Jun 29, 2014

ላይመለሱ የሚሄዱ…

ላይመለሱ የሚሄዱ…
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››

 

ምድር በበርካታ ላይመለሱ በሚሄዱ እርካቦች የተሞላች ናት… ላይመለሱ የሚሄዱ!! ከዚህ ርዕስ ስር የቀረቡ ቃላትን እያነበብን ስንመጣ፣ ላይመለስ ለሚሄድ ጊዜ ቦታውን እየሰጠን ነው፡፡ ላይመለሱ የሚሄዱ ቅርፊቶች በርካቶች ናቸው፡፡
በምድር የሄደ ሁሉ ይመለሳል፤ የወጣው ይወርዳል የወረደው ይወጣል በሚል መስተጋብርም እንደተሞላች እናውቃለን!! ላይመለሱ የሚሄዱ ነገሮች ግን በእጅጉ  የመወጠር ኃይላቸው የሰፋ ነው፡፡ እስኪ ላይመለሱ የሚሄዱ ክብደቶችን እንዘርዝራቸው…
ላይመለሱ የሚሄዱ፡-
ክፉ ቃል ከአፍ ውስጥ ሲወጣ፣ ወሳኝ የፍጹም ቅጣት ምት /በሰኮንዶች ቆይታ ውስጥ ማለፍ እና መውደቅ ይመዘንበታል/፣ዐለምን ያጠፋው ሂሮሽማን እና ናጋሳኪን ያወደመው የሰኮንዶች ቅጽበት ውሳኔ፣ የሄዋን አጸ በለሥ ወደ መብልነት መቀየር፣ የይሁዳ ቅናት ዛር ለ30 ዲናር ከእራት ተነስቶ መሄድ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የሽጉጥ ቃታ ድምጽ ቀ.ጭ…! ዷ…-ጸጥ!!! ለርካታ….
በየቀኑ የምናዳብረው የስንፍና አባዜ/ ራስን ከመግዛት የሚያሸሸን፣ ጥበብን ከመሻት የሚያርቀን የመናፍስት ደዌ፣ ይቅርታን እንድንከዳ የሚያደርገን ሽሽት… እነዚህ ሁሉ ላይመለሱ የሚሄዱ ክስተቶች መሰረቶች ናቸው… የሄዱበት ርምጃ፣ የየቀን መንጎድ የሚመለሱበትን ፍጥነት ያሸሹታል፡፡ ከተፈጥሮ እንሸሻለን… ሲኦልን እንጠራለን…. ሁካታን እንስባለን፣ አመጻን እንጎትታለን፣ ጥፋትን እናከማቻለን፣ ሕይወትን እናጠፋለን፣ ሞትን እናመልካለን… ላንመለስ እንሄዳለን…. ለይቅርታ ላንሄድም እንመለሳለን!ላንመለስም እንሄዳለን!
ዛሬ
ዛሬ ላይ ቆም ብለን ራሳችንን እንመለከታለን፡፡ ቆም ብለን የምንመለከትበት ጊዜ እንኳ መኖሩ ከሄድንበት ለመመለስ ፍጥነታችንን እያሳየን ነው ተብሎ ሊቆጠርልን ይችላል፡፡
የት እየሄድን ነው?  ማንም የቆመ ቢለስው እርሱ እንዳይሳሳት… ማንም የቆመ አይደለምና፡፡ በተክለ እግር አምሳያ የቆምን ቢመስለን በእያንዳንዷ ቅጽበት ውስጥ ህዋሳት እየሄዱ ነው… አይመለሱም… ህዋሳት/ሴሎች/ ይሞታሉ… በአዲስ ይተካካሉ… እንደገና ይሄዳሉ… የሄዱት ግን ላይመለሱ እየነጎዱ ነው…!
አሁን
ህዋሳቶቻችን እየሄዱ፣ ላይመለሱ እየሄዱ ነው! እኛም ያው ነን…. የዛሬ አርባ ቀንም ሆነ የዛሬ አርባ ዓመት እኛ ያው ነን.. የግንባር ጸጉር ሳስቷል፣ የጠጉር ጥቁረት አሁን ነጽቷል… የሰውነት ጠረን ከትላንት ዛሬ ተቀይሯል… ህዋሳት ይተካካሉ.. ይሄዳሉ…!!

 በመተካካት ከሚኖግዱት- ላይመለሱ ከሚሄዱት በእጅጉ ያንሳሉ… ከትላንት ክምችቶች የነገዎች አላፊዎች እና ላይመለሱ የሚሄዱት ብዛታቸው ሰፊ ነው… ስፍር ቁጥር የለውም…የሚመጡት ሁሉ ላይመለሱ ለመሄድ ነው….! አሁን ግን ዘላለማዊ ናት… አሁን የመዳን ቀን ናት… አሁን ይቅርታ ቀን ናት…. አሁን የመለወጥ ስጦታ ናት… አሁን ላትመለስ ልትሄድ በአሁን እየተተካች ናት… አሁን ላይ ተንፍሰን- አግስተን ምን ያዝን?
 
አሁን ላይ ስራ አጥተን ቆመን ይሆናል፣ አሁን ላይ በህመም እየተሰቃየን ይሆናል፣ አሁን ላይ በጥላቻ እንሆን ይሆናል፣ አሁን ላይ በሰደት ላይ እንገኝ ይሆናል፣ አሁን ላይ በሱስ ተጠምደን ይሆናል፣ አሁን ላይ ትላንት የሄደችብንን/ የሄደበንን ሰው እየጠበቅን ይሆናል… አሁን ላይ ባዶነት ተሰምቶን ይሆናል፣ አሁን ላይ የግንባር ስጋ አይነት ችግር ተደንቅሮብን ይሆናል..አሁን ላይ እልፍ ጎልያዶች ተደቅነውብን ይሆናል… አሁን ላይ በኑሮው ውድነት እና በግለሰቦች መካከል ባለው ልዩነት ተሸማቅቀን ይሆን ይሆናል….-፡፡ ህይወት ጨው የሌለው አልጫ ሆኖብንም ይሆናል… በብዙ....
ላይመለስ በሚሄደው እኛነታችን ላይ አሁን ጎጆዋን እየሰራች ይሆናል/ ነውም፡፡ አሁን ካለችው አሁን ግን ቀጥላ በምትመጣው አሁን ላይ እኛነታችን መታደስ አለበት….! ዘመን እኛነታችንን ቢለውጥም-  እኛም ዘመንን እንለውጣለን !! በዘመን ላይ እኛነታችን ተለውጦ መታዬት አለበት!!!
እኛ ነገን መቀየር መወሰን አንችልም… አሁንን ግን መቃኘት /መመልከት፣ የዜማ ቅኝቱን መለዋወጥ/ ይቻለን ዘንድ አሁን በእጃችን ላይ የተሰጠች ታላቅ ስጦታ ናት… ዛሬ የነገዋ ትላንት ናት …. ነገ በዛሬ ላይ አንዳችም ኃይል የላትም… ልትመለስ እየሄደች መሆኗን ግን በነገ መነጽር መመልከት ችለናል… ነገ ዛሬን ማዬት እንደሚቻለው ግን መጠራጠር የለብንም… ዛሬ የትላንቷ ነገ ነበረችና… ነገ ላትመለስ እየመጣች… ላትመጣ ልትሄድ ነው… ላይመለሱ ከሚሄዱት ውስጥ ዋነኞቹ ‹‹አሁን እና እኛ›› ብቻ ነን… ቺሊዎች በእግር ኳስ ጨዋታቸው  ላይመለሱ እንደሚሄዱት አይደለም ሌላ 4 ዓመታትን ጠብቀው ሊመለሱ ነው… ላይመለሱ የሚሄዱት አሁን እና እኛ ብቻ ነን….!!! የዛሬ 4 አመት እኛ ምንድን ነን? ላንመለስ እየሄድን ነው? ወይስ ለመሄድ ብቻ እየተመላለስን!?

44 ዓመታት የገዙን ንጉስ አሁን ከገቢያ ውጭ በሆነች መኪና ላይመለሱ ሄደዋል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደምን›› አንግበው የተንተገተጉት ኃይሎች አሁን ወደ ኋላ ተሰልፈዋል.. እነሱም ላይመለሱ ሄደዋል-፡፡ አሁን ላይ ያሉት ላይመለሱ እንደሚሄዱ ዘንግተውታል..-፡፡ አሁን ላይ ላንመለስ እየሄድን መሆናችንን ካላሰብን አሁን ላይ በእርግጥም ወድቀናል.. ላንመለስ ሄደናል!! ላይመለሱ የሚሄዱትን ሆነናል፡፡
ላይመለሱ የሚሄዱተት ተረኞች ሆነናል…!!

No comments: