Apr 26, 2014

እውነት በዚህች አለም

***እውነት በዚህች አለም***

“ሳራ” ከስራ ወደ “ሳር” ቤት፡-
በተማሪዎች ማመላለሻ ውስጥ እንገኛለን፡፡ አንዲት የ8ኛ ክፍል ውብ ተማሪ- ኢትዮጵያዊ ውብ ቀለም፤ ወደ ከተማው ታማትባለች፡፡ ከገጠር ከመጣች 4ኛ አመቷን ግንቦት 20 ላይ ታከብራለች፡፡ መሄድ መሄድ አሰኝቷታል፡፡ ከተማው ለእርሷ- የውበት መደምደሚያ የእውነት መቋጫ መሆኑን ትካዜዋ እና የአይኗ ሳቅ አሳባቂ ነው፡፡ ማስቲካዋ ከሜይሊ ሳይረስ የአምልኮ ዝማሬ አልፎ  ለሾፌሩ የአስረሽ ምቺው ሩምታ ነው፡፡ ከተማውን ታማትባለች፡፡ መሄድ መሄድ ያሰኛታል፡፡ ከተማው የእውነት መስሏታል፡፡ ዓለም የእውነት መስሏታል፡፡ ዓለም እውነት እየመሰላቸው ስንቶች ተሸኝተዋል? ስንቶች ተሰጥተዋል፡፡ ስንቶች ነፍሳቸውን አጉድለዋል፡፡ ጸሐዮቻቸውን ዐጨልመዋል… ከአለም ምን ይገኛል? እኔም የሌላኛውን ጠርዝ መስኮት ተደግፌ ወደ ውስጠኛው ከተማ ተምዘግዝጌ ይህንን እውነት መሳይ የጥጥ ፈትል ባዘትኩ… እውነት እምነት ነው፤ በፈተልነው ልክ የምንለብሰው…በዘራነው ልክ የምናጭደው፡፡ በበግጥም ፈተልሁት- ልበሱት፡፡ በቅኔ ዘራሁት-አጭዱት!! እነሆ….

አውነት በዚህች አለም
እንዲህ ተቀልማ በጽልመት ተቃርማ
በጠዋት ታጅባ- በብኩን ቀን ታማ…
በፍጥረት ግብግብ በአንድ አይነት መንጋ
በጎልያድ ቁመት በዳዊት ጽኑ ልብ በጨቅላነት ለጋ
በውሸት ብልጥነት- በእውነት ሞኝነት- ሌሊቱ ሊነጋ!!
ሲወጡት ሲወርዱት የመንጋት የመምሸት
የመወለድ መሞት በድንግዝግ ማየት
እውነት ማለት? እውነት ማለት?
እውነት በዚህች አለም
በጨለማ መሃል ጸሐይ እንደማትቆም
በጥቁር ህዝብ ዓለም ነጩ እንደማይተም
መዳረሻው ያው ነው የሁሉም ቀይ ደም!!
የጥላ መፈጠር የልዩነት ቀለም
የጸሐይ ክበቧ የኦርዮን ጠልሰም
በማንም አይቆምም በማንም አይደምቅም!
የምድር ፍጥረታት እነኚያ የቆሙት
እኛን ሊያደምቁ ነው ሌት ተቀን ሚዞሩት..!?
አንቺ ታናሽ ሴት ልጅ- ውበትሽ ሚያስፈራ
ለስጋና ለነፍስ ህይወት የሚዘራ
በመስኮቱ ዘልቀሽ ስታይ ከተማውን
አዲስ ዓለም መስሎሽ ስትሰጭ ትካዜውን
ተመስጠሸ ነበር ልታይ ከተማውን
አማትበሽ ልትገቢ ልትሸጭ ማንነትሺን
ወንዝ ልትሻገሪ ሊከብር አባትሽ ልትከፍይ ስጋሽን…!!
የባቡሩ መንገድ፤ የቀለበት ጉዞ፤ የህንጻው መደቀን
የምጣኔው ማደግ የህዝቡ መሰልጠን
ዕዳ ነው ይህ አለም ፍርሃት ሰቀቀን-
ማበድ ነው መቅበዝበዝ ዘመኑ መሰይጠን!
በውስጥሽ ሳታይ ሳትመለከቺ ያን ውብ ውበትሽን
የግዜር ውብ ፍጥረቱ ዓርዓያ ገጽሽን
ሳትመሰጪበት-ባንቺ ውስጥ ያለውን ረቂቅ አምሳሉን
የመኖር የመሞት የመሄድ የመምጣት የህይወት ሚስጥሩን
ተመለሽ… ተመለሽ ካሳብሽ ፈቀቅ በል ትካዜ
በኋላ ሞት አለው የማያልቅ ኑዛዜ!!
እውነት በዚህች አለም
እንደ ጤዛ በርታ ወዲያው የምትጨልም
እንደ ውብ አበባ ወዲያው የምትከስም
እንጉዳይ ስስ ቀለም- ብናኝ እንደ አረም
እንዳትጎዳኚው ክፉ ይህ አለም!!
አብሪ ነሽ ለአለም- በራስሽ ክበብ ስር እልፍ ለዝንት አለም
እንዳትቆራኚ ከዚህ የወረዛ የትንፋሽ ልም ቀለም
ታይቶ የሚጠፋ ውብ መሳይ ቅል አለም!!
ውብ ከተማ አለልሽ ወደ ውስጥ ሲታለም…

                                                     *ተስፋ በላይነህ*

No comments: