Apr 7, 2014

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!
በተስፋ በላይነህ

ክፍል -1
   ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ ለብዙ ቀናት ተሟግቻለሁ! “ጽሑፉንስ ጻፈው ግን አደራ እንዳታወጣው!” ይለኛል አንደኛው ተሟጋች፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ በስም ማጥፋት ወንጀል!” ተብለህ እነዳትከሰስ፡፡ ሌላኛው ተሟጋች ደግሞ “አንተ ምን ባይ ነህ የሰው ስም ጠቅሰህ አንድ የባለ ረዥም ባለታሪክን አገር ታሪክ መክሸፍ ከጥቂት የግለሰቦች ስብዕና ጋር አያይዘህ የምትለጥፈው” ይለኛል፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ኧረ እባክህ አርፈህ ተቀመጥ!” ብሎ የተለመደውን ምክንያት የለሽ ክርክር ያቀርብና ሊሞግት ይቃጠዋል፡፡
  ምክንያት የለሽ ሙግት ደግሞ ከሰነፎች ልብ የሚፈልቅ ኢትዮጵያን ለዘመናት ያቆረቆዘ የታሪካችን ውድቀት ምክንያት ነው ብዬ ለመወሰን ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ “ተማርን” በሚሉት የኢትዮጵያ ዜጎች/ መሪዎች/፡፡ ያለምክንያት ተሟግቶ አለማመን፣ አለመተማመን፣ መሸነፍን አለማመን ማሸነፍን ብቻ ማመን ደግሞ ሌላኛው ደዌ! ክፉ መርዛማ ደዌ ነው! የመክሸፍ ሸክሞቻችን ናቸው፡፡
አንድ ፈላስፋ እንዲህ አለ፡፡ “እውነትን ከያዝህ ለክርክር አትቸኩልም፣ ከተከራከርክ ግን አትሸነፍም፡፡” ድንቅ አባባል! በብዛት የሚከራከሩ ሰዎች ውሸተኞች ናቸው፡፡ ሁሉም እውነተኛ ቢሆንማ ክርክር የሚባል ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ አንድ ውሸት ግን ስትመነጭ በብዙ እውነቶች ውስጥ ተደንቅራ ታከራክራለች፡፡ እውነተኞች ግን አሸናፊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡፡ ለክርክር አይቸኩሉም፤ ከተከራከሩ ግን አይሸነፉም፤ እውነት አትሸነፍም! እውነትን ለማወቅ ደግሞ አውቀት ያስፈልጋል፡፡ እምነትም እንደዚሁ፡፡ እውነት እና እውቀት ያንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ ናቸው፡፡ በሌላኛው ገጽታ እምነት አለ፡፡ የሚታየውን ተራራ አይቶ መኖሩን ማወቅ እውቀት ላያስፈልገው ይችል ይሆናል፤ መኖሩንም መተማመን ይኖርብናል፡፡
ውሸት ተጋንና፣ ተበራክታ፣ ተደላድላ ተቀምጣ ስትታይ፤ ቀስ በቀስ እውነት ለመምሰል የምታደርገውን የውሸት ህይወት የሚመለከቱ እውነተኞች ዝም ማለት አይችሉም፡፡ በተፈጠረው የውሸት ህይወት ምክንያት ብዙ ፍጥረታት ውሸቱ እውነት መስሏቸው ተቀብለውት ስለሚኖሩ እውነተኞች ይነቀፋሉ፡፡ ተከራካሪ ይባላሉ፡፡ ነገረኛ፣ አደናጋሪ፣ ጠብ አጫሪ ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ እውነትን ለማሳየት ሲሉ ብቻ ከብዙ ምድራዊ ጥቅማጥቅሞች ይገለላሉ፡፡ በጥቂት ሰዎች ዘንድ ግን ይታወሳሉ፡፡ ይህንን ምድር የሚገዙት እና የሚመሩት ግን ውሸተኞች እንጂ እውነተኞች ስላልሆኑ አለም የምትመራው በውሸተኞች መሆን የጀመረው ዓ/ም ተብሎ ከታወጀበት ዕለት ይመስለኛል፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ዓ/ም ብለን የምንጠራው ላመኑባት፣ ለተከተሏት እና ለተገበሯት ብቻ ነው፡፡ ንጉሱ ክርስቶስ ጌታ ቢሆንም፤ የዚህ አለም ገዢ ግን ሰውን እንደ መልኩ እና እንደ አሻራው ለያይቶት ይገኛል፡፡ ብዙኃኑ   በተንኮለኞች እና በውሸተኞች እንዲመራ አድርጓል፡፡ አለም የምትመራው በውሸተኞች ነው፡፡ ይህንን ካላመናችሁ፤ ይህንን ጽሑፍ ባታነቡት እመርጣለሁ፡፡ አለም የምትመራው በጥቂቶች እጅ መዳፍ ተጨፍልቃ፤ በተንኮል እና በሸፍጥ  በተመረዙ ሴረኞች፤ በሆዳሞች እና የሰውን ልጅ ሰብዕና ለማኮላሸት ሌት ተቀን በሚንደፋደፉ ሸረኞች ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ካልተገነዘቡ ይህንን ጽሑፍ እንዳያነቡት፡፡ ካመኑበት እና ከገባዎ ግንማንበብዎን  ይቀጥሉ፡፡
እየቀጠሉ ከሆነ አምነውበታል ማለት ነው፡፡ ሳያምኑበት የሚቀጥሉ ከሆነ እየዋሹ ነው ማለት ነው፡፡  ራስዎን አይዋሹ፤ ራስን መዋሸት ዋነኛው የክሽፈታችን ምንጭ ነው፡፡ ራስን መዋሸት አንድም ካለማወቅ ነው አሊያም ከተንኮል ነው፡፡
የዚህን ጽሑፍ ርዕስ የመረጥሁት ባሳለፍነው ዓመት በወጣ መጽሐፍ ላይ ለተሰጠ ምላሽ ሲብላላ ቆይቶ ለመጠጥነት የደረሰ “መጠጥ” ነው፡፡ እውነተኛ መጠጥ በጊዜ ሲብላላ ጣፋጭ ይሆናል፡፡ አንድም መድሐኒት፤ አንድም አስካሪ!
እውነት እንደሚያሳምም ባሳለፍናቸው የስራ ጊዜያት ሳንገነዘበው የቀረን አይመስለኝም! አውነት ያሳምማል! ለውሸተኛሞች አውነት አስካሪ መጠጥ ነው! እውነትን ለሚሹ ግን መድሐኒት፡፡ እውነተኛው ክርስቶስ በአንዳንዶቹ እንደ “ጋኔላም” ለምን ታዬ? ለአንዳንዶቹ ደግሞ ትንሳዔ ለምንስ ተባለ?  እውነትን በአይነ ልቡናቸው ስላሳያቸው አይደለም የስቅላቱ መንስዔ?!
መጽሐፉ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፤ ብዙዎችን አነጋግሮ አልፏል፡፡ ታዲያ ላለፈ ነገር ምን አስጨነቀህ? ምንስ አስቀባጠረህ እንዳትሉኝ እሰጋለሁ፡፡ ካላችሁ ደግሞ ይህንን ጽሑፍ መቀጠል የለብዎትም ብዬ ካሳሰብኩዎ አንዱ ነዎት ለማለት ይዳዳኛል ፡፡ መጽሐፉ ከወጣ ከ365 ቀናት በላይ ከማሳለፉም በላይ፤ ዲ/ን ዳንኤል በጡመራው የሰጠውን አስተያየት በማየት የተሰጡትን አስተያየቶች ብዛት እና ይዘት ስንመለከት ዝም እንደንል አይገፋፋንም፡፡
ቀጣይነት የሌለው ውይይት፤ ቀጣይነት የሌለው ሃሳብ መተማመኛ የሌለው ውይይት “ክሽፈትን” እንደሚያስከትል ግልጽ ነው! “መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ” የነገሰበት ምክንያት ነው የውይይታችን መሠረት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መክሸፍን እንደምን ተሸከምነው!? ሰባኪው ሰለሞን በዘመኑ እንዲህ ሲል መሠከረ፡-
ከጸሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዥ የሚወጣ ስህተት ነው፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ፡፡
መክብብ 10፡6
   የትላንቱ ታሪክ በዛሬ ተዘግቦ፣ በዛሬ ተጠንቶ፣ ተወያይተንበት የጠራ እውነት ላይ ካልደረስን ውሸታሞች ነን ማለት ነው፡፡ አሊያም የተጣራ ታረክ በዘጋቢው አልደረሰንም ማለት ነው፡፡ አሊያም አልተደማመጥንም፡፡ የኳስ ጨዋታ ዘጋቢ የተሳሳተ ዘገባ ቢዘግብም፤ ኳስ ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢዶልትም፤  ተጫዋቾች የተራገጡበት አውላላ ሜዳ ከተገኘ፤ ሜዳው ቢጋጋጥ፤ ቢላላጥ ከጨዋታው ተመልሰው የተገኙ ተጫዋቾች ቢገኙ፤ ተጫወትን ብለው ቢዘግቡ ሆኖም ዘጋቢ የተባለው /“ኮሜንታተር”/ አሁንም ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢያነበንብ… ኳስ ጨዋታው እና ዘጋቢው ምንና ምን ናቸው፡፡ የኳስ ጨዋታ ዘጋቢው ከዘመናት በኋላ የዘገበውን መረጃ ብናገኘው ከትክክለኛው የኳስ ጨዋታ ጋር ባይገናኝ እና ትውልድ ግን የሚሰማው ይህንን የተሳሳተ መረጃ ቢሆን… ይህንን ሃሳብ ከታሪክ ዘገባ እና ዘጋቢዎች/ጸሐፊዎች/ ጋር አገናኝተው የራስዎን ሃሳብ ይውሰዱ እና ይመራመሩበት፡፡ ልታግዙኝም ትችላላችሁ፡፡ /ወደኋላ እንመለስበታለን፡፡/
  ትላንት እኮ ነገ ነበረ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ከሆነ በኋላ አልፎ ደግሞ ትላንት ሆኖል፡፡ ቀናትን በነገ፣ በዛሬ እና በትላንት መከፋፈሉ እንደ እኔ እይታ ከስህተት ለመማር ብቻ ይመስለኛል፡፡ አንድ አባባል አባባል እጅጉን ይማርከኛል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“የምጽአት ቀን ለምን እንዲህ ረዘመ?” ሲባል
“ለንስሃ!” የሚል መልስ ያስደስተኛል፣ ያረካኛል፣ ያሳምነኛል፣ ያጽናናኛል፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ ስማር ለነገ የተሻላ ስለምሆን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ አልፎ ትላንት ሲሆን  ከዛሬው ትላንትና እንድማር ስለሚረዳኝ ዛሬ ላይ መሆኔ እድለኛ ነኝ! ዛሬ የንስሃ ቀን ናት! ዛሬ የመዳን ቀን ናት! ነገ የምጽአት ቀን ናት ምክንያቱም ማንም ስለ ነገ እርግጠኛ የሚሆን የለምና፡፡ ሞት መቼ እንደሚወስደን ስለማናውቅ ፤ እንደ ሌባ ባልታወቀ ሰዓት እንደሚመጣ ተነግሮናል፡፡ ዛሬ ማለት ደግሞ አሁን ማለት ነው፡፡ ተደጋጋሚ አሁን /ንስሃ/ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው! እነዚህ ተደጋጋሚ ዛሬዎች ደግሞ ትላንትን አሻሽለው ነገን ፍንተው አድርገው ካላሳዩን እነዴት የተሻሉ ይሆናሉ? ስለዚህ አሁን የትላንቱን የምንጨነቅበት፣ የምንዋጋበት፣ የምንጨቃጨቅበት እና ቂም የምንያያዝበት ሳይሆን የምንማማርበት፣ የምንወያይበት፣ የምንለወጥበት እና ንስሃ የምንገባበት ስህተታችንን የምንናዘዝበት ሊሆን ይገባል፡፡ “ትላንት ያልዘራው ዛሬ አይበቅልም፤ ዛሬ ያልተዘራው ነገ አይበቅልም” በ“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” /ገጽ 51/፡፡
በዚህኛው አንቀጽ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የዛሬ ዓመት ለወጣ ጽሑፍ አሁንም ምለሽ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡ ያስገደደኝ ቂም አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ጥላቻ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ክርክር መውደድ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ አውነትን ማምለኬ ነው፡፡ የማመልከው አውነት ራሱ ይፍረድብኝ፡፡
 ለ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ ምላሽ በርካታ አስተያየቶችን አንብቤያለሁ፡፡ መጽሐፉንም ባንዴ በማነብነብ ሳይሆን ቀስ እያልኩ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁንም ነገም አነበዋለሁ፡፡ ለመጽሐፉ ከተሰጡት አስተያየቶች ደግሞ በርካታ ተከታዮች ያለው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሰጠው ትኩረቴን ስቦታል፡፡  ጦማሪው ወደ 27ሺ የሚጠጉ ወዳጆች/ላይክ/ እና ከ4 ሚልዮን ጡመራውን/Blog/ እንደጎበኙት አብስሮናል፡፡ ስለመጽሐፉ አስተያየት በሰጠበት ጽሑፍ ስርም ቢያንስ ከ120 በላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱንም ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ስለመጽሐፉ የተሰጡት ምላሾች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሳያነብ አስተያየት የሚሰጠው ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰው እንግዲህ 120 ሰዎችን  የመያዝ እድል አለው፡፡ ይህ ለኔ መሪ/ ገዥ/ ነው፡፡ ራስን መምራት ከመመራቶች ሁሉ ከባድ እና ታላቅነት ነው፡፡ አባት/ የቤተሰብ መሪ/ ቀጥሎ በመሪነት ደረጃ ትልቅ ድርሻን ይይዛል፡፡ 4 ሚልዮን ጊዜ ሰው የተከታተሉት፤ እና በአንድ ጡመራ ገጽ ብቻ ከ120 በላይ አስተያየቶችን የያዘ ደግሞ ትልቅ መሪ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እንዲህ አይነት እድልን ያገኙ መሪዎች/ገዥዎች/ ደግሞ ለአንድ ማህበረሰብ እና አገር መለወጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ 
በአገረ አበሻ ልምድ ውስጥ ነገሮች በአይን ከመታየታቸው ውጭ በሚነገሩት እና ባልታዩ ምክንያቶች አማካኝነት ውሸት ሳትታሰብ ነግሳ የቆየች ይመስለኛል፡፡ በአይን ከነበረው እና ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰው ይልቅ ያልነበሩት ሰዎች ብዙ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ሳይታይ የሚወራ ነገር ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርላችን /99.9/ ውሸት ነው፡፡ አደራ ሰዎች ፓርላማውን ውሸት አላልኩም! ፓርላማውን የጠቀስኩት ለ99.9 ለምትለዋ መረጃ ብቻ ነው!
ታዲያ በነዚህ ቀናት ውስጥ መጽሐፉን ሳነብ፤ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የጻፈውን ምላሽ ሳነብ እና የተሰጡ አስተያየቶችን ስመለከት ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከውስጤ ጋር ተሟግቼ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡ የተገደድኩበትን ምክንያት ከላይ ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ-ከቶም የጽንፈኝነት የጨለምተኝነት እና የጥላቻ ሆነው እንደሰይተረጎሙ፡፡
ከዲ/ን ዳንኤል ምላሽ ውስጥ በጣም ግራ የተጋባሁባቸው ሃሳቦች ነበሩ፡፡ በመሰረቱ የዲ/ን ዳንኤል ምላሽ ልክ እንደፓርላማው/99.9/ ያህሉ አስቂኝ ነው፡፡ አደራ አሁንም ፓራላማውን አስቂኝ አላልኩም! ፕ/ር መስፍንም በምላሻቸው በነጥብ በነጥብ አስቀምጠውታል፡፡
ከላይ ጀምሬ የተውኩትን የኳስ ጨዋታ እና የዘጋቢውን ትስስር በማስታወስ ልመልስዎ፡፡ የጠቀስኩት ዲያቆን ዳንኤልም ለምሳሌነት ስለጠቀሰው ነው፡፡ አንዲህ ሲል፡-
ታሪካችን ከሽፏል ብንል እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?
ለእኔ ይህ አካሄድ አንድ ሰው ሌላ ሰውን የገደለበትን ዜና የሠራውን፣ ለዜናው ትንታኔ ዜና ያቀረበውን ጋዜጠኛና ተንታኝ የግድያው ወንጀል አባሪ ተባባሪ፣ ወይም ደግሞ ለግድያው ምክንያትና መነሻ አድርጎ እንደማቅረብ ነው፡፡ ዘጋቢውን ‹ወንጀለኛ› ማለትና ዘገባውን ‹የወንጀል ዘገባ› በማለት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ዘጋቢው ወንጀለኛ የሚባለው የሠራው ዘገባ ሕግን የተላለፈ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ዘገባውን የወንጀል ዘገባ የሚያደርገው ግን ስለ አንድ ስለተፈጠረ ወንጀል የቀረበ ዘገባ ከሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ጥናት ለብቻው ቢተነትኑትና ያም ትንተና የታሪክ አጻጻፋችንና አተናተናችን የተሳካ ነው ወይስ ያልተሳካ? አስመስጋኝ ነው ወይስ አስነቃፊ? ተመስጋኝ ነው ወይስ ተነቃፊ? የሚለውን ቢተነትኑት እስማማ ነበር፡፡”
በሚል ሃሳብ ለመተንተን ከሞከረ በኋላ የዝናብ መዝነብን ከሜትሮሎጂ ባለሙያ፤ የሂሳብ ኦዲተር ባለሙያን ከድርጅት ትርፋማነት-ኪሳራነት፤ የእግር ኳስ ዘጋቢን ከኳሱ ውጤት ጋር በማያያዝ በማቅረብ የታሪክ ጸሐፊ ባለሙያን ከታሪክ ስኬት እና ክሽፈት ጋር አቆራኝቶ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ በማለት መቀመጡ የአስተያየቱ ትልቁ ስሕተት ነው፡፡ ይህንንም ቢያመን እና ለ4 ሚልዮን ተከታዮቹ ቢያሳውቅ አሸናፊው እርሱ ነበር፡፡
የመጀመርያው የታሪክ ክሽፈትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንዴት ነው የተገናኙት? የታሪክ ክሽፈትን ለማሳየት የታሪክን ሂደት ተከትሎ አንድን ሁነት ከየት ተነሥቶ የት እንደደረሰ በመተንተን፣ ያም ሁነት ከሽፎ ከሆነ የከሸፈበትን ምክንያት ማቅረብ ሲገባ ታሪካችን ከሽፏል ብንል  እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት? ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
   ከፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ከገጽ 41 ጀምሮ እስከ ገጽ 54 ድረስ ዲያቆን ዳንኤል ለጠየቀው ጥያቄ ማብራሪያ የሚሰጥ መልስ ይዘዋል፡፡ ሁነት ምንድን ነው፣ የታሪክ ሁነት ምንድን ነው፣ ታሪክ መጻፍ ዓላማ አለው ወይ? በሚሉ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦች አጥጋቢ በሆነ በጥልቅ ምርምር እና ፍልስፍና ተውበው ተጽፈዋል፡፡ በገጽ 43 የተጻፈውን ሃሳብ ጥልቅ ምርምር እና አስተማሪ ይዘት ያለው ፍልስፍና ተቀምጦ ሳንረዳው የመጽሐፉን ገጽ ብንቆጥር ማነብነብ ብቻ እንደያዝን ተደርጎ እንዲቆጠርብን እናሳብቃለን! የሚያንገበግበውም ይህ ነው፡፡ ቢያንስ 4 ሚልዮን ህዝቦች ይህንን ጥልቅ ምርምር እንዳያነቡት ሆነዋል፡፡ ቢያነቡትም እንዳይረዱት ሆነው፡፡
ክፍል 2

ታሪክን ልንቀበል ከምንችልባቸው ዘዴዎች ውስጥ የታሪክ ጸሐፊዎች ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ የጠጠረ ድንጋይን መካድ ስለማንችል በተጨባጭ የሚገኙ ቀዳሚ መረጃዎች/ ፕራይመሪ ሪሶርስስ/ እንደ ታሪክ ነጋሪ፤ አስተማሪ መስካሪ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ ልሳን አበጅተው ግን በዚህ ወጥቶ በዚህ ገብቶ እንደዚህ ባለው መንገድ አድርጋችሁ ስሩኝ፣ አፍርሱኝ፣ ለውጡኝ፣ ተማሩ፣ ከትላንት ተሸላችሁ ተገኙ እያሉ ሊያስተምሩን አይቻላቸውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ታሪክ ዘጋቢው ነው፡፡ የዜና መዋዕል  አይነት የታሪክ መዝጋብ፣ ለትውልድ ትውልድ አስተማሪ እና ከታሪክ ተሸሎ እንድንገኝ የሚረዳን ቁልፍ ነው፡፡ የታሪክ ዘጋቢው ግን ትክክለኛ ዘገባ ካልያዘ፣ አስተማሪ የሆነ የሃሳብ መንገድን ካልጠቆመ፣ ታሪክ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲጓዝ እና ዛሬ ከትላንት እንዲሻል፤ ነገም ካዘሬ የተሻለ እንዲሆን የሚያደርጉት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን እየታወቀ፤ አንድ የእግር ኳስ ዘጋቢ ተጫዋቶቹ በሚሰሙበት ሜዳ እንደ ደጋፊ /ቲፎዞ/ እየዘገበ ሚያጫውት በጨዋታው ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል እያወቅን፤ ኳስ ዘጋቢ የኳስ ጨዋታውን ሲዘግብ ለውጤቱ ስኬታማነት የሚረዱ ሃሳቦችን እየጠቆመ ቢያጫውት ለሚደረገው ጨዋታ እንኳ ለውጥ ባያስመጣ ለቀጣይ ጨዋታዎች መሻሻል አይነተኛ እና ቁልፍ ሚና ሊጫወት እንደሚችል በመዘንጋት ዲ/ን ዳንኤል የኳስ ዘጋቢን ከእግር ኳስ ጨዋታ ስኬት/ውድቀት ጋር ማነጻጸሩ በግላጭ የአስተሳሰብ ጥልቀቱን ያሳየበት ነጥቡ ነው፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የተጠቀሱት የታሪክ ምሁራን እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ዘጋቢ አድርጎ መውሰድም ተገቢ አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ዘጋቢ/ኮሜንታተር/ በወቅቱ የነበረ ሰው ሲሆን እነዚህ የታሪክ ምሁራን ያቀረቡት ጽሑፍም ባልነበሩበት ዘመን የመዘገቡትን ድርሳን ነው፡፡
ጸሐፊያን የትላንትን ታሪክ መቀየር ፈጽሞ ባይችሉም፤ በተደራጀ እና በተጠና አዘጋገብ እና ለትውልድ ማስተላለፍ ስራ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸው ፕሮፌሰሩ አስረድተውናል፡፡ ተፈጥሮም አስተምሮናል፡፡
ደቀመዛሙርት ትክክለኛወን ትምህርት ከመምህራቸው ባያገኙት፣ ባይቀበሉት፣ ባይጽፉት፣ ባያስተላልፉት እና ክርስትና በዓለም ቢጠፋ ተጠያቂው ማን ነው?  ሰባኪያን በአንደኛው ክ/ዘመን አልነበሩም፡፡ ሆኖም ግን ለ21ኛው ክ/ዘመን ሚያስተምሩት ት/ት ምን ያክል ወሳኝነት እንዳለው ለሰባኪው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የምነግረው እኔ አይደለሁም፡፡
የታሪክ ዘጋቢ ትክክለኛ መረጃን ባያቀርብ፤ ያቀረበውም መረጃ ከታሪክ እንድንማር፤ ከትላንት ልንሻሻል የምንችልባቸውን ነጥቦች ባይጠቁምልን የታሪክ መጻፍ ዓላማው ምንድን ነው? የታሪክ ህልውናስ ምኑ ላይ ነው?
በዚህ ምክንያት የታሪክ ቅብብሎሹ ይበጣጠሳል ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አሁን የተፈጠረው “ብሔር ብሔረሰብ” አሁን ያሉ ምሑራን ባስቀመጡልን አረዳድ እና አተረጓጎም በመቅረቡ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እና  አስተሳሰብ በተቀመጠልን የታሪክ ምሁራን/ዘጋቢዎች አሊያም መሪዎች ተጽዕኖ መሆኑ እየታወቀ፤ የተፈጠረው የታሪክ ምሑራን አረዳድ/አተረጓጎም ከአገር ግንባታ አጠቃላይ ገጽታ አንጻር የተለየ ሆኖ ቀርቦልን ቢሆንም ጥቅሙን እና ጉዳቱን ማመዛዘን እንችላለን፡፡ ይህ በአደባባይ የሚያሳየን የታሪክ ምሁራን በታሪክ ላይ የሚኖራቸውን አሻራ ነው፡፡
ገበሬው ትላንት የዘራውን ዘር ለዛሬ ሲያስተላልፈው ዘሩን እንዲበቅል ከማስተላለፉ በተጨማሪ የአዘራሩንም ሁኔታ፣ የአበቃቀሉንም ሁኔታ፣ የተሻሻለ መንገድን እየጠቆመ ካልመጣ የነገው ዘር ዘሪ ከትላንት የተሻለ ምርት፣ ከዛሬ የተሸለ ውጤት ሊያገኝ ይከብደዋል፡፡ የነገው ዘር ዘሪ በራሱ ፈልጎ የሚዘራውን ዘር ከዛም ተተኪው ዘር ዘሪ ሌላ የራሱን ዘር ቢዘራ፤  ሁሉም የራሱን ዘር እየዘራ ቢቀጥል፤ የመጀመሪያው ዘሪ ለመጪው ዘሪ አልተጨነቀም፤ የዛሬው ዘሪ ከትላንትናው ዘሪ አልተማረም፤ የነገውም እንደዚሁ፡፡ በኢትዮጵያም ታሪክ የምናየው ይኽንን ነው፡፡ አንዱ ይነሳል ሌላኛውን ይደፈጥጣጣል፤ ይበጥሰዋል፤ ያከሽፈዋል…. መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የቀረበውም ይኸው ነው፡፡
የሚገርመው መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የቀረበው የመጽሐፍ ታሪክ በዋናነት የያዘው ሐሳብ አጀማመሩ በምዕራፍ አንድ ላይ መክሸፍ እንደ… ተብሎ ሳይሆን መክሸፍ በ… ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ዲያቆኑም ይህንን ገጽ አላየውም ወይንም አይቶት አላስተዋለውም አሊያም እያየዬ በተንኮል አልፎታል፡፡ ማን በቀናነት ይዬው? መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ እና መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በጉልህ ይተያያሉ፡፡ መክሸፍ በ….እና መክሸፍ እንደ.. ተብለው መቀመጣቸው ዲያቆን ዳንኤል ለጠየቀው ትልቁ ጥያቄ መልስ ነበር፡፡ ታሪክ ይከሽፋል ለሚለው ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን በግልጽ ቋንቋ ለማስረዳት ከመጣራቸውም ባሻገር መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ መጽሐፋቸውን ጀምረዋል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል እንዲህ ብሎ ጻፈ
አንድ መሪ
ለመሆኑ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ የብላታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ የአለቃ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የአቤ ጉበኛ፣ የበዓሉ ግርማ፣ ቤታቸው የት ነው? የት ነበር የጻፉት? ረቂቃቸው አለን? የጻፉበት ብዕር አለን? ምን ሰየምንላቸው? በምን እናስታውሳቸዋለን? ለመሆኑ የኢትዮጵያን የድርሰት ጉዞ የሚያሳይ አንድ ሙዝየም እንኳን አለን? የሺ ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የምንደሰኩር ጀግኖች ሥነ ጽሑፋችን ከየት ተነሥቶ የት ደረሰ? የድርሰት ጉዟችን ከየት መጥቶ የት ደረሰ? የዕውቀት አባቶቻችንና እናቶቻችን እነማን ነበሩ? እስካሁን ምን ያህል ደራስያንን አፍርተናል? እነማን መቼ ተነሡ? እነማንስ ምን ሠሩ?
ፕሮፌሰር በመጽሐፋቸው አጥብቀው የከተቡት ይህንን ሐሳብ ነበር፤ ዳንኤል ክብረት አጥብቆ የተከራከረበት ሐሳብ ይህ ነው የተከራከረውም መጽሐፍ ደግሞ የፕሮፌሰሩን ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሀሳብ እና ተጨማሪ አስተማሪ፣ አስደማሚ፣ አመራማሪ ጭብጥ ያላቸው ዓበይት እና ንዑሳን መዘክሮች ተቀምጠው በተሳሳተ መንገድ መጽሐፉን መረዳት፤ ያልተረዱትን ማሳሳት፤ የተረዱትንም ማወናበድ፤ ከዚያም “በመሪነት” ትልቅ ዕድል ይህንን ድርጊት መፈጸም ትልቅ የታሪክ ክሽፈት ሸክም ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የዚህ ጥሑፍ ሐሳብም በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን ነው!
የመክሸፍ ሸክሞቻችን እነማን ናቸው?
በግለሰብ ደረጃ አሊያም በቡድን የተወሰነ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ ይሰራል፣ታሪክ ያበላሻል፣ታሪክ ያሳካል፣ታሪክ ያከሽፋል፡፡ መሪዎቻችን የተቀበሉት የመሪነት እድል በጠበንጃ መሆኑ ትልቁ የመክሸፍ ሸክሞቻችን መንስኤያት ናቸው፡፡ በመሪነት ደረጃ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድናት ስህተታቸውን በመጀመሪያ ደረጃ ሊገነዘቡት በተገባ፤ ክልተገነዘቡትም የሚገነዘብ ግለሰብ.ቡድን እንዲኖር የመፍቀድ ስርዓትን ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱ በሬዎች ሲዋጉ የሚጎዳውን እንገንዘበው፡፡ ሰዎች ሊዋጉበት የሚገባቸው ቀንድ አልተሰራላቸውም፣ ጭንቅላታቸው የሚዋጉበት ጠፈጥሮአዊ ጸጋ ነው፡፡ ይህም ቀንድ ሊያስበቅል ሳይሆን አንዱ አንዱን ሊጎዳው ሳይሆን በሀሳቡ አሳምኖት ሊተማመኑ፤ የወሰደውን ርቀት ተጉዘው ሰው መሆናቸውን እንዲያሳን ነው፡፡ ሰው እንዲማር ነው፡፡ ሰው እንዲሰለጥን ነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል እና ፕ/ር መስፍን “ሲዋጉ” እጅግ በጣም ተደስተን ነበር፡፡ በታሪካችን ላይ “እየተዋጉልን” ነው ብለን ተደስተን ነበር፡፡ ሰው በሃሳብ ሲዋጋ አንዱ ወገን እንዲሚያሸንፍ እና እንደሚተማመኑ የተፈጥሮ ግዴታ ነው፡፡ ይህ ባይንማ ከመጀመሪያውኑ መዋጋት ባልተፈጠረ ነበር፡፡ ሐሳብ ተሰነዛዝሮ በቀጥተኛ በሐሳቡ ላይ ተወያይተው መዳረሻ ያለው ሐሳብ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱም ሰዎች ጥላ ስር ሆነው ያሉ ሰዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡ ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖች ሶስት እድል ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሰር መሰፍን  እና ዲ/ን ዳንኤል ወደ ሜዳ ሲሄዱ “ጨዋታው” ማርኮን ነበር፡፡ ውጡቱን ግን አላየነውም፡ ማን አሸነፈ? ማን ተሸነፈ? እንዴት እኩል በእኩል ወጡ? ያሸነፈውን ማንኛውም ሰው በራሱ አረዳድ እና አተረጓጎም ሊዘይደው ይችል ይሆናል፤ ያ አይደለም ብቸኛው እና ትልቁ ጭብጥ፤ ትልቁ ጭብጥ እንዴት ተስማሙ? የትኛው አካል መሸነፉን አመነ? በመሸነፉ ምን ተማረ? ምን አስተማረ? ምን ውጤት ተገኘ?
በታሪካችን ብዙ ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ ያሸነፈው ማን እንደሆነ አልተነገረንም! ከመሸናነፍ ምን እንደተገኘ አላወቅንም… ሌላ ውጊያ ለመጠንሰስ እንነጋገራለን…. ውጤቱ መክሸፍ ነው!!
ይህም አንድም አላዋቂነት አሊያም ተንኮለኝነት፡፡ አላዋቂ እንዳንላቸው የአዋቂነት መልክን ይዘዋል፤ ተንኮለኛ እንዳንላቸው ቅቤ ምክርን ለማንጠር ተዘጋጅተዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ መሪዎች ኢትዮጵያን ለዘመናት መርተዋታል፡፡ የከሸፈ ታሪክ ሸክሞቻችንም እነርሱ ናቸው፡፡ አምነው አይቀበሉም፤ ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም፤ የመሪነት ቦታውን/ዙፋኑን ግን ይዘውታል፡፡ አይለቁትም፤ እንኳንስ ከዙፋናቸው ሊለቁ ከራሳቸው አላዋቂነትም ለመላቀቅ ፍንጩም የላቸውም፡፡ የያዙዋቸውን ተማሪዎችም/ተከታዮችንም/ እንዳሳሳቱ እንደገዘቱ ይኖራሉ፡፡ በመሪዎች ስንፍና የሚመጣ  ስህተት ክፉ ነው፡፡ ሰለሞንም የመሰከረው ይህንን ነው፡፡
ከጸሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዥ የሚወጣ ስህተት ነው፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ፡፡
መክብብ 10፡6


No comments: