Jan 23, 2014

ኢትዮጵያ ቀሚስ የለበሰች ‘ለት

ኢትዮጵያ ቀሚስ የለበሰች ‘ለት

ተስፋ በላይነህ

እንደዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ እምነት መሰረት፤ አገር የምታድገው አይደለም በጦር መሳርያ ክምችት እና ሩምታ፤ አይደለም በመፈንቅለ መንግስት ሴራ፤ አይደለም በፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ብዛት፤ አይደለም በአውራ ፓርቲ ዘላለማዊ ግዛት ግዞት፡፡ አገር የምታድገው በጥበብ ነው፡፡ አገር የምትለወጠው በጥበብ ተለውጠው በሚገዟት መሪዎች እና ለጥበብ ተገዝተው በሚኖሩባት ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ አገር ማለት ደግሞ ሰው ነው፡፡
“ቀሚስ የለበስኩ ‘ለት በዚህ ጽሑፍ አተረጓጎም ፤ ከሄኖክ አየለ ፊልም የተወሰደ ሃሳብ ሲሆን፤ የቀረበውም በህይወት ጉዞአችን አንድ ቀን የምንሰራውን ስህተት የሚገልጽ ሀሳብን የያዘ ርዕስ ነው፡፡ በህይወታችን የምንሰራው ስህተት ምን ያክል ዋጋ እንደሚያስከፍል እና ልንወስድ የሚገባንን እርምጃ ከእምነት፣ ከጊዜ ወይንስ ከስሜት ተረድተን እንደምንፈታው የሚጠቁመንን ሃሳብ የያዘ በርቱ! የሚያስብል ‹‹ፊልም›› ነው፡፡
አገራችን በጥበብ ጥማት ሺህ ዘመናትን አሳልፋ አሁን እንዲህ የጥበብ ድርቅ እና ጠኔ ተመትታ ብትሰቃይም፤ በዚህች አገር በብርቱ የተፈለገች፤ በብርቱ የተዘከረች ነገር ብትኖት ጥበብ ናት! በምድርም ላይ ልትፈርድ የምትነሳው ‹‹ጥበብ›› ስትሆን ኢትዮጵያዊቷ ንግስትም አብራ ለጥበብ ትፋረዳለች!!
አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ በያለበት ለበጥበብ ቢያዝ፤ ለጥበብ ቢገዛ፤ በጥበብ ቢገዛ እና ለሰዓታት እንኳ ጊዜ ሰጥቶ ጥበብ ቢዘመርለት፤ በጥበብ ዝም ቢል፡፡ ጥበብ ቢወሳለት እንዲሁም ጥበብን ፍለጋ ቢወጣ እንዴት ያለ ለውጥ ማዬት እንደምንችል መገመት አያዳግትም፡፡
ከጥበብ ትሩፋቶች ውስጥ በዚህ ጽሑፍ ቀርቦ የሚፈተሸ የስነ-ጥበብ/ስነ-ጽሑፍ  ዘርፍ ሲሆን ፤ አገር ልክ እንደ ምጣኔ ሃብቱ እና እንደ ፖለቲካው እድገት ሁሉ የስነ-ጥበቡም እርምጃ ሁሉንም አገራዊ መስተጋብሮች ሊመራ የሚችል መሆኑን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ አገር በስነ-ጥበብ ታድጋለች፡፡ ስነጥበባዊ አብዮት ህዝብን ታሳርፋለች፡፡ ሰው በስነ-ጥበብ ያድጋል፡፡ይማራል፡፡ ይለወጣል፡፡
“ቀሚስ የለበስኩ ‘ለት “የተሰኘ ‹‹ፊልም›› አይተን ስንወጣ ለሰዓታት ተወያየንበት፡፡ ለጥበብ እንዲህ መወያየት ምንኛ መታደል ነው፡፡ ፊልሙን የሰሩትንም እጅግ አድርገን ልናደንቅ እንደሚገባ እና ከፊልሙ ጅማሮ እና መዳረሻ  የታዩንን መሰረታዊ ቅርጾች በጽሑፍ ጽፈን ልናስቀምጥ ግድ አለን፡፡
በመጀመሪያ ፊልሙ ሲጀምር ያልተለመደ፤ ቀላል የሚመስል ነገር ግን መሰረታዊ የሆነ ስራ ተመለከትን፡፡ የእያንዳንዱ የፊልሙ አቅራቢ፣አዘጋጅ፣ ደራሲ፣ የብርሃን ቀማሪ እንዲሁም መላው ተሳታፊ ባለሙያዎች በአማርኛ ትርጉም በየስራ ድርሻቸው መቀመጣቸው እጅጉን አስደሳች እና በፊልሙ የታሰበው አለማ የላቀ ሊሆን እንደሚችል የምስራች ነበር፡፡
‹‹የፊልሙ ኢንደስትሪያችን›› እጅጉን ወደኋላ እንደቀረ አናጣውም፡፡ መሰረትነቱ ከመቶ አመታት በላይ ቆይታ ቢኖረውም ወደ ኋላ 100 አመት እየተጓዘ አንደሆነ ብንናገር ጨለምተኛ ልንባል አይገባንም፡፡ ወደ ኋላ የመቅረታችንን ምክንያት/ችግር/ስሕተት ብንነጋገርበት፣ ብናውቀው እና ውሉን ብንፈታው፤ ካለን ታሪክ እና የጥበብ ክምችት አንጻር ምድርን ማስደመም እንደምንችል እንመሰክራለን፡፡
ፊልሙ ተጀመረ… እየታየ ነው… ምን እንደሚመጣ ማወቅ አልተቻለም… ከሶስቱ መሰረታዊ የፊልም አይነቶች በአንደኛው ማለትም ‹‹ዶክመንታሪ›› በሚሉት ልንመድበው እንደማንችል ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ‹‹ሊኒየር›› ወይንስ ‹‹ነን ሊኒየር›› ውስጥ ነው ብለን ለመመደብ ትንሽ ሞግቶናል፡፡ ምናልባት ነን ሊንየር?
ወጣ ገባ እያለ የሚፈሰው ታሪክ፤ በፊልሙ ውስጥ የምናያቸው ገጸ- ባሕርያት የሚቀርቡበት እይታ/ሲን/ ውስጥ ፈትሾ ለማውጣት ተቸግረናል፡፡ በጣም የተቆራረጡ ‹‹ሲኖች›› በዝተዋል፡፡
አንደኛው ወዳጃችን እኔ ፊልሙን የወደድኩት ሙሉአለም እና ሰራዊት ባለመኖራቸው ነው ብሎ የተለመደ አስቂኝ ትዝብቱን ጣል አደረገልን፡፡ የሁለቱ አርቲስቶች የግል ጥላቻ ኖሮበት ሳይሆን ለዓመታት በጣም ገንነው የታዩት ሰዎች የሌሉበት ድንቅ ፊልም መሆኑን ለመናገር ይሁን ሌላ ልንገምተው ሳንችል ተሳስቀን አለፍነው፡፡ አዳዲስ እና ወጣት ገጽ ማየት በራሱ ዕድልም ድልም ነው፡፡ ጠፍተው እንዳይቀሩብን እንጂ!?
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን በስነ-ጥበቡ ውስጥ ማየታችን ለሙያው ያለውን ክብር እና ቦታ ልንቀበልበት የሚችል ነው፡፡ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንነታቸው ባሻገር በፊልሙ ውስጥ ማየታችን የሚመሰገን ሆኖ እያለ በብቃት ተጫውተውታል ብለን ግን ለመናገር መድፈር ያስረዛዝባል፡፡ የመጀመሪያ ስራ ከመሆኑ አንጻር ባንጫነውም በሌሎችም ተዋንያን ላይ ያየነውም በመሆኑ ክፍቱ በሚገባ ሊታይ ይገባዋል፡፡
ሳምራዊት/ዘሪቱ የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕርይ ከመሆኗም ባሻገር፤ የፊልሙን ዋና ጭብጥ ይዛ የምትተውን “ወንዳወንድ” “ደረቅ” “ዝምተኛ” “ጠንካራ” ሴት ሆና ስትተውን ማየት ይቻላል፡፡ ሆኖም ማንኛውም ጾታ ውስጥ ልናገኝ የምንችለውን ጥልቅ ስሜት ፈልገን ማግኘት አልተቻለንም፡፡ በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለችን ሴት በእውነተኛ ስሜት ውስጥ ሆና ማየት የውሃ ሽታ ሆኖብን በመቀጠሉ ምነው ዘሪቱ? እንድንል አስገድዶናል፡፡ ዘሪቱ በከፍተኛ ዝምታ ውስጥ ሆና የዝምታዋን ጥንካሬ፤ ውበት፣ ሕይወት ማየት ካልቻልን ‹‹ፊልም›› የሚባለው የስነጥበብ ዘርፍ ቦታውን ይስታል፡፡ ኢሞሽን! ኢሞሽን! ስሜት… ህይወት… እስትንፋስ መሰረታዊ የፊልም ጥበብ ቅመሞች ናቸው፡፡ ወንዳወንድ፣ደረቅ ዝምተኛ ሴትን ገጸ-ባሕርይ የተሰጣት ነች ብለን ብናቀርብም እንኳ ከሰው ስሜት ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ያውም አመዛዝኖ ከፍተኛ የሕወት ውሳኔን ለምትሰጥ ገጸ-ባሕርይ፡፡
‹‹በፊልም›› ጥበበ ውስጥ እያንዳንዷ ‹‹ሲን›› ለአጠቃላይ ‹‹የፊልሙ›› ጭብጥ መወጣጫ ደረጃዎች ናቸው፡፡ በመጀመሪያዎቹ ‹‹ሲኖች›› ውስጥ የሚቀርቡት ንግግሮች፤ የገጸ-ባሕርያት አለባበስ/ማንነት እና ሌሎች ትዕይንታት ለፊልሙ ጭብጥ መሰረት እና ታሪክ ናቸው፡፡ ሔኖክ አየለ አስተማሪ የሆነ ገጸ-ባይርይ ተላብሶ እያየነው በፊልሙ መገባደጃ ግን ጠፍቷል፡፡ እስትንፋሱ ሳይወጣ የተቀበረ ሟች ገጸ-ባሕርይ፡፡ በፊልሙ ውስጥ ለምን ተወለደ…? እንዴትስ ሞተ….? የፊልሙ ደራሲ መና ሲያስቀረውም ራሱ ለገጸ-ባይርይው ሕይወት ህልውና ሲል መከራከር ነበረበት!
‹‹አይዳ›› ውብ ሆና በውበት ተውናዋለች፡፡ ‹‹መሳይም›› ግሩም ነበር፡፡ የሳምራዊት ጸሎት ጠንካራ ነበር! ሳምራዊት እና ዲበኩሉ ከምትገባዋ ጸሐይ ስር በመኪና ድጋፍ ተያይዘው ያየነው ምስል እጅግ ማራኪ ነበር፡፡ ተመስገን ለተፈጥሮአችንን እና ዘመኑ ለፈጠረው ‹‹ቴክኖሎጂ››፡፡ በካሜራ እድገታችንም መሻሻል ማየት መታደል ነው፡፡
ተመልካቹ ከምንግዚውም በተለየ ከ1 ሰዓት በላይ ዝም ብሎ መመልከትን ሳይወድ በግዱ እንዲለማመድ አድርጎታል፡፡ ይህ ነው የጥበብ ዋነኛ ግቡ፡፡ ሰው ዝም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ መጠየቅ አለበት፡፡ መመራመር አለበት፡፡ ሲጠይቅ…አዕምሮው ሲሰራ እና የአዕምሮ ልፋት ውጤቱን መገንዘብ ሲጀምር ይለወጣል፡፡ ግለሰብ ይለወጣል፡፡ ህብዝ ይሻሻላል፡፡ አገር ትለወጣለች፡፡
ሆኖም የተለመደው ዘመነኛ አገራዊ ፊልሞቻችን ‹‹ከመሳረር›› ባልበለጠ ጭብጥ፤ ከመሳለቅ ባልዘለለ ፍንጭ ፤ የጊዜያዊ ጭብጨባ እና ሙገሳ መልስ ካልሆነ በስተቀር፤ እንዲህ ዝም ብለን እያዳመጥን፤ እያሰብን ዝም እንዳልን ሳንስቅ፣ ሳናጨበጭብ መውጣት ስላልተለመደ፤ ፊልሙ ‹‹ተፈጸመ›› ሲል የተናደደው እጅግ በርካታ ተመልካች መሆኑን የአይን ምስክር ነበርን፡፡ ሰርግ- ዕልልታ- ጭፈራ- ሞት አሊያም ሌላ የተለመደ አጨራረስ ባለታየቱ ለፊልሙ ዋጋ ማሳጣት ምክንያት ሲሆኑ በማየታችን ከመዘንም አልፈን ተበሳጭተናል፡፡ ግሩም ፍጻሜ ነበር!! ዋነው ጭብጡም ክብር ለማን እንስጥ የሚለው በመሆኑ!! በመንፈስ አጨብጭበናል!! በመንፈስ ተከብረናል!! በመንፈስ ኮርተናል…ተምረናል!!
የሁሉንም የልብ ትርታ ማወቅ ባንችልም ለኔ እና ለወዳጆቼ ግን ከፊልሙ ያገኘነው ጭብጥ ወደር የለሽ ግንባታ መሆኑን ለመመስከር ለደቂቃዎች ከመቀመጫችን አለመነሳታችን ያሳብቅብናል፡፡ ሁሌም ከአንድ ‹‹ፊልም›› የሚጠበቀው ይዘት የሚለካው በመጨረሻው በሚነገረው ‹‹ቃል›› ወይንም ‹‹ድርጊት›› ነው፡፡ ታላቅ መልዕክት ሰማን/ አየን፡፡ ማንም ያጨበጨበ ባይኖርም፤ ቤቱ ሄዶ የሚያጨበጭበው  እንደማይጠፋ ግን እርግጠኞች ነበርን፡፡ አሊያም ዘመንን ተሻግሮ፤ ህዝብ ‹‹ለሰው ክብር ዋጋ›› በሚሰጥበት ዘመን/ትውልድ ውስጥ ስንደርስ ሊጨበጨብለት የሚችል ፊልም እንደሆነ መስካሪዎችም ነበርን፡፡
ሙሉ በሙሉ የፊልም ጥበብን ያሳካ እና የተላበሰ ነው ብለን ማውራት እንደማንችል -ለኛም ለፊልሙ አባላትም የተገለጠ ሀቅ ነው፡፡ ይቀረናል፡፡ ብዙ ልንራመድ ይገባናል፡፡ ሆኖም “ቀሚስ የለበስኩ ‘ለት” ፊልም በዚሁ እርምጃ ተሻሽሎ/አስተውሎ  ከተራመደ ነገ የሚጠብቀን የጥበብ ትሩፋት ወደር የሌለው እንደሚሆን መተንበይ አያዳግተንም፡፡ ነቢይ መሆንም አያስፈልገንም፡፡
ማንኛውም የስነ-ጥበብ ስራ ተሰርቶ ከተጨረሰ በኋላ በሚገባ በምሁራን ሊፈተሸ እንደሚገባው አይከራክረንም፡፡ በተለይ ፊልም ተሰርቶ ካለቀ በኋላ በምሁራንም ሆነ በፊልም አፍቃሪያን ህብረት ስር ሆኖ ለውይይት ቢቀርብ፤ ሊገኝ የሚችለው ውጤት ፊልሙ ከተጻፈበት ጭብጥ የበለጠ ሃሳብ ሊገኝ እንደሚቻል አለም ዓቀፋዊ የፊልም ተሞክሮዎች ይነግሩናል፡፡ እነ ሄኖክ ይህንን አድርገው ይሆን?
እኛ በሕይወት ዘመናችን አንድ ጊዜ የሰራነው ስሕተት ምን ዋጋ አስከፈለን? ስህተቱን ከመስራታችን በፊት ምን ያክል ተጠነቀቅን? ስህተቱን ከሰራን በኋላስ ምን አይነት መፍትሔ ወሰድን? ከስህተታችንስ ምን ተማርን? ለሌሎች ምን አስተማርን…? ከፍተኛ መስዋዕትነት፣ዋጋ እና ክብር ሊሰጥ የሚገባ ለማን ነው? ለምንስ ነው….?
አሁን እንዲህ የሰው መንፈስ በኦና ምድር እየተንሳፈፈች በምትገኝበት ዘመን፤ የሰው ክብር ዋጋ-ቢስ ሆኖ በከሰበት ዘመን፤ ከስሜት እና ከንዋይ በልጦ ሊዘከር የሚችል ነገር ምንድን ነው?
እኛ ‹‹ቀሚስ የለበስን ‘ለት›› የሰራናት ስሕተት ምን አይነት ዋጋ እያስከፈለችን ነው? ምን አይነት መስዋዕትስ ሆንን? በምን አይነት ዘዴ እና ጥበብ እንዲሁም ውሳኔስ ተገዝተን መልስ/መፍትሔ ሰጠን…?
አገራችን ኢትዮጵያ ‹‹ቀሚስ የለበሰች ዕለት›› ምን አይነት ስህተት ሰራች…? ምን አይነት ውሳኔስ ወሰነች…? ምን አይነት መፍትሔ አማጠች…? ለእምነት… ለጊዜ ወይንስ ለስሜት ተገዛች…? ውሳኔዎ የሰውን ክብር አሳጣ ወይንስ የጊዜ ክብርን… ? ለጊዜው ልንከበር ወይንም ልንከብር እንችል ይሆናል፡፡ በዘመን እና በትውልድ ቅብብሎሽ ግን ክብራችን ሲዋረድ እና የሰው ሕይወት ክብር አጥቶ ሲገኝ በዘመን ሚዛን እንመዘናለን  ቀልለንም እንገኛለን፡፡ በተደጋጋሚ ቀሚስ መልበስ… በተደጋጋሚ ስህተት መስራት… በተደጋጋሚ መሳሳት… ከስህተት አለመማር… ክብር መስጠት የሚገባንን ትተን ከበር መቅረት…!?
በጥበብ ከስህተት መቆጠብ እንችላለን፡፡ በጥበብ ከስህተት መማር እንችላለን፡፡ ስነ-ጥበባችን ሊያስተምረን ሊማምረን ይገባል፡፡ ጥበብን እየገደልናት ነው!!
እኛ ሆይ ክብር ለሰው-ክብር ለጥበብ!
የእኛን ‹‹የፊልም›› ጥበብ ሰርተን እስክናሳያችሁ-ቸሩ በቸር ያቆየን!!
መስራት የምትፈልጉም ካላችሁ www.tesfabeaynehh.blogspot.com  ይዘክሩን፡፡



No comments: