ቲ ከው አውትኒ? አገርህ የት ነው?/በቅማንትኛ/
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
ለቅማንትኛ ቋንቋ መማሪያ አዘጋጆች
እና አስተባባሪዎች መልዕክት፡፡
በአንድ ‹‹የቅማንት ብሔረሰብን
ራስ አስተዳደር እንዲፈቀድ›› ከሚታገል ስብሰባ ተገኝቼ ነበር፡፡ የዛሬውን በስፋት ለየት የሚያደርገው አንድ ብሔረሰብ እውቅና እና
ራስን ለማስተዳደር በህገ-መንግስቱ ከተቀመጡት መስፈርቶች ማለትም ቋንቋን እና ባሕልን ለመግለጽ የታየው ጥረት እና እርምጃ ሂደት
የወደፊቱን አቅጣጫ ያመላከተ ነበር፡፡ ትግል እንዲህ ነው፡፡ በየጊዜው እየተጠናከሩ በየጊዜው እያደጉ መሄድ ነው፡፡ መሻሻል፡፡ ለትግሉ
የሚየስፈልጉ መስፈርቶችን ማምጣት፣ ሰላማዊ! ሂደቶችን ሁሉ መጠቀም አለብን፡፡
በዚሕኛው የቅማንት ህዝብ ጥያቄ
፡- ከሚታማበት የቋንቋ መኖር አለመኖር ውዝግብ በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ የሚችል ስራ ተሰርቷል፡፡ ዋናው ቁምነገሩ እና የኔ የዚህ
ጽሑፍ ዓለማ የዝግጅቱን ውስንነት እና ምሉዕነት ለመተንተን አይደለም፡፡
እየተዘነጋ እና እየተዘለለ ባለው ኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ
የግል ሀሳቤን ለመሰንዘር ነው፡፡ ለመንግስትም ለህዝቡም…
ኢትዮጰያ ነች ዓላማችን፡፡ ኢትዮጵያ
ነች አገራችን፡፡ኢትዮጰያዊነት ነች ማንነታችን፡፡ ይሕ ምን ማለት ነው?
እኔ ጎሳን ያጠነጠነ ማንነት
ላይ ከማጠንጠን ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን ማጠንጠን ላይ ብንረባረብ እደግፋለሁ፡፡
ይሕንንም የምገልጽበት ጉዳይ አለኝ፡፡ ባለፈው ታሪካችን ተጎድተናል እና ኢትዮጵያዊነት "የለም" ካልን፤ ካለፉት መንግስታት እና ህዝቦች ወደ ኋላ መቅረታችንን እያመላከትን እንዳንሆን ቆም ብለን እንድናስብ ነው፡፡
ይሕም
ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ማንኛቸውም የጎሳ መገለጫዎች ማወቅ፣ ማጠንጠን፣ መግለጥ፣ መጠቀም፣ ማሳደግ፣ ማዋሃድ እና ሌሎች
የሚፈለጉትን የእኩልነት እና የአንድነት መስፈርቶች ማሟላት ነው፡፡
አንተ የምን ጎሳ ነህ? ብትሉኝ
አላውቀውም ነው መልሴ!
ይሕም ማለት በኢትዮጵየ ውስጥ የሚገኙ የማንኛቸውም ዓይነት ጎሳዎች እና ነገዶች ይገልጹኛልና፡፡ በአባቴ
ሸዋ አማራ ነኝ፣ በእናቴም እንዲሁ
ትግሬ፣ በአባቴ ቅድመ አባት /እናት ኦሮሞ ነኝ፣ በእናቴ አባት አማራ ፤ በእናቴ አያት ኤርትራ ውስጥ፣ ከቅማንት፣ በእናቴ
አያት ጉራጌ…. እያለ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይሕን እንዳገኝ ያደረገችኝ እምዬ ኢትዮጵያ ናት! ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
ታወቂው ደራሲ እና
የፍስልፍና መምህር ሰለሞን ደሬሳ ያለው ሁሌም በአዕምሮየ ያቃጭላል፡፡ “ማነሽ ኦሮሞ ነኝ የምትይ? ማነሽ አማራ ነኝ የምትይ? በአያትሽ
ደጃፍ ያለፈውን አማራ ሳትመለከቺ ንጹህ ኦሮሞ ንጹህ አማራ ነኝ ማለት አንችልም..”/ ቃል በቃል እንዲህ ላይሆን ይችላል ጽንሰ
ሐሳቡ ግን እንዲሁ ነበር/
ኢትዮጵያዊነት ማለት የቅማንት፣
የአማራ፣ የአርሲ ኦሮሞ፣ የከፋ፣ የሱማሌ፣ የአፋር፣ የትገረ፣ የኩናማ፣ የሀድያ፣ የሙርሲ፣ ወይጦ፣ የጉራጌ… ከ80 በላይ ጎሳዎች የፈጠሩት
ከተለያዩ ነገዶች የተውጣጡበት ድንቅ ውህደት የሚፈጠርበት ማንነት ነው-ለኔ፡፡
እኔ ትግሬ ብቻ ነኝ ብዬ ባህሉን፣
ቋንቋውን፣ ታሪኩን የምመለከት ብቻ ከሆነ ኢትዮጵያ ትደማለች፡፡ ኢትዮጵያ ታለቅሳለች፤ ኢትዮጵያ ትገነጣጠላለች፣ እርስ በርስ ነፋስ
ይገባል፡፡ "ሰይጣን" ስራውን ይሰራል፡፡ የሠውን ልጅ ማለያየት ነውና አላማው፡፡
የሰው ልጅ ሁሉም እኩል ነው…!
የሰው ልጅ ከዘር፣ ጎሳ ቋንቋ በዘለለ የነፍስ የስጋ እና የደም አንድነት ያለው በዙ ማንነቶች ያሉት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ!!
ኦሮምኛ ቋንቋን የማወቅ መብት
ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለብኝ!! ኢትዮጰያዊ ነኝና!! አማርኛ ቋንቋ ብቻ የመቻል ኢትዮጵያዊነት ጎዶሎ ነው፡፡ ከኋላ ታሪካችን ይሕ
አይነት ስርዓት በግዴታ እየተለጠፈ ከሆነ ስሕተት ነው፡፡ እንቃወማለን፡፡
ትግርኛን ባለመቻሌ ኢትዮጰያዊነት ከሙሉነቱ እየጎደለ ነው፡፡
ቅማንትኛ ቋንቋን መማር የማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብት እና ግዴታ ነው፡፡ እኔም ቅማንት ነኝ -አይደለሁም፤
ይሕ ልጅ ቅማንት ነው
እንዴ? የሚል አስተሳሰብ እንደተለጠፈብን እርግጠኛ ነኝ!! ቅማንት ነኝ… ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነኝና!!
አምቦ ውስጥ ተወልጄ አድጌ
ይሆናል.. በኢትዮጰያዊነት ውስጥ ግን ቅማንት አለና፤ ኢትዮጵያዊነት
ቅማንቱን ከትግሬው፣ ከአፋሩ፣ ከኩናማው የሚያዋህደው ማንነት ነውና!!!
የትምህርት ስርዓቱ በዋነኝነት
በየትኛውም የኢትዮጰያ ድንበር እና "ክልል" ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ማንኛቸውንም አይነት ጎሳዎች ለማዋሃድ መሳሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ሥነጥበቡ፡፡ የመንግስት ስርዓት አወቃቀሩ በፍቅር እና በአንድነት መንፈስ የሚያዋህደን ያለፈን ታሪክ እያስታወሰ የሚያለያየን ማንነት
ከመገንባት የሚያዋህደንን ስርዓት መገንባት በብዙ እጥፍ የሚሻል ነው፡፡
‹‹የከፋፍለህ ግዛ›› ጨቋኝ
አገዛዝ ስርዓት በብዙ እጥፍ ይመቻል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ግን ያለያያል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያዳክማል፡፡
እኔም በስብሰባው የተገኘሁት
ኢትዮጵያዊ ሆኜ ነው እንጂ በአባቴ በእናቴ ዘር ቆጥሬ አይደለም፡፡ መጽሐፍቱን ገዝቻለሁ፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ
ማደግ አለበት!! ከህዝብ ቆጠራ የተሰረዘበትን ምክንያት እንዲጠና በሰላም እና በፍቅር እንዲፈታ እታገላለሁ፡፡ ቅማንት ብቻውን ራሱን
ማበልጸግም የለበትም፡፡ ቋንቋውን ማሳደግ ያለባቸው ቅማንት ነን የሚሉት ሰዎች ብቻ መሆንም የለባቸውም፡፡ ቅማንትነት የኢትዮጵያ
ልጅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች ያሏት አገር ናት፡፡ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት እና በአንድነት በፍቅር ትስስር የምታስተናገድ
አገር መሆን እንድትችል እታገላለሁ፡፡
መንግስታት የተወሰኑ ሰዎች የሚፈጥሩት
ስብስብ ስለሆነ መንግስታት የሚፈጥሩትን ስርዓት እያስታወስን ብቻ ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ አገር፤ ኢትዮያዊነት የሚባል የጋራ ማንነት የለም
የምንል ከሆነ፤ ኢትዮጵያ ትደማለች፡፡ ኢትዮጵያ ታለቅሳለች፡፡ ኢትዮጵያ ትሸነሸናለች፡፡ ኢትዮጵያ ትፋረዳለች!! ፍቅር ያሸንፋል….!!
ግልጽ ለማድረግ ያክል
1. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውም የነገድ ዝርዝሮች በእኩልነት ሊታዩ ይገባል፡፡ በአንድነትም ሊዋሃዱ፡፡
2. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም ጎሳዎች ለአንደኛው ጎሳ ብቻ የተሰጡ ማንነቶች አይደሉም፡፡
3.
ቅማንትኛን ኦሮሞው ሊያውቀው፣ ሊማረው፣ ሊጠብቀው ይገባል ቅማንቱም ኦሮምኛ ትግርኛ ኮንሶኛ ጉራጌኛ ሊያውቅ ይገባል፡፡
4. ብሔርተኝተን የሚጠቅመውን በራስ ቋንቋ አለማፈር፣ ባሕልን ከማሳደግ አንጻር የሚደገፍ ሲሆን አገራዊ ማንነትን የሚያጠፋ
ከሆነ ግን ለተንኮል የተረጨ መርዝ ነውና ልናስወገደው ይገባል!!
5. ኢትዮጵዊነት ውህደት ነው፡፡ ኢትዮጰያዊነት የልዩ ልዩ ነገዶች ስብስብ፣ እቅፍ አንድነት መሰረት ነው፡፡ የሰላም እና
የፍቅር ተምሳሌት፤ የሰውን ልጅ በአንድ የሚጠቀልል ማንነት ነው፡፡ አንድ አይነትነት ግን አይደለም! ህብር ውበት ማንነት ነው! ሁላችንም ደማችን ቀይ ነው፤ ስጋችን አንድ ነው፤ መንፈሳችን
አንድ ነው… መጠቅለያው ደግሞ ፍቅር ነው!!!
6. አውቃለሁ ይሕ ከባድ ነው፡፡ ስብከት ሊመስል ይችላል:: እናውቃለን፤ አንድን አገር ለመገንባት/ ለማዋሃድ ክፍለ ዘመናትን ሊወስዱ ይችላሉ፤ አንድን
አገር ለመነጣጠል ግን ዓመታት ይበቃሉ….
አገ እንገንባ፣ አንድ እንሁን… ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ህዝቦች በአንድነት እና በእኩልነት
እንይ… ይሕ ነው ኢትዮጰያዊነት ለኔ!!!
7. “ቲ ከው አውተኒ? “/አገርህ የት ነው/ ለሚለው ጥያቄ መልስ
“ይ"ይከው ጎንደር ጋላ” /የኔ አገር ጎንደር ነው/ ከሚሆን መልሱ ከማለት “ይከው ኢትዮጵያ ጋላ” /የኔ አገር ኢትዮጵያ ነው/ በሚል አስተሳሰብ
ቢለወጥ ነው ዋናው መልዕክት፡፡
8. በቅማንትም ያሉ ስሜታዊነቶች እንዳይታበዩ፣ ሌሎች ጎሳዎች እና ነገዶችም በቸለልተኝነት እንዳያዩት፤ ጉዳዩ የሁላችን ነው፤
ጉዳዩ የኢትዮጵያ ነው…!!!
ይደረለይን/ እግዚአብሔር ይስጥልኝ በቅማንትኛ…./
እንተዴው ዳንግኦ ጋ/ እናንተ ደህና ሁኑ…ማለት ነው::
No comments:
Post a Comment