እንግዲህ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር በአሁኑ ሰዓት
የ100 ዓመት ታሪክ አድርገን የምንወስድ ከሆነ በታሪክ የምናውቃትን ‹‹ኢትዮጵያ›› ከምድረ-ገጽ ማጥፋት ያክል ወንጀል እንደሆነ
አምናለሁ፡፡ የ3ሺ ዓመት ታሪክ አልፎም 5ሺ ዓመት ተብሎ በሚቀርብልን መረጃ የማምን ስለሆንኩ ጥበቧን፣ ታሪኳንና ክብሯን የምጀምረውም
ከዚሁ ከ3ሺ እና 5ሺ ዓመት ህልውናዋን በመያዝ ይሆናል፡፡ የታሪኩን ሂደት በሌላ የታሪክ ፅሑፍ የምናየው ይሁን፡፡
አለም በሮምና በኢትዮጵያ ትመራ ነበር የሚል መረጃን በመያዝ በተለይ የሃይማኖት
መጽሐፍትን በማጣቀስ ከዘፍጥረት ጀምሮ የተጠቀሰችና ይህንንም ስም ደረጃ በደረጃ ይዛ ለታላላቅ ፈተናዎች የተሰጠች አገር በኩሽ ምድር
ከዚያም በኢትዮጵያ ስያሜ ትገኛለች፡፡ በታለቁ መጽሐፍ ኢትዮጲያን በተደጋጋሚ እንደምናገኛት ግልጽ ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችው
ኢትዮጵያ የአሁኗ ኢትዮጵያ አይደለችም የምትባል አማርኛ አትገባኝም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ እኔ ነኝ ብለው ከሚቀርቡት አገራት
አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን እየተማመንን አሁንም የመተማመኛ ስሌቱን በሌላ ጽሑፍ የምናየው ይሁን፡፡
ዋናው ነገር ግን ከሩቅ ምስራቅ መጥተን እስካልተከራከርን ድረስ፤ ከአሜሪካ ምድር መጥተን ኢትዮጵያዊነትን
እስካልቀማን ድረስ ሁልጊዜም በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰችን ኢትዮጵያ የአሁኗንም ይወከወላል ብሎ ማውራትንና ማሰብን እንደ ወንጀል
የሚቆጥሩ ‹‹በምዕራባዊያን ቅኝት›› ስር የሚጋለቡ አዋቂዎች፤ የባዕዳኑን ስልጣኔ ናፋቂዎች ይመስሉኛል፡፡ ከጥቅም አንጻር ብናየው
እንኳ አንድን ህዝብ ባለ ረዥም ታሪክ ባለቤት አድርጎ መቅረጽ ምን ያክል እንደሚጠቅምና ሰለጠኑ የሚባሉ አገራት አንኳ ሲመኩበት
የምናየው ነው፡፡
ታሪክንና ባህልን ጠብቆ መሰልጠን የሰውነት ድርሻ ነው፡፡ የረዥም ታሪክ ባለቤትነት
ለአንድ ትውልድ የሚያበረክተውን ፋይዳ በማሰብ ሁልጊዜም ታሪክ አለኝ የሚል ትውልድ ለአለበት ዘመንና ለሚመጣው ትውልድ አሻራ እንዲጥል
ያደርገጋል እንጂ ሲጎዳው አይታይም፡፡ ምናልባት ‹‹በታሪክ መኮፈስ›› ብቻውን ካልሰሩበት /ካልተማሩበት/ የእውነት ሊያሳስበን ይገባል፡፡
በእኔ በኩል ኢትዮጵያን በመጽሐፍ ቅዱስ የምመለከታት ለእስራኤል ህዝብ መመረጥ
ከታላቁ አባት አብርሃም ከከለዳዊያን ምድር፤ ከዚህ አለም መንግስት ተምሳሌት ከነበረችው በጣዖታት በማምለክ የሚታወቁትን ህዝቦች
