ሰው ለምንድን ነው ገዳም የሚገባው?
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንዳንድ
ምሑራን የሚገልጽዋቸውን ምልከታዎች በተደጋጋሚ ልናነብ እንችላለን፡፡ የነገስታትን እና ገዳማትን ትስስር የተቃኘበት ምልከታ በጣም
ደንቆኛል፡፡ ኢትዮጵያን ወደኋላ ያስቀራት ነገስታትን ወደ ገዳም በመላክ የቤተ መንግስታቸውን ጥበቃ እና ኃላፊነት ጥሎ ገዳም እንዲገቡ
በመደረጉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ነገስታት ወደ ገዳም ሲሄዱ አገር በጠላት ይወረራል፡፡ ለምን? እንዴት? በምን ምክንያት? እና ወደ
ውስጥ ለመግባት ብዙ ኃይል እና ፍተሻ ስለሚጠይቅ ወደ ጎን እንተወው… ገዳም መግባት ግን ሁሉንም መናቅ እነደሆነ እረዳላሁ፡፡፡
አሁን ግን ስለ [[ገዳም መግባት]]
ለመጻፍ ያነሳሳኝን ጉዳይ ላካፍላችሁ…! እውነተኛ ታሪክ ነው… ከተጠቀሱት ስሞች በስተቀር፡፡
ዛሬ አያ ልሳን ወደ ቤታችን
መጡ፡፡ ከወትሮው ለየት ባለ ገጽታ፡፡ ዝምድናችን በጋብቻ ነው፡፡ ከሳ ብለዋል፡፡ ጠቆር፡፡ ጫማቸው የዛሬ አርባ ዓመት እንደለበሷት
አይነት የታጋዮች ጥልፍልፍ ፕላስቲክ ጫማን ቀለሟ ቀይራ መጥታለች፡፡ የታጋዮች ጥቁር ነበረች፡፡ አሁን ልምላሜ እና እድገት ነው፡፡
አረንጓዴ ሆናለች፡፡
አቤት የነበራቸው ገጽታ… ግርማ ሞገስ… ሰሊጥ ማሽላ ምናምን ይሞክሩ ነበርና
ሳንቲም ከኪሳቸው አይጠፋም ነበር፡፡ ያገኙትን ሰው መጋበዝ ነው አልኳችሁ፡፡ ምናልባትም አሁን ገዳም ከገቡበት አንደኛው ምክንያት የገንዘብ አጠቃቀም ሊሆን
እንደሚችል በግምት ውስጥ ይዤዋለሁ፡፡/
ታሪካቸውን በዚህ አጭር ግድግዳ
ላይ ጽፌ እንደማልጨርሰው እንደምታውቁ ይሰማኛል፡፡ ምናልባትም አንድ ራሱን የቻለ ስራ ሊወጣው ስለሚችል፡፡
አያ ልሳን እድሜያቸው ወደ
70ዎቹ መጨረሻ ነው፡፡ ሶስት መንግስታትን ያዩ ናቸው፡፡ በኢህአፓነት የተሰደዱ ልጆች አሏቸው፡፡ በ1965 ግርግር ጊዜም አንድ
ልጅ ወልደዋል፡፡ ከዚያም ሌሎችን፡፡
ኢህአፓ መቼስ የመበታተን እጣ
ፈንታ ሲደርሳት፣ አባላቱም የት እንደገቡ እና እንደወደቁ ሳይታወቅ አንዱ ልጃቸው የት እንደገባች ሳትታወቅ ከጠፋች 17 ዓመት በኋላ
አሜሪካ መሆኗ ተሰማ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ ደርግ ወደቀ፡፡ እሰየው ተባለ፡፡ መንደር ቀውጢ ሆነ፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ይኖሩ በነበሩባት
መንደር ውስጥ አንድ ታላቅ ሰርግ ሆነ… የኢህአዴግ መግባት እና የልጅ ከአማሪካ መገኘት!!
ዴሞክራሲ ተሰበከ፣ መብት ተለፈፈ፡፡ አዲስ የብሔር መዋቅር ተደረገ፡፡ ድንበር
ተሰመረ፡፡ እኩልነት ተጻፈ..ልማት ተዘመረ… አያ ልሳን እንደገና ተወለዱ፡፡ ህዳሴ፡፡ህገ መንግስት ጸደቀ…… ልማት፣ ሰላም ዴሞክራሲ….!
ታድያ አያ ልሳንን እና ህገ-መንግስትን
ምን አገናኛቸው? ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እንዴት አያገናኛቸው!!!! ያገናኛቸዋል እንጂ፡፡ እንዲህ ‹‹ኮማንድ ፖለቲክስ›› በገነነባት
አገር ማን ነው ከፖለቲካው ውጭ መሆን የሚችለው…?
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የትግራይ
ክልል ተከዜን የሚያካልል መሆኑ ሲቀየር እና ሲያጠቃልል፡፡ የወልቃይት ህዝብ በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካለል፡፡ በዝግመተ ለውጥ አይነት
መፈንቅለ ርስት መካሄድ በኋላ አገር መልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸውልኛል፡፡
አማሪካ ያለችው ልጅም “አባዬ
ግዴሎትም” ወደ ከተማ ይግቡና እኔ እልካለሁ አለች
በደህና ሰዓት የተገኘች ልጅ
ተስፋቸውን አለመለመች፡፡ አጽመ ርስት፣ ቀዬ፣ መንደር ሲካለል፤ በደህና ጊዜ የተገኘቸው ልጅ ልትጦር ቃል ገባች፡፡ አማሪካን አመሰገኑ!!!
ሁለተኛ አገርም አደረጓት፡፡ ከዛማ ምን ቸግሯቸው፡፡ ምንዛሬውን በስምንት እያባዙ፣ በ9 እያባዙ፣ በ12 እያስመነዘሩ.. በ14 ሲመነዘር
ሁሉም ነገር ቀና ነበር፡፡ /ምናልባትም ይሕንን ገንዘብ በጥንቃቄ ቢጠቀሙት እና ማድረግ የሚገባቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ቢያሟሉበት
አሁን እንዲህ አይሆኑም ነበር የሚል ግምት ለመስጠት ሞክሬያለሁ፡፡/
እሺ ገንዘባቸውን በአግባቡ አልተጠቁሙበትም
ብለን ችግሩን ከራሳቸው ጫንቃ ላይ እንከምረው፡፡ ገዳም ቢገቡ “የራሳቸው ጉዳይ ነው!” እንበል፡፡ ነገር ግን እያለቀሱ፣ የአይናቸው
እንባ ወደ ከንፈሮቻቸው እየጎረፉ ያለቀሱበትን የርስት ባለቤትነት በማን ጫንቃ ላይ ይከምሩታል??
አሁን እኛ ቤት የመጡት ሊሰናበቱን
ነበር፡፡ ገዳም ሊገቡ፡፡ ልጃቸው አሁን ህዳሴው በተቀነቀነበት እና አንድ ዶላር 20 ብር በገባበት ዘመን ባዶ ሲሆኑ፤ ብር ስለሌላቸው
ብቻ ሚስታቸው የፍች ጥያቄ አቀረቡላት፡፡ “የሚያበላኝ ከሌለ ምን ያደርግልኛል” ነበር የፍቺው መንስዔ፡፡ አማሪካ አዲዎስ… ወልቃይት
አድዮስ… ህዳሴ አድዮስ….
በዛች ጥልፍልፍ ጫማ ከጫካ መለስ
ወደ ዓለም የገቡት ታጋዮች አሁን የጫማው ስም እንኳ አይታወቃቸውም፡፡ እግራቸውም አይመሰክርም፡፡ የተጫሟቸው ጫማዎች የአያ ልሳን
ዓመት ቀለብ ናቸው፡፡ አያ ልሳን ግን ያቺን ጫማ አድርገው ወደ ገዳም
እየገቡ ነው፡፡…. ምሑራን ይሄንን እነዴት ሊተረጉሙልን ይችላሉ፡፡ ነገስታት በፕላስቲክ ጫማ ከጫካ ወደ ወደ ቤተ-መንግስት ይገባሉ፡፡
አያ ልሳን በፕላስቲክ ጫማ ጫካ ይወርዳሉ፡፡ ገዳም ይገባሉ…፡፡
No comments:
Post a Comment