ለፕሮፌስር መስፍን ወ/ማርያም
እና ለዲቆን ዳንኤል ክብረት የቀረበ ሃሳብ፡፡
በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርዓአቱን የመሰረቱን
አልናገረም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን››
**
ውሃ የሌለበት ጅረት
ሚስት የሌለችበት ቤት
ጀግና የሌለበት ጦርነት
እውነት የሌለበት ሙግት
ሁሉንም አይጠቀሙበት
ተጠየቅ!
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎች፣ ወጎች ሰልጣኔ እና የታሪክ ሃብታም ነች፡፡ ከቀን ወደ ቀን፤
ከወር ወደ ወር፤ ከአመት ወደ አመት፤ ከዘመን ወደ ዘመን ስንሸጋገር ግን ይህ ሁሉ ሃብት ሲዳከም ሲቀዘቅዝና ደብዛው ሲጠፋ
እያየን እንገኛለን፡፡ ብዙ ነገሮቻችን አሁን ላይ የሉም:: የጥንቶቹ ትክክል አልነበሩምና አሁን እየተጠቀምናቸው አይደለም ብለን
ብንወስድ ካደጉ የተባሉ ሀገራት ግን የጥንት ታሪኮቻቸውን ከዘመናዊው ስልጣኔና ጊዜ ጋር በማጣመር የበለጠ ሲምዘገዘጉ፡፡ እያየን
ነው ለምሳሌ እንግሊዝና ጃፓንን መውሰድ እንችላለን::
የእንግለዝ
ክሮዋዌል አገሩ የኢንዱስትሪ አገር እንድትሆን ያመቻቸው አብዮት ግቡን ሲመታ የጃፓኑ አፄ ሙትስሒቶም ሂቶም ጃፓንን ከመሳፍንት
አገዛዝ ነፃ ሲያወጣ የኛው አፄ ቴዎድሮስም ተመሳሳይ አላማ ነበረው ታዲያ የትኛው ተሳካ?
እንገሊዝ
በ28 እጥፍ ትበልጠናላች የሚል እሳቤ አለኝ፡፡ 1ፓውንድ ለ28 ብርን በማሰብ፡፡ እንግሊዝ አሁንም የቀደመ ማንነቷን ከዘመናዊው
ስልጣኔ ጋር በማዋሀድ ቀደምትነቷን እያሳየች ትገኛለች::
አንዳንዴ በቴሊቭዥን መስኮት የፓርላማቸውን ክርክር በምመለከትበት ወቅት
አስተውላለሁ፣ እናዳዳለሁ፡፡ ብዙ ትምህርት እወስዳለሁ፡፡ በጣም
የሚገርመው የፓርላማው አይነት ክርክር ሙግት በኛው አገር የነበረ በህዝቡ ዘንድ እንደ ባህል ሆኖ የሚሰራበት የታሪክ ክስተት
ነበር፡፡ ተጠያቅ! ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሙግት ስልቱን ቀይሮ በዘመናዊው ስልጣኔ ተደግፎ ህግና ደንብ ወጥቶለት ጊዜና ገደብ
ተሰጥቶት ብንጠቀምበት የተሳካ ታሪክ አካል ያደርገው ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለ ትውልድ ግን ይህን ባህል አያውቀውም:: ይህንን የአደባባይ የችሎት ባህል ወይንም ልማዳዊ የአሞጋገትና የዳኝነት ስርዓት
የዘመናዊውን ለውጥ ተፅኖ መቋቋም አቅቶት ከአደባባይ ገለል ማለት አልፎም ደብዛው የጠፋ የታሪክ አካል ሀኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
መክሸፍ የሚለው ቃልስ አያሰጠውም ትላላችሁ? የግሪክ ፈላስፎች ቀኑን ሙሉ ሽንጣቸውን ገትረው ሲወያዩና ሲከራከሩ ሃሳባቸውን
ሲያፋጩ እንደነበር አንብበናል፡፡ ፍልስፍናው በክርክር /በሙግቱ/ ሲቀርብ ፈጣሪ አለ የለም የሚለው ከኾነ በተገለጠ እውነት ላይ
መሟገት አዕምሮንና ጊዜን ማባከን ይመስለኛል፡፡ በተጨባጭ እውነቶች/በተረጋገጡ እውነቶች/ ላይ ግን መሟገትና መከራከር ግን
ህዝብን እያስተማሩ ወደ አንድነት ወደ እውነት የሚያመጣ በመኾኑ ሊበረታታ የሚገባ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡
ይህንንም በማሰብ ታሪኮቻችን ከሽፈው ይቅሩ ማለት ሳይሆን ያሉበትን
በመፈተሽ የሚጠቅመውንና ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ እንድንጠቀምበት መቻል ታላቅነት ነው፡፡ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የከሸፈን ወይም
የጠፋን ታሪክ መደተሸ ወደ ታሪክ ስኬትም የሚመራ ጭብጥ ይኖረዋል፡፡
‹‹በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርዓአቱን የመሰረቱን
አልናገረም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን››
እየተባለ ሁለት ከሳሽና ተከሳሽ የአሞጋገትና የአነጋገር ሰልትን
የመቅሰሚያ፤ ህግና ዳኝነትን የመመሪያ፤ ከሹማምንትና ከመሳሰሉት ከፍተኛ ሰዎች ጋር የመተዋወቂያና ለዳኝነትም ሆነ ለሌላ ስልጣን
የመመረጫ ቦታ ጭምር በመኾኑ ትልቅ ሰፍራ የነበረው ባህል ነበር::
ልምድ ያላቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ የሚባሉት ታሟጋቾች እንኳ
ልምድ ከሌላቸውና ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ተመጓቾች በሚቀርቡበት ወቅት የባለ ብዙ ልምድ ተሟጓች ደካማ ተሟጋቹን በንቀት አይን
በማየት እንዴት እንደሰደበው እንዲህ ሲል ሃሳቡን ይሰጣል::
ባለ ልበልሃ
ያጤ ሰርዓቱን የመሰረቱን
አልናገርም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን
በሳማ ሲባላ ጣቱን የሚልሰው
አደባባይ ቆም አንድ የማይመልሰው
ሚሰቱ ስትቆጣው እጓሮ
እሚያለቅሰው
አንተም ከኔ ጋር እኩል ሰው እኩል
ሰው፡፡ በማለት ይናገራል፡፡
ይህ
ባህል በሰለጠነው ህዝብ ዘንድም አንደ ጥብቅና ስራ በመዘናዊ
መልኩ ሲቀርብ እናየዋለን፡፡ የአሜሪካ የዳኝነት ስርዓት መልኩን ለውጦ የቀረበ ይመስለኛል፡፡ ማትሎክ የተባለ ተከታታ
የቴሌቪዥን ድራማን እያስታወሱ፡፡ በአንድ ወቅት አገራችን ይህንን ባህል ተጠቅማበት ነበር፡፡
ተበደልኩ የሚል፤ ተጓዳሁ የሚል ለሹሙ ሄዶ ጉዳዩን በማስረዳት ተከሳሹ
ይቀርብና በላ ልበልሃ እየተባበሉ እውነትን ይዘው ይሟገቱ
ነበር:: ከዛም በዳኛው ፈራጅነት በታዳሚው መስካሪነት ፍርድ ተፈርዶ ከሳሽ እስጥ ፈረስ ፣ ዋርዲት በቅሎ እስጥ፣ ዳማ ፈረስ
እሰጥ፣ ቦራ ፈረስ እሰጥ፣ ሳሙና ፈረስ፣ እሰጥ ሻሽ የመሰለ ማር እስጥ! እያለ ተከሣሽም ለፈረሰህ እገባ እየተባባሉ እስጥ-አገባ ወይንም ውርርድ ያቀርባሉ::
ተከሳሽም እሸነፋለሁ ብሎ ካሰበ /ጥርጥር ውስጥ ከገባ / ከሳሽ ውርርዱን ዝቅ እንዲያደርግለት ‹‹ውርርድህን አሰላስል››
ይለዋል፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ በቅሎ እስጥ ብሎ ከሳሽ ውርርዱ ተክሎ እንደሆን ‹‹ፈረስ እስጥ›› በማለት ይለውጥላትና ተከሳሽም ‹‹አገባ›› ብሎ
ለፈረስ ውርርድ የተተመነውን መቀጮ ይከፍላል፡፡ እስጥ-አገባ የሚለውም አባባል የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ተከሳሽ ክሱን ካመነ ግን ‹‹አጉራህ
ጠናኝ!›› ብሎ ሙግቱን ባጭሩ ይቀጨዋል፡፡
ባጉራህ ጠናኝ የተፈታ
መሀል አአዳውን የተመታ
የሚባለውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ እንዲህ እየተባባሉ እውነትንና
ፍርዱን የሚያገኙበት ባህል በዚህች አገር ነበር፡፡
ወቅቱ
እየሄደ የነበረውም ሙግት መልኩን እየቀየረ መሄዱ አለቀረም፡፡ በፈራጅና በተሟጋቾች መካከል ያለው ቅርበት፤ ሰውም ያለምንም ስራ
አደባባይ ሙግት ብቻ ማየትን እንደ ትልቅነት ማየቱ እየተከሰተ በመምጠቱ እንደጉዳት የሚታይ ቢሆንም እውነትን የያዘ ህሊና ያለው
ዳኛ እስካለና የሙግቱን ስርዓት የጊዜ ገደብና ደንብ ቢኖረው ጥቅሙ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህንንም ነጋድራስ ገብረ-ሕይወት ባይከደኝ
‹‹መንግስትና የህዝብ አስተዳዳር› የተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በአገራችን ስለሚገኙ ብሄራዊ ችግሮች ውስጥ ሙግትን በሚመለከት
ጽፈዋል፡፡ ስራን ትተው በክርክር በሙግት ብቻ መዋለን
እንደችግር አስቀምጠዋል፡፡ ሆኖም በዘመናዊ አሰራር ቢቀርብና እውነትን ወደ
አደባባይ የማውጣት ባህል፤ እንደበተ ርቱዕነትን፤ በራስ የመተማመንና ባህሉንም ከማስተላለፍ አኳያ ሊሰራበት የሚችል ጉዳይ
ይመስለኛል፡፡ ዶክተር ሀይሌ ወልደ ሚካኤልም ‹‹የሞራል ውድቀት ዝንባሌ በትምህርት እድገት በኢትዮጵያ ላይ›› የሚል ጥናታዊ
ጽሑፍ ይህንን ሀሳብ በመደገፍ አቅርበው ነበር፡፡
በዚህ
ሙግት ወቅት በችሎት ይሰሙ የነበሩት የሙግት ግጥሞችና ምሳሌያዊ አነጋገሮች ጥልቀትና ውበት አሰተዋፅኦ ሳያደርግ እንዳልቀረ በመጠቆም
ነገር ግን ሙግቱ እውነት የሌለው ከሆነ ስራ መፍታት በመሆኑ ጭምር እውነትን የሚያስገኝ ሙግት ( ክርክር) መታማመን ያለበት
ሂደት ቢኖር ህዝብ ቢማርበትና ቢለወጥበት አጅግ አኩሪ የሆነ ባህል መሆኑ እያጠራጥርም፡፡
በለ ልበልሃ
ያጤ ስርእቱን የመሰረቱን
አልነገርም ሀሰቱን
ሁሉ እውነት እውነቱን!
ላምህ ብትወልድ ዛጎላ
ሚስትህ ብትላብስ ነጠላ
አንተ ብትለው እጥላ!
አንደኛው
ሲለው አደባባይ የማያዘወትረውና የኑሮ ደረጃው ዝቅ ያለም ተሟጋች
በላ ልበልሃ ብሎ የተለመደውን ስንኝ ይከተልና
ላሜ ብትወልድ ዛጎላ
አውራውን አስመስል ብላ
ሚስቴ ብትለብስ ነጠላ
ቀን እስቲያልፍ ብላ
እኔ ብውል እጥላ
ያንተን ብጤ ነገረኛ ብጠላ!
በማለት የሆዱን ይመልሳል፡፡ በሙግቱ ወቅት ወቀሳ አሽሙርና ስድብ
የነበረበት ቢሆንም ይህንን ለይቶ በማውጣት በእውነትና በአመክንዮ
ከዛም መተማመንን በመያዝ መከራከር ግን ይቻላል፡፡ ስድብና
አሽሙርን በማስቀርት፡፡
ይህንን
ባህል የተለያዩ የውጭ ፀሐፊያን ጠቅሰውታል፡፡ ዶናልድ ሌቪን ‹‹በዋክስ ኤንድጎልድ ( ሰምና ወርቅ) መጽሐፋቸው የጠቀሱት
‹‹ሙግት በአማራው
ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ጉዳት ጠቅሰው አልፈዋል፡፡ ቻያናዊያን ይህንን ባህል አይጠቀሙበትም ነበር፡፡ ወደ ፍርድ ቤት መሄድን
እንደጊዜም ሆነ ገንዘብ አባካኝነት ይቆጥሩት ነበር፡፡ በቻይና ባለጉዳዮች በሻይ ቤት ውስጥ ተሰብሰበው በመወያየትና በመደራደ
በመካከላቸው ለተፈጠረው ቸግር መፍትሄ ይሹ ነበር፡፡ በማለት የፃፉ
ሲሆን ይህም ግን መልኩን ቀየረ እንጂ ተነጋግሮና ተስማምቶ ፍርድን ከማምጣት ጋር የሚለያይ አይመስለኝም:: ቀኑን ሙሉ ሲሟገቱ መዋል ጉዳቱ ግልጽ ነው፡፡ ቢሆንም ከላይ
እንደጠቀስኩት ጊዜና ገደብ፤ ስርዓትና ደንብ ይዞ ግን መገልገል የሚጎዳ መስሎ አይታየኝም ::
ጀርመናዊው
ፕሮፌሰር ኢኖ ሊተማንም ከፍተሃ-ነገሥት እየተጠቀሰ ፍትኀ፥
ርትዕ በሚሰጥባቸው ሽንጎዎች ( አደባባዮች) እየተገኘሁ የእስጥ-አገባን ሙግትና ፍርድንም በማዳመጥ ያስለፍኳቸው ቀናት ለኔ
እንደገና ትምህርት ቤት እንደ መግባት ነበር ብሏል፡፡:
ጄነራል
ቨርጂን ‹‹እኔ የማውቃት አቢሲኒያ›› The Abyssinia I know መጽሐፋቸውme በተሟጋቾች መካከል የሚደረገውን ሰርዓት
ማራኪ መሆኑን፤ የነበረውን የቃላት አጠቃቀም በተሟጋቾች መካከል የሚደረግ የሰውነት እንቅስቃሴ ሳይቀር እጅግ ውብ እንደነበር
ጽፏል፡፡ እንግዲህ አንድ አገር የኋላ ታሪኩን አጣርቶ በመያዝ ለአሁኑና ለወደፊቱ ትውልድ ጊዜው በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ በመደገፍ
ማንነቱን ካለቆና ካላስተላለፈ የታሪክ አስፈላጊነት የሚቀርበት እድል ሊከሰት ይችላል፡፡ የዚህም ፅሑፍ ዋና አላማ በኢትዮጵያ
ታሪክ ውስጥ የሚያጠነጥነውን ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፍ ላይ በመመርኮዝ በወቅቱ ለተነሱት ክርክሮች
ሀሳቦች ላይ በመታዘብ ለምን ተጠየቅ! የሚለውን ባህላችንን
እናስታውስበትም? በፕሮፌሰሩ መጽሐፍ በተቃራኒ ገጽታው ላይ ሃሳብ
ያላቸውን ሰዎች በማሰባሰብ ብንጠቀምበትስ የሚል ነው፡፡ በተለይ አስተያየት የሰጠውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን በማሰብ ይህ
ገጠመኝ በታሪክ ትልቅ ስፍራ ሊኖረው እንዲችል በማሰብ ጥያቄውን ለሁለቱም ግለሰቦች አስተላልፋለሁ:: በዚህ ርዕስ ጉዳይ
መጽሐፉን በማንበብ ያልተነጋገረ፣ ያልተገረመ፣ያልተበሳጨ፣ ያላዘነ፣ ያልተወያዬ፣ ያልጻፈ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡መክሸፍ እንደ
ኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ርዕስ ነው:: የዛሬውና የነገው ትውልድ ትልቅ መልስ የሚያገኝበት፤ ታሪኩን አውቆ ነገ ምን ልስራ ብሎ
እንዲያውቅ ሃሳብ እንዲገበይ የማያደርገው በመሆኑ ክርክሩ/ውይይቱ/
ቢሳካ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳ ከሳሽ ተከሳሽ ባይኖርም::
ፈራጅ ዳኛ ህዝብ ሆኖ ሊያወያይ የሚችል አካል ቢኖርና ለታሪክ ትምህርት ቅርበት ያላቸው ምሁራን፤ የሚመለከታቸው አካላት፤
ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ነኝ የሚል ግለስብ ቢሳተፍና ለህዘብ እውነቱ ቢቀርብ ለትውልድ ትልቅ አሻራ ሆኖ የሚያልፍ ተግባር
ይመስለኛል፡፡ ስለ መጽሐፉ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ/ም በብሄራዊ ቲያትር የቀረበ ቢሆንም አጥጋቡውን ውይይት ማድረግ
አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል ወይንስ አልከሸፈም የሚባል ነውን? በሚል ርዕስ በሁለት ቡድናት ቢካሄድ የሚኖረው
ታሪካዊ አሰተዋጽኦ ትንሽ አይባልም:: በትንሽ ነገር ብዙ መስራት ይቻላልና፡፡ ይህ ትውልድ እውነት ይፈለጋል! እውቀትን የያዘ
መረጃ የተደገፈ አንድ ሊያደርገው የሚችል ሀሳብ ይፈልጋል:: በታሪክ ውስጥ አንትና ይህን አደረገ:: ብሎ መፈራረድና ጥላቻን
መፍጠር ሳይሆን በታሪካችን ከነበሩ ክስተቶች ለአሁንና ለነገ ማንነታችን በምን መልኩ ሊወሰዱና ትምህርት ልንቀስምባቸው
እንችላለን? በሚለው ጉዳይ ላይ መወያየት የሚያወጣ ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ ይህ የሙግት ( የመከራከሪያ ) ባህል ተጠየቅ በሚል
መልኩ ቢዘጋጅ አንድም ባህልና ወግን ከማዳን አንጻር ሌላም እውነትን ነማስጨበጥ አንጻር ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ውሃ የሌለበት ጅረት
ሚስት የሌለችበት ቤት
ጀግና የሌለበት ጦርነት
እውነት የሌለበት ሙግት
ሁሉንም አይጠቀሙበት
እየተባለ የሚመካከሩበት ሙግት ነበረን
ካያያዝ ይቀደዳል
ካነጋገር ይፈረዳል
አንድንተ ያለ ዘንገኛ
አይወለደም ሁለተኛ
ፍየል መንታ ትወልዳለች
አንዱ ለመጣፍ
አንዱ ለወናፍ
መጣፉ እኔ ወናፉ አንተ!
እየተባሉ አሽሙር የሚነጋገሩበት ነበር በአሽሙር መነጋገር መሰዳደብ
ሳይሆን
መሪ የሌለበት መንግስት፤ እውነት የሌለበት ሙግት የሚለውን በመውሰድ
ለእውነት እንኑር! በግል ሀሳብንና መልስን ከመመለላስ ተቀራርቦ፣ ተያያዞ ለህዝብ አርአያ ሆኖ በታሪክ ትልቅ ስኬትን መፍጠር
ታላቅነትና አዋቂነት ይመስለኛል:: እንጂ ውስጥ ለውስጥ መጎነታተል፤ መተማማት የዚህ ዘመን የሚደገም መሆን የለበትም፡፡ ምንም
እንኳ ጊዜው ተቀይሮ በጽህረ ገጽ፤በጋዜጦችና በመጽሔት ክርክርን መመላለስ አንደ ዘዴ መቁጠር ብንችልም፡፡ የራሱን የቻለ መነሻና
መድረሻና ያለው መረጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ ተቀራርቦ፣ ተነጋግሮ፣ ሰላምነወ አሳይቶ በደስታና በፍቅር መለያየት የአገር ወግ ነው:: የአገር እድገት ነው፡፡ ከአያቶቻችን
የወረስነውም ነው፡፡ ተመካክሮ ይቅር ተባብሎ መኖር መታደል ነው፡፡ ሰለዚህ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ጋር በተጠየቅ! ዝግጅት እንዲገኙና ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን በሁለቱም ወገን ሀሳብ ያለው ግለሰብ (ቡድንም ) ሀሳብን እንዲያካፍሉን
እንዲያወያይና ከታሪክ እንድንማማር በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ አለምን የፈጠረ አምላክ ነው::
እንወያይ፣ እንመካከር፣ አንለወጥ!
- ይህ ደብዳቤ ለሁለቱም ግለሰቦች የሚደርስ ይሆናል፡፡
- ይህንን ዝግጅት ሊያዘጋጅ የሚችል አካል ይበረታታል፡፡
* ስለ በላ ልበልሃ /የጥንት እስጥ-አገባ ሙግት/ በሺበሺ ለማ
የተጻፈቸውን ተጠየቅ! መጽሐፍ ቢያነቡ በእጅጉ ይማረካሉ፡፡ በዚህች ትንሽ መጽሐፍ ብዙ ይማራሉ፡፡
(ተጠየቅ! ሺበሺ ለማ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት-1985)
የዚህን ጽሑፍ አዘጋጅ በtes_bel@yahoo.com
Tesfabelaynehh.blogspot.com ማግኝት
ይችላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment