Jun 6, 2014

የሸሕ ለጋስ ልጅ!

የሸሕ ለጋስ ልጅ!
አስደናቂ የፍቅር ታሪክ፡፡

‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነሀ›››››››
የሸህ ለጋስ ልጅ በከተማችን ሙስሊሞች በብዛት በሚገኙበት የንግድ አካባቢ የሚኖር አብሮ አደጌ ነው፡፡ የሸህ ለጋስ ልጅ፡፡ የሸሕ ለጋስ ልጅ እውነተኛ ስሙ ነው፡፡ ምናልባትም ት/ቤት፣ ቀበሌ እና ሆስፒታል የሚያውቁት ስም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሁላችንም ግን የሸህ ለጋስ ልጅ እንለዋለን፡፡
የሸህ ለጋስ ልጅ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን በፍቅር እንድወዳቸው ያደረገኝ ሰው ነው፡፡ የልጅነት አብሮ አደግ ጉዋደኛ፡፡ በኢትዮጵያ ሙስሊም ቤቶች ያለውን ትስስር ያሳየኝ፡፡ ሙስሊምነት የእውቀት ምሽግ፣ የሰላም ጽዋ፣ የትዕግስት ሐይማኖት አድርጌ እንድወስድ ያደረገኝ ሰው ነው፡፡ ላለያያችሁ መጣሁ ብሎ በነገረን መሰረት ክርስቶስ እንዳለያየን ተረድቻለሁ፡፡ እሱም ተረድቷል;፡
እቤታቸው ስሄድ አያቱን እንዴት እንደሚያቅፋት፣ እሷም እንዴት እንደምትሳሳለት ስመለከት ግርም ይለኝ ነበር፡፡ አብረን ስንቀመጥ ከአጠገቧ ቁጭ ይልና በዛ ባሕላዊ “አረብያን መድሪስ” ላይ እጥፍጥፍ ሲል ድንቅ ይለኛል፡፡ አያቱም እጁን ስታሻሸው፤ ጸጉሩን ስትደባብሰው በአግራሞት ነበር የማዬው፡፡ አቤት የሁለተኛ ታናሽ እህቱ ቁንጅናናናናና………!! ጥርስ ምንድን ነው፣ ሳቅስ ምን የሚሏቸው አማልክት መልዕክት ስብሰብ ነው? እንዲህ ያለ መግነጢስ የምን ሃይል ነው…. ረህመት!!! ለኔስ በትዳር መስመር ‹‹ተፈጥሮአችን›› አግዶናል፡፡
በተደጋጋሚ ቅዳሜ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እቤታቸው እንሆናለን፡፡ ስጋ ይወዳሉ፡፡ በየሳምንቱ በግ ያርዳሉ፡፡ ‹‹ቢስሚላህ›› ተብሎ ይታረዳል፡፡ እቺ ቃል አንድን ፍጡር ከአንድ ሐይማኖት ወደ አንድ ሐይማኖት እንደምትቀይር ተረድቻለሁ፡፡ በቃ ‹‹ቢስሚላሂ!›› ሲባል ብቻ ያ በግ ሙስሊም ይሆናል!!! እኛ ቤት ደግሞ ‹‹በስመአብ›› ሲባል ክርስቲያን ይሆናል!! ዱለቱ፣ ወጡ፣ አጥንቱ፣ መረቁ፣ ቋንጣው፣ ሁሉም ነገር ሙስሊም ይሆናል፡፡ ለኔ ደግሞ ሽሮ ይሰራልኛል፡፡በቤታቸው ውስጥ በጣም ሻሂ ይወደዳል፡፡ ሲተኙ ብቻ ነው ሻሂ የማይፈላው ብል እያጋነንኩ እንዳይመስላችሁ-አይደለም!!! ሲተኙ ምድጃው ረመጥ ያዝላል፡፡ በቃ ያኔ ሻሂ የለም፡፡ ጧት ሲነሱ ረመጡ ወደ ‹‹ፍም እሳት›› ይቀየራል፡፡ ያቺ ኩስኩስት ተጥዳ ትውላለች፡፡ ስኳሩም አብሮ ነው የሚፈላው…..!!
አንድ ቀን ያጋጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ እነርሱ ስጋቸውን እየጋጡ፣ መረቃቸውን እየጠጡ፣ ለኔ ሽሮ ተፈልቶልኝ ራሴ አማስዬ፣ ዘይት አድርጌ፣ ጨው ጨምሬ መብላት ጀመርኩ፡፡ ስቀምሰው ስኳር ስኳር ይለኛል፡፡ ያው ከሙስሊም ቤት ያለው ምግብ ከኛ ቤት ካለው ጋር ስለሚለያይ በሚል እሳቤ ዝም ብዬ ስኳር በሽሮየን ጥርግ አድርጌ በላሁ፡፡ በሙስሊም ቤት ሽሮው እንዲህ ሆኖ የሚቀየር ከሆነማ ስጋው፣ ዱለቱ እና ቋንጣው እንዴት ጣእሙ ሊቀያየር እንደሚችል አሰብኩት!! ‹‹ቢስሚላሂ›› የማይቀይው ነገር ምን አለ? /ከብዙ ጊዜ በኋላ ሽሮው የሚፈላበት ውሃ ፤ሻሂ የሚፈላበት ውሃ መሆኑን ተረድቻለሁ/፡፡ የሚቀየር ነገር የለም…..???
የሸሕ ለጋስ ልጅ እንዲህ ነው፡፡ ቀይ፣ ያለ እድሜው ፊቱንና ደረቱን ጸጉር የሞላው፣ አፍንጫ ሞላላ፣ ረዘም ያለ ቁመት፣ መሃል ፒያሳ ላይ አቅፎህ የሚሄድ፣ የበዓሉ ግርማ መጽሐፍትን በቁጥር ያስነበበኝ፤ የእጅጋየሁ ሽባባው ዜማዎችን በዛች ፊሊፕስ ቴፕ ያሰማኝ፣ የአሰፋ ጎሳዬን አስተዋይነት በአዲስ አድማስ ያስተማረኝ… የሲቪክስ ትምህርትን ከፊዚክስ እንዳስበልጥ ያደረገኝ፣ መለስ ዜናዊን እንዳዳምጥ ያደረገኝ..ፖለቲካን እንድከታተል የገፋፋኝ…! ሙስሊም መጽሐፍትን እንድፈትሽ… ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምን ያስተዋወቀኝ… ቤተክርስትያን አብሮ ገብቶ የመከረኝ…. ኢትዮያዊነት ረቂቅ ትርጉም በተግባር ያሳየኝ ሰው ነበር- የሸሕ ለጋስ ልጅ!!!
የሸሕ ለጋስ ልጅ ከኛ ቤት ሲመጣ ከአባቴ ጋር የሚያወሩት ወሬ ይገርመኛል፡፡ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ጀብሓ ምናምን እተባባሉ የሚወያዩት ወሬ ዛሬም ላይ አይገባኝም፡፡ ሓይሌ ፊዳ ማለት እኮ…. ፊዲስት ታውቃለህ… ነገደ ጎበዜ ማለት እኮ የጎበዜ ጣፈጠ ልጅ ነው፡፡ የልጅ እያሱን መጽሐፍ ጽፏል…. እየተባባሉ ሲነጋገሩ ይሕ “ልጅ” እያልኩ እገረም ነበር፡፡ በልቤም የያዝኩት ያኔ ነው….!!!
አሁን የሸሕ ለጋስ ልጅ የሙስሊም መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ ውስጥ እንደገባ በአንድ ጋዜጣ ላይ ሙሉ ስሙን አገኘሁ፡፡ ምናልባትም ሙስሊሞች እስከ አያት ስማቸው ሊመሳሰሉ ስለሚችሉ ብዬ እንዳልጠራጠር / በቅንፍ ውስጥ የሸህ ለጋስ ልጅ/ ይላል፡፡
ልብ በሉ ይሕ ልጅ ከሕጻንነት ጀምሮ አብሮኝ አድጓል፤ ከመች ጀምሮ ‹‹ቢስሚላህ›› ብሎ ተሳልሞ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንደቀየረ አላውቅም፡፡/ተቀይሯል የሚል ዕምነት የለኝም- ዕውነቱም እንደዚሁ//
ከባርዳር ፖሊ ቴክኒክ ት/ት ክፍል በኬሚካል ምህንድስና የከፋተኛ ማዕረግ ተሸላሚ እንደነበር በእጄ የሚገኝ ምስክር ወረቀት ያሳየኛል፡፡
ጂጂ…. አዲስ አድማስ… በዓሉ ግርማ…. የሚጣፍጥ ሽሮ ወጥ…በርካታ እውነቶች በልቤ ውስጥ አሉ፡፡ አሁን ረህመትን የት ማግኘት እንደምችል አላውቅም፤ ባለፈው ከፍርድ ቤት ሲመለሱ በአረንጓዴ “ቸንቶ” ህዝቡ ሰላምታ ሲሰጣቸው ተገኝቼ ነበር፡፡ረህመትን ላገኛት አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ፊታቸውን ከሚሸፍኑት እንስታት ውስጥ ልትሆን እንደምትችል ገምቻለሁ፡፡ ሂጃቡ የጠቀመው ለወንዶች  ነው!!!!!!
የሸሕ ለጋስ ልጅ መቼ ነው አብረን ሽሮ የምነበላው፣ በኣየትህ የቆዩ ጨዋታዎች/ ትንቢቶች/ የምንሳሳቀው? ሻሂ ስናፈላ የምንውለው?  ጂጂን አብረን የምንሰማው? በአስመራ ምድር አብረን የምንመላለሰው…..በዓሉን የምነዘክረው?
…..አይ… ዘመን ከሚወዷት ባለቤት ጋር ብቻ አይደለም የሚለያዬው! ካደጉበት መንደርም ብቻ አይደለም የሚነጣጥለው፣ 23 ዓመት ከማፈቅረው አብሮ አደጌም ጋር ጭምር እንጂ…!!! 23 ዓመት!!!!!

ያንተው ረዊና ይልማ ኢብሳ!!

No comments: