Dec 22, 2013

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!
በተስፋ በላይነህ

ክፍል -1
   ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ ለብዙ ቀናት ተሟግቻለሁ! “ጽሑፉንስ ጻፈው ግን አደራ እንዳታወጣው!” ይለኛል አንደኛው ተሟጋች፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ በስም ማጥፋት ወንጀል!” ተብለህ እነዳትከሰስ፡፡ ሌላኛው ተሟጋች ደግሞ “አንተ ምን ባይ ነህ የሰው ስም ጠቅሰህ አንድ የባለ ረዥም ባለታሪክን አገር ታሪክ መክሸፍ ከጥቂት የግለሰቦች ስብዕና ጋር አያይዘህ የምትለጥፈው” ይለኛል፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ኧረ እባክህ አርፈህ ተቀመጥ!” ብሎ የተለመደውን ምክንያት የለሽ ክርክር ያቀርብና ሊሞግት ይቃጠዋል፡፡
  ምክንያት የለሽ ሙግት ደግሞ ከሰነፎች ልብ የሚፈልቅ ኢትዮጵያን ለዘመናት ያቆረቆዘ የታሪካችን ውድቀት ምክንያት ነው ብዬ ለመወሰን ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ “ተማርን” በሚሉት የኢትዮጵያ ዜጎች/ መሪዎች/፡፡ ያለምክንያት ተሟግቶ አለማመን፣ አለመተማመን፣ መሸነፍን አለማመን ማሸነፍን ብቻ ማመን… ደግሞ ሌላኛው ደዌ! ክፉ መርዛማ ደዌ ነው! የመክሸፍ ሸክማችንም ናቸው፡፡
አንድ ፈላስፋ እንዲህ አለ፡፡ “እውነትን ከያዝህ ለክርክር አትቸኩልም፣ ከተከራከርክ ግን አትሸነፍም፡፡” ድንቅ አባባል! በብዛት የሚከራከሩ ሰዎች ውሸተኞች ናቸው፡፡ ሁሉም እውነተኛ ቢሆንማ ክርክር የሚባል ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ አንድ ውሸት ግን ስትመነጭ በብዙ እውነቶች ውስጥ ተደንቅራ ታከራክራለች፡፡ እውነተኞች ግን አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ ለክርክር አይቸኩሉም፤ ከተከራከሩ ግን አይሸነፉም፤ እውነትን አትሸነፍም! እውነትን ለማወቅ ደግሞ አውቀት ያስፈልጋል፡፡ እውነት እና እውቀት ያንድ ሳንቲም አንድ ግጽታ ናቸው፡፡ በአንድ ገጽ አብረው የሚኖሩ፡፡
  ውሸት ተጋንና፣ ተበራክታ፣ ተደላድላ ተቀምጣ ስትታይ፤ ቀስ በቀስ እውነት ለመምሰል የምታደርገውን የውሸት ህይወት የሚመለከቱ እውነተኞች ዝም ማለት አይችሉም፡፡ በተፈጠረው የውሸት ህይወት ምክንያት ብዙ ፍጥረታት ውሸቱ እውነት መስሏቸው ተቀብለውት ስለሚኖሩ እውነተኞች ይነቀፋሉ፡፡ ተከራካሪ ይባላሉ፡፡ ነገረኛ፣ አደናጋሪ፣ ጠብ አጫሪ ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ እውነትን ለማሳየት ሲሉ ብቻ ከብዙ ምድራዊ ጥቅማጥቅሞች ይገለላሉ፡፡ በጥቂት ሰዎች ዘንድ ግን ይታወሳሉ፡፡ ይህንን ምድር የሚገዙት እና የሚመሩት ግን ውሸተኞች እንጂ እውነተኞች ስላልሆኑ አለም የምትመራው በውሸተኞች መሆን ከጀመረ ዓ/ም ተብሎ ከታወጀበት ዕለት ይመስለኛል፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ዓ/ም ብለን የምንጠራው ላመኑባት፣ ለተከተሏት እና ለተገበሯት ብቻ ነው፡፡ ንጉሱ ክርስቶስ ጌታ ቢሆንም፤ የዚህ አለም ገዢ ግን ሰውን እንደ መልኩ እና እንደ አሻራው ለያይቶት ይገኛል፡፡ ብዙኃኑ   በተንኮለኞች እና በውሸተኞች እንዲመራ አድርጓል፡፡ አለም የምትመራው በውሸተኞች ነው፡፡ ይህንን ካላመናችሁ፤ ይህንን ጽሑፍ ባታነቡት እመርጣለሁ፡፡ አለም የምትመራው በጥቂቶች እጅ መዳፍ ተጨፍልቃ፤ በተንኮል እና በሸፍጥ  በተመረዙ ሴረኞች፤ በሆዳሞች እና የሰውን ልጅ ሰብዕና ለማኮላሸት ሌት ተቀን በሚንደፋደፉ ሸረኞች ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ካልተገነዘቡ ይህንን ጽሑፍ እንዳያነቡት፡፡  ካመኑበት እና ከገባዎ ግን ይቀጥሉ፡፡
እየቀጠሉ ከሆነ አምነውበታል ማለት ነው፡፡ ሳያምኑበት የሚቀጥሉ ከሆነ እየዋሹ ነው ማለት ነው፡፡  ራስዎን አይዋሹ፤ ራስን መዋሸት ዋነኛው የክሽፈታችን ምንጭ ነው፡፡ ራስን መዋሸት አንድም ካለማወቅ ነው አሊያም ከተንኮል ነው፡፡
የዚህን ጽሑፍ ርዕስ የመረጥሁት ባሳለፍነው ዓመት በወጣ መጽሐፍ ላይ ለተሰጠ ምላሽ ሲብላላ ቆይቶ ለመጠጥነት የደረሰ “መጠጥ” ነው፡፡ እውነተኛ መጠጥ በጊዜ ሲብላላ ጣፋጭ ይሆናል፡፡ አንድም መድሐኒት፤ አንድም አስካሪ ነው!
እውነት እንደሚያሳምም ባሳለፍናቸው የስራ ጊዜያት ሳንገነዘበው የቀረን አይመስለኝም! አውነት ያሳምማል! ለውሸተኛሞች አውነት አስካሪ መጠጥ ነው! እውነትን ለሚሹ ግን መድሐኒት፡፡ እውነተኛው ክርስቶስ በአንዳንዶቹ እንደ ጋኔላም ለምን ታዬ? ለአንዳንዶቹ ደግሞ ትንሳዔ ለምንስ ተባለ?  እውነትን በአይነ ልቡናቸው ስላሳያቸው አይደለም የስቅላቱ መንስዔ?!
መጽሐፉም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፤ ብዙዎችን አነጋግሮ አልፏል፡፡ ታዲያ ላለፈ ነገር ምን አስጨነቀህ? ምንስ አስቀባጠረህ እንዳትሉኝ እሰጋለሁ፡፡ ካላችሁ ደግሞ ይህንን ጽሑፍ መቀጠል የለብዎትም ብዬ ካሳሰብኩዎ አንዱ ነዎት ለማለት ይዳዳኛል ፡፡ ቀጣይነት የሌለው ውይይት፤ ቀጣይነት የሌለው ሃሳብ “ክሽፈትን” እንደሚያስከትል ግልጽ ነው! “መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ” የነገሰበት ምክንያት ነው የውይይታችን መሠረት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መክሸፍን እንደምን ተሸከምነው!? ሰለሞን በዘመኑ እንዲህ ሲል መሠከረ፡-
ከጸሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዥ የሚወጣ ስህተት ነው፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ፡፡
መክብብ 10፡6
   የትላንቱ ታሪክ በዛሬ ተዘግቦ፣ በዛሬ ተጠንቶ፣ ተወያይተንበት የጠራ እውነት ላይ ካልደረስን ውሸታሞች ነን ማለት ነው፡፡ አሊያም የተጣራ ታረክ በዘጋቢው አልደረሰንም ማለት ነው፡፡ የኳስ ጨዋታ ዘጋቢ የተሳሳተ ዘገባ ቢዘግብም፤ ኳስ ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢዶልትም፤  ተጫዋቾች የተራገጡበት አውላላ ሜዳ ከተገኘ፤ ሜዳው ቢጋጋጥ፤ ቢላላጥ ከጨዋታው ተመልሰው የተገኙ ተጫዋቾች ቢገኙ፤ ተጫወትን ብለው ቢዘግቡ ሆኖም ዘጋቢ የተባለው /“ኮሜንታተር”/ አሁንም ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢያነበንብ… ኳስ ጨዋታው እና ዘጋቢው ምንና ምን ናቸው፡፡ የኳስ ዘጋቢው ዘገባ ከዘመናት በኋላ የዘገበውን መረጃ ብናገኘው ከትክክለኛው የኳስ ጨዋታ ጋር ባይገናኝ እና ትውልድ ግን የሚሰማው ይህንን የተሳሳተ መረጃ ቢሆን… ይህንን ሃሳብ ከታሪክ ዘገባ እና ዘጋቢዎች/ጸሐፊዎች/ ጋር አገናኝተው የራስዎን ሃሳብ ይውሰዱ እና ይመራመሩበት፡፡ ልታግዙኝም ትችላላችሁ፡፡ /ወደኋላ እንመለስበታለን፡፡/
  ትላንት እኮ ነገ ነበረ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ከሆነ በኋላ አልፎ ደግሞ ትላንት ሆኖል፡፡ ቀናትን በነገ፣ በዛሬ እና በትላንት መከፋፈሉ እንደ እኔ እይታ ከስህተት ለመማር ብቻ ይመስለኛል፡፡ አንድ አባባል አባባል እጅጉን ይማርከኛል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“የምጽአት ቀን ለምን እንዲህ ረዘመ?” ሲባል
“ለንስሃ!” የሚል መልስ ያስደስተኛል፣ ያረካኛል፣ ያሳምነኛል፣ ያጽናናኛል፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ ስማር ለነገ የተሸላ ስለምሆን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ አልፎ ትላንት ሲሆን  ከዛሬው ትላንትና እንድማር ስለሚረዳኝ ዛሬ ላይ መሆኔ እድለኛ ነኝ! ዛሬ የንስሃ ቀን ናት! ዛሬ የመዳን ቀን ናት! ነገ የምጽአት ቀን ናት ምክንያቱም ማንም ስለ ነገ እርግጠኛ የሚሆን የለምና፡፡ ሞት መቼ እንደሚወስደን ስለማናውቅ ፤ እንደ ሌባ ባልታወቀ ሰዓት እንደሚመጣ ተነግሮናል፡፡ ዛሬ ማለት ደግሞ አሁን ማለት ነው፡፡ ተደጋጋሚ አሁን /ንስሃ/ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው! እነዚህ ተደጋጋሚ ዛሬዎች ደግሞ ትላንትን አሻሽለው ነገን ፍንተው አድርገው ካላሳዩን እንደምን የተሻሉ ይሆናሉ? ስለዚህ አሁን የትላንቱን የምንጨነቅበት፣ የምንዋጋበት፣ የምንጨቃጨቅበት እና ቂም የምንያይዘበት ሳይሆን የምንማማርበት፣ የምንወያይበት፣ የምንለወጥበት እና ንስሃ የምንገባበት ስህተታችንን የምንናዘዝበት ሊሆን ይገባል፡፡ “ትላንት ያልዘራው ዛሬ አይበቅልም፤ ዛሬ ያልተዘራው ነገ አይበቅልም” በ“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” /ገጽ 51/፡፡
በዚህኛው አንቀጽ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የዛሬ ዓመት ለወጣ ጽሑፍ አሁንም ምለሽ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡ ያስገደደኝ ቂም አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ጥላቻ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ክርክር መውደድ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ አውነትን ማምለኬ ነው፡፡ የማመልከው አውነት ራሱ ይፍረድብኝ፡፡
 ለ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ ምላሽ በርካታ አስተያየቶችን አንብቤያለሁ፡፡ መጽሐፉንም ባንዴ በማነብነብ ሳይሆን ቀስ እያልኩ ለማንበብ ሞክሬያሁ፡፡ ለመጽሐፉ ከተሰጡት አስተያየቶች ደግሞ በርካታ ተከታዮች ያለው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሰጠው ትኩረቴን ስቦታል፡፡  ጦማሪው 4 ሚልዮን ተከታታይ እንደለው አብስሮናል፡፡ ስለመጽሐፉ አስተያየት በሰጠበት ጽሑፍ ስርም ቢያንስ ከ123 በላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱንም ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ስለመጽሐፉ የተሰጡት ምላሾች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሳያነብ አስቴት የሚሰጠው ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰው እንግዲህ 130 ሰዎችን  የመያዝ እድል አለው፡፡ ይህ ለኔ መሪ/ ገዥ/ ነው፡፡ ራስን መምራት ከመመራቶች ሁሉ ከባድ እና ታላቅነት ነው፡፡ አባት/ የቤተሰብ መሪ/ ቀጥሎ በመሪነት ደረጃ ትልቅ ድርሻን ይይዛል፡፡ 4 ሚልዮን ተከታታይ እና በአንድ ጡመራ ብቻ 123 ሰዎችን የያዘ ደግሞ ትልቅ መሪ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እንዲህ አይነት እድልን ያገኙ መሪዎች/ገዥዎች/ ደግሞ ለአንድ ማህበረሰብ እና አገር መለወጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ 
  በአገረ አበሻ ልምድ ውስጥ ነገሮች በአይን ከመታየቸው ውጭ በሚነገሩት እና ባልታዩ ምክንያቶች አማካኝነት ውሸት ሳትታሰብ ነግሳ ቆይታለች፡፡ በአይን ከነበረው እና ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰው ይልቅ ያልነበሩት ሰዎች ብዙ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ሳይታይ የሚወራ ነገር ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርላችን /99.9/ ውሸት ነው፡፡ አደራ ሰዎች ፓርላማውን ውሸት አላልኩም! ፓርላማውን የጠቀስኩት ለ99.9 ለምትለዋ መረጃ ብቻ ነው!
ታዲያ በነዚህ ቀናት ውስጥ መጽሐፉን ሳነብ፤ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የጻፈውን ምላሽ ሳነብ እና የተሰጡ አስተያየቶችን ስመለከት ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከውስጤ ጋር ተሟግቼ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡ የተገደድኩበትን ምክንያት ከላይ ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ፡፡
ከዲ/ን ዳንኤል ምላሽ ውስጥ በጣም አስቂኝ ሃሳቦች አሉ፡፡ በመሰረቱ የዲ/ን ዳንኤል ምለሽ ልክ እንደፓርላማው/99.9/ ያህሉ አስቂኝ ነው፡፡ አደራ አሁንም ፓራላማውን አስቂኝ አላልኩም!
ከላይ ጀምሬ የተውኩትን የኳስ ጨዋታ እና የዘጋቢውን ትስስር በማስታወስ ልመልስዎ፡፡ የጠቀስኩት ዲያቆን ዳንኤልም ለምሳሌነት ስለጠቀሰው ነው፡፡ አንዲህ ሲል፡-
ታሪካችን ከሽፏል ብንል እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?
ለእኔ ይህ አካሄድ አንድ ሰው ሌላ ሰውን የገደለበትን ዜና የሠራውን፣ ለዜናው ትንታኔ ዜና ያቀረበውን ጋዜጠኛና ተንታኝ የግድያው ወንጀል አባሪ ተባባሪ፣ ወይም ደግሞ ለግድያው ምክንያትና መነሻ አድርጎ እንደማቅረብ ነው፡፡ ዘጋቢውን ‹ወንጀለኛ› ማለትና ዘገባውን ‹የወንጀል ዘገባ› በማለት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ዘጋቢው ወንጀለኛ የሚባለው የሠራው ዘገባ ሕግን የተላለፈ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ዘገባውን የወንጀል ዘገባ የሚያደርገው ግን ስለ አንድ ስለተፈጠረ ወንጀል የቀረበ ዘገባ ከሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ጥናት ለብቻው ቢተነትኑትና ያም ትንተና የታሪክ አጻጻፋችንና አተናተናችን የተሳካ ነው ወይስ ያልተሳካ? አስመስጋኝ ነው ወይስ አስነቃፊ? ተመስጋኝ ነው ወይስ ተነቃፊ? የሚለውን ቢተነትኑት እስማማ ነበር፡፡”
ይለንና የዝናብ መዝነብን ከሜትሮሎጂ ባለሙያ፤ የሂሳብ ኦዲተር ባለሙያን ከድርጅት ትርፋማነት-ኪሳራነት፤ የእግር ካስ ዘጋቢን ከኳሱ ውጤት ጋር በማያያዝ በማቅረብ የታሪክ ጸሐፊ ባለሙያን ከታሪክ ስኬት እና ክሽፈት ጋር አቆራኝቶ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ ይህንንም ለማጠየቅ አይኑን አያሽም
የመጀመርያው የታሪክ ክሽፈትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንዴት ነው የተገናኙት? የታሪክ ክሽፈትን ለማሳየት የታሪክን ሂደት ተከትሎ አንድን ሁነት ከየት ተነሥቶ የት እንደደረሰ በመተንተን፣ ያም ሁነት ከሽፎ ከሆነ የከሸፈበትን ምክንያት ማቅረብ ሲገባ ታሪካችን ከሽፏል ብንል  እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?

   ከፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ከገጽ 41 ጀምሮ እስከ ገጽ 54 ድረስ ዲያቆን ዳንኤል ለጠየቀው ጥያቄ ማብራሪያ የሚሰጥ መልስ ይዟል፡፡ ሁነት ምንድን ነው፣ የታሪክ ሁነት ምንድን ነው፣ ታሪክ መጻፍ ዓላማ አለው? ወይ በሚሉ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦች አጥጋቢ በሆነ ጥልቅ ምርምር እና ፍልስፍና ተውበው ተጽፈዋል፡፡ በገጽ 43 የተጻፈውን ሃሳብ ጥልቅ ምርምር እና አስተማሪ ይዘት ያለው ፍልስፍና ተቀምጦ ሳንረዳው የመጽሐፉን ገጽ ብንቆጥር ማነብነብ ብቻ እንደያዝን ተደርጎ እንዲቆጠርብን እናሳብቃለን! 
                                                                                                       ይቀጥላል.....

No comments: