May 10, 2014

የቄሳር ሰይፍ፡-

የቄሳር ሰይፍ፡-
በውቀቱ ስዩም፣ አገኘሁ አሰግድ፣ በስነጽሑፍ ትሩፋታቸው ተለይተው የሚታዩኝ ሰበዞች

ችግር እንዳለብኝ የሚነግሩኝ ሰዎች አሉ፡፡ ታዋቂውን ገጣሚ በውቀቱ ስዮምን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ወቅሰሃል፣ ይስማዕከ ወርቁን ገስጸሃል አልፈህ ሄደህም ዲየቆን ዳንኤል ክብረትን ተቃርነሃል በሚል፡፡ ፕር መስፍን /ማርያምን ትከተላለህ ብሎ ከወቀሰኝ በኋላ ደግሞ "ኄዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛ ናት" የሚለውን የፕሮፌሰሩን ጽሑፍ ስቃወም ግራ የተገቡብኝ ጥቂት አልነበሩም፡፡ በማናቸውም ጊዜ ከተፈጥሮ ያፈነገጡ፣ ማህበራዊ እሴቶችን ከስር መሰረት የሚያናጉ ሐሳቦች ተድበስብሰው እነዲያልፉ አልፈልግም፡፡ ሀይማኖትን/እምነትን መንካት የለብንም፤ የግለሰቦችን ሐሳብ መሰረት በማድረግ ግን የተሰማንን ልናካፍል፣ ልንግባባ እና ለተደራሲያኑ ሰፊ ሜዳ ልንሰጠው ግድ የሚያስብለን ተፈጥሮአዊ ማንነታችን አለ፡፡ ለምሳሌ በውቀቱ ስዩም በእዮብ መኮንን ሞት የተሰማውን ስሜት ሲያካፍለን በአነስተኛ ጽሑፍ ብዙ ነገር አስነብቦናል፡፡ በእርግጥ በውቀቱ ስዩም ጥልቅ እይታ ያለው በግንቦት 20 እና በመስከረም 2 ዝናሮች በተበሳሱ ቀዳዳዎች ውስጥ ሆኖ ለዘመኑ የተሰጠ ጸሐፊ ነው፡፡ የግጥሞቹ ስንኞች አንድ ክረምት ያሻግራሉ፤ ከጥቢ ጸደይ ከበጋ ክረምት ያፈራርቃሉየክረምት ጸሐፊ ይመስለኛል፡፡ልረሳሽ እየጣርኩ ነው!” የሚለውን ግጥም ስንቶቻችን ተደምመንበታል?
                                                          **--**
‹‹ኢዮብ!!! በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለ ግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብየ እንደማምን ታውቃለህ፡፡ይሁን እንጂ ለዛሬ እንኳ፣ የኔ እምነት ከሽፎ ያንተ እምነት እውነት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡በምድር ለገጠመህ መራራ እጣ ሰማያዊ ካሳ (ጉማ) እንድታገኝ እመኛለሁ፡፡››
   ይህንን ሐሳብ ስንመለከት ምን እንገነዘባለን ‹‹በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለ ግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብየ እንደማምን ታውቃለህ፡፡››
                                                           **--**
ላባቴ
ሰው ብቻ አይደህም፣ ካፈር ወጥተህ ላፈር
መላክ ነህ፣ ሉሲፈር
ክብርህ ማንነትህ ፣ባመጽ የሚታፈር፡፡
ሉሲፈርን ልብ ይበሉ!
                                     **--**
ገንዳውበሚለው መሳጭ ግጥሙ ላይ
‹‹የሰማይ አማልክት አላጋጭ ቀልደኛ
ራበን መግቡንስንላቸው እኛ
ብዙ መና ጋግረው ሲያዘንሙ ከሰማይ
የእኛን ጎታ ስተው ከተቱት ገንዳው ላይ::

ከቶ ለምን ይሆን
ያፍሪቃ ህፃናት በደቦ ሚያልቅሱ
የወተቶች አዋሽ - የርጎ ሚሲሲፒ - በበዛበት ዓለም - ጤዛ የሚልሱ
የሹራብ ተራራ - የቡልኮ ጋራ - በበዛብት ዓለም - ጭጋግ የሚለብሱ
የምድር ጠቢባን
ለዚህ ግዙፍ ምስጢር - መልስ አገኝ ብላችሁ - ጠፈር አታስሱ
አሜሪካ ያለው - የቆሻሻ ገንዳ - ግጣሙ ሲከፈት - ወለል ይላል መልሱ::››
‹‹የሰማይ አማልክት አላጋጭ ቀልደኛ ›› ለዚህ ግዙፍ ምስጢር - መልስ አገኝ ብላችሁ - ጠፈር አታስሱ
አሜሪካ ያለው - የቆሻሻ ገንዳ - ግጣሙ ሲከፈት - ወለል ይላል መልሱን -ልብ ይበሉ!!
 **--**
በርካታ ስራዎችን እነደ ሰበዝ እየመዘዝን ብንመለከታቸው ይህ ግድግዳ ላይበቃን ይችላል፡፡ የተልባ ፍንጣሪ ያክል የሚሰማን ሰዎች ልንኖር እንችላለን፡፡ በሰማያዊ አይን እይታ ግን እየተቆላ ያለው ተልባ ሳይሆን ፈንጅ ነው! የፈንጅ ፍንጣሪ የሚያደርሰውን ጉዳት ፈንጅ አምካኙ መምከር አልተቻለውም….! "ከስህተቱ የማይማረው ፈንጅ አምካኝ ብቻ ነው" የሚለውን አባባል ልብ ይሏል!!
ይስማዕከ ወርቁ አስማታዊ ልማትን የሚሰብክበትን ክብር ቃል/ክቡር ድንጋይ ስንቶቻችን ተመልከተን ተገነዘብን? የንጋት ኮከብን እነደ ዘንዶ ሲተጣጠፍ ተመለከትኩትእያለ ወደ ውሻ የሚቀየርበትን ሥራ ስንቶቻችን ትራስ አድርገነዋል?
አሁን ደግሞ ለእነዚህ ሁሉ አብልጬ የምቀርበው ወጣት ጸሐፊ አገኘሁ አሰግድ በአማርኛ መሪነቱ አዳዲስ ምጸቶችን በወግ እያዋዛ ሲያቀማምሰን ደስ እያለን ነው፡፡ በየመሃሉ ያሉትን ፍንጣሪዎች ልብ ይበሉ!! አምላክን መዝለፍ/በአምላክ መዘበት በስነጥበቡ አለም ውስጥ እንደ መታወቂያ ሆኖ ተለጥፎ ጭብጨባ ሲበዛልን ወደ ከፍታው እየከነፍን የሚሰማው ስሜት “”ከፍ ከፍም እላለሁየተባለውን የዲያቢሎስን ውድቀት እንደ መሪ መፈክር ማነገብ እየታየ ነው፡፡ የግል ጥላቻም ሆነ ተቃርኖ የለኝም ብዬ ከመጽሐፍ ላይ መዳፌን አስቀምጬ እምላለሁ፡፡
 **--**
 የክርስቶስን መሰቀል ከእኛ የፖለቲካ መከራ ጋር ካያያዝነው፤ እንደ ክርስቶስ ተሰቅለናል ብለን የሚበላ ዳቦ አጥሮናል- ነጻነት ተነፍገናል- በፖሊስ ተደብድበናል- ክርስቶስን ሆነናልየሚለው አስተሳሰብ በሚገባ ሊጤን የሚያሻው የዘመነኛ ስነጽሑፍ ከታቢዎች ወንድማዊ ምክር ነው፡፡ የቄሳርን ለቄሳር የሚለው መሰረታዊ ቃል ፈጽሞ አልገባንም! እናምታታዋለን….

‹‹መፅሀፉ፣የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነውይላል። እኔ ግንየጥበብ ሁሉ መጀመሪያ፣ መጨረሻውም ሁሉንም መፍራት ነውብያለሁ። ፈርቻለሁም። እግዜር ሰይፍ የያዙ መላዕክት አሉት። መንግስት ዱላ እና ጠመንጃ የጨበጡ ፌደራሎች አሉት። ስለዚህ እግዜርንም መንግስትም መፍራት ጥበብ ነው። የሰው ልጅ ከላይ በሰይፍ ከታች በዱላ የታጠረ ምስኪን ፍጡር ነው።›› ከሚለው ጽሑፍ ውስጥ የመላዕክት ሰይፍ የሰውን ልጅ ሊንከባበኩ የተቀመጡ ዘላለማዊ ቀኝ እጆች መሆናቸውን አለመገንዘብ ብቻ አይደለም መምታታቱ፤ በሰይፍ ቢሆንማ ክርስቶስን ሊሰቅሉ ከመጡ ካህናት አንደኛው ወታደር ጀሮውን /አገኘሁ አሰግድ በተረዳው ሰይፍ/ ሲቆረጥ የክርስቶስን መልስ አገኘሁ አልሰማውም አሊያም ሰምቶ አልተረዳውም አሊያም ተረድቶ ሰርዞታል!! "በሰይፍ ቢሆንማ አባቴ የሰማይ መላዕክትን ያመጣልኝ ነበር" የሚል መልዕክት መቀመጡን ካለመረዳትም ባሻገር የጦር እቃን ልበሱ በሚለው መልዕክት ውስጥ ሰይፍ ማለት በኤፌ 617 `የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው` ተብሎ መጻፉን አለመገንዘብ ከዚያም የቄሳርን ለቄሳር አለመለየት በሚከሰተው ክፍተት ወዳቂው ብዙ ነው፡፡
 የቄሳር ሰይፍ ከእግዚአብሔር መላዕክት ሰይፍ በእጅጉ ይለያል፡፡ በአንድ ከተረዳነው ግን በውደወቀት ጥልቅ ባህር ውስጥ ነን! ነጻ ከምናወጣው ይልቅ በነጻ የምንቀጣው ይበልጣል! በሰፊው ሜዳ ተገናኝተን በሰላም በፍቅር እና በመደማመጥ እንዲሁም ያለነቀፋ ነውራችንን ብንነጋገር ውጤቱ አንድነት ነው! ለማለት የፈለጉት ነገር የተገለጸለት ካለ ቢያግዘኝ በቀና መንፈስ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ምናልባትም ተሳስቼም ከሆነ፤ የተሳሳትኩት ባይኖርም የሳትኩት ካለ ለመደጋገፍ ወደ ቀጥተኛው መንገድ እንድንሄድ ተማጽኖዬ ነው፡፡ መደጋገፍ ዋነኛው የሰው ልጅ የመኖር ትርጓሜ ውጤት ነው!! ይኸው ሜዳው….! የቄሳር ሰይፍ የለበትም…!!
የቄሳር ሰይፍ፡-

በውቀቱ ስዩም፣ አገኘሁ አሰግድ፣ በስነጽሑፍ ትሩፋታቸው ተለይተው የሚታዩኝ ሰበዞች

No comments: