Mar 12, 2013

ዲ.ዳንኤል ክብረት ከ‹‹ላይፍ›› መጽሔት ጋር አስደንጋጭ ቃለ-ምልልስ፡፡

‹‹የአከሱምንና የአቡነ ጴጥሮስን አይነት ሞራል ማጣታችን የታሪካችን ቁንጽል አካል ነው፡፡››
 ዲ.ዳንኤል ክብረት ከ‹‹ላይፍ›› መጽሔት ጋር አስደንጋጭ ቃለ-ምልልስ፡፡
በተስፋ በላይነህ
መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሐፍ ለንባብ ከበቃ ወዲህ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ፕሮፌሰሩ በርግጥ ለዘመናት ተደባብሶ የተያዘን ሃሳብ ይዘው መቅረባቸው ምሁርነታቸውን፤ የተሸሸገውን በማውጣት ህዝብ እንዲወያይበት ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ነገር ነው፡፡ የ5ና የ3ሺህ ዓመታት ባለታሪክ አገር፤ ከሜሶፖታሚያ ከባቢሎን ከሮም ስልጣኔ ጋር እኩል ትራመድና ትታይ የነበረች አገር እንዲህ በአለም ኋላ ቀርና በድህነት አዘቅት ውስጥ መታየቷ አይደለም ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቀርቶ አለም እንኳ የሚስማማበት ሀቅ ነው፡፡ ይህች አገር 30ና የአርባ ዓመት ባለታሪክ አደለችም፡፡ እንዲህ ስላጣኔያቸው ጣራ ደርሶ የምናያቸው አገራት መፈጠራቸው ሳይታወቅ ይህች አገር ነበረች፡፡ የገንዘብ መገበያያ ምንነቱን ሳያውቁ ይህች አገር ትገበያይ ነበር፡፡ የካም ህዝብ ቅኝ ግዛት ሲሰቃይ ተደራጅታና በሰው ግዞት ውስጥ መኖርን እንደ ህልውና ቆጥራ የታገለች አገር ኢትዮጲያ መሆኗንም አለም ያውቃል፡፡ /የአሁኑ ትወልድ በደንብ እያወቀው ባይሆንም/ የባቢሎንና የሮም ስልጣኔ የት እንደደረሰ ማየት እንችላለን፡፡ የኢትዮጲያ ስልጣኔ የት ደረሰ? የሌሎች ስልጣኔዎች እንኳ ወደሌሎች አገራት በመሸጋገር  ከባለታሪኩ ሂደት ባሻገር ተላልፎ አሁንም እያየነው እንገኛለን፡፡ ይህች አገር ግን የነበራትን ስልጣኔ አይደለም ለሌሎች አገራ ልታሸጋግር ለራሷ ህዝቦች እንኳ አላስተላለፈችም፡፡ ኢትዮጲያዊነት የትም ላይጠፋ ይችላል፡፡ ታሪክ አይፋቅምና፡፡ ለወደፊት ግን የዚህችን አገር ታሪክ በሚገባ ፈትሾ አሁን የት ደረስ? ምን ላይ ይገኛል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በታሪክ ውስጥ የተከሰቱትንን ማንኛውንም አሻራ በማጥናት የዛሬንና ለወደፊት ማስተላለፍ ታላቅነት ነው፡፡ እንግዲህ ይህቺን የታሪክ ባለሃብት፤ የስልጣኔ መነሻ  አገር አስከ አሁን የመጣችበትን ሂደት መርምሮ መሻሻል እና እድገት ካለ አጠናክሮ መቆየት ካለበለዚያም እየደበዘዘ የሚመጣ ከሆነ፤ ይባስ ብሎ ቁልቁል የሚወርድ ከሆነ መክሸፉ ግልጽ ነው፡፡ ታሪክ ከሸፈ የሚባለው ጠቅላላ ነገ የሚመጣውን ያጠቃልላል ማለት አይደለም፡፡ በፕሮፌሰሩም መጽሐፍ ይህንን አይጠቅስም፡፡ የትናንትናውን ታሪክ በመመልከት፤ እስከ አሁኑ ሰዓት ያለውን ፍጻሜ በማመዛዘን የትናንቱ ከዛሬው ሲነጻጸር ምን ላይ ደረሰ? ተሻሻለ ወይስ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ? ይህ ነው ትልቁ ጥያቄ!
 እስካሁን ከዳንኤል ክብረት ያየሁት ግን በመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ሳይሆን መክሸፍ በሚለው ቃል ብቻ ነው፡፡ ቃልን መሰነጣጠቅ እና እዛው ለዛው በመሽከርከር ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ በአንድ ወቅት በዳንኤል ክብረት ጡመራ ላይ ያነበብኩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ቀኑንና ርዕሱን ማስታወስ ባይቻለኝም የፍትሃ ነገስት ባለቤት የሆነችው አገራችን ከተለያዩ አገራት በተውጣጡ ህግጋት መደገፏን ያዘነበት ጽሁፍ ሁልጊዜም ከአዕምሮዬ አይጠፋም፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ በፓርላማ የተናገሩትን በመጥቀስ አገራችን ህግና ደንብ ፍለጋ ከሌሎች አገራት መሄዷ  አሳዝኖት ነበር፡፡ ታዲያ ይህንና መሰል ሃብቶችን ይዘን መጠቀም አለመቻላችን አያሳዝንም? አዋቂ ግን የሚያደርገው ዝም ብሎ ወሬ መጠረቅ ሳይሆን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄና ምሁራዊ ትንተና በማቅረብ ህዝብን ማወያየት፤ ችግሩን በማወቅ ምላሽ መፈለግ፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ጥቅም ላይ አልዋለም? ያኔ የህጎች ሁሉ በለይ እንዳልተባለ አሁን ለምን ሊገለጥ አልተቻለም፡፡ ቀጣይነቱ ለምን አልዘለቀም? ይህ ክሽፈት ነው፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ከሸፈ? ለምንስ ጥቅም ላይ መዋል አልቻለም? ብሎ በመጠየቅ የነገ ህልውናውን ለማስረገጥ መጠየቅና ምሁራዊ ትንታኔ ማቅረብ ግን ይቻላል፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ከሸፈ? ማለት ግን የነገውን የፍትሃ ነገስት ጥቅም ላይ ማዋል አያከሽፈውም፡፡ እንደውም እንዲሳካና ነገ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚረዳው ጅማሬ እንጂ፡፡ ስለዚህ ታሪክ ከሸፈ ስንል አጠቃላይ የነገን ታሪክ መዳረሻን አያጠቃልልም፡፡ እስከ አሁኑ ሰዓት ያለውን ሂደትና ተጨባጭ ህልውና ግን ሊያመሳክርልን ይችላል፡፡ የኋላን በመፈተሸ፤ የት ደረሰ ብሎ ሁነቱን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ያለበትን ሁኔታም በግልጽ በማየት በመፈተሸ የነገን ጉዞ መተንበይ ይቻላል፡፡ ይህን ሁሉ ሃሳብ የተረዳሁት ከመክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሃፍ ውስጥ እንጂ መክሸፍ ከሚለው ቃል አይደለም፡፡ የኢትዮጲያን ታሪክም ስንመለከት እስከ አሁን የመጣንበትንና ያለንበትን በማጤን ከትናንትናው ጋር በማመዛዘን ትናንት አለም የሚያደንቀውን የእጅ ስራ ጥበብ ሰርተን ዛሬ ለሌላ አገር ስልጣኔ መሰጠቱ ከክሽፈት ሌላ ምን ስያሜ ያሰጠዋል? በዚሁ ክ/ዘመን እንኳ ኢትዮጲያዊነት ከየት ወዴት እንደተጓዘ መመልከት ይቻላል፡፡ በመጨረሻው የንጉስ ዘመን እንኳ ህንዶች የአሜሪካን ዜግነት ለማግኘት አማርኛ ሲማሩ፤ ኢትዮጲያኖች ምንም አይነት ገደብ ሳይኖርባቸው እንደ ህንዶች የተወሰነ ኮታ ሳይኖርባቸው ተፈቅዶላቸው መመላለስ እንደቻሉ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ አሁን አይደለም እና መደበኛው ዜጋ ጳጳሳት የአሜሪካን ዜግነት እየያዙ ነው ተብለን በምንሰማበት ሰዓት ይህ የኢትዮጲያዊነት ስሜት እንዴት ተቀየረ? ነው ወይስ የድሮዎቹ ልክ አልነበሩም? እንደዛ አገርን መውደዳቸው፤ እንደዛ ለአገር መስዋዕትነት መክፈላቸው ልክ አልነበርም? አሁን ስንት ምሁራን ናቸው እየፈለሱ የሚገኙት? ለጊዜያዊ ስራ እንኳ ተልከው ጥገኝነት በመጠየቅና ስርዓትን ከመቃወም በግዞት መኖርን የሚመርጡ ሰዎች በየጊዜው እንደ አሸን እየፈሉ በምንሰማበት ሰዓት ካለፈው ሁኔታ ጋር ስናወዳድረው ከክሽፈት በላይ ምን ይገልጸዋል፡፡ ምክንቱን በማቅረብ መፍትሄ መውሰድ ግን የነገውን ሁኔታ አያከሽፈውም፡፡ የበለጠ እንድንጠነቀቅና እንድናስብበት ያደርገናል እንጂ! ብዙ ምክንያቶች ማቅረብ በተቻለ፡፡ ነገር መደጋገም ያሰለቻል እንጂ፡፡
  እጅጉን የገረመኝ ነገርም ይህ ነው፡፡ አንድ ስንት መጽሐፍ አነባለሁ ከሚለን ሰው ጋር ይህ ሃሳብ እንዲህ ማጨቃጨቁና አንድን መጽሐፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ ከሚል ሰው ይህን አይነት ምላሽ ማግኘቱ ያሳስባል፡፡ ያስቆጫል፡፡ ነገስ ማን ነው የሚገዛን ወደሚል ሃሳብም ይወስድና ያስጨንቃል፡፡ በ‹‹ላይፍ›› በሚባል በመጤ ቋንቋ በተሰየመ ‹‹መጽሔት›› ስር የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ቃለ-ምልልስ ሳነብ እስኪ ምን ብሎ ደግሞ ተናገረ ለማለት ተዋስኩት፡፡ በነገራችን ላይ እነ ‹‹አዕምሮ›› ‹‹ጦቢያ›› ‹‹ሙዳይ›› በተነበቡበት አገር በውጭ ቃል ስያሜ መጠቀማቸው አያስገርማችሁም፡፡ ይህች አገር የስንት ቋንቋ ባለቤት ሆና ሌላ ባህርን የተሻገረ ቃል መፈለግ ከክሽፈት ሌላ ምን ሊባል ይችላል?  መቃጠል ነው!
 በዚችሁ ‹‹ መጽሔት›› ቅጽ 7 ቁጥር 102 መጋቢት 2005 እትም ስር ከገጽ 3 ጀምሮ እስከ ገጽ 5 ድረስ ከዲያቆኑ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በአንዳንድ ቃላት የትየባ ግድፈት እያገጣጠሙ ያነባሉ፡፡ በተለይ ወደ መክሸፍ ታሪክ በሚገቡበት ጊዜ ደጋግመው ሊያነቡት ይችሉ ይሆናል፡፡ እኔ በበኩሌ እየተቃጠልኩ ያነነብኩት ቃለ-ምልልስ ነበር፡፡
  ቃለ-ምልልሱ የሚጀመረው ስለ ስድስተኛው ጳጰስ ምርጫ ሂደትና በተያያዙ ጉዳዮች ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ስር ያለኝ እውቀት ላይ ላይ በመሆኑ አልቀባጥርም፡፡ አንድ ሰው ስልሁሉ ነገር ሲቀባጥር ችግር ያመጣል፡፡ ሁላችንም በሁሉም ነገር የተካንን አይደለንም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን ብናተኩርና ብንካን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ብዙዎችንም መለወጥና ግልጽ የሆነ መረጃና እውቀት መስጠት ያስችለናል፡፡ እኔም አንብቤ ወደ ገባኝና አስተያዬቴን መሰንዘር ወደምችልበት ሃሳብ ላምራ፡፡
  በቃለ-ምልልሱም ከቤተክርስትያን ወጣ እንበል በማለት በቅርቡ  በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት በቀረበው የመጽሐፍ ውይይት የሚለው ጥያቄ እናመራለን፡፡ በስፍራው ለምን አልተገኘህም ተብሎ የተጠየቀው ዲያቆን ይህንን ነገር ካነሳኸው እናውራ በማለት ይቀጥላል፡፡ ዲያቆኑ የሚለው በአስፈላጊው ሰዓት አልሰማሁም መልዕክቱ የደረሰኝ በሶስተኛ ሰው ነው ነበር ምላሹ፡፡ በመጀመሪያ ግን ከብርሃኑ ደቦጭ እንደሰማ ይነግረንና ከዛም ከአሜሪካ በተደወለ ስልክ ማለትም አርብ ዕለት ስለዝግጅቱ ሰማሁ ይለናል፡፡ ለማረጋገጥም የፌስቡክን መልዕክት እመለከተዋለሁ ይላል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው በሚገባ ሳይነገረው ጽሁፍ ታቀርባለህ ከተባለ ችግር የለውም ማለት አንችልም፡፡ ችግር አለው፡፡ ነገር ግን በዝግጅቱ ቀርቦ ጽሑፍ ማቅረብ ባይቻል እንኳ ዝግጅቱ መኖሩን ከታወቀ ተገኝቶ መወያየት፤ ለህዝብ በግልጽ እውነትንና ሃሳብን ማስረዳት ከአንድ ኢትዮጲያዊ የሚጠበቅ ሃላፊነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግዴታ ነው ብለን ግለሰቡን ማስገደድ ባንችልም በአሁኑ ሰዓት አሳሳቢ ለሆነ ጉዳይ፤ በተለይም ሃሳብ የሰጠን ሰው ከመመልከትም አልፎ ይዞት ለተነሳው ሃሳብ የጠራ መረጃና አስተያየት  መስጠት የሚያስችል መድረክ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ እዚህ ላይ የግል ውርደት፤ ቂም፤ጥላቻ አይደለም የሚቀድመው ኢትዮጲያ ነች ቀዳሚዋ፡፡ ወደ ጦርነት እንኳ ተገድደን የሄድንበት ጊዜ እኮ ነበር፡፡ ይህ ደግም ከጦርነት ሺህ እጥፍ የሚበልጥ አጋጣሚ ትልቅ አገራዊ ጥቅም የሚያሰጥ መድረክ ነበር፡፡ በሃሳብ ለመወያት፤ እውነትንና እውቀትን ለማፋጨት የቀረበን ታሪካው አጋጣሚ መኖሩን እያወቅን አልተጋበዝኩም፤ ህጋዊ ማህተም ያለው ደብዳቤ አልደረሰኝም ብሎ ማመካኘት፡፡ በበኩሌ የተቃጠልኩበት ወሬ ነበር! በግድ መገኘት አለብህ እያልኩ አይደለም ዲያቆን- እያልኩ ያለሁት ስንትና ስንታ መነጋገሪያ የሆነ ሃሳብ ቀርቦ እስቀድመህም ያገባኛል ብለህ ሃሳብ መስጠቱ፤ ለፈጠንክበት ርዕስ ውይይቱ ምሁራዊ ሆኖ በግልጽ መቅረቡን አመካኝቶ መቅረት ለፍርድ የማይመች ውሳኔ ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ሲጀመርስ በጽሁፍህ ላይ ሃሳብ ለመሰንዘር ማን ጋበዘህ? ኢትዮጲያዊነት አልነበረም? ይመለከተኛል ብለህ አልነበረም? ነው ወይስ ይጻፉልን የሚል በህጋዊ ማህተም የተላከልህ ደብዳቤ ደርሶሃል? ከአንድ አንባቢ ነኝ ባይ ኢትዮጲያዊና ከአንድ መንፈሳዊ ነኝ ባይ አማኝ የማልጠብቀው ገጠመኝ ነበር ለኔ፡፡ በወቅቱም በጣም የማከብረው የታሪክ ተመራማሪ ብራሃኑ ደቦጭ እንኳ አልተጋበዝኩም! ለምንስ ሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጀው በማለት የሰነዘረከው ቡራ ከረዮ እጅጉን አስገርሞኛል፡፡ይህንን የመሰለ ዝግጅት ኢህአዴግ ያቀርበዋል ብለን እንጠብቅ ነበር? ለምንስ አንድ ያልታወቀ ድርጅት ወይንም መንግሰት ወይንም ግለሰብ አያዘጋጀውም? ዋናው ጉዳያችን ከቀረበልን ርዕስ ላይ ነው እንጂ ሌላ ጭቅጭቅ ወስጥ ምን አስገባን? በጣም ገርሞኝ ነበር በወቅቱ፡፡ ይህችን አገር የሚመራት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ነው? ክሽፈት! ለነገሩ በሰዓቱ አርቲስት ደበበ እሸቱ አሳማኝ መልስ ሰጥቶናል፡፡ የአፍሪካን ኳስ በደሌ ቢራ ለምን አስተላለፈው ተብሎ ይጮሃል እንዴ? እኔ ከቢራው ምን አለኝ? ከኳሱ እንጂ በማለት መልሶልናል፡፡ እግዜር ይስጠውና!
 ይቀጥላል ሁለተኛው ጥያቄ፡- ‹‹በመጽሐፉ ዙሪያ ለሰጠኸው ሃሳብ ምላሽ አለመስጠትህን ጠጠር ከወረወሩ በኋላ ዝም ማለትህን ከመጀመሪያው የሰጠኸው አስተያዬት ትክክል አለመሆኑን የሚያመላክት አይደለም?›› ለተባለው ጥያቄም ምላሹ በይበልጥ ያቃጠለኝና አንድ ጣሳ ውሃ ያስጠጣኝ መልስ ነበር፡፡ በስንቱ ልቃጠል አለች…
  ‹‹እንኳን አነስተኛ የገጽ ብዛት ያለውን መጽሐፍ ይቅርና ብዙ ሲ/ሺ ገጾች ያላቸውን መጻሕፍት አነባለሁ፡፡›› በማለት የመለሰው በእጅጉ ገርሞኛል፡፡ ከመገረምም አልፎ አበሳጭቶኛል፡፡ ለዚህች አገር ብዙህ ሺ ገጽ መጽሐፍ ማንበብ ምን ይጠቅማታል፡፡ ያነበቡትን በትክከለኛ መልኩ ተረድቶ ህዝብን ካልለወጠ! ብዙ ሺ ገጽ መጽሃፍስ ማንበብ እውቀት ሆኖ ነው? በአንድ ስንኝ እንኳ ስንት ሃሳብ እያስተላለፉ፤ በ30 ሴኮንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስንት ሰው መለወጥ የሚያስችል ማስታወቂያ እየሰተሰራ ባለንበት ዘመን ብዙ ሺ ገጽ ያለው መጽሐፍ አነባለሁ! ብሎ ማውራት ለኔ እንደ መልስ የሚቀርብ አልነበረም!
  የፕሮፌሰሩንም መጽሐፍ ባልከን መሰረት ደጋግመህ አንብበኸዋል እንበል፡፡ ደጋግሞ ማንበብስ አውቀት ነው? ይገርማችኋል በጣም የምወዳት የወንድሜ ልጅ አለች እድሜዋ 8 ነው ስሟን ያወጣሁላት እኔው ነኝ ብሌን ታባላለች፡፡ከቄስ ትምህረት ቤት የተማረችውንና የሸመደደችውን የግዕዝ ንባብ ሁልጊዜ ትልልኛለች፡፡ ትርጉሙን ግን አንዱንም እንኳ አ.ታ.ው.ቀ.ው.ም! ደጋግሞ ማንበብ ዋናውን ጭብጥ ካልያሳዘን ለምን እንደሆነ ተጎልቶ የሚወራው በኔ በኩል አልገባኝም፡፡ እባካችሁ የገባችሁ ካላችሁ አስረዱኝ! በተደጋጋሚም ዲያቆኑ የሚያነሳው ክሽፈት በሚለው አርዕስቱ ብቻ ነው፡፡ ለመጽሐፉም ክሽፈት የሚለው ርዕስ መሰጠቱን ከላይ ጠቅሰነዋል፡፡ የነገን ሂደት የሚያጠቃልል ሳይሆን እስካለንበት ጊዜ ያለውን የሚያመላክት ነው፡፡ አንድ ነገር ሲቋረጥ ከሸፈ ልንል እንችላልን ነገ ግን ከተስተካከላና በደረሰበት የክሽፈት መጠን ልክ ማሳካት የምንችልበት ሆኖ ቢነበብ እመርጣለሁ፡፡ ይህንንም ርዕሱን ከማንበብ ሳይሆን መጽሐፉን ደጋግሞ ማንበብም ሳይሆን አንዴ አንብቦ መረዳት የምንችልው የመጽሐፉ ጭብጥ ሲገባን ነው፡፡
  ሌላው ተብሎ የቀረበውም ከ41 ዓመታት በኋላ ጸሐፍቶች ሲሞቱና አልጋ ላይ ሲወጡ ጠብቀው መጻፉን እንደ ትልቅ ህጸጽ መታየቱ ደንቆኛል፡፡ መጽሐፉ ለህትመት እንዲበቃ የታሰበው በደርግ መንግስት እንደነበር ሰምቻለሁ አልከን፡፡ እሳቸውም ተናግረውታል፡፡ ይህንን እንደ ምክንያት እንውሰድና በዚህ ወቅትም መቆየቱ ምናልባት ከሽፏል የተባለው የኢትዮጰያ ታሪክ ይሳካ ይሆናል ተብሎም የተጠበቀ አጋጣሚ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ እሳቸው አስበው ባያደርጉትም ጠቢበኛው ለሁሉም ጊዜ አለው ብሎ መናገሩን እናውቃልን፡፡ ያኔ ለመጻፍ ተሞክሮ በሳንሱር ምክንያት አለመታተሙን እንደ ችግር ብንወስደው እንኳ ፕሮፌሰሩ በኢህአዴግ አገዛዝ ስር ሆነው እኔ የማውቀው 4 መጽሐፍትን ጽፈውልናል፡፡ እነዚህም መጽሓፍት የኢትዮጲያን ታሪክ በከፍተኛ መልኩ ሊመሩ የሚችሉ ሃሳቦችን ይዘዋል፡፡ በተለይ በ80ዎቹ የተጻፈችን ኢትዮጲያ ከየት ወዴት? የምትወለው ትንሽ መጽሐፍ በሚገባ ብትነበብ ስንት ለውጥ ባየን! አልተነበበችም እንጂ! ከዚህችም መጽሐፍ በኋላ የክደት ቁልቁለት፤ መንግስት ፖለቲካና አገዛዝ እንዲሁም አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ ምሁራዊና ለዚህች አገር ጉዞ አመላካች መጽሐፍት ነበሩ፡፡ በተገቢው አልተነበቡም፤ ቢነበቡም አልተገበርናቸውም እንጂ! እሳቸውም እነዚህን ሞከሩ የተሳካ ነገር አላዩም፤ ለውጥ አልመጣም ስለዚህ አሁንም በቃኝ ብለው አልተቀመጡም ታሪክ አያቆምምና፡፡ መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ በሚል ርዕስ አጠቃለው ማውጣታቸው እንደውም ዘገየ ሳይሆን ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቆ ወጣ የሚባልለት አገጣሚ ነው፡፡ ሳይጽፉት የሰው ልጅ ወደ ማይቀርበት ጸጥታ ቢሄዱስ? ይህ ነበር ሊታሰብ የሚገባው፡፡ የጊዜ ሰጭና ነሺን አምላክ የምናመሰግንበት ገጠመኝ ነው እንጂ!
ሌላኛው ቅጥል እርር ብግን ያስደረገኝ መልስ ደግሞ ይኸውላችሁ፡፡‹‹መስፍን? በቁጣ ስሜት ለእኔ መልስ ማለት ለጻፉት ጽሑፍ ምላሽ ያልሰጠሁት አንደኛ ለእርሳቸው አክብሮት ስላለኝ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም በዚህች አገር ላይ…›› ምናምን ማናምን ምናምን….ጉድና ጅራት ወደ ኋላ ነው አለ ያገሬ ሰው! ጎበዝ ሁለት ሰዎች እኮ በሃሳብ ደረጃ ሲወያዩና ሲመላለሱ ሁልጊዜም በሃሳባቸው ላይ መመላለስ እንጂ ከግለሰብ አክብሮትና ማንነት ላይ ምን አገኛኘው? እንደ አይሁድ አዋቂ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃዊያን ህግና መጽሐፍትን ተርጓሚና የተከበረ ማን ነበር? ነገር ግን እውነተኛው ክርስቶስ ‹‹መከበር አለባቸውና›› ብሎ ዝም አላለም፡፡ እስኪገርፉት፤እስኪተፉበት፤ እስኪሳለቁበት፤ እስኪሰቅሉትና እስኪሞት ድረስ እውነትን ሰበከ! ተሰቀለ ነገር ግን እውነት ይኸው 2ሺ ዘመናትን አስቆጠረች፡፡ ክርስቶስ እውነትን ባይናገር ኖሮ እውነትን ባይሰብክ ኖር ዝም ቢል ኖሮ እኛ እንዲህ አንቆምም ነበር፡፡ ክርስትናም የሚያስተምረን የድቁናም ሆነ የሌላ ማዕረግ የምታበቃን ክርስቶስን መሪና ተምሳሌት አድርጋ ነው፡፡ኢትዮጲያም ለዘመናት ያጣችው ይህንን ነው፡፡ እሱ ንጉስ ነው! እሱ የተመረጠ ዘር ነው! እሱ የተከበረ ነው በማለት ስንት እውነት ተቀብራ ቀረች? ስንት ሀቅ ለተውልድ ሳትተላለፍ ቀረች? አሁንም ያውም ከዚህ ትውልድ ‹‹ስለማከብራቸው ዝም አልኩ›› ማለት ሌላ 3ሺ ዘመን እንድንመለስ የሚያደርግ ምላሽ በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ነው ወይስ ምላሽህ ስድብ ብቻ ነበር? ከመሳደብ ዝም ይሻላል ከሆነ ሌላ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እውነትና እውቀት አለን ብለን ዝም ማለት ትልቅ ክሽፈት ይመስለኛል! በበኩሌ ፕሮፌሰሩ ሁለተኛ ምላሽን በመዝሙር 115 አያይዘው እስኪጽፉ ምላሽህን ጠብቄ ስለነበርና ያልመለስክበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ብዬ የጠበኩትን ያክል ያገኘሁት መልስ በጣሙን አሳዝኖኛል፡፡ መልስ አትስጥ በማለት ምክራቸውን ለግሰውኛል ያልከውንም ስቄበታለሁ! ሲጀመር ለመጻፍ ስትነሳሳ አትጻፍ አለማለታቸውም ደንቆኛል፡፡ ለአገር እድገት ለታሪክ መሳካት ዝም ብለን ውስጥ ለውስጥ ከመገፋፋት እውነቱ ይውጣ! እንወያበት! እውነት ደግሞ ሁልጊዜም አንድ ናት፡፡ ይህች አገር ኋላ ካስቀሯት አንደኛው ምክንያትም ይህ ነው፡፡ ደፋፍኖ አለባብሶ ማለፍ፡፡ ረመጡ ይጎዳናል!
 ‹‹ስለ ቤተ መንግስቱ›› ወሬም ሲነሳ ይህንን ታሪክ የሚያውቁት 6 ሰዎች ብቻ ናቸው የተባለው መልስም ከላኞይቹ መልሶች ጋር አይለይም፡፡ ስድስትም ሰው ይወቀው ስድሳም ይወቀው አንድም ይወቀው እ.ው.ነ.ቱ ይውጣልን! ዋናው ቁም ነገሩ እውነትን ማጋለጥና ለህዝብ በማቅረብ እንማርበት፤ አንወያይበት እንለወጥበት! ይህ ነው ትልቅ እድገት የሚያመጣው፡፡ የተፈጸመው ነገር በግለሰብ ደረጃ የሚቀርብ ከሆነ ብዙም ላይጠቅም ይችላል፡፡ በታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ የሚያመጣና በተለይም ከመጽሐፉ ጋር የሚገናኝ ከሆነ የእውነቱ ሰዓት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ፕሮፌሰሩም በጤናና በህይወት እያሉ ይነገረን፡፡ ካለበለዚያ በሚስጥርና በድፍንፍን መጥቀሱ ተንኮል ሊያደርገው ይችላል፡፡ እውነት አትደበቅም!
  ‹‹የአከሱምንና የአቡነ ጴጥሮስን አይነት ሞራል ማጣታችን የታሪካችን ቁንጽል አካል ነው፡፡ ይህንን በማንሳት ብቻ ታሪካችንን ከሽፏል ማለት አንችልም›› የሚለው መልስ ወደ መጨረሻ የሚመጣው መልስ ነው፡፡ ስሜቴን በመቆጣጥር ለዲያቆኑ ጸሎቴን አቀረብኩ! ምን ነካው ዲያቆን በማለት፡፡
ይታያችሁ ለአንድ አገር እድገት መሰረታዊ ከሚባሉት ነገሮች ውስጥ እጅ ስራን ወይንም ጥበብን ስልጣኔን የሚያመላክቱ እሴቶች ከህሊና ወይንም እውነተኛነት ስሜት ጋር ተዋህደው ሊፈጠር የሚችለውን ትውልድ ማሰብ ከዛም አልፎ ጥቅሙን መገንዘብ አይደለም ከአንድ አንባቢ ጸሐፊና ዲያቆን ከተባለ ሰው ይህንን አይነት መልስ መስማቴ ወደ መጨረሻው ውሳኔዬ ወደስዶኛል፡፡ አንድ ሀገር በጥበብ ስልጣኔን ይዛ፤ እውነተና የጽድቅ መስዋዕትነትን ብታዋህድበት የት በደረሰች! በአሁኑ ሰዓት አገራችን ያጣቸው ደግሞ አንዱን ብቻ ሳይሆን ሁለቱን ነው! ይህ ደግሞ የክሽፈቶች ታላቅ ክሽፈት! የጥበብ ስልጣኔ የሌለው ትውልድ ከዛም አልፎ የጴጥሮሳዊነት ሞራል የሌለው ህዝብ ሲጨመርበት -ህዝብ ከአራዊትነት አልፎ ድንጋይ የሚሆንበት ክሽፈት አይደለምን?
 ፕሮፌሰሩም አንድ የተሳካ ታሪክ ፈልጌ ማግኘት አላችልኩም ላሉት ሃሳብም ዲያቆኑ ‹‹አልፈለጉም›› ብሎ ነበር  የመለሰው፡፡ በነገራችን ላይ በብሔራዊ ቲያትር የመጽሐፉ ውይይት ላይ ይህንን ሃሳብ እርሳቸው መልሰዋል፡፡ ሲመልሱም ምናልባት ‹‹የኢትዮጲያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ወደ ጦርነት በጋራ ሆ! ብሎ መዝመትን እሳካሁን አይቻለሁ፡፡ ይህ ያልከሸፈ ነገር ነው ብለዋል፡፡ ሌላም ፈልገዋል በግላቸው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ዲያቆንም እገምታለሁ ብሎ አንድ እንኳ የተሳካውን የታሪክ አካል ሊገልጽልን አልተቻለውም! የተሳኩ ታሪኮች አሉን ብለን የምናስብ ከሆነ በምሳሌ ተንትኖ ማስቀመጥ፡፡ ይህ ነው ምሁራዊ ውይይት፡፡ ሌላው ወሬ ነው!
 ‹‹የኢትዮያን ህዝብ ተረድቼዋለሁ የማትለው ልዩ ሕዝብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ በቃ ጨርሷል ስትለው ብድግ የሚል፤ ተኝቷል ስትለው የሚነሳ ከ97 በፊት የነበረውን 97 ላይ ለምንድን ነው ብድግ ያለው ለሚለው ያንን እንኳ ተንትኖ የሚነግርህ የለም፡፡›› በማለት ቃለ ምልልሱ ያበቃል፡፡ ጋዜጠኛው በራሱ ይህንን ሃሳብ አሜን ብሎ መቀበሉ ገረመኝ፡፡ እዪት እንግዲህ ተናጋሪውን፤ እዩት ጠያቂውን፡፡ ታዲያ ይህች አገር በነዚህ ነው እንዴ የምትመራው? አዘንኩ! አፍክን ስትከፍት ጭንቅላትክን አየውህ የሚል አባባል አስታወስኩ፡፡ ጌታ ሆይ ከዚህ ዘመን አውጣን! እውነትህን ግለጥ! ‹‹ማውራት ጥበብ የሆነባት አገር›› የሚል የኤፍሬም ስዩም ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ ለካ እኔም እያወራሁ ነው… አምላክ ሆይ እውነትን እንድናወራ እንድንመሰክር እርዳን፡፡የኢትዮጲያ ህዝብ ያጣችው እውነትን ይዞ የሚመራት መሪ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ አምላኩን ይፈራል፡፡ እርስ በርሱ ይዋደዳል ግን አንድ አድርጎ በልዩነቱ የሚመራው እውነተኛ መሪ ይፈልጋል፡፡ ግን በማንም ሲመራና ሲዘበትበት ሲወራበት እያየን ነው፡፡ አምላክ ሆይ እውነተኛውን መሪ ስጠን! ብናወራው አያልቅም!
ቸሩ ቸር ያቆየን!
 


No comments: