የጥቋቁር አምላኮች ጥቋቁር ነጥቦች
‹‹‹‹‹‹‹ተስፋ በላይነህ›››››››
“መሀየሲያ”
ድምቡሽቡሽ ያለ የሚያምር፣ ከእናቱ
ማኅፀን ወጥቶ፣ አይኖቹ ጭምብስብስ፣ እጆቹ እጥፍጥፍ፣ ጥፍሮቹ ድብቅብድ ብለው አንድ ጨቅላ ይታየኛል፡፡ እግሩን ሲያንጠራራ አየሁት፣
እጁንም ብዕር ለማራዘም ሲከጅለው ተመለከትኩ፡፡ ከዛም አስነጠሰው፡፡ “አ..ጥሽሽ!!” ሰው ለምን ያስነጥሳል? ብዬ ልጠይቅ አሰብኩና
ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዳይወስደኝ በማሰብ ተመለስኩ፡፡
ነገር ግን ሰው ሲያስነጥስ “ይማርህ!”
እና “እደግ ተመንደግ!” ማለት የተለመደ ነው፡፡ ይሄ አዲስ የተወለደ ህጻንም ማንጠራራቱን አይቼ፣ ማስነጠሱን ተመልክቼ በርታ፣
እደግ ተመንደግ ማለትን ፈለግሁ፡፡ ይማርህ አንለውም ምክንያቱም የሰራው
በደል የለውምና!! እደግ ተመንደግ የምንለውም ካለው ተስፋ ሰጪነት አመለካከት እና አያያዝ ነው፡፡
ግጥምን ያክል ነገር እንደመተርጎም
የሚከብድ ነገር የለም ብሎ የግጥም መድብል የሚያሳትም ሰው ‹‹በር›› ላይ ቆሟል!! ማንም ሰው በራሱ ዕይታ ሃያሲ መሆን ይችላል
የሚል መልዕክትም ተጨምሮበታል፡፡ በጎ ነው፡፡ መሀየሲያ ገጽ ላይም ይሕንን ልንጽፍ ገደድን!! እደግ ተመንደግ ለማለት…..!
ስሜታችን ያዘዘንን መጻፋችን
አይጎዳም፣ አይጠቅምም፡፡ የተጻፈው ስሜት የሌሎችን ስሜት የሚነካ፣ የሚኮረኩር፣ ውበት ያለው ተፈጥሮ የሆነ ትላንትን የሚያስታውሰን፣
ዛሬን የሚነግረን ነገን የሚያመላክተን ከሆነ “ግጥም” ብለን እንሰይመዋለን፡፡ ግጥም [[ሳጥናኤል]] ነው የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ያለ ሙዚቃ መሳሪያ የሚያዜሙት በመሆኑ፣ ያለክንፍ ካጽናፍ አጽናፍ የሚከንፉበት፣
ጠሊቅ ስሜትን ልክ እንደ ጉድጓድ ውሃ ጭልፋ እየላከ የሚቀዳ፣ የሚያጠጣ፣ የሚያረካ…. ግጥምን ለመተርጎም ምንም እንኳ ሃያልነቱን
ብንረዳውም፤ POWER IS NOTHING WITHOUT CONTROL እንዲሉ… ሃያል ነገሮችን መግለጽ /መተርጎም/ ካልቻልን፣ አልተቆጣጠርናቸውም
አሊያም አላወቅናቸውም፡፡ እግዚአብሔርን የሚያክል ስም፣ እግዚአብሔርን የሚያክል ኃያል፣ ምጡቅ፣ ረቂቅ፣ ግዙፍ ነገር ማን ሊተረጉመው ይችላል??? እግዚአብሔርን ማወቅ
አሊያም መተርጎም ስላቃተን ይመስለኛል እንዲህ የምንወዛወዘው፡፡ ሁላችንም፡፡ እግዚአብሄርን ለመተርጎም አሊያም ለማወቅ አንድ ቃል
ብቻ እንደገለጸው ያውቃሉ? ፍቅር!!! እግዚአብሔርን የሚያክል ግዙፍ ምጡቅ ረቂቅ ነገር በፍቅር እንደተተረጎመም እናውቃለን!! እግዚአብሔር
ፍቅር ነው!!
ግጥም “ሳጥናኤል” ነው!!!
ሳጥናኤል መላዕክ ነው፡፡ በቀደመ ክብሩ የመጀመሪያ ፍጥረት፡፡ ግጥም ፍጥረት ነው፡፡ ሳጥናኤል ሐሳቡን ሲገልጽ እንደሌሎቹ መላዕክት
ማሲንቆ፣ በገና፣ እንዚራ፣ አታሞ አሊያም ሌላ መሳሪያ አይጠቀምም ነበር፡፡ ሳጥናኤል ግጥም ላይሆን ይችላል፡፡ ግጥም ግን ሳጥናኤል
ነው….፡፡
‹‹በኪሩቤል አበበ›› የተጻፈን
‹‹ጥቋቁር አምላኮች›› የግጥም መድብል ምናልባትም ራሱ ጸሐፊው እንድመለከትለት
እና ሐሳቤን እንድገለጽ የጠቆመበት መስመር ስለደረሰኝ፤ የእርስ በርስ መሄያየስ ጠቃሚ ነው በሚል ሐሳብ እሞነጫጭር ጀምሬያለሁ፡፡ እርስ በርስ መተያየት፣ መጠቋቆም፣ መሄያየስ እንዴት
ይጠቅም መሰላችሁ!!!!?
((((!i)))) በዚህ ቅንፍ
ውስጥ የምናገኛቸው የሁለት ጽንፍ ተቃርኖዎች የምድራችን ሁለንተናዊ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በጥቋቁር አምላኮች የግጥም መድብል ውስጥ
በተደጋጋሚ ተቀምጠዋል፡፡ ምልክቱ መቀመጡም ብቻ ሳይሆን በግጥሞቹ
ሐሳቦችም ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ‹‹ክፉን ማን ፈጠረው›› ‹‹መሪ ያጣ ግዛት››ን ያጤኗል!! ሰልፍ በሚለው ግጥም ላይም ታስቦበት
ይሁን ሳይታሰብበት !i ምልክቶች ተቀምጠዋል፡፡
ሴትና ወንድ፤ ጥቁር እና ነጭ፤
አንዱ መምህር ነው፣ አንዱ ደቀ መዝሙር፤ አንዱ ብርሃን ነው፣ አንዱ ጭለማ፤ አንዱ ሰጪ ነው አንዱ ተቀባይ፤ ዝርግ መስመር አለ፣
ክብ መስመር አለ፤ እሳት አለ፣ ውሃም አለ….ሰማይ አለ፣ መሬት አለ….ላይ አለ፣ ሐብታም አለ፣ ድም እንደዚሁ፤ ታችም አለ፤ ቀኝ
አለ፣ ግራም አለ!!!
ይሕ የምድራችን ዕውነታ ነው፡፡
የሚታይ የተረጋገጠ፡፡ ከሁለቱ ውጭ አለ ብለን የምናቀርበው እውነታ አለ?? ከብርሃን እና ከጭለማ ውጭ ሌማ ምን ምርጫ አለ?? ምናልባትም
በቀዝቀዛ እና በሙቅ መካከል ላይ ያለውን ‹‹ለብ ማለትን›› ብንጠቅስ በራድ ወይም
ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም
ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። የሚለውን ትልቅ ቦታ ልንሰጠው እንችላለን፡፡ እጅግም ጻድቅ እጅግም ሰነፍ
አትሁን ከሚለው ጋር ግን እንዳይጋጭብን፡፡ አሊያም በሒሳብ
ግንዛቤው በነጋቲቭ አንድ እና በነጋቲቭ አንድ መካከል የሚኖውን አልቦ/ዜሮ/ን በምን መልኩ ነው የምንረዳው?
እንደኔ የአረዳድ ልኬት እና
የእምነት ልቀት/ ደረጃ/ መሰረት ከሁለቱም ውጭ ሌላ ምርጫ እንደሌለ ነው፡፡ አንድም ሲኦል ነው አንድም ገነት፡፡ ከሁለቱም ውጭ
ህላዌ ይገኛል ብዬ አላምንም፡፡ አልገምትም፡፡ በሩቅ ምስራቃዊያን ፍልስፍና እና እምነት ምናልባትም የህንዳዊያን ቁጥር ዜሮ/ ምንም/
ባዶነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ሲተረጎም አናያለን፡፡ ዩኒቨርሱ የጥቁር እና የነጭ የጭለማ እና የብርሃን መስተጋብር እንደሆነም በዪን
እና ያንግ / yin and yang/ ኮንፊስየስ ፍልስፍና የተገለጸ
ነው፡፡ ‹‹ምንምነት›› አለ ቢባልም አንኳ የሌለን ነገር መግለጽ አንችልም ብዬ አምናለሁ፡፡ መግለጽ የለብንም የሚል እምነትም አለኝ፡፡
ከቡድሃ እምነት ተከታዮች ጋርም በተደጋጋሚ ተወያይተናል!!!! እስኪ አንድ ሐሳብ ከግጥም እንምዘዝ…
‹‹እናም ክፉና ደግ ያንድ እናት
ያንድ አባት ልጆች ሆነው ሳለ
ያንን ደግ ወንድሙን ከሞት ከታደገ
በፍቅር ካዳነ
እሱ ለምን ሲኦል ከጽልመት ይጣላል
ክፉ እየተባለ?›› ‹‹መፅሀፍ ላጣቅስ›› ገጽ 23
ቀጥሎም ‹‹መሪ ያጣ ግዛት›› በገጽ 31 ላይ
‹‹ገነትና ሲኦል በሰማያዊ ቤት
አሉ ብለውኛል
ለክፋትህ ቤትህ ገሀነም ነው
ብለው አስፈራርተውኛል፡፡
እኔ ግን ፈጣሪ
በፈጣራት ስጋ የሚጨክን አንጀት
ያለው አይመስለኝም
ለሞተላት ነፍሴ እንጨት በመቆስቆስ
ለእሳት አይሰጠኝም፡፡
ስለዚህ ፈጣሪ የሲኦል ገዢ ነው
ቢሉኝ አላለቅስም
የታበየ ቃል ነው አምላክ በልጁ
ላይ እሣት አይለኩስም!››
ስንኞችን ቀጠል ያደርግና፡-
…
‹‹ስለዚህ በሲኦል ምንድን ነው
ካላችሁ ዕድሌ የኔ’ጣ
አምላክ ክፉ ሆኖ ሳጥናኤል ካልራራ
ከተንኮል ካልወጣ
መቃጠል አይኖርም ጥሩ ወይም
መጥፎ ያልሆነ እስኪመጣ!›› በሚል ይቋጫል፡፡
የኔም ማጠቃለያ እና መቋጫ የሚሆነው
እንዲሁም ግጥሞችን የመመልከት ድርሻዬ ግጥሞቹ ካዘሉት ጽንሰ ሐሳብ ጋር ለመደጋገፍ ነው፡፡ የስነ-ጥጽሑፉን ግምገማ ለባለሙያ በመተው፡፡
ለገጣሚው ማስረዳት የምፈልገው ነገር በአጭሩ ፡- የሲኦል እና የገነት እጣ ፈንታ በምርጫ የሚገኝ እንጂ አንዱ በአንዱ ላይ አስገድዶት
የሚደረስበት ቦታ አይደለም፡፡ ሳጥናኤል መርጦ ነው ሲኦል የገባው/ ሲኦል ማለት እግዚአብሄር የሌለበት ቦታ ነው፡፡ ስለዚህ አንተ፣
እኔ እሷ ሁላችንም የሲኦል እና የገነት መግባታችን ሁኔታ በምርጫ የሚወሰን ነው፡፡ ወደ ህግጋቱ አልገባም፡፡
አጫጭር ግጥሞች በዝተዋል፣ ምጡቅ
ሐሳብ ያዘሉ ግጥሞችም አልጠፉም /‹‹ስንት ጅቦች አሉ››/ /‹‹ፀጥታ››/፤ ባዶ ግጥምም/‹‹ንጹህ ነጭ ወረቀት››/ አረንጓዴ…
ቢጫ… ቀይ… ቫላንታይን ደይ? እና መሰል ግጥሞችን መመልከት እንችላለን፡፡
ገጣሚው የግጥምን ትርጓሜ እስኪያገኝ
ድረስ፣ የኃያሉን ኃያል ምስጢር፣ መዳረሻ እስኪቆጣጠር ድረስ ሁለተኛውን ስራ ሰርቶ እስከሚያሳየን እንጠባበቃለን፡፡ በተለይ የግጥምን
ትንታኔ ወይንም ትረጉም እስኪያገኝ ድረስ ብዙ ቢተጋ ወንድማዊ ምክርን እለግሳለሁ!!!
‹‹እውነትን እንጂ ውሸትን እንዳልጣፍኩ እምላለሁ›› የሚለው ‹‹እምነትን››
እንጂ ተብሎ ቢታወስ እጠቁማለሁ፡፡ ‹‹ለመማማር እንጂ ለመወቃቀስ ስንኞችን እንዳልሰደርኩ ቃል እገባለሁ›› በሚለው መሰረትም እኔ
ይሕንን ሐሳብ የገለጽኩበት ምክንያቴ ነው፡፡
‹‹ኩሩቤል አበበ›› የሰማዩን
ክፉና ደግ አሊያም ሲኦልና ገነት ጥምረት ተረድቶ አስቦትም ይሁን ሳያስበው በምንምነት ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንዳይሆን ለማስረገጥ
እፈልጋለሁ፡፡ ይሕ በአሁኑ ሰዓት የምድራችን ተላላፊ በሽታ ነውና፡፡
ጠፍተናል፡፡ ወደ የትም እንዳንሄድ፡፡ የትም ተንጠልጥለን እንድንቀር እየተደረግን ነው፡፡ Spiritual loss!!
ከማይታየው እና ከማይጨበጠው
የጽንፍ ጠርዛት ጋር ግብ ግብ ከመግጠም በምድር፣ እዚሁ ቅርብ ሳንሄድ ‹‹ጥቋቁር አምላኮቻችንን››ጋ ብናጤን የተሻለ ይመስለኛል፡፡
ዐለማችን ‹‹እውነ›› እየነገረችን ነው፡፡ ያ ‹‹እውነት›› ምን ያክል እውነት ነው? በሰማያት ያሉትን እውነቶችን ወደ ምንም ከምንቀይራቸው፤
ምድር ላይ የተቀበልናቸውን እውነታዎች ብንመረምር አይሻልም………??
ቀላል ምሳሌ ላንሳ፡- ማንዴላ!!!!!!????? ማዲባ የእውነተኛ የነጻነት ተምሳሌት ነውን? የኤፍሬም ስዩምን ማንዴላ ውብ ግጥም ጋብዤ ልሰነባበት፤ በሬ ክፍት ነው!!
ማንኳኳትም አይጠበቅብህ….! አግኝታችሁኝ ይሆን፣ አጥታችሁኝስ ይሆን… ወይስ ምንም?
No comments:
Post a Comment