን አይገርመንም፡፡
እንዲህ ተብሎ መዘፈን የሚታወጅበት ቀን ሳይመጣ፣ ጫት ጠቃሚነቱ በቀሳውስት እና በሰባኪያን ዘንድ የሚለፈፍበት ቀን ሳይመጣ፣ የጫትን አስከፊነት አስብ…!! የምጣኔ ሐብታችን ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ድግግሞሽ… ‹‹ለኮንሰንትሬሽን›› ላቅ ያለ አስተዋጽዖ…ጫት በአገራችን ቢታገድ ምን እንደሚሆን አስባችሁት ታውቃላችሁ?
ስለ ጫት ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ የጤና ጠንቅ እንደሌለው የህክምና ባለሙያዎች ሲናገሩም እንሰማለን፡፡ በጥናት የተረጋገጠ ልክ እንደነ ሲጋራ፣ መጠጥ፣ አደንዛዥ እጾች እንደሚያስከትሉት የጤና እክል ዓይነት ተጠንቶ ባለመቅረቡ ጫት በአገራችን ሊታገድ አይገባውም ብሎ የተከራከረኝን ‹‹የጤና መኮንን›› አስታውሰዋለሁ፡፡ የአለም ጤኛ ድርጅት የሚያወጣውን የጤና ትርጉም መመልከት ብቻ በቂ ነው….፡፡
አገሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ በጫት ያልተጎዳ አካል የለም ብሎ መናገር ‹‹የምርቃና›› ወሬ ነው ብንል የተጋነነ ነው? አገራችን በምግብ ዋስትና ራሷን ችላለች ተብሎ ከተዘገበው ዜና ውስጥ በጫት ጠግቦ- የቆርቆሮ ጣራን ቀድዶ- ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ሲንፈላሰስ የሚያድረውን ‹‹የምርቃና ሲሲፈስ›› ማሰብ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ የእናቶችን ስቃይ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ የሕሊናን ስቃይ ቆጣሪ እንደ ኮከብ ቆጣሪ  ከስሮ ስለቀረብን እንተወው፡፡ “የምርቃና ሲሲፈስ”፡- ጫትን እየቃመ እድሜ ልኩን ሙሾ ሲደረድር፣ የድጥና ማጡን ፣ቆጥ የባጡን ሲፈትል የኖረ ሰው አምሳያ ነው፡፡ ባልተጨበጠ ራዕይ የሚንቦገቦግ፣ ባልተዳሰሰ ህልም የሚቃዥ እድሜውን በሙሉ ምርቃናን ሲገፋ የሚኖር….እንደ ማለት ነው፡፡ /‹‹አምሳለ ሲሲፈስን›› በውቀቱ ስዩም ላይ ያስታውሷል/
ጫት ሲወገዝ እና ሲታገድ የሚነጋነገውን የሕብረተሰብ ክፍል፣ የምጣኔ ሐብት ቀውስ፣ የስነ-ጽሑፍ እና የጥበብ ክስረት ሳስብ ድንቅ ይለኛል፡፡ ቃሚዎች ላይ ፍርድ ለመጣል አሊያም ከደሙ ንጹሕ ነኝ በሚል ራስን ለማንጻት የግብዝነት ብዕር ተሸክሜ ልወጋበት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ በጫት የደረሰብንን ስናስብ… የደረሰልን ስላልነበረ… ትውስ የሚለን ከልብ ሐዘን የመነጨ ንዝናዜ፣ የሕሊና ደወል…! ውዝዋዜ፣ ቅጥቃጤን በማስታወስ የተሰጠ ሐሳብ ነው፡፡ በጫት መከራ የደረሰብን፣ በጫት ያጣነውን ክብር፣ ይሉኝታ ቢስነት፣  በጫት ያጣነውን ገንዘብ፣ በጫት ያሳለፍነውን የወጣትነት እሳትነት መሯሯጫ የዘመን ጊዜ በደሳሳ ቆርቆሮ ምሽግ ቤት ስንቀብረው፣ በጫት የከፈልነውን መስዋዕትነት እና ኪሳራ የትውልድ ክሽፈት አስቦ ለሚኖር አካል ግን ምን ለማለት እና ምን ማለት እንደሚኖርብን ሳይገነዘበው የሚያልፍ አይኖርም!!!! ሳይገነዘብ የሚሸሽ ከተገኘም ሕሊናውን ይፈትሽ!!
ጫት በእንግሊዝ አገር ሊታገድ ነው የሚል ዜና በብረቲሽ ብሮድ ካስት/BBC/ ሰማን፣ [[ሶማሊያኖች]] እንዴት ጫት ‹‹ባን›› ይደረጋል ብለው ተቃውሞአቸውን አሰሙ… ‹‹ፐብ›› Pub በእንግሊዝ አገር ‹‹ባን›› ሳይደረግ ጫትን ‹‹ባን›› ማድረግ ህገ-ወጥ መሆኑን ‹‹አንዳንድ›› የጫት አስመጭ እና ላኪዎች ተናግረውም ነበር፡፡
ጫት ሲቅም የተገኘ ስልሳ ፓውንድ እንደሚቀጣ፣ ከዛም በሽያጭ ተሰማርቶ የተገኘ እስከ 14 ዓመታት እስር እንደሚጠብቀው አዲስ ጉዳይም ዘግቦታል፡፡ / አዲስ ጉዳይ፡ ቁጥር 222 ሰኔ 2006፡ ዋጋ 11.99/
ጫት በአገራችን ቢታገድ ምን እንደሚሆን አስባችሁታል? 
በአንድ ውብ ቤት ውስጥ ተጋብዤ ገባሁ- ቦታውን አልጠቅስም፡፡ አዲስ አበባ መሆኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ ቤቱ የሠዓሊያን እና የቀራጺያን መሰብሰቢያ እና ስራቸውን የሚከውኑበት ነው፡፡ ‹‹ድንቃ ድንቅ›› የእጅ ስራዎች ይወጣሉ፡፡ ባለ አራት ኮከብ የለ ባለ አምስት ኮከብ ቄንጠኛ ሆቴሎቻችን ስራዎቻቸው ከዚህ ቤት ነው ታትመው የሚወጡት… ታዲያ እነዛ ስራዎች ታትመው ሲወጡ፤ ጠዋት እና ማታ ሲገባ እና ሲወጣ የሚታዬው ኩንታል ጫት እና ገራባን የተመለከተ ይሕንን መልስ መመለስ ያዳግተዋል፡፡ ቤቱ ሙሉ የጫት ገራባ ክምር ነው…አልጋው… ወንበሩ…ሳሩ…!!
ስንትና ስንት ‹‹ፕሮፖዛሎች››፣ ስንትና ስንት ‹‹የፊልም ስክሪፕቶች››፣ የሙዚቃ ዜማና ግጥሞች፣ እቅዶች፣ ‹‹ፕሮጀክቶች››፣ ‹‹የሃይዌይ ዲዛይንና ሰርቬይንግ ዳታዎች›› ኧረ ስንቱ…. በጫት ንግድ የቆመው ምጣኔ ሐብት፣ ጫት ቤቶች፣ ቤት አከራዮች….ጥቂቶቹን ማሰብ በቂ ነው… መልሱን ግን ለፈጣሪ መተው ብቻ ይመስለኛል፡፡
አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ባለቅኔ ገጣሚ የስ-ነጽሑፍ ምሽት ላይ ተጋብዞ መጥቶ ህዝብ ሲያጨበጭብለት እና ወጣቱ ሲቆም ሲነሳ ተመለከትኩ፡፡ ለዘመኑ ገጣሚያን እና ጥበብ ፈላጊዎች ‹‹አርኣያ›› እንደሆነ የሚጠቀስ ነው፡፡ ወጣት ገጣሚያኑ ተሰብስበው ግጥም አቀረቡ… ፎቶ  ተነሱ.. እሱ ‹‹ዝም›› ነበር የሚለው… በዝምታው ትልቅነቱ እየገነነም ይሄድ ነበር… ዝም በማለቱ ታጋሽነቱ እና የዋህነቱ ተነገረ…የዝምታው ምክንያት ግን ገጣሚው ((((((በጉንጩ ጫት)))))) ይዞ እንደነበር ሳስተውል ለወሬ የማይመች እንደሆነ መገንዘብ ችያለሁ፡፡
ጫትን በሚገባ ጠንቅቀው ለማያውቁት፤ ስሙን ‹‹ካት›› እያሉ የሚጠሩት አሁን የጫት አሉታዊ ተጽዕኖ ገብቷቸው ቃትን/ካትን/ ጫትን ‹‹ባን›› አድርገዋል….!!
1ሺህ ቀናት ጫትን ሲቅም የነበረ አንድ ተማሪ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ‹‹ሰቃይ›› ተማሪ ተብሎ የወርቅ ሜዳሊያ በአንገቱ ሲያጠልቅ “ምስጋና ለጫት!!” ሲል ተሰምቷል፡፡/ ከ33ቱ የኒቨርሲቲዎቻችን በአንዱ… 33 የኒቨርሲቲዎቻችን ቢፈተሸ የጫት ጥናትና ምርምር ተቋማት ሊመስሉ እንደሚችሉ በማከል/
ጫት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢታገድ የሚነጋነገው ህልቆ መሳፍርት መዛግብት እንደሚወጣላቸው ጥልቅ ምርምር ማድረግ አያሻም፡፡ የኢትዮጵያን ወጣ..ቶች መመልከት ብቻ ነው…. የኢትዮጵያን እናቶች ጓዳ መፈተሸ ብቻ በቂ ነው…ኢትዮጵያን መመልከት ብቻ ነው….!!
አይ አንቺ አገር…!
‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
“ጫት ላይ ተንተርሰን
አንቅልፋችን አጥተን
አንሶላና ቆዳ-ክብራችን ተገፈን
ምጣኔ አካብተን
በጫት ተስፋ ጥለን
ቀናችን አሟጠን
ሕሊናችን ቀብረን
አካይስት ሲሰሙን
መናፍስት ሲጠሙን….!
የመረረው ጥሞን
የጣመው መ.ረ.ረ.ን…፡፡

ጫትን የሚቃወም ‹‹ሸር›› ያድርግ

No comments: