“የአንድ አይነ ሰውር “ልብ” ኑዛዜ”
ተስፋ በላይነህ
በልቤ ሰገነት
“ባልኮኒ” በሚሉት
ዙፋን ተዘርግቶ
ተንጣሎ ተስፋፍቶ
የሚታየኝ እውነት
“ባልኮኒው” “ባንኮኒ”- የቅዠት ሥምሪት፤
ለመሞት መፈጠር- ለመፈጠር መሞት!!
******
የሰው ልጅ መሰረት
በማያልቅ ፏፏቴ፤ አንድም በሞት ዥረት
ሽቅብ ቁልቁል ፈስሰው ተግተው ሚጠፉበት
በትዝታ ተስፋ ዘላለም ሚዋትት
የሰው እጣ ፈንታ
ለመሞት መፈጠር- ለመፈጠር መሞት!!
******
ሲደርስ፤ሲመላለስ
ሲፈርስ፤ሲቆራረስ
የማየው የሰው ልጅ
ስጋ ቅብ አፈር ቅጅ…
ራሱን የማያይ- የውስጥ ውቅንያኖሱን
ሊዋኝ ይሞክራል የምድር ስፋቱን፤
ሊለካ ይዳዳል የጠፈር ጥልቀቱን፡፡
******
“ልብ” ባህር ሃሳብ ነው
“ጭንቅላት” ውቅያኖስ- መንፈስ የተሞላው
ኅልቆ መስፈረት ልኬት ህያው መልክ የዘራው
የሰው ልጅ ከንቱ ነው ጥበብ ከጎደለው፡፡
******
በደመና ሽታ በጥላ ዘመን ስር የሚመላለሰው፤
በሰልፍ የሚያዘግመው፤ሲያሻው ሲሽቀዳደም ሲሞት የሚታየው፤
የሰው ልጅ ወረት ነው- ፍቅር ከተለየው፤
የሰው ልጅ ወረት ነው ፤ የሰው ልጅ ከንቱ ነው!!
No comments:
Post a Comment