ሲለቅ እንደ ማረፊያነት የመረጣት ኢትዮጵያን /አዜብ/ ነበር፡፡ ከዛም ኢትዮጲያዊቷን ኬጡራን እንዳገባ በዘፍጥረት 25 እናነባለን፡፡
ታላቁ ነብይ ሙሴም ህዝብን ከስጋ ባርነት ለማዳን ሲመረጥ ሸሽቶ የመጣው ወደ ዚህች ምድር ነው፡፡ በካህኑ ዮቶር አማክኝነት ተስተናግዶ
ልጁን ሲጳራን እንዳገባ ዮቶርም ከአብርሃም የኋለኛ ሚስት ከነበረችው ከኬጡራ ዘር እንደሆነ በዘጸአት 3 እና ሌሎች የብሉይ መጽሐፍትን
አጣቅሰን ማመሳከር እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ይህንና ሌሎችን የኢትጵያን ህልውና በመያዝ ታላቁን ጠቢበኛ
ልትፈትን ከአለም የተመረጠች የአዜብ ንግስት መኾኗ፤ የእስራኤል ታላቅ ሀብት ጽላተ ሙሴ፤ እንዲሁም ከእየሩሳሌም ውጭ ክርስትናን
የተቀበለች የመጀመሪያ አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ እስልምናንም ስንመለከት የሰላም ምድር ተብላ የተጠቀሰች ቀደምት አገር የአሁኗ ኢትዮጵያ
ነች፡፡
ይህን ሁሉ በማንኛውም ኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ቢቀመጥና፤ ለታሪክ ለባህልና
ለስልጣኔ እንዲሁም ለመንፈሳዊነት ቦታ ሰጥተን የአሁኗንና የነገዋን ኢትዮጵያ ብንገነባ ስሕተቱ አይታየኝም፡፡ ይህንን ሁሉ በመተው
ግን በቁስ ብቻ ማደግን በአለም በምጣኔ ሃብት ቁጥር ብቻ ማደግን እንደ ታላቅ ታሪክ ሰሪነት አድርጎ ራስን መቁጠር፤ የሌላን ህዝብ
ባህልና ስልጣኔ ለማወቅ መታከት፤ በታሪክ የነበረውን ፍሰት በመተው ራስን እንደ ፍጹም መሪና የተማረ ትውልድ አድርጎ መውሰድ በተለይ
ላለፉት 40 አመታት በዚህች አገር የታየ ትልቅ ችግር ነው፡፡ አፍሪካዊነትና ኢትዮጵያዊነት እስኪዘገነን ድረስ በተለይ መሪዎቻችን
ያለፉትን መሪዎች ሲያንቋሽሹ እና እኔ አስተካከልኩት የሚል ልክፍት ተጠናውቷቸዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም የሰሩት ስህተት አይታያቸውም፡፡
ላለፉት ሶሰት ተከታታይ መንግስታት የታየኝ ትልቁ መመሳሰል የስልጣን ገደብ አለመስጠት ሆኖ እኔ ጥሩ ሰራሁ እኔ ብቻ ፍጹም ከኔ
ወዲያ ላሳር እያሉ የስልጣን እድሜ ማራዘም... ትልቅ ቁስል ጥሎብናል! ይቅርታ ከርዕሳችን ውጪ ሄድኩ መሰለኝ፡፡
ትውልድ የራሴ
የሚለውን ታሪክ እያጣ የባዕዱን የሚናፍቅ እየሆነ፤ በባዕድ ታሪክ ተረት ተረት እየሰለጠነ፤ ለማመን እንኳ የሚያስቸግሩ አፈ-ታሪኮች
በመጽሐፍ፣ በትምሕርትና በ‹‹ፊልም›› እያየ ከሚያድግ የራስን ታሪክ በተረት መልኩ እየተመለከተ ቢሰለጥን የሚሻል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ንጉሰ ነገስት ቀ.ኃ.ሥ ሐምሌ 12 ቀን 1947 ዓ.ም እንዲህ አሉ "ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት እውነተኛ ትምሕርት የኑሮ ዘዴና የእጅ
ስራ ጥበብ ብቻ ሳይሆን የወጣቶቹን የመንፈሳዊ ዕውቀትንም ያገር ልማድንም ማክበር ጭምር የሚያጎለምስ መሆን አለበት"፡፡
ወደ ጽሑፌ አላማ የሚያመራኝ ይህ ሃሳብ ነው፡፡ የአንድ አገር ስልጣኔ በድንጋይ ጥበብ፤ እጅ ስራ እና የባዕዳንን ስልጣኔን ባህል
መከተል ዘመናዊነት ወይንም እድገትን ሊለካ አይችልም፡፡ እንደውም ውድቀትን ያመላክታል ብዬ አስባለሁ፡፡
በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ በተለይ የንቡረዕድ ኤርሚያስ ከበደን መጽሐፍት
ሳነብ ያገኘሁትና በ2005 ዓ.ም ለህትመት ከበቁት መጽሐፍት ‹‹ጥንታዊው ውጊያ›› /ግደይ ገብረ ኪዳን/ ጋር ያገናኘሁበትን እንመልከት፡፡ ንቡረዕድ ኤርሚያስ ስለ ሰላምታ አሰጣጣችን
ባህልና ሚስጥር ሲያስረዱን ኢትዮጵያዊያን ሰላምታ ሲሰጣጡ ‹‹እጅ ይነሳሉ›› እንጂ ‹‹እጅ አይሰጡም›› ይሉናል፡፡ በምክንያትም
አስቀምጠዋል፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ባህላችን እንደተበረዘ የምናውቀው ሃቅ ነው፡፡ በዚህ ጊዜም
ነበር የሰላምታ አሰጣጣችንን እጅ ወደ መስጠት/ በመጨባበጥ/ የተቀየረው፡፡ እንደ ግደይ ገብረ ኪዳን መጽሐፍ አገላለጽም ሚስጥራዊ
ቡድናት ከሚታወቁባቸው ድብቅ ምልከቶች አንዱ በእጅ ሰላምታ አሰጣጥ መሆኑን ስመለከት በእጅጉ ደንቆኛል፡፡ ታሪክን፣ ቋንቋንና ባህልን
በመጠበቅ ከሚታወቁት ህዝቦች ተምሳሌት ጃፓንን ስንመለከትም የሰላምታ ባህላቸው አሁንም ድረስ እንደጠበቁት መመልከት እንችላለን፡፡
ለኛ ግን ይህንን አሁን ማሰብና ማውራት እንደ "ቅዠት"
የሚታይ ይመስለኛል፡፡ በርካታ ነገሮችን መመልከት እንችላለን፡፡ በየቦታው የምናያቸው የምግብ ቤት፣ የንግድ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣
ታላላቅ መስሪያ ቤቶች ምንም እንኳ በተለያየ ጊዜያት ከአንድ አገር ወደ አንድ አገር የስልጣኔ መወራረስ ሂደት ቢኖርም ወደራስ ባህል
ማዛመድ የራስን ባህል ማስተዋወቅ እና በለውጥ ውስጥ ራስን መፈለግ ፈጽሞ እየጠፋ የሄደ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በማሰብ ታሪክንና
ባህልን በማስጠበቅ ለሚኖር ሰው ይህ ህመም ነው፡፡
ይህንን እንደ መግባቢያ ካልን ወደ ርዕሳችን ሀሳብ ብመለስ በምክንያት የምንግባባ
ይመስለኛል፡፡ የሩቅ ምስራቋ ንግስት ‹‹ቻይና›› በአለም ደረጃ በምጣኔ ሐብት እድገት ቁንጮ አፍሪካን ከምንም ጊዜውም በተለየ የተቆጣጠረችበት
ወቅት አሁን ይመስለኛል፡፡ የመንገድ፣የትራንስፖርት፣ የህንጻ ግንባታና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በእርግጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያስፈልጉን
የሚችሉበት በመሆኑ አዎንታዊ ገጽታውን ልንክድ አንችልም፡፡ ‹‹እኔና ቹ›› የጋዜጠኛ ፍስሃ ያዜ መጽሐፍ ብዙ ታሳስበናለች፡፡ በእርግጥም
ኢትዮጵያ ለዘመናት የእነዚህን ልማቶች ስትጓጓና ስትናፍቅ ኖራለች፡፡ ስልጣኔን አንቀበልም፤ የምጣኔ ሃብትን እድገት አንፈልግም ልንልም
አንችልም፡፡ በእርግጥም ያስፈልጉናል! ጥርጥር የለውም! ዋናው ቁም ነገሩ ግን በእነዚህ እድገቶችና ልማቶች ማንነታችንና ባህሎቻችንን
እየጨፈለቅን ከዚያም አልፎ የሌሎችን ባዕድና ሰይጣናዊ መልዕክት ያዘሉ ወጎቸን ፣ባህል፣ ስልጣኔና ህልውና ብቻ የምናስቀድም ከሆነ
ህመሙ የባሰ ነው፡፡ የራስን እየዘነጉ፣ የራስን እየናቁ የሌሎችን መሸከም ከሆነ ለኔ ይህ መሰልጠን ሳይሆን ‹‹መሰይጠን›› ወደ
ሚለው ቃል ይለወጥብኛል፡፡ መሰልጠን ለመሰይጠን፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በተደጋጋሚ ገልጾልናል፡፡
ቻይና የራሴ ታሪክና ስልጣኔ አለኝ ብላ የምታምንና ባወቅንም ባላወቅንም ይህንን
ስልጣኔዋንና ታሪኳን ልታስቀምጥ ትሞክራለች፡፡ ይህ የማንም የሰለጠነ አገር ሴራ ነው፡፡ በተለይ የዋህ ህዝብ ሲገኝማ ጨዋታው የሰፋ
ይሆናል፡፡
ቻይናዊያንና ታላላቅ የእስያ አገራት በኮንፊሺየስ ህልውና ውስጥ ሆነው የባህል፣ የፖለቲካና፣ የስልጣኔያቸውን
መሰረት ይከተላሉ፡፡ ምዕራባዊያንን በሶቅራጠስ እንደሚታወቁት ሩቅ ምስራቆች በኮንፊሽየስ አስተሳሰብ ይመራሉ፡፡ ኮንፊሽየስ በቻይና
ከ500 ዓመት በፊት ነበረ ሰው ሲሆን በሩቅ ምስራቅ ውስጥ ለተፈጠሩ የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ እና የትምህርት አስተሳሰቦች
ላይ መሰረት የጣለ ነው፡፡
"ዪን" እና "ያንግ" Yin and
Yang በሩቅ ምስራቅ ፍልስፍና ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ስሞች ናቸው፡፡ ከላይ ከስዕሉ ለማየት እንደምንችለው በሁለት የጥቁርና የነጭ
ምልክቶች የቀረቡልን ምስሎች ስያሜያቸው ከሁለት የተለያዩ የምድር ተቃራኒ ክስተቶችን ያመላክቱናል፡፡ በአንድ ላይም ተዋህደው ያታያሉ፡፡
‹‹ዪን ኤንድ ያንግ›› ይሏቸዋል፡፡ በአንድ ክብብ ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ቀለሞች ከላይ ወደታች ከታች ወደላይ ሁለት ጽንፍ ተቃራኒ
ክስተቶች ለማመላከት የተሰየሙ ናቸው፡፡ ዪን /Yin/ አብዛኛውን
ጊዜ አሉታዊ፣ ጨለማን፣ ሴትነትን፣ መሬትን፣ ቀዝቃዛነትን፣ የመዘግየትንና መሰል ሃሳቦችን ሲይዝ በተቃራኒው ደግሞ ማለትም ያንግ
/yang/ አዎንታዊ፣ ወንድነትን፣ ሰማይን/ገነትን/፣ ብርሃንን፣ ሙቀትን፣ ፍጥነትን ይወክላል፡፡ የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን
ቁርኝት በማሰብ ቻይናዊያን የዪንና ያንግን ክበባዊ ኡደት ከብረት፣ ከእንጨት፣ ከውሃ፣ ከእሳትና ከመሬት ጋር ማገኛኘት ከጥንት ፍልስፍና ጋር ሢወራረስ የመጣ ነው፡፡ ሁለቱንም
በተረጋጋ መንፈስ ማቆምና ማሰብ ባንችልም በተለዋዋጭ ሚዛናዊ እሳቤ ማስቀመጥ የሚል እይታን እናገኛለን፡፡ የአንዱ መኖር ለሌላኛው፤
የአንዱ ጥንካሬ ለሌላኛው ድክመት ይሰጠዋል፡፡ አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ዪን ነው ማለት አንችልም፡፡ አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ያንግ
ነው ማለትም አንችልም፡፡ አንዱ አንዱን ይመግበዋል፡፡ ከዛም ወደ ሌላኛው ይታደሳል፡፡ ጠንካራ የነበረው ደካማ እየሆነ ደካማ ደግሞ
የነበረው እየጠነከረ ኡደቱ ይቀጥላል፡፡ ዪን ያንግን ይፈጥራል ያንግ ደግሞ ዪንን ያነቃቃዋለል /ይቀሰቅሳል/፡፡ የጠዋት ፀሐይ መውጣት
ለማታ ፀሐይ መግባት ወሳኝ ሲሆን፤ የገባቸው ፀሐይ ለሚቀጥለው ቀን ፀሐይ መውጣት ሽግግር ትሆናለች፡፡ ብርሃን ጨለማን ጨለማ ብርሃንን
ይተካል፡፡ የአንዱ መብዛት አንደኛውንም እንደሚጎዳው ይገለጻል፡፡ እንዲህ እና በተላያዩ ሃሳቦች የሚከሰተውን ተፈጥሪአዊ ልዩነት
በማስተካከል የዪን እና ያንግ ንጽጽሮች ይቀጥላሉ፡፡ እንደ ፍልስፍና ከዚያም አልፎ ወደ ሃይማኖት ንክኪ ስንሄድ በግለስብ ደረጃ
መልሱንና ውሳኔውን በመተው ወደ ግል ሃሳቤ እቀጥላለሁ፡፡
ከአለማችን
ምስጢራዊ ቡድናት ውስጥ ከሚታወቁት የፍሪ ሜሰኖች ማህበር ይህንን አስተሳሰብ ባልተለያየ መልኩ ሲያራምዱት እናስተውላልን፡፡ በአብዛኛው
በጥቁርኛ ነጭ ምንጣፍ በተደጋጋሚ በተለይ በሙዚቃው የምንመለከተው የጥቁርና ነጭ ምንጣፍ ከዚሁ አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ብርሃን እንዳለ ሁሉ ጨለማ አለ፤ ላይኛው እንዳለ ሁሉ ታችኛውም አለ፡፡ ጨለማ እንዳለ ሁሉ ብርሃን አለ፤ ታችኛው እንዳለ ሁሉ ላይኛውም
አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡ የሱ ተቃራኒም ሰይጣን አለ፡፡ ሰይጣን አምላክ ነው የሱ ተቃራኒ እግዚአብሔር ወደታች ይሆናል
ማለት ነው ወደ ሚል ድምዳሜ ያደርሱናል፡፡ `In God we trust` የሚለው አባባል /ሁልጊዜ የምናውቀውን ፈጣሪ እግዚአብሔርን
ማለት እንዳልሆነም ያስታውሱ፡፡/
እንግዲህ የዚህ ጽሑፍ አላማ ይህንን አምልኩ ይህንን አታምልኩ ሳይሆን፡፡ ማለት
የተፈለገው አንድ አገር/ቡድን ወይም ማህበር/ ስልጣኔውን ሲያስፋፋ በዛው ውስጥ እያስፋፋ የሚሄደውን የአስተሳሰብ ተጽዕኖ ልብ እንድንል
የሚያሳስብ ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ የሌላኛውን ባህል ታሪክና ስልጣኔ ሳይመለከት የራሱን ብቻ የሚያረምድ ከሆነ በዚህኛው አገር ሰው
የለም እንዴ ያስብላል፡፡ በ2012 የተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክስ ይዞት የወጣው አርማ 2012 የሚለው ቁጥር zion ‹‹ፅዮን›› የሚል ስለሆነ ይቀየርልን የሚል መልዕክት ከወደ ኢራን አገር
ተሰምቶ ነበር፡፡
ቻይና ያልገባችበት ቦታ የለም፡፡ በዚህ ውስጥ የስራ ባህልን፣ ጠቃሚ የስልጣኔ
ውርሶችን በሚገባ ለይተን ከራስ ባህልና ታሪክ እንዲሁም ስልጣኔ ጋር በማጣራት ልንፈጽምና ለመጪው ትውልድ ልናስተላልፍ የሚገባ ይመስለኛል፡፡
ስለ አንበሳ አውቶብስ ወደ ‹‹ቢሾፍቱ ባስ›› መቀየር በቴክኖሎጂ ሽግግርና
ለውጥ፤ እድሜ ጠገብ ከሆኑ አገልግሎት ሰጪ የከተማ አውቶብሶች ወደ አዲስና ያውም በአገር ምድር የተገጣጠሙ መኪኖችን ስናገኝ የምናበረታታው
የምንደሰትበት ነው፡፡ በአንድ ወቅት በማላስታውሰው ጋዜጣና ስም የወጣ ጽሑፍ እንዳለ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ጸሐፊው ያቀረቡት
የአንበሳ አውቶብስ ምልክት ለማስታወቂያ በሚለጠፉ ምስሎች የአንበሳ ምልክቶች እየተሰረዙ መሆኑን የጠቆመበት ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ
በአለም የምንታወቅበት አንበሳ ምልክት ቀስ በቀስ ወደ ሌላ ባዕድ ምልክት ሲቀየር ደግሞ በይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው
ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ‹‹ቴሌ ኮሚዩኒኬሽን›› ስያሜውንና አርማውን ሲቀየር ይዞት ብቅ ያለው ምልክት ብዙዎችን ሳያሳስብ እንዳልቀረ
አንዘነጋውም፡፡ የአንበሳውን አርማ የተካው የእንግሊዘኛ ፊደል የ‹‹ኢ›› ምልክት ሲሆን ይወክላል ተብሎ የቀረበው ትርጉም ግን የሁልጊዜም
ጥያቄያችን ነው፡፡ እንደውም የዚህ ምልክት ‹‹በስሞል ሌተር ኢ›› /e/የቀረበ አረንጓዴ ምልክት በዪን እና ያንግ አርማ የምናየውን
የአንዱን ነጠላ አርማ ይዞ መውጣቱን ማሳሰብም አያስኮንንም፡፡
አንደኛውን ቆርጥን ስናዋወጣው የምናገኘው የ'e'ን
ምልክት ሊሆን አይችልም?ይህንንም ከአዲሱ የቴሌ አርማ ጋር ያነጻጽሩ፡፡
ወደ ውስጥ እየተመራመርን በየጊዜው የሚወጡትን
ምልክቶች ምንነት ካጠናን ከጀርባ ብዙ ሚስጥራት ይከተላሉ፡፡ የራስ ሳይሆን የባዕድ አስተሳሰብ ቀንበር ስር መውደቅና የአንድን አገር
ታሪክ ህልውና እንዲሁም የወደፊት መጻኢ ተስፋ የሚያጨልም፤ አገርንና ትውልድን ታሪክ አልባ ማድረግ ስለሚሆን የሚመለከታቸው ክፍሎች
ትምህርት እንዲወስዱ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በስህተት ካለማወቅ ወይስ ሆን ተብሎ? መሪዎቻችንን እንጠይቃለን፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል
ሰውም ይህንን እንደ ቀላል ነገር መውሰድ የለበትም፡፡ እኔ የሚታይኝን ግንዛቤ ሌላው ላያየው ይችላል፡፡ እኔ የማላየውን ደግሞ ሊያይ
የሚችል ስለሚኖር በጋራ የምናስብበት ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
እድገት እንፈልጋልን፤ ስልጣኔ እንሻለን፤ ለውጥ እንናፍቃለን
ነገር ግን ታሪክን ባህልን ወግንና ማንነትን እየዘነጉ ከሆነ ከሰውነት ድርሻ ያስወጣናል፡፡
ሁልጊዜም የሚገርመኝ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ትምህርት ቤት/ አ.አ ዩኒቨርሲቲ/
ነው፡፡ የነበረው ተማሪ ትንሽ ሆኖ ይሁን ወይንም የተለየ ትውልድ ሆኖ አላውቅም በየጊዜው ለሚነሱ ሃሳቦች ምሁራዊና አገራዊ ምለሽ
ይሰጡ ነበር፡፡ ለሌሎች አገራት መብትና ህግ መጣስ ድረስ ይታገሉ ነበር፡፡ ዋነው ተጠቃሹና ሁላችንም የምናከብረው ዋለልኝ መኮነን
ነው፡፡ ከዚሁ ከኔ ርዕስ ጋር የሚሄደውን ገጠመኝ እናስታውስ፡፡
የብሔራዊ ባህላችንን ሊያዳብርና ከልጅ ልጅ ሊተላለፍ የሚገባው የዩኒቨርሲቲውን
አዳራሻችን ከቶውም የምዕራብ ቡትቶ የለበሱ ልጃገረዶችን እግር የምናይበት መድረክ ሊሆን ሊሆን ይገባል? በሚል ሃሳብ
ዋለልኝ በተቋሙ በምትታተም ‹‹ታገል›› "ጋዜጣ" ስር ሃሳቡን አቀረበ፡፡ በ 1960 ዓ.ም ከአሜሪካ በመጡ የ‹‹ፋሽን››
ትርዒት አቅራቢዎች የነበረውን ተቃውሞ ያቀረቡበት አድማ 50 ዓመት አልሞላውም፡፡ ከአሜሪካን የመጡ እኚህ አጭር ቀሚስ ለባሾች
/ሚኒ ስከርት/ ለኢትዮጲያዊያን ሴቶችም የማስተላለፍ አላማውን አልተቀበሉትም፡፡ በተማሪዎችን በመንግስት መካከል አለመግባባት ተፈጠረ፡፡
አድማ ተካሄደ፡፡ መንግስትም አድማ ያስነሱትን ተማሪዎች አሰረ፡፡ ትምህርት ለተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ፡፡ ነገር ግን መንግስት እጁን
ሰጠ፡፡ ይታያችሁ መንግስት እጅ የሰጠበት ጊዜም ነበር፡፡
ሰው ያሻውን ይልበስ፤ የፈለገውን ይከተል ነገር ግን አንድ ዜጋ ታሪኩን ባህሉንና
ወጉን በሚገባ ጠንቅቆ ካደገ እንደዘኒህ አይነት መጤ ክስተቶችን ሳይገደድ የሚያደርግበት አጋጣሚ እንደሚከሰት መገመት አለብን፡፡
ሁሉም ባህል ሁሉም ወግ ይጠቅማል እያልኩ አይደለም፡፡ ጉዳቱንና ጥቅሙን በዘመናዊው ስልጣኔና ዓይን እያሳደግን ብንሄድ የሚበጅ ነው
ብዬ አስባለሁ፡፡ ነው ወይስ ተሳሳትህኩ? የ60 ዎቹ ትውልድ ሁሌም ይገርማኛል፡፡ የአገር ፍቅር፣ የባህል፣ የታሪክ ክብሩ ልዩ ነበር፡፡
ፈላጭ ቆራጩ ደርግ በብረት የደፋው፤ ወያኔ/ኢህአዴግም/ የቀበራቸውን በየሜዳው ቀሩትን አሁንም በመላው አለም የተሰደዱትን ስናስብ
ይህች አገር ለተሮርቋሪዎቿና ለተንገብጋቢዎቿ አትሆንም ያስብላል፡፡ በዚህ ትውልድ ብዙ እውቀት፣ ሃይል፣ ገንዘብና እድል ያላቸው
ዜጎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ አንድ የተሸሸገ ትውልድ ግን ያለ ይመስለኛል፡፡ ትውልድ በመንፈስ ሲጠፋና ሲሞት ማየት ምንኛ አለመታደል
ነው? በተለያዩ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ከተፈጠሩ ሁሉም
የተማረ ዜጋ አገሩን ታሪክና ባህል ቢጠብቅ በሚፈጠሩት አዳዲስ ለውጦች ውስጥ ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ለማግኘት አንቸገርም፡፡ የሳይንስ/
ሥነ እውቀት/ እና የቴክኖሎጂ /ኪን/ አዋቂዎች፣ የምጥኔ ሃብትና የህብረተስብ ሳይንስ ምሁራን፣ የስነ-ጥበብ ሰዎች ታሪክንና ባህልን
ተረድተው፤ የኔነት ስሜት በውስጣቸው አድሮ ስራቸውን ቢሰሩ ለውጡ
የራስን ታሪክና ባህል እንዲሁም ስልጣኔ ለማስተዋወቅ ጥሩ በር ይከፍታል፡፡
ፊልሞችችን/ሰፋድለ ስፋድለ ስዕል ወይም ሥዕላዊ ተውኔቶቻችን እጅግ አሳፋሪ
ደረጃ የደረሱበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ቋንቋዎቻችን በራሳቸው ህልውናቸው እየጠፋ እየተዳቀሉና ስያሜ ያጡ ቃላቶች ተበራክተዋል፡፡
አዳዲስቃላት ሲመጡ ቀጥተኛና ትክክለኛ ስያሜ የሚሰጥ ቡድን መስፋፋት አለበት፡፡ ለተተኪውም ትውልድ ማስተላለፍ የሚገባን በቋንቋችን
ስያሜ የሌላቸውን ቃላት ከሆነ እውነትም አንድ ትውልድ ተሸሽጓል ወደ ሚለው ሃሳብ ያመራናል፡፡ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ቁጥጥር
ተቃም የ2005 ዓ.ም አመታዊ ዝግጅት ሲያከብር ይዞት የወጣው መፈክር ‹‹ክሬቲቪቲ ዘ ኔክስት ጄኔሬሽን›› ይሰኛል፡፡ ይህ በራሱ
የሚያሳይን ነገር አለ፡፡ በመንግስት ደረጃ እንኳ ያለልታሰበበት መሆኑን ልብ እንበል፡፡ አንዳንደ የ‹‹ሬድዮ›› /ነፋስ ድምፅ/
ዝግጅቶቻችን እግር ጥሎኝ ስከታተል በእጅጉ የሚያሳምም ነው፡፡ ብርሃኑ የሚባል ስም ‹‹ብሮስ›› ተመስገን ‹‹ቶም›› ሌላም ሌላም...
ስልጣኔ ሌሎችን ለመምሰል ይሉሃል ይህ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ ጉዳዮች ሞልተዋል፡፡ ለማን አቤት እንደሚባልም አልታወቀም፡፡
ከዚህ በታች የቀረበውን ምልክት በሚገባ ያስተውሉ፡፡ ቢሾፍቱና ሂንግ
‹‹ቢ እና H›› በዘላለማዊ "የዪንና ያንግ" ቁርኝት ተምሳሌት፡፡ ቻይና ትፈጥራለች ኢትዮጲያ ታነቃቃለች.? እስከመቼ!?
No comments:
Post a Comment