Jan 29, 2014

የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው” ምሳሌ 20፡27

“የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው”
ምሳሌ 20፡27

አግዚአብሔር ሆይ! ባሳለፍናቸው መራራ እና ጣፋጭ ቀናት ያለፉብንን እና ያለፍናቸውን የህይወት ክስተቶች በሙሉ እያስታወስንህ እናመሰግንሃለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ነገሮች አልፈውናል፡፡ 

ያሳለፍናቸው እና ያለፉብን በቁጥር ጥቂት የሚባሉ አይደሉም…! ጥቂት አለመሆናቸው ብቻም ሳይሆን በቁጥር አንሰው ቢገኙም ለዘመናት የምንኖርባቸው እና የምንኖርላቸው ይመስለን ዘንድ ተጣብቀናቸዋል፡፡ እጅ ሰጥተንላቸዋል፡፡ ክብር አጥተንባቸዋል፡፡ በሚዛን ቀልለንባቸዋል፡፡ በስጋ-በመንፈስ ረክሰንባቸዋል፡፡ ታስረን-ተተብትበንባቸዋል፡፡ ወደ ዘላለሙ ጸጥታ ስንሄድ ግን አንዳቸውንም አላስከተልናቸውም፡፡ የሚከተለን ጭለማን አሊያም ብርሃንን የሚያዝለው መንፈሳችን ብቻ  ነው፡፡ በማይከተሉን እላፊዎች የዘላለሙን መንፈስ ማጠልሸት ምንኛ ምርጫ ነው..?

አግዚአብሔር ሆይ!  የተማርንባቸው እላፊዎች እንዲበዙ ፤ የተማረርንባቸው ቢሆኑም እንኳ ጭለማን እንዳይዘሩብን፤ ምሬትን በሬት ለውሰው መንፈሳችንን ጽልምት እንዳያወርሱት እንለምንሃለን፡፡ ለዚህም እንተጋለን!! ሳናቋርጥ እንተጋለን!!
ጨለማን እንዳላወረስከንም ስናስብ የምናመሰግንበት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከብርሃን በብርሃን እና ወደ ብርሃን እንደሆንን ስናስብ አብልጠን እንድንከተልህ መነሻ እና መድረሻ ምክንያታችን ነው፡፡ 

እንደ ደመና በተመሰለው ሕይወታችን ውስጥ ብርሃኑ ሰንጥቆ ለዘላለም ያበራ ዘንድ ዛሬ ብርሃንህን ላክልን፡፡  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚደንቀን አባባል አለ፡፡

“የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው” የሚለው፡፡

እውነት ባሳለፍናቸው፤ ባለፍናቸው፤ ባለፉን እና በተላለፍናቸው እንዲሁም በተማርንባቸው እና በተማረርንባቸው የሕይወት ጊዜያት ውስጥ ያጋጠሙን "እላፊዎች" በሙሉ የመብራታችንን ብርሃን እንዳያጨልሙብን እንንጠንቀቅ፡፡ መንፈሳችን በብርሃን ሆኖ ብርሃንን ይወረስ ዘንድ እንትጋ፡፡ ብርሃኑ በምድርም በህላዌም ያበራ ዘንድ በብርሃን እንመላለስ፡፡ የዘወትር ምግባችን እና ጥረት ትጋታችን ለዚሁ ነው፡፡ አሜን- ይሁንልን!
የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው የሆዱን ጕርጆች ሁሉ የሚመረምር። ምሳሌ 20፡27


የሎዛ ማርያም”፡፡

No comments: