Jan 23, 2014

‹‹የቢዮንሴ አላማ እና ኢላማ!››

የቢዮንሴ አላማ 
                                                              በታምራት ፍስሃ

ይቺ የምናያት ዘፋኟ ቢዮንሴ ናት ፡ የመጨረሻው እራት ተብሎ በሚታወቀው ስእል ፊት ለፊት ተቀምጣለች፡ ፊት ለፊት በመቀመጧ ማንን እንደከለለች ታያላችሁ? ተወዳጅ መድሃኒት ክርስቶስን ነው ፡ በርግጥ እሱን መከለል ይቻላታልን? እርሱ በሁሉ ስፍራ ሙሉ ነውና ፤ ነገር ግን የሰይጣንን ተልእኮ ታስፈፅም ዘንድ በክርስቶስ ፈንታ እሷ መታየትን ወዳ እርሱን ከለለችው ፡ አለም ከክርስቶስ ይልቅ ለእርሷ እንደተማረከ አይታለችና ፡ አለም ከክርስቶስ ይልቅ ለዲያቢሎስ እንደተገዛ አይታለችና በዲያቢሎስ ሃይል ከፍ ብላ የክርስቶስን ቦታ ልትይዝ ደፈረች፡፡ 


ይህን ለማድረግ ይቻላታልን? እርሱ ተወዳጅ መድሃኒት ክርስቶስ የማይደፈር ሃያል ፡ የማይነቀንቁት ልዑል ፡ የማይነኩት ግሩም ነውና ከእርሱ ይልቅ ማን ይበረታል? ከአፉ በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያወጣል ፡ ፊቱም ከፀሃይ ይልቅ ያበራል ፡ አይኖቹ የእሳት ነበልባል ናቸው ፡ እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ ፡ በእጁ መዳፍ ምድሪቷን የያዘ ፡ የሰማይና የምድር ንጉስ ፡ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ማን ሊገዳደረው ይችላል?

ነገር ግን የመጨረሻው ዘመን እንደደረሰ ያሳዩ ዘንድ እኒህ የበረቱ መሰሉ ፤ የነፃነት አምላክ እርሱን ተፈታተኑት ፡ የፍቅር አምላክ እርሱን ከፉበት ፡ በዝና በገንዘብ በውበት ህይወት ክርስቶስን ካዱ ፡ መድሃኒት ክርስቶስን ሰደቡ ፡፡ አንደበትን የፈጠረ ጌታ በፈጠረው አንደበት ተሰደበ ፡ ሽክላ ሰሪውን አዋረደ ፡፡ 

ምን እንላለን? አለም በክርስቶስ ላይ ጦርነት አውጃለች ፡ አለም ለዲያቢሎስ ተንበርክካለች ፡ ነፍሷንም ለእሱ አስማርካለች ፡ ክርስቶሳውያን ጠውልገው ፡ ዲያቢሎሳውያን ደምቀው እያየን ነው ፡ እንግዲህስ አሰላለፋችንን እናስተካክል ፡ የማን አድናቂ ነን? ለማን እናጨበጭባለን? ለማን ነፍሳችን ትማረካለች? የማንንስ ተልእኮ እናስፈፅማለን? 


መድሃኒት ክርስቶስ ግን በጴጥሮስ በኩል አሁንም እኛን ትወዱኛላችሁን? ይለናል ፤ ምን እንመልሳለን? ይህን ተወዳጅ ጌታ እንወደዋለንን? እንኪያስ ይችን አለም ክደን ለክርስቶስ እንበርከክ ፡ የዚችን አለም ጣእም ንቀን መድሃኒት ክርስቶስን እንከተል ፤ አለም የክርስቶስ የሆኑትን ልትሰቅል ፡ የዲያቢሎስ የሆኑትን ልትሾም በርትታለችና ክርስቶስን የምንወድ የክርስቶስን መስቀል እንሽከም፡፡

ዮሃ ራእ 22፡11 "ዓመፀኛው ወደፊት ያምፅ ፡ ርኩሱም ወደፊት ይርከስ ፡ ፃድቁም ወደፊት ፅድቅ ያድርግ ፡ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ"
https://www.facebook.com/tamirat.fisseha

No comments: