Nov 6, 2013

ከውበት ፍካት ጥፋት

ከውበት ፍካት ጥፋት

ምን ጠይቀህ ነበር በህይወትህ ዘመን?
በነዚያ በጨቅላ- በዳዴ ወራትህ- አጥንትህ ሲጠገን
የናት ጡት ሲያቆምህ ሲያሮጥህ ከወገን
ምን?
         ***--***--***
ምን ፈልገህ ነበር ነፍስህም ስትቃትት፤
ምን ተመኝታ ነበር የልብህስ መሻት
በህልምህ በ’ውንህ የወደፊት ምኞት…   
በነዚያ ቀናቶች ባማሩ በጸዱ፤ በፈኩ ወራቶች
በምን ተተካኩ የሕይወት ምስጢሮች?
በምን?
        ***--***--***
አእምሮህ ጠይቆ ለመልስ ሲንከራተት
ምን አገኘህ ዛሬ ምን ፈለግህስ ትናንት…?
የጠየቅከው ቀመር ምን ሰጠህ ስሌቱ
የነፋሱ መንፈስ የጸሐይ መግባቱ?
          ***--***--***
ጥበብንስ ሽተህ መንፈስንም ክደህ
ከጥልቁ ውቅያኖስ ካውድማው ሸምተህ
ከድቅድቅ ጨለማው ከጉም ሽንቱ ዘግነህ
ስንት አተረፍክ ቁና ምኑን ሰፍረህ መጣህ…?
       ***--***--***
ህይወት ያ ለከት
ፍቅር ካለ ጽናት
ነገ ካለ ተስፋ ዛሬ ያለ እምነት
ምድር አንደው ግዙፍ ሕይወት እንደው ወረት
ጠፈር እንደው ሰፊ ፍቅርም ሲሆን በት!
ሕይወት??
            ***--***--***
ምን ጠንክረህ ታገልህክ በጉብዝናህ ወራት
ምን አድነህ ገደልህክ በዝናህ ኩንትራት፡፡//ዝና ኩንትራት ነው!//
ምን ፈልገህ ቋጨህ በዘመን ዓመታት
ጥቋቁር ፀጉሮችህ ሲተኩ በሽበት
ነጫጮቹ ጥርሶች ጠቆሩ ከቅጽበት
          ***--***--***
የፈካው ፊትሽም ሲደበዝዝ ድንገት
ዋላ መሳይ ጡቶች ሲተኙ ወደንብርት
         ***--***--***
የገደለው ጡንቻ የታገለው አጥንት
የሟሸሸው ቆዳ የጎበጠው ስሜት
ሕይወት?
         ***--***--***
በጊዜ ተዋረድ በዘመን ትሩፋት
ምን እያየሽ መጣሽ በጸዳልሽ ፍካት
ምን ተምረሽ ቆየሽ በውበትሽ ጥፋት?
        ***--***--***
ምን አትርፈህ መጣህ ከተጓዝከው ትላ-ንት?
              ከሕይወት ፍካት
                   -ጥፋት!?

   

                           

No comments: